የመንገድ ዘርፉን ተግዳሮቶች ለመፍታት የምርምር ስራዎች ሚና

የመንገድ መሰረተ ልማት ለኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊና፣ ፖለቲካዊ ለውጥ ከፍተኛ ድርሻ አላቸው። የኢትዮጵያ መንግስትም ይህን ከግምት ውስጥ በማስገባት ብዙ ቢሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ በመመደብ የመንገድ መሰረተ ልማት መስፋፋትና ደረጀ ማሳደግ ስራዎችን በትኩረት ሲሰራ ቆይቷል። ይህን ተከትሎም በዘርፉ የሕዝብንና የሀገርን ተጠቃሚነት ለማሳደግ ጉልህ ድርሻ ያበረከቱ የመንገድ መሰረተ ልማቶች ተገንብተዋል።

ይሁንና ፍላጎቱና የተከናወነው ተግባር ሲነጸጻር በመንገድ መሰረተ ልማት ግንባታ ላይ የሕዝቡን ዘላቂ ተጠቃሚነትን ከማረጋገጥ አኳያ ብዙ መስራትን፣ ለእዚህም ይበልጥ ኢንቨስት ማድረግን የሚጠይቅ ፍላጎት ስለመኖሩ የዘርፉ ባለሙያዎችም መንግስትም ያምናሉ።

ለእዚህም ከአገራት ተሞክሮ የሚወሰድባቸው እና የቴክኖሎጂ ሽግግር የሚደረግባቸው በምርምር የተደገፉ የመንገድ ተደራሽነትን የተመለከቱ ስራዎች ተሞከሮ እንደሚያስፈልግ እየተጠቆመ ሲሆን፣ ለአንድ አገር ኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ ጉዳዮች መሳለጥ እንዲሁም የዜጎች ተጠቃሚነት እውን መሆን የአዳዲስ የመንገዶች ግንባታ፣ የተጎዱ መንገዶች ጥገና እንዲሁም የአገልግሎት ጊዜያቸውን የጨረሱ መንገዶች ደረጃን የማሻሻል ስራዎች ወሳኝ መሆናቸው ይገለጻል።

ሰሞኑን ቃሊቲ በሚገኘው የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር የመንገድ ምርምር ማዕከል በተካሄደውና በዘላቂ የመንገድ መሰረተ ልማት ላይ ባተኮረው ኮንፍረንስ ላይ እንደተመለከተውም፣ የመንገድ ዘርፍ ልማቱን በሚፈለገው ልክ ማስኬድ ያላስቻሉ በርካታ ተግዳሮቶች ይስተዋላሉ።

በመድረኩ ላይ በኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር የመንገድ ምርምር ማዕከል ዳይሬክተር ዶክተር ወርቁ አስራቴ እንዳስታወቁት፤ በአገሪቱ በመንገድ በዲዛይንና በማማከር አገልግሎቶች ላይ በማተኮር ምርምር እየተደረገ ይገኛል። የምርምር ስራዎቹም የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ ሲካሄዱ ቆይተዋል።

ተቋሙ እንደ ማዕከል ተቋቁሞ በአዲስ መልኩ እየሰራ የሚገኘው እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር ከ2010 ዓ.ም ጀምሮ ነው። የመንገድ ልማት ዘርፍ አገሪቱ በነበራት ውስን የመንገድ መረብ ምክንያት ኢኮኖሚውንም ማኅበራዊ ጉዳዩንም ማሳለጥ ከባድ ነበር። ከዚህ በመነሳትም ማእከሉ የመንገድ መሰረተ ልማቱን ማሳለጥ በሚያስችሉ ተግባሮች ላይ ሲሰራ ቆይቷል።

ይህ ስራ በምርምር ቢደገፍ የተሻለ ውጤት ሊኖረው ይችላል በሚል እምነት ማዕከሉ መቋቋሙን ዳይሬክተሩ አስታውሰዋል። ማእከሉ አሁንም የምርምር ስራዎችን እያከናወነ እንደሚገኝ አስታውቀው፣ አጠቃላይ የመንገድ ዘርፉን በምርምር እና በቴክኖሎጂ ስርፀት መደገፍን ዓላማው አድርጎ እንደሚሰራም አመልክተዋል።

