አስናቀ ፀጋዬ
ከወጣትነት ወደ ጉልምስና መሸጋገሪያ እድሜ ላይ እንደሚገኝ ያስታውቃል። ከሰዎች ጋር ለመግባባት ብዙ አይቸገርም።ለሰዎች ያለው አመለካከትም ቀና ነው።ትምህርቱን በትውልድ ሀገሩ ቢከታተልም አብዛኛውን የስራ ህይወቱን በሳኡዲ አረቢያ አሳልፏል።በሳኡዲ አረቢያ በነበረው ቆይታም በአንድ ኩባንያ ውስጥ በኤሌክትሪሺያን ሙያ ተቀጥሮ ከረዳትነት እስከ ሱፐርቫይዘርነት ደረጃዎች ሰርቷል።ከዚሁ ኩባንያ ጋር በመሆኑም ወደ ሌሎች የመከካለኛው ምስራቅ ሀገራት ተዘዋውሮ በሙያው አገልግሏል።
ከሳኡዲ አረቢያ ወደ ሀገሩ ከተመለሰ በኋላም ረጅም ዓመታት የቆየበትን የኤሌክትሪሺያን ሙያና ልምድ ተጠቅሞ ዛሬ ላይ የራሱን የሴኪዩሪቲ ቴክኖሎጂ ድርጅት በማቋቋም በሌላው ሀገር እንደመሰረታዊ ጉዳይ የሚቆጠረውንና በኢትዮጵያ ደግሞ እንደቅንጦት የሚታየውን የደህንነት ካሜራ ገጠማ ስራ እየሰራ ይገኛል።በዚህ ስራም በአጭር ጊዜ ውስጥ ለበርካታ የንግድ ህንፃዎች፣ ፋብሪካዎች፣ መኖሪያ ቤቶችና ልዩ ልዩ ተቋማት የደህንት ካሜራዎችን በመስራት ኑሮውን ማሳደግ ችሏል።
በዚሁ ድርጅት አማካኝነትም ለወጣቶች በቀጥታና በተዘዋዋሪ የስራ እድል ከመፍጠሩም በላይ በተለያዩ ቦታዎች ለግለሰቦችና ለተቋማት በገጠማቸው ካሜራዎች ፖሊስ የስርቆት ወንጀል ሲፈፅሙ የነበሩ ሰዎችን እንዲይዝ ትልቅ እገዛ አድርጓል።በእርሱ ድርጅት በኩል ካሜራ ያስገጠሙ ሌሎች ደምበኞችም ከንብረትና ሃብት ስርቆት ስጋት እንዲላቀቁ አስችሏል።
የሴኪዩሪቲ ቴክኖሎጂ በሀገሪቱ እንዲጎለበት በተለይ ደግሞ ወጣቶች ከዚህ ስራ ጋር በተያያዘ እውቀቱ ኖሯቸው ሰርተው እንዲጠቀሙበት በግሉ ጥረት እያደረገም ይገኛል።የሳሊህ ሴኪዩሪቲ ቴክኖሎጂ ድርጅት ባለቤትና ስራ አስኪያጅ አቶ ሳሊህ አወል።
አቶ ሳሊህ አወል ትውልድና እድገቱ አዲስ አበባ ሼህ ሆጀሌ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ነው።የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቱን በእድገትና በላይ ዘለቀ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ተከታትሏል።የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ደግሞ በመድሃኒያለም ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተምሯል።በመቀጠልም ጄኔራል ዊንጌት ቴክኒክና ሙያ ትምህርት ኮሌጅ ገብቶ በኤሌክትሪሲቲ እ.ኤ.አ በ2001 በዲፕሎማ ተመርቋል፡፡
