
ኢትዮጵያ ከሰባት ዓመታት በፊት ያስተናገደችውን ለውጥ ተከትሎ በብረት ዘንግ ተዘግተው የነበሩ አያሌ በሮች ተከፍተዋል። በሺዎች የሚቆጠሩ የፖለቲካ እስረኞች ተፈተዋል። ብረት አንስተው ሲታገሉ የነበሩ ኃይሎች በሰላማዊ መንገድ ለመንቀሳቀስ ወደ ሀገር ቤት ገብተዋል። አሳሪና የማያሰሩ የሕግ ማዕቀፎች ተሻሽለዋል።
የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ፣ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት እና የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ገለልተኛ ሆነው በአዲስ መልክ ተዋቅረዋል። ሴቶች በስፋት ወደ አመራርነት በማምጣት ቁልፍ የኃላፊነት ቦታዎችን እንዲይዙ ተደርጓል። በበርካታ መንግሥታዊ ተቋማት የሪፎርም ሥራዎች ተሠርተዋል። በተለይም የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ሀገር አክሎ እንደ አዲስ እንዲደራጅ ተደርጓል።
በዲሞክራሲ ባህል ግንባታ ረገድም ኢትዮጵያ የተሳካ ምርጫ ማካሄድ ችላለች። የአፍሪካ ኅብረት ምርጫ ታዛቢ ቡድን “በቅድመ ምርጫ እና በድምፅ መስጫ ዕለት የተከናወኑት ተግባራት ሥርዓት ባለው፣ ሰላማዊ እና ተዓማኒነት ባለው ሁኔታ ተከናውነዋል” ሲል ለምርጫው ሂደት ምስክርነቱን ሰጥቷል። ውጤቱን ተከትሎም 416 ወንበሮችን ያገኘው ገዢው ፓርቲ መስከረም 24 ቀን 2014 ዓ.ም አዲስ መንግሥት መሥርቷል። በኢትዮጵያ ፖለቲካ ባልተለመደ መልኩ በየደረጃው በሚገኙ የመንግሥት የኃላፊነት ቦታዎች ላይ የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮች ሥልጣን እንዲይዙ ተደርጓል።
የለውጡ መንግሥት የዓለም አቀፍ አበዳሪ ተቋማትን እና የሀገራትን ዕዳ ከባዶ ካዝና ጋር ተረክቦ፣ የሀገሪቱ ምጣኔ ሀብት እንዲያንሰራራ በኢኮኖሚ ዘርፍ አበረታች ሥራዎችን ሠርቷል። በግብርናው ዘርፍ የበጋ መስኖ ስንዴን በማልማት በተከታታይ ዓመታት ከፍተኛ መሻሻል የታየበት ከፍተኛ መጠን ያለው ተጨማሪ ምርትም ማግኘት ተችሏል። በኢንቨስትመንት፣ በብድር እና በርዳታ የተገኙ በርካታ ቢሊዮን ዶላሮች ለሀገር ልማት ውለዋል።
የኢትዮ ቴሌኮምን ድርሻ ለውጭ ኩባንያዎች በማስተላለፍ ኢንቨስትመንትን በመሳብ ከስምንት ቢሊዮን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሪ ተገኝቷል። በሀብት ብክነትና በግንባታ ጥራት ችግር ተቋርጦ የቆየውን የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ፕሮጀክትን ከአደጋ ታድጎ በማጠናቀቅ ሪባኑን ለመቁረጥ ከመንፈቅ ያነሰ ጊዜ የቀረበት ደረጃ ላይ ማድረስ ተችሏል። ሌሎችም በጅምር የቆዩ የኢንዱስትሪ ፓርኮች የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ጣቢያዎችና የልማት ተቋማት ግንባታቸው እንዲጠናቀቅ ተደርጓል።
በቱሪዝም ዘርፍም በገበታ ለሸገር፣ ገበታ ለሀገር እና ገበታ ለትውልድ ፕሮጀክቶች በርካታ አካባቢዎችን በማልማት የቱሪስት መዳረሻ ማድረግ ተችሏል። የዳግማዊ ዓፄ ምኒልክ ቤተመንግሥት እና ብሔራዊ ቤተ መንግሥት ቅርስነታቸው ተጠብቆ እድሳት ተደርጎላቸው ለሕዝብ ክፍት ሆነዋል። በኮሪደር ልማት ፕሮጀክት የአፍሪካ መዲናዋን አዲስ አበባን ለስሟ እንድትመጥን በማድረግ ረገድ የተከናወነው ተግባር ማርሽ ቀያሪ ርምጃ ሆኗል።