በምርምር ስራዎቹም ከብዙ ባለድርሻዎች ጋር እንደሚሰራ ጠቅሰው፣ ፕሮጀክቶችን ጀምሮ ከማጠናቀቅ ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን በተወሰነ መረጃ ለመዳሰስ መሞከሩን ተናግረዋል። ይህም የተሰራው ግንባታው ከፕሮጀክት ማኔጅመንት፣ ከጊዜ፣ ከገንዘብ፣ ከጥራት፣ ከአካባቢ፣ ከማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች አኳያ ካበረከተው አንፃር እየታየ መሆኑን ገልጸዋል። ስራው ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አመላክተዋል።

ዳይሬክተሩ በግንባታ ዘርፉ በተለይ ከጥራት፣ ከገንዘብ እና ከጊዜ አኳያ በተቀመጠው ልክ የመፈፀም ተግዳሮት ቢኖርም፣ ለውጦች እየታዩ ናቸው ሲሉ ጠቅሰው፣ መጀመሪያና አሁን ልዩነት አለ፤ ስራው የበለጠ ለውጥ የሚፈልግ በመሆኑ የፕሮጀክት አፈፃፀምን ማሻሻል ይገባል ብለዋል።

ለውጡን የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር በተለይ በራሱ የምርምር ማዕከል እና አማካሪዎች እያስጠና እንደሚገኝ አመልክተው፣ የምርምር ስራው ሲጀመር በአብዛኛው ይገነባ የነበረው የጠጠር መንገድ እንደነበርም አስታውሰዋል። አሁን የፍጥነት መንገዶች ጭምር እየተገነቡ መሆናቸውንና ይህም ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ጠቁመዋል።

በዘርፉ ለውጥ የመጣው በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የተወሰኑ ጥናቶች ተካሂደው በተገኘ ግብኣት መሰረት ተሰርቶ መሆኑን ገልጸዋል። በተለይ ፕሮጀክትን በጊዜ ከማጠናቀቅ ጋር ተያይዞ የሚነሳው ጉዳይ አጠቃላይ የግንባታ ኢንዱስትሪውን እንደሚነካ አስታውቀውዋል፤ የተቋራጩን፣ የአማካሪውን፣ የማኅበረሰቡን፣ የየአካባቢዎቹን መስተዳድሮች ሁሉ እንደሚነካና በጋራ እንደሚሰራ ጠቅሰው፣ በዚህ ላይ ለውጥ ለማምጣት ጥናቶቹ የድርሻቸውን እየተወጡ መሆናቸውን አስታውቀዋል።

እሳቸው እንዳሉት፤ የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር ከምርምር አንጻር በአብዛኛው ትኩረት የሚያደርገው የመንገድ ዘርፉ ምን ተግዳሮቶች አሉበት? እንዴትስ ሊፈቱ ይችላሉ? በሚሉት ላይ ነው። ባለፉት ዓመታት ዋጋ በመንገድ ልማት ዘርፍ ምን እንደሚመስል ጥናት ተደርጓል። በመንገድ ፕሮጀክት ላይ የጤና፣ የደህንነትና የጥራት ጉዳይ እንዲሁም መንገዶች በሚፈለገው ጊዜ እና ጥራት ደረጃ መገንባታቸውን የተመለከቱ ጥናቶችን ጨምሮ ዘርፈ-ብዙ የጥናት ስራዎች ተደርገዋል።

ከዚህ አኳያም እንደ አገር መሻሻል እንደሚያስፈልግ ጠቁመው፣ ጥናቶች ሲታዩም ለአንድ ሺህ ሰዎች ስንት ተመራማሪ መኖር አለበት የሚለው ዓለም አቀፍ መስፈርት ወይም ስታንዳርድ አለ ሲሉም ያመለክታሉ። ኢትዮጵያ ከተቀመጠው ዓለም አቀፍ ደረጃ በታች መሆኗን ጠቅሰው፣ ይሄንን ታሳቢ በማድረግ የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር የተመራማሪዎችን አቅም ለማጎልበት እየሰራ መሆኑንም ተናግረዋል። አሁን 40 የሚጠጉ የምርምር ባለሙያዎች እንዳሉ ጠቅሰው፣ በትምህርት ዝግጅት በኩል ቀሪ ስራዎች እንዳሉም ጠቁመዋል።

እሳቸው እንዳስታወቁት፤ የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር ከምርምር ስራ አኳያ እንደ አገር ያለው ችግር በተቋሙም የሚስተዋል ቢሆንም፣ ከቀደሞው አንጻር ግን እየተፈታ መጥቷል። ‹‹የምርምር ማዕከሉ የምርምር ስራውን ከሀገር ውስጥ ተመራማሪዎች እና ዩኒቨርሲቲዎች እንዲሁም ከዓለም አቀፍ ተመራማሪዎች ጋር እንደሚያካሂድ አመልክተዋል።

