ጉምቱው ብዕረኛ!

ሀገራችን በስነ-ጽሁፍ ታሪክ ቀደምት እንደመሆኗ ልዩ አሻራቸውን የጣሉ ቁጥር ስፍር የሌላቸው የኪነጥበብ ሰዎችን አፍርታለች። በእያንዳንዱ ዘመንም በርካታ የጥበብ ሰዎች መጥተዋል፣ ሄደዋልም፡፡ ኢትዮጵያ መቼም ጥበበኞችን ነጥፋ አታውቅም፡፡

በዛሬው የዝነኞች ገጻችን የዚህኛው ዘመን የኪነ-ጥበብ ፈርጥ ከሆኑት መካከል ስለ አንድ ሰው የሕይወት ታሪክ፣ ዘመን አይሽሬ ከሆኑ ስራዎቹ ጋር በማጣመር ልናቀርብላችሁ ወደናል። ይህ ሰው በሰራቸው የስነ-ጽሁፍ ስራዎቹ ከአንባቢያንና ሀያሲያን ዘንድ ትልቅ አድናቆትንና ዝናን የተቸረ፣ ድንቅ በሆኑ የፈጠራና በራሱ የአጻጻፍ ስልት ልዩ ልዩ ሽልማቶችን ማግኘት የቻለ ባለ ብዙ ተሰጥኦና ድንቅ አዕምሮ ባለቤት ነው። ደራሲና ገጣሚ አዳም ረታ።

ሐምሌ 8 ቀን 1950 ዓ.ም በአዲስ አበባ ከተማ የተወለደው አዳም ረታ ገና በልጅነቱ በውስጡ የተጸነሰው የስነ-ጹሁፍ ዝንባሌ ዛሬ ላበረከታቸው ተወዳጅ ስራዎቹ መሰረት ጥሎለታል። በአንድ ወቅት በአዲስ ነገር ጋዜጣ ላይ ስለዚህ የተናገረውን እንመልከት፡፡ ”5ኛ ከፍል እያለሁ ዓርብ ዓርብ ከሰዓት በኋላ ሪፖርት እናቀርባለን፡፡ ደንቡ ከጋዜጣ ያነበብነውን ወይም ከሬዲዮ የሰማነውን ነገር በራሳችን አማርኛ አሳጥረን ጽፈን ክፍል ውስጥ ማቅረብ ነው፡፡

ሁልጊዜ ርዕስ የሚሆኑት የጃንሆይ ጉብኝት፤ የአዲስ አበባ አንደኛ ዲቪዚዮን እግር ኳስ ውድድር ውጤት እና የመካከለኛው ምስራቅ ግጭት ነው፡፡ ነገር ግን ይህን መጻፍ ሰለቸኝ፡፡ አንድ ቀን በመንገድ ላይ ስሄድ የዶሮ ነጋዴዎች ሀይለኛ አውሎ ነፋስ መጥቶ ሲያተራምሳቸው እና ዶሮዎቹ ከቅርጫት እየበረሩ ሲያመልጡ ነጋዴዎቹም እነሱን ለመያዝ የሚያደርጉትን መውደቅና መነሳት አየሁ እና ገረመኝ። ያን ለመጻፍ ወሰንኩ፡፡ ጽፌም ክፍል ውስጥ አቀረብኩና ተማሪዎቹን ትንሽ አስደሰትኳቸው። ከዚያ መምህሩ ከየት አመጣከው ሲሉኝ ከጋዜጣ አንብቤ ነው አልኩ፡፡ ጋዜጣ ላይ እንዲህ አይነት ነገር አይጻፍም ብለው ጢሜን አበረሩኝ፡፡ ከዚያ ግን ለተማሪዎች አዳሙ ደራሲ ነው የሚሆነው ብለው ተናገሩ፡፡ ደራሲ መሆን ማለት ምን ማለት እንደሆነ ያኔ አልገባኝም፡፡”

አዳም በአብዛኛው የሚጽፈው ልቦለዶችን ቢሆንም ግጥሞችንም የመጻፍ ልዩ ችሎታ አለው። ግጥሞቹ በተለያዩ ጊዜያት መፅሔቶች ላይ መታተም የቻሉ ቢሆንም ያልታተሙ ግጥሞችና የስነ-ጽሁፍ ስራዎቹ በርካታ ናቸው። በስነ-ጽሁፉ ብቻ ሳይሆን በቀለም ትምህርቱም የተሻለ ደረጃ ላይ መድረስ የቻለው አዳም ረታ በጂኦግራፊ የመጀመሪያ ዲግሪውን ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የተቀበለ ሲሆን፤ ሁለተኛ ዲግሪውን ደግሞ በውጭ ሀገር አግኝቷል።

