የተፈጥሮ ጸጋዎችን ለግብርናው በተቀረጹ ኢኒሼቲቮች

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በግብርናው ዘርፍ እየተደረገ ያለው እንቅስቃሴ በርካታ ውጤቶች እንዲመዘገቡ አስችሏል። መንግሥት ለዘርፉ ሥራ ስኬታማነት አስፈላጊና ወሳኝ የሚባሉ ፖሊሲ እና ስትራቴጂንም ቅርጾ ወደ ትግበራ በማስገባት፣ የተለያዩ ኢኒሼቲቮችንም በመተግበርና በርካታ ድጋፎችንም በማድረግ ያከናወናቸው እነዚህ ተግባሮች የዘርፉ ምርትና ምርታማነት እየጨመረ እንዲመጣ እያደረጉ ናቸው።

ለዘርፉ ውጤታማነት አስተዋጽኦ ከሚያደርጉ ወሳኝ ጉዳዮች መካከል ሰላም አንዱ ነው። አስተማማኝ ሰላም ለግብርናው ዘርፍ ወሳኝ ነው። የቱንም ያህል ፖሊሲ፣ ስትራቴጂ፣ ወዘተ ተቀርጾ ቢተገበር፣ ድጋፍ ቢደረግ አስተማማኝ ሰላም ከሌለ የሚፈለገው ውጤታማነት እውን ሊሆን አይችልም።

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት በሁለተኛ ምዕራፍ የመጀመሪያው ዙር የ”ስለኢትዮጵያ” መርሃ ግብሩ “ሰላም እና ኢኮኖሚ” በሚል ርዕሰ ጉዳይ በቅርቡ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ቡታጅራ ከተማ ባዘጋጀው መድረክ ላይ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ የጀርባ አጥንት በሆነው የግብርና ዘርፍ ላይ የመነሻ ጽሑፍ ያቀረቡት የግብርና ሚኒስትር ዴኤታው ፍቅሩ ረጋሳ (ዶ/ር) በግብርናው ዘርፍ እየተከናወነ ስላለው ተግባር፣ ስለዘርፉ እምቅ አቅሞች እንዲሁም ሰላም ለዘርፉ ባለው ፋይዳና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ላይ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

ሚኒስትር ዴኤታው እንዳሉት፤ ኢትዮጵያ ብዙ የሰብል አይነቶችን ማምረት የሚያስችላት የተፈጥሮ ጸጋ እንዲሁም እንስሳትን ለማርባት የሚያስፈልጉ ምቹ ሁኔታዎች አሏት። እነዚህ ጸጋዎች ደግሞ ተፈጥሮ የለገሰቻቸው ስጦታዎች ናቸው።

‹‹ይህን የተፈጥሮ ጸጋ በጸጋነቱ ብቻ ለረጅም ጊዜያት ስናየው መቆየታችንና ሳንሰራበት ጊዜያችንን በከንቱ ማሳለፋችን ይታወሳል›› ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው፣ ከለውጡ ወዲህ ግን በተፈጥሮ የተቸርነውን ጸጋ በትኩረት በመከታተልና በሚገባው መንገድ በማልማት የሀገርን የኢኮኖሚ እድገት ማላቅ እንደሚቻል በተጨባጭ ማሳየት እየተቻለ መጥቷል ይላሉ።

ሚኒስትር ዴኤታው፤ የሀገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያውን ዋቢ አድርገው እንዳሉትም፣ ግብርናው የሀገሪቱ አንደኛው የኢኮኖሚ መሰረት ሆኖ ለሌሎች ዘርፎችም ግብዓት እንዲሆን እና ኢኮኖሚውን ተሸክሞ እንዲሔድ በትኩረት እየተሠራበት ይገኛል።

ያም በመሆኑ ግብርናው ለኢትዮጵያ ኢኮኖሚ አንድ ሶስተኛ አስተዋጽኦ እያደረገ ነው። ከ75 በመቶ በላይ ለሚሆነው የኅብረተሰብ ክፍል ደግሞ የሥራ እድልም ይፈጥራል።

