የግብርናውን ዘርፍ ለማዘመን ተስፋ የተጣለበት የልህቀት ማዕከል

ኢትዮጵያ ምንም እንኳን ከ80 በመቶ በላይ የሚሆነው ሕዝቧ መተዳደሪያ የግብርና ዘርፍ ቢሆንም፤ ሰፊ የሚታረስ መሬት ቢኖራትም፣ የግብርና ሥርዓቱን ካለዘመኑ፣ በዝናብና በበሬ ላይ ጥገኛ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ምርትና ምርታማነትን በሚገባው ልክ ማሳደግ ሳይቻል ቆይቷል፡፡ ይህ ለሀገሪቱ ምጣኔ ሀብት ቁልፍ ሚና እየተጫወተ የኖረ ዘርፍ ምርታማ እንዲሆን የተለያዩ ጥረቶች ሲደረጉ ቆይተዋል፡፡ ይህን ተከትሎም ለውጦችም ሲመዘገቡ ኖረዋል፡፡ ይሁንና ለውጡ የሚፈለገውን ያህል አልነበረም፡፡ ለእዚህ ምክንያቱ ደግሞ ዘርፉ በቴክኖሎጂ የተደገፈ አለመሆኑ ነው፡፡

መንግሥት ይህን ሁኔታ ለመቀየር ከለውጡ ማግስት ጀምሮ ላለፉት ስድስት ዓመታት በሜካናይዜሽን የሚደገፍ የግብርና ሥርዓት ለመፍጠር ጥረት እያደረገ ይገኛል። በተለይም የኩታ ገጠም እርሻ እንዲስፋፋ በማድረግ አርሶአደሩ ዘመናዊ የግብርና መሣሪያዎችን በጋራ እንዲጠቀምና ምርታማነቱን እንዲያጐለብት እየተደረገ ባለው ርብርብ አበረታች ውጤቶች እየተመዘገቡ መሆናቸው ይታወቃል፡፡ ለዚህም በዋናነት አብነት ተደርጎ የሚጠቀሰው የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት ሲሆን፣ በዚህም በአጭር ጊዜ ውስጥ ሀገሪቱን ከስንዴ ተረጂነት ወደ ላኪነት በማሳደግ ከፍተኛ የሚባል እምርታ እንድታስመዘግብ ማድረግ ተችሏል፡፡ ይህ እውን የሆነው ዘመናዊ አሠራር እንዲተገበር በመደረጉ ነው፡፡

ሜካናይዜሽን የሚጠቀም ግብርናን ለመፍጠር እየተከናወነ ባለው ተግባር መንግሥት ትልቁን ሚና ሲጫወት ቆይቷል፤ ከዚህ በተጓዳኝም የተለያዩ ሀገራትና የልማት አጋር ድርጅቶች ድጋፍ በእዚህ ሥራ ውስጥ ሊጠቀስ የሚገባው ነው፡፡ እነዚህ አካላት ቴክኖሎጂዎችን በማምጣትና የእውቀት ሽግግር በማድረግ በዘርፉ ብዙ እየተሠሩ ይገኛሉ፡፡

ከእነዚህም አካላት ሥራዎች መካከል አንዱ በደቡብ ኮሪያ መንግሥት ድጋፍ ተገንብቶ በቅርቡ የተመረቀው በኢትዮጵያ የመጀመሪያ የሆነው የግብርና ሜካናይዜሽን የልህቀት ማዕከል ነው፡፡ ይህ ማዕከል በሰባት ወራት ውስጥ ነው የተገነባው፡፡

በማዕከሉም የግብርና ሜካናይዜሽን ማሽነሪዎች ፍተሻ፣ ቁጥጥር፣ ምርምር እና የጥገና ሥራዎች የሚከናወኑ ሲሆን፣ በተጨማሪም በዘርፉ የሠለጠነ የሰው ኃይል ለማፍራት የተለያዩ ሙያዊ ሥልጠናዎችም የሚሰጡበት መሆኑን በምረቃ ሥርዓቱ ላይ ተገልጿል፡፡

