የመጀመሪያ ምዕራፉን ያጠናቀቀው ብቸኛው ራስ-ገዝ ዩኒቨርሲቲ

በሚኒስትሮች ምክር ቤት ውሳኔ መሰረት ራስ-ገዝ የሆነው አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ውሳኔው አካዳሚያዊ እና አስተዳደራዊ ነፃነቱ ተጠብቆ መንቀሳቀስ እንዲችል፣ በትምህርት ዘርፍ ለተጀመረው የሪፎርም እንቅስቃሴ ፈር ቀዳጅ ሆኖ እንዲወጣ ዕድል ይፈጥርለታል ተብሎ እንደነበር ይታወሳል። በወቅቱ የአካዳሚክ ነፃነት እንዲረጋገጥ፣ ከፖለቲካዊም ሆነ አስተዳደራዊ ጣልቃ ገብነት ነፃ ሆኖ የመማር ማስተማር እና የምርምር ሥራዎችን በላቀ መልኩ መፈጸም እንደሚችልም ታምኖበት ወደ ተግባር መገባቱም አይዘነጋም።

“ዩኒቨርሲቲዎች ወደ ራስ-ገዝ እንዲሸጋገሩ የሚደረገው በዋናነት የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ ነው” የሚለው እንዳለ ሆኖ፤ ለከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ራስ-ገዝ መሆን ማለት የአካዳሚክ ነፃነት የተረጋገጠ መሆን፣ ከፖለቲካዊም ሆነ አስተዳደራዊ ጣልቃ ገብነት ነፃ በመሆን የመማር ማስተማር እና የምርምር ሥራዎችን በላቀ መልኩ መፈጸም መቻል ወዘተ ማለት መሆኑ ከዓመት በላይ ሲነገር ቆይቷል።

ስለ ዩኒቨርሲቲዎች ራስ-ገዝነት ሃሳባቸውን የሰጡ ምሁራን ሁሉ (ለምሳሌ ነገሪ ሌንጮ (ዶ/ር) በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሰው ሀብት ልማት የሥራ ስምሪት እና የቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ (የራስ-ገዝ ዩኒቨርሲቲዎችን ማቋቋሚያ አዋጅ የውሳኔ ሃሳብ ለምክር ቤቱ የቀረበው በእሳቸው አማካኝነት ነው)፤ በላይ ሃጎስ (ዶ/ር) በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የትምህርት ምርምር እና ጥናት ተቋም ዳይሬክተር፤ የኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ፕ/ር ፍቅሬ ደሳለኝ እና ሌሎችም) ማለት በሚቻል ደረጃ የተስማሙበት መሠረታዊ ሃሳብ ቢኖር ዩኒቨርሲቲዎች ራስ-ገዝ (autonomous) ሲሆኑ ራሳቸውን በራሳቸው የማስተዳደር ሥልጣን እና ነፃነት ያገኛሉ። ራስን በራስ ያለማንም ጣልቃ ገብነት የማስተዳደር እና በነፃነት የሚንቀሳቀስበትን ሰፊ እድል ያገኛሉ። ተቋማዊ ነፃነትና ሥልጣን ይሰጣቸዋል። ዩኒቨርሲቲዎቹ የበለጠ አቅማቸውን በማጎልበት የላቀ ሥራዎችን እንዲሰሩና ተልዕኮዋቸውንም በተሳካ ሁኔታ እንዲወጡ አቅም ይፈጥርላቸዋል። አሁን ያለውን መዋቅር በራሱ ከልሶ በሚያዋጣው መልኩ የመቀየር እና የማሻሻል ብሎም ዩኒቨርሲቲውን የሚመሩ አካላትን እስከመሰየም የሚያስችል አቅምንና ሥልጣንን ይሰጣቸዋል። እንዲሁም:-

