‹‹አዲስ ቱሞሮ›› – የነገዋ አዲስ አበባ አዲስ የገፅታና የኢኮኖሚ አቅም

ሀገራት የኢንቨስትመንት ዘርፋቸውን በማሳደግ ጥቅል አገራዊ እድገታቸውን ዘላቂ ለማድረግ ከሚተገብሯቸው አሰራሮች መካከል አንዱ ልዩ የኢኮኖሚ ቀጣናዎችን (Special Economic Zones) ማቋቋም ነው። ልዩ የኢኮኖሚ ቀጣናዎች የሚፈጥሩትን የስራ እድል፤ ለአገር በቀል የሎጂስቲክስ ኢንዱስትሪው መስፋፋት የሚያደርጉትን አስተዋጽኦ፤ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ፍሰትን፣ የቴክኖሎጂ ሽግግርን፣ የባለሙያዎችንና የሠራተኞችን ክህሎት ለማሳደግ እንዲሁም የዋጋ ግሽበትን ለመቀነስ የሚኖራቸውን ወሳኝ ሚና እንዲሁም የወጪና ገቢ ንግድን ለማቀላጠፍ ያላቸውን አበርክቶ በአጠቃላይ ለሀገራዊ የምጣኔ ሀብት እድገት መሻሻል የሚኖራቸውን ጉልህ ፋይዳ ከግምት ውስጥ በማስገባት አገራት ልዩ የኢኮኖሚ ቀጣናዎችን ያቋቁማሉ፣ ያስፋፋሉ።

የምጣኔ ሃብት ሳይንስ ጥናቶች እንደሚያስረዱት፤ ልዩ የኢኮኖሚ ቀጣናዎች ኢንቨስትመንትን በማሳደግ ለስራ እድል ፈጠራ፣ ለምርት አቅርቦት እና ለውጭ ምንዛሬ ግኝት ከፍተኛ አዎንታዊ አስተዋፅዖ ያበረክታሉ። የእነዚህ ቀጣናዎች ዋና ዋና ዓላማዎች የስራ እድል ፈጠራን እና ምርትንና ምርታማነትን መጨመር፣ የወጪ ንግድን ማስፋትና የውጭ ምንዛሬ ግኝትን ማሳደግ እንዲሁም ካፒታልና ቴክኖሎጂን መሳብ ናቸው። ልዩ የኢኮኖሚ ቀጣናዎች የራሳቸው የምርት ስፍራ/ወሰን፣ የአስተዳደር ስርዓት፣ የታክስ ሕግጋት እና የጉምሩክ ስርዓት አላቸው። ቀጣናዎቹ በትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ፣ በጥሬ እቃ አቅርቦት እንዲሁም በምርት አቅርቦትና ግብይት ተግባራት ላይ የሚሰማሩ አካላትን ቁጥር ይጨምራሉ። ይህም የልዩ የኢኮኖሚ ቀጣናዎች ልማት ከኢንቨስትመንት እድገት ጋር ቀጥተኛ ትስስር እንዳለው ማሳያ ነው።

ኢኮኖሚያዊ ትስስር ስር እንዲሰድ ለማድረግ እንዲሁም የግብርና ልማትን፣ የምግብ ዋስትናን፣ የኢንዱስትሪ ልማትንና የኢኮኖሚ መዋቅራዊ ለውጥ ለማምጣት ወሳኝ የሆነውንና የሰዎች፣ የካፒታል፣ የእቃዎችና አገልግሎቶች ነፃ እንቅስቃሴ የሰፈነበት አህጉራዊ ገበያ ለማምጣት ያለመው ‹‹አጀንዳ 2063›› ስኬታማ እንዲሆን ነፃ የኢኮኖሚ ቀጠናዎች ልማት አስፈላጊ እንደሆነ በአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጣና ስምምነት መመስረቻ ሰነድ ላይ ተጠቅሷል። ከዚህ በተጨማሪም ለንግድና ኢንቨስትመንት በቂ መሰረተ ልማት ለመዘርጋት እንዲሁም ቀረጥን በመቀነስ ወይም ደረጃ በደረጃ በማስወገድ እና ለንግድና ኢንቨስትመንት ማነቆ የሆኑትን ቀረጥ ያልሆኑ መሰናክሎችን ለማስወገድ በስምምነቱ አባል ሀገራት ዋስትና ያለው የእቃዎችና አገልግሎቶች ገበያ ለመፍጠርና ለማስፋፋትም ነፃ የኢኮኖሚ ቀጠናዎች ወሳኝ ሚና እንዳላቸው በሰነዱ ላይ ተመላክቷል።