የግብርና ሚኒስትሩ ግርማ አመንቴ (ዶ/ር) በወቅቱ እንደገለፁት፤ በግብርና ዘርፉ ላይ መዋቅራዊ ሽግግር ለማምጣት ልዩ ትኩረት ከሚሹ ጉዳዮች አንዱ በሬና ገበሬ የሚለውን አስተሳሰብና ትርክት መቀየር ነው። ይህ ትርክት ካልተቀየረ ግብርናን ማዘመን የሚታሰብ አይደለም፡፡ ከዚህ አንፃር የለውጡ መንግሥት ሥራ እንደ ጀመረ ከወሰዳቸው ርምጃዎች መካከል የሜካናይዜሽንና የመስኖ መሣሪያዎችን ከቀረጥ ነፃ እንዲገቡ ማድረጉና የፖሊሲ ለውጥ ማካሄዱ በዋናነት ይጠቀሳሉ፡፡

‹‹ከዚያ በመነሳት ባለፉት አምስት ዓመታት በትራክተር የሚታረስን መሬት እስከ አምስት ሚሊዮን ሄክታር መድረስ ችሏል›› ያሉት ሚኒስትሩ፤ ‹‹ይህ ውጤት ከተመጣበት ሁኔታ አንፃር የሚበረታታ ቢሆንም፣ ሀገሪቱ ካላት ሰፊ የሚታረስ መሬት አኳያ በቂ የሚባል አይደለም›› ብለዋል፡፡ የግብርና ሜካናይዜሽን የልህቀት ማዕከሉ መገንባት ለግብርና ሜካናይዜሽን ዘርፍ ዕድገት አዲስ ምዕራፍ እንደሚከፍት እና የሚታረሰውንም መሬት በእጥፍ ለማሳደግ የተያዘውን ሀገራዊ ግብ ለማሳካት እንደሚያግዝ አስታውቀዋል፡፡

‹‹ሜካናይዜሽን ሲባል ማሽን መግዛትና ማሰራጨት ብቻ ሳይሆን እነዚህ ማሽኖች ምንአይነት ናቸው? እንዴትስ ነው መጠቀም ያለብን?፤ ለየትኛው መሬት? የሚሉትን መለየት ነው›› የሚሉት ግርማ (ዶ/ር)፤ መንግሥት ለሀገሪቱ መልክዓ ምድር የሚሆኑትን ማሽኖች በመግዛትና በማሰራጨቱ ብቻ የሚፈለገውን ውጤት ማምጣት እንደማይቻል ይናገራሉ፡፡ በመሆኑም አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን ከማላመድ ባሻገር በራስ አቅም ወደ ማምረት መግባት አለበት የሚል አቅጣጫ ተይዞ እየተሠራ ስለመሆኑ ያብራራሉ፡፡

ማዕከሉን በደቡብ ኮሪያና በኢትዮጵያ መንግሥት ትብብር መገንባት ያስፈለገውም ይህንኑ ታሳቢ በማድረግ እንደሆነ ያመለክታሉ፡፡ ‹‹ኢትዮጵያ ማሽን እያስገባች ብቻ ልማቷን ማፋጠን አትችልም፤ ለዚህም ነው በአሁኑ ወቅት ቴክኒክና ሙያ ማዕከሎቻችን ተንቃሳቃሽ ትራክተሮችን እንዲያመርቱ ጥረት እየተደረገ ያለው›› ሲሉ ይጠቅሳሉ፡፡

የልህቀት ማዕከሉም ከውጭ ተገዝተው የሚመጡትን ብቻ ሳይሆን ሀገር ውስጥ የሚሠሩትንም ማሽኖች ጥራትንና ደረጃን የጠበቁ መሆናቸውን ይፈትሻል፤ ያሰራጫል ይላሉ፡፡ በተጨማሪም ሀገሪቱም የራሷ የሆነ ደረጃና ተስማሚነት ምዘና ሥርዓት እንዲኖራት የሚያስችላት መሆኑንም ነው ግርማ (ዶ/ር) የጠቀሱት፡፡