ተቋሙ ብቁና ተወዳዳሪ እንዲሆን ከማስቻልም ባለፈ፤ የአካዳሚክ ነፃነትን በመስጠት ዩኒቨርሲቲው የራሱ የሆነ የተማሪዎች ምልመላና ቅበላ ፖሊሲ በማዘጋጀት በራሱ መስፈርት ተማሪዎችን የመቀበል መብት እና በየትምህርት ክፍሎች የሚኖሩ ተማሪዎችን ቁጥር የመወሰን፣ የትምህርት ፕሮግራሞችንም ያለማንም ይሁንታና ጣልቃገብነት ተፈላጊነትንና ተመራጭነታቸውን በመመዘን በራሱ የመቅረጽ መብትና ሥልጣን፤ እንዲሁም የትምህርትና የሥልጠና ጥራትን ለማረጋገጥ የራስ የሆነ ማዕቀፍ እንዲኖር ነፃነትን ይሰጣል። ራስ-ገዝነት በሚሰጠው የሰው ሀብትን የማስተዳደር ነፃነትንም ለዩኒቨርሲቲው የሚያስፈለገውን የሰው ሀይል ቅጥር፣ የደረጃ ዕድገትና የመሳሰሉትን የራስን መስፈርት በማውጣትና በመከተል ማከናወን የሚያስችል መብትን፣ በሚኖረው የፋይናንስ ነፃነትም የራስን ገቢ ማመንጨትና የመጠቀም መብትን ያጎናፅፋል። ተቋሙ ዓላማውን ለማሳካት እስካስቻለው ድረስ በተለያዩ የገቢ ማመንጫ ዘርፎች ላይ በመሰማራት ገቢን በማመንጨት እና በራስ በመንቀሳቀስ ከጊዜ ወደ ጊዜ ከመንግሥት ጥገኝነት የሚላቀቅበትን እድል ያመጣል።

የአንድ ተቋም ራስ-ገዝ ዩኒቨርሲቲ መሆን ጥራት ያለው ትምህርትና ሥልጠና ለመስጠት፣ ያለን ሀብትን ያለ ብክነት በጥንቃቄ ለመጠቀም እና ተመራጭና ተወዳዳሪ የትምህርት ፕሮግራሞች እንዲኖሩ ዕድል የሚሰጥ ሲሆን፣ በሌላ በኩል ደግሞ ራስ-ገዝ ዩኒቨርሲቲ ለመሆን በዋናነት ጠንካራ የሰው ኃይል፣ ጠንካራ የፋይናንስ አቅም፤ እንዲሁም መሠረተ-ልማት መኖር ወሳኝ ጉዳይ መሆኑንም ከላይ የጠቀስናቸው ምሁራን ያሰምሩበታል።

ዩኒቨርሲቲዎች ራስ-ገዝ ሲሆኑ ከመንግሥት እጅ እንዲወጡ በማድረግ ተቋማቱ ሳይንሳዊ በሆነ እና ውጤታማ በሚያደርጋቸው መንገድ እንዲሠሩ ነፃነትን የሚሰጣቸው መሆኑን የተናገሩት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የትምህርት እና ሥነ ባህሪ ኮሌጅ የትምህርት ዕቅድ እና ሥራ አመራር ትምህርት መምህር እና ተመራማሪ፤ እንዲሁም የጥራት ማረጋገጫ ዳይሬክተር ፕሮፌሰር አበባው ይርጋ ዩኒቨርሲቲው ራስ-ገዝ መሆኑን ተከትሎ ከዩኒቨርሲቲው የማኅበረሰብ ሬዲዮ ጣቢያ ጋር በነበራቸው ቆይታ የኢትዮጵያ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ባሰቡት ልክ ውጤታማ ሆነው እንዳይቀጥሉ ካደረጓቸው ምክንያቶች መካከል ራስ ገዝ አለመሆናቸውን በቀዳሚነት አንስተው ነበር። ከዚህ አኳያ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የራስ-ገዝን እድልን ማግኘቱ በረከት ሲሆን፤ የበለጠ ፍሬያማ፣ ውጤታማ የመሆን እድሉንም በቀዳሚነት አግኝቷል ማለት ነው።

በአሁኑ ሰዓት በርካታ የመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች ወደ ራስ-ገዝነት ለመሸጋገር የቤት ሥራዎቻቸውን እየሰሩ ሲሆን፣ ከእነዚህም መካከል አንዱ የኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ ጥር 23 ቀን 2016 ዓ.ም የአካዳሚክ የኮሌጅ ዲኖች፣ ምክትል ዲኖችና የትምህርት ክፍል ኃላፊዎች ተቋሙ ራስ-ገዝ ዩኒቨርሲቲ ለመሆን እያደረገ ባለው የሽግግር ወቅት ተግባራት እና ዩኒቨርሲቲው እስካሁን ባደረጋቸው እንቅስቃሴዎች ላይ በተደረገው ውይይት እንደተገለፀው ራስ-ገዝ ዩኒቨርሲቲ መሆን ለተቋማት፤ በተለይም ለዩኒቨርሲቲዎች ትልቅ ዕድል እንጂ እንደ ስጋት ሊወሰድ አይገባም።

