በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች የሚገኙ ማዕድናትን የመለየትና አልምቶ ለመጠቀም የሚያስችሉ ሥራዎች በሰፊው እየተከናወኑ ይገኛሉ፡፡ ከዚህ አኳያ በማእድን ሚኒስቴርና ተጠሪ ተቋማቱ እየከተናወነ ካለው ተግባር በተጨማሪ በዩኒቨርሲቲዎች እና ከዩኒቨርሲቲዎች ጋር የሚከናወኑ ተግባሮችም ይጠቀሳሉ፡፡
ዩኒቨርሲቲዎች በማእድን ዘርፉ ጥናትና ምርምር በማድረግ የዘርፉን እምቅ ሀብት አልምቶ ለመጠቀም አስቻይ ሁኔታዎችን በማመላከት ላይ ይገኛሉ፡፡ በማዕድን ዘርፍ ጥናትና ምርምር በማድረግ የድርሻቸውን እየተወጡ ካሉ ዩኒቨርሲቲዎች መካከል የወሎ ዩኒቨርሲቲ አንዱ ነው፡፡ ዩኒቨርሲቲው በደቡብ ወሎ ደላንታ አካባቢ በስፋት በሚገኘው የኦፓል ማዕድን ላይ ጥናት በማድረግ የምርምር ሥራ ሰርቷል፡፡ በተለይም በደላንታ አካባቢ ባደረገው ጥናት የዘርፉን እምቅ ሀብቶች ጠቁሟል፤ ማእድኑን በማልማት ሂደት እያጋጠሙ ያሉ ችግሮችን በመለየትም መፍትሄዎችንም ማመላከት ችሏል፡፡
በወሎ ዩኒቨርሲቲ የጂኦሎጂ ትምህርት ክፍል ኃላፊ ዶክተር ሲሳይ አወቀ እንዳሉት፤ በዩኒቨርሲቲው አስተባባሪነት በደቡብ ወሎ አካባቢ የሚገኙ የማዕድን አይነቶች ልየታ የሚል ቡድን ተዋቅሮ የተለያዩ ሥራዎች ተሰርተዋል፡፡ ጥናቱ ትኩረት ካደረገባቸው መካከል በደቡብ ወሎ ደላንታ ወረዳ በስፋት የሚገኘው የኦፓል ማዕድን አንዱ ነው፡፡
እሳቸው እንዳሉት፤ ጥናቱ በማዕድን ዘርፉ በተለይም በኦፓል ላይ የሚስተዋሉ ችግሮችን መለየትና ማህበረሰቡን ተጠቃሚ ማድረግ የሚችሉ አሰራሮችን እንዴት መፍጠር ይቻላል የሚሉና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ ትኩረት አድርጓል፡፡
በመጀመሪያ በአካባቢው ያለውን የኦፓል ማዕድን ማህበረሰቡ አልምቶ ለመጠቀም ያጋጠሙት ችግሮች ምንድናቸው የሚሉትን መለየት ተችሏል፡፡ በዚህም ማዕድኑን ለማውጣት ቁፋሮ የሚደረግበት መንገድ አንዱና ዋነኛው ችግር እንደሆነ ተመላክቷል፡፡ ቁፋሮው የሚከናወነው ባህላዊ በሆነ መንገድ፣ በተጣበበና ምቹ ባልሆነ ሁኔታ ነው፡፡ በዚህ ሁኔታም ከስድስት መቶ እስከ ሰባት መቶ ሜትር ወደ ውስጥ ይቆፈራል፡፡ ይህም ሕይወት ማጣትን ጨምሮ ለጤና መታወክና ለሌሎች አደጋዎች ተጋላጭ እንደሚያደርግ ጥናቱም አመላክቷል፤ ማዕድኑን ለይቶ ካለማወቅ የተነሳም ለብክነት ሊጋለጥ የሚችልበትን ሁኔታም ጠቁሟል፡፡
