ድንገተኛ ታዋቂነት ብቻውን ሲመጣ

‹‹አታሞ በሰው እጅ ያምር፤ ሲይዙት ያደናግር›› የሚባለው አባባል በየአጋጣሚዎች ልንጠቀመው የሚያስገድድ ገላጭ አባባል ነው። ‹‹ለተቀማጭ ሰማይ ቅርቡ ነው›› የሚለውም ይተካዋል። የእነዚህ ሁለት ምሳሌያዊ አነጋገሮች ትርጉም፤ እኛ ልናደርገው የማንችለውን ነገር፣ ሌላ ሰው ሲያደርገው ግን እንተቻለን፣ እንወቅሳለን ለማለት ነው።

ታዋቂ ሰዎች መድረክ ላይ ወይም ሚዲያ ላይ ቀርበው በሚናገሩት ነገር አጀንዳ ሲሆኑ ይስተዋላል። ተቀምጦ የሚከታተላቸው ሰው ነገሮችን ለማሰላሰል፣ ዓውዳዊ ትርጉም ለመስጠት፣ መባል ያለበትንና የሌለበትን ለማገናዘብ የተረጋጋ ቀልብ አለው። ስለዚህ የተናገሯትን ሁሉ ይመነዝራል። ተናጋሪው ግን በተለይም የቀጥታ ሥርጭት ከሆነ፤ በሆነ ቅጽበታዊ ስሜት ሊሳሳት ይችላል። የፕሮዳክሽን ቀረጻም ቢሆን በየመሐሉ ‹‹ይሄን ቁረጡልኝ›› አይልም። የሚቆረጠውንና የማይቆረጠውን የሚወስነው የሚዲያው ዝግጅት ክፍል ነው። እንደ ሚዲያው ባሕሪ ደግሞ አነጋጋሪ የሆነ ነገር የሚፈልግም ይኖራል፤ ያንን ርዕስ ያደርገዋል። በአጭሩ ታዋቂ ሰዎች ሰው ናቸውና በቅጽበታዊ ስሜት ሊሳሳቱ ወይም መባል የሌለበት ነገር ሊናገሩ ይችላሉ ለማለት ነው።

ዋናው ጉዳዬ ግን ብዙ ታዋቂ ሰዎች ታዋቂነት ብቻውን የመጣባቸው መሆኑን ነው። ምንም እንኳን በቅጽበታዊ ስሜት ማንኛውም ሰው አግባብ ያልሆነ ነገር የሚያስብና የሚያደርግ ቢሆንም፤ ታዋቂነት ሲመጣ ግን ተደራሽነት ይሰፋልና ጥንቃቄ ያስፈልጋል፤ አዋቂ ለመሆን መዘጋጀት ያስፈልጋል።

ከወቀሳው በፊት ግን አንድ ነገር ላድንቅ። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የማያቸው ወጣቶች አስተዋይነታቸው፣ ትሕትናቸው፣ ጥንቃቄያቸው ይገርመኛል። በሆነ አጋጣሚ ታዋቂ ሆነው ቴሌቪዥን ላይ ሲቀርቡ፤ የሆነ ስህተት ሠርተው ይህ የተወደደላቸው ታዋቂነት እንዳይበላሽ እያልኩ እሳቀቃለሁ። ሲናገሩ ግን ምሑራን ላይ እንኳን የማይታይ ትሕትና እና ጥንቃቄ ያላቸው ናቸው። በተለይም አንዳንዱ ጠያቂ የተመልካች ቀልብ ለመያዝ ሲል ወይም ፕሮግራሙን ለማስተዋወቅ ሲል የማይጠየቅ ጥያቄ ይጠይቃል። በዚህ ጊዜ ልጆች በጥንቃቄና በጥበብ የሚወጡበት መንገድ ያስደንቀኛል።

