በማዕድን ዘርፍ ዳታ በማመንጨት ቀዳሚው ኢንስቲትዩት

ኢትዮጵያ በማዕድን ሀብቷ የበለጸገች ሀገር ብትሆንም ቀደም ባሉት ጊዜያት ይህንን ሀብቷን ጥቅም ላይ በማዋል ረገድ የተሰሩ ሥራዎች እምብዛም አልነበሩም። ይሁንና አሁን ለኢኮኖሚ አስተዋጽኦ ያበረክታሉ ተብለው ከተለዩት አምስት ዘርፎች አንዱ ሆኗል። በመሆኑም በዘርፉ መሻሻሎችና ለውጦች እየታዩ ነው።

እንደ ሀገር ያሉትን ማዕድናት ጥቅም ላይ በማዋል ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ እንዲያስገኙ ከማድረግ አኳያ ዘርፈ ብዙ ሥራዎች እየተሰሩ ነው። በተለይ በማዕድን ዘርፍ በሚሰሩ ተቋማት አማካኝነት የማዕድናት አለኝታ ቦታዎች በመለየት በዘርፉ ለመሰማራት ለሚፈልጉ ባለሀብቶች ምቹ ሁኔታዎች ለመፍጠር የሚያስችሉ በርካታ ሥራዎች እየተሰሩ ነው። በዚህ ዘርፍ ከሚሰሩት ተቋማት መካከል የረጅም ጊዜ ልምድ ያካበተው የኢትዮጵያ ጂኦሎጂካል ኢንስቲትዩት ተጠቃሽ ነው፡፡

ኢንስቲትዮቱ በአዋጅ በተሰጠው ስልጣንና ተግባር መሠረት የማዕድናት አለኝታ ቦታ በመለየትና ዳታ በማመንጨት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ ይገኛል። ኢንስቲትዩቱ የረጅም ጊዜያት ልምድ ያለው እንደመሆኑ በአገሪቱ የሚገኙ ማዕድናት ላይ ጥናት እያደረገ የአለኝታ ቦታ በመለየት የሰበሰበውን ዳታ በዘርፉ ኢንቨስትመንት ለመሳተፍ ለሚፈልጉ አካላት እየሰጠ ይገኛል።

አቶ ኢጃራ ተስፋዬ የኢትዮጵያ ጂኦሎጂካል ኢንስቲትዮት ዋና ዳይሬክተር ናቸው። እሳቸው እንደሚሉት፤ ኢንስቲትዮቱ የተቋቋመው በእ.ኤ.አ 1968 ነው። የተቋቋመበት ዓላማ በዋናነት የሥነ ምድር መረጃን ማመንጨት ነው። የሥነ ምድር መረጃ ስንል የማዕድን ፍለጋ፣ የጂኦተርማል፣ የሥነ ምድር አደጋ እና የመሳሳሉት ሥራዎች ላይ የተለያዩ ማጥኛ ዘዴዎች ተጠቅሞ ያጠናል። ጥናቱ ሲጠናቀቅ የተገኘው ዳታው ለሚመለከተው አካላት ይሰጣል። በተጨማሪም የማማከር ሥራንም ይሰራል። እንዲሁም አብዛኞቹ አገሪቱ ውስጥ የሚገኙ ማዕድናትና ማዕድንነክ ምርመራዎች የላብራቶሪ አገልግሎትም ይሰጣል።

ኢንስቲትዮቱ ዘርፈ ብዙ ስራዎችን ይሰራል። በተለይ በማዕድን ዘርፉ ቀዳሚ አድርጎ ትኩረት ሰጥቶት እየሰራ ያለው አገሪቱ ማዕድኑ እያላት ከውጭ የምታስገባው የማዕድናት ውጤቶች ላይ ነው። ይህም ከውጭ የሚገቡ የማዕድናት ውጤቶችን በሀገር ውስጥ የመተካቱ ሂደት በመንግሥት አቅጣጫ ተይዞ እየተሰራበት መሆኑን ዋና ዳይሬክተሩ ያመላክታሉ፡፡

ኢትዮጵያ ብዙ አይነት ማዕድናት ይኑራት እንጂ እስካሁን ባለው ሁኔታ ሀብቱን በሚፈለገው ልክ ጥቅም ላይ ለማዋል የሚያስችሉ ሥራዎች አልተሰሩም የሚሉት ዋና ዳይሬክተሩ፤ በዚህ የተነሳ እስካሁን አገሪቷ ማዕድኑ እያላት ከውጭ የማዕድናት ውጤቶችን በማስመጣት እየተጠቀመች እንደምትገኝ ይገልጻሉ። አገሪቷ ከውጭ የምታስመጣው ማዕድኑን ሳይሆን ፕሮሰስ የተደረገው የማዕድን ውጤት መሆኑንም ይገልጻሉ። ለአብነትም ብረት፣ ማዳበሪያ፣ ማርብል፣ የድንጋይ ከሰል፣ ሴራሚክን እና ሌሎች ማዕድናት መጥቀስ ይቻላል፡፡