እሳቸው እንዳስታወቁት፤ የሀገሪቱ አማካሪዎች የውጭውን ልምድ ወደ አገር ውስጥ እንዲያመጡ ለማድረግም እየተሰራ ነው፤ ለዚህም በጃይካ ድጋፍ ከጃፓኑ ኪዮቶ ዩኒቨርሲቲ፣ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ እና ከጂንካ ዩኒቨርሲቲ ጋር የምርምር ፕሮጀክት ይሰራል። ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጋር የመንገዶች አስተዳደር የራሱ ፕሮጀክት ያለው ሲሆን፣ እንግሊዝ ከሚገኘው በርሚንግሃም ዩኒቨርሲቲ ጋርም በተመሳሳይ ፕሮጀክት ነበረው። የዚህም ጥናት ውጤት የታተመ ሲሆን፣ የዚህ አይነት ስራዎች ተጠናከረው ይቀጥላሉ።

ከማዕከሉ የመንገድ ዘርፍ ልማት ሶስት ዓላማዎች አንዱ የዘርፉን የአገር ውስጥ ተቋማት አቅም መገንባት ነው። እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ1997 አካባቢ አምስት እና ስድስት የሚሆኑ የአገር ውስጥ ተቋራጮችና አማካሪዎች ብቻ ነበሩ። አሁን ግን 50 እና 60 የሚሆኑ የአገር ውስጥ ተቋራጮች በመንገድ ዘርፍ ላይ ብቻ እየሰሩ ናቸው። ይህም በመንገድ ዘርፉ ለመጣው ለውጥ አንድ ማሳያ ነው።

የመንገድ ምርምሩ ልምድ ባለውና የትምህርት ዝግጅቱም ከፍ ባለ ባለሙያ ይሰራል። ይሄን ከግንዛቤ በመውሰድ በማዕከሉ ዝቅተኛው የትምህርት ዝግጅት ሁለተኛ ዲግሪ ያለው ባለሙያ እንዲሆን ተደርጓል። የሶስተኛ ዲግሪውንም አጠናክሮ ለመቀጠል ታስቧል። ለዚህም የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን የራሱን በጀት መድቦ በአገር ውስጥም በውጭ አገራትም ባለሙያዎችን እያስተማረ ነው።

የምርምር ማዕከሉ ተግዳሮት ከሆኑት ማእከል አንደኛው ከምርምር ባህል ጋር የተያያዘው መሆኑን ዳይሬክተሩ ጠቅሰዋል። ምርምር ውጤቱ በአጭር ጊዜ እንደማይታይ ገልጸው፣ ምርምር በአብዛኛው እንደ ስራ የማይታይበት ሁኔታ አንድ ተግዳሮት መሆኑን አስገንዝበዋል።

በሀገሪቱ የባለሙያ እጥረት ተግዳሮት እንደነበር አስታውሰው፣ እጥረቱን ለመፍታት በተከናወኑ ተግባሮች መሻሻሎች መታየታቸውንና ይህንንም አጠናክሮ መቀጠል እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል። በማዕከሉ እየተደረጉ የሚገኙ በርካታ ምርምሮች የሀገሪቱን የመንገድ መሰረተ ልማት ዘርፍ ለማሻሻልና ለማሳደግ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚኖራቸው ጠቅሰው፣ መሰል ጥናቶች መጠናከር አንደሚገባቸውም አመላከተዋል።

የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስትር ዴኤታ ኢንጂነር ወንድሙ ሴታ እንዳሉት፤ በዓመት አንዴ የሚካሄደው ይህ የመንገድ ዘርፍ ጥናትና ምርምር አውደ ጥናት ዘንድሮ ለ7ኛ ጊዜ ነው የተካሄደው። አውደ ጥናቱ የትምህርት ተቋማት፣ የኢንዱስትሪው አስፈፃሚዎች እና የመንገድ ምርምር ማዕከሉ በተለይ በመንገድ ዘርፍ የሚያከናውናቸው ጥናትና ምርምሮች የሚቀርቡበት ነው። በጥናት ምርምሮቹ ላይም ከባለድርሻዎች ጋር ውይይት ይደረጋል፤ ለቀጣይ ስራዎችም አቅጣጫ ይመላከትበታል።

