የወጣቱ ተሳትፎ በአንድ ጀንበር የችግኝ ተከላ

በዓለማችን በየጊዜው የሚከሰተው የአየር ንብረት ለውጥ ስጋት መሆን ከጀመረ በርካታ ጊዜያትን አስቆጥሯል። ለውጡ በዓለም ላይ እየደረሱ ላሉ ተግዳሮቶችና ለኦዞን መሳሳት መንስኤ ሆኖም ይታያል። ለእነዚህ ሁሉ ችግሮች በዋና ምክንያትነት የሚጠቀሱት ደግሞ ወደ ከባቢ አየር የሚለቀቁ የበካይ ጋዞች ልቀት መጨመርና የደን ሀብት እየተመናመነ መምጣት ነው።

የኢትዮጵያ የደን ሽፋን ከጊዜ ወደ ጊዜ እየቀነስ በመምጣት 3በመቶ መድረሱ የቅርብ ጊዜ ትዝታችን ነው። ሆኖም ባለፉት ዓመታት በተደረጉ የአረንጓዴ ዐሻራ የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር አሁን ላይ ከሀገሪቱ የቆዳ ስፋት 15 በመቶ ወይም 17 ሚሊዮን ሄክታር ብቻ መሸፈኑን በቅርቡ የወጡ የተለያዩ ጥናቶች ያሳያሉ ከዚህ ውስጥ 15 ነጥብ 8 ሚሊዮን ሄክታሩ የተፈጥሮ ደን ሲሆን የተቀረው በችግኝ ተከላ የተሸፈነ መሆኑን በተለያዩ አካላት የተደረጉ ጥናቶች ያሳያሉ። በተጨማሪ ሀገሪቱ በደን ምንጠራ ባዶ የሆነና ደንን መልሶ ለማልማት ምቹ የሆነ 18 ሚሊዮን ሄክታር ባዶ መሬት እንዳላትም ይነገራል።

በሀገሪቱ ዋነኛ የደን ጭፍጨፋ መንስዔ የሚባሉት የግብርና ልማት ማስፋፊያ፣ ከሰል እና ለግንባታ የሚቆረጠው እንጨት መጨመር፣ ልቅ ግጦሽና የሰፋፊ እርሻዎች መስፋፋት ሲሆኑ በተለይ በሀገሪቱ የተለያዩ ክልሎች የሰፋፊ እርሻ ልማት መስፋፋት በሀገሪቱ ለሚታየው የደን መመናመን ዋነኛ ምክንያት መሆኑ ይገለፃል።

ይህንን አደጋ ለመከላከል በየዓመቱ በቢሊዮን የሚቆጠሩ ችግኞችን የመትከል ዘመቻ መካሄድ ከጀመረ ሰንበት ብሏል። የግብርና ሚኒስቴር መረጃ የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ ባለፉት አምስት ዓመታት 32.5 ቢሊዮን ችግኝ መተከሉን ዘንድሮም 7.5 ቢሊየን ችግኝ በመትከል 40 ቢሊየን ለማድረስ እየተሰራ መሆኑ ያሳያል።

ይህንን በተመለከተ አዲስ ዘመን በተለይ በችግኝ ተከላው የወጣቶች ተሳትፎ ምን ይመስላል የሚለውን ለመቃኘት ሞክሯል። በተለይም በአንድ ጀንበር የ600ሚሊዮን ችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ወጣቱ ያደረገው ቅድመ ዝግጅት ምን ይመስላል የሚለውን ከአዲስ አበባ ወጣቶች ማህበር ዋና ጸሐፊ ወጣት ይሁነኝ መሐመድ እና ከኦሮሚያ ወጣቶች ማህበር ሰብሳቢ ወጣት ከድር እንዳልካቸው ጋር ቆይታ አድርጓል።

ወጣት ይሁነኝ እንደሚናገረው፤ በኢትዮጵያ የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር በክረምት ወቅት በስፋት ይከናወናል። የዚህ ምክንያትም የክረምት ምቹ የአየር ሁኔታን ተጠቅሞ ዛፎችን መትከል መቻልና ከባቢያዊ ሁኔታን ለመቀየር በማሰብ ነው ይላል።

የችግኝ ተከላን በተመለከተ ከጊዜ ወደጊዜ እንደ አዲስ አበባ ወጣቶችም ሆነ እንደ ኢትዮጵያ ወጣቶች ብዙ ልምዶችን አግኝተናል የሚለው ወጣት ይሁነኝ፤ ችግኝ ተከላን የአንድ ወቅት የዘመቻ ተግባር አድርጎ ከመውሰድ ይልቅ እንደ በጎ ፈቃድ በቋሚነት ክረምት በመጣ ቁጥር የምናከናውነው ተግባር ሆኗል ይላል።

