አዲስ እና እየተዘወተረ የመጣው የሁነቶች ቱሪዝም

ከሶስት ዓመት በፊት የተገኘ መረጃ እንደሚያመለክተው በዓለማችን ለዲፕሎማሲ ተመራጭ ከሆኑ ከተሞች መካከል ከኒውዮርክ እና ብራስልስ ቀጥላ በ3ኛ ደረጃ ላይ የምትገኘው አዲስ አበባ ከ116 በላይ ሀገራት ኤምባሲያቸውን እና ቆንስላ ጽሕፈት ቤቶቻቸውን መቀመጫ ያደረጉባት ከተማ ነች።

የበርካታ ኮንፈረንሶች፣ ወርክሾፖች፣ የሁለትዮሽ/ የሶስትዮሽ ግንኙነቶች፣ የዓለምአቀፍ ስብሰባዎች መካሄጃ፤ የንግድ፣ የጤና፣ የልማት፣ የኢንቨስትመንት፣ ስለ ሠላምና እርቅ መወያያ መድረክ በመሆን የምትታወቀው አዲስ አበባ በማይስ ቱሪዝምም እየታወቀች በመምጣት ላይ ነች ።

ይህ የጉባዔ፣ የኮንፍረንስ፣ የጉዞና የዓውደ ርዕይ ሁነቶችን የሚያካትተው የማይስ ቱሪዝም ዘርፍ መዳረሻ (MICE destination) ወደ ፊትም ተጠናክሮ ስለመቀጠሉ ማሳያዎቹ በርካታ ናቸው ፤ ከዚህ ውስጥ አንዱም በዚሁ ዓመት ተጠናቅቆ የተከፈተውና ዘመናዊው አዲስ አፍሪካ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን እና ኤግዚቢሽን ማዕከል ነው።

በተለይ ካለፉት ሶስት አስርት ዓመታት ወዲህ (ንጉሥ የተባሉ ሰው “የዓለም ዲፕሎማሲ ማዕከሏ – አዲስ አበባ!” በሚል ርእስ ኤፕሪል 15, 2021 ያሰፈሩት ጽሑፍ እንደሚነግረን) ጽህፈት ቤታቸውን ሌላ ሀገር ያደረጉ አህጉራዊ ድርጅቶች ለስብሰባ የሚመርጡት አዲስ አበባን ነው፡፡

ሌላ አፍሪካ ሀገር ውስጥ ሊካሄድ የነበረ ስብሰባ በማንኛውም ምክንያት የስብሰባ ቦታ ለውጥ ቢደረግ ሁነቱ ይከናወን ዘንድ የሚመረጠው ከተማ አዲስ አበባ ነው፡፡ እንደ አፍሪካ ህብረትና ለሌሎቹን ሳንዘረዝር፣ የምስራቅ አፍሪካ የሠላም አስከባሪ ኃይል መምሪያና የሥልጠና ማዕከል ያለው እዚህ አዲስ አበባ ነው፡፡ በመሆኑም፣ አዲስ አበባ አበባነቷ ሁሌም ነው።

በዚሁ ዓመት ኅዳር ወር ውስጥ የሠላም ሚኒስቴር አመራሮችና ሠራተኞች በተቋሙ የተከናወኑ ዓለም አቀፍ እና አህጉራዊ ኮንፈረንሶች አፈፃፀምን መገምገማቸው በመገናኛ ብዙሃን መገለፁ ይታወሳል። በግምገማው ወቅት የሠላም ሚኒስቴር የሠላም ግንባታና ብሔራዊ መግባባት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር ከይረዲን ተዘራ እንደተናገሩት፣ የተከናወኑት ዓለም አቀፍ የኃይማኖት ተቋማት እና አህጉራዊ የሠላም ኮንፈረንሶች በአጠቃላይ ሰላሣ ስድስት ሀገራትን ያሳተፉ ነበሩ።

ሚኒስትር ዴኤታው ሥራን ከተለያዩ ተቋማት ጋር በቅንጅት መሥራትና መምራት መቻላቸው ኮንፈረንሶቹ ውጤታማ ሆነው እንዲጠናቀቁ እንዳስቻላቸው መናገራቸውም በተቋሙ ኦፊሴላዊ ድረ-ገፅ ላይ ሰፍሮ ይገኛል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ያለፈውን ስድስት ወር አፈፃፀም በተመለከተ ከምክር ቤት አባላት ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ በሰጡበት ወቅት (መጋቢት 11 ቀን 2017 አ/ም) እንደተናገሩት (በሌላ ጽሑፋችንም ጠቅሰነዋል) ባለፉት ስድስት ወራት ውስጥ “ኢትዮጵያ ከ80 በላይ ዓለምአቀፍ ኮንፈረንሶችን አካሂዳለች። ይህ በአፍሪካ በቀዳሚነት የተመዘገበ ውጤት ነው።”