ዋና ዳይሬክተሩ እንዳብራሩት፤ የኢንስቲትዩቱ የማዕድን ዘርፍ ዋንኛ ሥራም ከውጭ የሚገቡ ኢንፖርት የሚደረጉ ምርቶች ላይ መሠረት ያደረገ ነው። ይህም ሲባል የመጀመሪያው ከውጭ የሚገቡ ምርቶች በሀገር ውስጥ ለመተካት የሚያስችል ዳታ ማመንጨት ነው። ዳታ ከመነጨ በኋላ በዘርፉ ለመሰማራት የሚፈልግ ኢንቨስተሮች ከሠሩበትና ፕሮሰስ ከተደረገ ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ መተካት ያስችላል። ሁለተኛው አሁን ላይ ዓለም ያመጣቸው ወይም እያነሳቸው ያለው ዋነኛ ማዕድናት/ ክሪቲካል ሚኒራል/ የሚባሉ አሉ። እነዚህ አሁን ላይ ዓለም አቀፍ ደረጃ የሚፈልጉና ትኩረት ተደርጎባቸው የሚሰራባቸው ማዕድናት ላይ ኢንስቲትዩቱም እንደ ሀገር ትኩረት ሰጥቶት እየተሰራ ነው።

ለአብነት መኪና ብንመለከት በነዳጅ መጠቀም ትተን ወደ ኤሌክትሪክ መቀየር እንደማለት ነው። ወደ ኤሌክትሪክ ሲቀየር ደግሞ ሊትየም፣ ኮባልት፣ ግራናይት፣ ኮፐር እና የመሳሰሉ ማዕድናት ያስፈልጋሉ። በአሁኑ ወቅት ደግሞ አብዛኛዎቹ የኤሌክትሪክ መኪና ወደ ኢትዮጵያ እየገቡ እንደመሆናቸው መጠን የእነዚህ መኪኖች አካላት ሆነ ባትሪ ለመስራት የማዕድን ውጤቶች ጥቅም ላይ የሚውሉ መሆኑን ጠቅሰው፤ እነዚህ ዓለም ትኩረት ያደረገባቸው ማዕድናት ላይ ለመስራት ጥናት እየተደረገ መሆኑንም ያስረዳሉ፡፡

ሦስተኛው ደግሞ መቼም ቢሆን ፍላጎቱ የማይቆም ማዕድን አይነት አለ። ለምሳሌ፤ እንደ ወርቅ አይነት ማዕድን፤ ይህንንና ሌሎች መሰል ማዕድናት ላይ ጥናት ያደረጋል። ኢንስትቲዮቱ በማዕድናት ላይ የሚሰራቸውን ሥራዎች በእንደዚህ መልኩ ከፋፍሎ እየሰራ መሆኑን ዋና ዳይሬክተሩ ያብራራሉ።

ኢትዮጵያ ብዙ ማዕድናት አይነቶች እንዳሉት ቢታወቅም ነገር ግን ጥልቀት ያላቸው ጥናቶች አልተጠኑም ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ፤ ይህ እንዳይሆን ያደረጉት ምክንያቶች ብዙ ቢሆንም ከእነዚህ መካካል ቀደም ባሉት ጊዜያት የማዕድን ዘርፉ ትኩረት ተነፍጎት የቆየና ብዙ ኢንቨስት ያልተደረገበት መሆኑ በዋናነት ያነሳሉ። ዘርፉ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ግን ትኩረት አግኝቶ ከአምስቱ የኢኮኖሚ ዘርፎች አንዱ መሆኑ ጥሩ መስመር እንዲይዝ ያደረገው መሆኑን ያመላክታሉ። ‹‹የማዕድን ዘርፉ ትኩረት አግኝቶ ሥራዎች እየተሰራበት ነው ስንል ብዙ ተግዳሮቶች ከፊታችን አሉ። ተግዳሮቶች ቢኖሩም የምንወጣቸው ናቸው›› ይላሉ።

