ወንድምዓለም – በክፉ ቀን…

የአባ ጎራው ልጅ…

ትንሹ ልጅ ደስተኛ ነው፡፡ ዛሬም እንደፊቱ እየሳቀ ይጫወታል፣ እየዘለለ ይቦርቃል፡፡ ከትምህርትቤት ባልንጀሮቹ ፣ ከመንደር እኩዮቹ ጋር ሳቅ ጨዋታው ልዩ ነው። የፊቱ ፈገግታ የአንደበቱ ለዛ ያሳሳል፡፡

ውዱ ጎራው ለቤቱ የመጨረሻ ልጅ ነው። መላው ቤተሰብ ይወደዋል፡፡ ሁሉም እሱ እንዲማር ፣ ራሱን እንዲችል፣ ይመኙለታል፡፡ ውዱ ልጅ ቢሆንም ከሁሉ ይግባባል፣ በቀልድ ጨዋታው አይጠገብም፡፡ ለቤተሰቡ ተገዢ፣ ለትንሽ ትልቁ ታዛዥ ነው፡፡ ንግግሩ ይማርካል፣ ጨዋታው ልብ ያሞቃል፡፡

ውዱ ከትምህርት ውሎ ዕውቀት ቀስሞ ሲመለስ እናት አባቱ አቅፈው፣ ስመው ይቀበሉታል፡፡ መነኩሴው አባቱ የማምሻ ፍሬያቸው ነው፡፡ ሲያዩት ይሳሳሉ፡፡ እናቱ ውሎ እስኪገባ ሲናፍቁት ይውላሉ፡፡ ቤተሰቦቹ የገጠር ነዋሪ ገበሬዎች ናቸው፡፡ የመሬት ጸጋ ከሚሰጣቸው በረከት የዘለለ ትርፍ ይሉት ሀብት የላቸውም፡፡ ኑሯቸው ዓመቱን ሙሉ በሚያዘምሩት እርሻ ላይ ተመሠርቷል፡፡ የዕለት ጉርስን አሸንፎ ነገን የሚያሳልፍ፣ ከርሞን የሚያሻግር ጥሪት ከእጃቸው የለም፡፡ ሁሌም ዛሬን አመስግነው፤ ነገን ተስፋ አድርገው ያድራሉ፡፡

የደበዘዘው ሳቅ …

ሳቂታው፣ ተጫዋቹ ህጻን ውዱ እንደቀድሞው መሆን ትቷል፡፡ የትናንት ደማቅ ጨዋታው ዛሬ ከእሱ አይደለም፡፡ ሲያናግሩት መልሱ አጭር አልያም ዝምታ ነው፡፡ ሁኔታውን ያሚያዩ ጨንቋቸዋል፡፡ ሁሉም ትንሹ ልጅ ደርሶ ዝምተኛ የሆነበት ምክንያት አልገባቸውም፡፡ ከጓደኞቹ ተነጥሎ በቁዘማ አንገቱን የሚደፋበት ጉዳይ አልታወቀም፡፡ ቀናት ተቆጠሩ ፡፡

ውዱ አንገቱ ላይ ዕባጭ ወጥቶ ከቤት አውሎታል። አሁን ጓደኞቹን ማግኘት፣ ትምህርት ቤት መሄድ አይፈልግም። የትናንቱ ቀልጣፋ ልጅ በዝምታ ተውጦ በብቸኝነት ይውላል፡፡ ፈገግታው ደብዝዟል፡፡ ደማቁ ገጽታ በኩርፊያ ተውጧል፡፡

አሁን ስለእሱ የጨነቃቸው ቤተሰቦች ምክንያቱን ደረሱበት ፡፡ ሳቂታው ታዳጊ ከአንገቱ ጥግ የወጣበት ዕባጭ እያስጨነቀው ኖሯል። እናት እጃቸውን ከልጃቸው አንገት አሳርፈው በስሱ ዳሰሱት፡፡ ዕባጩ ጠንክሯል፡፡ መላ አካሉ በትኩሳት ግሏል፡፡ ደነገጡ፡፡

ህመሙ የተሰማቸው እናት ጠዋት ማታ ፈጣሪያቸውን እያማረሩ ነው፡፡ ከዚህ ቀድሞ ሁለት ልጆቻቸውን በሞት ተነጥቀዋል፡፡ አሁን ደግሞ የዓይናቸው ማረፊያ የሆነው ትንሹ ልጅ በህመም እየተፈተነ ነው፡፡ ‹‹እንዴት ለምን›› ሲሉ ማዘን ፣ ማልቀሳቸውን ቀጠሉ፡፡

