“ወንጂ ሸዋ የዛሬ አምስት ዓመት ከስኳር ፋብሪካ በተጨማሪ ሌሎች በርካታ እህት ፋብሪካዎች ይኖሩታል” አቶ ጀማል አማን

አቶ ጀማል አማን የወንጂ ሸዋ ስኳር ፋብሪካ ዋና ሥራ አስኪያጅ

ቀዳሚና የመጀመሪያ ስኳር ፋብሪካ ነው። ግንባታና የሸንኮራ አገዳ ተክል ልማቱ፤ በአየር ፀባዩ፣ በመሬት አቀማመጡ ምቹነት ተመራጭ በሆነው፤ የወንጂ መሬት ላይ የአዋሽ ወንዝን ተንተርሶ የተገነባው ወንጂ ሸዋ ስኳር ፋብሪከ ተቀማጭነቱ ኔዘርላንድ (ሆላንድ) በሆነው አውሮፓዊ ኩባንያ ኤች.ቪ.ኤ(H.V.A)ኢንተርናሸናልና በኢትዮጵያ ንጉሠ-ነገሥት መንግሥት በአክሲዮን ድርሻ በ1946 ዓ.ም የተቋቋመ ነው።

ከዛሬ 70 ዓመት ጀምሮም ስኳርን ለሕዝብ ከማስተዋወቅ ጀምሮ ፍላጎቱን ለማሟላት በርካታ ሥራዎችን የሠራ ፋብሪካ ነው። በጊዜ ሂደት ባጋጠሙት የእርጅናና አንዳንድ ችግሮች ምክንያት ብዙ ሲፈተን እስከ መዘጋት ደርሶም ነበር።

አቶ ጀማል አማን በአሁኑ ወቅት ድርጅቱን በሥራ አስኪያጅነት እየመሩት ያሉ ናቸው። አቶ ጀማል የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን “በድራይ ላንድ ክሮፕና በሆርቲካልቸራል ሳይንስ” ከመቄሌ ዩኒቨርሲቲ አግኝተዋል ፤ ሁለተኛ ዲግሪያቸውን (Msc) “በፕላን ባዮ ቴክኖሎጂ” ከጅማ ዩኒቨርሲቲ አግኝተዋል፤ በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ መምህርና የዩኒቨርሲቲ የምርምርና ኳሊቲ አሹራንስ ሃላፊ ነበሩ፤ ትግራይ ክልል ባዮ ቴክኖሎጂን በዋና ዳይሬክተርነት መርተዋል።

ወደ ስኳር ኢንዱስትሪው ከመጡ በኋላም በኢትዮጵያ ስኳር ኮርፖሬሽን ረዳት ተመራማሪ፤ በተለይም ለስኳር ኢንዱስትሪው የሥልጠና ማዕከል በማቋቋምና በዳይሬክተርነት በመምራትም ትልቅ ዐሻራቸውን አኑረዋል። አሁን ደግሞ የወንጂ ሸዋ ስኳር ፋብሪካን ከውድቀት አንስተው በሁለት እግሩ ለማቆም ሰፊ ጥረትን እያደረጉ ነው። እኛም በፋብሪካው እየተከናወኑ ባሉ የሪፎርም ሥራዎችና ቀጣይ አቅጣጫ ዙሪያ ቆይታን አድርገናል።

አዲስ ዘመን ፦ እርስዎ ወደ ፋብሪካው ሲመጡና ሲረከቡት የነበረበት ቁመና ምን ይመስል ነበር?

አቶ ጀማል ፦ እንግዲህ ፋብሪካው የተቋቋመው በ1946 ዓ.ም ሲሆን በርካታ ታሪካዊ ሥራዎችን ሠርቷል። ለስኳር ኢንዱስትሪውም ፈር ቀዳጅ ነው። ብዙ ታሪካዊ ኩነቶች በማለፍም አሁን ላለበት ደረጃ ደርሷል፤ ይህም ቢሆን ግን በተለያዩ ወቅቶች ባጋጠሙት ችግሮች ተዳክሞ ነበር።

በተለይም እኔ ወደ ድርጅቱ አመራርነት ስመጣ 1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ኩንታል በዓመት ከማምረት አቅሙ ወደ 3 መቶ ሺ ወርዶ ነበር። ለፋብሪካው መዳከም መሠረታዊ ችግሮቹ ምንድን ናቸው? የሚለውን የመለየት ሥራ ቅድሚያ የተሰጠው ነበር።

