ቅድመ መከላከል የሚሻው የሕፃናት የነርቭ ዘንግ ክፍተት

ያንቺ አምላክ አንማው ይባላሉ።ራቅ ካለው የሀገራችን ክፍል ደብረ ኤልያስ መጥተው ልጃቸውን ለማሳከም በዘውዲቱ ሆስፒታል በጠዋቱ ተገኝተዋል።ወገባቸውን ታጥቀው ልጃቸው እንዳይታይባቸው ሽፍንፍን አድርገው አዝለውት ወዲያና ወዲህ ሲሉ ነበር የተገናኘነው።ዓይኖቻቸው እንባ አርግዘው ሲዋከቡ ላያቸው አንዳች ነገር እንደገጠማቸው ተረዳን፤ ወደ እርሳቸው ጠጋ በማለት ‹‹እማ ምን አጥተው ነው›› አልናቸው።

ጥያቄያችን ግን ወዲያው መልስ አላገኘም።ይልቁኑ እንባቸውን መቆጣጠር አቅቷቸው ማልቀስ ጀመሩ። እንደምንም አረጋጋናቸውና የሆኑትን እንዲያጫውቱን ጠየቅናቸው። እርሳቸውም የውስጣቸውን ምንም ሳይሸሽጉ ሀሳባቸውን እንዲህ በማለት አጫወቱን።

‹‹የልጄ ነገር ሆኖብኝ ብዙ ቦታ ተንከራተትኩ፤ ከሀገር ሀገር አቋርጬም ሄድሁ።ዛሬም የሪፈር ወረቀቴን ይዤ ዘውዲቱ ሆስፒታል ተገኘሁ። ነገር ግን ሕክምናውም ለልጄ መፍትሔ ሳይሰጠው እንክርቱ አደከመኝ። በዚህም ልጄ አይድንልኝ ብዬ ስለሰጋሁ ውስጤ አዝኖ ነው ያስጨነኳችሁ። በዚያ ላይ የማርፍበት ቦታና ዘመድ የለኝም። ሆስፒታሉ ባይተባበረኝ ልጄም ሆነ እኔ መኖር አንችልም ነበር። የልጄ ምርመራ ቢጀመርም ተኝቶ መታከሚያ አልጋ አለማግኘቱም እንዲሁ ጭንቀቴን አበዛው›› አሉን።

እኛም እንዴት ወደዚህ መጡ፤ በቅርብ ርቀት ሕክምናው አይሰጥም ነበር፤ ልጅዎ ያጋጠመውን ሕመም ምን እንደሆነ እንዴት አወቁ ስንልም ሌሎች ጥያቄዎችን አከልን። እርሳቸው ሁኔታውን በዝርዝር ማስረዳቱን ቀጠሉ ‹‹የልጄን ሕመም ከዓመት በኋላ ነው የተረዳሁት።እስከ ሦስት ወሩ ድረስ ምልክት አላየሁም። የጭንቅላቱ እብጠት በየጊዜው እየጨመረ ሲሄድም ይድናል ብዬ ዝም አልኩት። ነገሩ ግን በጣም ከባድ ነበርና ሊሻለው አልቻለም። ስለዚህም ቅርብ ጤና ጣቢያ መሄድ እንዳለብኝ ወሰንኩ፤ አደረኩትም።

የቅርብ የጤና ክትትሉ ግን መፍትሔ አልባ ነበረ። ስለዚህ ከብዙ ድካም በኋላ ወደ ዘውዲቱ ሆስፒታል ሪፈር ተባልኩ። እዚህም መጣሁ።ግን እስከአሁን ለውጡን አላየሁትም። መቼም ቢሆን ግን ተስፋ አልቆርጥም። በቅርቡ ልጄ እንደ እድሜ እኩዮቹ ሆኖ ይጫወታል። ለዚህ ደግሞ የተቻለኝን ሁሉ አደርግለታለሁ›› ሲሉም መፍትሔ ለማግኘት የተጓዙትን ርቀትና የወሰዱትን መፍትሔ አጫወቱን፤ እኛም ብርታቱን እንዲሰጣቸው ተመኝተንላቸው ‹‹ልጅዎን ፈጣሪ ይማርልዎት›› ብለን ተሰናበትናቸው።

