በባዶ እግር የተጻፈው የወርቅ ታሪክ

አንድ ለስፖርት ቅርብ ያልሆነ ሰው ‹‹አበበ ቢቂላ ምንድነው?›› ተብሎ ቢጠየቅ ‹‹ሯጭ›› ማለቱ ግልጽ ነው። እንዲያውም አንድ ማሳያ እንጥቀስ። እሸቱ መለሰ የሚባለው የ‹‹ዩትዩብ›› ፕሮግራሞች አዘጋጅ በአንድ ፕሮግራሙ የገጠር አርሶ አደሮችን ወግ እያሳየ ነበር። በመጨረሻም የታዋቂ ሰዎችን ፎቶ እያሳየ ‹‹ይሄ ማነው?›› እያለ ይጠይቃል። አንድ አርሶ አደር የአትሌት ኃይሌ ገብረሥላሴን ፎቶ (በሩጫ ድርጊት ላይ እያለ) ሲያሳያቸው ቶሎ ብለው ‹‹አበበ ቢቂላ›› አሉ። አበበ ቢቂላ እዚህ ድረስ በሰዎች አዕምሮ ውስጥ ተሠርቷል ማለት ነው።

አበበ ቢቂላ ኢትዮጵያ በዓለም ታሪክ ከታወቀችባቸው እንደ ዓድዋ ያሉ ድሎች አንዱ ነው ማለት ይቻላል፤ ምክንያቱም በዓለም አደባባይ ኢትዮጵያ ስሟ የሚጠራበት ታሪክ ያስመዘገበ ጀግናዋ ነው። ይህን ጀግና በዚህ ሳምንት እናስታውሳለን። ከዚያ በፊት ግን እንደተለመደው ሌሎች የሳምንቱ ክስተቶችን እናስታውስ።

ከ52 ዓመታት በፊት በዚህ ሳምንት ጳጉሜ 1 ቀን 1964 ዓ.ም (በአውሮፓውያኑ 1972) በሙኒክ ኦሊምፒክ ለመሳተፍ ወደ ምዕራብ ጀርመን የሄዱት 9 የእስራኤል አትሌቶች በፍልስጤሙ ‹‹ጥቁር መስከረም›› (Black September) ድርጅት ተገደሉ።

ከዛሬ 556 ዓመታት በፊት በዚህ ሳምንት ልክ በዛሬዋ ቀን ጳጉሜ 3 ቀን 1460 ዓ.ም የኢትዮጵያ ንጉሠ የነበሩት አፄ ዘርዓያዕቆብ አረፉ። የሰለሞናዊ ሥርዎ መንግሥት አካል የሆኑት እኚህ ንጉሥ ባለቤታቸው ንግሥት እሌኒም በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ጎልተው ይታወቃሉ።

በዚሁ ሳምንት ከ105 ዓመታት በፊት ጳጉሜ 3 ቀን 1911 ዓ.ም ደግሞ የወሎ ንጉሥ የነበሩት ንጉሥ ሚካኤል አረፉ። ወደ አበበ ቢቂላ ታሪክ ስንሄድ በዚህ ሳምንት ሁለት ታሪኮች አሉት። አንደኛው በግልጽ በዓለም ሰነድ ላይ የሰፈረው የሮም ኦሎምፒክ ታሪኩ ሲሆን ሁለተኛው ግን የተወለደበት ቀን ነው።

