አስመረት ብስራት
በዓለማችን የአይንን ብርሃን ከሚያሳጡ በሽታዎች መካከል ከአይን ሞራ ግርዶሽ ቀጥሎ በሁለተኛነት የተቀመጠው ግላኮማ ወይም የአይን ግፊት በሽታ ነው። የበሽታውን ምንነት አስመልክቶ በአሚን አጠቃላይ ሆስፒታል ‹‹አል አሚን የአይን ህክምና ማእከል›› ውስጥ የሚሰሩት የአይን መስታወት ንቅለ ተከላ ስፔሻሊስት ዶክተር ኤልያስ ሀይሉ የሚነግሩን አለ። ይህ በሽታ ከአይን ሞራ በተለየ የአይን ብርሃንን ካሳጣ በኋላ እይታው የማይመለስ መሆኑ ከአይን ሞራ በላይ የከፋ ያደርገዋል።
ግላኮማ በተለምዶ የዓይን ውኃ ግፊት ተብሎ የሚጠራ የዓይን ህመም ነው። ስሙ ትራኮማ ከሚባለው የዓይን ህመም ጋር ስለሚቀራረብ ብዙ ሰዎች ተመሳሳይ የሆኑ ምልክቶችን ማለትም የዓይን መቅላት፣ ማቃጠል፣ ማሳከክ፣ መለብለብ እና ቅምጥ (ዓይናር) መያዝ የመሳሰሉ ስሜቶችን ቢያዩም የህመሙ ተፈጥሮ እና ስሜት እንዲሁም ምልክቶች ግን ከትራኮማ (የዓይን ማዝ) ፈፅሞ የተለዩ ናቸው።
ግላኮማ (የአይን ውኃ ግፊት) ምንድን ነው?
ዓይናችን በሰውነታችን ውስጥ ካሉ እጅግ ውስብስብ የሆኑ አካላት ውስጥ አንዱ ነው። ከአምስቱ የስሜት ህዋሳት ውስጥም አንዱ ሲሆን ለጭንቅላታችን ግብዓት ከሚሆኑ ነገሮች ውስጥ 60 በመቶ የሚሆነውን የሚያቀብል ተዓምራዊ አካል ነው። ብርሃን ከምናየው ነገር ላይ ካረፈ በኋላ ወደ ዓይናችን ይገባል።
ከዓይናችን ውስጥ ገብቶ ሪቲና ከተባለው የውጨኛው የአንጎላችን ክፍል ላይ ያርፋል። በዚህ የአንጎላችን ክፍል ያረፈ ብርሃን የምናየውን ነገር ምስል እንደያዘ ብዙ ኬሚካላዊ ተግባራቶች ከተካሄዱበት በኋላ ወደ ኤሌክትሪካል መልዕክትነት ይቀየራል።
ይህንን ኤሌክትሪካል መልዕክት ትርጉም ኖሮት እንድናይ የሚያስችለን የአዕምሮአችን ክፍል ከራስ ቅላችን የኋላ ክፍል ላይ ይገኛል። ስሙም ቪዡዋል ኮርቴክስ ይባላል። ኤሌክትሪካል መልእክቱን ከሪቲና ተቀብሎ ወደ ቪዡዋል ኮርቴክስ የሚያደርስልን ከ12ቱ የማእከላዊ ነርቮች ውስጥ አንዱ የሆነው ኦፕቲክ ነርቭ የሚባለው ነው። በዚህ ሂደት ውስጥ የትኛውም ቦታ ላይ ችግር ከተፈጠረ ዕይታችንን እንደ ጉዳቱ መጠን በቋሚነት እናጣለን።
ግላኮማ ማለት ኤሌክትሪካዊ መልዕክቱን ከሪቲና ተቀብሎ ወደ ቪዡዋል ኮርቴክስ የሚያደርስልን ነርቭ (ኦፕቲክ ነርቭ) ሙሉ በሙሉ ወይም በከፊል መጎዳት (መሞት) ማለት ነው። ነርቩ መሞት የሚጀምረው ከመካከሉ ላይ (ከምናየው የዕይታ አድማስ ከዳር እና ዳር ያለውን የእይታ ክልል መልዕክት ይዞ የሚሄደውን) ስለሆነ፣ ትኩረት ሰጥተን የምናየውን (የማዕከላዊ ዕይታ አድማሳችንን) አይነካም።
ቀስ በቀስ ግን የነርቩ የጉዳት መጠን እየጨመረ ሲመጣ የማዕከላዊ ዕይታችንንም ጭምር ይጎዳል። በመጨረሻም ዕይታችንን ለዘላለም ይነጥቃል። ብዙ የግላኮማ ዓይነቶች ቢኖሩም በአብዛኛው ሰው ላይ የሚታየው ግላኮማ ያለ አንግል መዘጋት የሚከሰተው ሲሆን ማንኛውንም ሰው ሊያጠቃ ይችላል።
የግላኮማ ምልክቱ እና ስሜቶቹ ምን ምን ናቸው?
