
ያለፉት ሰባት የለውጥ ዓመታት በኢትዮጵያ ምድር ዘርፈ ብዙ የአመለካከት ለውጥ የመጣባቸው፤ መስከ ብዙ የልማትና የብልፅግና መንገድ የተጀመረባቸው፤ አብነታዊ ተግባራት ተከናውነው አስደማሚ ውጤቶች የተገኘባቸው ናቸው። ይሄው ተግባር እና ውጤት ታዲያ እንደ ሀገርም፣ እንደ ቀጣናም፣ እንደ አሕጉርም፣ አለፍ ሲልም እንደ ዓለም አድናቆትና እውቅና እየተቸረው ይገኛል፡፡
ለዚህ ውጤት መገኘት ደግሞ አንኳሩ ጉዳይ፣ መንግሥት እና ሕዝብ በመሠረታዊ የልማት እና የለውጥ አጀንዳዎች ላይ ተናበው እና የጋራ ፍላጎት ይዘው መሥራት መቻላቸው ነው። በሰላሙም፣ በግብርናውም፣ በትምህርትና በጤናውም፣ በመንገድና በሰው ተኮር የልማት እንቅስቃሴዎችም፤ ሌላው ቀርቶ በበጎ ፈቃድ አገልግሎት የተገኙ ደማቅ ውጤቶች ሁሉ መንግሥት ከሕዝቡ ከፍ ያለ ድጋፍ የማግኘቱ፤ ሕዝቡም በመንግሥት ላይ ከፍ ያለ እምነት የማሳደሩ አብነቶች ናቸው፡፡
በዚህ መልኩ የሕዝብ እና መንግሥት የመተማመንና የመተባበር መንገድ ተጉዞ የተገኘው ዘርፈ ብዙ ውጤት ታዲያ፤ ዛሬ ላይ ኢትዮጵያ በሁሉም መስክ የሚገለጥ የፈጣን ልማትና ዕድገት ባለቤት እንድትሆን አድርጓታል። ይሄ ፈጣን ልማትና ዕድገት የአንድ መስክ ብቻ አይደለም። በሀገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርም ሰነዱ ላይ በግልጽ እንደተመላከተውም ሆነ፤ በአስር ዓመቱ ሀገራዊ የኢኮኖሚ ልማት አቅጣጫ ላይ እንደተገለጸው በሁሉም መስክና አቅጣጫ እየተከወነ ያለ ተግባር፤ በሁሉም መስክና አቅጣጫ እየተገኘም ያለ ውጤት ነው፡፡
ለምሳሌ፣ በኢኮኖሚው መስክ ብናይ፣ ኢትዮጵያ በግብርናው ዘርፍ ከተረጂነትና ከሸማችነት ወጥታ በራሷ አቅም የምግብ ፍላጎቷን ያሟላች፤ አልፋም ስንዴን ወደ ውጪ መላክ የጀመረች፤ ከፍ ሲልም ከአፍሪካ ቀዳሚ ስንዴ አምራች ሀገር መሆን የቻለች ነች። በአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብርም ከአርባ ቢሊዮን የተሻገረ ችግኝ መትከል ችላለች። በሌማት ትሩፋት ኢኒሼቲቭ የተጀመረው ግስጋሴም፣ ለምግብ ዋስትናም ለሥራ ዕድል ፈጠራም አቅም ሆኗል፡፡