እዚህ ላይ አንድ የሥራ ባልደረባዬ በቅርቡ ያጋራኝን ሀሳብ ልጨምር። ‹‹የ12ኛ ክፍል ከፍተኛ ውጤት ያመጡ ተማሪዎች ከውጤታቸው በላይ የሚያስገርመኝ አስተዋይነታቸው ነው›› ነበር ያለኝ። እኔም በቀረቡበት ሚዲያ ሁሉ ልብ ብዬ ሳይ ከአካዳሚ ውጤታቸው በላይ አስተዋይነታቸው አርዓያ ይሆናል። በልማዳችን እውቀት የምንለው ሒሳብ፣ ኬሚስትሪ፣ ፊዚክስ… በአጠቃላይ አካዳሚያዊ በሆኑ የትምህርት አይነቶች ነው። ዳሩ ግን ሁለገብ የሆነ አስተዋይነትና ግንዛቤ ነው ብቁ የሚያደርጋቸው።

አንዳንድ በዘፋኝነት ወይም በሆነ ተሰጥዖ ተፅዕኖ ፈጣሪ የሆኑ ሰዎች ሚዲያ ላይ ቀርበው ሲናገሩ ስሰማ ያስደምሙኛል። በዚህኛው ሙያ ውስጥ ሆነው እንዴት ይሄኛውን አወቁት እያልኩ እቀናባቸዋለሁ። አስተዋይ ናቸው፤ ጠንቃቃ ናቸው። መባል ያለበትንና የሌለበትን እንደ ዓውዱ የሚለዩ ናቸው።

በተቃራኒው ግን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ አሳቃቂ የሆነው ታዋቂነት በድንገት የመጣባቸው ሰዎች ነገር ነው። አዋቂነት ሳይኖራቸው በሆነ ድንገተኛ አጋጣሚ ታዋቂነት ይመጣባቸዋል። እነዚህ ሰዎች በቀረቡበት ሚዲያና መድረክ ሁሉ የሚያሳቅቅ ንግግር ያደርጋሉ፤ በእርግጥ አንዳንዶቹ መነጋገሪያ መሆኑን ስለሚፈልጉትም ነው ይባላል።

ታዋቂ ሲሆኑ ብዙ ልብ መባል ያለባቸው ነገሮች አሉ። ምክንያቱም ታዋቂ ሲሆኑ ብዙ ሚዲያ እና መድረክ ላይ የመቅረብ ዕድሉ ይመጣል። እነዚህ መገናኛዎች ላይ ሲቀረብ ተደራሽነት ይሰፋል፤ በብዙዎች ዓይንና ጆሮ መግባት ይመጣል። ስለዚህ ‹‹ወደ ሕዝብ ስሄድ ምን መሆን አለብኝ?›› ለሚለው ከፍተኛ የሆነ ቅድመ ዝግጅት ያስፈልጋል። በየዘርፉ ያሉ ጓደኞቻቸውን ማማከርና መጠየቅ ያስፈልጋል። ማንበብና ሚዲያዎችን መከታተል ያስፈልጋል። በትንሹም ቢሆን ሀገራዊ ጉዳዮችን ማወቅ፣ ቢያንስ ጉልህ ጉልህ የሆኑትን ታሪካዊ ክስተቶችንና የሀገር ባለውለታዎችን ማወቅ ያስፈልጋል።

ችግሩ ግን ታዋቂነት በድንገት ለመጣባቸው ሰዎች ከዜሮ መጀመር ነውና አስቸጋሪ ያደርገዋል። በአስተዳደጋቸው ያልነበረ ነገር ከሆነ፤ በድንገተኛ ታዋቂነት አዋቂነት ሊመጣ አይችልም፤ ምክንያቱም ታዋቂ ከሆኑ በኋላ ጊዜ የላቸውም። በብዙ ነገር ይዋከባሉ፤ የሚያስተናግዱት ሰው ይበዛል። ስለዚህ አላዋቂ ሆኖ ለመቅረት ይገደዳሉ ማለት ነው።

ታዋቂነት በድንገት የመጣባቸው ሰዎች በየመድረኩና በየሚዲያው በሚሠሩት ስህተት ሲወቀሱ፤ ብዙ ሰዎች ‹‹ምን አገባችሁ! አርፋችሁ የራሳችሁን ኑሮ ኑሩ፣ ምቀኝነት ነው..›› ይላሉ። ‹‹የወፍ ምስክሯ ድንቢጥ›› መሆኑ ነው። አንድ ሰው በማኅበራዊ ጉዳዮች ላይ አያገባህም አይባልም። ሀገራዊ ጉዳይ የሚሆኑት እነዚህ ትንንሽ የሚመስሉ ማኅበራዊ ጉዳዮች ናቸው።