ሁሌም እንደሚገለፀው ፤ ኢትዮጵያ የአፍሪካ ማዕከል ስትሆን፤ አዲስ አበባም የአፍሪካ መዲና ነች። በመሆኗም ለሁነቶች (ኮንፈረንስና የመሳሰሉት) ቱሪዝም ምቹነቷ አሻሚ ባይሆንም የበለጠ ከተሠራ ግን ከዚህም በላይ ብዙ ማትረፍ ይቻላልና መዘናጋት አይገባም። ከላይ የተለያዩ ምንጮችን ተጠቅመን ላቀረብነው ማብራሪያ ማሳያ ይሆኑን ዘንድ የተወሰኑትን እንጥቀስ።

ህዳር 2017 ዓ.ም “የበለፀገችና ሠላማዊ አፍሪካን እንገንባ” በሚል መሪ ሃሳብ የተካሄደው የአፍሪካ አሕጉራዊ የሠላም ኮንፈረንስ፤ ከህዳር 6 እስከ 9 /2017 ዓ.ም “የአፍሪካን የብየዳ ሙያ በማጎልበት ቀጣናዊ ትስስር እና ዓለም አቀፋዊ ተወዳዳሪነትን ማረጋገጥ” በሚል መሪ ቃል በዓድዋ ሙዚየም የተከበረው 3ኛው የአፍሪካ የብየዳ ፌደሬሽን ዓመታዊ ጉባዔ እና ዓለም አቀፍ ኮንፈረንስ፤ እንዲሁም በቅርቡ ይካሄዳል ተብሎ የሚጠበቀው ባህልን የተመለከተ ዓለም አቀፍ ጉባዔ ሀገራችን፤ በተለይም መዲናችን አዲስ አበባ በማይስ ቱሪዝሙ ሴክተር እየተነቃቃች ስለ መሆኗ ጥሩ ማሳያዎች ናቸው።

ከጥቅምት 26 እስከ 28/2017 ዓ.ም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድን (ዶ/ር) ጨምሮ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ኢንዱስትሪ ልማት ዋና ዳይሬክተር ገርድ ሙለር በተገኙበት በኢትዮጵያ የተካሄደውንና ዓለምን ከረሃብ ነጻ ለማድረግ ተጨማሪ 500 ቢሊዮን ዶላር የሚያስፈልግ መሆኑ የተገለፀበት የ “ከረሃብ ነጻ ዓለም ጉባዔ” እና ሌሎችንም ስለ ዘርፉ እያበበ መሄድ ሲባል እዚህ መጥቀሱ አስፈላጊ ነው።

ቱሪዝም ሚኒስቴሩ በማህበራዊ ትስስር ገፁ ላይ ባሰራጨው መረጃ “አዲስ አበባ በዘንድሮው የካቲት ወር ብቻ በርካታ ዓለም አቀፍ እና አህጉራዊ ኮንፈረንሶችን አስተናግዳለች” በማለት ያወጀውንም እዚሁ ላይ ደርቦ ማየትና የማይስ ቱሪዝምን አበረታች ግስጋሴ መገንዘብ ይቻላል።

የቀድሞዋ የሀገሪቱ ርእሰ-ብሔር ሣህለወርቅ ዘውዴ በዓለም አቀፍ ደረጃ የቱሪዝም ኢንዱስትሪ በቀን ከ 3 ነጥብ 5 ቢሊዮን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሪ እያስገኘ መሆኑ እየተነገረለት ያለውን የማይስ ቱሪዝም ዘርፍ የሚመራው የኢትዮጵያ ኮንቬንሽን ቢሮ ምስረታ ላይ ተገኝተው የማይስ ቱሪዝም መለያ ዓርማን ይፋ ባደረጉበት ወቅት እንደተናገሩት፣ ምድረ ቀደምቷ ኢትዮጵያ የጎብኚዎችን ቀልብ የሚስቡ ከባህል፣ ተፈጥሮና ታሪክ ቱሪዝም ፀጋዎች ባሻገር በሁነቶች ዝግጅትም በቱሪዝም ዘርፍ ተወዳዳሪ ሊያደርግ የሚችል እምቅ አቅም ያላት ሀገር ነች።

እኛም እንላለን፣ በአስር ዓመቱ ስትራተጂክ እቅድ ላይ የተቀመጠውን ወደ መሬት በማውረድ ይህንን እምቅ አቅምና ሀብት ወደ ኢኮኖሚ መቀየሩ ላይ የጋራ ርብርብ ማድረግ ይገባል።

ግርማ መንግሥቴ

አዲስ ዘመን ረቡዕ ሚያዝያ 29 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You