በዚህም ስትራቴጂክ ፕላን ተዘጋጅቶ ባለሙያዎችም በጥናቱ ላይ ሰፊ ተሳትፎን እንዲያደርጉ ሆኖ ችግሮችን ወደመለየት ገባን። ካገኘናቸው ችግሮች ሰፊ የአገዳ ማሳ አለመኖሩ አንዱ ሲሆን እኛ ስንመጣ ያገኘናት 12 ሄክታር የመሬት ሽፋን ብቻ ነው። አብረውት የሚሠሩ አርሶ አደሮች ዘንድ የተነሱ ጥያቄዎች መልስ ባለማግኘታቸውም ፋብሪካውን ጥለው ሄደዋል።

ይህ ሁኔታ ደግሞ ፋብሪካው በራሱ 6 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ ብቻ ተወስኖ እንዲቀር አስገድዶት ነበር። ይህም ሁኔታ በፋብሪካው ላይ የአገዳ ምርት ማነስን እንዳስከተለ ተረዳን።

ሁለተኛው ችግር ባለው መሬትም እየተሠራ እንኳን ምርትና ምርታማነቱ ላይ በጣም ችግር ነበር። ከዚህ አንጻርም የምርትና ምርታማነት ማነቆዎች ምንድን ናቸው? ምርታማነቱስ በዚህን ያህል ደረጃ ለምን ሊወርድ ቻለ? የሚለውን ጥናት አድርገን የመለየት ሥራውንም ሠራን።

አዲስ ዘመን ፦ በጥናት ሂደታችሁ ላይ ዋና ዋና ብላችሁ የለያችኋቸው ችግሮችና የተቀመጡ የመፍትሔ አቅጣጫዎች ምን መልክ አላቸው?

አቶ ጀማል ፦ ጥናት አድርገን ችግሮቹን ከለየን በኋላ ሂደት በሂደት የመመለስ ሥራውን ጀመርን ። ፋብሪካው ከተቋቋመ 70 ዓመቱ ነው ፤ በዚህ መካከል ደግሞ በርካታ የመሠረተ ልማቶች ተጎድተዋል፤ ለረጅም ዓመታትም ምንም ዓይነት እድሳትን አግኝተውም አያውቁም። በዚህም ፋብሪካው በራሱ አቅም አንዳንዶቹንም ጨረታ በማውጣት ለመሥራት ሙከራዎችን አደረገ።

ለምሳሌ የወንጂ መሬት አነስተኛ ተዳፋትነት ያለው ከመሆኑ አንጻር የመስኖ ውሃ ከማሳው ተንጠፍጥፎ እንዲወጣ የሚያደርገው መሠረተ ልማት ተደፍኖ ነበር፤ ይህንን የመክፈት ሥራ ተሠራ፤ ሌላው ምርትና ምርታማነቱን ሊያሳድጉ የሚችሉ ግብዓቶች ላይ ያለውን ችግር ለመፍታት ከሥራ አመራር ቦርዱ ጋር በመነጋገር ማዳበሪያ የተለያዩ ኬሚካሎች በወቅቱ ቦታው ላይ እንዲቀርቡ ለማድረግ ተቻለ።

ሶስተኛው ችግርና ዋናው ደግሞ ፋብሪካው ለረጅም ዓመታት ሠራተኞቹን ረስቶ የነበረበት ሁኔታ ነው። ሠራተኞች የለመዱት በየዓመቱ እድገት፣ የደመወዝ ጭማሪና ቦነስ ለ13 ዓመታት የሰጣቸው አልነበረም ። በዚህ ምክንያት ፋብሪካው የኔ ነው የሚለው ስሜት ሙሉ በሙሉ የጠፋበት ሁኔታ ነበር።

ከዚህ አንጻር ሥራዎች ይሠሩ የነበረው በባለቤትነት ስሜት ሳይሆን አሠራር ስላለ ከተጠያቂነት ለመሸሽ ብቻ ነበር። አቅም ያላቸው ሠራተኞችም ፋብሪካውን ጥለው ወደሌሎች ለመሰደድም ተገደው ነበር። ይህ ሁሉ ሲደማመር ፋብሪካው በዓመት መሥራት የነበረበት 200 ቀናትና ከዛ በላይ ቢሆንም ይሠራ የነበረው 50 እና 60 ቀናት ብቻ ሆነ። አብዛኛውን ሠራተኛም ሳይሠራ ደመወዝ የሚከፈለው ነበር።