አዳም ረታ ለመጀመሪያ ጊዜ ልዩ ተሰጥኦው እንደ ሻማ ያበራበትና በኢትዮጵያ የስነ-ጽሁፍ ተከታታዮች እና አንባቢያን ልብ ውስጥ የመሠረት ድንጋይ ያስቀመጠበትን የበኩር ስራውን ይዞ በ1977 ዓ.ም በአንዲት መጽሃፍ ብቅ አለ። ይሄውም “አባ ደፋር እና ሌሎች አጫጭር ታሪኮች” የተሰኘው መጽሀፍ ነው። በዚህ የአጫጭር ታሪኮች ስብስብ ውስጥ የተለያዩ ጸሐፊዎች የተሳተፉበት ሲሆን፤ ደራሲ አዳም ረታ ድብድብ፣ ዕብዱ ሺበሺ፣ ሲሮኮ እና ሲፊንክስ በድምሩ አራት ስራዎችን በመጽሃፉ ውስጥ ለማካተት ችሏል።

በ1990 ዓ.ም “ጭጋግና ጠል” የአጭር ታሪኮች ስብስብ ውስጥ “ዘላን” የተሰኘ ልቦለዱ ታትሟል። እነዚህ ሁለቱ ከሌሎች ደራሲዎች ስራዎች ጋር በጥምረት የታተሙለት በመሆኑ እንደ ወጥ ሳይቆጠሩ ቀርተዋል።

ደራሲው የመጀመሪያ ወጥ የአጫጭር ልቦለዶች ስብስብ የሆነውን “ማህሌትን” ለመጀመሪያ ጊዜ በ1981 ዓ.ም ለማሳተም በቅቷል። ሌላው በሻማ ቡክስ በ1997 ዓ.ም የታተመው “ግራጫ ቃጭሎች” የሚለው መጽሀፉ ለአዳም ረታ ትልቅ የመሸጋገሪያ ድልድይና ልዩ ችሎታው የታየበት ወጥ ረጅም ልብወለድ ነው።

ጉዛቸውን የቀጠሉት የአዳም ረታ የማይነጥፉ የብዕር ጠብታዎቹ በ2001 ዓ.ም አለንጋና ምስር እንዲሁም እቴሜቴ ሎሚሽታ በ2002 ዓ.ም ከሰማይ የወረደ ፍርፍር፣ በ2003 ዓ.ም ይወስዳል መንገድ ያመጣል መንገድ እና በ2004 ዓ.ም ሕማማት እና በገና በተከታታይ በየዓመቱ ታትመው ለንባብ በቅተዋል። ከዚህ በኋላ ደግሞ መረቅ በ2007 ዓ.ም፣ የስንብት ቀለማት በ2008 ዓ.ም ሌላው በ2010 ዓ.ም አፍ የተሰኙ በርካታ ድንቅ ስራዎችን በተለየ አቀራረብ በመስራት ለአንባቢያን እነሆ ማለት ችሏል።

በአንድ ወቅት በአዲስ ነገር ጋዜጣ ላይ በከተበው ጽሁፍ ስለራሱ ሲናገር በድግግሞሽና በአንድ አይነት መንገድ መሄድ በጣም እንደሚያሰለቸው ገልጾ ነበር። ለዚህ ደግሞ ስራዎቹን መመልከት ከቻልን ወጣ ባለ በራሱ የአቀራረብ ስልት ይዞ መምጣቱ ምስክር ነው።

ቀደም ሲል “በአባ ደፋርና ሌሎች” ስብስቦች ውስጥ ስራዎቹን የማቅረብ እድል በማግኘት የጀመረው የአዳም ረታ የጥበብ ጉዞ ከስኬቶቹ ኋላ ቆየት ብሎም ሌሎች ወጣት ጸሃፊያን ፈለጉን ይከተሉ ዘንድ “አማሌሌ” በተሰኘው መጽሃፍ ላይ አብሯቸው በጥምረት ሰርቷል።

ስራዎቹ በብዛት በማህበራዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ሀይማኖታዊና መሰል መስተጋብሮቻችን ውስጥ በሚገኙ ቀላል በሚመስሉ እምቅ ሀሳቦች ላይ የሚያጠነጥኑ ሲሆኑ፤ ኪናዊ ለዛን በተላበሰ መልኩ በጨዋታ እያዋዛ ልባችንን እንዲኮረኩሩን አድርጎ አቅርቧቸዋል። ቆም ብለን ደግሞ በጥልቀት እንድናስብና እራሳችንን እንድንመረምር ያደርገናል። የምናቡ ርቀትና ገለጻው፣ የሚያነሳቸው ሀሳቦችና የቋንቋ ሀብቱ ሁሌም አፍ ያስከፍታሉ፡፡