ይህን ግብርና በተለመደው መንገድ መቀየር እንደማይቻል አስታውቀው፣ ወደ 130 ሚሊዮን የሚጠጋውን ሕዝብ መመገብ፣ የምግብ እና ሥነ ዋስትናን ማረጋገጥ፤ በሚፈለገውም ልክ ኢኮኖሚውን መደገፍ እንደማይቻል አስታውቀዋል። በዘርፉ ለውጥ ለማምጣት ለየት ባለ መንገድ ስትራቴጂዎች ተቀርጸው ወደ ትግበራ መገባቱንም አመልክተው፣ በዘርፉም የሚመለከታቸው አካላት ሁሉ እየተሳተፉ እንደሚገኙም ተናግረዋል።

ለችግሮቻችን በአጭር ጊዜ መፍትሔ ሊያስገኙ በሚችሉ ለየት ያሉ የተፈጥሮ ጸጋዎች ላይ ትኩረት ሰጥቶ መሥራት ይገባል ሲሉም ጠቁመው፣ መሠራት የሚገባቸውን ሥራዎችንም እንዲሁ በመለየት በኢንሼቲቭ መልክ እንደየአካባቢው ሁኔታ ጸጋው ታይቶ እንዲሠራ በመንግሥትም በሕዝብም ርብርብ እየተደረገ መሆኑን አመልክተዋል።

ይህን ተከትሎም አመርቂ ውጤቶች ማምጣት እየተቻለ መሆኑን ጠቅሰው፣ ውጤቶቹ ለምግብና ስነ ምግብ ዋስትና መጠበቅ ትልቅ አስተዋጽኦ እያደረጉ መሆናቸው የአደባባይ ምስጢር ነው ብለዋል። ከዚህ አኳያ ታሪክን የቀየሩ ሥራዎች እንዳሉ ገልጸዋል።

ሚኒስትር ዴኤታው እንዳስታወቁት፤ በሀገሪቱ ከታዩት ለውጦች መካከል የሀገሪቱ የግብርና ሥራ ባህል እየተሻሻለ መምጣቱ በዋናነት ሊጠቀስ ይገባዋል። ከዚህ በፊት አርብቶ እና አርሶ አደሮች በዓመት አንዴ ብቻ በማረስ ሌላውን ጊዜያቸውን ረብ በሌለው ነገር ሲያሳልፉ ነበሩ። ይህ ሁኔታ በቂ ምርት እንዳይመረት ምክንያት ሆኖ ኖሯል።

አሁን ሁሉም እንደሚያውቀው የመኸር እርሻ አለ። መኸር እንደተሰበሰበ ወዲያው የበጋ እርሻ ይተካል፤ እሱ እንደተሰበሰበ የበልግ እርሻ ይከተላል ሲሉም የግብርናው ሥራ ምን ያህል ለውጥ እንደመጣበት አመላክተዋል። ስለዚህ የግብርናውን ዘርፍ የሥራ ባህል በማሻሻል ባመጣው ለውጥ በዓመት በትንሹ ሶስት ጊዜ ማምረት የሚያስችል ሁኔታ መፍጠር መቻሉን ጠቅሰዋል።

ዶክተር ፍቅሩ እንዳብራሩት፤ በዚሁ አግባብ በመሬት ልማት ሽፋንም ለውጥ ተመዝግቧል፤ አስርና አስራ አምስት ሚሊዮን ሔክታር መሬት አካባቢ የነበረው የለማ መሬት፣ ዘንድሮ ወደ 30 ነጥብ አምስት ሚሊዮን ሔክታር ማድረስ ተችሏል። ምርታማነቱም እንዲሁ በዚያው ልክ እድገት አምጥቶ ወደ አንድ ነጥበ አራት ቢሊዮን ኩንታል የማምረት ደረጃ ላይ ተደርሷል።

የሥራ ባህል መቀየሩ፣ የሚታረስ መሬት ሽፋን መጨመሩ በዚያው ልክ ምርታማነት እየጨመረ እንዲመጣ አስችለዋል፤ ይህ ትልቅ ድል ነው ብሎ መናገር ይቻላል።

ቀደም ሲል የማይታወቁና የማይሠሩ ሥራዎች እና የማይለሙ አንዳንድ ቦታዎችም ነበሩ፤ እነዚህ ቦታዎችና ሥራዎች በአሁኑ ጊዜ ወደ ሥራ እንዲገቡ ተደርገዋል።