በማዕድን ዙሪያ ምን ተሰራ ብለን ስንጠይቅ እዚያ ቦታ ላይ በዚህ ያህል መጠን እንደዚህ አይነት ማዕድን አለ የሚለው በደንብ መታወቅ አለበት። ይህንን ለማድረግ ደግሞ ጅምር ሥራዎች ቢኖርም ገና ብዙ አይነት ጥናቶች ያስፈልጋሉ። አንድ ቦታ ላይ ያለን ማዕድን ለማወቅና ለመለየት ከመጀመሪያ እስከመጨረሻው ድረስ ዘርፈ ብዙ ጥናቶች ይደረጋሉ፤ በዚያው ልክ ወጪውም ብዙም ነው። ይህም ደግሞ በጀት፣ የተማረ ሰው ኃይል እና ሌሎች ነገሮችን ይፈልጋል። እነዚህ ነው ከሰራን ብዙ ስራዎች መስራት ይቻላል ሲሉ ተናግረዋል፡፡

ቀደም ባሉት ጊዜያት የተሰሩ የተወሰኑ ስራዎች ቢኖሩም ኢትዮጵያን የሚመጥን ሥራዎች ተሰርተዋል ማለት አይቻልም፤ ያሉት ጥናቶች በጥልቀት ያልተጠኑ ውስን ናቸው›› የሚሉት ዋና ዳይሬክተሩ፤ ዘርፉ ትኩረት ከተሰጠ በኋላ ግን በተመረጡና ወሳኝ በሆኑ ማዕድናት ላይ ብዙ ሥራዎች ለመስራት ታቅዶ እየተሰራ መሆኑን አስታወቀዋል፡፡

እንደ እሳቸው ማብራሪያ፤ ኢንስቲትዮቱ በ50 ዓመታት እድሜ ውስጥ በርካታ የሥነ ምድር ዳታዎች አመንጭቷል። የማዕድናት አለኝታ ቦታዎች ከመለየት አኳያ ሰፊ ሥራዎች ተሰርተዋል። የከበሩ ማዕድናት ብዙ አለኝታ ቦታዎች ተለይተዋል። የባሕላዊ ወርቅ አመራረት ላይ ጥናቶች ተጠንተዋል፤ ብዙ ምርትም ተገኝቷል። የጂኦተርማል የአለኝታ ቦታዎች በጥናት ተለይተዋል።

በ2016 በጀት ዓመት በማዕድን ዘርፍ በርካታ ሥራዎች ተሰርተዋል። የኢንስቲትዩቱ የሥነምድር ዳታን ያመነጫል ሲባል የተቋሙ ባለሙያዎች በየመስኩ በመገኘት ጥናትና ምርምር ያደርጋሉ፤ ናሙናዎቹ ተሰብስበው ላብራቶሪ ገብተው ትንተና ከተሰራላቸው በኋላ ተገምግሞ ሪፖርቱ ይዘጋጃል። በዚህ ሂደት ዘንድሮ የተጀመረው ሥራ ሪፖርቱ በሚቀጥለው ዓመት ነው የሚደርሰው። ምክንያቱም በዘንድሮ ዓመት መስክ ተወጥቶ ናሙናዎች ተሰበስበው ላብራቶሪ ይገባሉ፤ ከዚያ አስፈላጊውን ሂደቶች ጠበቆ ስለሚሰራ ረጅም ጊዜያትን ሊፈጅ ይችላል ሲሉ አስረድተዋል።

በዚህ መሠረት በዘንድሮ ዓመት የተጀመረው ሥራ ሪፖርት የሚደርሰው በሚቀጥለው ዓመት በ2017 ነው ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ፤ በዘንድሮ ዓመት ብዙ ክልሎች ላይ የድንጋይ ከሰል፣ የደለል ወርቅ፣ የኒኬል ማዕድን፣ የኢንዱስትሪያል ማዕድን፣ የሊትየም እና የብረት ማዕድናትን የአለኝታ ቦታ ልየታ መስራቱን ያመላክታሉ። በተያዘው በጀት ዓመት በተለያዩ ክልል የጂኦሎጂ ካርታ፣ ጂኦኬሚስትሪ ጥናት፣ የሥነ ምድር አደጋ፣ የጌጣጌጥ ማዕድናት፣ እና ጂኦተርማል የአለኝታ ቦታ መካሄዱንም ይገልጻሉ። የአለኝታ ቦታ ልየታ ከተሰራባቸው ክልሎች መካካል ሲዳማ ክልል የደለል ወርቅ፣ ጅማ ዞን የድንጋይ ከሰል፣ ደቡብ ክልል ምዕራብና በጋምቤላ ክልል የኒኬል ማዕድን፣ ሐረርና ምስራቅ ሐረርጌ ኢንዱስትሪ ማዕድን፣ ድሬዳዋ አካባቢ ሊትየም ማዕድን፣ ሱማሌ ክልል እና ምስራቅ ሐረርጌ አካባቢ፣ ብረት ማዕድን፣ ደቡብ ምዕራብና ጋምቤላ አካባቢ ክሮማይት፣ ደቡብ ኢትዮጵያ ጌጣጌጥ ማዕድን ላይ መስራቱን አስታውቀዋል።

