ትራምፕ በዓለም አቀፍ ርዳታ ላይ የወሰዱት ውሳኔ ያስከተለው ጣጣ

የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ አሜሪካ ለውጭ ሀገራት የምትሰጠው ርዳታ (ለአስቸኳይ ጊዜ የምግብ እርዳታ እንዲሁም ለእሥራኤል እና ለግብፅ ከሚሰጠው ወታደራዊ ድጋፍ በስተቀር) እንዲቆም ማዘዛቸውን ተከትሎ በዓለም አቀፍ ተረጂዎች ዘንድ ችግር እየተፈጠረ እንደሆነ ተገልጿል፡፡ የፕሬዚዳንቱ ወደሥልጣን መምጣት ተከትሎ የተላለፈው ይህ ውሳኔ ብዙዎችን ከማስደንገጥ አልፎ እያነጋገረ ይገኛል፡፡ በአሜሪካ መንግሥት የተወሰደው ይሄ ውሳኔ ‹‹ቅድሚያ ለአሜሪካ›› ከሚለው የፕሬዚዳንቱ አቋም ጋር የተያያዘ እንደሆነና በጊዜያዊነት እንደቆመ ይገለጻል፡፡

ከዚህ ውሳኔ ጋር በተያያዘ በዓለም ዙሪያ የሰብዓዊ ድጋፍ በሚደረግላቸው ሰዎች ላይ ጫና እየደረሰ እንደሆነ ታውቋል፡፡ ከአንዳንድ ወሳኝ ትግበራዎች ውጪ በአሜሪካ መንግሥት በኩል የሚደረግ የትኛውም የውጪ ርዳታ ለሦስት ወራት እንዲታገድ የወጣው መመሪያ በጦርነት፣ በአስቸኳይ ሰብዓዊ ርዳታና በመሰል ሁኔታዎች ውስጥ ላሉ ተረጂዎች ከባድ ሁኔታን መፍጠሩ ተገልጿል፡፡

ትልቁ የረድዔት ተቋም ‹‹የባንግላዴሽ ሩራል አድቫንስመንት ኮሚቴ/BRAC›› በአራት ሀገራት ባቋረጣቸው ልገሳው ምክንያት ሦስት ነጥብ አምስት ሚሊዮን ሰዎች ችግር ላይ እንደሚወድቁ አሳውቋል፡፡ በአንድ የርዳታ ድርጅት ስር የሚሠሩ ሠራተኛ ለቢቢሲ እንደገለጹት ‹የአሜሪካ መንግሥት ውሳኔ ብዙዎቻችንን አስደንግጧል፡፡ በርዳታ አቅርቦቱ ላይ እንደ ድንገተኛ አደጋ ነው የተሰማን›› ሲሉ ተናግረዋል፡፡

በዚህ የርዳታ መቋረጥ ምክንያት የግብረ ሠናይ ፕሮግራሞችን ጨምሮ በዓለም የረድዔት ሥርዓት ውስጥ ከፍተኛ መደናገጥ መፍጠሩ ተገልጿል፡፡ ተጨማሪ የገንዘብ መቋረጥ ችግር እንዳይመጣባቸው የሰጉ የግብረ ሠናይ ሠራተኞች ስጋታቸውን በግልጽ ለመናገር ድፍረት ቢያጡም አንዳንድ ሠራተኞች ግን የአሜሪካንን ውሳኔ ተችተዋል፡፡

እ.አ.አ በ2003 በፕሬዚዳንት ቡሽ ይፋ የተደረገውና በዓለም ዙሪያ የኤች አይ ቪ ስርጭትን በመከላከል ሥራ ላይ የተሰማራው የፕሬዚዳንቱ የአደጋ ጊዜ የኤድስ ድጋፍ ዕቅድ (PEPFAR) ሠራተኞች ኮምፒውተራቸው ላይ ወደሚገኘው አካውንት እንዳይገቡ መታገዳቸውን በአሜሪካ መንግሥት ዓለም አቀፍ የልማት ድርጅት (US­AID) የቀድሞ የዓለም ጤና ድርጅት ረዳት አስተባባሪ የነበሩት ዶ/ር አቱል ጋዋንዴ ተናግረዋል፡፡

ድርጅቱ ዶክተሮችንና ነርሶችን ጨምሮ ከ250ሺህ በላይ ሠራተኞችን በ55 ሀገራት አሰማርቶ በኤች አይ ቪ ኤድስ ስርጭት፣ ቅድመ ጥንቃቄ እና የመድኃኒት አቅርቦት ላይ ያተኮረ እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡ ይህ ተቋም በዓለም ዙሪያ የበርካታ ሚሊዮን ሰዎችን ሕይወት በመታደግ እና የኤች አይቪ ስርጭትን በመቀነስ ረገድ ከፍተኛ ሚና የተጫወተ ተቋም ነው፡፡

“ፕሮግራሙ ተቋርጧል፣ አገልግሎቶች ቆመዋል” ሲሉ ለቢቢሲ የተናገሩት ዶክተር ጋዋንዱ፣ በዓለማችን በኤች አይቪ ለተያዙ 20 ሚሊዮን የሚሆኑ ሰዎች አገልግሎት የሚሰጡ ክሊኒኮች ከፍተኛ ተፅዕኖ ደርሶባቸዋል ብለዋል። በባይደን የሥልጣን ዘመን በዩኤስ ኤይድ ግብረ ሠናይ ተቋም ውስጥ በከፍተኛ ኃላፊነት የተሾሙት ዶ/ር ጋዋንዱ በምዕራብ አፍሪካ የኤምፖክስ (የዝንጀሮ ፈንጣጣ) ወረርሽኝ፣ የአደንዛዥ ዕፅ ስርጭትን መግታት ላይ ጨምሮ በአሜሪካ መንግሥት ርዳታ የሚደገፉ መሰል የበጎ አድራጎት ሥራዎች ዕጣ ፈንታቸው እንደማይታወቅ ገልጸዋል፡፡

የትራምፕ አስተዳደር በምድረ አሜሪካም ቢሆን እንደ ፅንስ ማቋረጥ፣ የቤተሰብ ምጣኔ፣ ብዙኃነትን እና መሰል በከፍተኛ ድጎማ የሚንቀሳቀሱ ፕሮግራሞች ላይ ተቃውሞ እንዳለው መናገሩ ይታወሳል፡፡ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ማርኮ ሩቢዮ ‹‹እያንዳንዷ የምናወጣት ዶላር፣ የምንደግፋቸው ፕሮግራሞች፣ የምንከተላቸው ፖሊሲዎች በምክንያት ሊሆኑ ይገባል› ሲሉ ተናግረዋል። በተጨማሪም ‹‹እነዚህ ልገሳዎች አሜሪካን ደኅንነቷ የተጠበቀ ያደርገዋል? ጠንካራ ያደርጋታል? ወይስ ያበለፅጋታል?›› በማለት ይጠይቃሉ፡፡

ዘላለም ተሾመ

አዲስ ዘመን ማክሰኞ ጥር 27 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You