
ሕይወት ሸክላ ናት። አንድም ድንገት ከዓለም እጅ አምልጣና ከምድር የሞት ወለል ላይ ተጋጭታ የምትሰበር ናት። ሁለትም ደግሞ፤ እሷም እንደ ሸክላ ስሪቷ ከአፈር ነውና ድንገት ብን ብላ አፈር መግባቷ ነው። “ሰው ክፉም ሠራ ደግም ሠራ፤ ይቀመጥለታል” ሲባል በሕይወት እስካሉ ድረስ ብቻም አይደለም። የሠሩት ከሞት በኋላም እንደሆነው ሆኖ ቁጭ ይላል። ብል አይበላውም። አይበሰብስም። ከእነዚህ ታሪክና ባለታሪኮች መካከልም አንዷ የሸዋሉል መንግሥቱ ናት። የሸዋሉል ግን ማን ናት?
ተቀጣጥለው እንደ ዓባይ ጅረት የሚርመሰመሱ ስንኞች ስምና ዝናዋን ተሸክመው ወደሩቅ ዘመን ይነጉዳሉ። የፈጠረቻቸው ዜማዎቿ ከላይ ተንሳፈውና ሌላ ጊዜም ተንጣለው በፍሰታቸው ቀልብ እየማረኩ በስሜት የሚያፈዙም ናቸው። የሸዋሉል ሕይወቷ የጥበብ፣ እጇ የብዕር ነው። እዚህም ሆነ እዚያም ጋር ሆና ከእጇ ብዕር አይታጣም። ቲያትሮችን ትጽፋለች። ድራማዎችን በውስጧ እያብሰለሰለች፣ የሃሳብ ጋራ ሸንተረሩን ትምሳለች። በዚያን ጊዜ፤ ምናልባትም በጣት ከሚቆጠሩ የሴት ጸሀፊ ተውኔት መካከል አንዷ ናት። አንዷ ብቻ ሳትሆን እንደ እንዝርት የምትሾር ምርጧ የጥበብ ደም ግባት ናት። በውበቷ ጥበብን የምታቆነጅ ሳምራ ናት። ግን ይህቺው የጥበብ እሳት የለበሰች ሱላማጢስ፤ ሳትጠግብና ሳትጠገብ፣ ገና በ32 ዓመቷ ሞት መዳፏን አነበበው። ለራሱ ተመኛትናም ከሕይወት ዙፋን ላይ አወረዳት። ጠልፎም ወሰዳት።
የሸዋሉልን ልጅነት ፍለጋ ከወጣን፤ ይዞን ወደ ምሥራቅ ሐረርጌ ይፈሳል። የኤጀርሳ ጎሮ አየር ጠረኗን አይዘነጋውም። ሳቂታዋን ተጫዋቿን፣ ምስሏን ይዟል። ስሟን እንኳ ለዘለዓለም አይረሳውም። በ1937ዓ.ም ተወልዳ እትብቷ የተቀበረው በዚህ ሥፍራ ነው። ጥበብ ጽጌረዳ አበባዋን የተከለችው ከዚያ እትብቷ ከተቀበረበት አፈር ላይ ነው። ትንሽዋ የሸዋሉል ግን ለእናቷ አንድ ብቻዋን የነበረች ምስኪን ናት። እናቷም ከዓይን ብሌናቸው በላይ የሚጠብቋትና የሚሳሱላት ልጃቸው ነበረች።
ልጅነቷን አከራካሪ ያደረገው አንዱ ስሟ ነው። “የሸዋሉል” ብሎ ያውም የሴት ስም በዚያን ዘመን አይታወቅም፤ አይጠራበትም የሚል ክርክር ያላቸው አንዳንዶች አሉ። የነገሩ እውነት ቢሸተን ለዚህ አንዱን ባለማህደር ዋቢ ላድርግ። የብዙ የሀገራችንን ታላላቅ የሀገር ባለውለታና ዝነኞችን ታሪክ በመጽሐፍ መልክ በማሳተም ታሪካቸውን የሚሰንደው “ተወዳጅ ሚዲያና ኮምኒኬሽን” የተሰኘ ማህደረኛ፣ በቅርቡ ለማሳተም በተዘጋጀው ሁለተኛ መጽሐፉ ላይ የሸዋሉልን የሕይወት ታሪክ የሚያካትት መሆኑን በመግለጽ፣ ልጅነቷን አስመልክቶ፤ ፍሬደሪክ ማርቴል የተባለን አንድ የፈረንሳይ ተመራማሪን ዋቢ ይጠቅሳል።
