ከነጻ እስከ ረዥም ጊዜ ክፍያ የዘለቀ የሕክምና አገልግሎት

በሀገራችን በተለይ በመዲናችን አዲስ አበባ ሰው ይበዛባቸዋል ተብለው በሚታሰቡ መንገዶች ላይ የታማሚን ባነር ሰቅለው፤ ባስ ሲልም እራሱን ታማሚውን መኪና ውስጥ አስቀምጠው የመታከሚያ ሲለመን መመልከት የመዲናችን የዘወትር አሳዛኝ ትእይንት ከሆነ ከራረመ። ሰው መረጃ አገኝበታለሁ፤ እዝናናበታለሁ ብሎ የሚጎበኛቸው ማህበራዊ ገጾችም ከመሰል የህክምና ወጪ በዝቶብናልና አግዙን ከሚሉ ልጥፎች ነጻ አይደሉም። የሁሉም ባይባልም አብዛኞቹ ለ“አግዙኝ” ጥያቄና እሳት የሆነውን የሰው ፊት ለማየት የዳረጋቸው ህመሙ ስር ሳይሰድ ወደ ህክምና ተቋማት ባለመሄዳቸው እንደሆነ ይታመናል። ቢቻል ህመሙ ምልክቱን ማሳየት ሳይጀምር ለጤና ምርመራ ካልሆነም ገና ህመሙ ሲጀምር የህክምና ተቋማትን ቢጎበኙ ኖሮ አብዛኞቹን ህመሞች በአጭር ጊዜና በአነስተኛ ወጪ ማስቀረት ይቻል ነበር።

በሀገራችን ታሞ ህክምናን ከመሻት ይልቅ ቅድሚያ ጤናን መጠበቅ ላይ ትኩረት ሰጥተው ከሚሰሩ የህክምና ተቋማት መሃል “ረዳት ሄልዝ ኬር” ተጠቃሽ ነው። የረዳት ሄልዝ ኬር ዋና ሥራ አስኪያጅ ወይዘሪት ምስጋና ሰለሞን፤ ድርጅታቸው ታሞ ህክምናን በመሻት ወደ ማእከሉ ለሄደ ታካሚ የህክምና አገልግሎት ከመስጠት ባሻገር በሽታን አስቀድሞ መከላከል ላይ ትኩረት ሰጥቶ የሚሰራ ድርጅት መሆኑን ያስረዳሉ። ለዚህም ያግዝ ዘንድ ድርጅቱ ሰዎች በበሽታ ከመያዛቸው በፊት በመለየት በጊዜ ሕክምና እንዲያገኙ ለማድረግ የሚያግዙ የተለያዩ የምርመራ ጥቅሎችን በማዘጋጀት ሕመማቸው ሥር ሳይሰድ በቀላሉ ጤናቸውን እንዲያውቁ ይሠራል።

በሀገራችን በአብዛኛው ሕብረተሰብ ዘንድ ሳይታመም የመመርመር ቀርቶ ሲታመም ካልባሰና የግድ ካልሆነ ወደ ህክምና ተቋማት የመሄድ ባህሉ አነስተኛ መሆኑን የሚያነሱት ወይዘሪት ምስጋና፤ ቀድሞ መመርመር እራስ ላይ በሽታን እንደመጥራት መቆጠሩ ሰዎችን ለምርመራ እንደማያበረታታ ያስረዳሉ። ባደጉት ሀገራት ግን ኢንሹራንስ ለመግባት እንደ የእድሜ ክልል የተለያዩ ቅድመ ምርመራዎችን ማድረግ በኢንሹራንስ ኩባንያዎች የተቀመጠ ግዳጅ መሆኑ ሕብረተሰቡ የምርመራ ባህሉን እንዲያዳብር አግዟል። ከቅርብ

ጊዜ ወዲህ በሀገራችንም የሚገባውን ያህል ባይሆንም ጤናን አስቀድሞ በመመርመር ረገድ ለውጥ መኖሩን ጠቅሰዋል። ረዳት ሄልዝ ኬር ይሄንን ባህል ለማዳበርና ሰዎች ሳይታመሙ አስቀድመው መከላከል እንዳለባቸው በጽኑ ስለሚያምን በተለያዩ ጊዜያት ለተለያዩ ድርጅት ሠራተኞች ነጻ የምርመራና የምክር አገልግሎት በመስጠት የበኩሉን ሚና በመጫወት ላይ ይገኛል።

ባሳለፍነው ሳምንት ረዳት ሄልዝ ኬር ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ሠራተኞች የነጻ ምርመራና የምክር አገልግሎት ሠጥቷል። የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት የዘርፈ ብዙ ጉዳዮች ክፍል ኃላፊ ወይዘሮ ብርሃኔ ሰለሞን ኢፕድ የሠራተኛው ጤና ስለሚገደው ከረዳት ሄልዝ ኬር ጋር በመተባበር ለተቋሙ ሠራተኞች ነጻ የህክምና አገልግሎት ማመቻቸቱን ጠቅሰዋል። የኢፕድ ሠራተኞች ከተቋሙ የሥራ ባህሪ አንጻር ለራሳቸው አስበው የጤና ምርመራ የሚያደርጉበት ሁኔታ አናሳ በመሆኑ የጤና ምርመራውን ወደ ሠራተኛው ማምጣት አስፈላጊ መሆኑን ጠቅሰዋል። ተቋሙ እንደባህል ሠራተኛው ባለበት የጤና ምርመራ እንዲያደርግና ጤናውን እንዲጠብቅ ታሳቢ ተደርጎ እየተሠራ መሆኑንና፤ በዚህም የደም ግፊት፣ የስኳር፣ የኮሌስትሮል ነጻ ምርመራና ህክምና እና ለሌሎች ምርመራዎች እንደአስፈላጊነቱ የዋጋ ቅናሽና የዱቤ አገልግሎት ተቋሙ ድረስ በመምጣት ለሰጠው ረዳት ሄልዝ ኬር ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