በብዙ የበይነ መረብ መረጃዎች አበበ ቢቂላ የተወለደው በአውሮፓውያኑ የዘመን ቀመር ነሐሴ (August) 7 ቀን 1932 (በኢትዮጵያ አቆጣጠር ነሐሴ 1) ተደርጎ ነው የተጻፈው። አንዳንድ የሀገር ውስጥ ሰነዶች ደግሞ ነሐሴ 30 ቀን 1925 ዓ.ም እንደተወለደ ነው የሚገልጹት። ለዚህ እንደ ማስረጃ የሚጠቀሰው በአንድ የቪዲዮ ምስል ላይ እናቱ ሲናገሩ ‹‹የነሐሴ ዓመት ሰላሳ ዕለት ነው የተወለደ›› ይላሉ። በልማዳዊ አጠራር ዓመት ሰላሳ ማለት የወሩ የመጨረሻ ቀን (30) ማለት ነው። በዘመኑ የልደት ምስክር ወረቀት ስለሌለ የተራ ሰዎች (አበበ በልጅነቱ ተራ ሰው መሆኑን ልብ ይሏል) ታሪክ የሚሰነድበት ዕድል አልነበረም። ለማንኛውም ይህን በአከራካሪነቱ ክፍት አድርገን እንተወውና በዓለም ሰነድ ላይ የተመዘገበውን ወርቃማ ታሪኩን እናስታውስ።

በአበበ ቢቂላ ሀገር የዘመን አቆጣጠር ጳጉሜ 5 ቀን 1952 ዓ.ም ((በአውሮፓውያኑ 1960) ሻምበል አበበ ቢቂላ በሮም ኦሊምፒክ የማራቶን ሩጫን በባዶ እግሩ ሮጦ በማሸነፍ የወርቅ ታሪክ አስመዘገበ። ይህ የአበበ ታሪክ የኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን የአፍሪካ ታሪክ ነበር፣ የአፍሪካ ብቻም ሳይሆን የዓለም ታሪክ ነበር። አዲስ ክብረ ወሰን ያስመዘገበበት ነበር። ከዚህ ደማቅ ታሪኩ ጋር በባዶ እግሩ መሆኑ ደግሞ ሌላኛው የታሪኩ አካል ነበር።

ቀደም ባሉት ዓመታት ጥቁሮች በስፖርታዊ መድረኮች ለመሳተፍ ከነጮቹ እኩል ዕድል የማግኘታቸው ነገር ቀላል አልነበረም። የ1952 ዓ.ም የሮም ኦሊምፒክ ሲከናወን በርካታ የአፍሪካ ሀገራት ገና በቅኝ ግዛት ቀንበር ስር ነበሩ። አንድ ጥቁር በውድድሩ ተሳትፎ አሸንፎ የወርቅ ሜዳሊያ ሲያጠልቅ፣ ለዚያውም የዓለም ክብረ ወሰንን ሰብሮ ሲሆን ልዩ ክስተት ነበረው።

አበበ ቀደም ሲል በጠቀስናቸው ቀናት (ነሐሴ 1 ወይም 30) ቀን 1925 ዓ.ም በቀድሞው የሸዋ ጠቅላይ ግዛት በደብረ ብርሃን አውራጃ፣ ደነባ አካባቢ፣ ልዩ ስሟ ጃቶ በምትባል ሥፍራ ተወለደ። ወጣቱ አበበ እንደአካባቢው ባህልና ልማድ በእረኝነትና በትምሕርት ተሰማርቶ በአሥራ ሁለት ዓመቱ የቄስ ትምህርቱን አጠናቀቀ።

አበበ ገና በጨቅላ ዕድሜው ስመ ጥር የገና ተጫዋች እንደነበር ይነገርለታል። በ1944 ዓ.ም ወደ አዲስ አበባ በመሄድ በክብር ዘበኛ ሠራዊት በወታደርነት ተቀጥሮ በገና ጨዋታ እና በስፖርት እየዳበረ ቆየ። ክቡር ዘበኛ ሠራዊት ውስጥ ሲገባም፤ ከስፖርት ጋር ይበልጥ ተቀራረበ እንጂ አልተራራቀም። ከውትድርና አገልግሎት ጎን ለጎን፤ በሠራዊቱ የስፖርት እንቅስቃሴ በተለይም በአትሌቲክስና በገና ጨዋታ ጎልቶ ለመታየት ጊዜ አልፈጀበትም።