የአካባቢው ማህበረሰብ ማዕድኑን አልምቶ ለመጠቀም አስፈላጊና ወሳኝ የሆኑ ዘመናዊ መሣሪያዎች ማለትም መቆፈሪያ፣ መነጽር፣ ጓንት፣ የአፍ መሸፈኛና ሌሎች አስፈላጊ የሆኑ ግብዓቶች እንደሌለው ጠቅሰው፣ ይህ በመሆኑም ማዕድኑን አልምቶ መጠቀም እንዳልቻለ ዶክተር ሲሳይ አስረድተዋል፡፡
ማህበረሰቡ የተለያዩ ችግሮችን ተቋቁሞ የሚያገኘውን ማዕድን ወደ ገበያ ይዞ ሲወጣ የሕገወጦች ሲሳይ ሊሆን እንደሚችል ጠቅሰው፣ ይህም ሌላው የዘርፉ ችግር መሆኑን ጥናቱ ማመላከቱን ጠቁመዋል። ዶክተር ሲሳይ እንዳሉት፤ አልሚዎቹ በብዙ ድካም ያገኙትን ማዕድን ገበያ ይዘው ሲወጡ ከተማ ሳይደርሱ መንግሥት የማያውቃቸው ሕገወጥ ነጋዴዎች ርካሽ በሆነ ዋጋ ይቀበሏቸዋል፡፡ በዚህ ምክንያትም ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታቸውን ማረጋገጥ አልተቻለም፡፡
ኦፓሉን ለማውጣት የሚጠቀሙባቸው መቆፈሪያዎች ባህላዊ በመሆናቸው ሊሰባበሩ የሚችሉበት ሁኔታ ሰፊ ነው፡፡ አልሚዎቹ የኦፓል ማዕድኑን የሚይዙበት መንገድም ሌላው ችግር ነው፡፡ ኦፓል ከወጣ በኋላ የሚቀመጥበት መንገድ ጥንቃቄ የተሞላበት ሊሆን ይገባል፡፡ ማህበረሰቡ ግን ይህን ሲያደርግ አይስተዋልም። በዚህ የተነሳም ማዕድኑ ለጉዳት እየተጋለጠ ይገኛል፡፡ ኦፓል በተፈጥሮው ብርሃን የሚፈልግ ባለመሆኑ ለጸሐይ ብርሃን ሲጋለጥ ሊሰባበር የሚችልበት ሁኔታ ከፍተኛ ነው፡፡ በዚህ ምክንያት ወደ ገበያ ይዘው የሚወጡት ኦፓል የተበላሸና ለከፍተኛ ብክነት የተጋለጠ ይሆናል፡፡
በደቡብ ወሎ ደላንታ አካባቢ ብቻ ከ30 በላይ የኦፓል ማዕድን የሚያወጡ ማህበራት እንዳሉ የጠቀሱት ዶክተር ሲሳይ፤ በእያንዳንዱ ማህበር ውስጥም ከ12 እስከ 20 የሚደርሱ ወጣቶች ተደራጅተው ኦፓሉን እንደሚያወጡ ተናግረዋል፡፡ ማህበራቱ ኦፓሉን ለማውጣት ወደ ጉድጓድ ውስጥ የሚገቡት በተራ መሆኑን ጠቅሰው፣ ከአንደኛው ማህበር አምስትና ስድስት ሆነው ገብተው ማዕድን ሲያገኙ ሌሎቹ ደግሞ በተራቸው ገብተው ሲቆፍሩ ውለው ማእድኑን ሳያገኙ የሚወጡበት ሁኔታ አንዳለ፣ በአንጻሩ ደግሞ በቀጣዩ ቀን ደግሞ ሌሎች ቆፍረው ሊያገኙና ሽጠውም ሊጠቀሙ የሚችሉበት ሁኔታ እንዳለ ተናግረዋል፡፡ ይህ አሰራር ሁሉንም የማህበሩን አባላት ተጠቃሚ ማድረግ ያላስቻለ ስለመሆኑ በጥናቱ ማረጋገጥ መቻሉን አስታውቀዋል፡፡
