ከልማዳዊ አሠራር ሥርዓት በማላቀቅ በምግብ ራስን ችሎ የሀገሪቱን ኢኮኖሚ ማገዝ የግድ መሆኑን ብዙዎች ይስማማሉ። በፍላጎትና በአቅርቦት መካከልም ያለውን የሚዛን መዛባት ለማረም ኋላ ቀር አሠራሮችን በመፈተሽ ዘርፉን የማዘመን እስትራቴጂካዊ አሠራሮች ላይ ልዩ ትኩረት እንደሚያስፈልግም ይታወቃል። ሰፊ ለም መሬት፣ ከፍተኛ መጠን ያለው የገጸ ምድርና የከርሰ ምድር ውኃ፣ ተስማሚ የአየር ፀባይ፣ እንዲሁም ከፍተኛ ቁጥር ያለው ወጣት የሰው ኃይል ባለበት አገር በምግብ ዕጦት መቸገር መብቃት ያለበት ጉዳይ እንደሆነ እሙን ነው።
በእንስሳት ሀብትም ከአፍሪካ አንደኛ ደረጃን ይዘን ሥጋ፣ ዶሮ፣ ቅቤ፣ ወተት፣ ዕንቁላል እና ሌሎቹ የእንስሳት ተዋፅዖ የቅንጦት ምግብ የመሆኑን እንቆቅልሽ ለመፍታት የአሠራር ሥርዓት በየደረጃው ተፈትሾ መስተካከል አለበት። የትኛውም አደጉ፣ በለፀጉ የምንላቸው ሀብታም ሀገራት የመጀመሪያው መሸጋገሪያ ድልድያቸው የግብርና ዘርፉን በሚያስፈልገው ሁሉ ማዘመን ነውና እንደሀገር በዘርፉ መከወን ያለባቸውና እየተከናወኑ ያሉ ሥራዎች ከንግግር ባለፈ የሀገራችንን ኢኮኖሚ አቅምን በሚያረጋግጥ እና በሚያረጋጋ ሁኔታ መሥራት ከሁሉም የሚጠበቅ ስለመሆኑ አያጠራጥርም።
የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ወጣቶች በዲጂታል ቴክኖሎጂ ላይ ያላቸውን ተሳትፎ ለማሳደግና ለማጠናከር በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ24ኛ ጊዜ “From Clicks to Progress: Youth Digital Pathways for Sustainable Development” (በሚል መሪ ቃል በኢትዮጵያ ደግሞ ለ21ኛ ጊዜ “ወጣቶችን በቴክኖሎጂ ማብቃት ለዘላቂ ልማት ግቦች ስኬት” በሚል መሪ ቃል ዓለም አቀፍ የወጣቶች ቀን ተከብሯል። በበዓሉም በሀገር አቀፍ ደረጃ በወጣቶች አማካኝነት የተፈጠሩ የዲጂታል ውጤቶች የፈጠራ ሥራዎችን የያዘ ኤግዚቢሽን ቀርቧል።
ወጣት አልዓዛር የሺጥላ በዚህ ኤግዚቢሽን የፈጠራ ሥራዎቻቸውን ይዘው ከቀረቡ ወጣቶች መካከል አንዱ ነው። (ጥሁር ባዮ ቴክ) የተሰኘ የቴክኖሎጂ ድርጅት መሥራች አባል የሆነው ወጣት አልዓዛር፤ የቴክኖሎጂ ኩባንያው ከተመሠረተ አራት ዓመት እንደሆነውና በዚህ ቆይታውም የተለያዩ የፈጠራ ሥራዎችን እንደሠራ ይናገራል። ጥሁር ባዮ ቴክ በዋናነት የሚሠራው የአፈር ማዳበሪያን ማምረት ላይ እንደሆነ የሚናገረው አልዓዛር፤ ይህንንም የሚያመርተው አፈር ውስጥ ከሚገኙና የአፈር ለምነትን ሊጨምሩ ከሚችሉ ደቂቅ አካላት ወይም ባክቴሪያዎች እንደሆነ ይገልጻል።
