ቲያጥሮን ምን በላው?

ቲያጥሮንን የበላ፣ ቲያትርን የነከሰ ጥርስ መኖሩ እርግጥ ነው። ውስጥ ውስጡን ደግሞ ጥቁር ሀሩንም ሆነ ወርቃማውን ቲያትር ሽበት ወሮታል። በሆነ ዘመን ላይ ደግሞ ቲያጥሮንን አስረክበን ቲያትርን ተቀብለናል። የተቀበልነውም በሽበት ተወሮ ከአናቱ ላይ ችፍፍ ብሏል። የጥቁር ዞማው በነጭ ሽበት ተለውጦ፣ ከጀርባ በወገብ አልፎ ተነስንሷል።

ቲያጥሮንም ቲያትር ነኝ ሲል ራሱን ክዷል። እና አሁን የምንመለከተው የኛ ቲያጥሮን ወይንስ የእነርሱ ቲያትር…ለዚሁ ምላሽም ከዕለታት በአንዱ ቀን የቀጠሮዬን ሰዓት ተጠባብቄ ወደ ጸሀፊ ተውኔትና ባለቅኔው አያልነህ ሙላት ዘንድ አመራሁ። አራቱን የመኖሪያ ቤቱን ደረጃዎች ሳለከልክ ወጥቼ ከማማው ቢሮው ላይ አገኘሁት። ከቲያጥሮን እስከ ቲያትር ብዙ ቢለኝም ለመጻፍ የቻልኩት ግን ጥቂቷን ብቻ ነው።

ከዚሁ የቲያትር ፎቴ ላይ ፊቱ ቁጭ ብዬ ገና በጥያቄ ስጀምር ነበር፤ “ቲያጥሮን የሚል የግእዝ ቃል እንዳለን ታውቃለህ?” ሲል ጥያቄዬን በጥያቄው አከናነበው። እርግጥ ነው አብዛኛዎቻችን ቲያትርን እንጂ ቲያጥሮንን አናውቅም። ለተራው ቀርቶ ለምሁራኑም የቸገረ ዓይነት ነው። ቃሉ የግእዝ ሲሆን በብዙ ጥንታዊ የብራና ጽሁፎች ውስጥም እናገኘዋለን። ትርጉም ካሉም ዛሬ “ቲያትር” ለምንለው የተውሶ ቃል አባት ለመሆኑ ጥርጥር የለውም። አያልነህም ከማያቆርጠው ጥልቅ ጥያቄው ጋር ቀጠለ፤ ”ቲያትር ሳይኖር ቲያጥሮን ከየት መጣ? እስካሁን ይህን እንኳን ለመተርጎም አልቻልንም። …ስለዚህ መጀመሪያም ቲያትር (ቲያጥሮን) ነበረን።

ላሊበላን ያህሉን ሠርቶ፣ ላሊበላ የሚባሉ አዝማሪያንን፣ አልቃሾችን…በሰበሰበ የዛግዌ መንግሥትና ማኅበረሰብ ቲያትር አልነበረም ማለት አይቻልም። የጎንደርን ሕንጻዎች ብንመለከት በውስጥ የቲያትር አዳራሽ፣ የቲያትር መድረክ አለ…” በማለት በወኔ በታጀበ አንደበቱ ገለጸልኝ። ያለው እውነት ነበር። እሳት ባልነደደበት አመድ አይታይምና ቲያትር ሳይኖር ቲያጥሮን የሚል የግእዝ ቃል ባልኖረን ነበር። ነገር ግን፤ “ቲያጥሮን”ን በጅብ ይሁን በቁማር የተበላን ዕለት ነበር ቲያትርን በማስተዛዘኛነት የተቀበል ነው። ተቀብለንም ዛሬ ላይ ቲያትር መቶ ዓመት ሞላው ስንል ከተበላን እንጂ እንደ አዲስ ከተዋወቅነው ከመሰለን ተሳስተናል። በየዓመቱ የምናከብረው የቲያትር ልደትም ቢሆን የእነርሱ እንጂ የኛ አለመሆኑን ልብ ይለዋል።

“ቲያትር መቶ ዓመት ሞልቶታል እንላለን፤ ግን የፈረንጅ እንጂ የኛ አይደለም። በቲያትር መድረክ ላይ የምንጠቀማቸው ነገሮች የኛ አይደሉም። በብሔር ብሔረሰቦች ላይ የተገነባ ነገር የለንም።”