ልክ እንደ ያንቺአምላክ ሁሉ ለልጇ ሕክምና መጥታ ያገኘናት ሌላኛዋ ባለታሪካችን ወጣት ማርታ አሰፋ ነች። እርሷም ‹‹የልጅ ሕመም አያድርስ›› ትላለች የገጠማትን ፈተና እያጫወተችን። በተለይም ሕመም እንደሆኑ የማይታወቁ በሽታዎች በልጅ ላይ ሲደርስ ያለው ስቃይ በቀላሉ የሚወጡት ዓይነት እንዳልሆነ ካጋጠማት በመነሳት ታስረዳለች።

ወጣት ማርታ እንደምትለው፤ የልጇ ችግር መታወቅ የነበረበት ሦስት ወር ላይ ቢሆንም ክትትል ያደረገችበት ጤና ተቋም ግን ችግሩን ተረድቶ አልነገራትም። ስለሁኔታው የተረዳችው ዘጠነኛው ወሯ ላይ ነው።ይህ ጊዜ ደግሞ ከወለደች በኋላ በሕክምኗ ልጇ እንዲረዳ ከማድረግ በስተቀር ምንም ማድረግ የምትችልበት አልነበረም።

ልጇ ሲወለድ የወገብ ክፍተት፤ የጭንቅላት ውሃ መጨመር ሕመምና የልብ ችግር ገጥሞታል። በዚህ ምክንያት በእያንዳንዱ እንቅስቃሴዋ ውስጥ የልጇ ሕክምና ቅድሚያ የመስጠት ግዴታ ውስጥ ገብታለች። ችግሩ የገጠማትና መፍትሔ ማግኘት የጀመረችው ከዛሬ አምስት ዓመት በፊት ቢሆንም ሙሉ ለሙሉ እስኪያገግም በየስድስት ወሩ እየመጣች ያለበትን ሁኔታ ታረጋግጣለች።

የልጇን ተደራራቢ ችግር ያዩ ሰዎች ‹‹ምንም አታስነካኪው የበለጠ ይታመምብሻል›› ሲሉ ይመክሯት የነበረችው ማርታ፤ ዛሬ ልጇ የዊልቸር ተጠቃሚ ሆኖ በራሱ እንዲንቀሳቀስ ማድረግ የቻለችው ወገቡንና ጭንቅላቱን የሚያገናኝ ቱቦ እንዲገጠምለት ስለፈቀደች እንደሆነ ትናገራለች። ያ ባይሆን በትንሹ ጭንቅላቱ አብጦ ለሚያየው ሁሉ የአዕምሮ ጫና እንደሚፈጥር ታስታውሳለች።

ማርታ ከዚህ ውሳኔዋ ጋር በተያያዘ ለእናቶች ‹‹በልጃቸው መቼም ተስፋ ሊቆርጡ አይገባቸውም። የሕክምና አማራጮችን በሙሉ መጠቀም አለባቸው። አሁን ላይ በመንግሥት ደረጃ እየተወሰዱ ያሉ መፍትሔዎች ይበልጥ አጋዥ ናቸው።ወጪ ቀንሰው ችግርን ስለሚያቃልሉ መፍትሔ ይሰጣሉ›› የሚል መልዕክት ታስተላልፋለች።

ወጣት ማርታ መንግሥት እያመቻቸ ካለው መፍትሔ ጋር ያነሳችው ከአዲሱ የዘውዲቱ ሆስፒታል ‹‹የሕጻናት የነርቭና ኅብለሰረሰር ቀዶ ሕክምና የልህቀት ማዕከል›› ጋር የተያያዘው ነው። እርሷ ከአራት ዓመት በፊት ወደ ዘውዲቱ ሆስፒታል ስትመጣ በዚህ ችግር ውስጥ ያሉ ሕጻናት በርካታ ናቸው። ወላጆቻቸው ማረፊያም፤ መቀመጫም አልነበራቸውም። ስለዚህም ቅድሚያ የሚያገኘው ችግሮቹ ተደራራቢ የሆነበት ሕጻን ብቻ ነው።ዛሬ ግን ሕክምናው በቅርብ ባሉ ሆስፒታሎች ሁሉ በመጀመሩ ወረፋው እምብዛም ነው።