በኅዳር ወር 1948 ዓ.ም በአሥራ ስድስተኛው የሜልቦርን ኦሊምፒክ ላይ የተሳተፈውን የኢትዮጵያን ቡድን ለመቀበል በተደረገው ሰልፍ ላይ ከለበሱት ልብስ ጀርባ በኩል የሀገራቸው ስም (‹ኢትዮጵያ›) የተጻፈበትን መለያ ልብሳቸውን ለብሰው ሀገራቸውን ወክለው የተወዳደሩትን ወጣቶች ባየ ጊዜ ከፍ ያለ የኩራት ስሜት ተሰማው።

አበበ ሁኔታውን በዝምታ ማለፍ አልቻለም። ‹‹እነዚህ ስፖርተኞች እነማን ናቸው›› ብሎ ጠየቀ። ስፖርተኞቹ እነ ማሞ ወልዴና እነ ባሻዬ ፈለቀ ነበሩ። የአትሌቲክስ ፍቅር ወደ አበበ ውስጥ የዘለቀው ከዚያች አጋጣሚ በኋላ እንደሆነ ይነገራል። ‹‹ኢትዮጵያ›› ተብሎ የተፃፈበት ልብስ ለመልበስና በዓለም አቀፍ ውድድር ሀገሩን ወክሎ ለመሳተፍ ቁርጠኛ ጥረት ጀመረ። በዚሁ ዓመት የጦር ሠራዊት ብሄራዊ ሻምፒዮና የማራቶን ውድድር ተካፈለ። በወቅቱ ታዋቂ ከነበሩት አትሌት ዋሚ ቢራቱና ሌሎች አትሌቶችም ጋር ተወዳደረ።

ዋሚ ቢራቱ የወቅቱ የአምስት ሺህ እና የ 10 ሺህ ሜትር የኢትዮጵያ ክብረወሰን ባለቤት ስለነበሩ፤ በዚሁ የማራቶን ውድድር እንደሚያሸንፉ ቢጠበቅ አይገርምም። ሩጫውን በቀዳሚነት እየመሩ ነበር። ከተወሰኑ ኪሎ ሜትሮች በኋላ ግን ስታዲዬም ውስጥ የነበረው ሕዝብ ውድድሩን ከሚዘግቡ ጋዜጠኞች ‹‹አበበ ቢቂላ እየመራ ነው›› የሚል ያልተጠበቀ ዜና ሰማ። ‹‹ማን ነው አበበ? ይህ አዲስ ባለታሪክ ማነው?›› በማለት በአድናቆት ሲጠብቅ የነበረው ሕዝብ መልስ አገኘ። አበበ ቢቂላ ለመጀመርያ ጊዜ በተሳተፈበት የማራቶን ውድድር አሸነፈ።

አበበ ቢቂላ በሌሎች ውድድሮችም አሸነፈ። በአምስት ሺህ እና በ10 ሺህ ሜትር ርቀቶች በአትሌት ዋሚ ቢራቱ ተይዞ የቆየውን ብሔራዊ ሪከርድ ሲሰብር፤ ብዙዎች ኢትዮጵያ አዲስ ጀግና አትሌት ማፍራቷን ተናገሩ። የአበበ የመጀመሪያ ህልምም እውን ሆነ። በውድድሮች ባሳየው ድንቅ ብቃት ለኦሊምፒክ ቡድን ተመረጠ።

በጦር ካምፕ ውስጥ አበበ የሚያደርጋቸውን ልምምዶች እና ውድድሮች በጥሞና ይከታተሉ የነበሩት ስዊድናዊ አሠልጣኝ ኦኒ ኒስካነን፣ የአበበን ችሎታ በመገንዘባቸው ከሌሎቹ አትሌቶች ጋር ተቀላቅሎ እንዲለማመድና፣ የሮም ኦሊምፒክ እስኪቃረብ ድረስም ከሁለት ሺህ ሜትር በላይ ከፍታ ባላቸው ተራራማ ቦታዎች ላይ የመሮጥና የአንድ ሺህ 500 ሜትር ተደጋጋሚ የፍጥነት ሩጫ ልምምዶችን እንዲሠራ አደረጉት። ኢትዮጵያ በታሪኳ ለሁለተኛ ጊዜ በምትሳተፍበት የሮም ኦሊምፒክ ላይ ሲያልመው የነበረውን ‹‹ኢትዮጵያ›› ተብሎ የተፃፈበት የብሔራዊ ቡድን ትጥቅ በመልበስ በ1952 ዓ.ም ወደ ሮም አመራ።

