
የአረንጓዴ ኢኮኖሚ፣ የአካባቢ ጥበቃና የተፈጥሮ ሀብት መንከባከብ ሥራ በሀገሪቱ የተፈጠረውን የመንግሥት ለውጥ ተከትሎ ትልቅ ትኩረት ተሰጥቶት በመሥራት ላይ ይገኛል። ቀደም ባሉት ዘመናት ኢትዮጵያ ከአጠቃላይ ምድራዊ ስፋቷ 60 በመቶ በደን ሀብት የተሸፈነ እንደነበር ታሪክ ያስረዳል። ይሁን እንጂ በሂደት የአካባቢ ጥበቃና የተፈጥሮ ሀብት ሥራ ከቁብ የሚቆጠር ስላልነበረ በሰው ሠራሽና በሌሎች ምክንያት የደን ሽፋኑ ወደ ሦስት በመቶ አሽቆልቁሎ እንደነበር ይታወሳል። ይሄም ለሀገሪቱ የአየር ንብረት መዛባት የራሱን አስተዋጽኦ አድርጓል። ለአፈር መከላት እና ለምነት መቀነስ፤ ለዱር እንስሳት መሰደድ ተጠቃሽ ምክንያት ሆኖ ነበር።
ሆኖም ግን ከለውጡ መንግሥት ጋር ተያይዞ ለአረንጓዴ ዐሻራ መርሀ ግብር በተሰጠው ልዩ ትኩረት የደን ሀብቱን የማልማትና ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር ኢኮኖሚን መገንባት ትልቅ ትኩረት ተሰጥቶታል። እስካሁን በተሠራው ሥራም የደን ሽፋኑን ከነበረበት ሦስት በመቶ ወደ 17 በመቶ ከፍ ማድረግ ተችሏል። ይሄ ውጤት ዝም ብሎ የመጣ አይደለም። በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አነሳሽነት፣ ክትትልና ድጋፍ በሁለት ምዕራፍ ተከፍሎ በተሠራው የአረንጓዴ ልማት መርሀግብር የተገኘው ውጤት ነው።
ከ2011ዓ.ም ጀምሮ በስድስት ዙር የአረንጓዴ ዐሻራ መርሀግብር በመላው ሀገሪቱ ተካሂዷል። የመጀመሪያው ምዕራፍ በ2011 ዓ.ም ክረምት ተጀምሮ የተጠናቀቀው በ2015 ዓ.ም ነው። በዚህ ምዕራፍ አራት ቢሊዮን ችግኞችን ለመትከል ግብ ተቀምጦ የነበረ ቢሆንም በአፈጻጸም ከዕቅድ በላይ ማሳካት ተችሏል። በወቅቱ በአንድ ጀምበር 200 ሚሊዮን ችግኞች የመትከል ዕቅድ ተይዞ በቀን ከ300 ሚሊዮን በላይ ችግኞች በመትከል በዓለም የክብር መዝገብ ለመመዝገብ በቅቷል። ይሄ ዓለምን ያስደነቀ ኢትዮጵያውያንን ያኮራና በቀጣይ በተከታታይ ለሚኖረው የአረንጓዴ ዐሻራ መርሀ ግብር ስንቅ ሆኖ ያለፈ ነበር። በየዓመቱም የሚተከለውን የችግኝ መጠን በቁጥር በማሳደግ እና የተክሎችን አይነት በማስፋት ጭምር ተጠናክሮ ቀጥሏል። በዚሁ መሠረትም በመጀመሪያው ምዕራፍ 25 ቢሊዮን ችግኞች ተተክሏል።