ፈረንሳዊው ተመራማሪ ፍሬደሪክ ማርቴል፤ የሸዋሉልን ታሪክ ለማወቅ በትውልድ መንደሯ ጭምር ሰፊ ጥናትና ምርምር ያደረገ ሰው ነው። ስለ ልጅነቷ ባሰፈረው ታሪኳ ውስጥ የስሟ ስያሜ እንዴት የሸዋሉል ሊሆን እንደቻለ ምክንያቱን ይናገራል። እንዳልነው የሸዋሉል ለእናቷ አንድ ብቻ ነበረች። ጉዳዩ ያለው ግን አንድ ብቻ በመሆኗ ሳይሆን እናትየው ልጅ አግኝተው ለመሳም የቻሉት በ46 ዓመታቸው መሆኑ ነው። እስከዚያ ዕድሜ ድረስ እናት፤ ባል ቢኖራቸውም ልጅ ለመውለድ ግን ሳይታደሉ ቆዩ። የደረቀውን አጥንት የሚያለመልም ፈጣሪም ፀሎታቸውን ሰምቶ፤ ለሳራ ይስሐቅን እንደሰጠው ሁሉ ለእሳቸውም የሸዋሉልን ሰጣቸው። በ46 ዓመታቸው ድንቡሽቡሽ ከረሜላ ልጅ ቢያገኙም ስሟን “የሸዋልዑል” ሲሉ ሰየሙላት። በኋላ ላይም የስሟን አጻጻፍ “የሸዋሉል” ያደረገችውም ራሷ ስለመሆኗ ፍሬደሪክ ጠቅሶታል።
የሸዋሉል በተአምር የተገኘች ናትና ፈጣሪም ብትሆን ጥበብ አንዳቸውም እንደ ብዙሃኑ ባክና እንድትቀር አልፈለጉም። በተአምር መፈጠሯን በተአምር ማሳየት ነበረባትና ገና በልጅነት ጥበብ ለብሳ ወጣች። በዘመኑ ለሴቷ ቀርቶ ለወንዱ እንኳን፤ ተማሪ ቤት ቤተ መንግሥቱ ነው። ተማሪ ሆኖ ትምህርት ቤት ለመግባት መቻል፣ ሥልጣን አግኝቶ ቤተ መንግሥት ከመግባት አያንስም። የሸዋሉል ግን ስትወለድም በተአምር ነውና አሁንም በተአምሩ ተማሪ ለመሆን በቃች።
በትውልድ ቀዬዋ ኤጀርሳ ጎሮ ውስጥ ትምህርት ቤት የነበረ መሆኑ ደግሞ እርሱም ሌላ…የሸዋሉል ግን ገና በትንሽነቷ የተለየች ነበረች። ቅልጥፍናዋ የአካል ብቻ ሳይሆን የአዕምሮም ጭምር ነው። የልጅ አዋቂነቷ ገና ከፊደል ተራ ሳትወጣ ምጡቅ ያደርጋታል። ፈጣሪ ሲፈጥራት፣ ያጎደለባት ምንስ ይሆን ተብሎና ተፈልጎ፤ የሚገኝባት ምንም ያለ አትመስልም። እግዜር በውጫዊ መልኳ ከመጠበቡም፤ ውስጣዊ ሥብዕናዋንም ሞርዶ የላካት ነው የምትመስለው።
