ሙሉቀን ታደገ
የሰው ልጅ እድገት እየጨመረ ሲመጣ እና የህዝብ ብዛቱም በዚያ ልክ ሲሆን ኑሮውን ለማቅለል የተለያዩ የመፍትሄ ሃሳቦችን ሲጠቀም መቆየቱ ይታወቃል።ከዚህ ጋር ተያይዞ የሰው ልጅ የሚደርስበትን ችግሮች ለመቅረፍ ሲል በአንድ አካባቢ የመሰባሰቡ እውነት ለከተሞች መፈጠር ምክንያት እንደሆነ የታሪክ ድርሳናት ያመላክታሉ።ይህ መነሻም በኢትዮጵያ ለተፈጠሩ አንዳንድ ከተሞች ታሪክ ጋር የሚቆራኝ ጭምር ነው ።
በአሁኑ ጊዜ የኢትዮጵያ የከተሜነት ድርሻ 20 በመቶ እንደደረሰ ይገመታል።በቅርቡ በከተማ ልማትና ቤቶች ሚኒስቴር በኩል የተደረጉ ጥናቶች እንደሚጠቁሙት የአገሪቷ የከተማ ህዝብ እድገት ምጣኔ በዓመት 5.4 በመቶ እንደሆነና ይህም በዓለም አቀፍ ደረጃ እጅግ በጣም ከፍተኛ ፍጥነት መሆኑን ያሳያል፡፡
ይህ የህዝብ እድገት ምጣኔ በ1996 እና በ1999 ዓ/ም በተደረጉት የህዝብና ቤቶች ቆጠራዎች መካከል ከታየው የ3.8 በመቶ ዓመታዊ የህዝብ እድገት ፍጥነት ጋር ሲነጻጸር ከፍተኛ ጭማሪ የሚያሳይ ነው።ይህ ከፍተኛ የህዝብ እድገት በከተሞች የመኖሪያ ቤቶችን እንዲሁም ሌሎች መሠረታዊ የማህበራዊ አገልግሎት ተቋማትን እና መሠረተ ልማቶችን ለመገንባት የሚያስፈልገውን የመሬት መጠን ከፍተኛ እንዲሆንና በየጊዜው እየጨመረ እንዲሄድ ያደርገዋል።ከከተሞች መስፋፋት ጋር ተያይዞ በነዋሪዎች ላይ የተለያዩ ተፅእኖዎች እንደሚፈጠር ይታወቃል።እነዚህን ችግሮች ለመፍታት በማሰብም የተለያዩ የመፍትሄ አቅጣጫዎች ተመላክተዋል።
የከተሞቹ ፈጣን የኢኮኖሚ እና የህዝብ ቁጥር እድገት በከተሞቹ ካለው በዝቅተኛ ደረጃ የሚገኝ የጥግግት መጠን ጋር ተዳምሮ በእስካሁኑ ሂደት በአብዛኛው የከተሞች ምስረታ ከፕላን ውጭ ሲከናወን መቆየቱ ይታወቃል።
በፕላን ያልተመሩ የከተሞች ምስረታን ተከትሎ ከሚፈጠሩ ያልተፈለጉ ውጤቶች አንዱ የከተሞች መበከል ነው ።
ነባር የከተማ ክፍሎች መልሰው እንዲለሙና እንዲያንሰራሩ የሚያግዙ የመልሶ ማልማት ስራዎችን በማከናወን ከተሞች ሰብሰብ ያለ እድገት እንዲኖራቸው ያስፈልጋል።ውስን የሆነውን የመሬት ሃብትና መሰረተ ልማትን በተሳለጠ መልኩ ለመጠቀም እንዲችሉ ማድረግም ተገቢ ነው።እንዲህ መሆኑ ከፈጣን የከተሞች እድገት ጋር ተያይዘው የሚመጡና ከመሬት ልማትና አስተዳደር ጋር የሚፈጠሩ ችግሮችን በመቅረፍ ረገድ አዎንታዊ አስተዋጽኦ እንደኖራቸው ያስችላል፡፡
የዛሬው ‹‹ጠይቁልኝ›› አምዳችን ወደ ኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ገብረ ጉራቻ ከተማ ይወስደናል።እንደሚታወቀው የገብረ ጉራቻ ከተማ ከአዲስ አበባ ወደ አማራ ክልል ለሚሄዱ እና ከአማራ ክልል ደግሞ ወደ አዲስ አበባ ለሚመጡ መንገደኞች ቁርስ እና ምሳ አገልግሎት በሚሰጡ ሆቴሎቿ ትታወቃለች ።
ይሁን እንጂ በገብረ ጉራቻ የሚገኙ ብዙ ሆቴሎች ከውስጣቸው የሚወጣውን የመጸዳጃ ቤት ፍሳሽና ቆሻሻ ለዚሁ አገልግሎት በተዘጋጁ ተሽከርካሪዎች ማስነሳትና ማጽዳት ሲገባቸው መጸዳጃ ቤታቸውን ቱቦ ከጎርፍ መፋሰሻ ዲሾች ጋር ማገናኘትን ልምድ አድርገዋል።የመጸዳጃ ቤታቸውን ቆሻሻ ለጎርፍ ማፋሰሻ በተሰራው ዲሽ በመጨመራቸውም የጎርፍ ማፋሰሻው በተለያዩ ነገሮች በሚዘጋበት ጊዜ ከመጸዳጃው የተለቀቀው ቆሻሻ ከዲሹ በላይ በመውጣቱ የህብረተሰቡን ጤና በእጅጉ እንዲታወክ ምክንያት ሆኗል ።