እንደ ወጣት ይሁነኝ ገለፃ፤ በችግኝ ተከላ ወቅት ችግኝ በማፍላት ብሎም ለተከላው የሚሆነውን ሥፍራ ማዘጋጀት የወጣቶች ቀዳሚ ኃላፊነት መሆን አለበት። ችግኝ ተከላ ከሌሎች ተግባራት በተለየ ሁኔታ ወጣትን በትክክል የሚመስል ተግባር ነው። ከዚህ አኳያ ከወጣቶች የሚጠበቀው ኃላፊነት የላቀ ነው ይላል።

የኦሮሚያ ወጣቶች ማህበር ሰብሳቢ ወጣት ከድር እንዳልካቸው በበኩሉ በኦሮሚያ አራት ነጥብ ሁለት ሚሊዮን ወጣቶች በአንድ ጀንበር የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር የሚሳተፉ ሲሆን ወጣቶቹም 320 ሚሊዮን ችግኞችን እንደሚተክሉ ተናግሯል።

ባለፉት ስድስት ዓመታት በአረንጓዴ ዐሻራ ተግባር ላይ ወጣቶች በሰፊው እንቅስቃሴ እያደረጉ እንደሚገኙ የሚናገረው ወጣት ከድር ሥራውን የሚሠሩ ወጣቶችን በማደራጀት፣ የችግኝ መትከያ ቦታዎችን በማዘጋጀት፣ በቦታዎቹም ጉድጓዶችን በማዘጋጀት የተለያዩ ሥራዎችን እየሰሩ ስለመሆኑ ይናገራል።

የአዲስ አበባ ወጣቶች ማህበር ፀሐፊ ይሁነኝ መሐመድ እንደሚናገረው በአዲስ አበባ አራቱም ማዕዘን የሚተከሉ ችግኞች ለአካባቢው የአየር ሁኔታ ተስማሚ የሆኑት የትኞቹ ናቸው የት ቢተከሉ ውጤታማ ይሆናሉ።

ችግኝ አንስቶ መትከል ብቻ በቂ አይደለም በአግባቡ መንከባከብ ከፍተኛ ትኩረት ሊሰጠው የሚናገረው ወጣት ይሁነኝ፤ ከባለፉት ዓመታት ልምድና ተሞክሮ በማዳበር ችግኞች እንዴት መተከል እንደሚገባቸው? በምን መልኩ ሲተከሉ የፅድቀት መጠናቸው የተሻለ ይሆናል የሚለውን በመረዳት መትከል ያስፈልጋል። ለዚህም እንደ ማህበር የግንዛቤ መፍጠር ሥራዎችን እየሰራን ነው ይላል።

እንደ ወጣት ከድር እንዳልካቸው በተለይ በአንድ ጀምበር የ600 ሚሊዮን ችግኝ ተከላ ላይ የሚሳተፈው የሰው ቁጥር ከፍተኛ ነው። ስለዚህም ኢትዮጵያ የያዘችው በአንድ ጀንበር የ600 ሚሊዮን ችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ይሳካል የሚል ሙሉ እምነት እንዳለው ተናግሯል።

ወጣት ይሁነኝ በበኩሉ ከህብረተሰቡ መካከል ምናልባት ከዚህ በፊት ችግኝ ተክሎ የማያውቅ ይኖራል። ስለዚህም ወጣቱ እየተከታተለ የማስተማርና የማሳየት ተግባር ሊፈጽም ይገባል።

‹‹ችግኙን ከፕላስቲክ አላቆ መትከል እንደሚገባ ለማገዝ፣ አፈር በመመለስ ሥራውን ለመደገፍ በተጨማሪም ከተከለው በኋላም በፕላስቲኮቹ ምክንያት አካባቢ እንዳይበከል ቦታውን የማፅዳት ሥራ ለመሥራት አዲስ አበባን ጨምሮ በመላው ኢትዮጵያ ያሉ ወጣቶች በንቃት መሳተፍ እንዳለባቸው›› ወጣት ይሁነኝ ይናገራል።

ወጣት ይሁነኝ አክሎም አንድ ሰው ሲሞት ሰዎች እንዳይረሱት ከፈለገ ቆንጆ ሃውልት ያሰራል ወይም ከህልፈቱ በኋላ በሰዎች መታወቅ ከፈለገ መጽሐፍ ይፅፋል፣ የሰው ልጅ ግን በሕይወት ባለበት ዘመን ከራስ አልፎ ለዓለም የሚጠቅም ነገር መሥራት ከፈለገ ችግኝ መትከል ያለበት ይላል።

