የሕክምና ቁሳቁስን በሀገር ውስጥ የማምረት ህልሙን ያሳካው ወጣት

የሕክምና መገልገያ ቁሳቁስ እጥረት ስለመኖሩ ወደ ሕክምና ተቋማት /በሆስፒታሎች/ በሄደባቸው አጋጣሚዎች ሁሉ አስተውሏል። እጥረቱ እየጨመረና እየባሰበት መምጣቱን ይመለከታል። ይህን ችግር አይቶና ሰምቶ ማለፍ አልሆንልህ ሲለው ችግሩን ለመፍታት ሃሳቦችን ያወጣና፣ ያወርድ ጀመር። ይሄኔ አንድ መፍትሔ ብልጭ አለለት።

በፍጥነት ወደ መፍትሔው ለመድረስ ችግሩን ከሥር መሰረቱ ማጥናት ጀመረ። የሕክምና መገልገያ ቁሳቁስ ፍለጋ ወደ ገበያ ሲያማትር ገበያ ላይ ምንም አይነት የሀገር ውስጥ ምርት አለመኖሩን ይረዳል። ከዚያም ‹‹እነዚህን ቁሳቁስ እንዴት በሀገር ውስጥ ማምረት አልተቻለም? ማምረት የሚቻል ከሆነ ደግሞ ለምንድነው በከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ከውጭ ሀገር የምናስገባው?›› የሚሉ ቁጭት የወለዳቸው ሃሳቦች በውስጡ ይመላለሱ ጀመር።

ለዚህ ችግር መፍትሔ ይሆን ዘንድ የህክምና ቁሳቁስን በሀገር ውስጥ ማምረት እንደሚያስፈልግ እያመነ መጣ። ለእዚህም ጥናት ወደ ማድረግ ገባ። ባደረገው ጥናትም የሀገር ውስጥ አምራች እንደሌለ አረጋገጠ። ሀሳቡን ወደ ተግባር ለመተርጎም በረጅሙ አቅዶ በቁርጠኝነት ተነሳ።

ያሰበው እውን ሆኖ የሕክምና መገልገያ ቁሳቁስን በሀገር ውስጥ የሚያመርተውን ‹‹ጦሳ ኢንጂነሪንግ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ድርጅት››ን መሰረተ። የዚህ ተቋም ሥራ አስኪያጅና መስራች አቶ ቢኒያም ተስፋዬ የዕለቱ የስኬት እንግዳችን ነው።

አቶ ቢንያም ወደ ሕክምና ተቋም /በሆስፒታል/ በሄደበት ጊዜ የገጠመውን እንዲህ ያስታውሳል። ‹‹የሀገራች የሕክምና ተቋማት ብዙ የሕክምና መገልገያ ቁሳቁስ እጥረት አለባቸው። እጥረቱ የሚጀምረው ከበር ነው። ስትሬቸር፣ ዊልቸር እና የታማሚ አልጋዎች ለማግኘት አስቸጋሪ ነው። እጥረት ስላለ ወረፋ መጠበቅ የግድ ሆኗል፤ ችግሮች በሁሉም ቦታዎች ጎልተው የሚታዩ ናቸው›› ይላል። በዚህ ምክንያት በሀገር ውስጥ ለማምረት በማሰብ ስራ መጀመሩን ይገልጻል።

አቶ ቢንያም ከሚዛን ቴፒ ዩኒቨርሲቲ በመካኒካል ኢንጂነሪንግ ትምህርት ተመርቋል። ይህን ሥራ ለመስራት በሙያው እውቀቱ ቢኖረውም፣ ብቻውን ለመስራት ግን አልፈለገም፤ ይልቁንም በሙያው ሊያግዙት የሚችሉ አምስት ሰዎች በማሰባሰብ በጥቃቅንና አነስተኛ ተደራጀ።

ከባልደረቦቹ ጋር ሥራውን ለመጀመር ሲነሱ ሃሳቡን ወደ አንድ በማምጣት ወደ ሥራው መግባት የመጀመሪያው ፈተና ሆኖባቸውም ነበር። ሆኖም ግን ፈተናውን አልፎ ሃሳቡን አሸንፎ ወደ ማምረት ሥራ ገቡ፤ ቀጥሎ ደግሞ ሌላ ፈተና መጣ። ሁሉም እስከመጨረሻ አብረው መዝለቅ ሳይችሉ ቀሩ። እርሱና አንድ ባልደረባው ብቻ ቀሩ። አብራው የቀረችው ለሥራው አጋዥ እንዲሆኑ ከመረጣቸው አምስቱ ሰዎች መካከል አንዷ ባለቤቱ ሐረገወይን አምባዬ ነበረች። ‹‹ከአምስታችን ሦስቱ የራሳቸውን ከፍተዋል። ይሄንን ሥራ ሁለት ሆነን ነው እየሰራን ያለነው›› ይላል ስለጉዳዩ ሲያብራራ።

