ተወልደው ያደጉት አዲስ አበባ ከተማ፣ ለገሃር አካባቢ ነው።ባለትዳርና የሁለት ልጆች እናት ናቸው።ከአገር ከወጡ ወደ 30 ዓመታት ያህል ተቆጥሯል።አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በቋንቋና ስነ ጽሑፍ ዲግሪያቸውን በመማር ላይ እያሉ ነበር ሳይጨርሱ ወደውጭ አገር የሄዱት።በአሁኑ ሰዓት ኑሯቸውም በአውሮፓዊቷ አገር ኖርዌይ ውስጥ ሲሆን፣ የእዚያው አገር ዜግነትም አላቸው።
ወይዘሮ ሰዋሰው ስለሺ የትውልድ እናት የእርቅና የሰላም ኢኒሼቲቭ የሚል አገልግሎት ከመመስረታቸው በፊት በትውልድ፣ በዘርና በቤተ እምነት መሃል ፈውስ ለማምጣት በሚል አገልግሎት መስርተው ላለፉት ብዙ ዓመታት በእርቅና በሰላም ጉዳይ ላይ ሲጮሁ ቆይተዋል።
በተለይም ዋና ትኩረታቸው ደግሞ ብሄራዊ ፍትሐዊ እርቅ ላይ ያጠነጠነ በመሆኑ ከዚሁ ጋር ተያይዞ አዲስ ዘመን ስለመሰረቱት ኢኒሼቲቭ፣ አገራዊ አንድነትና እርቀሰላም የሚኖረው ፋይዳ፣ እንዲሁም ማን ከማን ጋር እርቅ እንደሚፈጽምና ሌሎችም ተያያዥ ጥያቄዎችን አንስቶላቸው እንደሚከተለው አጠናቅሮ አቅርቧል፤ መልካም ንባብ ይሁንልዎ።
አዲስ ዘመን፡- ኢኖሼቲቩን ለመመስረት ያነሳሳዎ ምክንያት ምን ይሆን?
ወይዘሮ ሰዋሰው፡– እኔ አንድ ጩኸት ስላለኝ ነው ኢኒሼቲቩን ለመመስረት የተነሳሳሁት፤ የምጮኸው ደግሞ እንደፖለቲከኛ አሊያም እንደተማረ ሰው ሳይሆን እንደእናት ነው።ለዚህ ምክንያቴ ባለፉት 40 እና 50 ዓመታት ኢትዮጵያ ውስጥ በተካሄዱ የፖለቲካ ውጥንቅጦች በርካታ ትውልድ ከምድሪቱ ረግፏል።ለዚህ ሰቆቃ በብዛት ዋጋ የምትከፍለው ደግሞ እናት ነች።ኢትዮጵያውያን እናቶች በብዙ ሰቆቃ፣ ድካምና ድህነት ውስጥ የሚያልፉ እንደመሆናቸው እነሱን በመወከል ነው የምጮኸው።እናቶች ያሳደጓቸው ልጆች ተምረው ለወግ ማዕረግ ሳይደርሱላቸው ሲቀር የሚሰማቸው አሰቃቂ ስሜት ነው።
ይህ የሚሆነው ደግሞ ፖለቲከኞች ነን በሚሉ አካላት ነው።ግን ስለትውልዱም ሆነ ስለእናቶች ፖለቲከኞች ብዙም ግድ ሲላቸው አይታዩም።ስለዚህም የአገራችንን ችግር ፖለቲካው ብቻ ላይፈታው ይችላልና እርቅና ሰላም ወደምድሪቷ የማምጣት ሁኔታ ቢፈጠር በሚል ነው፤ ጊዜው የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ወደስልጣን የመጡበት ወቅት ነው ለኢትዮጵያ መንግሥት ስወተውት የቆየሁት፡፡
በውጭ አገር ያሉ ተቃዋሚ ድርጅቶችም፣ ዲያስፖራውም ለአገር ግንባታም ሆነ ውድመት ራሱን የቻለ አስተዋጽዖ አለው፤ እናም አብዛኛዎቹ ተቃዋሚ ድርጅቶች ደግሞ ሲንቀሳቀሱ የነበረው ከኢትዮጵያ ውጪ ነው።
እነዚህም ቢሆኑ እውነተኛ በሆነ አካሄድ ለህዝብ መብት የሚታገሉ እንዳሉ ሁሉ ደግሞ አገር በማፍረሱም ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽዖ ስለሚያደርጉ በወቅቱ በኢትዮጵያ መንግሥትና በተቃዋሚዎች መካከል በጠረጴዛ ዙሪያ ተቀምጠው ቢነጋገሩ እና ችግሮቻቸውን በጥይት የመፍታቱ ነገር ቢቆም በሚል ነው ከሰባት ዓመት በፊት የመጀመሪያውን ተነሳሽነት የጀመርኩት።