አሁን ቤተዘመድ ስለትንሹ ልጅ እየመከረ ነው፡፡ ሁሉም በአንገቱ ላይ የታየው ዕባጭ ዕጢ መሆኑን ገምቷል። እንዲህ ሲያጋጥም መፍትሄ አይጠፋም፡፡ በዕውቅ ባለሙያ ፣ በሀገር ባህል መድሃኒት ታክሞ ይድናል፡፡ በወቅቱ ግን ይህን ሊያስቀድም የደፈረ የለም፡፡ የቤተሰቡ ምክር ልጁን ወደ ህክምና መውሰዱ ላይ አጋደለ፡፡

ውዱ ከአማራ ሳይንት ወረዳ አቀስታ ሆስፒታል በደረሰ ጊዜ ለህክምናው አልዘገየም። ከሀኪሞች እጅ ገብቶ ሙሉ ምርመራ አገኘ። ውሎ አድሮ በውዱ አንገት የታየው ዕባጭ ካንሰር እንደሚያሳይ ተደረሰበት፡፡ ይህ እንደታወቀ በአስቸኳይ ወደ ደሴ ሆስፒታል ተላከ። በየሆስፒታሉ ተጨማሪ የናሙና ምርመራ የተደረገለት ህጻን ውጤቱ ተመሳሳይ ነበር፡፡ በትክክልም የአንገቱ ላይ ዕባጭ ካንሰር እንደሆነ ያመለክታል፡፡

ይህ እውነት በነውዱ መንደር ሲሰማ አብዛኛው ቤተሰብ በተስፋ መቁረጥ ተመላለሰ። በአካባቢው ካንሰር ገዳይ በሽታ መሆኑ ይታወቃል፡፡ በእነሱ ግንዛቤ ማንም ይህ ህመም ቢታይበት መጨረሻው ሞት ነው፡፡ አስደንጋጩ ዜና ለሚሰሙት ሁሉ ከባድ ሆኖ ሰነበተ፡፡ ስለውዱ ከንፈራቸውን የሚመጡ በረከቱ፡፡

ከጥቂት ቀናት በኋላ የውዱ ታላቅ ወንድም ለጥቁር አንበሳ የተፃፈውን የህክምና ማስረጃ ይዞ ወደ አዲስአበባ አቀና፡፡ የአስራ አንድ ዓመቱ ውዱ ሊታከም መሆኑን እውቋል፡፡ ሁለቱም ‹‹ለሰዉ እንግዳ ፤ ለአገሩ ባዳ›› ናቸው። እከሌ የሚባል ዘመድ የለምና አዲስ አበባ እንደደረሱ እግራቸው የረገጠው የጥቁር አንበሳን ጊቢ ሆነ፡፡

የውዱ ወንድም ማስረጃውን ይዞ ሀኪሞች ዘንድ ቀረበ፡፡ ህክምናው የሚጠይቀውን ምርመራ ፈጥኖ እንዲያስፈጽም ታዘዘ፡፡ በወቅቱ የተጠየቀው ገንዘብና በኪሱ ያለው ብር የሚደራረስ አልሆነም፡፡ የአቅሙን ያህል ጥቂት ሞካክሮ ወደቤተሰቦቹ ደወለ፡፡

ላይድን ህመም…

የእነ ውዱ ቤተሰቦች የተጠየቀውን ገንዘብ በሰሙ ጊዜ ሁሉን ትቶ እንዲመለስ ነገሩት፡፡ አብዛኞቹ ታክሞ ለማይድን በሽታ መድከም፣ መልፋት እንደማይገባ አምነዋል። መድሃኒት ለሌለው ህመም እሱም ህፃኑም መንገላታት እንደሌለባቸው ነግረውታል፡፡ ታላቅ ወንድም የተባለውን ሰምቶ ወደ ሀገርቤት ተመለሰ፡፡

