የመምህራን የልዩ ስልጠና ዓላማና መሰረታዊ ፋይዳ

በተለያዩ የዓለም አቅጣጫዎች የተለያዩ ስልጠናዎች ይሰጣሉ። ስልጠና ከሌለ ቆሞ መቅረት ስለሚመጣ ዓለም ያለ ስልጠና ውላ አታድርም። በተለይ በዚህ በአሁኑ የተዋከበና የተካለበ ዘመን ብሎም ሁሉም ነገር ባስቀመጡበት በማይገኝበት ሸዋጅና እጅጉን ፈጣን ጊዜ ከመማር ቀጥሎ ብቸኛው ዓይን ገላጭ መንገድ ስልጠና ነው። ስለዚህ ስልጠና ብርቅ ነው፤ ስልጠና ክቡር ነው፤ ስልጠና እስትንፋስ ነው፤ ስልጠና ዘመናዊና የሰለጠነ የሥራ ማከናወኛ ሁነኛ መሳሪያ ነው።

ብዙዎች እንደሚሉትና እንደሚስማሙበትም፣ “ተሀድሶ” የሚለው ቃል ለፌሽታ ሳይሆን ለስልጠና ነው መዋል ያለበት። “ለምን?” ቢሉ፣ ስልጠና ያነቃል። ስልጠና ከአዳዲስ አስተሳሰቦችና አሰራሮች ጋር ያስተዋውቃል። ስልጠና ዓይንን ይገልጣል። እጅን ያፍታታል። በተለይ አስተሳሰብን ያሰላል። ዘመናዊነትን ያጎናፅፋል። ከዚህ አኳያ “ሙያን ሙያ ያደረገው ስልጠና ነው” ቢባል ማጋነን አይሆንም።

ይህን አጭር መንደርደሪያ እዚህ ላይ “እነሆ” ያልንበት ምክንያት ርእሰ ጉዳያችን ሲሆን፤ እሱም ትምህርት ሚኒስቴር ሰሞኑን ስልጠናውን ከሌሎች ስልጠናዎች ሁሉ በመለየትና በ”ልዩ ስልጠና”ነት በመመደብ በርካታ ልዩ ሰልጣኝ መምህራንን ማስመረቁ ነው። የምረቃው ሥነ ሥርዓት ልዩ መሆንም መነሻው ይኸው የስልጠናው “ልዩ” መሆን እና የእድለኛ ሰልጣኞቹ ልዩ ሰልጣኝነት ነው።

ከዚህ በፊት፣ ስልጠናው ከመድረሱና ሰልጣኞች ወደየሚሰለጥኑባቸው ተቋማት ከመግባታቸው በፊት የተግባሩ ባለቤት በሆነው ትምህርት ሚኒስቴር የመምህራን እና የትምህርት ልማት ዴስክ ኃላፊ ከሆኑት ወይዘሮ አሰገደች ምሬሳ ጋር ቆይታ አድርገን በነበረበት ወቅት በዘንድሮው ዓመት በሀገር አቀፍ ደረጃ ለ60ሺህ መምህራን “ልዩ የክረምት ስልጠና” ለመስጠት፤ “አስፈላጊው ዝግጅት መጠናቀቁ”ን ነግረውን እንደ ነበር መግለፃችን ይታወሳል።

የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ የ2016 ዓ.ም የሁለተኛው ሩብ ዓመት የሥራ አፈጻጸም ግምገማ ሪፖርትን ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ባቀረቡበት ወቅት ስልጠናው የአንደኛ ደረጃ እና የሁለተኛ ደረጃ መምህራንን አቅም ማሳደግን ታሳቢ ያደረገ መሆኑን መግለፃቸውንም ማስታወሳችን አይዘነጋም። በዛው መሠረት፣ ጊዜውን ጠብቆ ተጀመረ፤ ተፈፀመም።

ስልጠናው መጠናቀቁን የተናገሩት የመምህራንና የትምህርት ቤት አመራሮች መሪ ሥራ አስፈፃሚ ዶክተር ሙሉቀን ንጋቱ እንዳሉት “ለተከታታይ 24 ቀናት ሲሰጥ የቆየው የመምህራንና ትምህርት ቤት አመራሮች ልዩ አቅም ግንባታ ስልጠና” ተጠናቅቋል። ስልጠናው “መምህራን በሚያስተምሩበት የትምህርት ዓይነት፣ የማስተማር ሥነ-ዘዴ እና በዲጂታል ቴክኖሎጂ ክሂሎት ላይ ብቃታቸውን ለማሻሻል ታሳቢ ተደርጎ ለመምህራን የ120 ሰዓታት፣ ለትምህርት ቤት አመራሮች ለ60 ሰዓታት ተሰጥቷል።” ሲሉም አስረድተዋል።