ከዚህ ቀደም ስንዴ ይመረት የነበረው በደጋ እና የወይና ደጋ የአየር ጸባይ ባለባቸው አካባቢዎች ላይ ብቻ ነበር። በአሁኑ ጊዜ ከዚህ በፊት ስንዴ በቅሎባቸው በማያውቁ ቦታዎች ሁሉ ስንዴ እንዲለማ እየተደረገ ነው፤ ይህ የሆነው መሬቱ እንዲታረስ እንዲሁም ሕዝቡ እሱን ባህል አድርጎ እንዲሠራ በመደረጉ ነው፤ ይህን መሬት ወደ ሰብል ልማት ማስገባት መቻሉ ቀላል የሚባል ለውጥ አይደለም።

የሩዝ ምርትን ለአብነት ጠቅሰው ሚኒስትር ዴኤታው ሲያብራሩ እንደተናገሩት፣ ኢትዮጵያ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ መቶ በመቶ በሚያስብል ደረጃ የሩዝ ምርትን በምግብነት ስትጠቀም የነበረው ከውጭ በማስገባት ነው። በአሁኑ ጊዜ በሀገሪቱ በሩዝ ምርት ላይ በእጅጉ አመርቂ የሚባል እድገት እየታየ ነው። በአጭር ጊዜ ውስጥም በሩዝ ምርት ሀገሪቱ ራሷን እንድትችል ለማድረግ እየተሠራ ነው። ወደ አንድ ነጥብ ሁለት ሚሊዮን ሔክታር በሚጠጋ መሬት ላይ ሩዝ እንዲለማ ለማድረግ ጥረት እየተደረገ ይገኛል።

በአርብቶ አደሩ አካባቢ ብዙም የሰብል ልማት በማይታወቅባቸው አካባቢዎች የሩዝ እና ስንዴ ልማት እየተካሄደ ነው። በዚህም አርብቶ አደሩ ወደሰብል እርሻ ገብቶ ምርታማነትንም በማሳደግ ላይ ይገኛል።

ቀደም ሲል አንዱ ጥሮ ግሮ፤ ሌላው ጠብቆ የሚኖርበት ሁኔታ ፣ አንዳንዶች በአንድ የግብርና ሥራ ብቻ ተሰማርተው የሚያመርቱበትም ሁኔታ እንደነበር አስታውሰው፣ በአሁኑ ጊዜ ይሄ ሁሉ እየተቀየረ መምጣቱን ገልጸዋል። የተለያየ የሰብል አይነት እንዲያለሙ እየተደረገ መሆኑን አመልክተዋል።

እነዚህ ሁሉ ግብርናው በእድገት ጎዳና ላይ ያለ ስለመሆኑ ማሳያዎች መሆናቸውን ጠቅሰው፤ ይህም በዘርፉ ትልቅ ስኬት እየተመዘገበ ነው ብሎ መናገር እንደሚያስችል አስታውቀዋል።

‹‹ግብርናው ያመጣውን ለውጥ ስመለከት ለዘመናት በተለያዩ መዝገበ ቃላት ስማችን በረሃብ ሲጠቀስ መኖሩ ያስቆጫል። በሰፊው አምርተን ለሌሎችም ሀገራት ጭምር መትረፍ ስንችል፣ በአየር ንብረት ለውጥ፣ በተለያዩ ግጭቶች ምክንያት የድርቅ አደጋ ሲመላለስብን ቆይቷል። በዓለም አቀፍ ደረጃም በርዳታ ጠባቂነት እንታወቅም ነበር›› ሲሉ አስታውቀዋል።

ዛሬ ሀገሪቱ በምግብ ራሷን በመቻል ስንዴን ለዘመናት ከውጭ ስታስገባ የነበረበትን ሁኔታ ማስቆም ችላለች ሲሉም አስታውቀው፤ ከዚህም አልፋ ስንዴ ለውጪ ገበያ ማቅረብ ውስጥ ገብታለች፤ ይህ ትልቅ ድል ነው ብለዋል። ሀገሪቱ ታሪክ የሚቀይር ሥራ እየሠራች ትገኛለች። ይህ የሥራ ውጤት የመጣው ግን በአንድ ሰው አሊያም በአንድ ሴክተር ሥራ ብቻ አይደለም፤ በመላ ኢትዮጵያውያን ርብርብ ነው ሲሉም አስረድተዋል።