ልዩ የኢኮኖሚ ቀጣናዎች የግል (Private) እና የመንግሥት (Public) ኢንቨስትመንቶችን በማበረታታት የኢንቨስትመንት ዘርፉ እንዲያድግ ያስችላሉ። ቀጣናዎቹ የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንትን (Foreign Direct Investment – FDI) በመሳብ የግል ባለሃብቶች በስፋት በኢንቨስትመንት እንዲሰማሩ ያደርጋሉ። በሌላ በኩል ልዩ የኢኮኖሚ ቀጣናዎች ሰፊ የመሰረተ ልማት ዝርጋታዎችን የሚፈልጉ በመሆናቸው መንግሥት በመሰረተ ልማት ኢንቨስትመንት (Infra­structural Investment) ላይ እንዲሰማራ በማድረግ የመንግሥት ኢንቨስትመንት እንዲነቃቃ እድል ይፈጥራሉ። በአጠቃላይ ልዩ የኢኮኖሚ ቀጣናዎች ለባለሃብቶች ምቹ እድሎችን የሚፈጥሩ በመሆናቸው ባለሃብቶች በኢንቨስትመንት ዘርፎች ለመሰማራት ተነሳሽነት ይኖራቸዋል።

በልዩ የኢኮኖሚ ቀጣናዎች ውስጥ የሚተገበሩ ሕጋዊ አሰራሮች ቀለል ያሉና ቢሮክራሲያዊ ውጣ ውረዶችን የሚቀንሱ በመሆናቸው ባለሀብቶች በኢንቨስትመንት ተግባራት ላይ ለመሰማራት የሚያደርጉትን ጥረት በአንፃራዊነት ቀላል ያደርጉላቸዋል። በነፃ የንግድ ቀጣናው ውስጥ ገብተው የሚሠሩ ባለሀብቶች፣ አስመጪና ላኪዎችም ሆኑ ድርጅቶች የልዩ ልዩ ማበረታቻዎች ተጠቃሚ ይሆናሉ። ይህ ደግሞ የሀገር ውስጥ እና የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን ለማሳደግ ጉልህ ሚና ይኖረዋል።

ከፍተኛ የሕዝብ ቁጥር እንዲሁም መሬትን ጨምሮ ሌሎች እምቅ ሀብቶች ያላት ኢትዮጵያ ልዩ የኢኮኖሚ ቀጣናዎችን በማቋቋም ረገድ በመዘግየቷ ከእነዚህ ቀጣናዎች ልማት ማግኘት የሚገባትን ምጣኔ ሀብታዊ ጥቅም ማጣቷ ተደጋግሞ ሲገለፅ ቆይቷል። የሀገሪቱን የምጣኔ ሀብት እንቅስቃሴ እግር ከወርች አስረው የያዙት አንዳንዶቹ መሰናክሎች ልዩ የኢኮኖሚ ቀጣናዎች በሚያስገኟቸው ጥቅሞች የሚፈቱ ናቸው። ስለሆነም ልዩ የኢኮኖሚ ቀጣናዎችን በማቋቋም የሀገሪቱን ተጠቃሚነት ማሳደግ አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ የልዩ የኢኮኖሚ ቀጣናዎች ለማልማት የሚያስችሉ ስራዎች ሲከናወኑ ቆይተዋል።

