ድንበር ተሻጋሪው ጀግና በዛሬዋ ቀን

አብዛኞቹ የኢትዮጵያ አርበኞች ታሪክ ከዓድዋ እና ከአምስት ዓመቱ የጣሊያን ቆይታ ጋር ይገናኛል። ኢትዮጵያ በፋሺስት ኢጣሊያ በተወረረችበት ወቅት ለአገራቸው ሉዓላዊነት ታግለው አኩሪ የጀግንነት ገድል ካስመዘገቡት አርበኞች መካከል አብዛኞቹ ድል ያስመዘገቡት እዚሁ ኢትዮጵያ ምድር ላይ ነው፡፡

ከዚህ ባሻገር ደግሞ ኢትዮጵያ የፋሺስቱን የቤኒቶ ሙሶሎኒን መንግሥት እዚያው አገሩ፣ ኢጣሊያ ላይ ተዋግተው ውርደትን ያከናነቡ ጀግኖችም ባለቤት ናት። ይህን ደማቅ ገድል ከፈፀሙ ኢትዮጵያውያን ጀግኖች መካከል የዚህ ሳምንት ክስተት የሆኑት ኮሎኔል አብዲሳ አጋ አንዱ ናቸው፡፡ በዛሬው ሳምንቱን በታሪክ ዓምዳችን ከ47 ዓመታት በፊት በዚህ ሳምንት ልክ በዛሬዋ ቀን ጥቅምት 3 ቀን 1970 ዓ.ም ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩትን ኮሎኔል አብዲሳ አጋን እናስታውሳለን፡፡ ከዚያ በፊት እንደተለመደው በዚህ ሳምንት የተከናወኑ ሌሎች የአገር ውስጥ እና ዓለም አቀፍ ክስተቶችን እናስታውስ፡፡

እንደ ዓድዋ፣ አርበኞች ቀን፣ ካራማራ… የመሳሰሉት የድል በዓላት ሲደርሱ በሬዲዮና በቴሌቪዥን ዘፈኑ በተደጋጋሚ የሚሰማው፣ የኮሪያው ዘማች እና የክራሩ ጌታ፤ ‹‹ፋኖ ፋኖ›› በተባለውና በሌሎች ተወዳጅ ሙዚቃዎቹ የሚታወቀው የክራር ተጨዋች ድምፃዊ ካሣ ተሰማ ያረፈው ከ51 ዓመታት በፊት በዚህ ሳምንት ጥቅምት 1 ቀን 1966 ዓ.ም ነበር፡፡

ንጉሰ ነገሥት ዳግማዊ አጼ ምኒልክ መስከረም 7 ቀን 1888 ዓ.ም የውጫሌ ውል እንደማይቀበሉና ሁሉም ኢትዮጵያውያን ሀገራቸውን ከወራሪ ጠላት እንዲከላከሉ የሚያሳስብ ታሪካዊ አዋጅ ካስነገሩ በኋላ፣ ጦራቸውን ይዘው ከአዲስ አበባ ወደ ዓድዋ ጉዞ የጀመሩት ከ129 ዓመታት በፊት በዚህ ሳምንት ጥቅምት 2 ቀን 1888 ዓ.ም ነበር፡፡

አንጋፋውና ተወዳጁ አርቲስት ፍቃዱ ተክለማርያም የተወለደው ከ69 ዓመታት በፊት በዚህ ሳምንት ጥቅምት 2 ቀን 1948 ዓ.ም ነበር፡፡

ገጣሚ፣ ሰዓሊ፣ ቀራፂ፣ ሙዚቀኛ፣ ፖለቲከኛ፣ የፎቶግራፍ ባለሙያ፣ ነጋዴ፣ ሹፌር፣ ባለቅኔ፣ የመኪና ጠጋኝ (መካኒክ) የነበሩት ነጋድራስ ተሰማ እሸቴ ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩት ከ60 ዓመታት በፊት በዚህ ሳምንት ጥቅምት 3 ቀን 1957 ዓ.ም ነበር፡፡