በወቅቱ የኢትዮጵያን መንግሥት ኖርዌይ ባለው ኤምባሲው አማካይነት እንዲሁም የኖርዌይንም መንግሥት አነጋገርኩኝ።የኖርዌይ ዜጋ ብሆንም የትውልድ ሐረጌ የሚመዘዘው ከኢትዮጵያውያኑ እንደመሆኑ እንደ አንዲት ኖርዌጂያዊ ኢትዮጵያዊት ነው ጉዳዩን ያነጋገርኩት።ስለዚህም ለእርቅና ለሰላም እንድንሠራ አገሬን ብታግዙኝ ስል ከሰባት ዓመት በላይ በዚሁ ጉዳይ ስጮህ ቆየሁ።
ውጭ አገር ባሉ በተለያዩ የመገናኛ ብዙኃንም ዘንድ ጉዳዩን በሚመለከት የተለያዩ ቃለ መጠይቆችን አድርጌያሁ።ጩኸቴም የነበረው ለምድሪቷ ፖለቲከኞች ብቻ ሰላም ሊያመጡላት አይችሉም።በመሆኑም በምድሪቱ ላይ እርቅና ሰላም መካሄድ አለበት በሚል ነበር፡፡
የዛሬ ሦስት ዓመት ገደማ በኢትዮጵያ የለውጡን መምጣት ተከትሎ አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር በትረስልጣናቸውን እንደያዙ በኢትዮጵያ ሰላምና እርቅ መካሄድ አለበት በማለት እኔ ስጮህበት የነበረውን አጀንዳ ሲያስጮሁ ደስታዬ ወደር አልነበረውም።በተለይም ደግሞ አንዱ ሌላውን መበደል የለበትም፤ ኢትዮጵያና ኤርትራም መታረቅ አለባቸው በሚል አንድ የአገር መሪ ይህን አንጀዳ ይዞ በመነሳቱ ብቻ እኚህ ሰው የኖቤል ሽልማት ይገባቸዋል በሚል የመጀመሪያውን ተነሳሽነት ወስጄ መንቀሳቀስ ጀመርኩ።ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለኖቤል ሽልማት መብቃት አለበት በሚል ተነሳሽነቱን ስጀምር የሚሆንም አልመሰለኝም ነበር።
ተነሳሽነቱን ወስጄ ስንቀሳቀስ የእርሳቸውን የፖለቲካ አቋም ተረድቼ አልነበረም።እኔ ከንግግራቸው የተረዳሁት ነገር ለትውልድ እርቅንና ሰላምን የሚያስብ መሪ መሆናቸውን ነው።የፈረሰ ቅጥር እናድስ ነው ሲሉ የነበሩትና እኔ ስጮህለት የነበረውን አጀንዳ የሚያስጮህ ሰው ስላገኘሁ ይህ ሰው የኖቤል ሽልማት ይገባዋል በሚል የኖቤል ሽልማቱም ሰጪ አካል ያለው ኖርዌይ ስለሆነ ተነሳሽነቱን ወስጄ ጉዳዩም ፈጣሪ ፈቅዶ በመሳካቱ ወደኖርዌይ ሲመጡም ተቀብያቸዋለሁ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ፣ የሰላም ሚኒስትሯ እና ልዑካቸው በመጡ ጊዜ የጠየቅኳቸው አንድ ነገር ቢኖር ውጭ ያለው ዲያስፖራ እንዲያግዛቸው የሚፈልጉት የኢኮኖሚውንና የፖለቲካውን ጉዳይ ብቻ መሆን የለበትም።
የሰላምና የእርቅ ጉዳይን በተመለከተም እንዲሁ ትኩረት ስለምን አታደርጉም የሚል ነበር።ምክንያቱም በዚህ ጉዳይ ባለድርሻ አካላት ናቸው ለተባሉት በጣም ብዙ ደብዳቤ ነው የጻፍኩት።ወደ ኢትዮጵያም መጥቼ የጠቅላይ ሚኒስትሩን አማካሪን ጨምሮ ብዙዎቹን አናግሬያቸው ነው የሄድኩት።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ አውሮፓ በመጡ ጊዜ ጀርመን ድረስ ሄጄ ደብዳቤ በእጃቸው እንዲደርስ አድርጌያለሁ።በመሆኑም ጉዳዩ ይሳካ ዘንድ የተቻለኝን ብቻ ሳይሆን ብዙ ሞክሬያለሁ።ከአንድ ሺህ በላይ ተጽፈው የተላኩ ደብዳቤዎችና ኢ-ሜይል ቢኖሩም መልስ እንኳ አልሰጣችሁኝም ብዬ ተናግሬያለሁ።
ነገሩን ከጀመርኩ እንዳልኩሽ ብዙ ዓመት በመሆኑ የዘንድሮ አመጣጤ ግን የመጨረሻውን ሙከራ ለማድረግ ነው ከወር በፊት ኢትዮጵያ የተገኘሁት።ከሰላም ሚኒስትሯ ወይዘሮ ሙፈሪያት ካሚልና ከሰላምና እርቅ ኮሚሽን ጋርም ተገናኝተን የያዝኩት ዓላማ መልካም ነው የሚል ምላሽ ሰጥተውኛል።
አዲስ ዘመን፡- በአሁኑ ወቅት ሃገራችን ያለችበትን ነባራዊ ሁኔታ እንዴት ይገልጹታል?