ታዲያ ይህ ሁሉ እያለ ኢትዮጵያዊ ቲያትር አለ ለማለት ይቻል ይሆን? ኢትዮጵያዊ ቲያትር ስንልስ…እዚህ ጋር ቲያትር የሚለው ቃል ፈረንጂኛ በመሆኑ ሳይሆን ፈረስ ያለ ኮርቻ አይጋለብምና ይህን ቃል ስንረከብ አብረው የገቡ ነገሮች በመኖራቸውም ጭምር ነው። ጸሀፊ ተውኔት አያልነህ ቀደም ሲል ያነሳው ሀሳብ ነበርና አሁንም ለጥያቄው ሌላ ጥያቄ አከለ። “ለመሆኑ በመጀመሪያ ደረጃ ኢትዮጵያዊ ቲያትር የምንለው በአማርኛ ስለተሠራ ነው?…” የሚል ጥያቄያዊ ምላሽ የጫነውን ጣል በማድረግ “የኔ ቲያትር ተተርጉሞ በእንግሊዝም ሆነ በጣሊያን ሀገር ታይቷል… እና ታዲያ በእንግሊዝኛ ስለተሠራ ቲያትሩ የእንግሊዝና እንግሊዛዊ ሆነ ማለት ነው? … አይደለም!” ከዚህ በመቀጠልም ኢትዮጵያዊ ቲያትር ልንል የምንችለው ከቱባው ባህሏ ጋር ራሷኑ ኢትዮጵያን የሚመስል መሆን እንዳለበት አስቀመጠ። ኢትዮጵያ ግን መልኳ የማን ነው? በማንስ እንመስላት? …ከሳለው መልክና ምስል በኋላ፤ በቲያትር ውስጥ ይህን መልክ ያጠለሹት ነገሮችንም አንስቷቸዋል።

የዚህ አንደኛውና ዋነኛው ችግር የሚመዘዘውም ቲያጥሮን ከስሞ ቲያትር መለምለም ከጀመረበት ጊዜ ነው። በልምላሜው ማግስት ከእኛነት ባህር እየተሻገርን ወደ እነርሱነት መትመም ጀምረን ነበር። ለዚህ ማሳያ የኛ ከሆነው ይልቅ በእነ ሼክስፒርና ፑሽኪን ቲያትሮች ተከትበን ነበር። በዩኒቨርሲቲ ደረጃ ሳይቀር የቲያትር ትምህርት ቤቶች ቢኖሩም ትምህርቱ ግን የእንግሊዝኛው ግልባጭ ትርጉም፣ የእነ ሼክስፒር ሀ ሁ ነበር። በእኛው አማርኛ የእነርሱን የቲያትር ካልኩሌሽን ነበር የምናጠናው። የቲያጥሮንን ባንዲራ ቀደን፣ የቲያትርን ዓርማ ከልባችን ላይ ሳይቀር ሰቅለነዋል። እናም እንደነበረው አቀባበላችን እና ትምህርታዊ የቲያትር ሥርዓታችን ቢሆን ኖሮ፤ ጥያቄው ኢትዮጵያዊ ቲያትር አለ ወይ? ብቻ ሳይሆን ነበር ወይ? እንድንል ጭምር የሚያስገድደን ነበር። ዳሩ እንዲህ ቢሆንም፤ በየዘመናቱ የኢትዮጵያን የቲያትር ጽላት ተሸክመው እዚህ ባደረሱ የቲያትር ባለሙያዎች እና መሰሎቻቸው ብርታት “የለም!” እንዳንል አድርገውታል። መሠረቱ በተናወጠው የእሳት ባህር ላይ እየቀዘፉም ቢሆን በቲያትሩ ውስጥ ኢትዮጵያዊነት እንዳይጠፋበት መስዋዕትነት ከፍለዋል። በልዩነት የምናመሰግነው ዘመንና በልዩነት የምናመሰግናቸው የቲያትር ጠቢባን መፈጠራቸውም እንዲህ ባለው ውስጥ ነው።