ከዚህ ጋር ተያይዞ በከተማ የሚገኙ ነዋሪዎች ይህን ችግር ተመልክቶ መፍትሄ የሚሰጠን አካል ማን ይሆን በማለት ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ ‹‹ጠይቁልን››አምድ አቤት ብለዋል ።የአዲስ ዘመን ዝግጅት ክፍልም ጉዳዩ ይመለከታቸዋል ያላቸውን የገብረ ጉራቻ ከንቲባ አቶ አለማየሁ ተክለማሪያምን ጠይቆ የሚከተለውን ምላሽ አግኝቷል።
አቶ አለማየሁ በምላሻቸው እንዲህ ብለዋል ‹‹ ነዋሪዎች ያነሱት ቅሬታ እውነት ነው።፤እንዲህ አይነቱን ድርጊት የሚፈጽሙ ባለሆቴሎች መኖራቸውን በከተማዋ የተለያዩ ቦታዎች በአካል በመገኘት አይተናል›› ብለዋል፡፡ይህን ችግር ለመቅረፍ እንቅስቃሴ ስለመኖሩ የተናገሩት አቶ አለማየሁ ፤ ችግሩን በዘላቂነት ለመቅረፍም ራሱን የቻለ ኮሚቴ መቋቋሙን አመላክተዋል ።
እንደ አቶ አለማየሁ ገለጻ ፤ የተቋቋመው ኮሚቴ ለችግሩ መፍትሄ ለማበጀት አዲስ የዲሽ ግንባታ እያሰራ ነው ።ከህብረተሰቡ እና ባለሆቴሎች ጋር በመቀናጀትም አስተማማኝና ሌላ መፍትሄ እስኪገኝ ከመጸዳጃ ቤቶቹ ቆሻሻ የሚወጣበት ቱቦ ኮንክሪት ተሰርቶ እንዲሸፈን ለማድረግ እየተሰራ ነው ።
በኮንክሪት የመድፈን ስራዎችን ለማከናወን ከሁለት መቶ ሺህ ብር በላይ ተመድቧል ያሉት አቶ አለማየሁ፤ ለዚህ ግንባታ የሚሆነው ወጭም በባለ ሆቴሎች እና በህብረተሰቡ አቅም እንደሚሸፈን ጠቁመዋል።
እንደ አቶ አለማየሁ ገለጻ፤ በአሁኑ ጊዜ ቁጥራቸው የበዛ ሆቴሎች ከመጸዳጃ ቤታቸው የሚወጣውን ቆሻሻ ለማስወገድ ዝናብ የሚጠብቁ ናቸው፡፡ሆኖም ፤መጸዳጃ ቤታቸውን ከዲሽ በማገናኘት ዝናብ አስከሚመጣ መጠበቅ ትክክል አይደለም፤ ይህ እንዲሆንም አይመከርም ። ይህ ስህተትም ነው ።ስለሆነም እነኝህ አካላት ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ ለማድረግ የከተማ አስተደዳሩ የግንዛቤ ማስጨባጫ ትምህርቶችን ከመስጠትም አልፎ በህግ ሊጠየቁ እንደሚችሉ ማስጠንቀቂያ ሰጥቷል፡፡ብለዋል የከተማዋ ከንቲባ።
እንደ አቶ አለማየሁ ገለጻ፣ የመንገዶች ባለሥልጣን አዲስ ዲሽ በከተማ ልሰራ ነው።ሆቴሎቹ አሁንም ቢሆን ወደ አዲሱ ዲሽ ቆሻሻ እንዳይጨምሩ ጥብቅ ቁጥጥር እየተደረገ ነው ።ምክንያቱም ወደ አዲሱ ዲሽ ከተጨመረ በከተማዋ የሚገኙ ብዙ አካባቢዎችን የመበከል አቅሙ ይጨምራልና ።
በከተማዋ የተለያዩ ክፍሎች የሚታየውን ችግር በዘላቂነት ለመፍታት እና በተሻለ ደረጃ ለማልማት የመልሶ ማልማት ስራዎችን እየተከናወኑ ነው የሚሉት አቶ አለማየሁ ፤ የልማት ስራዎቹ ከከተማዋ ፈጣን እድገት ጋር ተያይዘው የሚመጡና ከመሬት ልማትና አስተዳደር ጋር የተቆራኙ ችግሮችን በመቅረፍ ረገድ አዎንታዊ አስተዋጽኦ ይኖራቸዋል ብለዋል፡፡
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 15/2013