ወይዘሮ ሰዋሰው፡– አሁን በአገራችን እየተፈጠሩ ያሉ ነገሮች ዛሬ የተፈጠሩ አይደሉም።ተያይዘው የመጡ ቁርሾዎች ናቸው።ለዘመናት የነበሩ የተሰበኩ ጥላቻዎች በቅለው ነው እዚህ ደረጃ ላይ የደረሱት።በመሆኑም እነዚህን ክስተቶች በአንድ ጊዜ ለማጥፋት የሚቻል አይመስለኝም።
ትውልድ አሁንም እየረገፈ ነው።አሁንም ወላጆች ልጆች አልባ እየሆኑ ነው፤ ሚስቶች ባለቤቶቻቸውን እያጡ ነው።ሽማግሌዎች ጧሪ አጥተው እየተሰቃዩ ነው።አዛውንቶች ያለቀባሪ እየቀሩ ነው።ይህ ሁሉ ነገር ካልደረሰብን ላይገባን ይችላል።በእርግጥ ይህ ጉዳይ አስከፊ ነው፤ መቅረት አለበት በሚል ሚሊዮኖች ድምፃቸውን አሰምተው ሊሆን ይችላል።በእርግጥም ደግሞ ጉዳት ለደረሰባቸው አካላት ተቆርቁረው የሚጮሁና የሚሞግቱ ድምፆች አሉ፤ ሌሎች ደግሞ በተቃራኒው የቆሙ ተቆርቋሪ ነን ባዮች አሉ።ለተጎጂዎች ነፃነት እንታገላለን በሚል በስማቸው የሚነግዱ ቁማርተኞች አሉ፡፡
ነገር ግን ይህ ሁሉ በሚሊዮን የሚቆጠር ድምፅ የሚያወራው መከራውን ነው።እኔ ማውራትም መሥራትም የምፈልገው መፍትሔው ምንድነው? በሚለው ላይ ነው።ከዚህ የተነሳ ነው በአገሪቱ ውስጥ ብሄራዊ ፍትሐዊ የሆነ እርቅ መካሄድ አለበት የምለው።ይህ ካልሆነ ደግሞ ገዳይም ሟችም እኛው በመሆናችን የእከሌ ድርጅት ነው ብለን የምንጠነቁልበት ነገር የለም።ትናንት የፈሰሰው ደም ይጮሃል።ትናንት ጉዳቱ የደረሰባቸው ወገኖች ዛሬም ያነባሉ።ምድሪቱንም ይረግማሉ።ስለዚህ የመረቀዘው ቁስል እንዲሽር መሠራት አለበት።ችግሩ የሆነ ቦታ ላይ ማቆም አለበት፡፡
ቁስሉ እንዲሽርና እስከአሁን ላለቀው ትውልድ ይሆን ዘንድ እስከአሁን ለፈሰሰው ኢትዮጵያዊ ደም ሲባል በጥቅሉ አንድ ብሔራዊ የኀዘን ቀን በማወጅ እውቅና መስጠት ያስፈልጋል ባይ ነኝ።እኛ ከጎናችን ዘመድ ብለን የምንጠራው ባይሞትም ወገናችን ረግፏል፤ ተፈናቅሏልና ጉዳቱ የደረሰባቸውን ወገኖች ኀዘናችሁ ኀዘናችን ነው በሚል የኀዘን ቀን እንዲታወጅ ነው መንግሥትን የምጠይቀው፡፡
ሁለተኛው ደግሞ በእኔ ዕድሜ እንኳ ያለፉትን አርባና ሃምሳ ዓመት ያዩሁት የትውልድ እልቂትን ነው የምናገረውና እንደእናትም የምጮኸው።አሁንም በየቦታው ሰው ይሞታል።ፖለቲከኞቹም የእኔ ዘር ይህን ያህል ተገደለብኝ ሲሉ ለፖለቲካቸው ማዳመቂያነት ከመጠቀም በዘለለ ለተጎዳው አካል ያን ያህል ግድ የሚሰጠው እምብዛም የለም።
ስለዚህ ይህን ሁሉ ጉዳት በጥቅሉ በመሰብሰብ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትርን ጨምሮ እንዲሁም የአገሪቱ ፕሬዚዳንት እና ባለስልጣናቱም በህዝብ ስም ሆነው ህዝቡን ራሱ ይቅርታ ቢጠይቁ መልካም ነው።እኛ ደግሞ ኢትዮጵያውያን በዚህ ሁሉ ጦስ ውስጥ በንግግርም ሆነ በብዕር ስም እንዲሁም በተግባርም ሆነ በሌላ ነገር እጃችን ስላለበትና ለትውልዱ እልቂት የየራሳችን አስተዋጽዖ ስላለን እኛም ደግሞ እንደ ህዝብ በደል የደረሰባቸውን ሰዎች ይቅርታ እንድንጠይቅ ያስፈልጋል፡፡
በተጨማሪም የኃይማኖት ተቋማቱ የየሁሉም ቤተ እምነቶች አንዳንዴ እኛ ቤት እስካልመጣ ድረስ በሚል ዓይነት ዝም ያሉበት ቦታ ሁሉ አለ።ምንም እንኳ በሽምግልናም ሆነ በጸሎት ያደረግናቸው ሥራቸው እምብዛም ለውጥ ስላላሳዩ አንዱን ቀን ደግሞ እንዲሁ ይቅርታ አድርገናል በሚል ይቅር ብንባባል መልካም ነው።መታረቅ ያለባቸው ኢትዮጵያና ህዝቦቿ ናቸው፡፡
አዲስ ዘመን፡- መንግሥት ከለውጡ ጋር ተያይዞ በርካታ አኩርፈው ውጭ የነበሩ የፖለቲካ ድርጅቶችን ወደሃገር ውስጥ አንዲገቡ ዕድል መስጠቱ ይታወቃል፤ ከዚህም ባሻገር ለብዙ ጊዜ አኩርፈው ውጭ የቆዩ ዜጎችም ዕድሉን ተጠቅመው ወደሃገራቸው ገብተዋል፤ ይህ ለሃገራዊ አንድነትና እርቀሰላም የሚኖረው ፋይዳ ምንድነው?