በአረንጓዴ ዐሻራ ልማት እየተመናመኑ የመጡት ለመድሃኒትነት የሚያገለግሉ እና ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ያላቸው ሀገር በቀል እጽዋቶች ልዩ ትኩረት ያገኙ ሲሆን ከተተከለው መካከልም 52 በመቶ የጥምር ደን እርሻ፣ የፍራፍሬ እና የእንስሳት መኖ የሚውሉ ናቸው። የፅድቀት መጠናቸው ደግሞ ከ80 በመቶ በላይ ተሻግሯል።
ሁለተኛው ምዕራፍ ባሳለፍነው ዓመት እጅግ አስደሳች በሆነ መልኩ የተካሄደ ሲሆን ዘንድሮም ሰባተኛውን ዙር ለማካሄድ ከዘር ማሰባሰብ እና ችግኝ ከማፍላት ጀምሮ ሰፊ የዝግጅት ሥራ እየተሠራ ነው። በ2017 ዓ.ም ሰባት ነጥብ አምስት ቢሊዮን ችግኝ ለመትከል ለተያዘው እቅድ እስካሁን አራት ነጥብ ሰባት ቢሊዮን ችግኝ መዘጋጀቱን የኢትዮጵያ ደን ልማት አስታውቋል። 441 ሺህ ሄክታር የችግኝ መትከያ ቦታ መለየቱም ታውቋል።
የአረንጓዴ ዐሻራ ልማቱ ከመጀመሩ በፊት በሀገር አቀፍ ደረጃ ከ45 ሺህ ችግኝ ጣቢያዎች ብቻ ነበሩ። ሆኖም ለዘርፉ በተሰጠው ልዩ ትኩረት ባለፉት ስድስት ዓመታት የችግኝ ጣቢያዎች ቁጥር ከእጥፍ በላይ አድጓል። አሁን ላይም ችግኙ እየተፈላ ያለውም ከ120 ሺህ በላይ በሆኑ የችግኝ ጣቢያዎች ላይ ነው።
የአረንጓዴ ዐሻራ ልማቱ መልከምድሩን በደን ከመሸፈን (ከደን ማገገም)፤ ለምግብነት ከመዋሉ በተጨማሪ የአፈር መከላትን በመከላከል ፤ ለምነቱን በመመለስ ትልቅ አስተዋጽኦ እያደረገ ነው ። ከዚሁ ጎን ለጎንም ባለፉት ስድስት ዓመት ለአንድ ነጥብ ሶስት ሚሊዮን ዜጎች ገቢ ማግኛ የሥራ እድል ፈጥሯል። ችግኝ በማፍላት፣ ችግኝ በመሸጥ፣ የተተከሉትን በመንከባከብ እንዲሁም በለሙ አካባቢዎች በንብ ማነብና በመሳሰሉት ተሰማርተው ገቢ ወደ ማመንጨት ተሸጋግረዋል። ይህም የምግብ ዋስትናን እና የሕዝብን ተጠቃሚነት በሚያረጋግጥ፣ የካርቦን ፋይናንስ ገቢን በሚያሳድግና የአፍሪካ 2063 አጀንዳ ስኬትን በሚያግዝ መልኩ እየተተገበረ ይገኛል። ኢትዮጵያ እያከናወነች ያለችው የአረንጓዴ ዐሻራ መርሀ-ግብር አህጉራዊ የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ሥርዓትን ለመገንባት ጉልህ አስተዋጽኦ የሚያበረክት ነው። ይሄ የአረንጓዴ ዐሻራ ኢኒሼቲቭ የሀገራችንን የነገ ዕጣ ፈንታ የሚወስን፣ ጊዜውን የሚዋጅ በመሆኑ ለተግባራዊነቱ ሁሉም ሊተባበር ይገባል። ለሰባተኛው የአረንጓዴ ልማት መርሀ ግብር ከወዲሁ መዘጋጀት ይጠበቅብናል። ባለፉት ዓመታት በተሠራው ሥራ የተገኘውን ውጤት በየዘርፉ እያጣጣምነው ስለሆነ ለቀጣይነቱ መበርታት ያስፈልጋል!
አዲስ ዘመን እሁድ መጋቢት 28 ቀን 2017 ዓ.ም