የማህበራዊ አገልግሎት አሰጣጥ ለመሻሻል፣ ለደህንነት፣ ለትምህርት፣ ለግብርናና፣ ለጤና አገልግሎት፣ በአጠቃላይ በሁሉም ዘርፍ ውጤታማ ለመሆን በቴክኖሎጂና በአዲስ የፈጠራ ሥራ መታገዝ የግድ ሆኗል፤ ያለ ቴክኖሎጂ ያለሙበት መድረስ ከባድ እየሆነ መጥቷል።
ያደጉትም ሆነ በማደግ ላይ ያሉ ሀገራት ቴክኖሎጂን በሚያስፈልጋቸው ዘርፍ እንደ አስፈላጊነቱ እየተጠቀሙ ችግሮቻቸውን እየፈቱና እድገታቸውን እያፋጠኑ ይገኛሉ። ኢትዮጵያም ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ለቴክኖሎጂ ፈጠራ ትኩረት ሰጥታ እየሰራች ትገኛለች። በኢትዮጵያ ቴክኖሎጂን በመጠቀም የግብርና፣ የጤና፣ የደህንነት፣ እና መሳል ዘርፎችን አቅም ለማሳደግ እየተሰራ እንደሚገኝ በተደጋጋሚ ይገለጻል።
ወጣት የሱፍ አብዱልሃሚድ ይባላል። ውልደቱ በመዲናችን አዲስ አበባ (መርካቶ) አካባቢ ቢሆንም ቤተሰቦቹ በሥራ ምክንያት የመኖሪያ ሠፈራቸውን በተለምዶ ካራቆሬ ተብሎ ወደሚታወቀው አካባቢ በመቀየራቸው ልጅነቱን ያሳለፈው በዛ አካባቢ ነው። ከመጀመሪያ እስከ ሁለተኛ ደረጃ ያለውን ትምህርቱን ልጅነቱን ባሰለፈበት አካባቢ በሚገኘው ረጲ የመጀመሪያና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ነው የተከታተለው።
በ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ወደ ከፍተኛ ትምህርት የሚያስገባውን ውጤት ማምጣት የቻለው ወጣት የሱፍ፤ ምንም እንኳ ውጤቱ ጥሩ ሆኖ የዩኒቨርሲቲ ምደባ ቢያገኝም ይህንን በመተው የቴክኒክና ሙያ ስልጠና ለመከታተል ተግባር እድ የቴክኒክ ኮሌጅ ገብቷል።
የከፍተኛ ትምህርት ዕድሉን በመተው ለምን የቴክኒክና ሙያ ትምህርት ለመማር እንደወሰነ ወጣት የሱፍ ሲናገር፤ ሁለት ምክንያቶችን ይጠቅሳል፤ የመጀመሪያው አሳዳጊ ወላጅ እናቱ ወደ ዩኒቨርሲቲ ቢሄድ ካላቸው የኢኮኖሚ አቅም አንፃር ”እኔን ለማስተማር ይቸገራሉ” ከሚል ሃሳብ ሲሆን በሁለተኛ ደረጃ ከልጅነቱ ጀምሮ የተለያዩ ብልሽት የገጠማቸውን የኤሌክትሮኒክስ ምርቶችን በመጠገን ገቢ ያገኝ ስለነበረ ሥራውን ጎን ለጎን እየሰራ ትምህርቱን ለመከታተልና ወላጅ እናቱን ለመደገፍ ካለው መሻት አንፃር ይህንን ውሳኔ እንደወሰነ ይናገራል። ሁለተኛ ደግሞ ለፈጠራ ሥራ የላቀ ፍላጎት ስለነበረው ነው፡፡
በተግባር ዕድ የቴክኒክ ኮሌጅ የዲፕሎማ የአውቶሞቲቪ ቴክኖሎጂ ትምህርቱን በማዕረግ በማጠናቀቅ የመምህርነት ሥራውን በዛው ኮሌጅ የጀመረው ወጣት የሱፍ፤ በትምህርት አቀባበሉ ባሳየው የላቀ አፈፃፀም የመጀመሪያ ዲግሪ የትምህርት ዕድል አግኝቶ በተለምዶ ኢትዮ ቻይና ተብሎ ከሚጠራው ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ በመጀመሪያ ዲግሪ ተመርቋል።