ወይዘሮ ሰዋሰው፡– ፋይዳ መኖሩ ብቻ ሳይሆን ከውጭ አገር የመጡም የበደሉ በመሆናቸው ይቅርታ ጠያቂም ጭምር ናቸው።ምክያቱም 40 ዓመት ሙሉ ነፃ አወጣለሁ እያሉ የነበሩ ድርጅቶች ናቸው ወደአገር ቤት የገቡት።
እነዚህ የነፃ አውጪም ይሁኑ የፖለቲካ ድርጅትም ይሁኑ የየራሳቸውን ያዋጣኛል ብለው ስም በያዙበት ሰዓት መንግሥትን በመቃወም የሚይዟቸው መፈክሮችና የሚያስጮኋቸው አጀንዳዎች ነበሯቸው።መንግሥትን በሚቃወሙበት ሰዓት ሰላማዊ ሰልፍ ያስወጣሉ፤ የትጥቅ ትግል በሚል ሰውን ያለምንም ከለላ ይማግዳሉ።
በዚህም ውስጥ በርካታ ወጣቶች ለእነሱ ሲሉ ተማግደው አልቀዋል፤ መንግሥት ብቻ አይደለም ህዝብ እንዲያልቅ ያደረገው።ተቃዋሚዎች ጨርሰዋልም፤ አስጨረሰዋልም።እነዚህ 40 እና 50 ዓመት ያላቸው የፖለቲካ ድርጅት መሪዎችም ሆኑ አመራሮች አልሞቱም፤ ዛሬም በህይወት አሉ።ሲያልቅ የነበረው ግን ኢትዮጵያዊው የድሃው ልጅ ወጣቱ ነው።
ስለዚህም እነዚህም ሲጨርሱና ሲያስጭረሱ የነበሩ ድርጅቶች ወጥተው ለትውልድ እልቂት የእኛም እጅ አለበት ብለው የኢትዮጵያን ህዝብ ይቅርታ ሊጠይቁ የተገባ ነው።ጸቡ ከመንግሥት ጋር ብቻ ሳይሆን ከእነሱም ጋር ጭምር በመሆኑ ነው።ለኢትዮጵያ እንታገላለን ከሚሉ ውስጥ ሁሉም በእውነት ታግለው ለውጥ ያመጡ አይደሉም።አብዛኛው የሚፈልገው ስልጣንን እንጂ ለኢትዮጵያዊ ህዝብ መብት እንዲመጣ ማድረግን አይደለም።
ከእነዚህ ውስጥ በምድሪቱ ላይ መርገመን ያስከተሉ ናቸው።ሌሎችም በበለጸጉ አገራት ተቀምጠው ድሃውን ወጣትና ህዝብ ሂድና ተዋጋ በሚል ጥይት የሚያቀበል ሁሉ የትውልድ ደም በእጃቸው ላይ ናትና እነርሱም ቢሆን ይቅርታ ጠያቂ ሊሆኑ ይገባል።ምናልባት ለሰላምና ለእርቀ አስተዋጽኦ ሊያደርጉ ይችላሉ፡፡
አዲስ ዘመን፡- እርስዎ የእርቀ ሰላም ኢንሼቲቭ መስርተው እየሠሩ ነው፤ ለመሆኑ የዚህ ማህበር ዓላማ ምንድን ነው? እስከአሁን ምን ምን ተግባራትን አከናውኗል?
ወይዘሮ ሰዋሰው፡- ቀደም ሲል ስሠራበት የነበረው የኃይማኖት ድርጅት ስለሆነ ሁሉንም የኃይማኖት ተቋማትን ሊያካትት አልቻለም፤ እናም ወደአንድ የኃይማኖት ተቋም ብቻ የሄደ ይመስል ነበር።እኔ ግን ከዚያ የየትኛውንም የኃይማኖት ተቋምና ብሄረሰብ አጀንዳ የማስፈጸም ዓላማ የለኝም።
የመንግሥትንም ሆነ የተቃዋሚውን አጀንዳ ማስፈጸም አልፈልግም።መጮህ ያለብኝ እንደእናት ነው የሚል የጸና እምነት ይዤ ነው።እናትነት ደግሞ በየትኛውም ኃይማኖትም ሆነ ብሄረሰብ ውስጥ ሰላለች ይህን ድርጅት ወደዚህ ለውጬ ለእርቅና ሰላም እንዲሠራ የጀመርኩት አሁን በቅርቡ ነው።ወደመስመር ከገባም ዓመት አልሞላውም።ገና በጅምር ላይ ያለ ድርጅት ነው።እስከአሁን የሠራኋቸው ሥራዎች ግን ያለፉት ዓመታት የተሠሩ ለአሁኑ መሰረት ናቸው።በኖርዌይ የተመዘገበና በአገሪቱ መንግሥት ህጋዊ እውቅና ያለው ነው።
ይህን ሥራ አስመልክቼ ለሰላም ሚኒስቴርም ሆነ ለሰላምና እርቅ ኮሚሽንም ያቀረብኳቸው ፕሮፖዛሎች አሉ።ከእነዚህም ውስጥ አንዱ በኢትዮጵያ ብሄራዊ ፍትሐዊ እርቅ ለማምጣት የቀረበ ፕሮፖዛል በሚል ርዕስ ያዘጋጀሁት ነው።የትውልድ እናት ለእርቅና ለሰላም በሚል በኖርዌይ የተመዘገበ ህጋዊ ድርጅት ስለመሆኑና መስራቿም እኔ ስለመሆኔ አስቀድሜም አሳውቄያለሁ።
