ሙሉቀን ታደገ
“አንዳንዴ ዓለምን በቴክኖሎጂ ማሳደግ ለወንጀለኛ መጥረቢያ እንደመስጠት ይቆጠራል” ይህ ከታዋቂው የሳይንስ ሊቅ አልበርት አንስታይን አባባሎች ውስጥ አንደኛው ነው። ቴክኖሎጂን ለመልካም ነገር የሚያውሉ ግለሰቦች እና ቡድኖች እንዳሉ ሁሉ ለመጥፎ ተግባር የሚጠቀሙ እንዳሉ ማንም የሚያውቀው ጥሬ ሃቅ ነው። ከዚህ ጋር ተያይዞ በሃገራችን ቴክኖሎጂን በመጠቀም በተለያዩ ማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ለተለያዩ አገልግሎት የሚውሉ ምርቶች መድኃኒት ናቸው በማለት የሚያስተዋውቁ እና የሚሸጡ ግለሰቦች እና ቡድኖች መኖራቸው ይታወቃል።
በእነዚህ ቴክኖሎጂን ተጠቅመው መድኃኒቶችን በሚሸጡ እና በሚያስተዋውቁ ግለሰቦች እና ቡድኖች ጉዳት የደረሰባቸው በአዲስ አበባ የሚኖሩ ሰዎች ስለጉዳዩ ለአዲስ ዘመን ዝግጅት ክፍል በመጠቆም፤ እነዚህን ግለሰቦች እና ቡድኖች የሚቆጣጠር አካል ማን ይሆን ? ምንስ እርምጃዎችን እየወሰደ ይገኛል? ሲሉ ጠይቁልን ብለዋል። በዚህም መሰረት ዝግጅት ክፍሉ ስለጉዳዩ ይመለከተዋል ያለውን በኢትዮጵያ ምግብና መድኃኒት ቁጥጥር ባለስልጣን መስሪያ ቤት የመድኃኒት ተቋማት ኢንስፔክሽን ዳይሬክቶሬት የኢንስፔክሽን ቡድን አስተባባሪ አቶ ሳሙኤል ማሬ ጠይቆ የሚከተለውን ምላሽ ይዞ መጥቷል።
እንደ አቶ ሳሙኤል ገለጻ፤ ለቤተሰብ ምጣኔ ከሚረዱ ውስን መድኃኒቶች ውጭ በማንኛውም አግባብ መድኃኒቶችን ማስተዋወቅ በአዋጅ የተከለከለ ነው። እንዲተዋወቁ የተፈቀዱ ለቤተሰብ ምጣኔ የሚረዱ መድኃኒቶች ብቻ ቢሆኑም፤ እነርሱም ማስተዋወቅ የሚችሉት የባለስልጣን መሥሪያ ቤቱን አስፈቅደው ብቻ ነው። ባለስልጣን መሥሪያ ቤቱን አስፈቅደው ከባለስልጣን መስሪያ ቤቱ የተፈቀደበትን የምስክር ወረቀት ወይም ደብዳቤ በመያዝ ለአስተዋዋቂው ድርጅት በማቅረብ ነው። ማስታወቂያዎች ለህብረተሰቡ ይፋ የሚደረጉት የማስተዋወቂያ ይዘት ሳይቀር ከተገመገመ በኋላ መሆኑንም ያስረዳሉ ።
ይሁን እንጂ አንዳንድ ግለሰቦች እና ድርጅቶች መድኃኒት ማስተዋወቅ አይቻልም እየተባሉ እና የሀገሪቱን ሕግ በማናለብኝነት በመጣስ በተለያዩ ማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ ማለትም በፌስ ቡክ፣ በቴሌግራም ወዘተ ለጸጉር በራነት፤ ቦርጭን ለማጥፋት፤ ለስፈንተ ወሲብ፤ ለማድያት ወዘተ በማለት ማስታወቂያዎችን ሲሰሩ እንደሚታዩ አቶ ሳሙኤል አመላክተዋል ።