በሮም ኦሊምፒክ ኢትዮጵያን ወክለው ለመሳተፍ ከአሰልጣኙ ጋር ወደ ሮም ካመሩት የኢትዮጵያ ተወዳዳሪዎች መካከል ለማራቶን ሩጫ የተመረጡት አበበ ቢቂላ እና አበበ ዋቅጅራ ነበሩ። ይሁን እንጂ ከ83 ሀገራት የተውጣጡ ከአምስት ሺህ በላይ አትሌቶች በተካፈሉበት የሮም ኦሊምፒክ ላይ የዓለም ሕዝብ ትኩረት በአውሮፓውያን አትሌቶች ላይ ነበር። ስለኢትዮጵውያን አትሌቶች በተለይም ስለ አበበ ቢቂላ የሚያውቀው ነገር አልነበረም። አበበ ቢቂላ ወይም ሌላ አፍሪካዊ አትሌት ሊያሸንፍ እንደሚችልም አልተጠበቀም፤ ከዚያ በፊት አንድም አፍሪካዊ በኦሊምፒክ ታሪክ ሜዳሊያ አግኝቶ አያውቅምና።

አሠልጣኙ ኒስካነን የሞሮኮው ራህዲ ቤን አብዴሰላም፣ የኒውዚላንዱ ባሪ ማጊ፣ የሶቭዬት ኅብረቶቹ ኮንስታንቲን ቮሮብዮቭ እና የወቅቱ የማራቶን ክብረ ወሰን ባለቤት የነበረው ሰርጌይ ፖፖቭ (2:15:17.0) እንዲሁም የብሪታንያው ዴኒስ ኦጎርማን የጊዜውን ምርጥ ማራቶን ተወዳዳሪዎች እንደነበሩ ለሁለቱ ኢትዮጵያውያን ሯጮች በጥብቅ ነግረዋቸዋል። ይሁን እንጂ የሞሮኮው ራህዲ ቤን አብዴሰላም ይለብሰዋል የተባለው የመለያ ቁጥሩ 26 የነበረ ቢሆንም የለበሰው መለያ ግን በአስር ሺህ ሜትር ውድድር ላይ ለብሶት የነበረውን መለያ ነበር። ስለሆነም አበበ የሞሮኮው ሯጭ የትኛው እንደሆነ አላወቀም ነበር።

ውድድሩ ተጀመረ። ታላቅ ህልም ያነገበው አበበ ማንም ሳይጠብቀው መሪዎቹን እየተከታተለና በመጨረሻም ቀድሟቸው ውድድሩን በአስደናቂ ብቃት በአሸናፊነት አጠናቀቀ።

አበበ ቢቂላ ውድድሩን በ2:15:16.2 በማጠናቀቅ የዓለምን ክብረ ወሰንን ሰብሮ የወርቅ ሜዳሊያ አገኘ። ራህዲ ሁለተኛ፣ ባሪ ማጊ ደግሞ ሦስተኛ ደረጃን አገኙ። የአበበ ፍላጎትና ሃሳብ ራህዲ እስከሚያጋጥመው ድረስ ጉልበቱን ለመቆጠብ ነበር። በዚህ ምክንያት ባይሆን ኖሮ ክብረ ወሰኑን በተሻለ ውጤት ይሰብር እንደነበር አሠልጣኝ ኒስካነን ጥርጣሬ እንዳልነበራቸው ገልጸዋል።