ማዕድን ለማውጣት ከፍተኛ የሆነ ቁፋሮ የሚካሄድ በመሆኑ የመሬት መንሸራተት ሊያጋጥም የሚችል ስለመሆኑም በጥናቱ ተረጋግጧል ያሉት ዶክተር ሲሳይ፣ በመሬት መንሸራተቱ ምክንያት በሰውና በእንስሳት ላይ አደጋ እንደሚያጋጥም ተናግረዋል፡፡ የመንገድ መዘጋትና ሌሎች ችግሮችንም በአካባቢው ላይ ሊያስከትል እንደሚችል ጠቅሰው፣ በቁፋሮ የሚወጣው አፈር ሊኖረው በሚችለው አሲዳማነት ሳቢያም የአካባቢው መሬት ምርታማነት እየቀነሰ ይገኛል ብለዋል፡፡
እሳቸው እንዳስታወቁት፤ ለልማቱ የሚጠቀሙባቸው መሳሪያዎች ባህላዊ መሆናቸው ምርታማነቱ እንዲቀንስ እያደረገ መሆኑንም ጥናቱ አመላክቷል፡፡ በሌላ በኩል ጉድጓዱ እየራቀ ሲሄድ አፈር ወደ ውጭ ለማውጣት ብዙ ጊዜና ጉልበት የሚወስድ በመሆኑ ወጣቶቹን ተጠቃሚ አያደርግም፡፡ እነዚህንና መሰል ችግሮችን በጥናቱ መለየት ተችሏል፡፡ ችግሮቹን ከመለየት ባሻገርም የመፍትሔ አቅጣጫ መመላከቱንም ዶክተር ሲሳይ ተናግረዋል፡፡
ማዕድኑን አውጥቶ ለመጠቀም በርካታ ችግሮች መኖራቸውን ጠቅሰው፣ ችግሮቹን ለመፍታት በዋናነት ቴክኖሎጂን መጠቀም የግድ ነው ብለዋል፡፡ ማዕድኑ በማይባክንበት መንገድ ቴክኖሎጂ ተጠቅሞ ማዕድኑን ማውጣት አስፈላጊና አማራጭ የሌለው መፍትሔ እንደሆነ ለሚመለከተው አካል መቅረቡንም አስታውቀዋል። እሳቸው እንዳሉት፤ በክልሉ፣ በዩኒቨርሲቲ፣ በወረዳና በዞን ደረጃ እንዲሁም በፌዴራል ደረጃ ሊተገበሩ የሚችሉ ተግባራትን በመለየት በአካባቢው የተደረገው የመጀመሪያው ዙር የኦፓል ማዕድን ጥናት መጠናቀቁን አመልክተዋል፡፡
በሁለተኛው ዙር የተደረገው ጥናትም እንዲሁ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ኦፓል ከሌሎች አገራት ጋር ሲነጻጸር ምን ደረጃ ላይ ነው በሚል ደረጃ መስጠት የሚያስችል ጥናት ተካሂዷል ያሉት ዶክተር ሲሳይ፤ በወሎ ደላንታ ውስጥ ከሚገኙ ስምንት ቦታዎች መካከል ሁለት ቦታዎች ለናሙና ተወስደው ጥናት እንደተደረገባቸው አስታውቀዋል፡፡ እነዚህ ሁለት ቦታዎችም ሁሉንም አይነት ኦፓሎች ሊወክሉ የሚችሉ በመሆናቸው ዘመናዊ መሳሪያዎችን በመጠቀም የኦፓሉን ባህሪያት መለየት ተችሏል ብለዋል፡፡
እሳቸው እንዳስታወቁት፤ ኦፓል በሁለት አይነት መንገድ ይለያል፡፡ አንደኛው መንገድ መልኩን በማየት ነው፡፡ በዚህም ከጸሐይ ብርሃን ጋር በሚኖረው መስተጋብር የሚፈጠረውን ማንጸባረቅ በማየት ይለያል። ኦፓል የጌጣጌጥ ወይም የውበት ቁስ ስለሆነ ውበት ይሰጣል ወይስ አይሰጥም የሚለውን በአይን በማየት መለየት ይቻላል፡፡
