ዛሬ ላይ ቴክኖሎጂ እጅግ የረቀቀ ደረጃ ላይ መድረሱ ሥራዎችን በማቅለልና ሕይወትን አዝናኝ በማድረግ ለሰው ልጆች ምቾት ፈጥሯል። በዚያ ልክ ግን ብዙ አደጋዎችም አሉበት። ለምሳሌ፤ የሰውን ልጅ የማሰብና የማሰላሰል አቅም እያዳከመ ስለመሆኑም የሚገልጹ አሉ። በዚህ ዙሪያ እንደ ዩቫል ኑዋህ ሃራሪ የመሳሰሉ ዓለም አቀፍ ሳይንቲስቶች እንደሚሉት፤ ሰው ሠራሽ አስተውሎትን የመሳሰሉት የቴክኖሎጂ ውጤቶች የሰውን ልጅ የማሰብ ተፈጥሮ የሚፈታተኑ እና ምናልባት ከዘመናት በኋላ ሀሳብ አልባ ዓለም እንዳይፈጠር ስጋት ይሆናሉ።
ምክንያቱም ቴክኖሎጂው፣ ከሒሳብ ስሌቶች መተግበሪያ ጀምሮ ምንም ነገር በራሳችን አስበን እንዳንሠራ አድርጎናል። ለአብነት፣ ‹‹ዛሬ ቀኑ ምንድነው!›› ብሎ ትንሿን ጉዳይ እንኳን ከማሰብ ይልቅ ስልክ ላይ ማየት የተለመደ ነው። እናም ስለየትኛውም ነገር ከማሰብና ከማሰላሰል ወጥተን ወደ ኢንተርኔትና ዩትዩብ መግባትን እንድንለማመድ መሆናችን፣ ከቴክኖሎጂው ተግዳሮቶች ጎራ የሚመደቡ ናቸው።
በሌላ በኩል ደግሞ በተለይም በየማኅበራዊ ሚዲያ ገጾች አወናባጅ እና ሐሰተኛ ነገሮች እንዲፈጠሩ አድርገዋል። በዛሬው የትዝብት ጉዳያችንም የምናየውም ይሄንኑ ሲሆን፤ በዋናነትም አስመስሎ (ፌክ) በሚሠሩ አሳሳች መረጃዎች ላይ በማተኮር ነው። ትዝብታችን ደግሞ ከአጭበርባሪዎች ይልቅ የተጭበርባሪዎች ለመጭበርበር ምቹ መሆንን የሚያመለክት፤ ይሄን መሰሉ የተጭበርባሪነት ሁኔታም ከአጭበርባሪው ይልቅ ተጭበርባሪውን አሳዛኝ የችግሩ ሰለባነት በማሳየት ላይ ያጠነጥናል።
ብዙ ጊዜ የታዘብኩት ነገር አብዛኞቻችን ለቴክኖሎጂ አዲስ እንደመሆናችን መጠን፤ ለመጭበርበርም ምቹ ነን። በዚህ በኩል ውስብስብ የማጭበርበሪያ መንገዶች መኖራቸውን አምናለሁ፤ ዳሩ ግን አብዛኞቻችን ሊያሳስት በማይችልና ሐሰተኛነቱ በጣም በግልጽ በሚታወቅ ነገር ሁሉ እንጭበረበራለን። ይሄ ደግሞ ዙሪያ ገባውን ልብ ብሎ እንደዚህ ሊሆን አይችልም የሚል ማሰላሰልና ግምገማ ያለማድረግ ውጤት ነው።
በቅርቡ አንድ ታዋቂ ሰው፤ በተለያየ ጊዜ ለተለያየ ጉዳይ የተናገረውን ነገር በመገጣጠም በሚፈልጉት መንገድ አድርገው ቲክ ቶክ ላይ ሲቀባበሉት አየሁ። ግለሰቡ፣ የተናገራቸውን ሀሳቦች ሁሉንም ስላደመጥኳቸው አውቃቸዋለሁ። ዳሩ ግን የሆኑ ወገኖችን የተሳደበ አስመስለው አቀረቡት። ይሄ ደግሞ ሰውየው ተሰደበ ለተባለው ወገን ይቀርባል ተብሎ ስለሚታሰብ፣ በእሱ በኩል ብናደርገው አሳማኝ ይሆንልናል በሚል ስሌት ይሁነኝ ተብሎ ለማጭበርበሪያ ተግባር እንዲውል ጥቅም ላይ የዋለ ነው።