አሁን በዕለቱ በዝርዝር ወደምናየው የኮሎኔል አብዲሳ አጋ ታሪክ እንለፍ፡፡

አብዲሳ አጋ የተወለዱት በ1911 ዓ.ም ወለጋ ውስጥ ነው፡፡ ዕድሜያቸው ለትምህርት ሲደርስም ወደ ነጆ ሚሲዮን ትምህርት ቤት አምርተው ፊደል ቆጥረዋል። ይሁን እንጂ ይህ የትምህርት ጅምራቸው ብዙ ርቀት መጓዝ ሳይችል ቀርቶ ስድስተኛ ክፍል ላይ ተገታ፡፡ ወላጅ አባታቸው ባላጠፉት ጥፋት ተወንጅለው ለእስራት በመዳረጋቸው ምክንያት አባታቸውን ከእስር ለማስፈታት ላይ ታች ሲሉ በትምህርታቸው መቀጠል ሳይችሉ ቀሩ። አባታቸው ፍትሕ እንዲያገኙ የጀመሩት ጥረትም ሊሳካላቸው አልቻለም፡፡

ወታደር ለመሆን ምኞት ያደረባቸው አብዲሳ፣ ለንጉሰ ነገሥት ቀዳማዊ አጼ ኃይለሥላሴ ቅርብ የሆኑ የአባታቸው ወዳጅ እንደ አማላጅ ወደ ንጉሰ ነገሥቱ ተልከው ስለ አብዲሳ ያቀረቡት ጥያቄ ተቀባይነት አገኘና ታዳጊው አብዲሳ ሆለታ ወደሚገኘው ገነት ጦር ትምህርት ቤት ገብተው ስልጠና ወሰዱ፡፡

ያ የወሰዱት ሥልጠና እነሆ የአገራቸውን ነፃነት ለማስጠበቅ አገለገለ፡፡ ኢጣሊያ ዓድዋ ላይ የተከናነበችውን ሽንፈት ለመበቀል ለአርባ ዓመታት ያህል ስትዘጋጅ ከኖረች በኋላ በ1928 ዓ.ም ኢትዮጵያን ወረረች፡፡ ወቅቱም አብዲሳ ከገነት ጦር ትምህርት ቤት የአስር አለቃነት ማዕረግ ያገኙበት ጊዜ ነበር፡፡ ታዳጊው አብዲሳም ገና በልጅነታቸው፣ የኢትዮጵያን ጦር በመቀላቀል ሀገራቸውን ማገልገል ጀመሩ። ከወራሪው የፋሺስት ኢጣሊያ ጦር ጋር ፍልሚያ የጀመሩት ገና የ16 ዓመት ታዳጊ ሆነው ሳለ ነበር፡፡

አብዲሳ ከሌሎች የገነት ጦር ትምህርት ቤት ሰልጣኞች ጋር ወደ ወለጋ በመዝመት ከፋሺስት ጦር ጋር ውጊያ ገጠሙ፡፡ በውጊያውም ወቅት መትረየስ ተኳሽ ሆነው የኢጣሊያ አውሮፕላኖችን እየመቱ ጥለዋል። ጣሊያኖችም የአብዲሳ ድርጊት ባደረሰባቸው ኪሳራ ከመበሳጨት አልፈው መገረም ጀመሩ፡፡ ጣሊያኖችም ኃይላቸውን በማጠናከር አብዲሳን ለመማረክ ሞክረው ሳይሳካላቸው ቀረ፡፡ አብዲሳን ጨምሮ 60 ያህል የተዋጊዎች ቡድን አባላት የፀረ ፋሺስት ትግሉን ለመቀጠል ወደ ጎጀብ በማምራት ከራስ እምሩ ጦር ጋር በመቀላቀል ከጠላት ጋር ግንባር ለግንባር ገጠሙ፡፡ በዚህ ወቅት አብዲሳ በውጊያ ላይ ሳሉ የመቁሰል አደጋ አጋጠማቸውና ተማረኩ፡፡ ሕክምና ተደረገላቸውና አዲስ አበባ ውስጥ በሚገኝ እስር ቤት ታሰሩ፡፡ ይሁን እንጂ ከመቁሰላቸው ባሻገር በጠላት መታሰራቸውን ማመንም መቀበልም ያቃታቸው ጀግናው ሰው፣ የእስር ቤቱን ጠባቂ መትረየስ ነጥቀው አመለጡ፡፡