በመንገድ ዘርፍ ከፍተኛ ኢንቨስትመንት እየተደረገ ቢሆንም፣ ይህ ኢንቨስትመንት የበለጠ ውጤታማ እንዲሆን ብዙ መስራት ይኖርበታል። የሚሰራውን እስከ አሁን ከተሰራው የተሻለ ማድረግ ያስፈልጋል። ይሄንን ለማድረግ ደግሞ የዘርፉ ማነቆዎች ምንድናቸው? የትኛው ችግር ቢፈታ የተሻለ መስራት ይቻላል? የሚሉትን መመልከትና ነገን የተሻለ ለማድረግ የሚያስችሉ አቅጣጫዎችን ይዞ መስራት ይገባል።

ለዚህም የዘርፉ ዋነኛ ተዋናይ ከሆኑት አንዱ የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር መሆኑን ገልጸው፣ አማካሪዎች፣ የማማከር የዲዛይን ባለሙያዎችና ተቋማት እንዲሁም በዚህ ዘርፍ የሚሰማሩ ተማሪዎችን የሚያሰለጥኑ ዩኒቨርሲቲዎች እንዲሁም አጥኚዎቻቸው ሌሎች ተዋናዮች መሆናቸውን አብራርተዋል። መንግስትም የጥናት ውጤቶችን ለቀጣይ ሥራ እንደሚጠቀም አመልክተው፣ በየዓመቱ ከሚደረጉ ኮንፍረንሶች በተጨማሪ ተከታታይ መድረኮች ቢኖሩ የበለጠ ውጤታማ ሥራ መስራት እንደሚቻል ገልጸዋል።

ሚኒስትር ዴኤታው እንደተናገሩት፤ ኢትዮጵያ ለመንገድ መሰረተ ልማት በየዓመቱ 70 እና 80 ቢሊየን ብር ትመድባለች። ስለ አንድ ፐሮጀክት ሲወራም ፕሮጀክቱ በወቅቱ መጠናቀቅ ይኖርበታል፤ ለረጅም ጊዜ ማገልገል እንዲችል በጥራት መሰራት አለበት። የሕዝቡን ተጠቃሚነት እና እርካታ ማረጋገጥም ያስፈልጋል።

በኢትዮጵያ አሁን ያለው ሁኔታ ሲታይ ግን በታሰበው የጊዜ ገደብ የሚጠናቀቁ ፕሮጀክቶች በተቀራራቢነት 32 በመቶ ብቻ ናቸው። ፕሮጀክቶች የሚዘገዩበት ጊዜ ሲታይም በአማካይ 45 በመቶ አካባቢ ነው።

ቀጠናዊ የምስራቅ አፍሪካ የፕሮጀክቶች የጊዜ ገደብ 42 በመቶ አካባቢ መሆኑን ሚኒስትር ዴኤታው ጠቅሰው፣ አጠቃላይ በዓለም አቀፍ ደረጃ ያለው ተሞክሮ ሲታይ ደግሞ 10 በመቶ አካባቢ መሆኑን አመልክተዋል። ይህ ሁሉ ፕሮጀክቶችን በወቅቱ ከማጠናቀቅ አንፃር ብዙ የሚቀር ነገር እንዳለ እንደሚያመላቱ ሚኒስትር ዴኤታው አስገንዝበዋል።

በአዋጅ ማሻሻያዎች፣ በዲዛይን ሂደት፣ በፕሮጀክት ማኔጅመንት ሂደት ላይ ያሉ ችግሮች ለፕሮጀክቶች መዘግየት መንስኤ መሆናቸውን ጠቅሰው፣ መንገዶች ረጅም ጊዜ አገልግሎት መስጠት እንዲችሉ ጥራታቸውን የጠበቁ መንገዶችን መገንባት እንደሚያስፈልግም አስታውቀዋል። ከዚህ አንፃር የሚታዩት የሕግ ማሻሻያ፣ ዲዛይን ነው እንዲሁም የጥራት ቁጥጥር እና ኮንትራት አስተዳደር መሆናቸውን አመልክተዋል።

በእነዚህ ሂደቶች ውስጥ ያሉ ማነቆዎችን መፍታት ከተቻለ የሕዝባችንን ዘላቂ ተጠቃሚነት ማረጋገጥ እንችላለን ተብሎ ይታሰባል ሲሉም ገልጸዋል። ዝቅተኛ ገቢ አላቸው ከሚባሉት አገራት አንጻር በአንድ ሺህ ኪሎ ሜትር ውስጥ ያለው የሀገሪቱ የመንገድ ጥግግት በጣም በርቀት ላይ እንደሚገኝም ጠቅሰው፣ ጥግግቱ በዓለም አቀፍ ደረጃ ካለው ጋር ሲነጻጸርም በብዙ ርቀት ላይ እንደሚገኝ አስታውቀዋል።