ቪዲዮው ላይ ንግግሩ የተቆረጠበትና የተቀጠለበት ቦታ ራሱ በግልጽ ያስታውቃል። የቪዲዮ አርትዖት (ኤዲቲንግ) ልምድ ያለው ሰው እንኳን አይደለም የሠራው። ተቆርጦ የተቀጠለበት ቦታ ላይ ሲነጥር ያስታውቃል። በተለያዩ ጊዜ፣ ለተለያየ ጉዳይ የተናገራቸውን ነገሮች ቆራርጠው ነው የገጣጠሙት።
ብዙ ሰው እውነት ይመስለው ይሆናል ብዬ ስለገመትኩ ከስር የሚሰጡ አስተያየቶችን አነበብኩ። ከ300 በላይ ከተሰጡ አስተያየቶች ውስጥ፤ ከዚህ በፊት ለሌላ ጉዳይ የተናገረው መሆኑን የጻፉት ሰዎች ሦስት ብቻ ናቸው። ሌላው በሙሉ ሰውዬውን የሚራገም ነው። ‹‹ደህና ሰው አልነበርክ እንዴ! እንዴት እንደዚህ ትናገራለህ!›› የሚል ነው። አብዛኞቹም በብሔርና በሃይማኖት ስም የሚሳደቡ ናቸው።
ይሁን እንጂ ይሄን መሰሉን አስተያየት ከመስጠት በፊት ግለሰቡ/ሰውዬው እንዲህ ይላል ወይ? ብሎ ቆም ብሎ ማሰብ ያስፈልግ ነበር። በእርግጥ ብዙ ሰው አቋሙን ሊቀይር፣ ብዙ ሰው ድንገት ያልተጠበቀ ነገር ሊናገር ይችላል ቢባል እንኳን፤ ዳሩ ግን ቢያንስ ለማደናገሪያነት ጥቅም ላይ የዋለው ቪዲዮ ከፍተኛ የአርትዖት ችግር ያለበት በመሆኑ መጠርጠር ያስፈልግ ነበር። ሁለተኛ፤ እሱ ብሏል አላለም የሚለውን ከሌላ መደበኛ ሚዲያ እስከሚያጣራው ወይም ሰውዬው ማስተባበያ እስከሚሰጥ መታገስ ያስፈልግ ነበር።
አስተያየቶቹ የሚያስረዱት ግን፣ ያ ሁሉ ተሳዳቢ ሰው ግለሰቡ ከዚያ በፊት በተለያየ ጉዳይ ላይ የተናገራቸውን ነገሮች ሰምቶ አያውቅም ማለት ነው። ዛሬ ላይ ደግሞ ብዙ ችግሮቻችን የሚከሰቱት በእንዲህ አይነት ጥራዝ ነጠቅነት ነው። ቆም ብሎ ማሰብ እና በትኩረት ማስተዋል ባለመቻል ነው። ምንም እንኳን የማይጠበቅ ንግግር የሚያደርጉ የሉም ባይባልም፣ ምንም እንኳን ብሔርን ከብሔር፣ ሃይማኖትንም ከሃይማኖት ለማጋጨት ነውር ነገር የሚናገሩ ቢኖሩም፤ ዳሩ ግን ያላሉትን አሉ በማለት የሚሰራጩ ሐሰተኛ መረጃዎች ከአጭበርባሪዎች ይልቅ የተጭበርባሪዎች ትብብር ያለባቸው ናቸው። ምክንያቱም ለመጭበርበር ተመቻችተን እየተባበርናቸው ነው ማለት ነው።
ከዓመታት በፊት ሐሰተኛ የሹመት ደብዳቤዎች የማኅበራዊ ገጾች ላይ ፋሽን ሆነው ነበር። በወቅቱ አንድ ጋዜጠኛ አንደኛውን ሐሰተኛ ደብዳቤ እንደማሳያ ወስዶ፤ ‹‹ምንም ማጣራት እና ማስተባበያ ሳያስፈልግ በእነዚህ ነገሮች ሐሰተኛ መሆኑን ማወቅ ይቻላል›› ብሎ በደብዳቤው ላይ ያሉትን የፕሮቶኮል ስህተቶችን ዘረዘረ። ብዙ ሰው ሲያሰራጨው እነዚያን ነገሮች ልብ አላለም ነበር፤ ወይም አያውቃቸውም ነበር ማለት ነው። ትክክለኛውን አጻጻፍ አያውቀውም ነበር ማለት ነው። እውነት ነው ሐሰት ነው ብሎ መጠየቅም አልፈለገም ነበር።