በሌላ በኩል እስከ ዛሬ ድረስ ማሽኖቹን የሚዘውሩ (ኦፕሬት የሚያደርጉ)፤ ሲበላሹ የሚጠግኑ ባለሙያዎች ባለመኖራቸው ምክንያት ከውጭ በከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ የገቡ ማሽኖች ጠጋኝና የሚዘውራቸው በቂ ባለሙያ ባለመኖሩ ያለሥራ የሚቀመጡበት ሁኔታ እንደነበር ያስታውሳሉ፡፡ ‹‹አሁን ላይ ግን ይህ ማዕከል በመገንባቱ ከክልሎች ሰዎችን አምጥተን ለማሠልጠን ያስችለናል›› ይላሉ፡፡

በክልሎች አነስተኛ የጥገና አገልግሎት መስጫ ማዕከላት አብሮ ለመገንባት በደቡብ ኮሪያ ቃል መገባቱን አስታውቀው፣ ይህም ያልተማከለ አገልግሎት ለመስጠት እንደሚያስችል ያብራራሉ፡፡

‹‹ይህ ማዕከል ኮሪያውያን ለኢትዮጵያን ያላቸውን አጋርነትና ወዳጅነት ያሳዩበት ነው›› ያሉት ግርማ (ዶ/ር)፤ ማዕከሉን መገንባት፣ እቃዎቹን ማስገባት ብቻ ሳይሆን ለአንድ ዓመት ሠልጣኞችን አብረውን አሠልጥነው አብቅተው እንደሚሄዱ ገልጸዋል፤ ይህ ሥራ እንደሀገር ራስን ችሎ ለመቆም አቅም እንደሚፈጥር ይናገራሉ፡፡

ከዚህ ባሻገርም በግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት 12 የግብርና ሜካናይዜሽን አገልግሎት ማዕከላት እየተገነቡ መሆናቸውን የጠቆሙት ሚኒስትሩ፤ ‹‹ይህም በአጠቃላይ ኢትዮጵያ ማሽኖችን ገዝታ ማስገባት ብቻ ሳይሆን ሀገር ውስጥ የማምረት፣ የማሠልጠን፣ መልሰን የመሥራት አቅም እየፈጠርን ለመሄድ ያስችለናል›› ብለዋል፡፡

በዚህ ረገድ ኮሪያውያን ከ50 ዓመት በፊት በእጅ የሚገፋ ትራክተር ሲጠቀሙ እንደነበር አስታውሰው፤ ‹‹ዛሬ ላይ የላቀ ቴክኖሎጂ ላይ ደርሰዋል፤ እኛ እነሱ የደረሱበት ለመድረስ ይህን ያህል ጊዜ ሊወስድብን አይገባም፤ ፈጥረን፣ ተምረን፤ አላምደን፣ ኮርጀንም ቢሆን ልማታችንን ማስቀጠል ይገባናል›› በማለት አስገንዝበዋል።

የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ ሶፊያ ካሣ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ማዕከሉ እንደሀገር በግብርና ሜካናይዜሽን ታሪክ የመጀመሪያው ነው፤ ይህ ማዕከል አጠቃላይ ወደ ሀገር ውስጥ የሚገቡ ማሽኖች ፍተሻ የሚካሄድበት ብቻ አይደለም፤ በጥገና ረገድ እንደ ሀገር የነበረውን ክፍተት ለመሙላት እንደሚያስችል ይናገራሉ፡፡ ‹‹ከዚህ በፊት የግብርና ሜካናይዜሽን እቃዎች በሰነድ ብቻ ነበር ወደ ሀገር ውስጥ የሚገቡት፤ አሁን ግን ይህ ማዕከል ያንን ችግር ለመቅረፍ ታሳቢ ተደርጎ ተሠርቷል›› ይላሉ፡፡