ሁለቱ ጥንዶች ትውልድና እድገታቸው ደሴ ከተማ ሲሆን፤ በጋብቻ ከተጣምሩ ጊዜ አንስቶ አብረው ለመስራት ያሰቡ ነበር። ምንም እንኳን ሙያቸው የተለያየ ቢሆንም የሙያቸውን ስብጥር በማስተሳሰር ይሰራሉ። እሷ በሕክምና ሙያ ዘርፍ ፋርማሲስት በመሆኗ በሙያው ዙሪያ ያሉ እጥረቶችን በሚገባ ታውቃለች። ሥራውን በቀላሉ ተግባብተውና ተጋግዘው በአንድነት በመስራታቸው ጥረታቸው ፍሬ ማፍራት ችሏል።

አቶ ቢንያም ‹‹ባለቤቴ በፋርማሲ ባለሙያ በመሆኗ የዘርፉን ችግር ከሥር መሰረቱ በሚገባ እንድረዳው አግዞኛል። በትዳር ብቻ ሳይሆን ሥራችንንም በአንድ አጣምረን ለመስራት አስችሎናል። ሁለት ሆነን እንደ አንድ እያሰብን ሥራችንን በመተጋገዝና በአንድነት እንድንሰራ ነገሮች ቀላል ሆነው አሁን ላለንበት ደረጃ እንድንደርስ አስችሎናል›› ይላል።

ጦሳ ኢንጂነሪንግ የሕክምና መገልገያ ቁሳቁስ ማምረቻ ፋብሪካ ቁሳቁሱን ማምረት የጀመረው ከዘጠኝ ዓመት በፊት በ2007 ዓ.ም ነው። በአሁኑ ወቅትም በኢትዮጵያ ላሉ የሕክምና ተቋማት የሚያስፈለጉ ማንኛቸውንም አይነት የሕክምና መገልገያ ቁሳቁስ እያመረተ ይገኛል። ድርጅቱ የህክምና ቁሳቁሱን ማምረት የሚያስችለውን ፈቃድ ከኢትዮጵያ መድኃኒት ቁጥጥር ባለስልጣን አግኝቷል።

ሥራ የጀመረው በ2ሺ 500 ብር መነሻ ካፒታል ነው። አሁን ላይ ከቻይና፣ ከህንድ እና ከአውሮፓ ሀገራት ይመጡ የነበሩ የሕክምና መገልገያ ቁሳቁስ እያመረተ ነው።

ጦሳ ኢንጂነሪንግ 25 አይነት የህክምና መገልገያ ቁሳቁስን ያመርታል። ዲሊቨሪ ቤድ፣ የምርመራ አልጋዎችን /ኤግዛማይኔሽን ቤድ/፣ የሕሙማን አልጋዎችን /ፔሸንት ቤድ ፣ አቴንደንት ቸር/ እና የመሳሰሉ የተለያየ ደረጃ ያላቸው የሕክምና መገልገያ ቁሳቁስ እንደየሰው አቅምና ፍላጎት ያመርታል። በአብዛኛው ሆስፒታሎች ውስጥ የታማሚ አልጋም ሆነ ወንበር እጥረት ስላለ እጥረቱን የሚቀርፉ ቁሳቁስን እያመረተ ያቀርባል። ወንበርም አልጋም ሊሆኑ የሚችሉ፣ ቦታ የማይፈጁ መሰል ምርቶችን ያመርታል። ለአንድ ታማሚ አንድ አስታማሚ እንዲያድር ሲፈቀድ አስታማሚው ቀን ቁጭ ብሎበት ማታ ደግሞ የሚተኛበት መገልገያ ቁስንም በማምረት ለተለያዩ ሕክምና ተቋማት ያቀርባል።