እንደ አቶ ሳሙኤል ገለጻ፤ መድኃኒቶች ለህብረተሰቡ መተዋወቅ ያለባቸው ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ከፈቀደ ብቻ ነው። ነገር ግን ማህበራዊ ሚዲያዎችን በመጠቀም መድኃኒት ማስተዋወቅ እና መሸጥ አይቻልም ሲባል በዋነኝነት ከግንዛቤ ውስጥ መግባት ያለበት ጉዳይ እነኝህ ድርጅቶች ወይም ግለሰቦች የሚሸጧቸው መድኃኒቶች ጥራታቸው፣ ደህንነታቸው እና ፈዋሽነታቸው ያልተረጋገጠ በመሆኑ ነው ።
በማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ ተዋውቀው የሚሸጡ ምርቶች ፈዋሽነት፣ ደህንነት፣ ጥራት እና ሌሎች ከመድኃኒት ጋር ተያይዞ የሚነሱ ቁልፍ የሚባሉ ሂደቶችን ያላለፉ በመሆናቸው ሕገወጦች ይህንን አጋጣሚ በመጠቀም ተመሳስለው የተሰሩ እና ትክክለኛውን የመድኃኒትነትን ግብዓት ያልያዙ፣ ደህንነታቸው፣ ፈዋሽነታቸው ያልተረጋገጠ እና ጥራት የሌላቸው ምርቶችን ለህብረተሰቡ እንደሚሸጡ ገልጸዋል።
በትክክል ቁጥራቸውን ማወቅ ባይቻልም የተለያዩ ማህበራዊ ሚዲያዎችን በመጠቀም ደህንነታቸው ያልተረ ጋገጡ ነገሮችን በመድኃኒት ስም የሚያስተዋውቁ እና የሚሸጡ አካላትን የተለያዩ አካሄዶችን በመጠቀም እና ማጣራቶች በማድረግ ከፖሊስ ጋር በመሆን ሕገወጦችን እጅ ከፍንጅ በመያዝ ለሕግ እያቀረቡ እንደሆነ ይገልጻሉ።
እንደ አቶ ሳሙኤል ገለጻ፤ ሜን ኦጀክሲዲን ጸጉር ያበቅላል ፣ ቪ ማክስ የስንፈተ ወሲብ መድኃኒት ነው ወዘተ በማለት ሕገ ወጦች የማህበራዊ ሚዲያዎችን በመጠቀም ወንጀሎችን በስፋት እና በተቀናጀ መልኩ ይሰሩ ነበር። ከዚህም በተጨማሪ የኮሮና ወረርሽኝ በአገራችን መግባቱ ይፋ ከተደረገ በኋላ በማስክ፣ በንጽህና መጠበቂያ ቁሶች እና ጓንቶች ላይ ሕገወጦች የተለያዩ ማህበራዊ መገናኛዎችን በመጠቀም በተለያዩ መልኩ የጅምላ ዘመቻዎች በማድረግ ምርቶችን ለማስተዋወቅ እና ለመሸጥ የተሞከረበት ጊዜ ነበር ።
በትክክል ቁጥራቸውን ማወቅ ባይቻልም የተለያዩ ማህበራዊ ሚዲያዎችን በመጠቀም ደህንነታቸው ያልተ ረጋገጡ ነገሮችን በመድኃኒት ስም የሚያስተዋውቁ እና የሚሸጡ አካላትን የተለያዩ አካሄዶችን በመጠቀም እና ማጣራቶችን በማድረግ ከፖሊስ ጋር በመሆን ሕገወጦችን እጅ ከፍንጅ በመያዝ ለሕግ እያቀረቡ እንደሆነ የሚገልጹት አቶ ሳሙኤል፤ እነኝህን ግለሰቦች እና ድርጅቶችን ለሕግ በማቅረብ አሁንም ሰፊ ሥራ እየተሰራ መሆኑን አመላክተዋል። ነገር ግን ተደራሽነቱ ላይ ክፍተት መኖሩን በመጠቆም ሁሉንም ለማስቆም ጥረት የሚደረግ መሆኑን ተናግረዋል ።