እ.ኤ.አ በ2015 የዩኔስኮን “በኢትዮጵያ ብቸኛው የመማር ከተማ” የሚል ዕውቅና ባገኘው ባህር ዳር ከተማ የሚገኘው ባህር ዳር ዩኒቨርሲቲም ወደ ራስ-ገዝነት ለመግባት የሚያስችለውን አሰራር ለመዘርጋት ይቻለው ዘንድ ራሱን የቻለ ጽሕፈት ቤት አቋቁሞና አደራጅቶ ሥራዎችን እየሰራ ሲሆን፤ በተሳካ ሁኔታም ራስ-ገዝ ዩኒቨርሲቲ እንደሚሆን የተቋሙ ማህበረሰብ አባላት እምነት ሆኗል።

ሐምሌ 28/2015 ዓ.ም በፀደቀው ማቋቋሚያ ደንብ መሠረት ራስ-ገዝ (Autonomous) ከሆነው፣ የራስ-ገዝነት ጉዞ የመጀመሪያ ምዕራፍ በመስከረም 2017 ዓ.ም እንደሚያጠናቅቅ፤ ቀሪ ተግባራቱንም በሁለት ምዕራፎች እስከ ሐምሌ 2017 ዓ.ም እንደሚፈፅም በዩኒቨርሲቲው ቻንስለር ብርሃኑ ነጋ ከተነገረለት አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በመቀጠል ራስ ገዝ ከሚሆኑ ዘጠኝ ዩኒቨርሲቲዎች (ሀሮማያ፣ ጅማ፣ መቐለ፣ ሀዋሳ እና ሌሎችም) መካከል አንዱ የሆነው፤ ባለፈው ዓመት (2015 ዓ.ም) 60ኛ ዓመቱን ያከበረውና በተለያዩ ዘርፎች ላይ ያተኮሩ 12 የምርምር ማዕከላት ያሉት ባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት መንገሻ አየነ (ዶ/ር) ከዩኒቨርሲቲው የአካዳሚክ ክፍል ዲኖች እና ኃላፊዎች ጋር በ2017 የትምህርት ዘመን የዩኒቨርሲቲው የአካዳሚክ ዘርፍ የትኩረት መስኮች ላይ ውይይት ባደረጉበት ወቅት እንደተናገሩት ዩኒቨርሲቲው ራስ-ገዝ ለመሆን የቅድመ ዝግጅት ሥራዎችን የሚያከናውን ጽ/ቤት የከፈተ ሲሆን፤ የራስ-ገዝነት ጉዞውን ዕውን ለማድረግም ግብረ-ኃይል ተቋቁሞ ወደ ሥራ ገብቷል።

የመጀመሪያ ምዕራፉን ወዳጠናቀቀው ተቋም እንምጣ።

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ራስ-ገዝ ሆኖ አካዳሚያዊ እና አስተዳደራዊ ነፃነቱ ተጠብቆ መንቀሳቀስ እንዲችል፣ በትምህርት ዘርፍ ለተጀመረው የሪፎርም እንቅስቃሴ ፈር ቀዳጅ ሆኖ እንዲወጣ፤ የራስ-ገዝ ዩኒቨርሲቲ ሥርዓትን በቀዳሚነት ተግባራዊ በማድረግ ለሌሎች ዩኒቨርሲቲዎችም አርአያ እንዲሆን ታስቦ የመጀመሪያነት እድልን አግኝቷል። ይህንኑ እድል በመጠቀምም ወደ ተግባር ተሸጋግሯል።

ባለፈው ማክሰኞ የአዲስ ተማሪዎች ቅበላ አሰራሩን አስመልክቶ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቶ የነበረው፣ የመጀመሪያው ራስ-ገዝ ዩኒቨርሲቲ ከመጪው መስከረም 2017 ዓ•ም ጀምሮ የእስከዛሬውን አሰራሩን ለመጀመሪያ ጊዜ እንደሚለውጥና በአዲስ አሰራርና መንገድ ጉዞውን እንደሚጀምር አስታውቋል።

