“ክብርና ፍቅር ለአረጋውያን!”

ጸጉራቸው ገብስማ፤ እድሜያቸው ቢገፋም ፈርጠም ያለ ትክለ ሰውነት የታደሉና ፈገግታ ከፊታቸው የማይጠፋ የ75 ዓመት አረጋዊ ናቸው። ጋሽ ሥዩም (ሥማቸው የተቀየረ) የእድሜያቸው ከጎልማሳነት ወደ አረጋዊነት መሻገሩን ተከትሎ የጆሯቸው የመስማት አቅም ተዳክማል። በዚህም ምክንያት ከስንት አንዴ ከሚያገኟቸው ጎብኚዎች ጋር የሚያደርጉት ቆይታ ባጭሩ እንዲቀጭ እያስገደዳቸው ይገኛል። በንግግር መሀል በተደጋጋሚ ምን አልክ/አልሽን? ተቋቁሞ ጨዋታን መቀጠል ለአብዛኞቹ ጠያቂዎቻቸው አድካሚ ስለሚሆንባቸው ከእሳቸው ጋር የሚያደርጉት ንግግር አጭር ነው።

ጋሽ ሥዩም ያኔ ትምህርት እንዲህ ሳይስፋፋ በፊት በእኩዮቻቸው ‹‹ቀለሜ›› በሚል ቅጽል የሚጠሩ ጎበዝ ተማሪ ነበሩ። በጥሩ ውጤት ትምህርታቸውን ካጠናቀቁም በኋላ ከባለሙያነት አንስቶ እስከ ከፍተኛ ኃላፊነት በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች ተዘዋውረው አገልግለዋል። የሚያገኙት የጡረታ ገንዘብ በአንዴ ተከታትለው ለመጡባቸው ደም ግፊት፣ ስኳርና መሰል ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች መድሃኒት መግዣነት የሚተርፍ አልሆነም። በጉብዝና ዘመናቸው ለፍተው ያሳደጓቸው አራት ልጆች ግን ደርሰው ዛሬን እየጦሯቸው ነው። ያም ቢሆን ሦስቱ ልጆቻቸው ትዳር ይዘው ከቤት ከወጡ ቆይተዋል። በዚህ የተነሳ ግፋ ቢል በወር አንዴ ቢገናኙ ነው። እቤት የቀረችው የመጨረሻ ልጃቸውና ባለቤታቸውም ማለዳ ወደ ሥራ ወጥተው ጀንበር ስትጠልቅ ይመለሳሉ። በሥራ ቦታ የዕለቱ ከበርካታ ሰዎች ጋር መዋል የለመዱት ጋሽ ሥዩም አሁን ላይ ብቻቸውን ሙሉ ጊቢ ውስጥ ለመዋል ከተገደዱ ከርመዋል። ለብቻቸው ወጣ ማለት የሚያምራቸው ቢሆንም “ተው አትችልም” የሚለው የባለቤታቸውና የልጃቸው የስስት ቁጣ ሃሳባቸውን ያስቀይራቸዋል። የድሮ የልብ ወዳጆቻቸው በብዛት በሕይወት የሉም፤ ካሉት ጋርም እንደልብ እንዳይገናኙ አድራሻቸው ተራርቆ በእነሱ አቅም መገናኘት ፈታኝ ሆኖባቸዋል።

ስለዚህ የቀኑ አብዛኛው ጊዜ ቴሌቪዥን በማየትና በመተኛት ያሳልፋሉ። ማታ ባለቤታቸውና ልጃቸው ሲመጡ ለጨዋታ ጓጉተው ቢጠብቁም እነሱ በሥራ ዝለው ይመጣሉና ጋሽ ሥዩም ቀን የዋለው ብቸኝነታቸው ማታም ይቀጥላል። ይሄ በሀገራችን የበርካታ አረጋውያን የኑሮ እውነታ ነው። ጋሽ ሥዩም የጤናቸው ሁኔታ እንደልባቸው ባያንቀሳቅሳቸውም ሰው ባገኙ ቁጥር ደስታቸው ወደር የለውም፣ ከእንጀራ በላይ የናፈቃቸው ሳቅ ጨዋታ ነውና ባገኙት አቅም ማህበራዊ ሕይወት ላይ ለመሳተፍም አይቦዝኑም።