የሮም ኦሊምፒክ የማራቶን ውድድር ውጤት የዓለምን ታሪክ ቀየረ። ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለመላው አፍሪካና ለዓለም ጥቁር ሕዝብ ድል ያበሰረ ችቦ አቀጣጠለ። በኦሊምፒክ ታሪክ የሜዳሊያ ባለቤት ለመሆን የቻለ የመጀመሪያው አፍሪካዊ ስፖርተኛ ሆኖ ስሙ በታሪክ መዝገብ ላይ በወርቃማ ቀለም ሰፈረ።

አበበ ቢቂላ የማራቶንን ርቀት ሮጦ ያሸነፈውና ሪከርድ ያስመዘገበው በባዶ እግሩ መሆኑ ደግሞ የመላ ዓለም ስፖርት አፍቃሪዎችን በእጅጉ ያስደነቀ፣ የአበበ ቢቂላን ስምና የኢትዮጵያን ዝና በመላው ዓለም ተቀርፆ እንዲቀር ያደረገ ነበር። ጋዜጠኞች አበበ ለምን ያለ ጫማ በባዶ እግሩ እንደሮጠ ጠይቀውት ‹‹ … እኛ ኢትዮጵያውያን ሁሌም የምናሸንፈው በጀግንነትና በወኔ እንደሆነ ለዓለም ሕዝብ ለማሳወቅ በመፈለጌ ነው…›› ብሏል።

በውድድሩ ማግሥትም፣ የኢጣሊያ ጋዜጦች በትልልቅ ፊደሎች ጎልቶ የሚታይ ርዕስ በመፃፍ ‹‹ሮምን የወረረ ኢትዮጵያዊ›› የሚል አዲስ ስም አወጡለት። አበበ የክብር ዘበኛ ወታደር እንደሆነ ጋዜጠኞቹ ስለሚያውቁ ‹‹ኢትዮጵያን ለመውረር የኢጣሊያ አገር ወታደር ሁሉ አስፈልጎ ነበር፤ ጣሊያን ኢትዮጵያን ለመውረር ግዙፍ ጦር አዝምቶም ነበር። ኢትዮጵያ ግን አንድ ወታደር ብቻ ልካ ድፍን ሮምን ወረረችው …›› የሚል ጽሑፍ ይዘው ወጡ። ለመጀመሪያ ጊዜ በኦሊምፒክ ውድድር አሸንፎ የወርቅ ሜዳሊያ የወሰደ ጥቁር አፍሪካዊ አበበ ቢቂላ ነው። ይህም አጋጣሚ ብዙ ጥቁር አፍሪካውያን በዓለም አቀፍ ውድድሮች እንዲሳተፉ በር ከፍቷል። የአበበ ቢቂላ ዝናም ከዓለም ጫፍ እስከ ጫፍ ተዳረሰ።

እስከ ጥቅምት 1954 ዓ.ም ድረስ አበበ በግሪክ፣ በጃፓን እና በቼኮዝሎቫኪያ በማራቶን ተወዳድሮ በሁሉም አንደኛ በመውጣት አሸንፏል። ሐምሌ 3 ቀን 1956 ዓ.ም አዲስ አበባ ላይ በተካሄደው የኢትዮጵያ የኦሊምፒክ ማጣሪያ ውድድር የኦሊምፒክ ሜዳሊያና ክብረወሰን ባለቤቱ አበበ ቢቂላ አንደኛ፣ ማሞ ወልዴ እና ደምሴ ወልዴ ደግሞ ሁለተኛና ሦስተኛ በመውጣት አጠናቀቁ፤ ሦስቱም ወደ ቶኪዮ እንደሚጓዙ ሲረጋገጥ ኢትዮጵያ አንድ ብቻ ሳይሆን ሦስት ኃይለኛ ተወዳዳሪዎች እንዳሏት በመላው ዓለም ተሰማ።