‹‹ሁለት አይነት የማዳበሪያ ምርቶችን እናመርታለን።›› የሚለው ወጣት አልዓዛር፤ የመጀመሪያው በፈሳሽ መልክ ሲሆን፤ ሁለተኛው ጠጣር ማዳበሪያ ስለመሆኑ ይገልጻል። ጠጣር ማዳበሪያው 125 ግራም ተዘጋጅቶ በ125 ብር ለገበያ እንደሚቀርብ የሚናገረው የፈጠራ ባለሙያው ይህም ለሩብ ሄክታር መሬት እንደሚበቃ ያስረዳል። በተመሳሳይ የፈሳሽ ማዳበሪያው አንድ ሊትር በሃያ ሊትር ውሃ ተበጥብጦ ለሩብ ሄክታር ማሳ በበቂ ሁኔታ መዋል እንደሚችል ይገልጻል። በአሁኑ ወቅት በብዛት አገልግሎት ላይ የሚውለው የኬሚካል ማዳበሪያ ከአየር ንብረት፣ ከዋጋ፣ ከአርሶ አደር ተደራሽነት አንፃር ያለው ችግር የሚታይና ጉልህ ነው የሚለው ወጣት አልዓዛር፤ ይህንን ችግር ለመቅረፍ ገበሬው መግዛት በሚችለው ተመጣጣኝ ዋጋ የተሻለ ምርት መስጠት የሚችል ማዳበሪያ ይዘው እንደመጡ ይናገራል።
‹‹ማዳበሪያውን ወደ ገበሬው ከማድረሳችን በፊት በራሳችን ላብራቶሪ፣ በእርሻ ላይ የተለያዩ ሙከራዎችን እናደርጋለን” የሚለው ወጣት አልዓዛር፤ ሙከራውን በሚያደርጉበት ወቅት ከተለመደው የኬሚካል ማዳበሪያ በተሻለ ከሃያ እስከ ሠላሳ በመቶ የምርታማነት ጭማሪ እንዳለው ይናገራል። በሌላ በኩል የማዳበሪያ ምርቱ የአፈር አሲዳማነትን በከፍተኛ ደረጃ እየቀነሰ እንደሚገኝ የሚናገረው አልዓዛር፤ በአሁኑ ወቅት በአምስት ክልሎች ለገበሬዎች፣ ለተለያዩ የግብርና ባለሙያዎች ሥልጠናዎችን በመስጠት የተለያዩ ሥራዎችን እየሠሩ እንደሚገኙ ያስረዳል። በዚህ የምርቱ ቅቡልናት ከግዜ ወደ ግዜ በከፍተኛ ደረጃ እየጨመረ እንደመጣ ይገልጻል።
በኢትዮጵያ የአፈር አሲዳማነት በየዓመቱ 2 ነጥብ 1 ቢሊዮን ብር የሚገመት የሃብት ብክነት እያደረሰ እንደሚገኝ የሚናገረው ወጣት አልዓዛር፤ በየዓመቱ 1 ነጥብ 47 ሚሊዮን ኩንታል ማዳበሪያ መስጠት ያለበትን ጥቅም ሳይሰጥ በአፈር አሲዳማነት ምክንያት ይባክናል። ይህ በሀገር ደረጃ ሲሰላ ጉዳቱ ከፍተኛ ነው ይላል። እንደ ወጣት አልዓዛር ገለፃ፤ በኢትዮጵያ እየታረሰ ካለው 16 ሚሊዮን ሄክታር መሬት መካከል 6 ነጥብ 5 ሄክታር መሬት በአሲዳማነት የተጠቃ ሲሆን፤ ከእዚህም ውስጥ ደግሞ 3 ነጥብ 7 ሚሊዮን ሄክታር የሚሆነው በጠንካራ አሲዳማነት የተጠቃ ነው። ይህም ጥቅም ላይ የዋለውን የእርሻ መሬት 43 በመቶ ድርሻ የሚሸፍን ነው ይላል።
ይህንን ችግር ለመቅረፍ ሁነኛ መፍትሔ ሆኖ የመጣውንና ከተፈጥሮ ነገሮች የሚሠራውን የአፈር ማዳበሪያ በስፋት በመላው ሀገሪቱ ተደራሽ ለማድረግ የተባበሩት መንግሥታት የዓለም የምግብ ፕሮግራምን ጨምሮ ከተለያዩ ዓለም አቀፍ ግብረሠናይ ድርጅቶች ጋር እየሠሩ እንደሚገኙ የሚናገረው ወጣት አልዓዛር፤ ከእነዚህ አጋር አካላት ያገኙትን የገንዘብ ድጋፍ በመጠቀም ምርቱን በስፋት ጥቅም ላይ ለማዋል ጥረት እያደረጉ ስለመሆኑ ይናገራል።