በዩኒቨርሲቲው ተጠባባቂ ፕሬዚዳንት ሳሙኤል ክፍሌ ዶ/ር አማካኝነት ይፋ በተደረገው መግለጫ ላይ እንደተመለከተው ከአዲሱ ዓመት (የትምህርት ካላንደር) ጀምሮ ዩኒቨርሲቲው የሚቀበላቸው ተማሪዎች በብሔራዊ መልቀቂያ ፈተና የላቀ ውጤት ያስመዘገቡ እና ልዩ ብቃት ያላቸው ሲሆኑ፤ እነዚህ ተማሪዎችም ቢሆኑ ተወዳድረው በማሸነፍ እንጂ በብሔራዊ ፈተና ከፍተኛ ውጤት በማምጣት ብቻ ወደ ዩኒቨርሲቲው መግባት አይቻሉም።

በሀገሪቱ የመጀመሪያው ራስ-ገዝ ዩኒቨርሲቲ ሆኖ የተቋቋመው ዩኒቨርሲቲ (አአዩ) ተቋማዊ፣ አስተዳደሪዊ፣ የፋይናንስ እና አካዳሚክ ነፃነት ማግኘቱን ተጠባባቂ ፕሬዚዳንቱ የገለፁ ሲሆን፤ ይህም ለዩኒቨርሲቲው “መምህራኑንም ሆነ ተማሪዎችን በራሱ መስፈርት የመምረጥ መብት ይሰጠዋል።”

መስፈርቶቹን በተመለከተም በመግለጫው የተገለፀ ሲሆን፣ አንዱ መስፈርት የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተናን 50 በመቶ እና በላይ ማምጣት ነው። 50 በመቶ እና በላይ ይባል እንጂ የተመዝጋቢዎችን ቁጥር ባገናዘበ መልኩ ውጤቱ 60 ወይም 70 በመቶ ድረስ ከፍ ሊል ይችላል ተብሏል።

እንደ ፕሬዚዳንቱ መግለጫ ከሆነ ዩኒቨርሲቲው በራሱ የሚያዘጋጀው የመግቢያ ፈተና (Undergraduate Ad­mission Test) የሚኖረው ሲሆን፣ ይህንን ፈተና ማለፍም ሌላው ዩኒቨርሲቲው ያስቀመጠው መስፈርት ነው።

ፈተናውን በተመለከተም:-

ፈተናው የአፕቲቲውድ (Apptitude) መልክ የሚኖረው ሲሆን፤ የተማሪዎችን የቋንቋ፤ የማመዛዘን፤ እንዲሁም የቀመር አቅማቸውን የሚለካ እንደሚሆን በተጠባባቂ ፕሬዚዳንት ሳሙኤል ክፍሌ ዶ/ር ተነግሯዋል። ፈተናው ከሌሎች የመግቢያ ፈተናዎች ጋር ተመሳሳይነት ሊኖረው እንደሚችል፤ የሚወጣው ፈተናም ሙሉ በሙሉ የዩኒቨርሲቲው እንደሚሆን ተብራርቷል።

“ለሴቶች፣ ለአካል ጉዳተኞች እና ከታዳጊ ክልል ለሚመጡ ተማሪዎች ልዩ ትኩረት” የሚሰጥ መሆኑን የገለፁት ዶክተሩ የክፍያ እና የስኮላርሺፕ ሁኔታን በተመለከተም “በዩኒቨርሲቲው ለመማር ጥያቄ የሚያቀርቡ ተማሪዎች በሁለት ዓይነት መንገድ እንደሚስተናገዱ የተናገሩ ሲሆን፤ አንደኛው መስፈርቱን አሟልተው እና ሙሉ ክፍያ ከፍለው የሚማሩ ተማሪዎች ሲሆኑ፤ ሌላው መንግሥት ስፖንሰርሺፕ እንዲሰጣቸው የሚጠይቁ ተማሪዎች ናቸው።”ሲሉ ገልጸዋል።

ይህን በተመለከተ የተቀመጠ ኮታ እንደሌለ የገለጹት ዶ/ር ሳሙኤል እንደ እቅዳቸው ግን 50 በመቶ በመንግሥት 50 በመቶ በግል ወጪያቸው የሚሸፈንላቸውን ተማሪዎች ለመቀበል እንደሆነ ገልጸው ካልሆነም ቁጥሩ በተወሰነ መልኩ ልዩነት ሊኖረው እንደሚችል ጠቁመዋል።