የልዩ ኢኮኖሚ ቀጣናዎች ልማት በሕጋዊ ማዕቀፍ የተደገፈ እንዲሆን የሚያስችሉ ብሔራዊ የልዩ ኢኮኖሚ ዞን ፖሊሲ እና የልዩ ኢኮኖሚ ዞን አዋጅ (1322/2016) ተዘጋጅተው ወደ ስራ ተገብቷል። የኢ.ፌ.ዴ.ሪ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ነሐሴ 27 ቀን 2014 ዓ.ም ባካሄደው 11ኛ መደበኛ ስብሰባው፣ በብሄራዊ የልዩ ኢኮኖሚ ዞን ረቀቂ ፖሊሲ ሰነድ ላይ ውይይት በማድረግ፣ ፖሊሲው በሥራ ላይ እንዲውል በሙሉ ድምጽ ወስኗል። ምክር ቤቱ ፖሊሲው በስራ ላይ እንዲውል ውሳኔ ያሳለፈው ኢትዮጵያ ለአገራዊ የኢኮኖሚ እድገት የጎላ አስተዋፅዖ ባለውና ከጊዜ ወደ ጊዜ በፍጥነት እየተስፋፋና እየጎለበተ በመጣው ዓለም አቀፍ እና ቀጣናዊ የንግድ ትስስር ንቁ ተሳታፊና ተጠቃሚ እንድትሆን አስቻይ ሁኔታዎችን መፍጠር አስፈላጊ በመሆኑ ነው። ፖሊሲው የአገሪቱን የወጪ ንግድ ስርዓት ለማሻሻል፣ የውጪ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ስበትን ለማሳደግ፣ የወጪ ንግድ አቅምን ለማጎልበት፣ ሰፊ የስራ እድሎችን ለመፍጠር እንዲሁም በአገሪቱ ዋና ዋና የንግድ ኮሪደሮች የደረቅ ወደቦችን ለማስፋፋትና የሎጂስቲክ አገልግሎትን ለማቀላጠፍ የሚያግዙ ስርዓቶችን እውን ለማድረግ የሚያስችል እንደሆነም ተገልጿል።

ከዚህ በተጨማሪም የኢ.ፌ.ዴ.ሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሚያዝያ 10 ቀን 2016 ዓ.ም ባካሄደው ሦስተኛ ዓመት የሥራ ዘመን 21ኛ መደበኛ ስብሰባው የልዩ ኢኮኖሚ ዞን አዋጅን አፅድቋል። የውጭ ኢንቨስትመንትን በቀላሉ ለመሳብ፣ ሰፊ የስራ ዕድል ለመፍጠር፣ የአምራች ዘርፉን ለማበረታታት፣ የምጣኔ ሀብት ትስስርን ለማጠናከር፣ የውጭ ምንዛሪ ገቢን ለማሳደግ፣ የቴክኖሎጂ ሽግግር ለማሳለጥ እንዲሁም ተግባራዊ የተደረገውን የኢንዱስትሪ ፓርኮች ስርዓት ዲዛይንና ትግበራ ወደ ልዩ ኢኮኖሚ ዞን ስርዓት በማሳደግ ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነት ከፍ ለማድረግ ከፍተኛ ፋይዳ እንዳለው ተገልጿል።

እነዚህን የልዩ ኢኮኖሚ ዞን ፋይዳዎችን እንዲሁም የፖሊሲና አዋጅ ዝግጅቶችን መሰረት በማድረግ በሀገሪቱ በተለያዩ አካባቢዎች ግዙፍ የሆኑ የልዩ የኢኮኖሚ ዞኖች ግንባታዎች እየተከናወኑ ይገኛሉ። በአዲስ አበባ ከተማ የሚገነባው ‹‹አዲስ ቱሞሮ›› ልዩ የኢኮኖሚ ዞን እና ግንባታው በኦሮሚያ ክልል የሚከናወነው ‹‹ገዳ›› ልዩ የኢኮኖሚ ዞን የዚህ እንቅስቃሴ ማሳያዎች ናቸው።