መሰል የልህቀት ማዕከላት መስፋታቸው ደግሞ ትንንሾቹን ችግሮች ለሌሎች የሕክምና ጣቢያዎች በመተው ከባዱ ችግር ላይ ትኩረት እንዲደረግ ያግዛል፤ ብዙ ሕጻናትንም ማትረፍ ይቻላል። ለእናቶችም ተስፋ ነው።በተጨማሪም ለእናቶች የሚሰጡ ቅድመ ጥንቃቄን የተመለከቱ ሥልጠናዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ ያስችላል። የወጣት ማርታ ቤተሰቦች ለልጇ ያላቸው አመለካከትና እንክብካቤ ከፍ እንዲል የሆነው በዚህ ምክንያት መሆኑንም ታነሳለች።

ስለ ሕመሙና ሕክምናው ጠቅለል ያለ መረጃ የሰጡን ደግሞ ዶክተር ዮርዳኖስ አሻግሬ ናቸው። ዶክተር ዮርዳኖስ በዘውዲቱ ሆስፒታል የኒዮ ሰርጀሪ ዩኒት ኃላፊ ሲሆኑ፤ የነርቭና ሕብለሰረሰር ሕመምን በቀዶ ሕክምና መፍትሔ እየሰጡ ይገኛሉ።

እርሳቸው እንደሚሉት፤ ይህ ሕመም የነርቭ ዘንግ ክፍተት (Neural Tube Defect) ይባላል።በአብዛኛው ሕፃናትን የሚያጠቃ ነው።የሚከሰተው ደግሞ ከላይኛው የአዕምሮ ክፍል እስከ ታችኛው ህብለሰረሰር ድረስ ሲሆን፤ የነርቭ ዘንግና መሸፈኛው የአፈጣጠር ችግር ሲገጥመው ነው።

በሽታ እንደ የዓለም ጤና ድርጅት ግምት በየዓመቱ እስከ 300ሺህ በሚደርሱ ሕፃናት ላይ ሞትና ጉዳትን ያስከትላል።በሀገራችንም እንዲሁ ከ10ሺህ በላይ ሕጻናት የችግሩ ሰለባ ይሆናሉ።ችግሩ በእርግዝና እና በወሊድ ወቅት (የፅንስ አፈጣጠር ጋር) ተያይዘው የሚመጣ ሲሆን፤ ሕመሙ ከፍ ሲልም እስከ ካንሰር የአንጎል፤ የጀርባ አጥንት ካንሰር፤ ዕጢ፤ ነርቮች ላይ የሚደርሱ አደጋዎች ጋር ይያያዛል።

የነርቭ ዘንግ ክፍተት ችግር ብዙ ጊዜ በኢኮኖሚያቸው ዝቅተኛ የሆኑ ሀገራት ላይ ይፈጠራል።ምክንያቱ ደግሞ በምግብ ውስጥ የፎሊክ አሲድ እጥረት ማጋጠም ነው።በዚህ ችግር ሳቢያ 85 በመቶ የሚሆነው ዜጋ በበሽታው እንዲጠቃ ይሆናል። ይህ ችግር አንዳንድ ጊዜ የሚጥል በሽታ ባለባትና መድኃኒት በምትወስድ እናት አማካኝነት ልጆች ችግሩ እንዲያጋጥማቸው ይሆናሉ።እናትየዋ ከፍተኛ የሆነ የሰውነት ሙቀት የሚያመጡ ኢንፌክሽኖች ካሉባትም እንዲህ አይነት ችግር ሊከሰትና በጣም በጥቂቱ ደግሞ በተፈጥሮ የሚመጣም የነርቭ ዘንግ ክፍተት ችግር ሊፈጠር እንደሚችል ዶክተር ዮርዳኖስ ይናገራሉ።

የነርቭ ዘንግ ክፍተት ጀርባ ላይ የሚፈጠር እብጠትንና ጀርባ ላይ ክፍተትን ልናይበት የምንችለው ሕመም ነው። ጀርባቸው ላይ ያሉ ችግሮች ሲከብዱ ደግሞ በአብዛኛው የአንጎል ላይ ውሃ መጠራቀም (hydrocephalus) ይከሰታል። ምክንያቱም ቱቦዎቹ በመዘጋታቸው የተነሳ ውሃው አንጎል ላይ ይጠራቀማል። በእርግጥ የአንጎል ላይ ውሃ መጠራቀም መነሻ ይህ ብቻ አይደለም። የአንጎል ላይ ዕጢ፤ ኢንፌክሽን፤ ቲቪና የመሳሰሉት ተያያዥ ችግሮች በሽታውን ሊፈጥሩት ይችላሉ ሲሉ ያስረዳሉ።