እነዚህ የሕክምና መገልገያ ቁሳቁስ ከውጭ በከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ይገዙ እንደነበር የሚገልጸው አቶ ቢንያም፤ ቁሳቁሱን በሀገር ውስጥ በማምረት ከውጭ ለማስመጣት የሚወጣውን የውጭ ምንዛሬ ማዳን መቻሉን ይናገራል። ምርቶቹ ብዙ ፈላጊ እያገኙ መሆናቸውን ጠቅሶ፣ ምርቶቹን በዋናነት የመድኃኒትና የሕክምና ቁሳቁሶች ጅምላ አከፋፋዮች፣የመንግሥትና የግል ሆስፒታሎች፣ ጤና ጣቢያዎች፣መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች እና መሰል ተቋማት ይገዛሉ ። ቀደም ባሉት ጊዜያትም ቢሆንም ምናልባት ምርቶቹ በሀገር ውስጥ አለመመረታቸው እንጂ ከተመረተ ለመግዛት የማይፈልግ የሕክምና ተቋም የለም ይላል።

ሀገር ውስጥ ያለውን ጥሬ እቃ በመጠቀም ሙሉ በሙሉ በመተካት በሀገር ውስጥ የሚመረቱ ምርቶች እንዳሉ ሁሉ የተወሰኑትን ከ10 እስከ 15 በመቶ ያህሉን ከውጭ በማስገባት ቀሪዎቹ ሀገር ውስጥ የሚመረቱበትም ሁኔታም እንዳለ ይገልጻል። እነዚህ ሥራዎች ሲሰሩ ከውጭ ሀገር የሚገቡ የሕክምና መገልገያ ቁሳቁስ አሻሻለው ፈጠራን አክለው በሀገር ውስጥ ካለው ነባራዊ ሁኔታ ጋር እንዲጣጣሙና ምቹ እንዲሆኑ ተደርገው እንደሚሰሩ ያስረዳል።

ለማምረቱ ስራ ከሚያስፈልጉት ግብአቶች 75 በመቶ ያህሉን በሀገር ውስጥ ይገኛሉ። ለአብነት አንድ አልጋ ለመስራት የሚያስፈልጉ ቁሳቁስ በአብዛኛው ሀገር ውስጥ ይመረታሉ። ብረት ከዱከም ኢንዱስትሪና ከቃሊቲ አምራቾች፣ ስፖንጅ ደግሞ ከስፖንጅ አምራች ፋብሪካዎች፤ሴንቴቲክ ሌዘር ከሀገር ውስጥና በተወሰነ መልኩ ከውጭ የሚመጣበት ሁኔታ መኖሩን ይጠቅሳል።

ሀገር ውስጥ የሚመረቱን እነዚህ ምርቶች በተመጣጣኝ ዋጋ ለገበያ ይቀርባሉ፤ ደረጃቸው ከውጭ በሚመጡት ምርቶች ደረጃ ቢሆንም ዋጋቸው ግን 25 በመቶ ያህል ይቀንሳል። ሀገር ውስጥ ሙሉ ለሙሉ በብረት ብቻ የምንሰራቸው ምርቶች 50 በመቶ እና ከዚያ በላይ ይቀንሳሉ። የምርቶቻችን ዋጋም በእንደምንጠቀመው የጥሬ እቃ አይነት ይለያያል። ዋጋቸው የተቋማቱን የመግዛት አቅም ያገናዘበ ምርቶችን እናመርታለን። ይህ ደግሞ ተቋማቱ በሚፈልጉት ልክና በአቅማቸው ገዝተው እንዲጠቀሙ ያስችላል ሲል ያብራራል።

ጦሳ ኢንጂነሪንግ የጥገና አገልግሎትም ይሰጣል። ለምሳሌ ቁሳቁሱ ሲበላሹ የመጠገን፤ የሚቀየረውን ደግሞ የመቀየር አገልግሎት ይሰጣል። ድርጅቱ የሚያመርታቸው ቁሳቁስ ጥራት ያላቸው ናቸው። ምክንያቱም የሕክምና ቁሳቁስ እንደመሆናቸው ጥንቃቄ የሚፈልጉና ጥራታቸውን የጠበቁ መሆን እንዳለባቸው አቶ ቢንያም ይገልጻል።

‹‹ምርቶቻችን ምንም አይነት የጥራት ችግር የለባቸውም። ከውጭ የሚመጡትን ግብዓቶችንም ቢሆን በጥራት ከሚያመርቱ አምራቾች ገዝተን ስለምንጠቀም እስካሁን ብዙ የቴክኒክ ችግር አልገጠመንም›› ይላል።