ያለፈው ተከድኖ ይብሰልና ከዚህ ሁሉ ማዕበል ውስጥ ሆኖ ወርቃማ የቲያትር ዘመን ነበር ስለምንላት ጉዳይም እናንሳለት። ጉዳዩ ማንንም በክርክር የሚያካርር አይደለም። አሁን እዚህ ሆነን በቲያትር ሽበት የተወረርን የሚመስለን ቲያትር ድኩማን ሁሉ፤ ዞረን ወደኋላ ብርቱ ወጣት የነበርንበትን እየናፈቅን፣ በጉብዝናችን ወራት በትዝታ ሽበታችንን እንደምናሽ እርግጥ ነው። ታዲያ ያን ትዝታ በውስጡ ሆነው ለኖሩት ለእነ አያልነህ ሙላትስ የኛ እውነት የእነርሱም ሀቅ፣ የኛ ትውስታ የእነርሱም ትዝታ ይሆን? እኛ ወርቃማ በምንለው ውስጥ እነርሱ ነበሩ። የነበሩ እነርሱስ ወርቃማ የሚሉት የትኛውን ነው? “አዎን ወርቃማ ዘመን ነበር…አብዮት የሚባለው ነገር ሲመጣ በጊዜው ብዙ ሕዝብ አልቋል።

ብዙ ወጣትም ተቀጭቷል። ነገር ግን በጥበቡ ዓለም ውስጥ ሰላማዊ የሚባለው ጊዜ ነበር። ቀደም ሲል በዘውዱ ሥርዓት የነበሩትም ያለምንም ልዩነት ቀጥለዋል። አዳዲሶችም ወጥተው ሁሉም በአንድነት ተቀነባብሮና ተዋህዶ መሥራት ጀመረ። …እንደ ጋሽ ጸጋዬና አቶ መንግስቱ ለማም ይጽፉና ይጠይቁ ነበር። ሌሎች ብዙዎችም ነበሩ። ሁላችንም የምንሠራው በአንድነት ተዋህደን ስለነበረ ያ ነገር ጥንክሬ ሆኖነናል። የቀደመውና አዲሱ በሚገባ ስለተዋሃደም ወርቃማ ዘመን ለመባል በቅቷል” ይላል ጸሀፊ ተውኔቱ አያልነህ ሙላት። እንደ ብዙዎች እሳቤም ወርቃማው ዘመን ማለት ብዙዎች የሚጠቅሱትን ያን 70ዎቹን ነበር።

በጊዜው የኛ ዳግማዊ ቲያጥሮን ባይወለድም እንደ ቲያትር ግን ኢትዮጵያና የኢትዮጵያ ሕዝብ ከፍ ብለው እንዲታዩ ከመስዋዕትነት ጋር ቆመዋል። “ማን ይናገር የነበረ ማን ያርዳ የቀበረ” እንዲሉ አያልነህ ራሱ ከወርቃማው ዘመን ባለወርቆች አንዱ ነበር። ቲያትር የሕዝብን እንባ አባሽ፣ ቲያትር የሀገር ሰላም ፈጣሪ፣ ቲያትር ሕዝብን አጽናኝ፣ ቲያትር መሪን መካሪ ካልሆነ ምኑን ቲያትር ሆነ? የሚል ውስጣዊ መርህ ያላቸው ይመስል ነበር። በእርግጥም መሆን የነበረበትም እንዲያ ነው። በዚህ ወርቃማ ቲያትር በመሥራት ፍጥጫ ውስጥ ከፊት ከነበሩት መካከል ሎሬት ጸጋዬ ገ/መድኅን፣ መንግሥቱ ለማ፣ ጸሀፊ ተውኔት አያልነህ ሙላትን ጨምሮ ጥቂት አውራዎች ነበሩ። ያኔ መጀመሪያ ላይ አያልነህ ሙላት 3ኛ ዲግሪውን ሊማር ራሺያ ገብቶ ነበር። “ትምህርቴን ልጨርስ አካባቢ ጋሽ ጸጋዬ ወደ ራሺያ መጥቶ ነበርና ካልመጣህ ሲል ጎትቶ ይዞኝ መጣ። እኔ ከመምጣቴ ቀደም ብሎ ወደ ኢትዮጵያ ተመለሰ። ሲመለስም ጽፌ አዘጋጅቼው የነበረውን ‘እሳት ሲነድ’ የሚለውን ተውኔት ተሸክሞ መጣ።