ወደ ቴክኖሎጂና ፈጠራ ሥራ እንዴት እንደገባ ወጣት የሱፍ ስናገር፤ ከልጅነቱ ጀምሮ ለምግብ ማብሰያ የሚያገለግሉ (ስቶቮችን) ኃይል ቆጣቢ እንዲሆን አድርጎ የተለያዩ ማሻሻያዎችን በማድረግ እየሰራ እንደሚሸጥ ተናግሮ፤ ይህ ፍላጎትና ልምዱ ሙሉ ትኩረቱን ቴክኖሎጂ ላይ እንዲያደርግ መነሻ እንደሆነው ይናገራል።
«በፈጠራ ሥራ ደረጃ የመጀመሪያ ሥራዬ የሞባይል ስልክን በመጠቀም የሠራሁት የደህንነት መቆጣጠሪያ ቴክኖሎጂ ነው›› የሚለው ወጣት የሱፍ፤ ይህ ቴክኖሎጂ ሶስት ዓይነት አማራጮችን በመጠቀም ማለትም በድምፅ፣ በምስል፤ በቪዲዮ ሰዎች የመኖሪያ ቤታቸውን፣ የንግድ ሱቃቸውን፣ የመኪናቸውን በአጠቃላይ ያላቸውን ንብረት ስልካቸውን በመጠቀም ብቻ ባሉበት ሆነው መጠበቅ እንዲችሉ የሚያደርግ ቴክኖሎጂ እንደነበር ይናገራል።
በአሁኑ ወቅት የፈጠራ ሥራውን በማጎልበት ለተለያየ አገልግሎት የሚውሉ ሰው አልባ የመሬት ድሮኖችን እያመረተ የሚገኘው ወጣት የሱፍ ወደ ድሮን ምርቶቹ እንዲገባ ምን ምክንያት እንደሆነው ሲናገር፤‹‹ ሰው አልባ ድሮኖች በአሁኑ ወቅት በተለያዩ የዓለም ክፍሎች ለተለያየ አገልግሎት ይውላሉ፤ እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ሀገራት ላይ ጥቅም ላይ እንዲውል ግን የቴክኖሎጂ አምራች ተቋማቱ ፍላጎት አነስተኛ ነበር፤ ይህንን መነሻ በማድረግ ከዛሬ ስድስት ዓመት በፊት በሀገር ውስጥ ለማምረት በመወሰን ድሮን ማምረት ጀመርኩ ››ይላል ።
የድሮን ምርቱ ዓላማ በመጀመሪያ የነበረው በተለያዩ የጦርነት ወቅቶች የተጣሉ ነገር ግን ያልፈነዱ ቦንቦችን በመለየት ሰዎች ላይ አደጋ ከማድረሳቸው በፊት በመለየት ማምከን ማስቻል ነበር የሚለው ወጣት የሱፍ፤ ነገር ግን የተለያዩ ማሻሻያዎችን በማድረግ አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ በተለየ በጦርነት ወቅት በራሳቸው በመለየት ጠላት ላይ ጥቃት መሰንዘር የሚችሉ እንዲሆኑ በማድረግ መሥራት እንደቻለ ይናገራል።
በሀገሪቱ ባለፉት ዓመታት በነበሩ ጦርነትና ግጭቶች በተጣሉና ተቀብረው በቀሩ ፈንጂዎች ከ18 ሚሊዮን በላይ ዜጎች ተጋላጭ ሆነዋል የሚለው ወጣት የሱፍ፤ አሁን ባለው ሁኔታ እነዚህን ፈንጂዎች ለማምከን የቴክኖሎጂ እጥረት ስላለ አሰሳው እየተደረገ ያለው በሰው ኃይል መሆኑን ያስረዳል፡፡ በሰው የሚደረግ ፍለጋ ደግሞ አደገኛ ነው። ከዚህ አኳያ ይህ ቴክኖሎጂ ፋይዳው ከፍተኛ ነው ይላል።
የሰራው ድሮን ካሜራ የተገጠመለት በመሆኑ ሰዎች በጨለማ እገታ ሲፈፀምባቸው አሰሳ በማድረግ ያሉበትን ቦታ ማወቅ እንዲቻል ከማድረግ በተጨማሪ የተሰራበት ወጪ በአንፃራዊነት አነስተኛ በመሆኑ እራሱን ከጠላት እይታ ሰውሮ የተሰጠውን ትዕዛዝ እንዲፈጽም ተደርጎ የተሰራ ነው ይላል።
ከዚህ ቴክኖሎጂ ጋር ተያይዞ በቅርቡ በሳይንስ ሙዚየም በተካሄደው የአቪዬሽን ቴክኖሎጂ ኢግዚብሽን ላይ የተገኙት ጠቅላይ ሚንስቴር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሥራዎቻችንን አይተው በተለይ የፈንጂ ማምከን ሥራዎችን በተመለከተ ከሀገር መከላከያ ጋር በጋራ መሥራት የሚቻልበት ሁኔታ እንዲኖር አቅጣጫ መስጠታቸውን ይናገራል።