ችግኝ መትከል የወጣቶች አንዱ ኃላፊነት ነው። ወጣት ምቹ የመሥሪያ ቦታን ይፈልጋል፣ ነገ ቤተሰብ የመመስረት ብሎም ሀገርን የመረከብ ኃላፊነት ያለበት የዛሬ ወጣት ነው፤ ከዚህ አኳያ የተረጋጋ፣ ቁጭ ብሎ ማሰብ የሚችልበት ቦታ ያለው፣ ንፁህ አየር መተንፈስ የሚችል ህብረተሰብ እንዲፈጠር የአካባቢ ሥነ ምህዳር ለሰዎች ተስማሚ እንዲሆን መሥራት የወጣቱ የቤት ሥራ ነው።

በተጨማሪም ወጣቱ ነገ እራሷን የቻለች፣ መልክዓ ምድሯ ያልተጎዳ ሀገርን መረከብ ብሎም ለሚቀጥለው ትውልድ ማስረከብ የሚችለው ችግኝን በመትከል ነው። ወጣቱ በዕድሜው ዘመን ተሻጋሪ የሆነ ሥራ መሥራት ከፈለገ አንዱ ሥራ ችግኝ መትከል መሆን ይኖርበታል።

ወጣቶቹ እንደተናገሩትም የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብሩ ሀገር በቀል እሳቤ ከመሆን ባለፈ ባለቤቱና ተጠቃሚው ሕዝቡና ሕዝቡ ብቻ በመሆኑ በዚህም በመርሃ ግብሩ በመታገዝ በርካታ የሥራ ዕድል መፍጠር የተቻለ ሲሆን በተለይ ወጣቶችና ሴቶች ችግኝ በማፍላትና በመንከባከብ በስፋት ተጠቃሚ መሆን ችለዋል።

ወጣት ይሁነኝም ሆነ ወጣት ከድር እንደተናገሩት በየአካባቢው የሚኖሩ ሥራ ፈጣሪ ወጣቶች ከሀገራዊው የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ማግኘት የቻሉ ሲሆን ችግኝ በማፍላትና በማቅረብ፣ ጉድጓድ በማዘጋጀትና ችግኞችን በመንከባከብ የራሳቸውን ገቢ አግኝተዋል።

በግላቸው ችግኝ የሚያፈሉ ወጣቶች በተጀመረው መርሃ ግብር በመነቃቃት ዓመቱን ሙሉ የዛፍ ፣ የአትክልትና ፍራፍሬ ችግኞችን ለግለሰቦችና ድርጅቶች በመሸጥ ገቢያቸውን ማሳደግ ችለዋል የሚለው ወጣት ይሁነኝ፤ ይህ ሥራ አጥነትን በመቀነስ ለወጣቶች ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት እንደሚያስገኝ ይናገራሉ።

ችግኝ በማፍላት የተሰማሩ፣ ፕላስቲክ በመዘጋጀት የሚሠሩ፣ ውሃ የሚያጣጡ፣ የተዘጋጀውን በማከፋፈል ገቢ እያገኙ የሚገኙ ወጣቶች ቁጥር ቀላል የሚባል አይደለም የሚለው ወጣት ይሁነኝ፤ የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብሩ የኢትዮጵያን ከባቢያዊ ሥነ ምህዳር ከመጠበቅ ባሻገር ለወጣቶች የሥራ ዕድል የፈጠራ ተግባር ስለመሆኑ ይናገራል።

የተተከሉ ችግኞች ሙሉ በሙሉ እንዲጸድቁ ተስማሚ ቦታ ላይ መትከል፣ ባለቤት እንዲኖራቸው ማድረግና የአረንጓዴ ዐሻራ ሥራን ተቋማዊ ማድረግ በቀጣይ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባው ጉዳይ እንደሆነ የሚናገረው ወጣት ይሁነኝ፤ ለሰው ልጅ እንክብካቤ እንደሚያስፈልገው ሁሉ ችግኞችንም መንከባከብ አስፈላጊ እንደሆነ ያስረዳል።

ሀገራችንን ከፍ ሲልም ዓለማችንን ለኑሮ ምቹ ለማድረግ የአካባቢ ጥበቃ ተግባራትን በማስፋት ማከናወንና የተፈጥሮ ሀብት በመንከባከብ፣ በአግባቡ መጠቀምን ከወዲሁ ማሰብ ይኖርብናል የሚለው ወጣት ይሁነኝ፤ ከዚህ አኳያ በተለይ ወጣቶች የሚጠበቅባቸውን ግዴታ ሁሉ መወጣት እንዳለባቸው ያስረዳል።