አቶ ቢንያም እንደሚለው፤ ድርጅቱ አሁን ላይ በወር 500 አልጋዎችን የማምረት አቅም አለው። ይህን በማስፋፋት በወር ከሁለት ሺ እስከ ሦስት ሺ አልጋዎችን ለማምረት አቅዶ እየሰራ ነው።

‹‹አሁን ባለው ሁኔታ በሀገር ውስጥ ያለውን ፍላጎት እናሟላለን ብለን አናስብም፤ ብዙ የመንግሥትና የግል ሆስፒታሎች ስላሉ ያለው ፍላጎትም ከፍተኛ ነው። እኛ ደግሞ የሀገር ውስጥ ፍላጎት ከመሙላት ባሻገር የውጭ ምንዛሪ ማምጣት አለብን ብለን ስለምናምን ምርቶቻችንን ወደ ውጭ ሀገራት ለመላክ አሰበንም እየሰራን ነው›› በማለትም ይገልፃል።

ጦሳ ኢንጂነሪንግ የማምረቱን ስራ የሚያካሂደው ፈረንሳይ ለጋሲዮን ጉራራ ኢንዱስትሪ ዞን አካባቢ ነው። ድርጅቱ ለ50 ሰዎች የሥራ እድል በመፍጠር ባለሙያዎችን ማፍራት የተቻለም ሲሆን፤ መካኒካል ኢንጂነሮች፣ ፋርማሲስቶች፣ ፕሮፌሽናል በያጆች እና የቴክኒክና ሙያ ምሩቃን ባለሙያዎች፣ ቀለም ቀቢዎችና ሌሎች የተለያዩ ሰራተኞችም አሉት።

በሁለት ሺ 500 መቶ ብር ካፒታል ሥራውን አሃዱ ብሎ የጀመረው ጦሳ ኢንጂነሪንግ፤ አሁን ላይ 30 ሚሊዮን ካፒታል ያስመዘገበ ኢንቪስትመንት ባለቤት መሆን ችሏል።

አቶ ቢንያም እንደሚለው፤ ምርቶቹን በእጥፍ በማሳደግ የሀገር ውስጥ ፍላጎትን በማሟላት ለውጭ ለመላክ የሚያስችላቸውን የዳሰሳ ጥናት በማድረግ ሀገራቱ ምርቶቹን የመግዛት ፍላጎት እንዳደረባቸው መረዳት ተችሏል ሲል ተናግሯል።

መንግሥት የሀገር ውስጥ አምራቾችን ለማበረታታት እያደረገ ያለው ጥረት ለአምራቹ ትልቅ አስተዋጽኦ ያበረክታል የሚለው አቶ ቢንያም፤ በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ የሀገር ውስጥ ምርቶችን ለማስተዋወቅና ለማበረታት በሚል በሚዘጋጁ አውደ ርዕዮች ላይ ተሳታፊ መሆኑን ገልጿል። በዚህም አምራቾች ምርቶቻቸውን እያስተዋወቁ የገበያ ትስስር መፍጠር መቻላቸውን ተናግሯል።

‹‹የሌሎች ሀገሮችን መነሻ ስንመለከት የሚያሳየን ይሄንኑ ነው። ይህ ደግሞ አምራቹና ሸማቹን ፣በዘርፉ ያሉት ተዋናዮችን በማገናኘት አብሮ ለመስራት ያስችላል። እኛም ምርቶቻችን በምናስተዋወቅበት ጊዜ የገበያ ትስስር ከመፍጠር ባሻገር ብዙ ልምዶችን ለማግኘት ረድቶናል›› ሲል አስታውቋል።

የሕክምና መገልገያ ቁሳቁስ ሀገር ውስጥ ተመርተው ጥቅም ላይ ሲውሉ መመልከት ብዙም አልተለመደም። ከሀገር ውስጥ ምርት ይልቅ የውጭ ምርት ተመራጭ የሆነ አስተሳሰብ በሚንጸባረቅበት ሀገር እነ ቢንያም ይህን አመለካከት ሰብረው የሕክምና ቁሳቁሱን እያመረቱ ነው።

አቶ ቢንያም ‹‹ይህን አመለካከት የሰበርነው ወደ ሥራ ገብተን የሕክምና ቁሳቁስ አምርተን በሰራነው ሥራ ነው፤ ቀደም ሲል ሁላችንም የነበረን አስተሳሰብ ከውጭው የሚመጣው ከኛ የተሻለ ነው የሚል ነበር። ወደዚህ ሥራ ከገባን በኋላ ግን ሰዎች እንዲያስቡና እንዲያተኩሩ የምንፈልገው በሚመረተው ቁሳቁስ ላይ ብቻ ሳይሆን ለሀገርና ለወገን በሚያመጣው ጥቅም ላይም ነው›› ይላል።