ሰው የለመደ ሰው ብቻውን ሲውል ድብርቱን መቋቋም አይችልምና፤ ጋሽ ሥዩምም ብቸኝነት የሌላቸውን ጸባይ እንዲያወጡ እያስገደዳቸው ነው። ከዚህ የባሰው ደግሞ በሀገራችን በተለያዩ የሙያ መስክ ፊት አውራሪ የነበሩ ጀግኖችን መንገድ ላይ እጃቸውን ለልመና ዘርግተው ማየት የተለማመድነው የዕለት ውሎአችን ሆኗል። በዓለም አቀፍ ደረጀ ለ34ተኛ በሀገራችን ደግሞ ለ33ተኛ ጊዜ “ክብርና ፍቅር ለአረጋውያን!” በሚል መሪ ቃል መስከረም 21 ቀን 2017ዓ.ም በጋምቤላ ከተማ የአረጋውያን ቀን ተከብሯል። በበዓሉ ላይ ንግግር ያደረጉት የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር የማህበራዊ ዘርፍ አማካሪ አቶ ጌታቸው በዳኔ፣ አረጋውያን በእድሜ ዘመናቸው ዕውቀታቸውንና ጉልበታቸውን ለልማት ያዋሉ የሀገር ባለውለታ በመሆናቸው በእርጅና ዘመናቸው ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ እንዲሁም የጤናና ሥነ-ልቦናዊ ችግር በሚያጋጥማቸው ወቅት ተገቢውን ድጋፍና እንክብካቤ በማድረግ ሁሉም የዜግነት ግዴታውን ሊወጣ እንደሚገባ አፅዕኖት ለመስጠት በዓሉ እንደሚከበር ጠቁመዋል።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት መረጃ እ.አ.አ በ2019 በዓለም ላይ እድሜያቸው ከ65 በላይ የሆኑ አረጋውያን ቁጥር 703 ሚልዮን መሆኑን ያሳያል። በኤስያ የሚገኙ አብዛኛው ሀገራት አሁንም እንደድሮ አረጋውያኖቻቸውን ከቤተሰብ ጋር ቀላቅለው በክብር ይዘው ቀጥለዋል። ምእራባውያን በግል ከኑሮ ሩጫ ጋር የቤተሰባቸው አካል የሆኑ አረጋውያንን መንከባከብ ሳይችሉ ሲቀሩ በጋራ ከእኩዮቻቸው ጋር ጊዜ የሚያሳልፉበትን የአረጋውያን ማእከላት በስፋት ገንብተዋል። በእነዚህ ማእከላት የቤተሰብ ፍቅርን ባይተካም በባለሙያ የተደገፈ ተገቢ እንክብካቤና ከእኩዮቻቸው ጋር የመገናኘት አጋጣሚ ተመቻችቶላቸዋል።

እኛም ጋር መቄዶንያ፣ ክብር አረጋውያንና ሌሎች በጣት የሚቆጠሩ ግብረሰናይ ድርጅቶች ከክፍያ ነጻ ዘመድ የሌላቸውን አረጋውያን በመሰብሰብ ምርቃታቸው ለሀገር የሚተርፍበት ሁኔታን ፈጥረዋል። የተወሰኑ የግል ተቋማት በክፍያ የአረጋውያን እንክብካቤ የሚሰጡም አሉ። ሆኖም በርካታ አረጋውያን በጎዳና ሀገር ያቀና እጃቸውን ለልመና ዘርግተው በማረፊያ እድሜያቸው የሰው ፊት የሚያዩበት አጋጣሚ ጥቂት አይደለም። በርካቶች ምን ይሉኝን ፈርተው አደባባይ ባይወጡም ባዘነበለ ጎጇቸው “ምን እበላ?” ብለው ጭንቅ የሆነባቸውና የሀገር ባለውለታዎች ተገቢውን ክብር አላገኙም።