ሥፍራው ሲደርስ ሌላ ሃሳብ ተነደፈ። ልጁ ከህክምናው ይልቅ ጸበል እንደሚሻለው ተወሰነለት፡፡ ለአጭር ጊዜ ትንሹ ልጅ ከጸበል ከረመ፡፡ ከጥቂት ጊዜያት በኋላ የትናንቱ ሕይወት ሊቀጥል ግድ ነበር፡፡ በራሱ ዓለም የሚባትለው ወንድም ወደሥራው ተመለሰ፡፡ ሌሎችም ወደግብርናው ፊታቸውን መለሱ፡፡

አሁን ውዱ ከቤት መዋል ጀምሯል፡፡ ዛሬም ታክሞ አይድንም ከተባለለት ህመም ጋር እየታገለ ነው፡፡ አንገቱ ላይ የታየው እባጭ ያለአንዳች መፍትሄ ቀናት መቁጠር ይዟል፡፡ አሁንም እያዘነ፣ ይቆዝማል፡፡

ውሎ አድሮ የአንገቱ ላይ እባጭ እየባሰበት ሄደ፡፡ እብጠቱ፣ መጨመሩን ያስተዋሉ ቤተሰቦች ለሌላ እርምጃ ፈጠኑ፡፡ በአካባቢው እንዲህ አይነት ችግር ሲገጥም በሀገር ባህል መድሃኒት ይፈተሻል፡፡ የውዱ ዕጣ ፋንታም ከዚህ አላለፈም፡፡ ከታየበት እባጭ ድኖ ፈውስ እንዲያገኝ ወደሀገር ባህል መድሃኒት አዋቂ ዘንድ ተወሰደ፡፡

መድሃኒት አዋቂው የልጁን አንገት በእጁ ነካክቶ ጥቂት እንዳፈረጠ ለመፍትሄው እንደማይቸገር ለቤተሰቡ አሳወቀ። በአጭር ጊዜ የትንሹ ልጅ ህክምና ተጀመረ፡፡ በቁስሉ ላይ የሚቀባው፣ የሚታሰረው ሁሉ ሆነ፡፡ ቆይታው ከስቃይ አላዳነውም፡፡ እያደር ቁስሉ እያመረቀዘ፣ እየሰፋ ታየ፡፡

በረከት እንግዳው ወንድም

ከቀናት በአንዱ ወደነውዱ መንደር አንድ ወጣት በድንገት ደረሰ፡፡ የትንሹ ልጅ ታላቅ ወንድም በረከት ጎራው፡፡ በረከት ከአካባቢው ከራቀ ሰንበት ብሏል፡፡ ራሱን ለመርዳትና ቤተሰቦቹን ለማገዝ ወጣ ብሎ ያገኘውን ሲሠራ ነበር፡፡ የዛን ዕለት ገና እግሩ እንደረገጠ ዓይኖቹ ከትንሹ ልጅ አንገት ላይ አረፈ፡፡ ጠጋ ብሎ የሚያውን እውነት ሊያረጋግጥ ሞከረ፡፡

ውዱ አንገት ላይ ያለው እባጭ ክፉኛ ቆስሏል፡፡ መድሃኒት ተብሎ የተቀባው ነገር ከማቁሰል ያለፈ የፈየደለት የለም፡፡ በረከት ለዓይን የሚከብደውን ቁስል እያየ ከልቡ አዘነ። ሁኔታውን ለመጠየቅ ያደረገው ጥረት ደግሞ አስደንጋጭ ነበር፡፡ ሁሉም ህመሙ ፣ ታክመው የማይድኑት ካንሰር መሆኑን አስረዱት፡፡

በረከት ተስፋ አልቆረጠም፡፡ ስለወንድሙ ማድረግ የሚገባውን ማሰላሰል ያዘ፡፡ ያማከራቸው አንዳንዶች ግን ቁስሉ ሳይደርቅ ሀኪም ዘንድ መውሰዱ እንደማይበጅ ደጋግመው ነገሩት፡፡ እሱ ምክራቸውን በሙሉ ልብ መስማት አልፈቀደም። ከራሱ መክሮ፣ ተማክሮ ከውሳኔ ደረሰ፡፡

በረከት ገጠር ተወልዶ ቢያድግም ከሌሎች የተሻለ ግንዛቤ አለው፡፡ ለትንሽ ግዜም ቢሆን የዩንቨርስቲን ግቢ ያውቀዋል፡፡ ብዙዎች የሚሉትን ‹‹ታሞ ፣ታክሞ ፣አይድንም›› አባባልን አምኖ መቀበል አይፈልግም፡፡ እሱ የቻለውን ሁሉ ሞክሮ ትንሽ ወንድሙን ማሳከም፣ማዳን ይፈልጋል፡፡