አባተ መኩሪያን አዘጋጅ፣ ገብረ ክርስቶስ ደስታን ደግሞ በመድረክ ዲዛይን፣ በጣም የታወቀውን ተፈራ አቡነ ወልድን ደግሞ በሙዚቃ አድርጎ እኔም በሌለሁበት ቆንጆ ሙዚቃዊ ተውኔት አድርጎ ሠራው” በማለት የሁለቱን መጀመሪያ አያልነህ ያስታውሳል። እሳቱም ደህና ይነድ ጀመረ። ከእነዚሁ ምሰሶዎች መካከል አያልነህ ከሎሬት ጸጋዬ ገ/መድኅን ጋር የበለጠ ትስስር ነበረው። ወርቃማውን ዘመን ለመሥራት ከከፈሏቸው መስዋዕትነቶችም፤ አንደኛው ሁለቱንም በአንድ ቀን በተመሳሳይ ሰዓት ከአንድ እስር ቤት፣ ከአንድ ክፍል ውስጥ አገናኝቷቸዋል። “እኔና ጋሽ ጸጋዬ ሁለታችንም የባህል ሚኒስትር ሠራተኞች ነበርን። እርሱ ቋሚ ተጠሪ፣ እኔ ደግሞ የቲያትር ጥበባት ድርጅት ኃላፊ ነበርኩ። በአንድ በጻፍኩት ቲያትርም በጣም ከባድ የሆነ…በደርግ መቃብር ላይ ሕዝባዊት ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ ትገነባለች… (ሻጥር በየፈርጁ) በሚለው ቲያትር ምክንያት ታሰርኩ። ጸጋዬን ደግሞ ሰበብ ፈልገው አንድ የደርግ አባልን ተሳድበሃል በማለት በአንድ ቀን ሁለታችንንም ወስደው እስር ቤት አስገቡን” ሲል፤ ካወሳው ውስጥ አንዱ ነበር።

በዚሁ መንደርደሪያ ወደ ቁጥቋጧው የቲያትርና ፖለቲካ ጋራ እንሻገር። ከቲያጥሮን መሰወር ወዲህ በሀገራችን ቲያትር አንገት ላይ ከቆሙ ነገሮች አንዱ ፖለቲካው ነበር። አንድም በፖለቲካ ተጨፍልቋል። ሁለትም በፖለቲካው ተረስቷል። በቀደሙት በዘውድና በደርግ ከበድ ባለ የሳንሱር ቡጢ ቢደቆስም እስከ ቤተ መንግሥት ድረስ ከፍ ያለ ቦታ ነበረው። በትንሹ ለማሳያነት…መሪዎቹ ሳይቀሩ በየቲያትሩ ምረቃና ልዩ ዝግጅት ላይ እየተገኙ ኋላም ባለሙያዎቹን ሸልመውና አበረታተው ይወጡ ነበር። ወዲህ ቀረብ ስንል ደግሞ የፈነዳው አብዮት ከከሰመ ወዲህ ውስጥ ውስጡን ስውር መርፌዎች ቢኖሩበትም ከላዩ ላይ የተጫነው ሳንሱር ግን ሊነሳለት ችሎ ነበር። ችግሩ ግን ጭነቱን እንዳነሱለት በል ደህና ሰንብት ተብሎ በዚያው ተረሳ። አትድረስብኝ! አልደርስብህም! ዓይነትም መስሎ ታየ። የቲያትሩ ቅዝቃዜና የሚያንሰፈስፍ ብርድ የሚጀምረውም ከዚሁ ነው። ይህንን በተመለከተም አያልነህ ሙላት ያነሳው ሀሳብ እጅግ ሰፊና ጥልቅ ቢሆንም በትንሽ በትንሹ መቀንጨቡ የግድ ነውና ካለውም…