ትንሿ የእሳት ነበልባል፣ የውስጧ የጥበብ ብልጭታ ብው! ብሎ መግነጢሳዊ በሚመስል መልኩ የወጣው ገና በስምንት ዓመቷ ነበር። ከየትና እንዴት እንደተማረችው ባይታወቅም፣ የሸዋሉል በዚያ ዕድሜዋ ጥበብን ትከትብ ነበር። ፊደልን ከፊደል አዋቅራ፣ ቃላትን ከቃል አዋዳ፣ ስንኞችን ከስንኝ አጋምዳ ግጥሞችን ትጽፍ ነበር። እኩዮቿ በእቃቃ ጨዋታ ላይ እየተወኑ፣ ስለምኑም ምንም ጥበብ ሳይገባቸው ልጅነታቸውን ሲቦርቁበት፣ የሸዋሉል ግን በምናብ ከገጸ ባህሪያት ጋር ማውራት ጀምራ ነበር። ታሪክና ሴራ እየከሰተች ድራማና ቲያትር በመጻፍ ላይ ነበረች። ዕድሉን ያገኙ አቻዎቿ ብዕር ይዘው፣ እየተወላገዱ ከሚያስቸግሯቸው ፊደላት ጋር ሲታገሉና ሀሁ አቡጊዳ ሲቆጥሩ፤ እርሷ ግን የደራሲነት ማዕረግ ላይ ደርሳለች። የመንደሯ ትንሽ ኮከብ ለሀገሩ ጨረቃ ልትሆን ተነሳች። ጥበብ የእውነትም ልዕልት አድርጋ አቆመቻት። ግንባሯን ስማም ወደ ዙፋኑ ሸኘቻት።
ከዕለታት በአንዱ ቀን በሕይወት ሳለች መቼም የማትዘነጋው አጋጣሚ ተፈጠረ። በጊዜው የሸዋሉል የ8 ዓመት ልጅ ነበረች። ጃንሆይም ከስደት መልስ የትውልድ ቀያቸው ናፍቋቸው ይሁን ወደዚያው አቀኑ። ታዲያ የጃንሆይ የትውልድ ቀዬ የነበረችው ደግሞ ያቺው የሐረርጌዋ ኤጀርሳ ጎሮ፣ የሸዋሉል መንደር ነበረች። ጃንሆይ ከዚያው ደርሰው ጉብኝታቸውን ማድረግ ጀመሩ። ከዝግጅቶቹ መካከል አንዱ በሆነው ዝግጅት ላይም ሀገሬው ሁሉ ከአንድ ስፍራ ላይ ሰብሰብ ብሎ፣ ንጉሡም ቦታቸውን ይዘዋል። በዚህ መሃል በእጇ ወረቀት ይዛ ግጥም ለማንበብ ወደፊት የወጣችው የስምንት ዓመቷ የሸዋሉል ነበረች። ወደፊት ስትወጣ እየተመለከቱ ጃንሆይም ፈገግ ብለው በአግራሞት ስታነብ ድምጽዋን ለመስማት በጉጉት የተጠባበቁ ይመስለኛል። የሸዋሉል ግጥሟን አንብባ ስትጨርስ አንጀታቸውን አራሰችውና ጃንሆይ 50 ብር አውጥተው ሸለሟት።
የሸዋሉልን ዳግም የገለጠው ታሪካዊ መጀመሪያ “የእዮብ ትዕግስት” ነበር። ያውም ጣፋጩ ትዕግስት። እንደ ሳንድዊች የሚገመጥ የድርሰት ሥራዋ ነው። ታዲያ ይህን ፈትል ፈትላና ደውራ፣ ውብ የሆነውን የጥበብ ሸማ ሠርታ ስታወጣ ዕድሜዋ 10 ብቻ ነበር። ያቺ የጃንሆይ 50 ብር ውስጧን ለኩሶ የባሰችው ነበልባል ሳያደርጋት አልቀረም። በወቅቱ ለዚህ ሥራዋ ድራማ አሊያም ቲያትር ትበለው ባይታወቅም፣ አንዳች ክብረ ወሰን የሰበረችበት እንደሆን ግን ጠረጥራለሁ። ቢሆንም ግን፤ ለዚህ ሥራዋ ቀን የወጣለት፣ ለእርሷም ታላቁ ብርሃን የበራላት ከትባ ካኖረችው ከ9 ዓመታት በኋላ ነበር።