በረከት ስለውዱ ህመም ዕንቅልፍ አጥቷል፡፡ እሱን ህክምና አድርሶ መፍትሄ ካላገኘ ሰላም ደስታ አይኖረውም። የሚያግዝ አይዞህ የሚለው ባያገኝም ርምጃውን እያፈጠነ ነው ፡፡ ለሥራ ወጣ ብሎ በቆየባቸው ጊዜያት አጠረቃቅሞ ያስቀመጠውን ሰማንያ ሺህ ብር አሰበው፡፡ ለእሱ ይህ ገንዘብ ጥቂት የሚባል አይደለም፡፡ ከወንድሙ ሕይወት እንደማይበልጥ ካመነ ግን ቆይቷል፡፡

አዲስ አበባ…

ታማሚውን ህጻን ይዞ የጀመረው የጤና መድህን ህክምና ተሳክቶለታል፡፡ ከዚህ በኋላ ያለው ውሳኔ ሙሉ መረጃውን አጠናቆ ወደ ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል መሄድ ብቻ ነው፡፡ በረከትና ውዱ አዲስ አበባ ሲደርሱ የተቀበላቸው ዘመድ የለም፡፡ ከተባሉበት ስፍራ ገብተው ህክምናውን መጀመር ቀላል አይደለም፡፡ ማደሪያ ቤት ፣ የዕለት ወጪ፣ በቂ ምግብና ሌሎች ሁሉ በነጻ አይገኙም፡፡

በመጀመሪያዎቹ ጥቂት ቀናት በድንገተኛ ክፍል አልጋ ይዘው እንዲቆዩ ሆነ፡፡ በረከት የወንድሙን ህክምና እንደ አዲስ አስጀምሮ ህክምናውን ቀጠለ፡፡ ከጊቢው ወጥተው አልጋ እንደያዙ ትንሹ ልጅ የመቅኔ ምርመራ እንዲያደርግ ታዘዘ፡፡

በየቀኑ የሚካሄደው የላብራቶሪ ፣ የናሙናና መሰል ምርመራዎች የበረከትን ኪስ ማሳሳት ይዘዋል፡፡ የመድሃኒቱ ዋጋ የሚቀመስ አይደለም፡፡ እሱ ለሁሉም ጉዳይ ገንዘብ እንደሚያስፈልግ ያውቃል፡፡ ህክምናው ይህን ያህል ጊዜ እንደሚፈጅ ግን መረጃ የለውም። በጊዜው ዕጢውን በአንዴ ንቅል አድርገው እንደሚገላግሉት ሲያስብ ነበር፡፡

ሁሉም ጉዳይ ግን እሱ እንዳሰበው ቀላል አልነበረም። አሁንም ተጨማሪ ገንዘብና ፣ በቂ ቆይታ ያስፈልጋል፡፡ በረከት መለስ ብሎ ወደ ኋላ ማሰብ ያዘ፡፡ በእነሱ አካባቢ ህመሙ ገዳይ መሆኑን ሲወራ ሰምቷል፡፡ ማንም ግን በዚህ ችግር ህክምናውን ሲወስድ አጋጥሞት አያውቅም፡፡ አሁንም ለተጨማሪ ምርመራዎች ሌሎች ቀናት ያስፈልጋሉ። በረከት የያዘው ገንዘብ እያለቀ፣ አቅሙ እየተፈተነ ነው፡፡ እሱ ከሁሉም ተሽሎ ያለአንዳች አጋዥ ወንድሙን ለህክምና አብቅቷል፡፡ ብዙ ተጉዞም የአቅሙን አድርጓል፡፡ አሁን ደግሞ ‹‹በቃኝ ‹ደከመኝ›› ሊል አይችልም፡፡ አንዳንዴ ግራ ሲገባው ወደ ሀገሩ አማራ ሳይንት ስልክ ይደውላል፡፡

በረከት የቤተሰቦቹን አቅም አሳምሮ ያውቀዋል፡፡ ከዕለት ጉርስ የዘለለ፤ ለህክምና የሚተርፍ ገንዘብ ከየትም አያመጡም፡፡ እነሱ ዘንድ መደወሉ ብር ለመጠየቅ፣ ‹‹አግዙኝ›› ለማለት አይደለም፡፡ በራሱ ፈቃድ የጀመረውን ጉዞ በጥንካሬ እንደሚወጣው እርግጠኛ ነው፡፡