ኢትዮጵያ በርካታ የአፈር አይነት፤ ሥነ-ምሕዳር እንዳላት ጠቅሰው፣ እሱን ታሳቢ ያደረጉ የግብርና ሜካናይዜሽን ቴክኖሎጂዎችን ተደራሽ የሚደረግበትና የምርምር ሥራ የሚካሄድበት እንደሆነም ሚኒስትር ዴኤታዋ ያስረዳሉ፡፡ ‹‹የደቡብ ኮሪያ መንግሥት ለዚህ ማዕከል ግንባታና ለማሽኖች 14 ነጥብ ሰባት ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ አድርጓል፤ ድጋፍ ማድረግ ብቻ ሳይሆን በራሳቸው ነው ክትትልና ቁጥጥር አድርገው ያሠሩት›› በማለት ይጠቁማሉ፡፡ በኢትዮጵያ መንግሥት በኩልም ሼዶችን የመሥራትና ግቢውን የማሳመር ሥራ መሠራቱን ጠቅሰው፤ ማሽኖችን ከቀረጥ ነፃ እንዲገቡ በማድረግ ሀገሪቱ ለያዘችው እቅድ መሳካት ሚናውን መወጣቱን አስታውቀዋል፡፡

በኢትዮጵያ የደቡብ ኮሪያ አምባሳደር ጃንግ ካንግ በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያና ደቡብ ኮሪያ የረጅም ጊዜ የሁለትዮሽ ግንኙነት እንዳላቸው ጠቅሰው፣ የልህቀት ማዕከሉን ግንባታም በትኩረት በመሥራት በአጭር ጊዜ መጨረስ መቻሉን አመልክተዋል። ማዕከሉም ለግብርናው ዘርፍ ምርታማነት ትልቅ አበርክቶ ይኖረዋል ሲሉ ገልጸው፣ የደቡብ ኮሪያ መንግሥትና ሕዝብ ኢትዮጵያ ልማቷን ለማሳለጥ ለምታደርገው ሁለንተናዊ ጥረት እንደቀድሞው ሁሉ ድጋፋቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ አረጋግጠዋል፡፡

የኮሪያ ቴክኖሎጂ እድገት ኢንስቲትዩት (ኪያት) ጀነራል ዳይሬክተር ባይክ ሱንግጂን እንደተናገሩት፤ ሀገራቸው በጦርነት ከወደመችበት ሁኔታ ወጥታ ራሷን እንደገና ወደመገንባት የገባችው በዓለም አቀፉ ኅብረተሰብ ድጋፍ መሆኑን ጠቅሰው፣ አሁን ከ70 ዓመታት በኋላ ኮሪያ በሃን ወንዝ ላይ ተዓምር ተብላ የምትጠራና በሰሚ ኮንዳክተር፣ በአውቶሞቢሎች፣ በመርከብ ግንባታ፣ በመሳሰሉት ጠንካራ የኢንዱስትሪ መሠረት ያላት ሀገር ለመሆን መብቃቷን አስታውቀዋል፡፡ ከፍተኛ የቴክኖሎጂ ኢንዱስትሪ ኃይል ካላቸው ሀገራት መካከል ልትመደብ እንደምትችልም ገልጸው፣ ከእነዚህ የርዳታ እጆች መካከል ኢትዮጵያ ትገኝበታለች ብለዋል፡፡

‹‹አሁን ደግሞ የኮሪያ ሪፐብሊክ በኢንዱስትሪ ጠንካራ ልትሆን የቻለችበትን እውቀትና ልምድ በችግራችን ጊዜ ለረዳችን ኢትዮጵያ በማሸጋገር ያገኘነውን እርዳታ እየመለስን እንገኛለን›› ሲሉም ገልጸዋል፡፡