ግላኮማ የአንግል መዘጋት እና ሌሎች ተጨማሪ ህመሞች ከሌሉበት በቀር ምንም ዓይነት የህመም ስሜት የለውም። ምልክቶቹ ደግሞ እንደ ግላኮማው ደረጃ ይለያያሉ፡ በዋናነት ግን የዓይን ውሃ ግፊት ሊጨምር ይችላል፤ የዕይታ አድማስ እየጠበበ ይሄዳል የኦፕቲክ ነርቭ መጎዳት ይስተዋልበታል።
ምንም የህመም ስሜት ስለሌለው ብዙዎቹ የግላኮማ ህመምተኞች ወደ ህክምና የሚመጡት እይታቸው ሙሉ በሙሉ ከጠፋ ወይም ሊጠፋ ሲደርስ ነው። ይህም ህክምናውን አስቸጋሪ ያደርገዋል።
ለግላኮማ መንስኤዎች ምንድን ናቸው?
የግላኮማ መንስኤዎች ብዙውን ጊዜ በወል አይታወቁም። ነገር ግን ከህሙማን በሚሰበሰበው መረጃ መሰረት የዓይን ውኃ ግፊት መጨመርን የሚያስከትለው የእድሜ መጨመር ምክንያት ማለትም ከ40 ዓመት በላይ መሆን በተለይም ሴቶች ላይ ይህ ይጎላል፤ ከቅርበት ላይ የማየት ችግር ያለባቸው ሰዎችም ለዚህ በሽታ ተጋላጭ ናቸው። በቤተሰብ ውስጥ ከዚህ በፊት ህመሙ ያለባቸው ሰዎች መኖርና ሌሎች የአይን ህመሞች መኖር በተዘዋዋሪ መንገድ ግላኮማ ያስከትላሉ የሚባሉ መንስኤዎች ናቸው። ከዚህም በተጨማሪ አይን ላይ የሚደርስ ሀይለኛ ምት ለግላኮማ መንሰኤ ነው።
ከእነዚህ መንስኤዎቹ ውስጥ በህክምና ማስተካከል የሚቻለው የመጀመሪያውን ማለትም የዓይን ውኃ ግፊትን ብቻ ነው። የአይን ውኃ ግፊት ከ10 ሚሊ ሜትር ሜርኩሪ ማነስ ከ21 ሚሊ ሜትር ሜርኩሪ ደግሞ መብለጥ የለበትም።
መፍትሄዎቹ ምን ምን ናቸው?
ማንኛውም 40 ዓመት እና ከዚያ በላይ የሆነ ሰው /የቤተሰብ አባል/ የዓይን ዉኃ ግፊት ማስለካት እና የውስጥ ነርቩን በቅርበት ከሚገኝ የዓይን ህክምና ቦታ በመሄድ ማሳየት አለበት። የግፊት መጠኑ የጨመረ ከሆነ ወይም የግላኮማ ምልክት ያለበት ከሆነ ወዲያውኑ ህክምና መጀመር አስፈላጊ ነው። ይህ ካልሆነ ግን ግላኮማ ዕይታን 100 በመቶ በማይመለስበት ደረጃ ይነጥቃል።
የግላኮማ በሽታ ምርመራ
የግላኮማን በሽታ ለመመርመር የአይን ሃኪም የእይታዎ ሁኔታን እና አይንዎን በተለጠጠ ፑፒልስ ምርመራ ያደርጋል። የአይን ምርመራው ትኩረት የሚያደርገው በኦፕቲክ ነርቭ ዙሪያ ሲሆን በግላኮማ ህመም ጊዜ የተለየ መልክ አለው። በተጨማሪም የኦፕቲክ ነርቭ ፎቶግራፍ ምርመራውን ከማገዙም በላይ የኦፕቲክ ነርቭ የመልክ/እይታ ለውጦችን ለመከታተል ይረዳል። በተጨማሪም
ቶኖሜትሪ (Tonometry) የተባለ ምርመራ የአይን ግፊትን ለመለካት ይሰራል።
የግላኮማ በሽታ ህክምና
የግላኮማ በሽታ ምርመራ የአይን ጠብታ፣ ላሰር ሰርጀሪ ወይም ማይክሮ ሰርጀሪን ያጠቃልላል። የአይን ጠብታዎች እነዚህ በአይን የፊት ክፍል ላይ የፈሳሽ መፈጠርን ይቀንሳል ወይም የፈሳሽ መውጣትን/መወገድን ይጨምራል። ሌላው ግላኮማን ለማከም የሚደረግ የላሰር ቀዶ ጥገና ከአይን ውስጥ ፈሳሽን ለማውጣት ወይም የፈሳሽ መታገድን ለማስወገድ ይደረጋል።
ማይክሮ ቀዶ ጥገና (Microsurgery) ትራብኩሎክቶሚ በተባለ የቀዶ ጥገና መንገድ ሲሆን ፈሳሹን ለማስወገድ አዲስ የመፍሰሻ መስመር መፍጠር/መስራት ነው። በዚህም መንገድ በአይን ውስጥ የሚፈጠረውን ግፊት በማስወገድ ግላኮማን ያስወግዳል።
የህፃናት/ውልደት ግላኮማ (Infant or Congenital Glaucoma) ይህ ማለት ሲወለዱ የግላኮማ በሽታ ተጠቂ ሆነው ይወለዳሉ። ይህ በሽታ የሚታከመው በመጀመሪያ በቀዶ ጥገና ነው። ምክንያቱም የዚህ ችግር መነሻው የፍሳሽ መስመር ችግር ስለሆነ ነው።
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 11/2013