የኢፕድ ሠራተኞች የተለያዩ የህትመት ውጤቶች በየዕለቱ ከመውጣታቸው ጋር ተያይዞ በሥራ ቦታቸው የጤናቸውን ሁኔታ የሚያውቁበት አሰራር አዲስ አለመሆኑን የሚያስረዱት ወይዘሮ ብርሃኔ፤ በ2016 ዓ.ም ነጻ የዓይንና የጥርስ ምርመራ ህክምና ከአለርት ሆስፒታል ጋር በመተባበር መደረጉን አስታውሰዋል። በዚህም ለዓይን እስከ ነጻ የቀዶ ጥገና (የኦፕራሲዮን ) ህክምና ተሰጥቷል። ለጥርስም የጥርስ ሙሌት፣ መንቀልና ማጠብ አገልግሎት ለሚያስፈልጋቸው ሠራተኞች እንዲያገኙ ተደርጓል። ከዚህ ቀደም የጡት ካንሰር የግንዛቤ መስጫ ወቅትን ታሳቢ በማድረግ የረዳት ሄልዝ ኬር እህት ኩባንያ ከሆነው ፓዮኔር ዲያግኖስቲክስ ላብራቶሪስ ጋር በመተባበር መክፈል ለማይችል ዘጠኝ የድርጅቱ ሴት ሠራተኞች ነጻ የጡት ካንሰር ምርመራና (የማሞግራፊ) የአልትራሳውንድ አገልግሎት ተሰጥቷል። በቀጣይም ተቋሙ የድርጅቱን ሠራተኞች ፍላጎት መሰረት በማድረግ የሠራተኛውን ጤና ለመጠበቅ የሚያግዙ ሥራዎች ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን ያስረዳሉ።

ሥራ አሥኪያጇ ወይዘሪት ምስጋና፤ ረዳት ሄልዝ ኬር በቅድመ ምርመራ ላይ የሕብረተሰቡን ንቃተ ህሊና ለማሻሻል በማሰብ በተለያዩ ጊዜያት የስኳር፣ የደም ግፊትና የኮሌስትሮል ምርመራዎችንና የምክር አገልግሎቶችን ለተለያዩ ድርጅቶች ሠራተኞች በነጻ አገልግሎት መስጠታቸውን ይጠቅሳሉ። ለኢፕድ ሠራተኞችም ከነጻ ምርመራው ባሻገር በህክምና ባለሙያዎች የአንድ ለአንድ የምክር አገልግሎት መሰጠቱና ተጨማሪ ምርመራዎች ሲኖሩም በከፍተኛ ቅናሽ አገልግሎቱ መሰጠቱ የድርጅቱ ሠራተኞች ጤናቸውን ለመጠበቅ ያስችላቸዋል። ኢፕድ ለሠራተኞቼ ጤናቸው ያለበትን ሁኔታ አሳውቁልኝ ብሎ ተነሳሽነቱን ወስዶ ወደ ድርጅቱ መሄዱ ከድርጅቱ አላማ ጋር የሚሄድ በመሆኑ መደሰታቸውን በመግለጽ በቀጣይም አብሮ የመስራት ፍላጎት እንዳላቸው አስታውቀዋል።

ድርጅቱ በተለያየ ጊዜ በነጻ ከሚሰጠው አገልግሎትና ከቅናሽ አገልግሎቱ በተጨማሪ ሰዎች በአንዴ ለአገልግሎቱ መክፈል ሊከብዳቸው ይችላል በሚል አገልግሎቱን በቅድሚያ ካገኙ በኋላ በስድስት ወር የሚከፈልበት አሰራር ከተለያዩ ድርጅቶች ጋር በመነጋገር አገልግሎቱን በዱቤ እያቀረበ ይገኛል። አሁን ለሠራተኞቻቸው የዱቤ አገልግሎት ካስጀመሩ ድርጅቶች በተጨማሪ ረዳት ሄልዝ ኬር ከሌሎች ድርጅቶች ጋርም የዱቤ አገልግሎት ለመስጠት ዝግጁ በመሆኑ ይህን አገልግሎት ሠራተኞቻቸው እንዲያገኙ የሚፈልጉ ድርጅቶች ቢያናግሯቸው ሠራተኞቻቸው “እንዴት እከፍላለሁ?” ከሚል ጭንቀት ነጻ ሆነው አገልግሎቱን የሚያገኙበትን ሁኔታ ለማመቻቸት ዝግጁ መሆናቸውን ሥራ አስኪያጇ ገልጸዋል።

ረዳት ሄልዝ ኬር በማእከሉ ከሚሰጠው የህክምናና የላቦራቶሪ አገልግሎት በተጨማሪ፣ የ24 ሰዓት የአምቡላንስ አገልግሎት፣ የቤት ለቤት ህክምና፤ እንዲሁም፣ በ9477 የጥሪ ማእከል በሕክምና ባለሙያዎች የ24 ሰዓት የቴሌ ሜዲስን አገልግሎት ይሰጣል። ኦክቶበር ወር “የጡት ካንሰር ግንዛቤ መስጫ ወር” መሆኑን በማስመልከትም የጡት ካንሰር ምርመራን (ማሞግራፊን) ከሀኪም የምክር አገልግሎት ጋር ወሩን በሙሉ 50 በመቶ ቅናሽ በማድረግ አገልግሎቱን በመስጠት ላይ ይገኛል።

ቤዛ እሸቱ

አዲስ ዘመን መስከረም 30/2017 ዓ.ም

 

Recommended For You