የምርት እድገትን ለማምጣት የሚያስፈልጉ አስቻይ ሁኔታዎች መኖራቸው እና ሀብትም መንቀሳቀስ መቻሉ ግብርናው በተሻለ ሁኔታ ላይ እንዲገኝ እንዳደረገው ሚኒስትር ዴኤታው ጠቅሰው፤ ግብርናው በተለመደው መንገድ ሳይሆን ስትራቴጂ ተቀርጾለት እንዲሠራ የተደረገበት ሁኔታም ሌላው የስኬቱ ምስጢር መሆኑን ጠቅሰዋል። ይህ የሚጀምረው ከፖሊሲ ቀረጻ ነው ብለዋል።

እንደ እሳቸው ማብራሪያ፤ ግብርና ሚኒስቴር የቀድሞውን የግብርና እና የገጠር ልማት ፖሊሲ ከልሶ ቁልፍ ቁልፍ የፖሊሲ ጉዳዮች ምንድን ናቸው? መስተካከልስ የሚገባቸው ነገሮች ምንድን ናቸው? በማለትና ከሀገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያው ጋር በማጣጣም የፖሊሲ ሪፎርም ሰርቶ በማስተዋወቅ ላይ ይገኛል። እነዚህ ፖሊሲዎች ደግሞ ለምናወጣቸው የሕግ ማሕቀፎች ድጋፍ የሚያደርጉ ናቸው።

በቅርቡም የተለያዩ አዋጆች ወጥተዋል፤ ከእነዚህ መካከል የመሬት አጠቃቀም እና አስተዳደር አዋጅ አንዱ ነው። ከተፈጥሮ ሀብታችን ይጀምራል። ይህ ብዙ ነገሮችን የሚያስተካክል ነው። መሬት ለሁሉም የማኅበረሰብ ክፍል እንዲዳረስ እና የባለቤትነት መብት እንዲኖረው የተደረገበትም ነው።

ሚኒስትር ዴኤታው እንደገለጹት፤ በሌማት ትሩፋት ኢኒሼቲቭ ባለፉት ሁለት እና ሶስት ዓመታት በርካታ ተግባራት ተከናውነዋል። ኢትዮጵያ ያላት የእንስሳት ቁጥር በአፍሪካ ደረጃ ከፊተኛው መስመር የሚያስቀምጣት ቢሆንም እስከቅርብ ጊዜ ድረስ ከዘርፉ የሚገባትን ያህል መጠቀም አልቻለችም።

በአሁኑ ጊዜ የእንስሳት ሀብቱ በሌማት ትሩፋቱ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶታል። ለዘመናት ቁጥሩን ብቻ ስንጠራ የነበረውን የእንስሳት ሀብት በዘመናዊ መልክ ማርባት እንዲቻልና እና ምርት እና ምርታማነቱ እንዲያድግ እየተደረገ ነው። በዚህም በእንስሳቱም ዘርፍ ትልቅ ለውጥ የመጣበት ሥራ ተሠርቷል።

ኢኮኖሚን ከመደገፍ አኳያም በቡና ልማት እና ኤክስፖርትም በጣም ከፍተኛ ውጤት ያለው ሥራ እየተከናወነ ይገኛል። ወደ ውጭ ከሚላክ ቡና ዘንድሮ ወደ ሁለት ቢሊዮን ዶላር ለማስገባት በትኩረት እየተሠራ ነው።

የምርት እና ምርታማነትን እድገት ለማምጣት ትልቁ እና ቁልፉ ጉዳይ የሰላም ጉዳይ ነው ሲሉም ሚኒስትር ዴኤታው አስገንዝበዋል። አምራቹ ማኅበረሰብ ከቤቱ ወጥቶ ወደ ሥራው መሔድ የሚችለው አካባቢው ሰላማዊ ሲሆን ነው ሲሉም ጠቅሰው፣ ከግብዓት አቅርቦት ጀምሮ፣ ማምረቱ እና ምርትን ወደ ገበያ መውሰዱ ሁሉ ሊከናወን የሚችለው ሰላም ሲኖር መሆኑን አጽንኦት ሰጥተው አስታውቀዋል።