እኔ የምፈልገው ብሔራዊ ብቻ ሳይሆን ፍትሐዊም እርቅ ጭምር ነው።ይህንኑ ሐሳብ ነው ለሰላም ሚኒስቴር አቅርቤ የነበረው፤ በወቅቱም ይህማ የተቀደሰ ሐሳብ ነው በሚል ነው በጽሑፍ አቀርብላቸው ዘንድ የጠየቁኝ።
ሌላው ደግሞ ቤተሰቦቻቸው ለተገደሉባቸው ሰዎች ኀዘናችሁ ያመናል ከሚል አባባል ባለፈ ቁስላቸውን ማከም መቻል አለብን።ስለዚህም የደም ካሳ መክፈል አለብን ብዬ አምናለሁ።ይህንን ማድረግ ያለብን መላ ኢትዮጵያውያን ነን።ይህ ጉዳይ መንግሥት ላይ ብቻ የሚጣል አይደለም።ምክንያቱም የሞትንም የገደልንም እኛው ነንና።በደሉም ያለው እጃችን ላይ ነው።
የበርካቶች ደምና እምባ በምድሪቱ ላይ እየጮኸ ነው ያለው።ስለዚህ የትውልድ ደም ካሳ የሚል ፈንድ አቋቁመን ህጋዊ ተቀባይነት ያለው ድርጅት የእርቅ ኮሚሽን ነውና በዚሁ ኮሚሽን ስር አካውንት ተከፍቶ በአንድ ቀን መላ የኢትዮጵያ ህዝብ አንድ አንድ ብርና ከዚያ በላይ በነፍስ ወከፍ እንዲያወጣ እንዲሁም ደግሞ እኛ ደግሞ ዲያስፖራው አካባቢ ያለውን በዚያ በኩል ሰብስበን ለተጎጂ ቤተሰቦች የደም ካሳ የሚሰጥበት ሁኔታ እንዲፈጠር የሚል ፕሮጀክት ሲሆን፣ ሁሉም ተስማምተውበት መቼ ይጀመር በሚል ጉዳይ ላይ ነን ያለነው።የኢትዮጵያን ህዝብ አንድ የምጠይቀው ነገር ቢኖር ለዚህ ዓላማ እንዲተባበር ነው።እንደእናትም ስለትውልዱ ይህን ለማድረግ ነው።
አዲስ ዘመን፡- ብሄራዊ እርቅና ብሄራዊ ፍትሐዊ እርቅ ልዩነታቸው ምንድን ነው?
ወይዘሮ ሰዋሰው፡- ለምሳሌ አንዱ ሌላውን በድሎ ታረቁ ሊባሉ ይችላሉ፤ ነገር ግን የደረሰው በደል ካሳ የሚፈልግ ሆኖ ዝም ብሎ ይቅር በል ከሚባል ይልቅ ይቅርታን በካሳ ማድረግ ቢቻል የበለጠ የሻከረ ነገር እንዲጠፋ ያደርጋል።ስለዚህ ፍትሐዊ የሚለው ቀደም ብዬ እንደጠቀስኩልሽ የደም ካሳ ለሚፈልገው ካሳ በመስጠትም ጭምር የሚጠይቅ ይቅርታ ነው።ለምሳሌ በነበረው አለመግባባት የአንድ ሰው እግር ተቆርጦ ቢሆን ለዚያ ሰው ሰው ሠራሽ እግር በማቅረብ ይቅር ብንባባል በተወሰነ መልኩ ቁስልን ሊሽር ይችላል የሚል እምነት አለኝ።
አዲስ ዘመን፡- አንዳንድ ሰዎች በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያውያን እርቀሰላም ያስፈልጋቸዋል ይላሉ፤ ሌሎቹ ደግሞ ማን ከማን ጋር ነው እርቀሰላም የሚያደርገው፤ ችግሩ የፖለቲከኞች ነው ይላሉ፤ ለመሆኑ ኢትዮጵያ እርቀሰላም ያስፈልጋታል ከተባለ ማን ከማን ጋር ነው እርቅ የሚያወርደው?
ወይዘሮ ሰዋሰው፡– አንደኛ ህዝብና መንግሥት ተቀያይሟል።መንግሥት የተቻለውን ሁሉ ቢያደርግ የሚያመሰግነው የለም።መንግሥት ክፉ ነገር ሲያደርግ ይወቀሳል፤ መልካም የሆነ ነገርም ሲያደርግ ይወቀሳል።ነገር ግን የሚያጠፋው መንግሥት ብቻ አይደለም፤ ህዝብም ነው የሚያጠፋው።ስለዚህ የኢትዮጵያ ህዝብ እርቅ ያስፈልገዋል።
ሁላችንም መታረቅ አለብን።እርቅ ሲደረግ የሚታረቁት ኢትዮጵያና ህዝቦቿ ናቸው።ህዝቡ እርስ በእርሱ ተጣልቷል ማለት ሳይሆን ፖለቲከኞችና ጥቅመኞች በሠሩት ሴራ ህዝብና ህዝብ እንዲጣላና እንዲቀያየም ነው ያደረጉት።ሁሉ በስጋት ውስጥ ነውና ከዚህ ሰቆቃ ለማስለቀቅ የመጀመሪያ ሥራችን እስከአሁን ላለቀ ትውልድ ካሳ ማድረግ መቻል አለብን፡፡
አዲስ ዘመን፡- በሃገራችን የእርቀሰላም ኮሚሽን ተቋቁሞ እንደነበር ይታወቃል፤ ለመሆኑ ከዚህ ኮሚሽን ጋር በጋራ ለመሥራት የሞከራችሁበት መንገድ ምን ይመስላል?