መንግሥት ከፍተኛ ብቃት ያላቸውና ተወዳዳሪ የሆኑ ተማሪዎችን ለሀገር በሚፈለጉ የሥልጠና መስኮች ወጪን ጭምር በመሽፈን የሚያስተናግድበት ሥርዓት እንደሚኖር በመግለጫው ተመላክቷል።

“ከመጪው 2017 ዓ•ም ጀምሮ በዩኒቨርሲቲው የሚማሩ ተማሪዎች በመንግሥት የሚመደቡ ሳይሆኑ፣ በተቋም መስፈርት መሠረት የሚመለመሉ” መሆናቸውን የገለጸው ዩኒቨርሲቲው ተጨማሪ መረጃዎችን በተከታታይ እንደሚሰጥ የገለፁት ተጠባባቂ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ሳሙኤል እንደ ተናገሩት ከሆነ ተማሪዎች በሚያመለክቱበት ወቅት ብዙ ቅጾችን ይሞላሉ፤ ስኮላርሺፕ የሚጠይቁ ተማሪዎች ከፍለው መማር እንደማይችሉ የሚያሳይ ማስረጃ ከሚመለከተው አካል ማሟላት ይጠበቅባቸዋል፤ የሚያስገቡት መረጃም ትክክለኛነቱ የሚጣራ ሲሆን፣ ሐሰተኛ ሆኖ ከተገኘ በሕግ ተጠያቂ መሆን ይከተላል።

ከላይ እንደተመለከትነው፣ የራስ-ገዝ ዩኒቨርሲቲን አጠቃላይ ምንነትና አሰራር፤ እንዲሁም ራስ-ገዝ የመሆን ፋይዳ ብዙ ነው። እነዚያን አሰራሮችና ራስ-ገዝነት የሚያስገኘውን ፋይዳ በተግባር ለማየት ለሀገሪቱ የመጀመሪያ የሆነው ራስ-ገዝ ዩኒቨርሲቲ (አአዩ) የመጀመሪያውን ምዕራፍ በዚህ መልኩ “ለመጀመር ዝግጅቴን ከወዲሁ አጠናቅቄያለሁ” ብሏል። ቀሪውን ጊዜው ሲደርስ የምናየው ሲሆን፤ አዲስ ይተገበራል በተባለው የቅበላ አሰራር በ2014፤ 2015 እና 2016 ዓ.ም የትምህርት ዘመን የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ የመልቀቂያ ፈተና ወስደው የማለፊያ ነጥብ ያገኙ ተማሪዎች የሚወጣውን መስፈርት ታሳቢ አድርገው በዩኒቨርሲቲው ፖርታል https://portal.aau.edu.et መመዝገብ የሚችሉ መሆኑን ዩኒቨርሲቲው አስታውቋል።

ዩኒቨርሲቲው የ2017 ዓ.ም የአካዳሚክ ካላንደሩንም ይፋ ያደረገ ሲሆን፤ የ2ኛ ዓመትና ከዚያ በላይ ተማሪዎች ምዝገባ በኦንላይን የሚከናወን ሲሆን፤ ምዝገባውም በዩኒቨርሲቲው ውስጥ ባለ ኔትወርክ ብቻ እንደሚከናወን፤ እንዲሁም፣ መስከረም 3/2017 ዓ.ም – በ2016 ዓ.ም የገቡ የአንደኛ ዓመት ተማሪዎች ወደ ካምፓስ መመለሻ። መስከረም 4-5/2017 ዓ.ም -የ2ኛ ዓመትና ከዚያ በላይ የማታ ተማሪዎች ምዝገባ፤ መስከረም 7- 8/2017 – ዓ.ም የ3ኛ ዓመትና ከዚያ በላይ የቅድመ ምረቃ መደበኛ ተማሪዎች ምዝገባ፤ መስከረም 14/2017 ዓ.ም የመጀመሪያ ሴሚስተር ትምህርት የሚጀመርበት መሆኑን አስታውቋል።

ግርማ መንግሥቴ

አዲስ ዘመን ሰኞ ጳጉሜን 4 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You