በ28 ዩኒቨርሲቲዎች ሲሰጥ የቆየ መሆኑን ገልጸው፤ 49ሺህ 505 መምህራንና የትምህርት ቤት አመራሮች፣ 2ሺህ 892 አሰልጣኞች፤ እንዲሁም 224 ዋና አሰልጣኞች የተሳተፉበት ይህ ልዩ ስልጠና ልዩ ትኩረትን ለማግኘቱ ሌላኛው ማሳያ በመክፈቻው ሥነ ሥርዓት እለት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በበይነ መረብ ባስተላለፉት መልዕክት “ሀገር እንዲጸናና የትውልድ ቅብብሎሽ እንዲኖር የመምህራን ሚና ከፍተኛ” መሆኑን፤ “መምህራን የጸናችና የበለጸገች ኢትዮጵያ እንድትኖር አይተኬ ሚና” እንዳላቸው መግለፃቸው፤ “ስልጠናው የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ የተጀመሩ ሥራዎችን የሚያግዝና መምህራን በሚያስተምሩት ትምህርትና የማስተማሪያ ሥነ-ዘዴ ላይ ተጨማሪ አቅም ማበልጸጊያ መሆኑን፤ መንግሥት በመምህራን ዘንድ የሚስተዋለውን የኑሮ ጫና ለመቀነስ አቅም በፈቀደ መጠን ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ” እንዳለ መናገራቸው ነው።

የአንድ ሀገር ሥርዓተ ትምህርት የሀገርን የረጅም ጊዜ ጥቅም ማስጠበቅ የሚችሉ ዜጎች ማፍራት መሆኑን፤ ስልጠናው እንደ ሀገር የገጠመንን የትምህርት ጥራት ችግር ለመፍታት ከሚሰሩ ሥራዎች መካከል አንደኛው እንደሆነ የገለፁት የትምህርት ሚኒስትሩ ብርሃኑ ነጋ በበኩላቸው ስልጠናው “ከፖለቲካ ጋር ያልተገናኘና ሙያ እና የማስተማሪያ ሥነ ዘዴ ላይ ብቻ ትኩረት ያደረገ መሆኑን” አብራርተዋል።

ስልጠናውን በአግባቡ ተከታትለው ለሚያጠናቅቁና ከ70 በመቶ በላይ ውጤት ለሚያስመዘግቡ መምህራንና የትምህርት ቤት ዳይሬክተሮች ሰርተፊኬት እንደሚሰጥ ጠቅሰው፤ ይህ ሰርተፊኬት በቀጣይ በደረጃ እድገትና በሌሎች የማትጊያ ሥርዓቶች ጥቅም ላይ እንደሚውል፤ ዘንድሮ በመምህራንና የትምህርት ቤት ዳይሬክተሮች የተጀመረው ስልጠና በቀጣዮቹ ሦስት ዓመታት ለሁሉም የመጀመሪያና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት መምህራንና ዳይሬክተሮች የሚሰጥ መሆኑን ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ አስታውቀዋል።

ከሐምሌ 22/2016 ዓ.ም እስከ ነሐሴ 16/2016 ዓ.ም በተመረጡ 28 ዩኒቨርሲቲዎች ሲካሄድ የነበረው ስልጠና አስተናባሪዎች ስልጠናው ሲጠናቀቅ እንደገለፁት ከሆነ፣ ስልጠናው በውጤታማነት የተጠናቀቀ ሲሆን፤ ሁሉም ሰልጣኝ መምህራንና የትምህርት ቤት አመራሮች በኦንላይን የብቃት ምዘና እንዲወስዱ ተደርጓል። ውጤታቸውም በቀጣይ የሚገለፅ ይሆናል።

