በስፖርት፤ በደራሲነት፣ በሙዚቃ፣ በሥዕል፣ በታሪክ፣ በሳይንስ ኪነ ጥበብና የምርምር ሥራዎችም ኢትዮጵያን በዓለም የበለጠ እንድትታወቅ ያደረጉ ትናንትናም ዛሬም ደምቀው የሚታዩ እንቁ ኢትዮጵያውያንና ኢትዮጵያውያት ብዙዎች ናቸው። ከእነዚህ የሀገር ባለውለታ ግለሰቦች መካከል ኢትዮጵያ በስፋት በምትታወቅበት የአትሌቲክስ ስፖርት በተለይ በረዥም እርቀት አትሌቲክስ በርካታ ውድድሮችን በማሸነፍ ታሪክ የሠራውና የሀገሩን ሰንደቅ ዓላማ በዓለም መድረክ ማውለብለብ የቻለው አንጋፋው አትሌት ሻምበል ማሞ ወልዴ አንዱ ነው።
ማሞ የተወለደው በ1932 ዓ.ም ላይ ከአዲስ አበባ 60 ኪ.ሜ. ርቀት ላይ አዳአ ከተማ በምትገኘው ድሪጂሌ መንደር ነበር። ከትውልድ መንደሩ ተነስቶ አዲስ አበባ ከገባ በኋላ በውትድርና የመሥራት እድል አግኝቶ በክቡር ዘበኛ በ19 ዓመቱ ተቀጠረ።
ለሁለት ዓመታት በውትድርና እየሰለጠነ ጎን ለጎን ትምህርቱን ሲከታተል ቆይቶ 21 ዓመት ሲሞላው የክቡር ዘበኛው 2ኛ ባታሊዮን በሰላም አስከባሪነት ወደ ኮሪያ ሲዘምት አብሮ ዘመተ። በክቡር ዘበኛ ወታደርነት ኮሪያ በዘመተው የሰላም አስከባሪ ጦር እና በሌሎች ሥራዎች ለ2 ዓመታት በማገልገል ልዩ ምስጋና አግኝቷል። በውትድርና ውስጥ ሆኖ ትኩረትን ወደ ስፖርቱ ማድረግ የጀመረው ከኮሪያ መልስ ነው። በተለያዩ የሀገር ውስጥ የአትሌቲክስ ውድድሮች ለመግባት የውትድርና አቋሙ ያገዘው ሲሆን በየጊዜው በሚደረጉ ብሔራዊ ሻምፒዮናዎች ይሳተፍም ነበር።
የኢትዮጵያና የሻምበል ማሞ የመጀመሪያ ኦሎምፒክ በ1956 እኤአ ላይ በአውስትራሊያዋ ሜልቦርን ከተማ የተካሄደው 16ኛው ኦሎምፒያድ ኢትዮጵያ በኦሎምፒክ መድረክ ለመጀመሪያ ጊዜ የተሳተፈችበት ነበር። በወቅቱ የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ቡድን በ8 ወንድ ኦሎምፒያኖች ብቻ የተገነባ ሲሆን በ29 ዓመቱ በእድሜ አንጋፋው የቡድኑ አባል ማሞ ነበር።
ሜልቦርን ላይ ኢትዮጵያ በታላቁ የኦሎምፒክ መድረክ ለመጀመሪያ ጊዜ ስትሳተፍ ሌሎቹ የአፍሪካ ሀገራት ጋና፤ ላይቤሪያና ደቡብ አፍሪካ ነበሩ። በዚያን ወቅት ባልተሟላ አደረጃጀት የተመሠረተው የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ በሜልቦርን ኦሎምፒክ የሚሳተፉ የኢትዮጵያ ፈርቀዳጅ ኦሎምፒያኖችን የመለመለው ከጦር ኃይልና ከተለያዩ የስፖርት ክለቦች ነበር።