ያኔ የሸዋሉል የ19 ዓመት ኮረዳ ነበረች። በፊትም ሆነ አሁን ግን መጻፏን አላቆመችም። የብዕሯ ዝናብ አባርቶ አያውቅም። የመጀመሪያው ድርሰቷም ልክ እንደ ርዕሱ ሁሉ “የእዮብ ትዕግስት” የሚያስብል ነው። ለዘጠኝ ዓመታት ሁሉ ሳትደክምና ሳትሰለች በክብር ማኖር መቻሏ፣ ምን ያህል ነገን እየተመለከተች እንደነበር የሚያሳይ ነው። በ9ኛው ዓመት የበራው ብርሃን በቀጥታ ወደ ኢትዮጵያ ሬዲዮ አደረሰው። በየት በኩል አድርጎ እንዴት እንደደረሰ እርግጠኛ ሆኖ የሚያወራው ባይኖርም፤ ብቻ ግን በሰፊው ሕዝብ ሬዲዮ ሊደመጥ ሆነ። ከዚያ በፊት ግን ድርሰቱ ማሻሻያ ተደርጎበታል። በልጅነት ያውም በ10 ዓመቷ የጻፈችው ነውና ዳግም መሞረዱ የማይቀር ነበር። ከዚያ በኋላ ነበር፤ “የቲያትር ጊዜ” በሚል መሰናዶ ከሞገዱ ጋር እየተወነጨፈ መደመጡ።
የሐረርጌዋ ልዕልት በዕድሜ ላይ ዕድሜ እየጨመረች፣ በታሪክ ላይ ታሪክ እየሠራች፣ ከጥበብ ወደ ጥበብ መዝለሏን ቀጠለች። ትንሿ የእሳት ነበልባል እንደ ወፍ በራ በሙዚቃ የወይን ዛፍ ላይ አረፈች። ይሄኔ የወፍ ጎጆ ቀልሳ፣ ጥበብ ቤቷን ሠራች። በዚያች ሰዓት፣ እዚያች የወይን ዛፍ ላይ በጥበብ ጎጆ ያውም በሙዚቃ ጎጆ ውስጥ ይኖሩ እነማንስ ነበሩ…ስንቶቹስ ይሆኑ ከቅርንጫፎቹ ላይ ቁጭ ብለው የሙዚቃን ቀመር ሲቀምሩ የነበሩ…ለትናንትናዋ የሸዋሉል ግን ማጨብጨብ ዛሬም ነው። ትናንትና ላይ ባንመለከታትም፣ ግጥሟን ስታነብ ባንሰማትም፣ በትናንትና ውስጥ ስናስባት ላለማጨብጨብ እጃችን ለመንቀጥቀጥ አይቻለውም። ከፊላው ስር፣ ከወይኑ ዛፍ በላይ ቁጭ ብላ “ወይ ዮቢ ዮቢ” ስትል ግጥም ገጥማ ለሙዚቃዊ የዜማ እንጉርጉሮ አሰበችው። ይህንን ሙዚቃም በሌላኛው የሐረርጌው ድምጸ መረዋ፤ ዓሊ ቢራ ሲስረቀረቅበት አድምጠነዋል።
እርሷ ግጥም ጽፋ፣ ዜማ ደርሳ ያቀበለቻቸው እጅግ በርካቶች ናቸው። ብዙዎቹ የሚገረሙባት የተዋጣላቸው ሥራዎችን ለመሥራት በመቻሏ ብቻ አይደለም፤ ስለ ፍቅር በምትሠራቸው ሥራዎቿ ውስጥ፣ ሴት ሆና ወንዱን ሙዚቀኛ ስታዘፍን፤ የመላውን ወንድ የልብ ትርታና ስሜት ጥንቅቅ አድርጋ በመረዳት ነው። ሴት ሆና ለወንድ የሚሆነውን ግጥም ስትጽፍ፣ በዚህን ያህል የመረዳት ደረጃ ውስጥ መሆኗ ያስገርማቸዋል። የሸዋሉል ግን ሁሌም ያለማቋረጥ እንደጻፈች ነው።