የዓለም መገናኛ ብዙኃንም ዝነኛውን አበበ በኦሎምፒክ ማራቶን በድጋሚ ለማየት እንደጓጉ አራት ዓመት አለፉና የቶኪዮ ኦሊምፒክ ደረሰላቸው። ይሁን እንጂ በዚህ የጉጉት ፈንጠዝያ መሐል አስደንጋጭ ወሬ ተሰማ፤ አበበ ታመመ። ኢትዮጵያውያን በድንጋጤና በኀዘን ሲዋጡ፤ ስፖርት አፍቃሪው የዓለም ሕዝብ ግራ ተጋባ። አበበ በትርፍ አንጀት ህመም መሮጥ ተቸግሯል፤ ካልታከመ መኖር አይችልም። የቀዶ ጥገና ህክምና ቢደረግለት የማገገሚያ ጊዜ ያስፈልገዋል። ለኦሊምፒክ የቀረው ጊዜ ደግሞ ከሁለት ወራት ያነሰ ነው። ወከባ ሆነ።

የቶኪዮ ኦሊምፒክ 40 ቀናት ሲቀሩት የቀዶ ህክምና ተደረገለት። በፍጥነት እንደሚያገግም ተስፋ በማድረግ የኦሊምፒክ ቡድን ውስጥ ተካተተ። ገና ጤናው ስላልተመለሰ እያነከሰ ነበር የሚራመደው። በቶኪዮ የተደረገለት ልዩ የአድናቆትና የፍቅር አቀባበል በፍጥነት እንዲያገግም እንዳገዘው ይነገራል። እንዲያም ሆኖ በውድድር ይሳተፋል ተብሎ አልተጠበቀም። በእርግጥ በሮም ኦሊምፒክም ያሸንፋል ተብሎ ሳይጠበቅ ነበር ዓለምን ጉድ ለማሰኘት የበቃው። በቶኪዮም ተመሳሳይ ታሪክ እንዲደገም ተስፋ ያደረጉም ነበሩ።

አበበ ከኢትዮጵያ የኦሊምፒክ ቡድን ጋር አብሮ ወደ ቶኪዮ ሲጓዝ በርትቶ ይወዳደራል ብሎ ያሰበ ብዙ ሰው አልነበረም። አበበ ግን አደረገው። ጥቅምት 11 ቀን 1957 ዓ.ም ከ41 ሀገራት ከተውጣጡ 79 ተወዳዳሪዎችና ከሁለቱ ኢትዮጵያውያን (ማሞ ወልዴና ደምሴ ወልዴ) ጋር ለውድድር ተሰለፈ። ያሸንፋል ብለው ያላሰቡት አድናቂዎቹ በውድድሩ በመሳተፉ ብቻ ፈንድቀዋል።

ከተወዳዳሪዎቹ መካከል ብዙዎች ውድድሩን አቋረጡ። ብዙዎች ጉልበታቸው ዝሎ በየመካከሉ እረፍት ማድረግ ግድ ሆነባቸው። አንዳንዶቹ ተዝለፍልፈው ወደቁ። ማሞ ወልዴ 15 ኪሎ ሜትሮችን ከሮጠ በኋላ አቋረጠ። ቀዶ ጥገና አድርጎ ብዙም ሳይቆይ ወደ ውድድሩ የገባው ልበ ብርቱው ሰዉ አበበ ቢቂላ ግን እንደተለመደው ብቻውን ወደፊት ገሰገሰ። አሯሯጡ ከጥቂት ሳምንታት በፊት ቀዶ ጥገና የተደረገለት አላስመሰለውም። አሯሯጡ የአትሌቲክስ ባለሙያዎችን ያስደነቀም ነበር።

ሞቃታማው የአየር ሁኔታ ሳይበግረው ወደፊት በረረ። ሲሮጥ ለሚመለከተው ከመሬቱ በላይ የሚንሳፈፍ ይመስል ነበር። አበበ ኦሊምፒክ ስታዲዮሙ ውስጥ የገባው ብቻውን ነበር። በዚያም ይጠባበቅ የነበረው 70 ሺህ ተመልካች በከፍተኛ ሁኔታ አድናቆቱን ገለፀለት። በዚህ ውድድር ላይ የራሱን ክብረ ወሰን በድጋሚ በማሻሻልም ማሸነፍ ቻለ። በሁለት የኦሊምፒክ ማራቶን ውድድሮች ላይ አከታትሎ ሁለት የወርቅ ሜዳልያዎችን ማግኘት ቻለ። አበበ ሁለተኛውን ወርቅ ይዞ ወደ ኢትዮጵያ ሲመለስ የአዲስ አበባ ሕዝብ በነቂስ ወጥቶ የጀግና አቀባበል ካደረገለት በኋላ ንጉሠ ነገሥቱ ቀዳማዊ አጼ ኃይለሥላሴ የሻምበልነት ማዕረግ እና አዲስ ቮልስ ዋገን ቢትል መኪና ሸለሙት።