ያ ጋዜጠኛ ‹‹ሐሰት የሚሆንበት ምክንያት›› ብሎ ከዘረዘረ በኋላ በሁለተኛው ይሁን ሦስተኛው ቀን የሚመለከተው አካል ሐሰት መሆኑን አሳወቀ። በእንዲህ አይነት ግልጽ ስህተት ባላቸው ሐሰተኛ መረጃዎች ሁሉ እንጭበረበራለን ማለት ነው። እናም ቢቻል ቢቻል በትክክል አስመስሎ የተጻፈውን እንኳን መለየት ነበረብን፤ ያ ቢቀር ግን ቢያንስ ጉልህ የሆኑ ስህተቶችን እንኳን ልብ ማለት ይገባል።
ምናልባት የሆሄያት ስህተት መደጋገም ለሐሰተኛነቱ ማረጋገጫ ላይሆን ይችላል፤ ምክንያቱም ትክክለኛ ደብዳቤዎችም የሆሄያት ግድፈት ሊያጋጥማቸው ይችላል። ያም ሆኖ ግን በአንድ ዓረፍተ ነገር ውስጥ ተደጋጋሚ የሆሄያት ስህተት ሲኖር፤ ሐሰተኛ መሆኑን ለመጠርጠር የመጀመሪያ እርምጃ ልናደርገው ይገባል። ምክንያቱም ትክክለኛ ደብዳቤዎች ሲጻፉ በጥንቃቄ ነው፣ በድጋሚ ታይተውና ማረጋገጫ ተደርጎባቸው ነው። በሌላ በኩል የሚጠቀሟቸው ቃላት ተቋማዊ የሆነ እና ከግል ስሜት ነፃ የሆኑ ናቸው። ተቋማዊ አገላለጽ እና በግለሰቦች ስሜት የተጻፈ ጽሑፍ ልዩነት አለው።
በጽሑፍ ከሆነ፤ በትክክል አስመስለው የሚጽፉ ይኖራሉ፤ ለምሳሌ ከዚህ በፊት ለሌላ አገልግሎት የዋለውን ትክክለኛ ቅጽ በማየት ሐሰተኛውን አስመስለው ሊጽፉት ይችላሉ። እነዚህን ለመለየት የተለየ ብቃት ሊጠይቅ ይችላል፤ የሚያሳዝነው ግን አብዛኞቻችን የምንሸወደው ሐሰተኛነቱ በቀላሉ በሚታወቀው ሁሉ ነው።
በቪዲዮና ኦዲዮ (በተንቀሳቃሽ ምስልና ድምፅ) ጥልቅ ማስመሰል (ዲፕ ፌክ) የሚባል አለ። ይሄ ማለት የባራክ ኦባማን ምስልና ድምፅ ወስዶ፤ የራስን ሀሳብና ንግግር በኦባማ ምስልና ድምፅ እንዲተላለፍ ማድረግ ማለት ነው። ከምስል ጋር በማዋሓድ ኦባማ የተናገረው ማስመሰል ማለት ነው። እንዲህ አይነት ቅንብሮች የቴክኖሎጂ አጠቃቀም ልምድ ያላቸውን ሰዎች ሳይቀር የሚሸውዱ ናቸው። ለመለየትም ራሱን የቻለ የቴክኖሎጂ አጠቃቀም አላቸው።
ሆኖም ግን፤ ባለሙያዎች እንደሚሉት በማየት ብቻ ለመጠርጠር የሚያስችል ሁኔታ አላቸው። ችግሩ ግን ብዙዎቻችን ይህን ልብ አንልም፤ ልብ ብሎ ከማየትና ዙሪያ ገባውን ከማጥናት ይልቅ ቶሎ ብሎ አጀንዳውን ለማራገብ እንፈልጋለን። በመሆኑም ሐሰተኛ መረጃዎች ስርጭታቸው የሚያድገው በአጭበርባሪዎች ብቻ ሳይሆን በተቀባዮችና በተጭበርባሪዎችም እገዛ ስለሆነ፤ አጠራጣሪ ነገሮችን ስናገኝ ቆም ብለን በማሰብና በማገናዘብ ችግሮችን ከማባባስ ልንቆጠብ ይገባል!
ዋለልኝ አየለ
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ታኅሣሥ 5 ቀን 2017 ዓ.ም