የጂኦፊዚክስ ምርምር በድሬዳዋ አካባቢ፣ የጂኦተርማርል ሲዳማ ክልል እንዲሁም ደቡብ ኢትዮጵያ ክልል መሰል ሥራዎች ተሰርተዋል። የጂኦተርማል ሰፋ ያለ ቦታዎች የያዘ መሆኑን ገልጸዋል። በእነዚህ በተጠቀሱት ቦታዎች ላይ የተገኙት ማዕድናት ዳታዎች ተሰብሰበው የላብራቶሪ ውጤታቸው እየወጣ ሪፖርታቸው እየተዘጋጀ መሆኑን ይገልጻሉ፡፡

በኢትዮጵያ በማዕድን ዘርፉ ኢንቨስት ለማድረግ የሚፈልጉ ባለሀብቶችና ተቋማትም በሁሉም የአገሪቷ አካባቢዎች ቢሰማሩ ብዙ መልካም እድሎች እንዳለሉ የጠቆሙት ዋና ዳይሬክተር፤ በአገሪቱ ብዙ ጥልቅ ጥናት ስላልተጠና ብዙ የማዕድን ሀብት እንዳልወጡ ያመላክታሉ። እሳቸው እንደሚሉት፤ የኢትዮጵያ ጂኦሎጂ ጥናቶች የሚያመላክቱት የማዕድን ሀብት ክምችት በታወቁ ቦታዎች አሉ። በአገሪቷ ሰሜን፣ ምዕራብና ደቡብ አካባቢዎች በአብዛኛው የወርቅ፣ ብረት እና ሌሎች ይገኛሉ። በምስራቅ አካባቢ ደግሞ በአብዛኛው የግንባታ ማዕድናት የሚገኝ ሲሆን፤ በመሀል አገር የኢንዱስትሪ ማዕድናትና የከበሩ ማዕድናት ይገኛሉ ።

ስምጥ ሸለቆም እስከ 10ሺ ሜጋ ዋት ጂኦተርማል ኃይል ማመንጨት የሚያስችል ሲሆን፤ ሰሜን አካባቢ የትግራይ አካባቢ የከበሩ ማዕድናት፣ ወርቅ እና ሌሎች ማዕድናት ይገኛል። የአፋር ክልል ጂኦተርማል፣ ፖታሽና ሌሎች በርካታ ማዕድናት አሉ። የሱማሌ ክልልም እንዲሁ ነዳጅ እና ሌሎች ማዕድናት እንዳሉት ይታወቃል።

በሌላ በኩል ኢንስቲትዩቱ በአገሪቱ ውስጥ በማዕድን ዘርፉ ላብራቶሪ አገልግሎት በመስጠት ቀዳሚ የሆነ የማዕድን ላብራቶሪም እንዳለው ዋና ዳይሬክተሩ ይገልጻሉ። ይህ ላብራቶሪ ለራሳቸውና ለውጭ ተጠቃሚዎች አገልግሎት እንደሚሰጥ ይጠቅሳሉ። ቀደም ባሉት ጊዜያት ላብራቶሪው በማዕድን ዘርፉ በምስራቅ አፍሪካ አሉ ከተባሉት ላብራቶሪዎች መካከል አንዱ እንደነበር ጠቅሰው፤ ዘርፉ ትኩረት ተነፍጎት በመቆየቱ የተነሳ በየጊዜ እየተዳከመ መምጣቱንና ድሮ ከነበረበት መውረዱን አልሸሸጉም። ያም ቢሆን ታድያ እንደገና በማደራጀት ብዙ ሥራዎች እየተሰሩ እንደሆነ አመላክተዋል። ‹‹አሁንም ቢሆን በላብራቶሪ ውስጥ ብዙ ሥራዎች ይሰራሉ። ለምሳሌ ያህል ኢትዮጵያ የምትገዛው ብሔራዊ ባንክ የሚገባው ወርቅ በዚህ ላብራቶሪና በቅርንጫፍ ባሉ ላብራቶሪዎች አማካኝነት በመሆኑ ላብራቶሪው አይተኬ ሚና አለው›› ይላሉ።