ለዓሊ ቢራ ከመጀመሪያው በተጨማሪ “አዋሽ” የሚለውን የሠራችው እርሷ ናት። ለዘመኑ የሴት ፈርጥ አስናቀች ወርቁ ደግሞ “እህ ልበል” እና “ሰላ በልልኝ” የሚሉትን ሸክፋላታለች። ከሁሉም በላይ የምትወደስበት ሥራዋ ደግሞ በ1969ዓ.ም የወጣው የሙሉቀን መለሰ አልበም ነው። አልበሙ 10 ሙዚቃዎችን የያዘ ሲሆን፤ አሥሩም የሸዋሉል መንግሥቱ ሥራዎች ናቸው።
በሙዚቃ ሥራዋ የነበራት ችሎታ እስከ ጥላሁን ገሠሰ ደርሷል። “አካም ነጉማ” የሚለውን ሙዚቃ ግጥምና ዜማ አሳምራ የሠራችው የሐረርጌዋ ሰንፔር፣ የሸዋሉል መንግሥቱ ናት። “ኦሆሆ! ገዳማይ” በትዝታው ንጉሥ ማህሙድ አህመድ ድምጽ ሲደመጥ ውብ አድርጋ ላዘጋጀችው የሸዋሉል ክብርና አድናቆታችን ይጨምራል። ከዚህ ሥራ ባሻገርም “ስደተኛሽ ነኝ” እና “አታውሩልኝ ሌላ” የተሰኙትን በግጥም፣ “አሸወይና” ለሚለው ደግሞ በዜማ ያዚያዜመችው እርሷው ናት። የሠራችውን ያህል ባይወራላትም፣ ከዳህላክ ባንድ እስከ ታንጎ ሙዚቃ ቤት፣ ከጀማሪ እስከ አንጋፋ ድምጻውያን ድረስ ዐሻራዋ ያላረፈበት የለም።
አብዛኛውን ጊዜዋን ያሳለፈችው በሐረርጌ ፖሊስ ማስታወቂያ ክፍል፣ በየሁለት ወሩ የሚታተመውን “የምሥራቅ በረኛ” መጽሔትን በማዘጋጀት ነው። ለሐረር ምሥራቃዊ ሰጎን ኦርኬስትራም በርካታ ግጥምና ዜማዎችን፣ ቲያትሮችንም ትጽፍ ነበር። ከቲያትሮቿ መካከል “ሰው መልዓክ ሆነ እንዴ?” የሚለውን ሥራዋ አይረሴና በብዙዎች አዕምሮ የቀረ ትውስታ ነው። “ሙዚቃ ዘሐረር” በተሰኘ መጽሔት ላይ በአዘጋጅነት ትሠራ ነበር። ወዲህ ደግሞ ከሐረርጌ እየተወነጨፈች ለኢትዮጵያ ሬዲዮ በወሬ አቀባይነት ትሠራ ነበር፤ ለዚሁ የአዲስ ዘመን ጋዜጣም ጽሁፎቿን ታቀብልም ነበር።
ስለ የሸዋሉል ለመከተብ ሳስብ አንድ ነገር ብልጭ አለብኝ…ይኸውም ከወራት በፊት የ1960ዎቹን የአዲስ ዘመን ጋዜጦች ሳገላብጥ ድንገት “የሸዋሉል መንግሥቱ ዜማና ግጥም በመድረስ ለዘፋኞች አበረክታለሁ ይላሉ” የሚል ርዕስ አነበብኩ። በወቅቱ ስሟን ብቻ የማውቃትን የሸዋሉልን ጽሁፍ ጋዜጣው ላይ በመመልከቴ፣ ከመገረምና ከማንበብ የዘለለ ሃሳብ አልመጣልኝም ነበር። ለተንኮሉ ደግሞ፤ በሌላ ጊዜ መልሼ እነዛኑ ጋዜጦች ባስስ ባገላብጥ ጽሁፉ እምጥ ይግባ ስምጥ ለማግኘት ሳልችል ቀረሁ። ሌሎችም አይጠፉም ብዬ አሰሳዬን ስቀጥል ግን፤ በ1962ዓ.ም ጋዜጣ ላይ “ሴቶች ብሄራዊ ስሜት ይኑራቸው” የሚል ጽሁፏን አገኘሁት። ይህ ጽሁፍም የሸዋሉል ለጋዜጣው ከላከቻቸው ጽሁፎች መካከል አንደኛው ነበር።