ከምንም በላይ ግን አንድ ልብ ያልተባለ ነገር አለ። እነዚህ ዕውቀትና ግንዛቤ የሌላቸው ታዋቂ ሰዎች ዝም ከተባሉ ነገ የሀገራዊ ጉዳይ ተሳታፊ ሆነው ይመጣሉ። በአንዳንድ መድረኮችም አይተናል፤ መንግሥት የሕዝብን ቀልብ የያዘ መስሎት በድንገት ታዋቂ የሆኑ ሰዎችን በአንዳንድ ቤተ መንግሥታዊ ጉዳዮች ሳይቀር ተሳታፊ ሲያደርግ ይስተዋላል። የሚፈለገው ፊታቸው መታወቁ ብቻ ነው ማለት ነው?

እነዚህ ድንገተኛ ታዋቂዎች ዝም ከተባሉ ለትልልቅ ኃላፊነቶች ይታጫሉ፣ ይመረጣሉ ማለት ነው። ብዙ ጊዜ የምናየው ችግርም ይሄው ነው፤ ከብቃት ይልቅ ፊታቸው በስክሪን ስለታወቀ ብቻ ለሆነ ኃላፊነት መምረጥ፣ አማካሪ ማድረግ።

ታዋቂ ሲሆኑ አማካሪ ያስፈልጋል። አማካሪ ማለት የግድ በከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት ደረጃ ያለው አይነት ማለት አይደለም። ለሚፈልጉት ዘርፍ ቅርበት ያለውን ሰው መጠየቅ ማለት ነው። ዳሩ ግን እነርሱ ማንን ፈርተው ያማክራሉ? እንደፈለጋቸው ይሳሳታሉ፣ እንደፈለጋቸው ያደርጉታል። ማኅበራዊና ሀገራዊ ጉዳይ ካበላሹ በኋላ ‹‹በእኔ ሕይወት ማን ምን አገባው!›› ይላሉ፤ በአንተ(አንቺ) ሕይወት ማንም አያገባውም፤ በሚናገሩት ነገር ግን ያገባናል።

አንዳንዶቹ ደግሞ የታዋቂነትን ባሕሪ የሚያውቁት አይመስልም። የሆነ ነገር ሲያጋጥማቸው ታዋቂ ስለሆኑ ያጋጠማቸው መሆኑን አያጤኑትም።

ለምሳሌ፤ ብዙ ታዋቂ ሰዎች ላይ የታዘብኩት ነገር፤ በስማቸው የሚከፈት የማኅበራዊ ገጽ ሲያስተባብሉ ሲሳደቡ ነው። በስማቸው አካውንት የከፈቱ ሰዎችን በነውር ቃላት ይሳደባሉ። እርግጥ ነው በታዋቂ ሰው ስም ሐሰተኛ አካውንት መክፈት ነውር ነው፤ በራስ አለመተማመን ነው። ይሄ ነውር መሆኑ ለማንም ግልጽ ነው። የታዋቂዎቹ ችግር ግን ታዋቂ ስለሆኑ ያጋጠመ መሆኑን ልብ አለማለታቸው ነው። ይህ በሌላውም ዓለም ያለ ነው። የእነርሱ አለመሆኑን ወይም ማኅበራዊ ሚዲያ እንደማይጠቀሙ ማሳወቅ በቂ ሆኖ ሳለ፤ የእርግማን መዓት ሲያወርዱ ይሰማል። እደግመዋለሁ! የችግሩ አሳሳቢነት ጠፍቶኝ አይደለም፤ ዳሩ ግን ታዋቂ ሲሆኑ የሚያጋጥም ነውና ጨጓራቸውን መላጥ አይገባቸውም።

እዚህ ላይ ግን ተከታዮችም ልብ ማለት ያለባቸው በታዋቂ ሰው ስም የተከፈተ የማኅበራዊ ገጽ ሁሉ የዚያ ሰው ነው ወይም አስተማማኝ ነው ማለት አይደለም።

በአጠቃላይ ታዋቂነት ሲያጋጥም አዋቂነትና አስተዋይነት ሊጨመርበት ይገባል።

ዋለልኝ አየለ

 አዲስ ዘመን ጥቅምት 2/2017 ዓ.ም

 

 

Recommended For You