በላብራቶሪው ብዙ አይነት ምርመራ እንደሚሰጥ የጠቀሱት ዳይሬክተሩ፤ ላብራቶሪ እንደ ድሮ አይደለም፤ መሳሪያዎቹ እያረጁ ስለሆኑ የሚጠቀሙባቸው ኬሚካሎችም ሆነ መሳሪያዎች እና ሌሎች ግብዓቶች ኢምፖርት የሚደረጉ ናቸው ብለዋል። ይህ ደግሞ ትልቅ ተግዳሮት ሆኖ ቢቆይም አሁን ላይ ተስፋ ሰጪ ነገሮች እየታዩ መሆኑን አመላክተዋል። መንግሥትም ትኩረት ሰጥቶት እየተሰራ በመሆኑ ላብራቶሪውን የማዘመን ሥራ እየተሰራ መሆኑን አስገንዝበዋል።

ኢንስቲትዮቱ በማዕድን ዘርፍ የሚሰራቸው አብዛኞቹ ሥራዎች የመስክ ሥራዎች በመሆናቸው የበርካታ አጋር አካላት ተሳትፎና ትብብርን ይጠይቃል። በዚህ የተነሳ ብዙ ችግሮች ያጋጥማሉ ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ፤ ለአብነትም የሰላም ሁኔታን አንስተዋል። በቂ የሆነ ተሽከርካሪዎች አስፈላጊ እንደሆኑም ጠቅሰዋል። የሠራተኞች ፍልሰት፣ ኢንፖርት የሚያደርጉ ኬሚካሎች፣ የመመርመሪያ መሳሪያዎች፣ መለዋወጫ ያለመገኘት እና የመሳሳሉት ተግዳሮቶች ይጠቅሳሉ። አሁን ላይ ለዘርፉ ትኩረት ስለተሰጠው ጥሩ ተስፋ ሰጪ ነገሮች እየታዩ መሆኑን ጠቅሰው፤ እነዚህን ተግዳሮቶች ለመቅረፍ እየተወሰዱ ያሉ እርምጃዎች ስላሉ ችግሮቹ በአጭር ጊዜ የሚፈቱ መሆናቸውን አስታውቀዋል።

የኢንስቲትዩቱ የማይነካው ዘርፍ የለም፤ ማዕድን፣ ኢነርጂ፣ ቱሪዝም፣ ውሃ፣ ግንባታ እና መሰል ዘርፎች ይነካል የሚሉት ዋና ዳይሬክተሩ፤ እንደተቋም በቀጣይ የተያዘው አቅጣጫ ደግሞ ከዓለም ጋር አብረው መሄድ የሚጠይቅ ነው። ምክንያቱም ዓለም የሚፈልጋቸው ማዕድናት ላይ እንደ ሀገር የሚሰሩ ሥራዎች መኖራቸው ይጠቅሳሉ። የመጀመሪያው ግን ኢንፖርትን የሚተኩ ማዕድናት ቅድሚያ በመስጠት የሚሰራባቸው ሲሆኑ፤ አገሪቷ ማዕድኑ እያላት ኢንፖርት የምታደርጋቸው የማዕድናት ውጤቶች ላይ ዳታ በማመንጨት ሥራ የሚሰራ መሆኑን አመላክተዋል።

ሁለተኛ በየጊዜው የማዕድን ፍላጎት ይቀያየራል። የዓለም አገራት አሁን ላይ የሚፈልጉት ማዕድናት ላይ እንደ ሀገር ደግሞ ዳታ በማመንጨት ሥራዎች ይሰራሉ። በጂኦተርማል፣ በሥነምድር አደጋዎች ላይ አስፈላጊ የሆኑ ሥራዎች ይሰራሉ። ይህ ሁሉ ሥራ እንዳለ ሆኖ ኢትዮጵያ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ በማውጣት ወደ ሀገር ውስጥ በምታስገባቸው ማዕድናት ላይ በትኩረት ይሰራል ሲሉ አስረድተዋል፡፡

በተጨማሪም አሁን ላይ የአለኝታ ቦታ ልየታ እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰው፤ የተወሰኑ አቅም ወይም ኃይል በማሰባሰብ ወሳኝ ወደ ሆነው የክምችት ግምት የሚገባቸው የማዕድን አይነቶች መኖራቸውን ገልጸዋል። በሌላ በኩል ኢንስቲትዩቱ በማዕድን ዘርፉ የሚሰበሰቡ ዳታዎችን መረጃ ለሚፈልጉ የተለያዩ አካላት እያሰራጨ መሆኑን ዋና ዳይሬክተሩ አስታውቀዋል።

ወርቅነሽ ደምሰው

አዲስ ዘመን ነሐሴ 24 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You