ይህን ለመቅረፍ ፋብሪካው ላይ መሠረታዊ የመዋቅር ለውጥ ተሠራ፤ የተሠራውንም መዋቅር ቦርዱ አይቶ መርምሮ በማጽደቁ ፋብሪካውን በአዲስ መልክ በማደራጀት ለሠራተኛው አዲስ የደመወዝ ስኬል፣ ባለፉት ዓመታት አጥቶት የነበረውን እድገት ጭማሪና ቦነስ እንዲያገኝ ተደረገ።

ፋብሪካው ከአካባቢው አስተዳደርና ከማህበረሰቡ ጋር ግንኙነቱ ሻክሮ ፋብሪካውን የሌላ ወገን አድርጎ የመሳል ከፖለቲካዊ እይታ ጋር የማስተሳሰር ዝንባሌዎች ነበሩ። ይህንን ለማስተካከልም የኢትዮጵያ ሕዝብ ሀብት መሪዎች ሲለዋወጡም የነበረ መሆኑን የማስረዳት ከአንድ መንግሥት ጋር የሚኖር ወይም የሚጠፋ አለመሆኑን በተጨባጭ የማስገንዘብ ሥራ ተሠራ።

ከአካባቢው መስተዳድርና ከኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ጋርም ሰፋፊ ሥራዎችን ሠርተን ፋብሪካው የሕዝብ እንደሆነ ግንዛቤ እንዲያዝ ለማድረግ ተችሏል።

አዲስ ዘመን ፦ ፋብሪካውን ገና ከመረከባችሁ አዲስ መዋቅር አስጠንቶና አጸድቆ ወደ ሥራ ማስገባት፤ ለሠራተኛው ጥቅማ ጥቅምን ማስከበር ከአቅም አንጻር አስቸጋሪ አልነበረም?

አቶ ጀማል ፦ እውነት ለመናገር ይህንን ስናደርግ ፋብሪካው ምንም ትርፍ አልነበረውም። እንደውም ኪሳራ ውስጥ ነበር። በዚህ አጣብቂኝ ውስጥ ሥራ አመራር ቦርዱም አመራሩም ያመነበት ሠራተኛውን በዚህ መልኩ መያዝ ካልተቻለ የሚታሰበው ለውጥ ሊሳካ አይችልም የሚል ነበር።

አዲስ ዘመን ፦ በሌላ በኩልም ፋብሪካው በርካታ ክሶች እንዳሉበትና ክሶቹም ለመዳከሙ ሚና እንደነበራቸው ይነሳል ፤ እንደው ከሳሾቹ እነማን ናቸው ? አሁንስ የክሱ ሂደት ምን ላይ ነው?

አቶ ጀማል ፦ አዎ! የተደራጁ የፍትህ መዛባቶች ነበሩ። ፋብሪካው ከ 5 መቶ ሚሊዮን ብር በላይ ክስ ነበረበት። ፋብሪካው ሸንኮራ አገዳን የሚያለማው በአርሶ አደር መሬት ላይ ነው፤ ይህንን ሲያደርግ ደግሞ ለህብረተሰቡ የተለያዩ መሠረተ ልማቶችን ይሠራል፤ መሠረተ ልማቶቹ ሲሠሩ በስምምነት ነው። ነገር ግን አርሶ አደሮቹ ከፋብሪካው ሲወጡ መሠረተ ልማቶቹ እኔ መሬት ላይ መሠራት አልነበረባቸውም በማለት ክሶች ይከፍታሉ፤ ከክሶቹ ጀርባ ደግሞ በርካታ ደላሎችም እንደነበሩ ደርሰንበታል።

እነዚህ ደላሎች ሚናቸው ፋብሪካው ላይ ክስ መቀስቀስ፤ ራሳቸው ክስ ማርቀቅ፤ አርሶ አደሩን ክሰስ ይህንን ታገኛለህ ብሎ ማባበል ነበር። በዚህም ላይ ሥራ አመራር ቦርዱ ከፍተኛ ውይይቶችን አድርጎ ከፍትህ አካላት ጋርም አብሮ ሠርቶ አሁን ላይ መስመር እንዲይዝ ሆኗል።

አዲስ ዘመን ፦ ዛሬስ ወንጂ ሸዋ ስኳር ፋብሪካ በምን ዓይነት ቁመና ላይ ነው?