አቶ ቢንያም እንደሚለው፤ እንደዚህ አይነት ቁሳቁስ በሀገር ውስጥ መመረታቸው ለሀገር የሚያመጡት ሌላው ጥቅም በስራው ብዙ የሰው ኃይል እንዲሳተፍ በማድረግ የሥራ እድል መፍጠር መቻላቸው ነው። የሕክምና ቁሱ 90 በመቶ ያህል እሴት ተጨምሮበት የሚሰራ በመሆኑ ቴክኖሎጂም ያመጣል። እነዚህን ጥቅሞች ማሰብ ከተቻለ የሀገር ውስጥ ምርትን ማበረታታትና መግዛት አለብን ሲል ጠቁሞ፣ በተጨማሪም የሀገር ውስጥ ምርቶች በሙሉ ዋስትና የጥገና አገልግሎት በቀላሉ ማግኘት የሚችሉበት ሁኔታ መኖሩም ሌላው ጥቅሙ መሆኑን አመልክቷል።

ቁሳቁሱ በሀገር ውስጥ መመረቱ አምራቹንና ሸማቹን በቅርበት ማገናኘትና ጥገናውን በቀላሉ ለማከናወን እንደሚያስችል የሚገልጸው ሥራ አስኪያጁ ፤ አንድ እቃ ከቻይና አሊያም ከህንድ ብናስመጣ እንደዚህ አይነት አገልግሎት ማግኘት አንችልም ሲል ይገልጻል። ከውጭ የተገዛው ቁስ አስፈላጊውን ጥገና ሳያገኝ ተበላሽቶ ይቀራል ሲልም ለአብነት ይጠቅሳል። ይህ እንዳይሆን የሀገር ውስጥ ምርትን ማበረታታት፣ መግዛትና መጠቀም ይገባል ሲልም አስገንዝቧል።

እንደ አቶ ቢኒያም ተደራጀተው ሊሰሩ የሚያስቡ ሰዎች ማድረግ ስላለባቸውም ይመክራል። እሱ እንዳለው፤ መጀመሪያ ማድረግ ያለባቸው ሥራ ወዳድ መሆን ነው። ለመስራት ማሰብ ብቻውን በቂ አይደለም። በፍቅር መስራት የሆነ ቦታ ለመድረስ ግብ አስቀምጦ መንቀሳቀስን ይጠይቃል።

በተለይ ወጣቶች ስራቸው ዛሬ ትንሽ ሊሆን ቢችልም፣ ነገ ትልቅ እንደሚሆን በማሰብ መትጋት ይኖርባቸዋል ሲል ከራሱ ተሞክሮ በመነሳት ይመክራል። ይህን ሃሳብ ይዘው ከተነሱ በርግጠኝነት እኛ ከደረስንበት ደረጃ መድረስ ይችላሉ ሲልም ያበረታታል። በመጨረሻ መልእክቱም ተስፋ መቁረጥ እንደማያስፈልግና ተባብሮ መስራት እንደሚገባም ተናግሯል።

ጦሳ ኢንጂነሪን የሕክምና መሳሪያዎች አምራች ድርጅት ማህበራዊ ኃላፊነት ከመወጣት አንጻርም በአካባቢው ለሚኖሩ አምስት አቅመ ደካሞች በየወሩ ድጋፍ እንደሚያደርግ አቶ ቢኒያም ይገልጻል።

በአማራ ክልል በጦርነቱ ለተጎዱ የሕክምና ተቋማት ድጋፍ ማድረጉን እንዲሁም በጦርነቱ የተጎዱ የሕክምና መገልገያ መሳሪያዎች የጥገና እና የእድሳት አገልግሎት መሰጠቱን ይገልጻል። ለአብነትም በደሴ ሆስፒታል በመገኘት የሕክምና መገልገያ ቁሳቁስ ድጋፍ አድርገናል። የድርጅቱ ሠራተኞች በጦርነቱ ለተጎዱ የሕክምና መገልገያ መሳሪያዎችን የጥገና እና የእድሳት አገልግሎት ሰጥተዋል ሲልም አስታውቋል።

ወርቅነሽ ደምሰው

አዲስ ዘመን ቅዳሜ ነሐሴ 4 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You