ስልጠናው በዓይነቱ የመጀመሪያ በመሆኑ በስልጠናው አሰጣጥ ሂደት የተስተዋሉ አስተዳደራዊና አካዳሚያዊ ተግዳሮቶች ተለይተው በቀጣይ የመፍትሔ ርምጃ የሚወሰድባቸው መሆኑን የገለፁት በትምህርት ሚኒስቴር የመምህራንና የትምህርት ቤት አመራሮች መሪ ሥራ አስፈፃሚ ዶ/ር ሙሉቀን፣ ይህ የክረምት መርሃ-ግብር በትኩረት ከሚመሩ የትምህርት ሚኒስቴር የሪፎርም ሥራዎች አንዱ በመሆኑ፤ በሚቀጥለው ዓመትም የመጀመሪያ ደረጃ መምህራን እና በዚህ ክረምት ስልጠና ያልተሳተፉ የ2ኛ ደረጃ መምህራንን የሚያሳትፍ ስለመሆኑ በማጠቃለያው ሥነ ሥርዓት ላይ ገልጸዋል። የስልጠናው ዋና ግብ የተማሪዎችን ብቃት ማሻሻል በመሆኑ መምህራን በስልጠናው ያገኙትን ልምድ እና እውቀት በመማር ማስተማሩ ሂደት እንዲተገብሩትም አደራ ብለዋል።

የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ በሀሮማያ ዩኒቨርሲቲ (በሌሎችም ተገኝተዋል) በመርሃ-ግብሩ ሲሰለጥኑ የነበሩ መምህራንን በጎበኙበትና ከሰልጣኞች ጋር ውይይት ባደረጉት ወቅት እንደተናገሩት የመምህርነት ሙያ የተከበረ እና የአንድ ሀገር የእድገት መሠረት በመሆኑ ይህን ታላቅ ሙያ ወደነበረበት ክብር ለመመለስና የመምህራንን አቅም በመገንባት ኑሮውን ማሻሻል የግድ በመሆኑ መንግሥት ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቶ በመሥራት ላይ ይገኛል።

ይህንንም ተግባራዊ ለማድረግ የአጭርና የረጅም ጊዜ እቅድ ተይዞ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመው ከደመወዝ ጭማሪ ጀምሮ የመምህራን ባንክ እስከመክፈት የሚደርሱ ሥራዎች እየተሰሩ መሆናቸውን፤ ይህ ባንክ ሙያውንና ኑሮአቸውን ለመቀየር ትልቅ ሚና እንደሚኖረውም ሚኒስትሩ ጨምረው ተናግረዋል።

ሰልጣኝ መምህራንም ስልጠናው ለሙያቸው ትልቅ አቅም እንደፈጠረላቸው፤ በስልጠናው አዳዲስ እውቀቶችን እንደቀሰሙና ቴክኖሎጂን በመጠቀም እንዴት ማስተማር እንደሚቻል ጭምር እውቀት ያገኙበትና ከዘመኑ ጋር የሚሄድ መምህር ለመሆን እንዳነሳሳቸው መግለፃቸው በወቅቱ ተገልጿል።

በትምህርት ሚኒስቴር የአጠቃላይ ትምህርት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ አየለች እሸቴ፣ 1 ሺህ 800 የሚሆኑ ተሳታፊዎች በ68 ክፍሎች ተከፋፍለው የመምህራን ሙያ ማሻሻያ ሥልጠናውን በሚገኙበት አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ተገኝተው ከዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ አመራሮች ጋር በመሆን የሥልጠና ሂደቱን በተመለከቱበት ወቅት እንዳሉት፣ ሥልጠናው የመምህራንን የማስተማር ዕውቀትና ክሂሎት የሚያዳብር ሲሆን፤ ትምህርት ሚኒስቴር የትምህርት ጥራትን ከማሳደግ ተልዕኮ አኳያ በርካታ ለውጦችን በሀገር ደረጃ እያከናወነ እንደመሆኑ መጠን ስልጠናውም የዚሁ ሥራ አካል ነው።

እንደ ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ አየለች እሸቴ ገለፃ የሪፎርሙ ተግባር ትውልድን የማሻገር ኃላፊነትና መስዋዕትነት መክፈልን የሚጠይቅ ሲሆን፤ ይህንን መስዋዕትነት መክፈል ደግሞ የሁላችንም ድርሻ ነው።

በትምህርት ሚኒስቴር የ”STEM DESK” የፊዚክስ ባለሙያና የሥልጠናው አስተባባሪ አቶ ደሴ መለሰ በበኩላቸው እንደሚናገሩት ሁሉም መምህራን ሥልጠናውን መውሰድ የሚገባቸው ቢሆንም፤ በቅድሚያ ለሒሳብ፣ ለሳይንስና ለቋንቋ ትምህርቶች ትኩረት በመስጠት በሁሉም 28 ዩኒቨርሲቲዎች ሥልጠናው እንዲሰጥ ተደርጓል። ሥልጠናው በአዲሱ ፍኖተ ካርታ መሠረት በተዘጋጁ ሞጅሎች፣ በዩኒቨርሲቲ መምህራን አማካኝነት ነው የተሰጠው።