አቶ ጀማል ፦ እውነት ለመናገር አሁንም በርካታ ሊሠሩ የሚገቡ ነገሮች አሉ። ፋብሪካችን ገና መድረስ የሚገባው ቦታ ላይ አልደረሰም። ይህም ቢሆን ግን አሁን ላይ ጅምር ተስፋዎች እየታዩ ነው ፤ ባለፉት ሁለት ዓመታት የሸንኮራ አገዳ ምርታማነታችን ጨምሯል። ፋብሪካው ወደቀድሞ ማንነቱ የመመለስ ዝንባሌዎች ይታዩበታል። ከአንድ ሄክታር ላይ ከ 1ሺህ 500 በላይ ይመረት ነበር፤ ይህ ግን ወርዶ ወርዶ 6 መቶ ኩንታል በአንድ ሄክታር ስናመርት ነው የቆየነው፤ በመሆኑም በዚህ ዓመት ይህንን ታሪክ ለመቀየር እየሠራን ሲሆን ባለን አፈፀጻጸም በአንድ ሄክታር 1ሺ 400 ኩንታልና ከዛ በላይ እያመረትን ነው።

በሌላ በኩልም ሠራተኞቻችን የደረሱባቸውን ችግሮች ስብራቶች ተሻግረው “የኔ ፋብሪካ ነው፤ ልጆቼን የማሳድግበት፣ እንጀራ የምበላበት ነው፤ ስለዚህ ያገባኛል “ በሚል ስሜት ውስጥ ስለገቡ ፋብሪካውን ሊደግፉ የሚችሉ የማሽነሪ ማሻሻያዎችን የፈጠራ ሥራዎችን እየሠሩ እኛም እያበረታታናቸው ነው።

አዲስ ዘመን ፦ ሌላው ችግር የግብዓት አቅርቦት፣ ከአርሶ አደሮች ጋር አለመስማማቶች ነበሩና እነሱንስ ለመፍታት ምን ዓይነት ስትራቴጂክ ፕላኖች ተቀመጡ?

አቶ ጀማል ፦ የግብዓት አቅርቦትን ለመፍታት ብዙ ሥራዎች እየተሠሩ ከመሆኑም በላይ አቅም በፈቀደ ሁሉ ቅድሚያ ሊያገኙ የሚገባቸውን እያስቀደምን እያቀረብን ነው ። አርሶ አደሮችን በተመለከተ ጥቅማቸው የሚከበርበትን መንገድ ተከትለን ሰፊ ውይይቶችን አድርገን ሰነድ ተዘጋጅቶ ዘመናዊ የኮንትራት ግብርና ሥርዓት ጀምረናል። በዚህም ቀድሞ አንድ ኩንታል ሸንኮራ ይሸጡበት ከነበረው 97 ብር ወደ 210 ብር ከፍ እንዲል ተደርጓል።

አሁን አርሶ አደሮቹም ወደሥራው በመሳብና ምርታማነትን ለማሳደግ ተግተው በመሥራታቸው ቀድሞ ከአንድ ሄክታር 600 ከዛ በላይ ኩንታል ይሰበስቡ የነበሩት አሁን ከ 2ሺህ ኩንታል በላይ ሰብስበዋል። ዘንድሮ ዝቅተኛ ምርት 1ሺ3 00 ኩንታል ሲሆን ከፍተኛው ደግሞ 2ሺ 500 ነው። ይህ እንግዲህ አርሶ አደሩ ገንዘብ እንዲያገኝ ተስፋ እንዲኖረው ፋብሪካውን እንዲወደው አድርጎታል።

አዲስ ዘመን ፦ ፋብሪካውን በሁለት እግሩ ለማቆም ሰፋፊ ሥራዎች እየተሠሩ ነው፤ ሁሉም ማለት ይቻላል ገቢ እንዳላቸው ወጪም አላቸውና ይህንን እኩል ለማስኬድ ምን እየተሠራ ነው?