አዳም ነዋሪነቱ በካናዳዋ ኦታዋ ይሁን እንጂ ሀገሩን በተመለከተ የምናብ ችግር የለበትም፡፡ እንዲያውም ከሌሎች ደራሲያን በተለየ የኢትዮጵያውያንን ሁለንተናዊ ገጽታ በድርሰቱ ውስጥ እስከ ጥቃቅኗ ቅንጣት ድረስ ወርዶ በዝርዝር ይተነትናል፡፡ በአንድ ወቅት ሀልዮ ከተባለ መጽሄት ጋር በነበረው ቆይታ ይህን ሲያስረዳ ”ከሀገርህ ስትወጣ ራስህን ባዶ አድርገህ አይደለም የምትወጣው፤ ሁሉን ነገር ትውስታህ ውስጥ ትይዛለህ” ብሏል፡፡ አክሎም “የትረካ ቅርጹን ነው እኔ የምፈጥረው፡፡ እንጂ በውስጡ ሊነሱ የሚችሉ ግብረገባዊ እና ሌሎች ነገሮችን እኔ የምፈጥራቸው አይደሉም፤ ዓለም የሚሰጠኝ ነው፡፡ እኔ ሕብረተሰቡ ውስጥ የምገኝ ቢሆንም በምጽፍ ጊዜ ግን ራሴን ነጥዬ ገለል ብዬ ለመመልከት እሞክራለሁ፡፡ ”በማለት የአጻጻፍ መንገዱን ተናግሯል፡፡

የአዳም ረታ የብዕር ስራዎችና ሀሳቦች እንደ አባይ ጅረት የማይነጥፉና ተቀድተው የማያልቁ ግዙፍ ባህር ናቸውና እስቲ ከሰራቸው ስራዎች መሃከል ከመጽሃፉ መጽሃፍ፣ ከገጽ ወደ ገጽ እየዘለልን በጥቂቱ እንቃኛቸው።

“ባዕዳን ከፋፍሎ ሊገዛህ ሲያሴር ካልገባህ እና እንደሰራህ ከተሰራህለት በአእምሮው ስፋት በለጠህ ማለት አይደለም? ለመሆኑ እግዚአብሄር ተፈጥሮንና ሰውን እንዴት ፈጠረው? በቃሉ ትዕዛዝ ነው። ሰው ሁን አለ ሰውም ሆነ። ዛፍ ሁን አለ፤ ዛፍም ሆነ ወዘተ…… ባዕዳን ተጣሉ ሲሉን መጣላት፣ ሩጡ ሲሉን መሮጥ፣ ራቁታችሁን ሁኑ ሲሉን መሆን፣ ሁሉ ነገራችን ከዚያም ዝቅ ያለ ነው። በተለይ በፖለቲካ ሳይንሱ። (የስንብት ቀለማት)

ይህ 960 ገጾችን የያዘው የስንብት ቀለማት መጽሐፍ ራሳችንን በደንብ እንድንመለከት ይጋብዘናል፡፡ ከተወሰኑ ገጾች መሃከልም፦

****

“የእኛ ሰፈር አዋቂ ይገርመኛል፤ ላባ አይቶ ‘አሞራ አየሁ’ የሚል፣ ጅና አይቶ ‘አንበሳ አየሁ’ የሚል፣ ጠብታ ውሃ አይቶ ‘ዶፍ በዚህ አልፎ ነበር’ የሚል፣ ቆዳ ቦት የሚያዘወትር ሰውዬ ቢያይ ‘ወታደር አየሁ’ የሚል ነው። (እነዚህን አይነቶች ፖለቲከኛ አያድርግብዎ!)

***

“የሚያስፈራኝ ደሃነትና የመንገድ መፍረስ አይደለም፡፡ የሥጋና የአጥንቴ መድከም አይደለም፡፡ የዕቃ መወደድ አይደለም፡፡ እግዜር የከፈተውን አፍ ሳይዘጋው ካደረማ፤ እግዜሩም እግዜር እኔም ሰው አይደለሁም።

(የስንብት ቀለማት)

***

“ፍትህ ትወዳለህ፤ ፍትህ እንደጎደለ እያወቅህ ግን ዝም ትላለህ። አየህ ይሄ አንድ ሰው ሲከፋፈል ነው።”

***

“መኖር የሚከብደው ከሰው ጋር ብቻ አይደለም፤ ከዶሮም ጋር ነው። አሁን ከጎረቤቶቼ መጣላት ብፈልግ በ’ዶሮአችሁን ሰብስቡ’ ሰበብ አምባጓሮ መቀስቀስ እችላለሁ። ዋናው እውነት መሆኑ አይደለም። ደፍሮ የመዘባረቅ ነው።”

(መረቅ)