በትምህርት ሚኒስቴር ድረ-ገፅ ላይ ከተገኘው መረጃ ለመረዳት እንደተቻለውና በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ መምህር እና አሠልጣኝ ዶክተር ስምዖን ሽብሩ እንደገለጹት ከሆነ የ2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የትምህርት አመራርና መምህራን አቅም ግንባታ ልዩ ሥልጠና በትምህርት ሚኒስቴር በተዘጋጀው መርሃ ግብር መሠረት በጥሩ ሁኔታ ተካሂዶ በስኬት ተጠናቋል።

እንደ አሰልጣኝ ዶክተር ስምዖን ሽብሩ አስተያየት ሥልጠናው የመማር ማስተማር አካሄድን በተግባርና በቴክኖሎጂ ማስደገፍ ላይ ትኩረት ያደረገ ሲሆን የተማሪዎች የመማር ፍላጎትንና ተነሳሽነትን ከፍ ለማድረግ መምህራንን ማብቃት አስፈላጊ በመሆኑ ይህንን ግብ ለማሳካት የተዘጋጀ ነው።

ሌላው የዩኒቨርሲቲው መምህርና አሠልጣኝ ዶክተር ቤታ ጸማቶ ከሰጡትና የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የብሩህ ተስፋ ማዕከል ካሰራጨው ዜና መረዳት እንደተቻለው፣ ሠልጣኞች ሥልጠናውን በልዩ ትኩረት እንደተከታተሉት፤ በልዩ መመሰጥ እርስ በእርስ ሲወያዩ፣ ሲማማሩና ከሥልጠና በኋላ በሚኖረው ምዘና እያንዳንዳቸው ከ90 ፐርሰንት በላይ ውጤት ለማስመዝገብ ግብ አስቀምጠው ሲሠሩ ነበር።

የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅና የመምህራንን አቅም ለማጎልበት (በጥቅሉ ነው የገለፅነው) በርካታ አስተዳደራዊና ቢሮክራሲያዊ መዋቅሮች፣ ዘርፎች ወዘተ ያሉ ሲሆን፣ በተለይ የሚከተሉት የትምህርት ጥራትን መጠበቅ እና መምህራንን ማብቃት ላይ በርትተው የሚሰሩ ናቸው። ምንም እንኳን ሥርዓት በተቀያየረ ቁጥር ሥርዓቱን ለመምሰል ሲቀያየሩ ቢስተዋልም ግን፣ ዋና አላማቸው እርስ በርሳቸው እየተመጋገቡ የትምህርት ጥራትን፣ ፍትሀዊነትን፣ ተደራሽነትን ወዘተ ማረጋገጥ ነው።

ከእነዚህም መካከል የትምህርትና ስልጠና ጥራት ማረጋገጥ ዳይሬክቶሬት፤ የትምህርትና ስልጠና ጥራት ቁጥጥር ባለስልጣን፣ በትምህርትና ስልጠና ጥራት ማረጋገጥና ምርምር ዳይሬክቶሬት፣ የኢንስፔክሽን ትምህርት ምዘና ዳይሬክቶሬት የሙያ ብቃት ምዘና ዝግ/አገ/አሰጣጥ ዳይሬክቶሬት፣ የእውቅና ፈቃድና እድሳት ዳይሬክቶሬት፣ የባለስልጣኑ የትምህርትና ስልጠና ጥራት ማረጋገጥና ምርምር ዳይሬክቶሬት እና ሌሎችም የሚጠቀሱ ናቸው።

ይሁን እንጂ፣ እስከ አሁኗ ደቂቃ ድረስ በእነዚህ ልክ ሥራዎች ተሰርተዋል ለማለት የሚያስችል መረጃም ሆነ ማስረጃ አልተገኘምና ሁሉም በሙሉ አቅማቸው ሊንቀሳቀሱ ይገባል እንላለን። የዛሬው ርእሰ ጉዳያችን የሆኑት፣ በልዩ ሁኔታ የሰለጠኑት መምህራንም በየሄዱበት የትምህርት ተቋማት ሁሉ ገደል አፋፍ ላይ ያለውን ትምህርታችንን ወደ ተራራው ጫፍ ያወጡታል ብለን ተስፋ እናደርጋለን።

ግርማ መንግሥቴ

አዲስ ዘመን ሰኞ ነሐሴ 27 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You