በዚህ ድርጊት ላይ የተሰማሩ ግለሰቦች እና ድርጅቶችን ከድርጊታቸው እንዲመለሱ ለማድረግ አዳዲስ ዘዴዎችን በመቀየስ እየተሰራ ነው የሚሉት አቶ ሳሙኤል፤ ጥቆማዎችም ከተለያዩ ቦታዎች ሲመጡ ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ በዘረጋው አሰራሮች ጥቆማዎችን የሚያጣራበት ዘዴዎች በመጠቀም እንደዚህ አይነት ስራ የሚሰሩ ሰዎችን ለሕግ እየቀረቡ መሆናቸውን አመላክተዋል ።
ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ በማህበረሰቡ ላይ የግንዛቤ የማስጨበጫ ስራዎችን እያከናወነ መሆኑን የሚናገሩት አቶ ሳሙኤል፤ የሚሰጠው የግንዛቤ ማስጨበጫ መድኃኒት አይደለም፤ በማህበራዊ መገናኛ ዘዴ ማስተዋወቅ ቀርቶ በማንኛውም መልኩ በመገናኛ ብዙኃን ማስተዋወቅ የማይቻል መሆኑን ጠቁመዋል። መድኃኒት ማስተዋወቅ አይቻልም የሚለውን ለህብረተሰቡ ግንዛቤ ከፈጠርን ሕገወጦች በማህበራዊ ሚዲያዎች መድኃኒትን ለመሸጥ በሚያስተዋውቁ ጊዜ ግንዛቤ የተፈጠረበት ሰው ለምን ብሎ ራሱን መጠየቅ እንዲችል ለማድረግ እየተሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
ድርጅቶች የሚያስተዋውቋቸው እና የሚሸጧቸው ምርቶች ደህንነታቸው፣ ጥራታቸው እና ፈዋሽነታቸው አይታወቅም። ስለዚህ የሚተዋወቁ የመድኃኒት ምርቶችን መጠቀም ለከፋ ጉዳት የሚያጋልጡ መሆናቸውን መገንዘብ እንደሚገባ አቶ ሳሙኤል የጠቆሙት፤ በተለያዩ ድረ ገጾች የሚተዋወቁ ምርቶችን መግዛት መጠቀም ማለት ያልተረጋገጠ ምርት እንደመውሰድ እና በራስ ሕይወት የሞት ፍርድ እንደመፍረድ መሆኑንም ይናገራሉ። በመሆኑም ማህበረሰቡ ምርቶችን መግዛት ያለበት ፈቃድ ከተሰጣቸው መድኃኒት መደብሮች ወይም መድኃኒት ቤቶች ብቻ መሆን እንዳለበት አመላክተዋል።
መድሃኒት በኢንተርኔት መሸጥም ሆነ ማስተዋወቅ በየትኛውም አለም ክልክል ነው የሚሉት አቶ ሳሙኤል፤ ህብረተሰቡ እነኝህን ምርቶች ከመግዛት በመቆጠብ እና ሌላውንም ህብረተሰብ በነኝህ አካላት ከሚደርስበት ጉዳት ለማዳን በ8ሺህ 482 ነጻ የስልክ መስመር በመደወል ወይም በአካል በባለስልጣኑ መስሪያ ቤት በመምጣት መጠቆም እንደሚቻል አመላክተዋል።
በዚህ ገፅ ላይ አንባቢያን በሚፈልጉት ጉዳይ ላይ ጥያቄ የሚያቀርቡበት እና እኛም የሚመለከተውን አካል መልስ ጠይቀን የምናስነ ብብበት ሲሆን፤ ማንኛውም ሰው በስልክ ቁጥር 0111264326 በመደወል ጥያቄ እና አስተያየት ማቅረብ ይቻላል።
አዲስ ዘመን ሚያዚያ 8/2013