ዛሬ በትንንሽ ምሬት ይሞላና ጊዜ ይለወጣል።

ምንም የረባ ሳይደረግ ሰዎች ወዲያና ወዲህ ይራራቃሉ፣

የተያያዙ ይፈታታሉ፣

ፍቅር የገመዳቸው ይበታተናሉ።

ሁሌም ሚስጥር ነው።

ለምን እንደወደድንም ለምን እንዳልወደድንም ሚስጥር ነው።

(እቴሜቴ_ሎሚ_ሽታ)

****

“ጠዋት እዚህ ፀሐይ ስሞቅ የቆረጥኩት የአውራ ጣቴ ጥፍር ለስንት ጉንዳን እራት ይሆናል? ባላርስም አበላሁ ማለት ነው… ሂሂሂ”

***

አብዮተኛ ውስጥ ቡርዧ አለ፣

ቡርዧ ውስጥ ፊውዳል አለ፣

ፊውዳሉ ውስጥ ገበሬ አለ፣

ገበሬው ውስጥ እረኛ አለ፣

እረኛ ውስጥ ላም አለ፣

ላሟ ውስጥ ሳር አለ፣

ሳሩ ውስጥ አፈር አለ፡፡

ለሊታችን ተቆፍሮ ቢታይ ሁላችንም የምናልመው በእርግጥ አፈር ነው፡፡ ታላቅ የመሰለው፣ የረቀቀ የመሰለው ፅንሰ ሀሳብ ሁሉ በምላስ ሙጫ የቆመ የአፈር እንክብል ነው።” (መረቅ)

****

ይሄ ኀብረተሰብ እኔን ጎድቶኛል።

ቁስሌን መፍጠራቸውን ረስተውታል።

እኔ አልረሳሁትም።

አንድ ጥፊ ሲሰጡት ሌላ የሚጠብቅ

ወይ ጠንካራ ጉንጭ ያለው ነው፣

ወይ ጅል ቅዱስ ነው

(ማሕሌት)

*****

“አዕምሮአቸው ብሩህ ባህላቸው ግን የባርያ የሆኑ ስንት አሉ በእግዜር። ባላምንበትም ልማልበት። አይ አም ኢንተለጀንት ብሎ የሚናገር ግን ዘር ማንዘሩ በቁንጫ የሚበላበት፣ በጎጥ ብራንድ የነደደ ሰው አያበሽቅህም? በ’ነኝ’ ሰው የሚበላለጥ ቢሆን የዓለም ጌታዋ ብዙ ነበር። ‘ውበት ሃሰት ነው ደም ግባትም ከንቱ ነው’ እንደሚባለው አዕምሮም ሃሰት ነው ብልጥነትም ከንቱ ነው። ሁሉ ረጋፊ ነው።” (አፍ)

አዳም ረታ በተለየ የአፃፃፍ ስልቱ እና በስራዎቹ ጥልቀት ከአንባቢያንና የጥበብ አፍቃሪያን አድናቆትን ከማትረፉ ባሻገር ከሀገራችን ጉንቱ ሃያስያን ዘንድ አዎንታዊ ሂስ እና ምስክርነትን ማግኘት ችሏል።

ለምሳሌ ያህል ዳኛቸው ወርቁ ስለ አዳም ረታ ይህንን ብሎለታል፤ በ“አደፍርስ” የኢፒሶዲክ ሕግጋትን አጋምሶ ለማስተዋወቅ ከሞከረ ወዲህ በአማርኛ ሥነ-ጽሑፍ በኢፒሶዲክ ተሟልቶ የተገኘ ድርሰት “ግራጫ ቃጭሎች” ነው። … “ግራጫ ቃጭሎች” ከገፀ-ባህሪው አካልና ሥነ-ልቡና አሳሳል አልፈን ድንቅ ዓላማውን፣ ቋንቋውንና የሕይወት አተረጓጎሙን ስንመለከት የአዳም ረታ እውቀትና ልምድ ጠንከር – ጠጠር ብሎ በመዝገቡ በኩል ሲያስተጋባ ነው የምንመለከተው።…

ደራሲና ገጣሚ አዳም ረታ በተለያዩ ጊዜያት በርካታ ሽልማቶችን ማግኘት የቻለ ሲሆን በዋናነት በ2009 ዓ.ም

ኢስትዌስት ኢንተርቴይንመትና ኤቨንት ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር ለመጀመሪያ ጊዜ ባዘጋጁት “ሆሄ” የሥነ ፅሑፍ ሽልማት ላይ በምርጥ የዓመቱ ረዥም ልቦለድ ዘርፍ “የስንብት ቀለማት” በተሰኘው መጽሃፉ ተሸላሚ ለመሆን በቅቷል።

ሙሉጌታ ብርሃኑ

አዲስ ዘመን ጥቅምት 3 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You