ወይዘሮ ሰዋሰው፡- እርቀ ሰላም ኮሚሽን ከተቋቋመ ሦስት ዓመት ሊሆነው ነውና ብዙ ሄዷል።ይሁንና አጥጋቢ ነው ለማለት አልችልም።ምክንያቱም በኮሚሽኑ የተካተቱ ሰዎች የትርፍ ጊዜ እንጂ የሙሉ ጊዜ ሠራተኞች አይደሉም።በዚህ ውስጥ ግን የታቻላቸውን ያህል ሙከራ ያደረጉ አሉ።
በእርግጥ በኮሚሽኑ ውስጥ ምርጫ ሲደረግም ፖለቲከኛ ሁሉ ገብቶበታል።ነገር ግን ፖለቲከኞች ራሳቸው ታራቂዎች ናቸው።በመጀመሪያ ደረጃ ከመንግሥትም ሆነ ከፖለቲካ ሰዎች በኮሚሽኑ ውስጥ መካተት አልነበረባቸውም ባይ ነኝ።በኮሚሽኑ ውስጥ ያሉ አካላት ይቅርታ ተጠያቂዎችም ጠያቂዎችም ናቸው።ስለዚህ ከአወቃቀሩ ጀምሮ የተወሰነ ጉድለት እንዳለው ይሰማኛል።
ኮሚሽኑ ዘንድ ቀርቤም እኔ የያዝኩትን ዓላማ ሳስረዳቸው የቀረን እሱ ክፍል ነበር፤ አንቺ ይዘሽ መጥተሸ አሟልተሻል ነበር ያሉኝ።ከዚህም የተነሳ የተቀበሉኝ በደስታ ነው።እነዚህ ሰዎች ይህን መሰል ነገር ለመሥራት የገንዘብም ድጋፍ ያስፈልጋቸዋል።ኮሚሽኑ አልሠራም ብዬ ለመውቀስ አይደለም፤ ብዙ ሊያጥረው የሚችል ነገር እንዳለ እገነዘባለሁ።ስለዚህም ነው የበኩሌን አንድ ጠጠር በመወርወር ላግዛቸው ከሚል ዓላማ ነው እነሱንም ማግኘትና መነጋገር የፈለኩት።ሰሞኑንም ተገናኝተን ተነጋግረናል።
አዲስ ዘመን፡- እርቀሰላም ለማውረድ ዋነኛው መሰረታዊ ጉዳይ ምንድነው፤ እርቀሰላም ለማውረድስ ያለፉ ቁርሾዎችን መተውና ስለወደፊቱ ማሰብ አይገባም ይላሉ?
ወይዘሮ ሰዋሰው፡– ያለፈ ቁርሾ ስትይ በሐሰት የተነገሩ ብዙ ነገሮች አሉ፤ ይህን የሐሰት ትርክት ሲጋት የኖረ ትውልድ አለ፤ ከዚህም የተነሳ ትውልዱ የተጋተውን የሐሰት ትርክት እንደጣዖት የሚያየው ነው።ምናልባትም አባቱ የአንድ ድርጅት አባል ሆኖ ለዚያ ድርጅት ቆስሎ አሊያም ተገድሎ ሊሆን ይችላል።ከዚህም የተነሳ ሌላ ልክ የሆነውን ነገር ለመስማት ፍላጎት አይኖረውም።ለዚያ ትውልድ አንዱና የመጀመሪያው ፍቅር ማሳየት ነው።
ለምሳሌ እንበልና ኢህአፓ የተባለ 40 ዓመትና ከዚያ በላይ የኖረ ድርጅት ውስጥ የ23 እና የ24 ዓመት ዕድሜ ያላቸው ወጣቶች የድርጅቱ አባል ሆነው ሲናገሩ ሳይ ድርጅቱን ምን ያህል አውቃችሁ ነው የምትሟገቱት ስላቸው አባቴ በዚህ ድርጅት ውስጥ በዚያን ጊዜ ሞቶ ቆስሎ የነበረው የሚሉት ነገር አላቸው።
ስለዚህ ይህ ትውልድ ቂምና በቀል አርግዞ የሚሄድ ነው።የኦነግንም ብትወስጂ እንዲሁ ነው፤ አባቴ ኦነግ ውስጥ ሲታገል ነው የሞተው ይላሉ፤ ህወሓትም እንዲሁ ተመሳሳይ ነው።በዚህ ዓይነት ግፊት ነው ወጣቱ ትውልድ አባትህ ስለሞተ ነው እየተባለ እየተማገደ ያለው።ስለዚህም የበቀልና የደም መላሽነት ፖለቲካ ነው እየተጋቱ ያደጉት።ይህ ዓይነቱ ደግሞ ለወገንም ሆነ ለአገር አይጠቅምም።
ስለዚህ ከዚህ የተነሳ ይህንን ሰንኮፍ ለመንቀል የሞቱትና የተጎዱት ሰዎች ጉዳይ ያመናል ብለን ህመማቸውን እንካፈል ብለን ነው የመጀመሪያውን እርቅ መጀመር አለብን የምንለው።እርቅ መደረግ ያለበት ትውልድ በተነጠቀውና ባልተነጠቀው ህዝብ መካከል ነው።በዚህ ውስጥ አባቱን፣ ወንድሙን፣ ዘመዱን፣ ጎረቤቱን ያጣው ሰው ቁስሉ ሊሽርለት ይችላል።በተወሰነ መልኩም ቢሆን ያለውን ውጥረት ያስተነፍሳል።የእኛ ቁስል የሚጠዘጥዘው አለ እንዴ ያስብላል፡፡
አዲስ ዘመን፡- አሁን ባለው ሁኔታ በሃገራችን እርቀሰላም እንዳይወርድ ያለፈውን ታሪክ እያነሱ አንዱን ማህበረሰብ ከሌላው ጋር ለማጋጨት የሚሠሩ የፖለቲካ ኃይሎች አሉ፤ እነዚህና ሌሎች ኃይሎች ባሉበት እንዴት ነው ሰላም ማውረድ የሚቻለው?
