ቁርጠኝነት-ተግባር-አንድነት የታየበት አረንጓዴ ዐሻራ

የ2017 ዓ.ም የአርንጓዴ ዐሻራ መርሀ ግብር በጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ (ዶ/ር) በይፋ ተጀምሯል። ይህን የአረንጓዴ ዐሻራ መርሀ ግብር በይፋ መጀመር ተከትሎም የተለያዩ የሀገሪቱ ክልሎች ርዕሳነ መስተዳድሮች አስጀማሪነት በአራቱም መዓዘናት ለቀጣይ ትውልድ ስንቅ የሚሆን ዐሻራን እያሳረፉ ይገኛሉ።

የዘንድሮ ዓመት አረንጓዴ ዐሻራ ‹‹በመትከል ማንሰራራት ›› የሚል መሪ ቃልን ይዞ ለሰባተኛ ጊዜ የሚከናወን ሲሆን፤ 7 ነጥበ6 ቢሊዮን ችግኞችን ለመትከል በዕቅድ ተይዟል። ከዚህ ውስጥም 40 በመቶ የሚሆነው ለደን ሽፋን የሚውል ሲሆን፤ 60 በመቶ የሚሆነው ችግኝ ደግሞ ለምግብነት የሚውል ነው።

ላለፉት ስድስት ዓመታት ሲካሄድ የቆየው ምድርን የማልበስ፣ ተፈጥሮን የመመለስ ሥራ ከንቅናቄ እና ከሰሞናዊ ጉዳይ ባለፈ ተጨባጭ ውጤት እያመጣ ነው። የአረንጓዴ ዐሻራ ንቅናቄ እንደ ሀገር ያለንን የደን ሽፋን በማሳደግ፣ የተፈጥሮ ሚዛንን በመጠበቅ ዓለም እየተፈተነበት የሚገኘውን የአየር ንብረት ለውጥ ለመዋጋት አይነተኛ ሚና ይጫወታል። እስካሁንም የሀገሪቱን የደን ሽፋን ቀድሞ ከነበረበት 3 በመቶ ወደ 27 በመቶ ማሳደግ ተችሏል።

በፍራፍሬ ምርቶች እንዲሁ በተለያዩ ክልሎች የተተከሉ ለምግብነት የሚውሉ ችግኞችን ለመትከል በተሠሩ ሥራዎች የቡና ችግኞች ምርት መስጠት ሲጀምሩ፤ በፍራፍሬ ምርቶች አፕል፣ ፓፓዬ እና የአቮካዶ ምርቶች በሀገር ውስጥ እና በዓለምአቀፍ ገበያዎች መቅረብ ጀምረዋል።

ንቅናቄው እንደ ሀገር ያለንንን ምርት ከማሳደግ ባለፈ የተለያዩ ችግኞችን በማፍላት፣ በማከፋፈል እንዲሁም በመንከባከብ የራሳቸውን ገቢ ማግኘት ለሚችሉ በርካታ ወጣቶች እና ሴት ሥራ ፈጣሪዎች የገቢ ምንጭ እና የሥራ እድል መሆን ችሏል።

አረንጓዴ ዐሻራ ኢኒሼቲቭ አረንጓዴ እና ለየአየር ንብረት ለውጥ የማትበገር ኢትዮጵያን ለመገንባት በማለም በ2011 ዓ.ም ተጀምሯል። በጊዜውም በአራት ዓመታት ውስጥ 20 ቢሊዮን ችግኞችን ለመትከል እቅድ የተያዘ ሲሆን 20 ቢሊዮን የሚጠጉ ዜጎችን በማስተባበር በአራት ዓመታት ውስጥ 25 ቢሊዮን ችግኞችን በመላው ሀገሪቱ ለመትከል መቻሉ ይታወሳል።

ባለፉት ስድስት ዓመታትም በተካሄደው የአረንጓዴ ዐሻራ መርሀ ግብር 40 ቢሊዮን ችግኞች ተተክለዋል። በአንድ ጀምበር 500 ሚሊዮን ችግኝ በሚል የንቅናቄ መርሀ ግብር በራስ አቅም ሀገር በቀል የሆኑ ኢኒሼቲቮችን በመቅረጽ እና ሕዝብን በአንድ በማስተባበር እስካሁን የተካሄዱትን የአረንጓዴ ዐሻራ መርሀግብሮች ማከናወን ተችሏል።

ኢኒሼቲቩ እንደ ሀገር እየተጋፈጥናቸው ያሉ የአየር ንብረት ለውጥ ፈተናዎች በቀጣይም ለመጋፈጥ የአካባቢ መራቆትን፣ የደን ልማትን፣ የተቀናጀ ውሃ እና አፈር ሀብት አያያዝን ያካተቱ ሁለገብ ምላሽን ለመስጠት ያላትን ቁርጠኝነት የሚያንጸባርቅ ነው። ይህ ሀገር በቀል ኢኒሼቲቭ ለዘርፉ እያደረገ ያለውን አስተዋጽኦ በመመልከትም በርካታ ዓለምአቀፍ ትኩረትን ማሳብ ችሏል።