የነርቭ ዘንግ ክፍተት ተጠቂ የሆኑ ሕጻናት የአንጎል ላይ ውሃ መጠራቀም፤ የመንቀሳቀስ እክል፤ የስሜት ማጣት፤ የአዕምሮ ውስንነት፣ ሽንት እና ሰገራ የመቆጣጠር ችግር ሊያጋጥማቸው ይችላል። ይህንን ችግር ለማከም ደግሞ ከፍተኛ የሆነ ወጪ ይጠይቃል። በተጨማሪም የብዙ አካላትን ርብርብ ይፈልጋል። በዚህም ዘውዲቱ ሆስፒታል ለ13 ዓመት ያህል ሲሠራ ቆይቷል። ዋነኛ መፍትሔ ግን ሕክምናው ሳይሆን መከላከል ላይ በስፋት መሥራቱ ነው።

ቀድሞ በመከላከል 85 በመቶ ያህሉን ዜጋ ከዚህ ችግር መታደግ ይቻላል። ለዚህም ነፍሰጡር እናቶች የፎሊክ አሲድን እንዲወስዱ ማድረግ ያስፈልጋል።አንዲት እናት ቅድመ እርግዝና ክትትል በማድረግ ከመጀመሪያው የእርግዝና ቀን ጀምሮ ለሦስት ወር የፎሊክ አሲድ እንክብሎችን መውሰድ ይኖርባታል። በተለይም ከዚህ በፊት ተመሳሳይ ችግር ያለው ሕፃን የወለደች እናት በፎሊክ አሲድ የበለፀጉ ምግቦችን መውሰድ የግድ ይላታል።

በቅርቡ የፀደቀው ‹‹ዱቄት ውስጥ ፎሊክ አሲድ መጨመር አለበት›› የሚለው ሕግ ብዙ ለውጥን እንደሚያመጣ የሚያምኑት ዶክተር ዮርዳኖስ፤ ,ቀስ እየተባለ በጨው ውስጥም እንደሁኔታው ይህ ነገር የሚጨመርበት ዕድል ይፈጠራል የሚለውን ሀሳብም ይደግፋሉ። ምክንያቱም ይህንን ማድረግ ዜጎችን ከዚህ በሽታ ሰለባነት ማውጣት ነው ብለው ስለሚያስቡ ነው።

ዶክተር ዮርዳኖስ ሌላኛው የመከላከል ዘዴ እንደሆነ የጠቆሙት፤ በእርግዝና ወራት ችግሩ መኖሩንና አለመኖሩን የማወቅና ለቀጣይ ሕክምናዎች ቤተሰቡን ማዘጋጀት ላይ መሥራትን ነው። ከዚያ ሕክምና ወሳኝ መሆኑን አምነው ክትትል ማድረግ ይጠበቃል ይላሉ።

ሕክምናው የተለያዩ አማራጮች ያሉት ነው።ሆድ ውስጥ እያሉ ጭምር መፍትሔ የሚሰጥበትም ነው።ለአብነት የሽንት መሽናት ችግር፤ የእግር ድክመትና መሰል ነገሮች ሲኖሩ በቀዶ ሕክምና መሥራት ስለማይቻል የሽንት መሽናት ችግሩ ሌላ ተጓዳኝ ችግር እንዳይፈጥር ይታከማል። የእግር ድክመቱን ደግሞ እግር እንዳይቆስል፤ እንዳይጣመምና ተጨማሪ ችግሮች እንዳይፈጥር ማድረግ ላይ ትኩረት አድርጎ ሕክምና ይሰጣል።

የአንጎል ላይ ውሃ መጠራቀም ችግርን በተመለከተ ደግሞ ልጆቹ ምንም ዓይነት ምልክት ሳያሳዩ ከነርቭ ዘንግ ክፍተቱ በተሻለ መልኩ ሕክምና ይሰጥበታል።ይህም በሁለት መልኩ ነው። ቱቦ በማስገባትና አንጎላቸው ውስጥ ውሃ የሚተላለፍበት ቀዳዳ ሠርቶ በማከም ነው ይላሉ።አሁን እየተፈጠሩ ያሉ መልካም አጋጣሚዎች ደግሞ ለዚህ ጥሩ መደላደል እንደሆነ ያነሳሉ።