“በመጀመሪያ ደረጃ እኛ ኢትዮጵያውያን ቀድሞ ያነበረብን ከባህላችን ውጭ የሆኑ ነገሮችን ተላምደናል። በመቀጠል ቲያትሩም ሆነ ኪነ ጥበብ ከፖለቲካ ውጭ የሚራመድ አይደለምና ፖለቲካው ሊመራውና ሊደግፈው ይገባ ነበር። ነገር ግን…በዚህም ምክንያት ኪነ ጥበብን ለኪነ ጥበብ የሚለው እሳቤ ይከሽፋል። …ኪነ ጥበብን ያልያዘ መንግሥት፣ በኪነ ጥበብ ያልተዋቀረ መንግሥት፣ የትም ሊደርስ አይችልም። አሁን አይደለም ትናንትና እንኳን አዝማሪውም ሆነ ሌላው አድዋ ድረስ ዘምቶ፣ በኪነ ጥበብ ተዋግቶ እያዋጋባት የመጣች ሀገር ናት። መንግሥትም ቢሆን እነዚህ ምን አሉ? እያለና የእነርሱን ቃል እየሰማ ነበር የሚሠራው። አሁን እዚያ አካባቢ ያሉ ነገሮች በሙሉ ትኩረት ተነፍጓቸው ቀስ በቀስ ፖሊሲ አልባ ሆነው ይታያሉ” የሚል ነበረበት። ኪነ ጥበብ በፖለቲካው ሥርዓት ውስጥ ፖሊሲ አልባ ሆኖ መሰንበቱን በተመለከተ በባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር የኪነ ጥበብና ስነ ጥበብ ዘርፍ ኃላፊዋ ክብርት ነፊሳ አልማህዲ በአንድ ወቅት ሲሉ የሰማሁትን አስታወስኩ። “በመንግሥት መዋቅር ውስጥ ኪነ ጥበብ የሚመራበት የራሱ የሆነ ፖሊሲ ሊኖረው የግድ ነውና ይህን ችግር ለመፍታት ሕገ ደንቦችን አርቅቀን ለማጸደቅ በመሥራት ላይ ነን” ሲሉ ነበር የተናገሩት። ይህ እውን ቢሆን በኪነ ጥበቡ ቅርጫት ውስጥ ላለው ቲያትርም እፎይታ ነበር። ካለፈው ወርቃማ ዘመን ልንወስደው የሚገባ አንድ ነገር አለ። ይኸውም ሙያውን በሙያው ላለ አዋቂ መስጠትን ነው። ለአብነትም ዛሬም ድረስ የምናወድሳቸው እነ ሎሬት ጸጋዬ ገ/ መድኅንና እነ ሜትር አርቲስት አፈወርቅ ተክሌን የመሳሰሉትን ፈርጦች ብንመለከት በፖለቲካው ውስጥም ትልቅ ሚና የነበራቸው ናቸው። በሠሩት ትልቅ ድልድይ ከፖለቲካው ጋር እንዲተያይ አድርገው ጉልበት ፈጥረውለታል። ዘርፉ የሚያስፈልገውን ያውቃሉና ከፖለቲካው ለኪነ ጥበብ የሚገባትን ቆርሰው ሲሰጡ ነበር። ድልድዩን ሠርተው ያን ዘመን አሻግረውታል። ለቲያትር ውድቀት አንደኛው ምክንያት ምናልባትም የዚህ ድልድይ መሰበር ይመስላል።

የሲኒማ ቤቱ ግዙፍ ጥላ በቲያትር ቤት አናት ላይ አጥልቶ ይሆን? እንደ አንድ ታዛቢ ምናልባትም እነዚህ ነገሮች ይታያሉ…አብዛኛው የቲያትር ባለሙያ ፊቱን ወደ ሲኒማው አዙሯል። የቲያትር ተመልካቹም ምርጫውን በፊልሞች ላይ አድርጎ ቲያትር ቤቱን አራቁቶታል። ዘመናዊነት ያመጣው ቴክኖሎጂ ደርሶ ከቲያትር ላይ ፊቱን አጥቁሯል። ስለእነዚሁ ሁለት ነገሮችስ አያልነህ ሙላት የሚለው ምን ይሆን…”በቲያትሩ ጠንከር ያሉ ጉዳዮች ቢሠሩ እንደኔ የፊልሙ ጉዳይ ለቲያትር የሚያሰጋ አይመስለኝም። በቲያትሩ ከመጀመሪያውም በተለያዩ ትላልቅ ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ ከቲያትር ዝግጅት አንስቶ ያስተምራሉ። ፊልም ግን ምናልባት በአንዳንድ የግል ተቋማት ውስጥ ካልሆነ በስተቀር በተለይ መጀመሪያ ላይ ምንም አልነበረውም። እየተሠራ ያለውም በቲያትር ቤት ዳይሬክተሮች ነው። በሲኒማውም ቢሆን አዲስ ነገር ልናይ አልቻልንም። …እናም ኢትዮጵያን የሚሸት ነገር ማምጣት እስካልቻልን ድረስ ቲያትር በፊልም እየተዋጠ ነው ብንል ለኔ ምንም ልዩነት የላቸውም” ይላል። ሆኖም ሲኒማው ላይ ብቻ ከማተኮር ባለሙያዎቹ ባሉበት ቲያትር ውስጥ ሆነው ትልቅ ነገር መሥራት ይኖርባቸዋል ሲልም ተናግሯል። ሲኒማውም ከቲያትር ጋር እኩል ጠቀሜታ አለውና መዘንጋት የለበትም።