እንደ አቶ ጌታቸው ማብራሪያ፣ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የአረጋውያንን ጉዳይ የሚከታተልና የሚያስተባብር ክፍል በመሪ ሥራ አስፈጻሚ ደረጃ በማደራጀት መዋቅሩን እስከታች ለመዘርጋት ከሚያደርገው ጥረት ጎን ለጎን የአሠራር ማዕቀፎችን የመቅረጽና የአስፈጻሚ አካላትን አቅም የማጎልበት ሥራ በትኩረት እየሠራ ይገኛል። በቀጣይም የአረጋውያን መብቶች በአግባቡ እንዲታወቁና እንዲከበሩ የአድቮኬሲና የንቅናቄ ሥራዎችን ከመሥራት ባሻገር የማህበራዊ ጥበቃ አገልግሎት ተደራሽነትን በማስፋፋት፣ ባለድርሻ አካላትን በማስተባበርና ሀብት በማሰባሰብ ለማህበራዊና አኮኖሚያዊ ችግር የተጋለጡትን ለመደገፍ የተጀመረው ጥረት ተጠናክሮ ይቀጥላል።

እንደ ተባበሩት መንግሥታት ድርጅት መረጃ ከሆነ በሁሉም የዓለም ክፍል የአረጋውያን ቁጥር በመጨመር ላይ ይገኛል። እ.ኤ.አ እስከ 2050 ባለው ጊዜ በዓለም ላይ የሚገኙ አረጋውያን ቁጥር ከዕጥፍ በላይ በመጨመር አንድ ነጥብ አምስት ቢሊዮን እንደሚደርስ ይገመታል። የሀገራችንም ሁኔታ ከዚህ እውነታ የተለየ አይደለም። ዛሬ ላሉን አረጋውያን ተገቢውን ክብርና አስፈላጊውን ድጋፍ ባንሰጥም ቁጥራቸው እየጨመረ ይሄዳል። የዛሬ አምራች ኃይል የነገ አረጋዊ ሲሆን የገቢ ምንጩ፣ የጤናውና የአካላዊ ሁኔታው እየደከመ መሄዱ አይቀርምና ዛሬ ላይ ለአረጋውያን ተገቢ ድጋፍ የሚሰጥበትን ሁኔታ ቆም ብሎ ማሰብ የሁሉም ኃላፊነት መሆኑ ሊዘነጋ አይገባውም።

የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ አረጋውያንን የሚንከባከቡ ሰዎች አረጋውያን ላይ ስሜታዊ የመሆን፤ ስህተቶች ሲያዩ አብዝቶ መተቸት፣ በሌሎች ጉዳይ አላስፈላጊ አስተያየት መስጠት እና ያንንም በሰዎች ፊት በተደጋጋሚ ማንጸባረቅ፣ ብስጩ መሆንና በተለያዩ ምክንያቶች ለተለያዩ ጉዳዮች እምቢ የማለት ባህሪያት ሊያስተውሉ እንደሚችሉ ይጠቅሳል። ሆኖም ከላይ የተጠቀሱት ባህሪያት ሲከሰቱ ከመናደድ ይልቅ በቤት ውስጥ ችግር አለመኖሩን በቅድሚያ እርግጠኛ መሆን የሚገባ ሲሆን፤ ነገሩን በእርጋታ እና በትዕግስት መያዝ፣ እጋውያኑ የሚወዱትን ነገር ማድረግ፣ ልምዳቸውን እንዲያካፍሉ እና እንዲደመጡ ማድረግ፣ መንፈስን የሚያረጋጉ እና ውስጣዊ ሰላምን የሚሰጡ የሚወዷቸውን ነገሮችን መከወን፣ የሚጠሉትን ነገር በፊታቸው አለማድረግ እንዲሁም ከአቻዎቻቸውና ከሌሎች ሰዎች ጋር ጊዜ እንዲኖራቸው ማድረግ በመፍትሔነት ተጠቅሰዋል። ይሄን ማድረግ ሲቻል በጧሪዎቻቸው ተደስተው የሚመርቁ አረጋውያንን ቁጥር ይጨምራል።

ቤዛ እሸቱ

አዲስ ዘመን መስከረም 23 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You