ሁለተኛው መንገድ ደግሞ መሳሪያዎችን ተጠቅሞ መለየት ነው፡፡ ለዚህም አውስትራሊያ ተጠቃሽ ስትሆን፤ ሀገሪቱ ዘመናዊ መሳሪያ በመጠቀም ለኦፓሎቹ ደረጃ አውጥታለች፡፡ ስለዚህ እነሱ የተጠቀሟቸውን መሳሪያዎች በመጠቀም ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉት ኦፓሎች አውስትራሊያ ካለው ኦፓል ጋር ሲነጻጸሩ የትኛውን ደረጃ ሊይዙ ይችላሉ የሚል ጥናት ተደርጎ አበረታች ውጤት ተገኝቷል ሲሉ ዶክተር ሲሳይ አስታውቀዋል፡፡ በዚሁ መሰረት ኢትዮጵያ ውስጥ በወሎ ደላንታ አካባቢ የሚገኘው ኦፓል አውስትራሊኖች ከፍተኛ ደረጃ ብለው ካስቀመጡት የኦፓል አይነት ጋር ተመሳሳይ እንደሆነ በጥናቱ ማረጋገጥ ተችሏል ብለዋል፡፡
ጥናቱ በክልሉ የሚገኘውንና ከፍተኛ ደረጃ ያለውን የኦፓል ማዕድን የአካባቢው ማህበረሰብ አልምቶ መጠቀም የሚችልበትን መንገድም አመላክቷል፡፡ ለአብነትም ኦፓልን የሚያወጡ ሰዎች ስልጠና እንዲያገኙ ማድረግና ኦፓሉን በአካባቢው አስውቦና አስጊጦ ለገበያ ማቅረብ የሚያስችል ማዕከል ማቋቋም የሚለው አንድ መፍትሄ ነው፡፡ በዚህ በኩል ቴክኒክና ሙያ ላይ የተጀማመሩ ሥራዎች ተጠናክረው መቀጠል ቢችሉ ዘርፉን አልምቶ የመጠቀም ምቹ ሁኔታዎችን መፍጠር ይቻላል የሚሉ ምክረ ሀሳብ ተሰጥቷል፡፡
እነዚህን አጠናክሮ ለማስቀጠልና በአካባቢው ተጨማሪ ሥራዎችን መስራት የሚያስችል ምቹ ሁኔታ አልተፈጠረም ሲሉ ዶክተር ሲሳይ አስገንዝበዋል፡፡ በጥናቱ የተለዩ ችግሮችን ለመፍታት ብሎም የማዕድን ዘርፉ በተለይም የወሎ ደላንታ ኦፓልን አልምቶ መጠቀም እንዲቻል የተሰሩ ሥራዎች ቢኖሩም መሬት የወረደ ሥራ እየታየ አይደል ብለዋል፡፡
ለዚህም በአንድ ወቅት ተከስቶ የነበው የኮቪድ ወረርሽኝ አንደኛው ምክንያት መሆኑን አመልከተው፣ በሰሜኑ ክልል የተፈጠረው ጦርነትም እንዲሁ ሌላው አካባቢው ላይ ተጨማሪ ሥራ እንዳይሰራ እንቅፋት ሆኖ መቆየቱን ገልጸዋል፡፡ ያም ሆኖ ክልሉ የተለያዩ ጥረቶችን ሲያደርግ መቆየቱን አመላክተዋል፡፡
ጥናቱ እየተካሄደ በነበረበት ወቅት ከተከናወኑ ተግባሮች መካከል የኦፓል የገበያ ማዕከልን ለመገንባት የተጀመረ ሥራ እንደነበር ያስታወሱት ዶክተር ፣ በደቡብ ወሎ ደላንታ ወገን ጤና ከተማ ላይ የኦፓል ገበያ ማዕከል የተቋቋመ ቢሆንም እስካሁን ተግባራዊ መሆን አልቻለም ብለዋል፡፡ በአካባቢው ያለው የኦፓል ማዕድን ከፍተኛ ሀብት መሆኑን ጠቅሰው፣ የማስተዋወቅ ሥራ በመሥራት የግል ባለሀብቱን በመሳብና ሀብቱን ጥቅም ላይ የማዋል ሥራ ተጠናክሮ ሊሠራበት ይገባል ብለዋል፡፡