ሆስፒታሉ ከአምስት ዓመት በፊት ከሁሉም ክልል ሕሙማንን ይቀበላል። በዚህም ጥራት ያለው አገልግሎት መስጠት ያዳግታል። ሕጻናቱንም በጊዜውና በሚፈለገው ደረጃ አክሞ ወደቤታቸው ለመሸኘት ፈተና ይሆናል። በኢኮኖሚያቸው ዝቅተኛ የሆኑ ዜጎች ስለሚበዙም ብዙ ችግሮቻቸውን ለመመለስ ይከብዳል። መድኃኒትን ጨምሮ በሆስፒታሉ ሠራተኞች እንዲሸፈንም ያስገድዳል። አሁን ግን ሕክምናው በቅርበት ከመሰጠቱ አንጻር፤ ዘውዲቱ ሆስፒታልም አዲስ የልህቀት ማዕከል ከመክፈቱ ጋር ተያይዞ ብዙ ለውጦች እየታዩ እንደመጡ ዶክተር ዮርዳኖስ ነግረውናል።

የሰው መጨናነቅ በመቀነሱ የልሕቀት ማዕከሉን ጨምሮ ከቀላሉ ችግር ይልቅ ውስብስብ ኬዞች እንዲታዩበት ዕድል ሰጥቷል።ባለፉት ሦስት ዓመታት ከ25 እስከ 30 ሕጻናትን በወር ቀዶ ሕክምና ይደረግ የነበረውንም ቀንሶታል። የአልጋ ቁጥር፤ የአስታማሚ መቀመጫ እጥረትን የመሳሰሉ ችግሮች መፍትሔ እንዲያገኙ ሆነዋል። ውስብስብና በጣም ያልተስተካከለ የአሠራር ሥርዓቱም በአዲሱ የልህቀት ማዕከል አማካኝነት ተፈቷል። ምክንያቱም በማዕከሉ ውስጥ የአንድን ሰው የሕክምና መብት ተጠብቆ፤ ግርግሩን ቀንሶ ተገቢውንና ጥራት ያለው ሕክምና እንዲሰጥ ዕድል ተፈጥሯል ሲሉ ያስረዳሉ።

የሕጻናት የአንጎል ካንሰር፤ ዕጢና ተጓዳኝነት ያላቸውን በሽታዎችን በቀዶ ሕክምና ለማከም የሚያስችል የራሱ የሆነ ክፍል አልነበረውም። አሁን ግን አዲስ የተከፈተ የልሕቀት ማዕከል በመኖሩ ይህንን ሥራ በስፋት ለማከናወን ያስችላል። ማዕከሉ የወላጆችንም ሆነ የልጆችን ደስታ ከፍ ከማድረግም በላይ ከሀገር ወጥተው የሚንከራተቱና ለከፍተኛ ወጪ የሚዳረጉትን ከመቀነስ አንጻር የማይተካ ሚና ይኖረዋል ይላሉ።

ማዕከሉ 3ነጥብ 2 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ወጥቶበት ሲሠራ ሀገር እንደ ‹‹ሪች አናዘር ፋውንዴሽን›› አይነት በየዘርፉ ተሳታፊ የሚሆኑ ደጋፊና ፈቃደኛ የሆኑ አካላት እንደሚያስፈልጓት የሚነግረን ነው። በእነርሱ እገዛ የጤና ዘርፉን አንድ ርምጃ ከፍ ማድረግ ይቻላል። ስለሆነም ይህ ተሞክሮ በሌሎችም ዘርፎች ሊወሰድ ይገባል። መንግሥትም እንዲህ አይነት ዕድሎች ሲመጡ ጠቀሜታውን ተረድቶ ወደ ተግባር መቀየሩ ላይ በትኩረት ሊሠራ ያስፈልጋል። እንዲህ አይነት ድጋፍ ለሚያደርጉ አካላትም ምስጋና መቸር ይገባል ሲሉ ሀሳባቸውን ሰጥተዋል።

ጽጌረዳ ጫንያለው

አዲስ ዘመን ቅዳሜ የካቲት 22 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You