ሁሌም የበረከት ስልክ ሲነሳ ከቤቶቹ የሚሰማው ድምጽ አስደንጋጭ ነው፡፡ ሁሉም ልጁን ለማይድን ህመም እያንገላታ በርሃብ እንዳይገለው እየተቆጩ ይናገሩታል፡፡ የእሱን ልፋት ያልተረዱም በከንቱ ገንዘቡን እንዳይጨርስ ይመክሩታል፡፡ በአስቸኳይ ልጁን መልሶ ለሀገሩ እንዲያበቃው ሲናገሩትም በቁጣ ነው፡፡

በየቀኑ ስለእናቱ አምርሮ ማዘንና ማልቀስ የሚሰማው ወጣት ውስጡ አብዝቶ ይጨነቃል፡፡ እንዲያም ሆኖ ተስፋ አይቆርጥም፡፡ ነገ ሌላና የተሻለ ቀን ስለመሆኑ ለውስጡ ሲነግረው በታላቅ መተማመንና ቆራጥነት ነው፡፡

አሁን በረከት ትዕግስተኛና ሆደ ሰፊ የሚሆንበት ጊዜ ላይ ነው፡፡ ሁሉንም ፈተና በአሸናፊነት ለማለፍ ቆም ብሎ ማሰብ ግድ ይለዋል ፡፡ ውዱ የሚደረግለት የ‹‹ኬሞ ቴራፒ›› ህክምና ቀላል የሚባል አይደለም፡፡ ብዙዎችን ያስጨንቃል። በእሱ ዕድሜ ያሉ ህጻናት በዚህ መንገድ ያልፋሉ፡፡ አብዛኞቹ ሂደቱን በስቃይ ይወጡታል፡፡ ህክምናው አቅምን ፈትኖ አካላዊ ገጽታን ይቀይራል፡፡

የቅርብ አማካሪ ወዳጅ ዘመድ የሌለው በረከት ሁሉንም ችግር የተወጣው ያለአንዳች አጋዥና ረዳት በብቸኝነት ነው፡፡ ውዱ ከአባቱ የተወለዱ አስራ አንድ እህት ወንድሞች አሉት ፡፡ አንዳቸውም ግን የእሱን ሕይወት ለመታደግ ጎኑ አልቆሙም፡፡ በክፉ ቀን መድህን የሆነው በረከት ደግሞ ዛሬም ድረስ ተስፋ አልቆረጠም፡፡ ‹‹ይሞታል፣ አይድንም›› የተባለ ታናሽ ወንድሙን እንደ እናት አባት ሊሆንለት ‹‹አለሁህ›› እያለው ነው፡፡

ወንድምነት – ልክ እንደእናት

እሱ ለውዱ ታላቅ ወንድሙ ብቻ አይደለም፡፡ ሁሌም እንደ እናት ያስብለታል፡፡ ነገ ከህመሙ ድኖ ለራሱና ለወገኑ የሚበጅ ዜጋ እንደሚሆን ይታየዋል፡፡ ይህን ሲያስብ ስለእሱ የከፈለው ዋጋ ሁሌም ያኮራዋል፡፡ በረከት ለወንድሙ ህክምናውን ሲጀምር ለራሱ ቃል ገብቷል፡፡ ለታቦትም ተስሏል፡፡ የእሱ ቃልና ስለት ውዱ ታክሞ ጤናው ሲመለስ በየገጠር ቤተክርስቲያን አድባራት እየዞረ ስለህክምና ወሳኝነት ለህብረተሰቡ ማስተማር ነው፡፡ ይህ ደግሞ በቅርቡ ዕውን እንደሚሆን አይጠራጠርም፡፡

በረከትና ወንድሙ የመጀመሪያውን ህክምና አጠናቀው ሀገር ቤት ሲመለሱ ዳግም ለህክምና ቀጠሮ አስይዘው ነበር። ታላቅ ወንድም አሁንም ለራሱ የገባውን ቃል አላጠፈም፡፡ ወንድሙን አሳክሞ የማዳን አደራው ዛሬም ከእሱ ጋር ነው፡፡