አሁንስ በዚሁ እንቀጥል? ወይንስ ዳግማዊ ቲያጥሮንን እናንግሥ? “አሁን ዋናው ኃላፊነት ዩኒቨርሲቲዎች ላይ ነው። ፈረንጅ የሰጠንን ዝም ብሎ ማስተማር ሳይሆን ወደኛ መመለስ አለብን። የራሳችን የሆኑ ጥናትና ምርምሮች ያስፈልጉናል። በቲያትር የትምህርት ሥርዓት ውስጥ ሀገር በቀል የነበረው ነገር ጠፍቶ በባዶ መሬት ላይ ነው የበቀልነው። የብሔር ብሐረሰቦችን ባህል መሠረት አድርገን እዚያ ላይ ነው ዘመናዊነት መብቀል ያለበት። አሁን እኮ እኛ የፈረንጅ ተቀጢላዎች ነን። አያልነህ ሙላት ምናምን የምትለው.. ደራሲ ምናምን የምትለው ስለፑሽኪን ያወራሃል። ስለ ሼክስፒር ያወራሃል። ስለ ዶስኮቭስኪ ያወራሃል። …ስለማንኛውም ቢሆን ያወራሃል። ነገር ግን ስለ እማሆይ ገላነሽ፣ ስለ አይናማው ጎሹ፣ ስለ ሼክ ጅብሪል ለሦስት ደቂቃ ብቻ ንገረኝ ብትለኝ አላውቅም። ከፈረንጅ ሊቅ የተማርነውና የምንማረው ምን ያህል ደንቆሮ እንዳደረገን ተመልከት እንግዲህ…” አለኝ አያልነህ ልቡ ተነክቶ አንድ ትልቅ ቁጭት ውስጥ እንዳደረ ያሳብቃል።

በስተመጨረሻ ሁሉን ጨርሰን ልሰናበተው ስል ቢሮውን ካካለለው መደርደሪያ ላይና ታች በረድፍ ተጠግጥገው ከሚገኙት መጽሓፍት መካከል የታጨቁትን ጥራዞች ተመልክቼ ቀልቤን ስለሳቡት እኚህ ምንድናቸው ስል ጠየቅኩት። ገና ያልታተሙ መጽሓፍትና መድረክ ያላዩ ቲያትሮች እንደሆኑ ከነገረኝ በኋላ አንድ በአንድ እያነሳ አስመለከተኝ። የሚገርም ብቻ ሳይሆን የሚያሳዝንም ጭምር ነበር። “ገና መድረክ ያላዩ…” በእርጅና ተረቶ ሊሞት ጥቂት ቀርቶት እርሱ ግን ገና ከ30 ዓመታት በኋላ የሚያፈራ ዛፍ ሲተክልና፣ ሰዎች ሲሳለቁበት የነበረው የአንድ ሰው ታሪክ ትዝ አለኝ። አያልነህም ስለቲያትርና ቲያትር ጽፎ ዛሬም በቃኝ ብሎ አልተቀመጠም። በግርምቴ መሀልም ቆይ ለምንድነው እየጻፍክ የምታከማቸው…ለምንስ ነው ቲያትሮቹ ያልተሠሩትና አሁን የማይሠሩት? ስል ነበር የጠየቅኩት ቀና ብሎ ከተመለከተኝ በኋላ ቅሬታ ባዘለ ድምጸት እንዲህ ነበር ያለኝ “እኔ እንደሆን ዕድሜዬ ገፍቷል። ምናልባት አንድ ቀን የገባው ትውልድ ሲመጣ ለእነርሱ ይሆናል” አለኝ። ከታላቁ ሰው ጋር የነበረኝ ትልቁ ንግግር ነበር።

ሙሉጌታ ብርሃኑ

አዲስ ዘመን ነሐሴ 23 /2016 ዓ.ም

 

Recommended For You