“ይህም የሕዝባችንን ተጨባጭ ተጠቃሚነት አላረጋገጥንም። በቂ የመንገድ መሰረተ ልማት ተደራሽነት የለንም። በመሆኑም መንገድ ላይ የበለጠ ኢንቨስት ማድረግ አለብን። አሁን እንደ አገር ያለንበት ቁመና ደግሞ ገና የሕዝቡን የልማት ጥያቄ መመለስ የሚችልበት ደረጃ ላይ አልደረሰም›› ሲሉም አስገንዝበው፣ ለእዚህም በጥናት በተደገፈ መንገድና ያለውን ውስን ሀብት ለላቀ ጥቅም የማዋል ሂደትን መከተል እንደሚገባ አስታውቀዋል። የዚህ አይነት ምክክሮች የሕዝቡን ዘላቂ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የጎላ ሚና እንዳላቸው አመላክተዋል።

በ10 ዓመቱ መሪ እቅድ መሰረት ለሚቀጥሉት 10 ዓመታት የሚሰሩ መንገዶች መለየታቸውንና ቅድሚያ በሚሰጣቸው ላይም ግልጽ መስፈርት መቀመጡን ጠቅሰዋል። ሁሉም አካባቢ ያለውን ሕዝብ ከሀገራዊ ለውጡ እኩል ተጠቃሚ ለማድረግ፤ አዳዲስ የልማት መዳረሻዎችን መክፈት የሚቻልበት ምቹ ሁኔታ መፈጠሩን ገልፀዋል። ይህም በእርዳታ፣ በብድር፣ በኢኮኖሚ ትብብር ከውጭ የሚገኝ እንዲሁም በኢኮኖሚ ማሻሻያው ምክንያት የመጣውን የውጭ ምንዛሪ እንዲሁም በዘርፉ የበለጠ ኢንቨስት የሚደረግ የአገር ውስጥ ገንዘብ አንደሚገኝ ታሳቢ እንደሚደረግ ጠቅሰው፣ ይህንን ሀብት በተሻለ ለመጠቀም እድል እንደሚፈጥር ተናግረዋል።

ጥገና ከሚያስፈልጋቸው መንገዶች አኳያ መንገዶቻችን ረዘም ያለ አገልግሎት የማይሰጡበት አንዱ ምክንያት እንደ አገር ለጥገና የምንመድበው በጀት ዝቅተኛ ከመሆኑ ጋር እንደሚያያዝ አመልከተዋል። አንዳንዶቹ መንገዶች የዲዛይን ጊዜያቸውን የጨረሱበትና ለብልሸት የተዳረጉበት ሁኔታ እንዳለም ጠቁመዋል።

ለአብነትም የአዲስ አበባ ቡታጅራ ሶዶ መንገድ የዲዛይን ዘመኑን መጨረሱን አመልክተው፣ ይሄንን በጥገና የማንዘልቀው በመሆኑም የመንገዱን ደረጃ ማሻሻል አለብን ተብሎ በቅርቡ ጨረታ ወጥቷል ሲሉም ጠቁመዋል። ከአዲስ አበባ ዓለም ገና ድረስ ያለው መንገድ በሆለታ በኩል ከሚሄደው ሎት ስር ተካቶ ጨረታ መውጣቱን ጠቁመው፣ ከዓለም ገና ቡታጅራ ድረስ ያለውም በተመሳሳይ ጨረታ ወጥቶ፣ ፋይናንስ ተከፍቶ ቦርድ በሚያፀድቅበት ሂደት ላይ መሆኑንም አስታውቀዋል።

ከቡታጅራ ሆሳዕና፣ ከሆሳዕና ሶዶ ያለው መንገድ ግንባታም በየደረጃው እንደሚተገበር ጠቁመዋል። በሌሎች መንገዶችም በዚህ ዓመት አንዱ አጀንዳ ተደርጎ የተወሰደው የመንገድ አሴት አስተዳደር እና የጥገና ጉዳይ መሆኑን ጠቅሰው፣ ለዚህ የሚመደበው በጀት አጠቃላይ የመንገድ አሴት አስተዳደሩ እና ጥገናው ላይ ያለውን ችግር በዘላቂነት አንደሚፈታ እንደሚጠበቅም አስታውቀዋል።

በኃይሉ አበራ

አዲስ ዘመን ቅዳሜ ነሐሴ 25 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You