ግንባታው በአዲስ አበባ፣ ጎተራ አካባቢ፣ በ35 ሄክታር መሬት ላይ የሚያርፈው ‹‹አዲስ ቱሞሮ›› ልዩ የኢኮኖሚ ቀጣና (Addis Tomorrow Special Eco­nomic Zone)፣ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እና በቻይናው ‹‹ቻይና ኮሚዩኒኬሽንስ ኮንስትራክሽን›› ኩባንያ (China Communications Construction Company – CCCC) ሽርክና የሚገነባ ግዙፍ ፕሮጀክት ሲሆን፣ የባህል፣ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ፓርክ እንዲሁም የቢዝነስና የንግድ፣ የመኖሪያና የመዝናኛ ማዕከላትን ያካትታል። ልዩ የኢኮኖሚ ዞኑ በግሉ ዘርፍና በመንግሥት ሽርክና ከሚገነቡ ግዙፍ የልማት ፕሮጀክቶች መካከል አንዱ ሲሆን፣ በአዲስ አበባ በተለያዩ አካባቢዎች ከሚከናወኑ የልማት ስራዎች ጋር ተቀናጅቶ የሚተገበር ነው።

የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ የልዩ ኢኮኖሚ ዞን ግንባታውን ባስጀመሩበት ወቅት፣ ልዩ የኢኮኖሚ ዞኑ አዲስ አበባን እንደስሟ ውብና አዲስ ለማድረግ የሚከናወኑ ተግባራት አካል እንደሆነ ተናግረዋል። አዲስ አበባን ውብና አዲስ ለማድረግ ከሚከናወኑ ተግባራት መካከል አንዱ በግልና በመንግሥት አጋርነት የሚሰሩ በከተማ ውስጥ ያሉ ከተሞችን መገንባት እንደሆነ የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ፣ እነዚህ ፕሮጀክቶች የነገዋን አዲስ አበባን መልክ የሚያሳዩ በመሆናቸው ከፍተኛ ሀብት የሚጠይቁ፣ የተለየ ዲዛይን ያላቸው፣ በሰፋፊ ቦታዎች ላይ የሚገነቡ፣ እጅግ ማራኪ የሆኑ እንዲሁም አስፈላጊ መሰረተ ልማቶችን የያዙ እንደሆኑ አስረድተዋል።

‹‹አዲስ ቱሞሮ›› ልዩ የኢኮኖሚ ዞን ረዘም ያለ ጊዜ የወሰዱ ንግግሮች የተደረጉበት መሆኑን አስታውሰው፣ ግንባታው መጀመሩ አዲስ አበባን ውብና ተመራጭ የማድረግን ዓላማ ለማሳካት አጋዥ እንደሚሆን ገልፀዋል። ‹‹በግሉ ዘርፍ ከፍተኛ መነቃቃት እየታየ ነው። በቅርቡ የተደረገው የማክሮ ኢኮኖሚ ሪፎርም የግሉ ዘርፍ በብዛት ኢትዮጵያ ውስጥ በኢንቨስትመንት ላይ እንዲሰማራ በር የሚከፍት ነው። የምንዛሬ ገበያው እንዲስተካከል እያደረገ እንዲሁም ብዙ ሕገ ወጥ ስራዎችን ወደ ሕጋዊነት እያመጣ ነው። በዶላርና በብር መካከል ያለውን ያልተገባ ዝምድና ለማረቅ የሚያግዝ ነው። ኤክስፖርት በማድረግ፣ ገቢን በማስገባትና በማስፋት፣ አዳዲስ ኢንቨስትመንት በመሳብ፣ ከውጭ የሚላክ ገንዘብ (ሬሚታንስ) በሕጋዊ መንገድ እንዲመጣ በማድረግ ኢኮኖሚያችንን በከፍተኛ ደረጃ እንደሚያነቃቃ ይጠበቃል። ‹አዲስ ቱሞሮ› ልዩ የኢኮኖሚ ዞንም የዚሁ አካል ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል›› ብለዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ በበኩላቸው፣ ፕሮጀክቱ የአዲስ አበባን ገፅታ የመቀየርና የሕዝቡን ሁለገብ ተጠቃሚነት የማሳደግ ጥረት አካል እንደሆነ ተናግረዋል። ‹‹ግንባታው የተጀመረው ‹አዲስ ቱሞሮ› ልዩ የኢኮኖሚ ዞን በከተማችን ውስጥ አዲስ ከተማን የመገንባት ያህል ግዙፍ ፕሮጀክት ሲሆን እንደቀደሙት ፕሮጀክቶች ሁሉ ለከተማችን አዲስ ገፅታን የሚያላብስ፣ ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነቷን የሚያጎላ፣ ተጨማሪ የውበት ምንጭ የሚሆን፣ በርካታ የስራ እድሎችን የሚፈጥር፣ ንግድን የሚያሳልጥ፣ ትልቅ ዓለም አቀፍ የግብይት ማዕከልን ለከተማችን የሚጨምር እንዲሁም መኖሪያ ቤቶችንና ማኅበራዊ አገልግሎቶችን ጨምሮ በርካታ መሰረተ ልማቶችን የያዘ ነው›› ብለዋል።