የካቲት 12 ቀን 1929 ዓ.ም በኢትዮጵያ የፋሺስት ኢጣሊያ እንደራሴ የነበረውን ማርሻል ሩዶልፎ ግራዚያኒንና ሌሎች የፋሺስቱን አስተዳደር ባለስልጣናት ለመግደል በተደረገው ሙከራ በርካታ ኢትዮያጵውያን በግፍ ተጨፈጨፉ፡፡ አብዲሳም ኢትዮጵያውያንን በግፍ ሲጨፈጭፉ ከነበሩ ጥቁር ሸሚዝ ለባሽ ወታደሮች መካከል የአንዱን ቡድን አባላት ከነመኪናቸው በመትረየስ አጋዩዋቸው፡፡ ቀድሞም ቢሆን እንዲታሰሩ ተወስኖባቸው እየተፈለጉ የነበሩት አብዲሳ፣ ይህ ድርጊታቸው ሲሰማ በቁጥጥር ስር እንዲውሉ ፍለጋው ተጠናከረባቸውና ተያዙ፡፡ እርሳቸውና ሌሎች ግለሰቦችም በእስር ቤት በከባድ ስቃይ ውስጥ ከቆዩ በኋላ ‹‹ጀግኖችን ስታገኙ ወደ እኔ ላኩልኝ›› ብሎ ያዘዘውን ቤኒቶ ሙሶሊኒን ለማስደሰት በወቅቱ የኢጣሊያ ቅኝ ግዛት በነበረው የሶማሊያ ክፍል በኩል ወደ ኢጣሊያ ተወስደው ለሌላ እስር ተዳረጉ።

በእስር ቤት በነበሩበት ወቅት ካጋጠሟቸው ክስተቶች መካከል ስለ አብዲሳ አጋ የሕይወት ጉዞ በሚተርከውና ‹‹በኢጣሊያ በረሃዎች›› በተሰኘው መጽሐፍ ላይ ይህ ተጽፏል፡፡

‹‹አንዲት የእንግሊዝ አውሮፕላን እኛ በታሰርንበት ወህኒ ቤት ላይ ስታንዣብብ ከቆየች በኋላ በተለያዩ ቋንቋዎች የተፃፈ ወረቀት በተነች፡፡ እኔም ወረቀቱን አንስቼ ኪሴ ውስጥ ከተትኩት፡፡ ይህን ተግባሬን የተመለከተ አንድ እስረኛ ለእስር ቤቱ ጠባቂዎች ተናገረ፤ ጠባቂዎቹም ወረቀቱን እንድሰጣቸው ጠየቁኝ፤ እኔ ግን አሻፈረኝ አልኩ፡፡ በዚህ ጊዜ እኔም ከጠባቂዎቹ መካከል አንዱን በቦክስ ስመታው መሬት ላይ ተዘረረ፡፡››

በአብዲሳ አጋ ኃይለኛነት የተጨነቁት የእስር ቤቱ ኃላፊዎችና ጠባቂዎችም አብዲሳን ለብቻቸው እንዲታሰሩ አደረጉ፡፡ በዚህ ጊዜ ነበር የኢጣሊያ መንግሥት ጥርስ እንደነከሰባቸው ያወቁትና ከእስር ቤት ማምለጥ እንዳለባቸው የወሰኑት፡፡

አልሸነፍ ባይነት መለያቸው የሆነው ጀግናው አብዲሳ፣ ሁሊዮ ከተባለ ዩጎዝላቪያዊ የጦር እስረኛ ጋር በመተባበር ከባድ ጥበቃ ከሚደረግበት እስር ቤት ለማምለጥ ማሰላሰል ጀመሩ። ተሳክቶላቸው ቢያመልጡ እንግዳ (ባዕድ) ሀገርና ሕዝብ እንደሚጠብቃቸው ቢያውቁም፣ በነጻነታቸውና በሀገራቸው የማይደራደሩት ጀግናው የኢትዮጵያ ልጅ አብዲሳ አጋ፣ እስር ቤት ውስጥ የተሰጣቸውን የብርድ ልብስ ቀዳደው በመቀጣጠልና የእስር ቤቱ ጠባቂዎች ላይ ጥቃት በመፈፀም ሌሎች እስረኞችን በመያዝ ከእስር ቤት አመለጡ።

ከዚያ በኋላ ግን ጀግናው አብዲሳ የመረጡት ሽሽት አልነበረም፡፡ ወደ ሳን ቪቺኖ ተራራ በመውጣት ስለቀጣዩ እቅዳቸው አሰላሰሉ፡፡ ከጥቂት ቀናት በኋላም በማታ ወደ እስር ቤቱ በመመለስ ጠባቂዎቹ ላይ ጥቃት በመፈፀም የቀሩትን እስረኞች በመሉ ነፃ ማውጣት ቻሉ። ነፃ የወጡት እስረኞችም ከእስር ቤቱ ጠባቂዎች በወሰዱት መሳሪያ በመታገዝ የአማፂያንን ጦር አደራጁ፤ ጦሩን እንዲመሩ የተመረጡትም ጀግናው አብዲሳ አጋ ነበሩ። በመቀጠልም የተለያዩ የኢጣሊያ ወታደራዊ ሠፈሮች ላይ ጥቃት በመፈፀም ወራሪዎቹ ጣሊያኖች ኢትዮጵያ ውስጥ ከነበረው የአርበኞች እንቅስቃሴ ያልተናነሰ ጥቃት በሀገራቸው ያጋጥማቸው ጀመር። ‹‹አብዲሳ አጋን ማርካችሁ አምጡልኝ›› ተብለው ከሙሶሎኒ የሚላኩት የኢጣሊያ የጦር አዛዦች በአብዲሳ እየተማረኩ ቀሩ፡፡