የአየር ንብረት ለውጥ አፍሪካውያን የሚፈተኑበት ጉዳይ እና ችግሩን ለመቅረፍ እየተሠራበት ያለ ሲሆን ኢትዮጵያ ችግሩን ለመቅረፍ እየሰጠችው የምትገኘው ምላሽ አፍሪካ የአየር ንብረት ለውጥ ተጎጂ ብቻ ሳትሆን የመፍትሄ አካል ጭምር መሆን እንደምትችል ያሳየ እና ለሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ተሞክሮ መሆን የሚችል ነው።

ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል በሠራችው ሥራ ሁለተኛውን የአፍሪካ የአየር ንብረት ለውጥ ጉባዔ ለማዘጋጀት ተመርጣለች። በአሁኑ ሰዓት የተለያዩ ዓለም አቀፍ ጉባዔዎችን የሚሰናዱባት ማዕከል የሆነችው ኢትዮጵያ ይህንን የአየር ንብረት ለውጥ ጉባዔ ስታዘጋጅ እንደከዚህ ቀደሙ እንደምታደርገው መድረኩ አፍሪካ ባልዋለችበት የአየር ንብረት ለውጥ ፈተና ከፍተኛ ተጎጂ የሆነችውን የአፍሪካን ድምጽ ለማሰማት የሚያስችል መሆኑ ተገልጿል።

ኢትዮጵያ ከዚህ ቀደም በነበሩ መሪዎች የአየር ንብረት ለውጥን ለመዋጋት የምታደርጋቸውን ጥረቶች በተግባር አሳይታለች። ከለውጡ ወዲህ እንዲሁ ያለማቋረጥ ለተከታታይ ስድስት ዓመታት የአረንጓዴ ዐሻራ መርሀ ግብርን በማከናወን 40 ቢሊዮን የሚጠጉ ችግኞችን በመትከል ያላትን የደን ሽፋን አሳድጋለች።

ከምትተክላቸው ችግኞች ለምግብነት የሚውሉ ችግኞችን በመጨመር እና እያንዳንዱን ቦታዎች በመጠቀምም ያላትን ቁርጠኝነት፣ በጉልህ የሚታይ ተግባር እና በህብረት ማሳካት የማይቻል ነገር እንደሌለ ያሳየችበት ነው። በእርግጥም ኢትዮጵያ ይህንን ጉባዔ ለማዘጋጀት መመረጧ ትክክል ነው።

የአረንጓዴ ዐሻራ ንቅናቄው እንደ ሀገር ያለውን የደን ሽፋን ለማሳደግ ባለፈ በተለያዩ ቦታዎች የመሬት መንሸራተት ስጋት የሆኑ ስፍራዎች አስቀድሞ ለመካከል ያስቻለ ነው። በተጨማሪም ሀገር በቀል ችግኞችን መትከል ላይ ትኩረቱን በማድረግ፣ ምርትን የሚጨምሩ ችግኞችን በማከል ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ እንዲኖረው እያደረገም ጭምር ነው።

በሀገራችን ተለምዷዊ ብሂል በእድሜ የገፉ እናቶች ልጆቻቸውን ቤተሰብ እንዲመሠርቱ በሚመክሩበት ወቅት ልጅ ለማሳደግ ልጆቻቸው ላይ የሚያዩትን ጭንቀት ለመቀነስ ‹‹ልጅ በእድሉ ያድጋል›› የሚለውን አባባል አብዝተው ይጠቀማሉ።

ነገር ግን ሰውን ሰው ሊያሰኝ በሚችል ሥነ ምግባር፣ ዓላማ ይዞ የሚያድግ የወለደውን ቤተሰብ፣ ያደገበትን ማህበረሰብ፣ ሀገርን እና ትውልድን የሚጠቅም ልጅን ለማሳደግ እድል ብቻውን በቂ አይሆንም። እንደ ወላጅ ልጅን በትክክለኛው መንገድ ለማሳደግ የሚያስችል ኃላፊነት መውሰድን ይጠይቃል።

ችግኝ መትከል አንዱ ትልቅ ርምጃ ሲሆን ዓላማውን ለማሳካት ግን የተተከሉት ችግኞች መጽደቅ አለባቸው። ለዚህም ይህ የአረንጓዴ ዐሻራ ንቅናቄ በየጊዜው የተተከሉ ችግኞችን ከቁጥር በዘለለ ኢትዮጵያ ሆነች አፍሪካ እየተጋፈጠች የምትገኘውን የአየር ንብረት ለውጥን በማገዝ ረገድ ትልቅ ፋይዳ ያለው መሆኑን በመረዳት በዘንድሮው የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር ላይ በነቂስ ወጥቶ ዐሻራን ማሳረፍ ይገባል።

ይህ አምድ በተለያዩ ፖለቲካዊ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ዜጎች ነፃ ሀሳባቸውን የሚሰጡበት ነው።በዓምዱ ላይ የሚወጡ ጽሁፎች የዝግጅት ክፍሉን አቋም አያመለክቱም።

ሰሚራ በርሀ

አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሐምሌ 12 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You