የመጀመሪያ ዲግሪውን በባዮ ቴክኖሎጂ ምሕንድስና ሁለተኛ ዲግሪውን ደግሞ በግብርና ባዮ ቴክኖሎጂ የትምህርት መስክ ያጠናቀቀው አልዓዛር፤ ይህንን የፈጠራ ሥራ በቡድን ለመሥራት ምክንያት ስለሆናቸው ነገር ሲናገር፤ በሀገሪቱ ያለው የኬሚካል ማዳበሪያ ዕጥረትና በከፍተኛ ደረጃ ምርታማነትን እየጎዳ የሚገኘው የአፈር አሲዳማነት ጉዳይ የመፍትሔ ሀሳብ ማመንጨት እንዲችሉ ምክንያት እንደሆናቸው ይናገራል።
የቴክኖሎጂ ኩባንያው መሪ ቃል “ሕይወትን በሕይወት እንመግብ” የሚል እንደሆነ የሚናገረው ወጣት አልዓዛር፤ በኢትዮጵያ አርሶ አደሮች የኬሚካል ማዳበሪያ ለመግዛት የሚያርሱበትን በሬ እስከ መሸጥ ይደርሳሉ። ይህንን የአፈር ማዳበሪያ ግን ዶሮና እንቁላል በሚሸጥበት ዋጋ መግዛት እንደሚችሉ ይናገራል። የአጠቃቀም ሂደቱም እጅግ ቀላል ነው የሚለው የፈጠራ ባለሙያው፤ የትራንስፖርት ወጪ የማይጠይቅና በሀገር ውስጥ የሚመረት በመሆኑ አርሶ አደሩ በፈለገበት ግዜ የፈለገውን መጠን በማዘዝ ተመርቶለት መውሰድ የሚችል በመሆኑ ለአርሶ አደሩ በብዙ መልኩ እፎይታ የሚሰጥ ነው ይላል።
በተጨማሪም በግብርና ላይ የተመሠረተ ማንኛውም ሰው አዲሱን ማዳበሪያ በሚጠቀምበት ወቅት ለአረም መከላከያ ተጨማሪ ወጪ ማውጣት አይጠበቅበትም የሚለው ወጣት አልዓዛር፤ የአፈር ማዳበሪያው በይዘቱ አረም መከላከል የሚችል በመሆኑ ወጪን ከመቀነሱ ባሻገር ምርቱ ለምግብነት ሲውል ከኬሚካል ማዳበሪያ ጋር ተያይዞ ከሚመጡ የጤና እክሎች ነፃ መሆን እንደሚቻል ይናገራል።
በሌላ በኩል አርሶ አደሮች ይህንን ማዳበሪያ አንድ ጊዜ ጥቅም ላይ ካዋሉት በኋላ፤ በቀጣዩ የእርሻ ወቅት ባይጠቀሙም የማዳበሪያው ይዘት አፈሩን በቶሎ የማይለቅ በመሆኑ ለተጨማሪ አንድ ዓመት ያለ ማዳበሪያ ምርት ማግኘት ይችላሉ የሚለው ወጣት አልዓዛር፤ ይህ አሁን ያለውን የኬሚካል ማዳበሪያ አጠቃቀም ልምድ የሚቀይር ምርታማነትንም የሚጨምር ነው ይላል። ማዳበሪያው መሬት የራሷን ሀብት በአግባቡ ለመጠቀም የሚያመች ስለመሆኑ የሚናገረው አልዓዛር፤ አፈር በተፈጥሮ የያዘውን ጠቃሚ ኬሚካል በውጤታማነት ጥቅም ላይ እንዲውል በማድረግ ምርትና ምርታማነትን የሚያሳድግ ፈጠራ መሆኑን ያስረዳል።
እንደ ወጣት አልዓዛር ገለፃ፤ ለአብነት አንድ ሰው የተለምዶ ኬሚካል ማዳበሪያ አንድ መቶ ኪሎ ግራም ቢገዛ ስልሳ አራት ኪሎ ግራሙ ድንጋይ ነው። ይህ የተፈጥሮ ማዳበሪያ ግን የተመረተው 125 ግራሙ ሙሉ በሙሉ ጥቅም ላይ የሚውል ነው። በተጨማሪም በሃያ አራት ሰዓት ውስጥ ማዘጋጀት የሚቻል ነው ይላል።