በኢንዱስትሪ ልማት ዘርፉም በአንድ በኩል ገቢ ምርቶችን በሀገር ውስጥ የመተካት፤ በሌላ በኩል ወጪ ምርቶችን እሴት ጨምሮ በመላክ በኩል እየተሠራ ባለው ሥራ የውጪ ምንዛሪን የማዳን ውጥኑን እያሳደገው ይገኛል። በማዕድን ዘርፉም በተሠራው ሥራ እንደ ሀገር ከፍ ያለ ውጤት እየተገኘበት ነው። በሳይንስና ቴክኖሎጂ መስክም ቢሆን እንደ ሀገር ወጣቶች የፈጠራ አቅማቸውን አውጥተው እንዲጠቀሙ፤ እንደ ሀገርም ከዲጂታሉ ዓለም ጋር ለመራመድና ከትሩፋቱም ለመቋደስ ያስቻለ አቅም ተፈጥሯል፡፡
በቱሪዝም መስኩ የተከናወኑ እና እየተከናወኑ ያሉ ተግባራትም፤ አንድም የነበሩትን እየገለጡ በማተለቅ፤ ሁለተኛም፣ አዳዲስ የቱሪዝም አቅም የሆኑ መዳረሻዎችን በማስፋት አስደማሚ ሥራ እየተከናወነ ይገኛል። ይሄ ደግሞ የቱሪዝም መስኩን በማዘመን ኢትዮጵያ እንደ ሀገር በታሪክም፣ በባህልም፣ በእምነትም፣ በተፈጥሮም ያሏት አቅሞች ተደምረው ለገጽታዋ ብሎም ለኢኮኖሚዋም ከፍታ መሰላል እየሆናት ይገኛል፡፡
በከተማ ልማት፣ በመንገድና ሌሎች ማኅበራዊም፣ ኢኮኖሚያዊም የመሠረተ ልማት ተግባራት በኩል እየታዩ ያሉ ሥራዎችም፤ በአንድ በኩል ሰው ተኮር ናቸው። በሌላ በኩል የልማት ማሳለጫ አቅሞች ናቸው። እነዚህን ሁለት አንኳር ጉዳዮች ተሳስረው የሚገለጡባቸው እነዚህ የልማት ተግባራት ታዲያ፤ ኢትዮጵያ ከትናንቱ ዛሬን ልቃ እንድትታይ አስችለዋታል። ፈጣን የሆነው የዕድገትና የልማት ግስጋሴዋም ለሌሎች የመነሳሳት ምንጭና፣ ተምሳሌትም እንድትሆን አድርገዋታል፡፡
ከሰሞኑም የፓን አፍሪካ ወጣት አመራሮች ጉባዔን ለመታደም አዲስ አበባ የተገኙ የአሕጉሪቱ ወጣት አመራሮች እና የዘርፉ ሚኒስትሮች ያረጋገጡትም ይሄንኑ ነው። ተሳታፊዎቹ በአዲስ አበባ ያሉትን የልማት ሥራዎች ከተመለከቱ በኋላ፤ ኢትዮጵያ እያስመዘገበች ባለው ፈጣን የልማት እንቅስቃሴ መደመማቸውንም፤ ይሄንኑ ልምድ ወስደው በሀገራቸው እንዲተገበር የመሥራት መነሳሳትን የፈጠረላቸው መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
በተለይ ኢትዮጵያ ባለፉት ጥቂት የለውጥ ዓመታት ያከናወቻቸው ተግባራት፤ እንደ ሀገር ታላቅነትና የነፃነት አብነትነቷን የሚመጥኑ፤ በሌላ በኩልም የአፍሪካ መዲናነቷን፣ የዓለም አቀፍ የዲፕሎማሲ ማዕከልነቷን በሚመጥን መልኩ እንድትታይ ያስቻሏት ናቸው። ምክንያቱም እነዚህ ተግባራት እንደ ሀገር ልማቷን ከማፋጠን ባሻገር፤ የቱሪዝምና የዓለም አቀፍ ኮንፍረንስ ማዕከልነቷን የሚያሳድጉ ናቸው። ይሄ ደግሞ ቀርበው ለጎበኙ ሁሉ መደመምን፣ መነሳሳትና በራስ ሀገር ለመተግበር ልምድን የሚቀምሩበት ሆኗል!
አዲስ ዘመን መጋቢት 30 ቀን 2017 ዓ.ም