በተማረበት የኤሌክትሪሲቲ ሙያ ወዲያውኑ የስራ እድል በማግኘቱ እ.ኤ.አ በ2002 ወደ ሳኡዲ አረቢያ አቀና።በሳኡዲ አረቢያ ቴክኖ ኤሌክትሮ ሜካኒካል በሚባል ኩባንያ ውስጥም በኤሌክትሪክ ሙያ ረዳት ሆኖ በመቀጠር ስራውን ‹‹ሀ›› ብሎ ጀመረ።ቀጥሎም ሙሉ የኤሌክትሪክ ባለሙያ ሆነ።በሂደት ደግሞ ሱፐርቫይዘር ሆኖ መስራት ቀጠለ። በኩባንያው ውስጥ በተለይ ‹‹ሎው ከረንት›› በተባለው የስራ ክፍል ይበልጥ በመሳቡ ወደ ደህንነት ቴክኖሎጂ ስራ ገብቶ የፐብሊክ አድሬስ፣ ፋየር አላርምና የደህንነት ካሜራዎችን በመስራት ብቃቱን አስመሰከረ።ይህንኑ ስራም መለያው አድርጎ መስራት ቀጠለ።
በዚሁ ኩባንያ አማካኝነት እ.ኤ.አ በ2009 እና 2010 በሳኡዲ አረቢያ የአሜሪካን ኤምባሲ ውስጥ ‹‹አሜሪካን ኒው ኮምፓውንድ ኮንሱሌት›› በሚል ፕሮጀክት ውስጥ በሱፐርቫይዘርነት የሰራው አቶ ሳሊህ፤ በዚሁ ኩባንያ ጋር በመሆን በሌሎች የመካከለኛው ምስራቅ ሀገራት በተለይ በዱባይ፣ አቡዳቢ፣ ኳታርና ሊባኖስ ተጨማሪ የደህንነት ቴክኖሎጂ ስራዎችን በመስራት ሙያውን አዳበረ።በደህንነት ቴክኖሎጂ ዘርፍም በቂ እውቀትና ልምድ ከማካበቱም በላይ ወደሀገሩ ሲመለስ በዚህ ዘርፍ ገብቶ ለመስራት ይበልጥ ተገፋፋ።
እ.ኤ.አ በ2019 ከሳኡዲ አረቢያ ወደ ኢትዮጵያ እንደተመለሰ ብዙም ሳይቆይ የደህንነት ቴክኖሎጂን በግል ለመስራት የሚያስችሉ አንዳንድ እቃዎችን ከቻይናና ዱባይ ማስመጣት ጀመረ።በመቀጠልም ‹‹ሳሊህ ሴኪዩሪቲ ቴክኖሎጂ›› የተሰኘ የራሱን ድርጅት በ500 ሺ ብር መነሻ ካፒታልና እርሱን ጨምሮ ሶስት ሰራተኞችን ቀጥሮ በማቋቋም ወደ ደህንነት ካሜራ ገጠማ ስራ ገባ። ለግለሰቦችና ለሌሎች ተቋማት ካሜራዎችን በብዛት መግጠም ጀመረ።ሰፋ ያለ ፕሮጀክት ሲኖረውም ተጨማሪ ሰራተኞችን በኮንትራት አካቶ የካሜራ ገጠማ ስራውን ገፋበት።
የሴኪዩሪቲ ካሜራ ቴክኖሎጂ ስራውን እንደጀመረ ከተጠቃሚዎች ጥሩ ምላሽና አቀባበል አገኘ። ይበልጥ ስራውን ተደራሽ ለማድረግና ድርጅቱን ለማስተዋወቅ የማህበራዊ ሚዲዎችን ተጠቅሟል።በተለይ ደግሞ ‹‹Trama security solution›› በተሰኘው የፌስ ቡክ አካውንቱ ስራዎቹን ይበልጥ ለማስተዋወቅ ሞክሯል።በዚህም የበርካታ ሰዎችን ቀልብ ለመሳብ ችሏል፤ በርካታ ስራዎችንም ሰርቷል።