አቶ ጀማል ፦ ይህ ፋብሪካ ላለፉት 70 ዓመታት የሚታወቀው ስኳር በማምረት ነው፤ አሁን ግን በርካታ ተጓዳኝ ሥራዎችን እየሠራ ነው። በዚህም ፋብሪካው ከ 25 ሺህ በላይ ዶሮዎችን በማርባት በዓመት ከ 9 ነጥብ 6 ሚሊዮን በላይ እንቁላል ይሰበስባል ። ዘጠኝ ያህል ምርጥ ዝርያ ያላቸው ላሞች ይዞ ወተት ያገኛል ፤ ከብት አደልበንም ባለፉት ሁለት ዓመታት ከ 1ሺህ በላይ ሰንጋዎችን ለገበያ አቅርበናል።

አዲስ ዘመን ፦ ፋብሪካ በአንድ አካባቢ ላይ ሲኖር ከሚጠበቁበት ነገሮች መካከል ማህበራዊ ሃላፊነትን መወጣት ነውና የወንጂ ሸዋ ስኳር ፋብሪካ በዚህስ ረገድ ያለበት ደረጃ ምን ይመስላል?

አቶ ጀማል፦ ተማሪዎችን እና አቅመ ደካሞችን የማገዝ ሥራ ይሠራል። ብርቱ የሆኑና በሀገር አቀፍ ፈተናዎች ላይ ጥሩ ውጤት ያመጡትን በተለየ ያግዛል፤ የሠራተኛ ተማሪዎች ሲሆኑ ደግሞ እንደ ፋብሪካ ይሸልማል።

አሁን ላይ በጅምር ያለ ቢሆንም የተማሪዎች ምገባ ፕሮግራም ላይ ይሳተፋል ፤ ወደፊት እነዚህን ሥራዎች አጠንክረን በመያዝ እየታዩ ያሉትን ጅምር ውጤቶች ለፍሬ እናበቃለን የሚል እምነት አለኝ።

አዲስ ዘመን ፦ አሁን ላይ አገልግሎት እየሰጠ ባይሆንም፤ ወንጂ የደስታ ከረሜላ ፋብሪካ እንደነበረው ይታወቃል፤ ይህንን ፋብሪካ ወደ ሥራ ለመመለስ እና ሌሎች ፋብሪካዎችንም ጎን ለጎን ለመሥራት የተቀመጠ እቅድ ይኖር ይሆን?

አቶ ጀማል፦ ደስታ ከረሜላ የኢትዮጵያ ህጻናትን ያሳደገ በወጣቶችም ዘንድ በሰፊው የሚታወቅ ነው። ድሮ በእኛ ጊዜ እናቶች ገበያ ሲሄዱ ቀኑን ሙሉ ከፍቶን እንውልና ማታ ደስታ ከረሜላን ይዘው በመምጣት ነበር ደስታችንን የሚመልሱት። በመሆኑም ይህ በበርካታ ኢትዮጵያውያን ልብ ውስጥ ያለ ፋብሪካ ቢሆንም ከምርት ሂደት ወጥቷል፤ አሁን ፋብሪካውን ወደምርት የመመለስ ሥራ ጀምረናል። በአዋጭነት ጥናቱም ፣አሁን ላይ ምን ያስፈልገዋል? ምን ጎሎታል? ገበያውስ ላይ እንዴት ነው የሚገባው? የሚለውን አስጠንተናል ለቦርድ ቀርቦ ሲወሰን በአጭር ጊዜ ውስጥ ወደ ምርት ይገባል።