እሷ ግን ደራሲም ነበረች። “እስከመቼ ወንደላጤ” የሚል ርዕስ የያዘ መጽሐፏን፤ ከሞቷ ጥቂት ዓመታት ቀደም ብሎ፣ የሰንፔር አበባዋ የተቀመጠችበት ሸክላ ከመሰበሩ 3 ዓመታትን ቀድሞ ለማሳተም ቻለች። በ1968ዓ.ም የደራሲነቷ ማህተብ ያረፈበት ይህ መጽሐፍ ለንባብ በቃ። በጊዜው ብዙ የተነበበ መጽሐፍ እንደነበረም የሚያስታውሱት ያስታውሱታል። ከላይ ዋቢ አድርገነው የነበረው ተወዳጅ ሚዲያ፤ ስለ መጽሐፏ የአንባቢያን አቀባበል ሲናገር፣ እንዲያውም በወቅቱ አነጋጋሪ መጽሐፍ ነበር ይለዋል። ለዚህ ምክንያቱ፤ ያነሳቻቸው ሃሳቦችና ጭብጦች “ተዳፍኖ ይብሰል” የሚባሉ ዓይነት አይነኬ ርዕሰ ጉዳዮች በመሆናቸው ነው። እርሷ ግን ብዕሯን ፈርጠም አድርጋ በሙሉ ነጻነቷ ውስጥ ሆና ጻፈችው።
የሸዋሉል ከሐረርጌ ሆና በጥበብ አዲስ አበባ ስትወነጨፍ፣ ሥራዎቿም መላውን ኢትዮጵያ ከጫፍ ጫፍ ሲያካልል ነበር። በአንድ ወቅት ግን አዲስ አበባ ውስጥ ተቀምጣ ለመሥራት ችላለች። በዚህ ጊዜም በኢትዮጵያ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ውስጥ ዜና አንባቢ ሆና በድምጽዋ ከሞገዱ በላይ ስታነሆልል ነበር። አዘጋጅ ሆናም ከፊት ታይታለች። ሳታበቃ ደግሞ እንደገና የሬዲዮ ድራማዎችን በመጻፍ በብዕሯ ጥበብን ስትፈለቅቅ ነበር። እንግዲህ ይህችው የሸዋሉል ነበረች ለሕይወቷ መቀጨት፣ ለሸክላው ሕይወት መሰበር ጦስ የሆናትን የፖለቲካ በር ማንኳኳቷ። ፖለቲካው በጦዘበት ሰሞን ላይ፣ በደርግ መንግሥት የአንድ ቀበሌ ሊቀመንበር አደረጋት። የከፋው ነገር ደግሞ፤ ከውስጥ የመኢሶን አባል መሆኗ ነው። በፖለቲካው የተለኮሰ የእሳት ብልጭታ ለሕይወቷ የሰደድ እሳት ሆነ። እንደ አብዛኛው ሁሉ፣ የፖለቲካው ወላፈን ዳፋው ለእርሷም ጭምር ነበር። በ1969ዓ.ም በግንቦት ወር ላይ እሳቱ ሰንፔሯን አበባ አነደዳት።
እርሷ እየነደደች የዚያን ሰሞን ሥራዋ ግን ከፍ ብሎ ሲደመጥና ስታደምጠው የነበረው፤ በዚያው 1969ዓ.ም የወጣውን የሙሉቀን መለሰን አልበም ነበር። በአልበሙ የካሴት ሽፋን ላይም የሸዋሉል እንዲህ ስትል የሚከተሉትን ቃላት አስፍራበታለች፤ “ሕይወት ሞት፣ ኀዘን፣ ደስታ፣ ፍቅር፣ ጠብ፣ ትዝታ፣ ሰላም፣ ጦርነት፣ ትግል እና ድል ብሎም ዓለም ሁለንተናዋ ይስበኛል። ዜማ እንድደርስ ግጥም እንድጽፍ ይጋብዘኛል። ስለሆነም እኔና ብዕሬ የትም መቼም ከሰፊው ሕዝብ ጋር ነን” የሚሉ ቃላት…
ሙሉጌታ ብርሃኑ
አዲስ ዘመን የካቲት 30 ቀን 2017 ዓ.ም