እስካሁን ባለው ሂደትም ድርጅቱ በሸኖ ከተማ ለአንድ አረቄ ፋብሪካ፣ በቃሊቲ ክፍለ ከተማ ለአንድ ሳሙና ፋብሪካ፣ በዱከም ለሻንጋይ ኢንጂነሪንግና ለፒፒ ከረጢት ፋብሪካና ለሌሎች በርካታ ፋብሪካዎች የደህንነት ካሜራዎችን ገጥሟል።ድርጅቱ ከተቋቋመ ከሁለት ዓመት ወዲህም ከ400 በላይ የሚሆኑ ከትንሽ እስከ ትልቅ ፕሮጀክቶችን ሰርቷል።
በአሁኑ ወቅት ደግሞ የሴኪዩሪቲ ቴኬኖሎጂ ድርጅቱ የደህንነት ካሜራ ገጠማ፣ የእሳት አደጋ ማንቂያ፣ የኮምፒዩተር ኔትዎርኪንግ፣ የኤሌክትሪክ አጥር፣ ኤር ኮንዲሽኒንግ፣ የጣት አሻራ ሰዓት መቆጣጠሪያና አክሰስ ዶር ስራዎችን ይሰራል።ከዚህ ውጪ የዓለም ጤና ድርጅት የሚደግፈውን የንፁህ መጠጥ ውሃ ለሰዎች እንዲደርስ የውሃ ማጣሪያ ማሽኖችን ለገበያ ያቀርባል።
ሁለት ዓመታትን የተሻገረው የሴክዩሪቲ ቴክኖሎጂ ድርጅቱ በአሁኑ ጊዜ አጠቃላይ ካፒታሉ 1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር ያህል የደረሰ ሲሆን ለወጣቶችም የስራ እድል ፈጥሯል፤ ይሄንኑ ቀጥሏል።አሁን ባለው ሁኔታም ለሰባት ሰራተኞች ቋሚ የስራ እድል ፈጥሯል።በሰፋፊ ፕሮጀክቶች ላይ ደግሞ ለተጨማሪ ዜጎች ጊዜያዊ የስራ እድል ይፈጥራል።
ደንበኞች በድርጅቱ የፌስቡክ አካውንት አድራሻ አማካኝነት ስራዎችን ተመልክተው የሚመጡ ሲሆን በቅድሚያ ስራ የሚሰራባቸውን ቦታዎች ለድርጅቱ ያሳያሉ።ድርጅቱም የቦታ ግምገማ ይሰራል።የካሜራውን አይነትና ብዛትም ይወስናል። በመቀጠልም ካሜራዎቹን የሚያስቀምጥባቸውን አንግል ፕሮፖዛል ሰርቶ ለደንበኞቹ ያቀርባል።ከዚህ በኋላ አሰሪዎች ስራው መሰራት እንደሚችል ሲያረጋግጡ ድርጅቱ ሙሉ የሰው ሃይሉን ይዞ ስራውን መስራት ይጀምራል።
ድርጅቱ ባሰቀመጠው የጊዜ ገደብ መሰረት ስራውን ካጠናቀቀ በኋላ ለደንበኞች ያስረክባል።በመጨረሻም የስራውን ብዛትና አይነት ከግምት ውስጥ በማስገባት የአገልግሎት ክፍያ ይጠይቃል።ለሚሰራቸው ስራዎች ሁሉ የአንድ ዓመት ነፃ አገልግሎትና የጥገና ዋስትና በመስጠትም ደንበኞቹ በስራው ይበልጥ እንዲረኩ ያደርጋል።