ፋብሪካው ይህ ብቻ አይደለም እቅዱ ጎን ለጎን በርካታ ፋብሪካዎችንም ለመክፈት እየሠራ ነው። ከእኛ ተረፈ ምርት አንዱ የሸንኮራ አገዳ ገለባ (ባጋስ) ነው፤ ባጋስ በሚገርም ሁኔታ ከላዩ ላይ በርካታ ምርቶችን ሊሰጥ የሚችል ነው። ለምሳሌ የኢትዮጵያ ወረቀት ፋብሪካ የተቋቋመው ወንጂ ላይ ነው ፤ ታሳቢ ያደረገውም የእኛን ባጋስ ነበር። ነገር ግን ይህንን ማድረግ ሳይቻል ብዙ ዓመታት አልፈዋል። አሁን ላይ የወረቀት ፋብሪካን ለማቋቋም እናስባለን ። ከዚሁ ከባጋስ ችፑድም ማምረት ይቻላል። በአጠቃላይ ባስጠናነው ጥናት ስኳር አምርተን ተረፈ ምርት ነው ካልናቸው ግብዓቶች ብቻ 53 ዓይነት ምርቶችን ማግኘት እንደሚቻል ለይተናል። በመሆኑም ቅድሚያ የሚሰጣቸውን ለይተን የውጤትና ግብዓት ሰንሰለትን በሚያሳይ መልኩ ሌሎች ምርቶችንም ይዞ የመውጣት ሥራው ይቀጥላል።

ምናልባትም የዛሬ አምስት ዓመት ፋብሪካ ውስጥ ከስኳር ሌላ ሌሎች በርካታ እህት ፋብሪካዎችን እናያለን ብለን እናስባለን።

አዲስ ዘመን ፦ ዘንድሮ 1 ሚሊዮን ኩንታል ስኳር ማምረት የፋብሪካው እቅድ ነው፤ የሠራተኛ የማኔጅመንት የድጋፍ ሰጪ እንዲሁም የሌላውን ቁርጠኝነት እንዴት ይገልጹታል?

አቶ ጀማል፦ ቁጥር በሰው ልጅ ጭንቅላት ውስጥ ትርጉም አለው፤ ፋብሪካችን በ 2016 ዓ.ም 3 መቶ ሺ ኩንታል ስኳር አምርቷል፤ ከዚህ ተነስተን በአመቱ 1 ሚሊዮን ኩንታል ስኳር ነው ግባችን ስንል በጣም ብዙ ሰው “አብዳችኋል ምን እያደረጋችሁ ነው “ ብሎን ነበር። እውነት ለመናገር እዚህ ላይ የሥራ አመራር ቦርዱ ምስጋና ይገባዋል። ነገር ግን ያሉትን አቅሞች በማሟጠጥና በተጨማሪ ሥራዎችን በመሥራት በርካታ ውይይቶችንም በማድረግ እንዴት እንደሚቻል ትንታኔዎችን በመሥራት በርካታ አቅሞችን በማቀናጀት ይቻላል ወደሚል ድምዳሜ ደርሰናል።

አሁን ላይ ሠራተኞች ባሉበት ሁሉ የሚነገረው 1 ሚሊዮን ኩንታል የምርት እቅድ ነው። ይህ ለምን ሆነ ካልሽ ከመጀመሪያው ጀምሮ አይቻልም የሚል መንፈስ ስለነበረ ነው። ሌላው ደግሞ በወንጂ ሸዋ ስኳር ፋብሪካ ታሪክ 1 ሚሊዮን ኩንታል የተገኘው አንድ ጊዜ ብቻ ስለነበረ ነው ። የሚገርመው ያኔ ፋብሪካው 1 ሚሊዮን ኩንታል ሲያመርት የነበረው የአገዳ መትከያ መሬት ስፋት 12 ሺ ሄክታር ነበር፤ አሁን ላይ እኛ ይህንን እንደግመዋለን ስንል ያለን የመሬት ስፋት 9 ሺ ሄክታር ነው። የሰው ፍራትም ከዚህ የመነጨ ነው። ነገር ግን ተወያይተን ተማምነን አቅዱን መሬት አውርደን እየሠራን ነው።

አዲስ ዘመን ፦ የአቅድ ዘመኑ ገብቶ ከግማሽ በላይ ወራቶች ተገባደዋል፤ ከዚህ አንጻር 1 ሚሊዮን እቅዱ የሚሳካበት ቁመና ላይ ነው?

