ግጭት እና ጦርነት ይብቃ የሚለው የሕዝብ ድምጽ ይሰማ!

የአማራ ሕዝብ እንደየትኛውም ኢትዮጵያዊ ለሰላም ትልቅ ከበሬታ ያለው፣ በእያንዳንዱ የሕይወት እንቅስቃሴው ውስጥ ስለ ሰላም የሚሰብክ ፣ የሚያዜም፣ድምጹን ከፍ አድርጎ የሚያሰማ፣ይህም የማህበረሰባዊ ማንነቱ መገለጫ የሆነ ሕዝብ ነው። ሃይማኖታዊም ሆነ ባሕላዊ እሴቶችም ሰላምን የሚሰብኩ፣ የሚያጸኑ እና የሚያስቀጥሉ ናቸው።

ሰላም በግለሰብ ሆነ በቤተሰብ ፣ በማህበረሰብም ሆነ በሀገር የዕለት ተዕለት ሕይወት እና እጣ ፈንታ ላይ የሚኖረውን አዎንታዊ እና አሉታዊ ተጽእኖ በአግባቡ መረዳት የቻለ ነው። በሀገረ- መንግሥት ግንባታ ታሪክ ውስጥ ካለው የረጅም ዘመን አበርክቶ አኳያም እንደሀገር የሰላም እጦት የቱን ያህል ዋጋ እንደሚያስከፍል በታሪክ ፍሰት ውስጥ በተጨባጭ ማየት እና ማስተዋል የቻለ ነው።

በማንነቱ ውስጥ የሀገር ፍቅር ጎልቶ የሚደመጥበት፣ ለሀገር ዕድገት እና ብልፅግና የሚቀና ፣ ለእዚህም በዘመናት መካከል በብዙ ትጋት የተመላለሰ፣ ዛሬም የሚመላለስ፣ ለነጻነት እና ለፍትሕ፣ ለወዳጅነት እና ለጉርብትና አብዝቶ ራሱን የሰጠ፣ ከቁሳዊው ዓለም ይልቅ ለሰብዓዊነት የሚቀና ነው።

በእዚህ ሁሉ ግን፤ በብዙ የሚሻውን ሰላም እና ከሰላም የሚመነጭ ልማት እና ብልፅግና የራሱ ማድረግ ሳይችል እንደ የትኛውም ኢትዮጵያዊ የድህነት እና ከድህነት የሚመነጭ የጉስቁልና ሕይወት ለመኖር የተገደደ፣ በዘመናት መካከል በተከሰቱ አለመግባባቶች በተፈጠሩ ግጭቶችም ብዙ ትናንቶች ያጣ ሕዝብ ነው።

በሀገሪቱ በተለያዩ ወቅቶች በተነሱ ሕዝባዊ ንቅናቄዎች ሆነ የለውጥ መነሳሳቶች በለውጥ ኃይልነት የሚጠቀስ፣ ለለውጥ ብዙ ዋጋ የከፈለ እና አሁንም እየከፈለ የሚገኝ፣ ከትናንት ሀገራዊ የታሪክ ትርክት በሚመነጭ ቁጭት፣ ነገን የተሻለ ለማድረግ የሚታትር ፣ ለእዚህ የሚሆንም ትጋት ያለው ነው።

ባለፉት ሰባት አስርት ዓመታት እንደሀገር በተፈጠሩ የለውጥ መነሳሳቶች፣ በብዙ መስዋዕትነት የታጀበ ከፍ ያለ ተሳትፎ የነበረው፣ ተሳትፎው በሀገራዊ የፖለቲካ ባሕል ውስጥ በነበረው ያልተገራ አስተሳሰብ ያልተገባ ዋጋ እንዲከፍል የተገደደ ፤በእዚህ ያልታከመ የልብ ስብራት ውስጥ የኖረ ነው።

በአሁናዊው ሀገራዊ ለውጥ ውስጥ በመስዋእትነት የታጀበ ተሳትፎ የነበረው ፤ በለውጡ በብዙ ተስፋ እንዳደረጉ የሀገሪቱ ብሔር፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች፣ ለውጡን የራሱ አድርጎ ከፍ ባለ ቁርጠኝነት የተንቀሳቀሰ ፣ ለውጡ ያጋጠመውን ፈተናዎች በጽናት በመታገል ግንባር ቀደም በመሆን የራሱን ታሪክ በደማቅ ቀለም መጻፍ የቻለ ነው።

ይህም ሆኖ ግን ከአብራኩ የወጡ ልጆቹ ከፍላጎቱ እና ከማህበረሰባዊ ማንነት ባፈነገጠ መንገድ ተስፋ አድርጎ ብዙ ዋጋ በከፈለበት ለውጥ ላይ በተቃርኖ ቆመው ብዙ ያልተገባ ዋጋ እንዲከፍል እያደረጉት ነው። በብዙ ድንጋጤ እና ግራ መጋባት ውስጥ፣ ነገን ሳይሆን የሚቀጥሉትን ደቂቃዎች እንዳያስብ በሚያደርግ የስቃይ ጥላ ውስጥ እንዲያልፍም እያስገደዱት ነው።

በዘመናት አብሮ የኖረውን ማህበራዊ መንፈሳዊ እና ባሕላዊ እሴቶችን በሚያሳንስ ፣ የአማራ ሕዝብ በዘመናት ሀገረ መንግሥት ግንባታ ታሪክ ውስጥ የነበረውን የደመቀ ታሪክ የሚያደበዝዝ ከእዚህም አልፎ እንደ ሕዝብ አብዝቶ በሚጠየፈው የባንዳነት ተግባር ውስጥ በመሳተፍ አንገቱን እንዲደፋ እያደረጉ ነው።

በእዚህም ከለውጡ ማግስት ጀምሮ በአማራነት ፣ በአማራ ስም በተፈጠሩ ጽንፈኛ እና ጽንፈኛ አስተሳሰቦች ሕዝብ ሰላሙንና በዘመናት መካከል በብዙ ትጋት የሰበሰበውን ሀብት ንብረቱን አጥቷል፤ ለነገ ተስፋ ያደረጋቸው ልጆቹን ገብሯል፤ ዛሬን በስጋት እንዲኖር በነገ ላይ ያለው ተስፋ እንዲደበዝዝ ሆኗል።

ነግዶ ማትረፍ፣ ወልዶ መሳም ፣ ገብቶ መውጣት የማይችልበት የስጋት ሕይወት ውስጥ እንዲኖር በስሙ ብዙ ተዘምቶበታል፤ ከብዙ ዝምታ እና ትግስት፣ ከብዙ ሆደ ሰፊነት እና ቻይነት በኋላ ሴራ ባንዳነትና ጦርነት ፍጻሜ እንዲኖራቸው አደባባይ ወጥቶ በቃ! ብሏል። ከምንም በላይ ሰላሙን እንደሚፈልግም ድምጹን ከፍ አድርጎ አሰምቷል። ሕዝብ በቃ ሲል ማድመጥ ደግሞ የብልሆች ተግባር ይሆናል!

አዲስ ዘመን ሰኞ ሰኔ 30 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You