ከዚህ ባሻገር ስራው ከተጠናቀቀ በኋላ ድርጅቱ በተወሰኑ ጊዚያት ውስጥ ለደንበኞቹ ስልክ በመደወል ካሜራው በትክክል እየሰራ እንደሚገኝ ያረጋግጣል።እስካሁን ባደረጋቸው የደህንነት ካሜራ ፍተሻም ችግር አላጋጠመውም።በጥራትና አስተማማኝነት በኩል ችግር እንዳያጋጥም ለኢትዮጵያ የሚሆኑ ጥራትና የኢንተርኔት ፕሮቶኮል ያላቸው የደህንነት ካሜራዎችን መርጦ ወደ ሀገር ውስጥ በማስገባት ስራ ላይ ያውላል፡፡
ድርጅቱ ስራ ላይ የሚያውላቸው የደህንነት ካሜራዎች ምንም ሳይሆኑ ከ25 እስከ ሰላሳ ዓመት ይቆያሉ።ሰዎች በቀላሉ በድንጋይ ወይም በመዶሻ ሊሰብሯቸው የሚችሉም አይደሉም።ውሃም ወደ ውስጣቸው በቀላሉ አያስገቡም። እሳትንም መቋቋም ይችላሉ።
አቶ ሳሊህ በአዲስ አበባ ከተማ በደህንነት ካሜራ ስራ የተሰማሩ ድርጅቶች አሁን አሁን እየተበራከቱ ቢመጡም ድርጅቱ የሚገጥማቸው ካሜራዎች ከአናሎግ ወደ ኢንተርኔት ፕሮቶኮል መለወጥ የሚያስችል የመጨረሻ የካሜራ የቴክኖሎጂ የደረሰበትን ሞዴል የሚጠቀም በመሆኑ ከሌሎቹ ልዩ እንደሚያደርገው ይገልፃል። አብዛኛዎቹ ካሜራዎችም የ2018 ሞዴል መሆናቸውንና ካሜራዎቹ በቀላሉ ከስማርት ስልኮች ጋር ተገናኝተው ከሀገር ውጪ ጨምሮ ሰዎች በየትኛውም ቦታ ላይ ሆነው ቤታቸውን አልያም ሌሎች ንብረታቸውን ለመቆጣጠር የሚያስችሉ እንደሆኑም ይናገራል።
ድርጅቱ ለሚገጥማቸው ካሜራዎች የአንድ ዓመት ነፃ አገልግሎትና አንድ ዓመት የጥገና ዋስትና የሚሰጥ መሆኑም ይናገራሉ።
በመካከለኛው ምስራቅ በነበረበት ወቅት ካለው ተሞክሮ በመነሳትና የካሜራን አስፈላጊነት ከግምት ውስጥ በማስገባት በቀጣይ የሴኪዩሪቴ ቴክኖሎጂ ድርጅቱ በአዲስ አበባ ከተማ የሚገኙ አብዛኛዎቹ ህንፃዎችና መኖሪያ ቤቶች ላይ የደህንነት ካሜራዎችን በስፋት የመግጠም እቅድ እንዳለው ይናገራል።
ይህንኑ እቅድ ለማሳካትም ህንፃዎችና መኖሪያ ቤቶች ልክ እንደ እሳት አደጋ መከላከያ መሳሪያዎች ሁሉ የደህንነት ካሜራዎች እንደሚያስፈልጋቸው ህብረተሰቡን የማስገንዘብ ስራዎችን አያይዞ እንደሚሰራም ይጠቁማል።የከተማ ቅኝት ካሜራዎች ገጠማ ላይ በስፋት የመሳተፍ ሃሳብ እንዳለውም ገልጾ፤ አዲስ በጀመረውን የውሃ ማጣሪያ ማሽኖች አቅርቦት ዙሪያም በስፋት የመስራት እቅድ እንዳለው ገልጿል።
‹‹የሀገሪቱ የሴኪዩሪቲ ቴክኖሎጂ ዘርፍ አሁን አሁን የሚያበረታታ እድገት ይታይበታል›› የሚለው አቶ ሳሊህ፤ በዛው ልክ የህብረተሰቡም በደህንነት ካሜራ አስፈላጊነት ዙሪያ ያለው ግንዛቤ እየሰፋ ስለመምጣቱም ይጠቁማል።ፖሊስም ዘርፉን በማበረታታት አንዳንድ ጊዜ በካሜራ የታገዙ የወንጀል ምርመራዎችን እያከናወነ እንደሚገኝና ሰዎችም ካሜራ እንዲያስገጥሙ እያበረታታ መሆኑን ይጠቅሳል።