ከለውጡ ማግሥት ጀምሮ አዲስ አበባን እንደስሟ ውብ፣ አበባ ለማድረግ በማለም በርካታ ስራዎች መሰራታቸውን የጠቆሙት ወይዘሮ አዳነች፣ በየዓመቱ እየተጠናቀቁ ለአገልግሎት የበቁ የሕዝቡን የኑሮ ጫና ያቃለሉ ፕሮጀክቶችን ጨምሮ የከተማዋን ጎስቋላ ገፅታ የቀየሩ፣ ሰፋፊ የስራ እድሎችን የፈጠሩ፣ አገልግሎቶችን ያሳለጡና ገቢን ያሳደጉ ሜጋ ፕሮጀክቶች የስኬቶች ማሳያዎች እንደሆኑ አስረድተዋል። ይህ ጉልህ ስኬት ሊመዘገብ የቻለው መንግሥት የመፈፀም አቅሙን በማሳደግ፣ ብክነትን በመቀነስ፣ የልማት አጋሮችንና የሕዝባችንን ሁለንተናዊ አቅም በማስተባበር እንደሆነም ገልፀዋል።

የ‹‹አዲስ ቱሞሮ›› ልዩ የኢኮኖሚ ዞን ግንባታን የሚያከናውነው የ‹‹ቻይና ኮሚዩኒኬሽንስ ኮንስትራክሽን›› ኩባንያ ምክትል ስራ አስኪያጅ ቼን ዦንግ፣ የፕሮጀክቱ ግንባታ ትብብርን በሚያጠናክር እንዲሁም የእውቀትና የቴክኖሎጂ ሽግግርን በሚያሳልጥ መልኩ እንደሚከናወን ገልፀዋል። ‹‹የኩባንያችንን እውቀትና ሃብት የኢትዮጵያን ሕዝብና መንግሥት ተጠቃሚ ለማድረግ እናውለዋለን›› በማለት ተናግረዋል። የኢኮኖሚ ዞኑ ሕዝብ ተኮር፣ ዘመናዊና ጤናማ ከተማን ለመፍጠር እንደሚያስችልም ገልፀዋል።

ኢትዮጵያ ዘርፈ ብዙ ጥቅም ከሚሰጠው ከልዩ የኢኮኖሚ ቀጣና ስርዓት ርቃ መቆየቷ ብዙ ጥቅሞችን አሳጥቷታል። የእነዚህ ጥቅሞችና እድሎች መታጣት ደግሞ በአጠቃላይ እድገቷ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እንዳሳደረባት አይካድም። በሀገሪቱ የምጣኔ ሀብት እንቅስቃሴ ላይ ከፍተኛ አሉታዊ ተፅዕኖ እያሳደሩ ያሉት አንዳንዶቹ መሰናክሎች ልዩ የኢኮኖሚ ቀጣናዎችን በማቋቋም ቀጣናዎቹ በሚያስገኟቸው ጥቅሞች የሚፈቱ ናቸው። ስለሆነም ልዩ የኢኮኖሚ ቀጣናዎችን ለማቋቋም የተጀመሩትን ጥረቶች በማጠናከር ሀገራዊ የምጣኔ ሀብት እድገቱ ትርጉም ያለው ለውጥ እንዲያስመዘግብ ማድረግ ይገባል።

አንተነህ ቸሬ

አዲስ ዘመን ነሐሴ 23 /2016 ዓ.ም

 

Recommended For You