አቶ ጀማል ፦ አዎ ማሳካት የምንችልበት ቁመና ላይ ነን። ምክንያቱም ከላይ እንደገለጽኩት ከጅምሩ ጀምሮ እንዴት ነው ልናሳካው የምንችለው የሚለውን ተንትነናል፤ ስለዚህ መቶ በመቶ እቅዱ ይሳካል በማለትም የሥራ አመራሩ (ማኔጅመንቱ ) ሰባቱንም ቀን ተከፋፍሎ በቀኑ ደግሞ ውጪ አድሮ አገዳ አስገብቶ ስኳር አውጥቶ ነው የሚውለው፤ ምዘናውም በዚህ ውጤት መሠረት ነው የሚሠራው።

ሁሉም የሥራ መሪ በእኔ ቀን ፋብሪካው የተሻለ ማምረት አለበት ብሎ ነው የሚሠራው፤ ፋብሪካውም እስከ አሁን 7 ሺ ኩንታል ስኳርን በቀን እያመረተ ነው። 7ሺ5 መቶና ከዚያ በላይ ለሚያመርት አመራር ደግሞ ማበረታቻ ይኖረዋል። በመሆኑም ሥራ መሪው ይህንን ይዞ በከፍተኛ ሞራልና ተስፋ እየሠራ ነው። ሠራተኛው ደግሞ ላለፉት በርካታ ዓመታት ደሞዝ ጥቅማ ጥቅም አጥቶ ስለነበር ባለፈው ዓመት ፋብሪካው ሳያተርፍ እኛ ሃላፊነቱን ወስደን ደመወዝ ስለጨመርንለት ደስተኛ ሆኗል። ከዛም በላይ ያላተረፈና ኪሳራ ውስጥ ያለ ፋብሪካ ይዞ ደመወዝ መጨመር እብደት ነው። ነገር ግን እናንተን ይዘን እንለውጠዋለን ብለን ቃል በማስገባት የሠራተኛውን ተነሳሽነት መመለስ ችለናል።

ይህ ብቻ አይደለም የደመወዝ ጭማሪ ባደረግን በዓመቱ ሠራተኛው ፋብሪካውን ትርፋማ ስላደረገ ቦነስ አግኝቷል። በነገራችን ላይ ይህ ማበረታቻ 3 መቶ ሺ ስላመረትን አይደለም ወደፊት አንድ ሚሊዮን ስለምናመርት የተሰጠ መሆኑም መታወቅ አለበት ። ስለዚህ ሠራተኛው የበላው ቀብድ ነው።

በዚህ ሁኔታ ሁሉም አምኖበት ቦርዱን ጨምሮ ደመወዝ ጭማሪ እድገት ቦነስ እንዲያገኝ ሆኗል። በዚህ ምክንያት ደግሞ አሁን ላይ ከ 1ሚሊዮን ኩንታል ውጪ ሌላ ነገር እየታየው አይደለም።

አምና በ 3መቶ ሺ ኩንታል 2 አርከን እድገት ያገኘ ሠራተኛ ዘንድሮ 7 መቶ ሺ ቢያመርት ምንም አያገኝም ፤ ስምንት መቶ ሺ ቢያመርት አንድ እርከን ያገኛል ፤ ስለዚህ ከ1 ሚሊዮን በታች ምርት እንዳያስብ ሆኗል፤ ይህንን ሊያጎድል የሚችል ምንም ዓይነት ችግር እንዳይፈጥር ይጥራል።

አሁን ያለው የሠራተኛና የአመራር ቅንጅት እጅግ ማራኪ ተስፋ ሰጪ ከመሆኑም በላይ ለሌሎች ፋብሪካዎችም ተሞክሮ ሊሆን የሚችል ነው። በዚህ አጋጣሚም ሠራተኞቻችንን ማመስገን ይገባል።

አዲስ ዘመን ፦ ወንጂ ሸዋ ስኳር ፋብሪካ በኮሪደር ልማቱም አንድ ርምጃ የተራመደ ሥራን ሠርቷልና በዚህ ላይ ምን ይላሉ?

አቶ ጀማል፦ የስኳር ፋብሪካው ዘመናዊ የከተማ ልማትን ኢትዮጵያ ውስጥ ካመጡ ፋብሪካዎች አንዱ ነው። የዛሬ 70 ዓመት የእኛ ፋብሪካ የሲኒማ አዳራሽ ነበረው፣ እዚህ ያለ ማህበረሰብ አዋሽ ሄዶ መዋኘት ቢችልም ዘመናዊ የመዋኛ ገንዳ እንደየሥራ ደረጃው የተዘጋጀለት ነበር፣ የመጠጥ፣ የአትክልት፣ የእቃና ልብስ ማጠቢያ ተብለው የተለዩ ውሃዎች የነበሩትም ነው።