በአራት ክፍለ ጦሮች ተከፍሎ የፋሺስትን ጦር እየተፋለመ በነበረውና በአብዲሳ አጋ በሚመራው ጦር ከባድ ኪሳራ የደረሰባቸውና እጅግ የተረበሹት ጣሊያኖችም በርካታ ስጦታዎችን ቃል በመግባት ውጊያውን እንዲያቆሙና የነሱን ጦር እንዲቀላቀሉ ለመኗቸው። የአገራቸው የኢትዮጵያ ሉዓላዊነት መደፈር ያንገበገባቸው አብዲሳ ግን ከፋሺስት ሥርዓት ጎን እንደማይቆሙ አስረግጠው በመናገር ጥያቄውን ውድቅ አድርገው ጣልያኖችን በሀገራቸው ማስጨነቁን ነበር ቀጠሉበት።

የሁለተኛው የዓለም ጦርነት ሲጀመር የጀርመኑ ናዚ አዶልፍ ሂትለርና የኢጣሊያው ፋሺስት ቤኒቶ ሙሶሊኒ በአንድ ወገን ተሰልፈው ነበር፡፡ እንግሊዝ፣ ፈረንሳይ፣ አሜሪካ፣ ሶቭየት ኅብረትና ሌሎች ሀገራት ደግሞ ‹‹የኅብረት ኃይሎች (Allied Powers)›› የሚል የጦር ኅብረት መስርተው ጀርመንንና ጣሊያንን እንዲሁም የፋሺስቶቹንና የናዚዎቹን አጋሮች መውጋት ጀመሩ። በወቅቱም የዚህ ‹‹የኅብረት ኃይሎች›› ጦር አባላት ጣሊያኖችን እያስጨነቋቸው የነበሩትን የአብዲሳን ዝና በመስማታቸው ባላንጣቸውን ኢጣሊያን ለማዳከም በማሰብ ለአብዲሳ ጦር የቁሳቁስ ድጋፎችን ማድረግ ጀመሩ።

‹‹ከእኛ በላይ ላሳር›› ያሉት ፋሺስቶቹና ናዚዎቹም ከኅብረቱ ኃይሎች የሚሰነዘሩባቸውን ጥቃቶች መመከት ሳይችሉ ቀርተው ለመሸነፍ ተገደዱ፡፡ ከኅብረቱ ኃይሎች ባገኙት ድጋፍ እየታገዙ የፋሺስቱን መንግሥት በአገሩ አፈር ላይ የሽንፈት ማቅ ማልበስ የጀመሩት አብዲሳ አጋ፣ የፋሺስቶቹና የናዚዎቹ ቡድን ተሸንፎ የኢጣሊያዋ ዋና ከተማ ሮም በአሜሪካና በእንግሊዝ በሚመራው ጦር ቁጥጥር ስር ስትወድቅ አብዲሳ አጋ የሚመሯቸውን ከተለያዩ አገር የተውጣጡ ወታደሮች በሙሉ በክንዳቸው ላይ የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ እንዲያስሩ በማድረግ የአገራቸውን መለያ እያውለበልቡ ሮም ከተማ ሲገቡ በኅብረቱ ጦር ትልቅ አቀባበል ተደርጎላቸዋል።

ከዚያም በኋላ ከተጨማሪ ወታደሮች ጋር በኅብረቱ ኃይሎች የሚመራ ጦር መሪ በመሆን የናዚውን የአዶልፍ ሂትለርን ጦር በማሸነፍ ጀርመንን ከናዚዎች አገዛዝ ለማላቀቅ በሚደረገው የመጨረሻ ውጊያ ላይ ተሳትፈው ግዳጃቸውን በሚገባ መወጣት ችለዋል፡፡ በርካታ የጀርመን ከተሞችንም ከናዚዎች ነፃ አወጡ፡፡ በጦርነቱ ሂደትም አብዲሳ አጋ የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ ከእጃቸው ላይ ሳይለዩ መቆየታቸው ለአገራቸው ኢትዮጵያ የነበራቸውን ፍቅርና አክብሮት ያሳዩበት አጋጣሚ ነበር።