የለውጡ ጉዞ በስኬትና ድል ብቻ የተሞላ አይደለም። በሀገር ውስጥና በውጭ ከባድ ፈተናዎች የተደቀኑበት እና የበርካቶችን መስዋዕትነት የጠየቀም ነው። በኮቪድ 19 ወረርሽኝ ምክንያት የዓለም ኢኮኖሚ የወደቀበት፤ የቱሪዝሙ ዘርፍ ተቀዛቅዞ ሆቴሎች ተዘግተው የከረሙበት፤ በርካታ ዜጎች ሥራ ፈትተው ቤት የዋሉበት፤ በውጭ ሀገራት በሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ወደ ሀገር ቤት የሚላከው ገንዘብ ያሽቆለቆለበት በመሆኑ ኢትዮጵያም እንደ ሀገር በከፍተኛ ደረጃ የተፈተነችበት ነው።
በርካታ ንጹሐን በታጣቂ ኃይሎች የተገደሉበት፤ ጽንፈኛ ወጣቶች መንገዶች በመዝጋት ከተሞችን ያነደዱበት፤ ፋብሪካዎች የወደሙበት፤ ሰዎች በአደባባይ የተሰቀሉበት፤ የአማራ ክልል ከፍተኛ ባለሥልጣናትና የሀገሪቱ የጦር ኃይሎች ኤታማዦር ሹም የተገደሉበት እንዲሁም ሚሊዮኖች የተፈናቀሉበት ታሪክም የለውጡ ፈተና ሆኖ ይጠቀሳል። በሀገር መከላከያ ሠራዊት የሰሜን ዕዝ ላይ ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም ምሽት በተፈጸመው ጥቃት ምክንያት የተቀሰቀሰው የሰሜኑ ጦርነት ሀገሪቱ በእጅጉ የተፈተነችበት አቀበት ነበር።
በዚህ ወቅት ዓለም አቀፍ የርዳታ ድርጅቶችና ብዙኃን መገናኛዎች የኢትዮጵያን ስም በማጠልሸት ዲፕሎማሲያዊ ጫናዎችን ለማበርታትና ማዕቀቦችን ለማስከተል በተደጋጋሚ የተቀናጁ ዘመቻዎችን አድርገዋል። ሲ ኤን ኤን፣ ሮይተርስ፣ ኒውዮርክ ታይምስ፣ አሶሼትድ ፕረስ፣ ዋሽንግተን ፖስት፣ ቢቢሲ እና ሌሎችም ዓለም አቀፍ ሚዲያዎች ሙያዊ መርሕን ባልተከተሉ ሐሰተኛ ዘገባዎች የኢትዮጵያን እውነት አዛብተው ለዓለም ሲያቀርቡ ቆይተዋል።
የመንግሥታቱ ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት በኢትዮጵያ ጉዳይ ከአስር ጊዜ በላይ ስብሰባዎችን አድርጓል። አየርላንድ የፀጥታው ምክር ቤት በትግራይ ክልል ስላለው የሰብዓዊ ርዳታ የኢትዮጵያን መንግሥት በመጫን በአንድ ድምፅ መናገር አለበት ስትል የአሜሪካ፣ የዩናይትድ ኪንግደም፣ ፈረንሳይ፣ ኖርዌይ እና ኢስቶኒያን ድጋፍ ይዛ በተደጋጋሚ ብትወተውትም በሩሲያ እና ቻይና በፊት አውራሪነት በመሩት በመላው አፍሪካውያን እና በሌሎችም የኢትዮጵያ ወዳጆች እምቢተኝነት ውድቅ ተደርጓል።
የአንበጣ መንጋ ያስከተለው የሰብል ውድመት፣ የጎርፍ አደጋና የውኃ መጥለቅለቅ ያደረሰው ጉዳትና በቅርቡም በቦረና የተከሰተው ድርቅ ደግሞ ተፈጥሮ ያከለችው ብርቱ ፈተና ናቸው። የመሠረታዊ ሸቀጦች ዋጋ በከፍተኛ ደረጃ መወደዱ ምክንያት ኑሮ መወደዱም ትልቅ ተግዳሮት ሆኖ ዘልቋል። ለእነዚህ ሁሉ ፈተናዎች ያልተበገረችው ኢትዮጵያ ጉዞዋን ቀጥላ አመርቂ ድሎችን እያስመዘገበች ትገኛለች።
“ውሾቹ ይጮሃሉ ግመሎቹ መንገዳቸውን ቀጥለዋል” እንደሚባለው ኢትዮጵያ በየጊዜው የሚደቀንባትን ፈተና እያለፈች መሻገሯ ይቀጥላል። ዜጎቿ እንደ ትናንቱ ሁሉ ዛሬም ለክብሯ ይዋደቃሉ። የአባቶቻቸውን አልገዛም ባይነት በደም ወርሰው ሀገራቸውን ለማቅናት ለልማት ይሰለፋሉ። ከፊታቸው የሚቆም የትኛውም ወጀብ እና መሰናክል አያስቆማቸውም። በብርቅዬ ልጆቿ ደም የቀጠለች ሀገር የተለመችውን እድገትና ልማት ከዳር ሳታደርስ መሐል መንገድ ላይ ወገቤን አትልም። ኢትዮጵያ በዕንቁ ልጆቿ ብርቱ ክንድ እንደገና ትነሳለች።
ይህ አምድ በተለያዩ ፖለቲካዊ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ዜጎች ነፃ ሀሳባቸውን የሚሰጡበት ነው።በዓምዱ ላይ የሚወጡ ጽሁፎች የዝግጅት ክፍሉን አቋም አያመለክቱም።
መግነጢስ
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ግንቦት 2 ቀን 2017 ዓ.ም