ጀነራል ዳይሬክተሩ እንዳስታወቁት፤ የደቡብ ኮሪያ የንግድ ኢንዱስትሪና ኢነርጂ ሚኒስቴር እና የኢንዱስትሪ ቴክኖሎጂ እድገት ኢንስቲትዩት በኢትዮጵያ የኢንዱስትሪ አቅም እድገትና ከፍተኛ እሴት ላይ በማተኮር የኢንዱስትሪና የኢነርጂ ፕሮጀክት እየሠሩ ናቸው፡፡ በኢትዮጵያ ከዚህ ፕሮጀክት በተጨማሪ ከከባቢ አየር ጋር ተስማሚ ከተማ ምሥረታ ፕሮጀክትና የጨርቃ ጨርቅ ቴክኖ-ፓርክ ፕሮጀክት እንዲሁም የውሃ አቅርቦት መሠረተ ልማትና የመሳሰሉት በርካታ ፕሮጀክቶችን በድምሩ 24 ሚሊዮን ዶላር የሚገመቱ የድጋፍ ሥራዎችን እያከናወነች ትገኛለች፡፡ ይህም ኢትዮጵያን ከአፍሪካ ሀገራት ቀዳሚዋ ከደቡብ ኮሪያ ጋር ትብብር ያላት ሀገር ያደርጋታል፡፡

እንደ እርሳቸው ማብራሪያ፤ ሁለቱ ሀገራት ባላቸው ትብብር መሠረት እ.ኤ.አ በ2021 የተጀመረው የግብርና ሜካናይዜሽን የልህቀት ማዕከል ፕሮጀክት፣ የግብርና ሜካናይዜሽንን አቅም በማጎልበትና በግብርና ማሽነሪ ምርምር ቁጥጥርና ጥገና ዘርፍ መሐንዲሶችን በማፍራት ለግብርና ማሽነሪ ኢንዱስትሪ ልማት ጉልህ ሚና ይኖረዋል፡፡ ከዚያም አልፎ በኢትዮጵያ ካሉ የደቡብ ኮሪያ ኩባንያዎች ጋር በትብብር የሚሠሩበትን ሁኔታም ይፈጠራል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

‹‹በዓለም ላይ ብዙ የግጭትና የጦርነት ዜናዎች ቢሰሙም ደቡብ ኮሪያና ኢትዮጵያ በደም የተቆራኙ በመሆናቸው እርስበርስ በመረዳዳት ወደ እድገት ጎዳና እየተራመዱ ይገኛሉ›› ሲሉ ጠቅሰው፤ ማዕከሉ የሁለቱን ሀገሮች ቀጣይነት ያለው የእርስበርስ ትብብር መጠናከር ምልክት እንደሚሆንም ይናገራሉ፡፡ ተጨማሪ ፕሮጀክቶችን በማስፋት በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን ትብብር ለማጠናከር እንደሚሠራም ጠቁመዋል፡፡

የደቡብ ኮሪያ ኢንዱስትሪ ማሽነሪ ማኅበር ምክትል ሥራ አስኪያጅ ዮን ካፕሰኦክ ‹‹ይህንን ፕሮጀክት ከኮሪያ መንግሥት በጀት በመቀበል ከ2021 ጀምሮ በኃላፊነት እየመራን እንገኛለን›› ሲሉ ጠቅሰው፣ በማዕከሉ ትራክተር፣ ዎኪንግ ትራክተርና የተለያዩ ማሽኖች እንዳሉ ተናግረዋል፡፡ ይህ ተቋም ከምርምር ባሻገር ኢትዮጵያ ውስጥ ሊሠሩ የሚችሉ የሥራ ኃይሎችን አቅም ለማሳደግ እንደሚሠራም ገልጸዋል፡፡

ማዕከሉ በሥልጠና ተቋሙ የሠለጠኑ ሰዎች በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች በመሄድ የቀሰሙትን እውቀት የበለጠ እንዲያስፋፉ እገዛ እንደሚያደርግ ያመለክታሉ። ፕሮጀክቱ የኢትዮጵያን ግብርና በማዘመን ረገድ ትልቅ ሚና ይኖረዋል ተብሎ እንደሚጠበቅም አስገንዝበዋል፡፡

ማሕሌት አብዱል

አዲስ ዘመን የካቲት 17 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You