ወይዘሮ ሰዋው፡– ለዚህ ጉዳይ የመገናኛ ብዙኃን ትልቅ ሚና አለው።የመንግሥት መገናኛ ብዙኃን የመንግሥትን አጀንዳ እንደሚያራግቡት እንዲሁም ተቃዋሚ ኃይሎች የራሳቸውን እንደሚያራግቡት ሁሉ ከእነዚህ ውጪ የሆንን አካላት አለንና በዚህ ላይ ትልቅ ሥራ ሊሠራ ይገባል ባይ ነኝ።ለትውልዱ በተለያዩ ቋንቋዎች መንገር መቻል አለብን።
ትልቁ ችግር ሁላችንም ፈራጆች ነን።ሁላችንም ራሳችንን ንጹሕ አድርገን ሌላው ላይ ነው የምንፈርደው።ስለዚህም ከፍረጃ ተላቀን ወደመተሳሰቡ በመምጣት የአንዱ ህመም ሊሰማን የሚችል ከሆነ ነገሮች ሁሉ ቀላል ይሆናሉ።ይህን ጉዳይ በተመለከተም ከሰላም ሚኒስቴርና ከሌሎችም ጋር በመሆን የሚሠራ በመሆኑ ጥሩ ይሆናል ብዬ አስባለሁ።ለወጣቱ የፖለቲከኞችን ቁማር ያውቁ ዘንድ በአግባቡ ልንነግራቸው ይገባል።
ፖለቲከኞች ነን የሚሉትም ሆኑ በውጭ አገር ሆነው በወገናቸው ላይ ሳያውቁትም ሆነ አውቀውት ችግር የሚፈጥሩ አካላት ነገ የትውልድ አገሬ ብለው የሚመጡበት፤ እነሱ ባይመጡ ደግሞ ልጆቻቸው የወላጆቼ አገር ብለው የሚመጡበት ነውና ይህን በመረዳት ራሳቸውን ለዚህ ዓላማ ማስገዛት አለባቸው።
በተለይ ባልተገባ መንገድ የሚሄዱ ፖለቲከኞችን የሚፎክሩበትን የፖለቲካ ጃኬት ማስወለቅ መቻል አለብን።ለአገር እንሠራለን ካላችሁ በአግባቡ መሥራት አለባችሁ ተብለው ሊነገራቸው ይገባል።የያዛችሁት የፖለቲካ አቋም ትክክል አይደለም ብሎ የኢትዮጵያ ህዝብ አንቅሮ ሊተፋቸው ይገባል።ምክያቱም ለኢትዮጵያ ህዝብ ታገልን እያሉ ለኢትዮጵያ ህዝብ ጦስ ካመጡ ህዝቡ ይመዝናቸዋል።
አዲስ ዘመን፡- በቀጣይ ኢትዮጵያ አሁን ካለችበት የፖለቲካ ምስቅልቅል እንድትወጣ ምን መሠራት አለበት ይላሉ፤ ከማንስ ምን ይጠበቃል?