የዓለም ሀገራት ለአካባቢ ጥበቃ ትኩረት ሰጥተው እየሰሩ ይገኛሉ። ኢትዮጵያም የደን ሀብቷን ወደ ነበረበት በመመለስ፤ የብዝሀ ሕይወት ሀብቷን ከጥፋት መታደግ ይገባታል። ከዚህ አንጻር በተለይም ከባለፉት ስድስት ዓመታት ጀምሮ በመላ ሀገሪቱ እየተከናወነ የሚገኘው የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር ያለው ጠቀሜታ ዘርፈ ብዙ በመሆኑ እንደ ሀገር ወጣቱ ብቻ ሳይሆን ሁሉም ዜጋ በንቃት መሳተፍ ይገባዋል።

እንደ አዲስ አበባ ወጣቶች ማህበር በከተማዋ በ119 ወረዳ፣ በአስራ አንዱም ክፍለ ከተማ ውስጥ የሚገኙና በክረምት የበጎ ፈቃድ ተግባር ማለትም በክረምት የማጠናከሪያ ትምህርት፣ በደም ልገሳ፣ በመንገድ ትራፊክ፣ በሰላምና ፀጥታ ብሎም በሌሎች መሳል የበጎ አድራጎት ሥራዎች ተሳትፎ እያደረጉ የቆዩ ወጣቶች በአጠቃላይ ነሐሴ 17 በሚካሄደው የአንድ ጀንበር የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር የመትከል፣ የማስተከል፣ የማስተባበር ተግባር ላይ እንዲሰማሩ ሰፊ ቁጥር ያለው ወጣት በማደራጀት ዕለቱን እየተጠባበቁ ስለመሆኑ ወጣት ይሁነኝ ይናገራል።

ከዚህ ባሻገር የከተማዋ ወጣቶች በችግኝ ተከላው ተሳታፊ እንዲሆኑ ለማድረግ እንደ ማህበር የተለያዩ አማራጮችን በመጠቀም የቅስቀሳ ሥራዎች እየሠሩ እንደሚገኙ የሚናገረው ወጣት ይሁነኝ፤ መርሃ ግብሩ እንደ ከተማ አስተዳደር ግቡን እንዲመታ ጥረት እየተደረገ ነው ይላል።

ሁለቱም ወጣቶች በጋራ እንደሚስማሙበት በተለያየ የበጎ አድራጎት ተግባራት ላይ እስከ አሁን የመሳተፍ ዕድል ያልነበራቸው ወጣቶች ሊኖሩ ይችላሉ፣ የችግኝ ተከላ ጉዳይ ግን በየትኛውም የዕድሜ ዕርከን ያለ ወጣት፣ መንቀሳቀስ የሚችል ጤነኛ የሆነ ወጣት ሁሉ መሳተፍ ያለበት በመሆኑ በመርሃ ግብሩ በንቃት ተሳትፎ ማድረግ ከሁሉም የኢትዮጵያ ወጣቶች ይጠበቃል ይላል።

በአየር ንብረት ሚዛን መዛባት ምክንያት የበረዶ ግግር እየቀለጠ፣ አካባቢን ለውሃ መጥለቅለቅ አደጋ እያጋለጠ፣ በአውሎ ንፋስና በእሳት አደጋ የሰው ህይወትና ንብረት እየጠፋ መሬት እየተደረመሰና ሕንፃዎች እየፈራረሱ፣ ይህም ሕይወት ያለውን ፍጡር እስትንፋስ እያሳጠረ ይገኛል። ኢትዮጵያም የዚህ ገፈት ቀማሽ ሀገር ናት፤ ይህንን ችግር ለማስቀረት ሁነኛ መፍትሔው ችግኝ መትከል በመሆኑ ወጣቱ ብቻ ሳይሆን ሁሉም ዜጋ የበኩሉን ሚና መወጣት ይኖርበታል።

የችግኝ ተከላ ተግባር ላይ መሳተፍ ማለት ለአካባቢ፣ ለሀገር እንዲሁም ለመላው ዓለም ሕይወትን መትከል ማለት ነው የሚሉት ወጣቶቹ ፤ ከዚህ አኳያ በተለይ ወጣቶች በተግባሩ በግንባር ቀደምትነት የመሳተፍ ግዴታ ያለባቸው በመሆኑ ይህንን ግዴታቸውን በፈቃደኝነት መወጣት እንዳለባቸው መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

ክብረአብ በላቸው

አዲስ ዘመን ዓርብ ነሐሴ 17 ቀን 2016 ዓ.ም

 

Recommended For You