ይሁንና የደህንነት ካሜራዎች አስፈላጊነትን ያህል ሰዎች ለቤት ፍጆታ ብቻ የሚውሉ ካሜራዎችን ከውጪ ወደ ሀገር ውስጥ ሲያስገቡ በመንግስት ቀረጥ እንዲከፍሉ የሚደረግበት ሁኔታ ተገቢ አለመሆኑን ያስረዳል።ከዚህ ይልቅ መንግስት የደህንነት ካሜራዎችን አስፈላጊነት በመገንዘብ ካሜራዎቹ ከቀረጥ ነፃ የሚገቡበት ሁኔታ ሊፈጠር እንደሚገባ ይጠቁማል።ይህም ህብረተሰቡ ካሜራ በመግጠም ደህንነቱን የመጠበቅ ባህሉን እንዲያዳብር ትልቅ አስተዋፅኦ እንደሚኖረው ያመለክታል።
በዘርፉ ውጤታማ መሆኑንም የሚገልፀው አቶ ሳሊህ፤ ‹‹የውጤቴ ማሳያ የገንዘብ ትርፍ ማግኘቴ ሳይሆን ከውጪ ሀገር ሰርቼበት ያገኘሁትን የሴኪዩሪቲ ቴክኖሎጂ እውቀት ወደ ሀገሬ ማሸጋገሬ ነው›› ይላል።በሴኪዩሪቲ ቴክኖሎጂ ዙሪያ በርካታ ወጣቶችን በማሰልጠንና እውቀት በማስጨበጥ ወደ ስራ እንዲገቡ ማድረጉም የውጤቱ ሌላኛው ማሳያ መሆኑን ይናገራል።ለዚህ ውጤት መምጣት ደግሞ በትጋት መስራቱና ሁሌም ድርጅቱን የማስተዋወቅ ስራ በመስራቱ እንደሆነም ይጠቅሳል።በሁለት ዓመታት ውስጥ 400 ያህል ፕሮጀክቶችን መስራት በራሱ ትልቅ ስኬት መሆኑንም ይገልፃል።
በተመሳሳይ ሌሎችም በዚህ የሴክዩሪቲ ቴክኖሎጂ ዘርፍ ገብተው እንዲሰሩ ለማድረግ ድርጅቱ የሴኪዩሪቲ ካሜራዎች እንዴት እንደሚገጠሙ የሚያስተምሩና አጫጭር ኮርሶችን ለመስጠት የሚያስችሉ ሰነዶች ለወጣቶች ማዘጋጀቱን አቶ ሳሊህ ይጠቅሳል።ለዚህም ‹‹Linkbase. security technology›› የተሰኘ የዩቲዩብ ቻናል መክፈቱንና በዚህ ቻናል የደህንነት ካሜራዎች እንዴት እንደሚገጠሙ የሚሳዩ አጫጭር ቪዲዮችን በመልቀቅ ወጣቶች ትምህርቱን እንዲያገኙ እንደሚደረግ ይጠቁማል።
ሁኔታውና ጊዜው የተመቻቸላቸው ወጣቶች ደግሞ በአካል ድርጅቱ ቢሮ መጥተው የደህንነት ካሜራ ገጠማ ስራ የተግባር ስልጠና ተመጣጣኝ ዋጋ እያስከፈለ የመስጠት እቅድ እንደያዘም ይገልፃል። ከዚህ በፊትም ወጣቶች በደህንነት ካሜራ ገጠማ ስራ ዙሪያ ስልጠና እንዲያገኙ በማድረግ ወደ ስራ መሰማራታቸውንም አስመልክቶ፤ በቀጣይ የድርጅቱ ድረ ገፅ ተሰርቶ ሲጠናቀቅ ስራዎቹን በስፋት የማስተዋወቅ ስራ እንደሚሰራም ይጠቁማል።
አዲስ ዘመን ሚያዚያ 16/2013