እርግጥ ነው የማዕድን ልማት ከፍተኛ ኢንቨስትመንት ይጠይቃል ያሉት ዶክተር ሲሳይ፤ የተሟላ መሰረተ ልማት እንደሚጠይቅ ተናግረዋል፡፡ ከዚህ ውጭ አካባቢውን ለኢንቨስትመንት ምቹ የማድረግ ሥራ በመስራት የግል ባለሃብቱን ወደ አካባቢው ማምጣትና የኦፓል ማዕድንን በስፋት አልምቶ ጥቅም ላይ ማዋል እንደሚቻል አስገንዝበዋል፡፡
እሳቸው እንዳሉት፤ ማዕድን የማይተካና አንድ ጊዜ ጥቅም ላይ ከዋለ መልሶ ማግኘት የማይቻል ውድ የተፈጥሮ ሀብት ነው፡፡ እንደዚህ አይነት የተፈጥሮ ሃብቶችን ደግሞ በአግባቡ መጠቀም ይገባል፡፡ ‹‹ማዕድንን ያለአግባብ ከመጠቀም ፈጽሞ አለመጠቀም ይሻላል›› ሲሉ አስገንዝበው፣ እንዲህ አይነት የተፈጥሮ ሀብቶች የዜጎች ሃብት እንደመሆናቸው በአግባቡ ተጠብቀው አቅምና እውቀት እንዲሁም ቴክኖሎጂ ሲኖር መጠቀም ይገባል ሲሉ መክረዋል፡፡ ይህ ሲሆን አገሪቱንም በተሻለ መልኩ ተጠቃሚ ማድረግ ይቻላል ባይ ናቸው፡፡ ይህ ካልሆነ ግን ከአቅምና ከዕውቀት እንዲሁም ከቴክኖሎጂ ውጭ መጠቀም የማዕድን ሃብቱን ለብክነትና ለብልሽት ከመዳረግ ባለፈ የሚያስገኘው ጥቅም የለም፡፡
እንደ ዶክተር ሲሳይ ማብራሪያ፤ ዘርፉ የሚሰጠውን ጥቅም መሰረት በማድረግ መጠቀም ከተፈለገም ዘርፉ የሚጠይቀውን ከፍተኛ የኢንቨስትመንት ወጪ ማውጣት ይገባል፤ ከፌዴራል እስከ ወረዳ ባለው የመንግሥት መዋቅር ማዕድንን በምን አግባብ መጠቀም እንደሚቻልና ከማዕድኑ መንግሥትና ሕዝብ የሚያገኙት ጥቅም ምን እንደሆነ በመለየት ሕጎችን አውጥቶ ተግባራዊ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ማዕድኑን ለማውጣት አስፈላጊ የሆኑ ቴክኖሎጂዎችን ማዘጋጀት ያስፈልጋል፡፡ በማዕድን ዘርፍ እየተስተዋለ ያለው ብክነት ቴክኖሎጂን ካለመጠቀም የመጣ እንደሆነ በጥናቱ ተመላክቷል ብለዋል፡፡
የተገኘውን ማዕድንም እንዲሁ ቦታውን ሳይለቅ ባለበት ቦታ ላይ እሴት መጨመር የሚቻልበትን የስልጠና ማዕከል ማቋቋም እንደሚገባ አስገንዝበው፣ በስልጠና ማዕከላቱ ማእድን አውጪዎቹን እንዲሁም የሚያስውቡና የሚያስጌጡትን ባለሙያዎች ማሰልጠን ያስፈልጋል፡፡ ይህም በዘርፉ የሚስተዋለውን ሕገወጥ እንቅስቃሴ ለመገደብ አማራጭ መሆኑን ዶክተር ሲሳይ አመልክተው፣ እነዚህንና መሰል ጥረቶች ማድረግ ከተቻለ ማህበረሰቡ ማዕድኑን አልምቶ መጠቀምና አገርም ከዘርፉ መጠቀም እንደምትችል ተናግረዋል፡፡
ፍሬሕይወት አወቀ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 1/2017 ዓ.ም