የድሮን መጠኑን በመቀነስና በመጨመር የመተኮስና የማምከንን ሥራ እንዲሰራ ማድረግ ይቻላል የሚለው ወጣት የሱፍ፤ የወታደራዊ አገልግሎትን በተመለከተ ሌሎች ሀገራት ከደረሱበት የቴክኖሎጂ አቅም አንፃር ኢትዮጵያም በራስ አቅም ዘመናዊ መሣሪያዎችን መሥራት እንደምትችል ማሳያ የሚሆን ነው ይላል።
«ሥራዎችን በተለያዩ የቴክኖሎጂ ኤግዚቢሽኖች በማቀርብበት ጊዜ ሰዎች ቴክኖሎጂው በሀገር ውስጥ የተሰራ አይመስላቸውም» የሚለው የሱፍ፤ አንዳንድ ጊዜ በራስ አቅም የተሰራ ቴክኖሎጂ እንደሆነ ለማስረዳት ጥረት በማደርግበት ወቅት ሰሚ እንደማያገኝ ይናገራል። ይህም ‹‹ ለራሳችን ካለን ዝቅተኛ አመለካከት የመነጨ ነው» ይላል።
ወጣት የሱፍ እንደሚናገረው፤ ይህንን የድሮውን ሥራ ለመሥራት ስድስት ወር ፈጅቶበታል፡፡ ‹‹በቴክኖሎጂው ቋንቋ ኮዲንግና ፕሮግራም ማድረግ ሙሉ በሙሉ አዲስና በራስ አቅም የሚሰራ ነው። ሌሎች የሲቪል አውሮፕላን ዓይነቶች ቢሆን የተለያዩ አጋዥ ዳታዎችን ማግኘት ይቻል ነበር፤ ይህ ሥራ ግን ምንም ዓይነት አመቺ ሁኔታ ሳይኖር እራሴን ለመፈተን በማሰብ ሰርቼ እውን ያደረኩት ነው›› ይላል።
ከዚህ ቴክኖሎጂ በተጨማሪ የግብርና ሥራን ውጤታማ ለማድረግና የነዳጅ ፍጆታን በመቀነስ በንፋስና በፀሐይ ኃይል የሚሰራ የውሃ መሳቢያ ፓምፕ መስራቱን የሚናገረው ወጣት የሱፍ፤ ይህንን መሳሪያ ከተመሳሳይ ምርት አንፃር ዋጋውን እርካሽ በማድረግ ለገበያ የማቅረብ እቅድ እንዳለው ይናገራል።
በሚሰራቸው ሥራዎች ከ17 በላይ የተለያዩ የእውቅና የምስክር ወረቀቶችን እንደተቀበለ የሚናገረው ወጣት የሱፍ፤ ይህ እንዳለ ሆኖ በጅምር ላይ ያሉ የቴክኖሎጂ ፈጠራ ሥራዎችን ወደ ገበያ ለማምጣት የፋይናንስ ድጋፍ ለማግኘት ጥረት በሚያደርግበት ወቅት አብዛኛውን ጊዜ አውንታዊ ምላሽ እንደማያገኝ ይገልጻል።
በሌላ በኩል የተለያዩ የጥበቃ ደህንነት ቴክኖሎጂዎች በስፋት እያመረተ እንደሚገኝ የሚናገረው ወጣት የሱፍ፤ ሰዎች በሚፈልጉት መልኩ ንብረታቸውን መጠበቅ እንዲችሉ የሚያደርግ ቴክኖሎጂዎች መሆናቸውን ይናገራል፤ ለአብነት ወንጀለኛ በተለመደ ቴክኖሎጂ የሚጠበቅ ቤት ወይም መኪና ሲሆን የት ቦታ ጉድለቱ እንዳለ አውቆ ቴክኖሎጂውን በመለማመድ ወንጀል ይፈፅማል፤ ይህ አዲስ ቴክኖሎጂ ግን ለአንድ ተቋም ወይም ግለሰብ ብቻ ታስቦ የሚሰራ በመሆኑ ሲስተሙን ተጠቅሞ ጥቃት ማድረስ አይቻልም ይላል።
ተመሳሳይ የቴክኖሎጂ ውጤቶች ከውጭ ሀገር እንደሚገቡ የሚናገረው ወጣት የሱፍ፤ ይህ የውጭ ምንዛሬ ከማስወጣቱም ባሻገር ከሀገር ደህንነት አንፃር ትኩረት የሚሰጠው በመሆኑ ቴክኖሎጂውን በራስ አቅም በሀገር ውስጥ ለማምረት በሚደረገው ጥረት መንግሥት እገዛ ማድረግ እንደሚገባው ይናገራል።