ከጦርነቱ መገባደድ በኋላም የእንግሊዝ፣ የካናዳ እና የአሜሪካ መንግሥታት አብዲሳ ጦራቸውን ተቀላቅለው እንዲቀጥሉ ዜግነት መስጠትን ጨምሮ በርካታ ጥቅማ ጥቅሞችን አቀረቡላቸው። አብዲሳ ግን ኢትዮጵያ ምንም ያህል ድሃ ብትሆንም ሕዝባቸውን እና የአገራቸውን መንግሥት ጥለው ሌላ አገር የማገልገል ፍላጎት እንደሌላቸው እንደማይሄድ አስረግጠው በመናገር የኃያላኑን መንግሥታት ጥያቄ ሳይቀበሉ ቀሩ።

አብዲሳ ‹‹የእኛን አገር ዜግነት ሰጥተንህ የእኛን ጦር ተቀላቀል›› የሚለውን የኃያላኑን መንግሥታት ጥያቄ አለመቀበላቸው ያስከፋቸው የኅብረቱ ጦር አባላት ‹‹ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት መጠናቀቅ በኋላ ጣሊያናውያን ላይ የበቀል እርምጃ እየወሰደ ነው›› ብለው የሐሰት ክስ ከሰሷቸውና ለእስር ተዳረጉ፤ እስራትም ተፈረደባቸው፡፡ እንግዲህ የዚህ ሁሉ የውሸት ውንጀላ ምክንያቱ አብዲሳ ‹‹በኢትዮጵያ አልደራደርም!›› በማለታቸው ነው፡፡ በኋላም እስራቱ ወደ ገንዘብ መቀጮ ተለውጦላቸው ከእስር ተለቀቁ፡፡ የሜዳሊያና የክብር መሸኛ ተሰጥተው ወደ ኢትዮጵያ ተመለሱ፡፡

አዲስ አበባ እንደደረሱም ንጉሰ ነገሥቱ ዘንድ ቀረቡ፡፡ ንጉሰ ነገሥቱም ከነ ራስ አበበ ጋር ተነጋገሩና ‹‹ሆለታ ገነት ጦር ትምህርት ቤት ሄዶ ኮርስ ይውሰድ›› ብለው ወሰኑ። ይሁን እንጂ አብዲሳ ካላቸው ልምድና ከፈፀሟቸው ጀብዱዎች አንፃር ይህ ውሳኔ ተገቢነቱ አጠያያቂ ስለመሆኑ በርካቶች ይናገራሉ፡፡

ለጉብኝት የሚመጡ የውጭ አገራት መሪዎች (የሲቪል ባለስልጣናትና የጦር መሪዎች) ስለ አብዲሳ አጋ ጀግንነትና ዝና ሲያወሩ የሰሙት ንጉሰ ነገሥት ቀዳማዊ አፄ ኃይለ ሥላሴ፣ ጀግናውን ሰው ወደ ቤተ መንግሥታቸው በማምጣት በኮሎኔልነት ማዕረግ የንጉሡ ጥበቃ ቡድን አባል አድርገው ሾሟቸው።

ኮሎኔል አብዲሳ አጋ ከፋሺስት ኢጣሊያ ጦር ጋር ሲፋለሙ በሰውነታቸው ውስጥ የገቡት ጥይቶች አገራቸውን በቅንነትና በታማኝነት ከማገልገል አላገዷቸውም፡፡ በ1956ቱ የሶማሊያ ወረራ ወቅትም ለኢትዮጵያ ሉዓላዊነትና ክብር አኩሪ ታሪክ ሰርተዋል። በወቅቱ በቶጎጫሌ ግንባር የ26ኛ ክብር ዘበኛ ሻለቃ የአንደኛ ሻምበል አዛዥ ሆነው የሶማሊያን ወራሪ ኃይል ተፋልመዋል፡፡

በመጨረሻም ለማመን የሚከብዱ አኩሪ የጀግንነት ገድሎችን የፈጸሙት ጀግናው ኮሎኔል አብዲሳ አጋ፣ ጥቅምት 3 ቀን 1970 ዓ.ም ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል፡፡ እነሆ ወደር የለሽ ጀግንነታቸው ሲዘከር ይኖራል!

ዋለልኝ አየለ

 

አዲስ ዘመን ጥቅምት 3 ቀን 2017 ዓ.ም

 

Recommended For You