በጣም የሚገርመው የወንጂ ሸዋ ስኳር ፋብሪካ ሲኒማ ቤቶች እስከ አሁን በሀገራችን የሌለ አባቶች፣ ልጆች፣ ባልና ሚስት ሲኒማ የሚያዩበት ቀን የተቀመጠለት ነበር። ያለ ፕሮግራሙ የመጣ ፊልም ተመልካች በምንም ምክንያት አይስተናገድም ነበር።

ይህ ብቻም አይደለም መዝናኛ ክበባት አካባቢም ሠራተኞች ከሥርዓት ውጪ እንዳይሆኑ የተጣሉ ሕጎች ነበሩ።

በዚህም ሠራተኞቻችን አካባቢው ምንድነው የሚያስፈልገው? የትናንትናዋንስ ወንጂ በምን መልኩ ነው አሻሽለን የምንደግማት? አዲሷንስ ወንጂ በምን መልኩ እንፍጠራት ? በሚልና ሠራተኞቻችን 24 ሰዓት የሚሠሩ ከመሆናቸው አንጻር አይናቸውን የሚያሳርፉበት ጊዜ ሲኖራቸውም የሚዝናኑበት ልጆቻቸውን የሚያጫውቱበት ነገር ያስፈልገዋል በማለት ይህንን የኮሪደር ልማት በጣም በጥሩ ሁኔታ የወንጂ ሸዋን ዐሻራ በሚያሳይ መልኩ ሠርተነዋል።

አሁንም ብዙ የሚቀሩን ሥራዎች ቢኖሩም አዋሽ ወንዝ ዓመቱን ሙሉ በደጃችን የሚፈስ ነው፤ እስከ አሁን ድረስም ለቱሪዝም አገልግሎት ውሎ አያውቅም ፤ ወደፊት በወንዙ ላይ መዝናኛ ሊሆኑ የሚችሉ መሠረተ ልማቶችን የመሥራት እቅድ አለን።

አዲስ ዘመን፦ ይህ አካባቢ በታደለው የተፈጥሮ ሀብትም እንዲሁም በፋብሪካው የምርት ውጤቶችና በሌሎችም በሀገር ግንባታው ላይ የራሱን ሚና ይወጣ ዘንድ ከማን ምን ይጠበቃል?

አቶ ጀማል ፦ ወንጂ ትንሿ ኢትዮጵያ ልንለው እንችላለን። ምክንያቱም አካባቢው የሁሉም ብሔር ብሔረሰቦች ስብጥር ያለበት ነው። ይህ ደግሞ ለእኛ ጠቅሞናል ። አብዛኛው ሰው ሠራተኛ ነው የሚግባባውም በሥራ ቋንቋ ነው።

ፋብሪካ አሁን 70 ዓመቱ ነው ለመጪው ትውልድ እየተላለፈ በርካታ 70 ዓመቶችን እንዲኖር ሠራተኛው አሁን ላይ ያዳበረውን የባለቤትነት ስሜት ይዞ መቀጠል አለበት ። የአካባቢው ማህበረሰብም ቢሆን የፋብሪካው እዚህ መኖር በተጨባጭ ጠቅሞታል ፤ ስለዚህ ፋብሪካውን እንደ ራሱ አይቶ ማገዝ ይገባዋል። ከመንግሥት፣ ከኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ፣ ከሥራ አመራር ቦርዱ በርካታ የሚጠበቁ ነገሮች አሉ።

አሁን ፋብሪካው በዓመት 1 ሚሊዮን ኩንታል ስኳር አመርታለሁ ቢልም በመንግሥት በኩል የግብዓት አቅርቦት ይፈልጋል ፣ ከአካባቢው ነዋሪዎች ጋር በመሆን የመሬት ፖሊሲን አጽድቆ ተጠቃሚ ቢያደርግ እስከ 1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ኩንታል ስኳር በዓመት የማምረት አቅም አለው።

አዲስ ዘመን፦ ለነበረን ቆይታ በጣም አመሰግናለሁ።

አቶ ጀማል ፦ እኔም በጣም አመሰግናለሁ።

እፀገነት አክሊሉ

ወደ ገጽ 9 ዞሯል አዲስ ዘመን ሰኞ የካቲት 10 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You