ወይዘሮ ሰዋሰው፡- ሁሌ ለሚፈጠረው ችግር መንግሥት ብቻ መፍትሔ እንዲያመጣ መጠበቅን መተው አለብን።ምንም እንኳ የለውጡ መንግሥት ለውጥ አመጣ ቢባልም በዚህች አገር ላለፉት 27 ዓመታት የነበረው ኢህአዴግ ነው።በእርግጥ በዚያ መንግሥት ውስጥ በጣም መልካም የሆኑ ሰዎች እንዳሉ ሁሉ መልካም ያልሆኑም አሉ።ስለዚህ መንግሥት ላይ ያለ ጫና እና ችግር በአንድ ቀን የመጣ አይደለም።
እናም የኢትዮጵያ ችግር መንግሥት ብቻ ሊፈታው እንደማይችል መጀመሪያ ማመን አለብን።መፍታት የምንችለው ሁላችንም ኢትዮጵያውያን ነን ብለን ልንቀበል ይገባል።ለዚህም ነው መንግሥትና ህዝብ ይታረቅ የምለው።እርቅ ከወረደ በኋላ ለኢትዮጵያ መፍትሔ ማምጣት ቀላል ነው።
የማይዋሽ ነገር በኢትዮጵያ ህዝብ እና በመንግሥት መካከል መቀያየም አለ።ላለፉት 27 ዓመትም ሆነ 40 እና 50 ዓመት ለተሠራው ተገቢ ባልሆነው ነገር የኢትዮጵያ ህዝብ መንግሥትን ተቀይሟል።ይሁንና በመንግሥት ያንን ሁሉ ወንጀል የሠራ ነው ብለን በእሱ ላይ ሁሉን መጣል አንችልም።በሁላችን እጅ ላይ የትውልድ ደም አለ።
ወይ ገድለናል፤ አሊያ አስገድለናል።ወይም ደግሞ ሲገደል ቆመን ዝም ብለናል።ቢገባንም ባይገባንም ለዚህ ጉዳይ አስተዋጽኦ አድርገናልና የዚህ በደል ተሸካሚ አድርገን ራሳችንን መቁጠር አለብን።ለዚህ ነው መንግሥትና ህዝብ ይቅርታ ይጠያየቅ የምለው።
የኢትዮጵያ ህዝብ ለበርካታ ዓመታት ከመንግሥት ሲሰማ የመጣው ነገር አብዛኛው ውሸት ስለሆነ በቀላሉ መንግሥት የሚለውን ነገር አያምንም።ያንን ነገር ለመገንባት ነው አሁን እርቅ በማድረግ ቅጥሩን መልሶ መገንባት ያስፈለገው።ለፖለቲካ ፍጆታ አሊያም አጀንዳ ለማስቀየሻ ሳይሆን እርቁ መደረግ ያለበት ከልብ ነው።
አዲስ ዘመን፡- ቀደም ሲል እንደገለጹልኝ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የኖቤል ሽልማት እንዲወስዱ ተነሳሽነቱን ያስጀመሩት እርስዎ መሆኑን ነው፤ ይሁንና ልክ እንደእርስዎ ሌሎች ሰዎችም እኔ ነኝ የሚል ነገር ሲያነሱ ተሰምቷል፤ ይህን ግልጽ ሊያደርጉልኝ ይችላሉ?
ወይዘሮ ሰዋሰው፡– በእርግጥ በጣም ብዙ ሰው ብዙ ብሏል።እኔ መናገር የምችለው ስለራሴ እንጂ ስለሌላው አላውቀም።እኔ ከዚህ ሂደት ክብር የመፈለግ ነገር እንዲኖረኝ አይደለም የምናገረው።እውነት ስለሆነ ብቻ ነው።ለኖቤል ሽልማት ዘመቻ ማካሄድና መጠቆም የተለያዩ ነገሮች ናቸው።
እንደሚታወቀው አንድ ሰውን ለኖቤል ሽልማት መጠቆም የሚችል ሰው ከዚህ በፊት የኖቤል ሽልማት የተሸለመ ወይም ደግሞ የዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሰሮች አሊያም ደግሞ በየትኛውም አገር በፓርላማ ውስጥ ስልጣን ያለው ሰው መጠቆም ይችላል።
ዘመቻ ማስጀመር ደግሞ ሌላ ነገር ነው።የመጀመሪያውን ዘመቻ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ ስልጣን በያዙ በአራት ወራቸው አካባቢ ነው፤ እኔ ደግሞ በወቅቱ በውስጤ ያለውን ጥማት የሚያስተጋባ መሪ አገኘሁ በሚል ነው ተነሳሽነቱን የወሰድኩት።ከልጄ ጋር አብረን በመሆን ነው ሽልማቱ እንደሚገባው የጻፍነው።እና በዓለም ዙሪያ ያሉ ኢትዮጵያውያን፣ በርካታ ኖርዌጂያውያን፣ በአሜሪካም ሆነ በአውሮፓ በድምሩ ‹አዎን ይገባዋል› የሚል ወደ 69 ሺህ ህዝብ ፈረመልኝ።
በዚህ መልኩ ጠቁሜ ለኖቤል ሽልማት አስገባሁ።ምክንያቴ ደግሞ እንዳልኩልሽ አገር ከአገር እያስታረቀ ስለነበር፤ እስረኛ እየፈታ ስለነበር፣ ስደተኛው እንዲገባ በማድረጉ ነው፤ ይህ ከሆነ ደግሞ አውሮፓ የተጠየፈችው ስደተኛ በአገሩ መመካት ይጀምራል በሚል ጭምር ነው ደብዳቤውን ያስገባሁት።የኖቤል ሽልማት ድርጅቱም ደብዳቤዬን ስለመቀበላቸው ማረጋገጫ ሰጥተውኛል።በእርግጥም ሺህ ሰው ጠቁሞት ሊሆን ይችላል፤ እነሱ ሁሉ የጠቆምኩት እኔ ነኝ የሚሉ ከሆነ ልክ ሊሆኑ ይችላሉ።እኔ ግን የማውቀው ስለራሴ ነው፡፡
አዲስ ዘመን፡- ለሰጡኝ ማብራሪያ ከልብ አመሰግናለሁ፡፡
ወይዘሮ ሰዋሰው፡- እኔም በጣም አመሰግናለሁ።
አስቴር ኤልያስ
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 15/2013