በሌላ ጊዜ አዲስ አበባ ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ሲመለስ እንደ ትናንቱ በኪሱ በቂ ገንዘብ አልነበረም፡፡ አሁን እሱና ታካሚ ወንድሙ ጎናቸውን አሳርፈው የዕለት ጉርስ የሚቀምሱበት የኪራይ ቤት ብርቃቸው ሆኗል፡፡ በረከት ነገን ተስፋ የሚያደርግበት ጥሪት ባነሰው ጊዜ ፈጣሪውን ይለምን ይማለድ ያዘ፡፡

እፎይታ…

አንድ ቀን ግን ለዚህ ጥያቄው ምላሽ አገኘ፡፡ ቀረብ ብሎ ችግሩን ያዋያቸው ሀኪሞች የጠቆሙት ቦታ ለእሱና ለወንድሙ ዘላቂ መፍትሄ ሊሆን አልዘገየም፡፡ ‹‹ማቲዎስ ወንዱ የኢትዮጵያ ካንሰር ሶሳይቲ›› ቅጥር ጊቢ በደረሱ ጊዜ በመልካም ገጽታ መልካም ሰዎች ተቀበሏቸው፡፡

ሁለቱም ባዕድነት አልያዛቸውም ፡፡ እነሱን ከመሰሉ የሰው ሀገር እንግዶች ጋር ተቀላቅለው ቤተሰብ ሊሆኑ አልዘገዩም፡፡ በዚህ አጸድ ውዱን የመሰሉ ህጻናትና እነሱን ለማሳከም ከሩቅ ቦታ የመጡ ወላጆቻቸው እፎይታን የሚያገኙበት፣ ችግራቸውን የሚቀርፉበት ነው፡፡ ታካሚዎቹ የጎደላቸው ሁሉ እንደነበር ሆኖ አይቀጥልም፡፡ ማረፊያና ምግብን ጨምሮ የመድሃኒት፣ የትራንስፖርት፣ የአምቡላንስና የሌሎችም ወጪዎች በድርጅቱ ይሸፈንላቸዋል፡፡ በረከት ዛሬ ስለሆነለት ሁሉ ፈጣሪውን እያመሰገነ ስለነገ ብሩህ ተስፋ ያልማል፡፡

ትንሹን ውዱንና ታላቅ ወንድሙን በረከትን ያገኘኋቸው በማቲዎስ ወንዱ የቤተሰቦች ማረፊያ ውስጥ ነበር፡፡ ሁለቱም ደስተኞች ናቸው፡፡ የአስራ ሁለት ዓመቱ ውዱ ጎራው ቀረቤታና ሥርዓቱ ደግሞ ይለያል፡፡ ንግግሩ የአዋቂ ይመስላል፡፡ ርጋታ በሞላው አንደበቱ የአሁንና የቀድሞ ሕይወቱን አወጋኝ፡፡

ውዱ ትናንትናን ባልጠነከረ ልጅነቱ ተፈትኖ በድል ተሻግሮታል፡፡ አምና ካቻምና በባህል ህክምና ያለፈበትን የስቃይ መንገድ አይረሳውም፡፡ ዛሬ ደግሞ ዕድሜ ለታላቅ ወንድሙ ነገን በተለየ ብርሃን ለማየት በተሰፋ ማደር ይዟል፡፡ የእሱ ምኞት ይህ ጊዜ አልፎ ወደ ትምህርቱ መመለስ ነው፡፡

ውዱ ከአምስተኛ ክፍል ያቋረጠው ትምህርቱ ፍጻሜ የሚያገኘው በሌላ መንገድ ላይ ሲቆም ነው፡፡ እሱ ተምሮ ሲጨርስ ዶክተር የመሆን ስንቅ ቋጥሯል፡፡ እንዲህ ማሰቡ በምክንያት ነው፡፡ ስለበሽታው ግንዛቤ ያጡ ወገኖቹን በተግባር ያስተምርበታል፡፡ እንደሱ በህመም መንገድ የሚያልፉትን አክሞ ያድንበታል፡፡ የዛሬው ትንሽ ልጅ የነገው ሀኪም ውዱ ጎራው፡፡

መልካምሥራ አፈወርቅ

አዲስ ዘመን ቅዳሜ ነሐሴ 18 ቀን 2016 ዓ.ም

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

Recommended For You