በመቀጠል ወደ ሜክሲኮ ኦሊምፒክ ያመራው ጀግናው አበበ፣ የሜክሲኮ ከፍተኛ የመሬት አቀማመጥ ከአዲስ አበባ ጋር ስለሚቀራረብ እንደሚስማማው ገምቶ ነበር። በተጨማሪም ጥሩ የብቃት ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ቀደም ብለው በተደረጉ ውድድሮች አውቋል። ስለሆነም አበበ የሜክሲኮውን ውድድር እንደሚያሸንፍ የበርካቶች እምነት ነበር።

አበበ 15 ኪሎሜትሮችን ከሮጠ በኋላ፤ እንደተፈራው ህመሙ ከአቅም በላይ ሆኖበት ውድድሩን ለማቋረጥ ተገደደ። አበበ ውድድር ሲያቋርጥ፤ የኢትዮጵያውያንና የአፍሪካውያን አሸናፊነት አልተቋረጠም። ‹‹ጀግና ጀግናን ያፈራል›› ነውና ከአበበ ጋር እየሮጠ የነበረው ኢትዮጵያዊ አትሌት ማሞ ወልዴ፤ ሳይጠበቅ ድል አድርጎ የማራቶንን ክብር ለኢትዮጵያ አጎናፀፈ።

አበበ በ1960 ዓ.ም ከአዲስ አበበ ወጣ ብላ በምትገኘው ሸኖ ከተማ መኪናውን እያሽከረከረ ሳለ የትራፊክ አደጋ ሲደርስበት፤ ዓለም ሁሉ ከኢትዮጵያውያን ጋር ደንግጧል፤ አዝኗል። በሀገር ውስጥና በእንግሊዝ ህክምና ቢደረግለትም በአደጋው የደረሰበት ጉዳት ከፍተኛ ስለነበረ ከወገቡ በታች ያለውን የሰውነት አካሉንና እግሮቹን ማንቀሳቀስ አልቻለም። ነገር ግን የስፖርተኛነት መንፈሱ እንደ ድሮው ብርቱ ስለነበር በተሽከርካሪ ወንበር ላይ ሆኖ አካል ጉዳተኞች በሚሳተፉባቸው ዓለም አቀፍ ውድድሮች ላይ ተሳትፎ ለማሸነፍ በቅቷል። የትራፊክ አደጋ ደርሶበት ሁለት አመት ሳይሞላው በኖርዌይ በተከናወነው የ25 እና የ10 ኪ.ሜ የአካል ጉዳተኞች ውድድሮች ላይ በማሸነፍና ለኢትዮጵያውያን የአካል ጉዳተኞች ስፖርት በግንባር ቀደምትነት የሚጠቀስ በመሆን ፈር ቀዳጅነቱን በድጋሚ አስመስክሯል።

ዓለም በመሰከረለት ጀግንነቱና ብቃቱ ህያውነትን የተቀዳጀው ሻምበል አበበ በቂላ፤ ጥቅምት 15 ቀን 1966 ዓ.ም፣ በ41 ዓመቱ ከዚህ ዓለም በሞት ተለይቷል። ሥርዓተ ቀብሩም ንጉሠ ነገሥቱን ጨምሮ እጅግ በርካታ ሕዝብ በተገኘበት ተፈፅሟል።

ዋለልኝ አየለ

አዲስ ዘመን ጳጉሜን 3 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You