ግብዓቱ ሁሉ በትክክል ጥቅም ላይ እንዲውል የሚደረገው ሰላም ሲኖር መሆኑንም ጠቅሰው፤ ‹‹ግብርናችን ለሰላማችን፤ ሰላማችን ደግሞ ለግብርናችን ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳለው በዚሁ አጋጣሚ ለመግለጽ እወዳለሁ›› ሲሉም አስገንዝበዋል።

እሳቸው እንዳስታወቁት፤ በግብርናው መስክ የተከናወነው ተግባር ብዙ ቢሆንም በዚያ በመኩራራት ራስን መገደብ አያሻም። እንዲያውም በዘርፉ ያለውን ክፍተት በመቅረፍ ረገድ ብዙ ሊሠራ ይገባል። ግብርና በሙሉ ትኩረት ሊሠራበት የሚገባ ዘርፍ መሆኑን ተገንዝቦ መሥራት እንደሚያስፈልግም ጠቅሰው፣ ይህ ካልሆነ ግን ወደኋላ ሊመለስ እንደሚችልም አስገንዝበዋል።

ግብርና አሳታፊ መሆንን የሚጠይቅ መስክ መሆኑንም ጠቅሰው፤ ቀደም ሲል አርብቶ አደሩን ቸል የማለት ነገር ይስተዋል እንደነበር አስታውሰዋል። አርብቶ አደሩን ወደ እዚህ ዘርፍ በማምጣት እየተከናወነ ያለውን ተግባር መጠናከር እንዳለበት አስገንዝበዋል። ወጣቶች፣ ሴቶች እና ሌሎቹ ዘርፉ የሚመለከታቸው አካላት እንዲሳተፉበት ማድረግ ይገባል። ይህ አይነቱ አካሔድ በከተማም በገጠሩም ተጀምሯል ብለዋል።

ከዚህ ቀደም አርሶ አደሩ በዓመት አንዴ ብቻ ካመረተ በኋላ ብዙ ጊዜውን ያባክን የነበረው በማይገባ አካሔድ ነው። ይህን ችግር ለመፍታትም በአሁኑ ወቅት ተግባራዊ በተደረጉ ኢኒሼቲቮች እንደየቦታው ሁኔታ እየታየ እየተሠራ ይገኛል። ይህን ማጠናከር የግድ እንደሚል ገልጸዋል።

ሚኒስትር ዴኤታው እንደሚሉት፤ የግብርና ሥራ ውጤቶችን ከማቀራረብ አንጻርም መሠራት አለበት፤ ከሕዝቡ ስሜት መረዳት እንደሚቻለው ከሰሜን እስከ ደቡብ እንዲሁም ከምዕራብ እስከ ምሥራቅ ሳይባል የመልማትና ራስን የመቻል ፍላጎት በሁሉም ዘንድ አለ። አመራሩ ደግሞ በእዚህ የሕዝቡ ፍላጎት መሰረት መንቀሳቀስ አለበት።

አንዱና ዋንኛው ተብሎ የተጤነው ጉዳይ ክልሎቹ ያላቸው አቅም ምንድን ነው? የሚለውን መለየትና እንደየክልሎቹ አቅም ደግሞ የግብርና ፍኖተ ካርታ ተሰርቶ ለሁሉም ክልል በሚባል ደረጃ ይፋ ማድረግ መቻሉንም አስታውቀዋል። ይህ ማለት ግን ለሁሉም ተመሳሳይ ልብስ መስፋት ሳይሆን እያንዳንዱ በራሱ አቅም እና ባለው የተፈጥሮ ጸጋ ታግዞ እንደየክልሉ የቅድሚያ ቅድሚያ መስጠት ባለባቸው ላይ ትኩረት ሰጥቶ መሠራት አለበት ማለት ነው ብለዋል።

አስቴር ኤልያስ

አዲስ ዘመን የካቲት 24 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You