ለአብነት የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚንስቴር የተለያዩ የፈጠራ ሥራዎችን የሰሩ ወጣቶች አወዳድሮ የእውቅና የምስክር ወረቀቶችን ይሰጣል የሚለው ወጣት የሱፍ፤ ነገር ግን ቀጣይነት ባለው መልኩ ቢያንስ በውድድር ያሸነፉ የቴክኖሎጂ ባለሙያ ወጣቶችን እውቅና ከመስጠት ባለፈ ሥራቸውን በመጀመሪያ ውጤታማ መሆን እንዲችሉ ድጋፍ ከማድረግ አኳያ ውስንነት አለ ይላል።
‹‹ኢትዮጵያ አቅም አላት፤ ብዙ መሥራት ትችላለች›› የሚለው የሱፍ፤ ነገር ግን የሚመለከታቸው አካላትና በቴክኖሎጂ ዘርፍ በተገቢው መንቀሳቀስ የሚጠበቅባቸው ተቋማት በዛ ልክ እየሰሩ እንዳልሆነ ይናገራል። ይህም ኢትዮጵያ በቴክኖሎጂ ዘርፍ በዘርፉ በቶሎ ውጤት እንዳታመጣ እንቅፋት የሚሆን በመሆኑ ችግሩን በተቻለ መጠን ለመቅረፍ ጥረት ማድረግ እንደሚገባ ይናገራል።
አሁን ያለንበት ዘመን ሁሉንም ነገር በቀላሉ በእጃችን ማግኘት የሚቻልበት የቴክኖሎጂ ዘመን በመሆኑ አንድን ነገር ለመከወን በሙሉ ልብ ከተነሱ የማይቻል ነገር እንደሌለ ይናገራል፡፡‹‹ ገንዘብ የለኝም ፤ የሚያግዘኝ ሰው የለም፤ በማለት እጃቸውን አጣጥፈው የተቀመጡ ወጣቶች አሉ፡፡ ሆኖም እነዚህ ወጣቶች ተስፋ ሳይቆርጡ በአካባቢያቸው ባለው ጸጋ ተጠቅመው እራሳቸውን ለውጤት ማብቃት ይችላሉ›› የሚል ምክር ያስተላልፋል፡፡
ቴክኖሎጂ በጥቂት የሰው ኃይልና ቦታ ትላልቅ ሥራዎች ለመሥራት ምቹ መሆኑ ዘርፉን በብዙ ተመራጭ እንደሚያደርገው የሚናገረው ወጣት የሱፍ፤ በሚመጣው ዘመን ተወዳዳሪ ሆኖ ለመገኘት ለቴክኖሎጂ ሥራና ምርምር ትልቅ ትኩረት መስጠት እንደሚያስፈልግ ይናገራል። ከዚህ አንፃር የኢትዮጵያ መንግሥት የነቃ ተሳትፎ በማድረግ ቴክኖሎጂን ከግምት በማስገባት የፖሊሲ ማሻሻያ በማድረግ ብሎም በቴክኖሎጂ ላይ ለተሰማሩ ተቋማትና ግለሰቦች አቅም በፈቀደ መጠን ሁሉ የፋይናንስ ድጋፍ በማድረግ መደገፍ እንዳለበት ያስገነዝባል።
ቴክኖሎጂ መጠቀም ሲባል ኮምፒዩተር ወይም ኤሌክትሮኒክስ ብቻ መነካካት ወይም መጠቀም ማለት አይደለም የሚለው ወጣት የሱፍ፤ ሁሉም ሰው በተሰማራበት የሥራ መስክ ላይ ቴክኖሎጂን ተጠቅሞ ቢሰራ በገበያው አሸናፊ ሆኖ እንደሚወጣ ይናገራል፡፡ በመሆኑም ወጣቱ ቴክኖሎጂ መፍጠር ባይችል እንኳን የተሰራውን ነገር በአግባቡ መጠቀም መቻል እንደሚገባው ይናገራል።
በመጨረሻም የፈጠራ ባለሙያው ወጣት የሱፍ፤ ባስተላለፈው መልዕክት በተለይ ወጣቱ መጪውን ዘመን በመረዳት፤ በዚህ የውድድር ዓለም አሸናፊ ለመሆን ምን ይፈልጋል? የወደፊቱስ ዘመን ምን ዓይነት ሊሆን ይችላል? የሚለውን በመለየት ዘመኑ ለሚፈልገው ነገር ዝግጁ መሆን አለበት ይላል።
ወጣት የሱፍ በመጨረሻ እንደሚለው አሁን ያለንበት የቴክኖሎጂ ዘመን እንደመሆኑ ዘርፉን መቀላቀል የግዴታ ውዴታ ነው። ከዚህ አኳያ ወጣቶች በዘርፉ ፍላጐት ኖሯቸው መሥራት አለባቸው፤ ነገሮች አልጋ በአልጋ ስለማይሆኑ ፈተናዎችን ተቋቁሞ ለማለፍ በሁሉም ረገድ እራሳቸውን ብቁ ማድረግ ይገባቸዋል።
ክብረአብ በላቸው
አዲስ ዘመን ዓርብ ነሐሴ 3 ቀን 2016 ዓ.ም