የክቡር ዘበኛ ወታደርና ስፖርተኛ የሆኖ ሻምበል ማሞ በተለያዩ የሀገር ውስጥ ውድድሮች የነበረው ልዩ ብቃትና ውጤታማነት በኢትዮጵያ የመጀመሪያ የኦሎምፒክ ቡድን ሲመረጥ ብዙዎች በማራቶን ውድድር እንደሚሰለፍ ገምተው ነበር። ይሁንና የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ ማሞን የመረጠው ደግሞ በ800 ሜትር፤ በ1500 ሜትር እና በ4X400 ሜትር እንዲወዳደር ነበር። ሻምበል ማሞ ወልዴ በዚህ የኢትዮጵያ ስፖርት አዲስ ምዕራፍ በመካከለኛ እና በአጭር ርቀት ለመሳተፍ ከበቁ የመጀመሪያዎቹ የኢትዮጵያ ኦሎምፒያኖች አንዱ ለመሆን የቻለ ነበር።
ሻምበል ማሞ በዚህ የኢትዮጵያ የመጀመሪያ ኦሎምፒክ ተሳትፎው ለፍፃሜ ውድድሮች ባይበቃም በመካከለኛ ርቀት ፈር ቀዳጅ ኦሎምፒያን መሆኑ የሚጠቀስ ታሪኩ ነው። በ1960 እኤአ ላይ የጣሊያኗ ሮም ከተማ 17ኛውን ኦሎምፒያድ ስታዘጋጅ በሀገር አቀፍ ደረጃ በሩጫ የተለያዩ የውድድር መደቦች ምርጥ ከሆኑ አትሌቶች አንዱ የነበረው ማሞ ወልዴ ለሁለተኛ ጊዜ በኦሎምፒክ መድረክ ለመሳተፍ ከፍተኛ ፍላጎት ነበረው።
በክቡር ዘበኛ ከአበበ ቢቂላ ጋር በውትድርናውም በስፖርቱም የነበራቸው ጓደኝነት አነሳስቶት በኦሎምፒክ የማራቶን ውድድር መሮጥ ቢፈልግም አልሆነለትም።
ሻምበል ማሞ በሮም ኦሎምፒክ የሚሳተፍበት እድል ቢበላሽበትም ሀገሩን በሚያገለግልበት ኃላፊነት መሰማራቱ አልቀረም። የተባበሩት መንግሥታት ኮንጎ ላይ ባሰማራው የኢትዮጵያ ሰላም አስከባሪ ጦር አባል ሆኖ ለ1 ዓመት ሀገሩን በውትድርና አገልግሏል።
በሮም ኦሎምፒክ የማሞ ወልዴ የቅርብ ጓደኛ፤ አጋር ወታደር እና ስፖርተኛ አበበ ቢቂላ በማራቶን ለአፍሪካ እና ለኢትዮጵያ ፈር ቀዳጅ የሆነ ድል ማስመዝገቡ ከፍተኛ መነቃቃት ፈጥሮ ነበር። ከአበበ የኦሎምፒክ የማራቶን ታላቅ ገድል በኋላ በ1964 እኤአ ላይ የጃፓኗ ቶኪዮ ከተማ 18ኛውን ኦሎምፒያድ ስታስተናግድ ለኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ቡድን በተለያዩ የአትሌቲክስ የውድድር መደቦች በተለይም በማራቶን ከፍተኛ ልምድ ያካበተው ማሞ ወልዴ፤ ለውጤታማነት ከተጠበቁ የኢትዮጵያ ኦሎምፒያኖች አንዱ ነበር።
ሮም ላይ በ10ሺ ሜትርና በማራቶን ውድድሮች ኢትዮጵያን በመወከል እንዲወዳደር ተመርጧል። ኢትዮጵያ በታሪክ ለ3ኛ ጊዜ በተሳተፈችበት የሮም ኦሎምፒክ ማሞ ሁለተኛውን የኦሎምፒክ ተሳትፎውን በ10ሺ ሜትር አድርጎ አራተኛ ደረጃ በማግኘት የዲፕሎማ ተሸላሚ ለመሆን በቃ።
1968 እኤአ ላይ 19ኛው ኦሎምፒያድ በሜክሲኮ ሲካሄድ ከአበበ ቢቂላ በኋላ ለሜዳልያ ውጤት የኢትዮጵያ ብቸኛ ተስፋ ከፍተኛ ልምድ የነበረው ምርጥ ኦሎምፒያን በወቅቱ የመቶ አለቃ ማዕረግ የነበረው ማሞ ነበር። እንደ ቶኪዮ ኦሎምፒክ ሁሉ ሜክሲኮ ላይ በኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ቡድን የተያዘው በ10ሺ ሜትር እና በማራቶን እንዲወዳደር ነው። ውጤታማ እንደሚሆንበት ከታመነው የማራቶን ውድድር አንድ ሳምንት ቀደም ብሎ በሜክሲኮ ኦሎምፒክ በመጀመሪያ በ10ሺ ሜትር ተወዳደረ።