የማዳበሪያ ምርቱ በገበሬዎች ዘንድ ያለው አቀባበል አስደሳች ስለመሆኑ የሚናገረው ወጣት አልዓዛር፤ በኬሚካል ማዳበሪያ ዙሪያ ያለውን ችግር ስለሚያውቁት አዲሱን ምርት ከመጠቀም አኳያ ተነሳሽነታቸው ይበል የሚያሰኝ ነው። በአሁኑ ወቅት በአዲስ አበባ ዙሪያ፣ በኦሮሚያ፣ በአማራና ደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የሚገኙ በግብርና ልማት የተሠማሩ ከሃያ ሺህ በላይ ግለሰቦች አዲሱን የማዳበሪያ ምርት በስፋት ጥቅም ላይ እያዋሉት ስለመሆኑ ይገልጻል። መንግሥት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተለይ ለቴክኖሎጂና ፈጠራ የሰጠው ትኩረት ይበል የሚያሰኝ ነው የሚለው አልዓዛር፤ ይህ የዓለም ወጣቶች ቀንን ምክንያት በማድረግ የተዘጋጀው ዓውደ ርዕይም ሀሳብና በጅምር ያለ የፈጠራ ሥራ ያላቸው ወጣቶች የተገኙበት ነው። በጅምር ያለ የቴክኖሎጂ ፈጠራ ሥራ ደግሞ ከፍተኛ ፋይናንስ የሚጠይቅ በመሆኑ የተለያዩ ኢንቨስተሮች አብረው እንዲሠሩ ለማድረግ ሥራዎችን ማሳየት የሚቻልበት አጋጣሚ መፈጠሩ በጎ ጅምር ስለመሆኑ ይናገራል።
ወጣት አልዓዛር እንደሚናገረው፤ ኢትዮጵያ ውስጥ ግብርናውን በቴክኖሎጂ በመጠቀም ዘመናዊ በሆነ መልኩ ካልተሠራ በሚሊዮን የሚቆጠር ሕዝብ በራስ አቅም መመገብ አዳጋች ነው። ሀገሪቱ ያላት ሕዝብ ቁጥር ከፍተኛ ነው። ወደ እያንዳንዱ ቤት መድረስ የሚቻለው ደግሞ በቴክኖሎጂ ነው። ስለዚህ ከምንም በላይ እንደ ሀገር ለዘርፉ ትኩረት መስጠት የውዴታ ግዴታ እንደሆነ ይናገራል። ጉዳዩ የሚመለከታቸው የቴክኖሎጂ ተቋማት ትብብር ምን እንደሚመስል ወጣት አልዓዛር ሲናገር፤ ለትብብርና አብሮ ለመሥራት ያላቸው ፍላጎት እጅግ አነስተኛ ነው። ምርቱን በስፋት ገበያ ላይ ለማዋል እንዲቻል የሚያግዝ የመመዘኛ ሥርዓት እንኳ የላቸውም ይህ ደግሞ ከፍተኛ ችግር እየፈጠረ እንደሆነ ይገልጻል።
‹‹የኬሚካል ማዳበሪያን ችግር መፍታት ማለት ጤናማ አመጋገብ ፈጠርን፣ ብቁ ምርት የማምረት አቅም መገንባት ቻልን ማለት ነው።›› የሚለው አልዓዛር፤ ቴክኖሎጂው ለሀገር ከሚኖረው ከፍተኛ ፋይዳ አንፃር፤ የመሥሪያ ቦታ ከማመቻቸት አኳያ ከፍተኛ ችግር እንዳለባቸው ይገልፃል። ይህንን ችግራቸውን ለመቅረፍ መንግሥታዊ ተቋማት እገዛ አያደርጉም ይህ በውጤታማነታቸው ላይ እያሳደረ ያለው አሉታዊ ተፅዕኖ ከፍተኛ መሆኑንም ያስረዳል።
የአዲሱን የማዳበሪያ ምርት በቅርቡ ወደ ጎረቤት ሀገራት መላክ እንደሚጀምሩ የተናገረው አልዓዛር፤ ይህንን ውጥናቸውን ከግብ ለማድረስ እስከአሁን ድጋፍ ሲያደርጉላቸው ከቆዩ ከተለያዩ ዓለም አቀፍ አጋር አካላት ጋር በጋራ እየሠሩ ስለመሆኑ ይናገራል። በሚቀጥሉት ዓመታት እንደ ቴክኖሎጂ ኩባንያ የሀገሪቱን የግብርና ሴክተር ችግር ለመቅረፍ ትልቅ ራዕይ አስቀምጠው እየሠሩ ስለመሆኑ የሚናገረው አልዓዛር፤ “የኢትዮጵያ ገበሬ ትንሽ ድጋፍ ብናደርግለት የተሻለ ምርት የማቅረብ አቅም ስላለው ይህንን አቅሙን አሟጦ መጠቀም እንዲችል ለማድረግ ያላሰለሰ ጥረት እናደርጋለን” ይላል።
ክብረአብ በላቸው
አዲስ ዘመን ዓርብ ነሐሴ 10 ቀን 2016 ዓ.ም