ኬንያዊው ናፍታሌ ቴሞ በአጨራረስ ብልጠት አሸንፎ የወርቅ ሜዳልያውን ሲወስድ ማሞ በሁለተኛ ደረጃ እንዲሁም የቱኒዚያው መሃመድ ጋሃሚ በሶስተኛ ደረጃ ውድድራቸውን በመጨረስ የብርና የነሐስ ሜዳልያዎችን ተጎናፅፈዋል። ማሞ ወልዴ በሶስተኛ የኦሎምፒክ ተሳትፎው የመጀመሪያውን የኦሎምፒክ የብር ሜዳልያ ለመጎናፀፍ የበቃው በ29፡ 27.75 በሆነ ጊዜ ርቀቱን በመሸፈን ሲሆን ይህ ውጤት ለኢትዮጵያ የረጅም ርቀት ሩጫ ፈር ቀዳጅ ሆኖ መጠቀስ ያለበት ነው።
ሻምበል ማሞ በ10ሺ ሜትር የብር ሜዳልያው ከተጎናፀፈበት ድል በኋላ ግን ከአድካሚው ውድድር እፎይ የሚልበት ጊዜ አልነበረውም፤ ከሳምንት በኋላ በማራቶን ሲወዳደር የአበበን የድል ታሪክ መድገም እንደሚኖርበት የኢትዮጵያን ክብር የማስጠበቅ ኃላፊነት የእሱ መሆኑን በወቅቱ አሰልጣኝ የነበሩት አሰልጣኝ ንጉሴ ሮባ ነገሩት። በሜክሲኮ ኦሎምፒክ በማራቶን ውድድሩ ላይ በሁለት ተከታታይ ኦሎምፒኮች ሁለት የወርቅ ሜዳልያዎችን በመጎናፀፍ የተደነቀውን አበበ ቢቂላን ለመፎካከር ከተሰለፉት የ44 ሀገራት አትሌቶች ውስጥ አንዱ ማሞ ነበር።
ሜክሲኮ ላይ ለሶስተኛ ጊዜ የኦሎምፒክ ማራቶንን እንደሚያሸንፍ የተጠበቀው አበበ ቢቂላ በህመም ውድድሩን አቋርጦ ለመውጣት ሲገደድ የኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን የመላው ዓለም የስፖርት አፍቃሪዎች ልብ በሀዘን ተሰበረ።
አበበ 20ኛው ኪሎ ሜትር ላይ ውድድሩን አቋርጦ ከመውጣቱ በፊት ከማሞ ጋር በሩጫ ላይ ያደረጉትን ምክክር አሜሪካዊው ኦሎምፒያን ኬኒ ሞር ለራነረስ ዎርልድ በፃፈው መጣጥፍ ላይ እንዲህ ይላል፦
‹‹ሉታነት ማሞ›› ሲል አበበ ተጣራ
‹‹ውድድሩን የምጨርስ አይመስለኝም።››
‹‹አንተ ግን ውድድሩን ማሸነፍ አለብህ››
‹‹አታሳፍረኝም መቼም›› አለና አበበ ቢቂላ በመጨረሻ ሩጫውን አቋረጠ ይላል።
ማሞ ግን ከአበበ ጋር ካደረጉት ምልልስ በኋላ በከፍተኛ ሞራል መሮጡን ቀጠለ። ዱካውን በመከተል ተፎካካሪ የሆነው የኬንያው ናፍታሊ ቴሞ ነበር። የመጨረሻዎቹን የማራቶን ርቀቶችን ለመጨረስ ከሜክሲኮው ኦሎምፒክ ስታድዬም አካባቢ ሲደርሱ ማሞ ፍጥነቱን ጨምሮ አፈተለከና የአሸናፊነቱን ሪባን በጠሰ። በኦሎምፒክ ማራቶን ለኢትዮጵያ ሶስተኛውን ለራሱ ደግሞ የመጀመሪያውን የወርቅ ሜዳልያ ለመጎናፀፍ በቃ።
ሜክሲኮ በ1968 እኤአ ላይ ባስተናገደችው 19ኛው ኦሎምፒያድ ላይ ሻምበል ማሞ ወልዴ በ10ሺ እና በማራቶን በተጎናፀፋቸው 1 የወርቅና በ1 የብር ሜዳልያዎች ኢትዮጵያ ከዓለም 25ኛ ደረጃ እንድታገኝ አስችሏል። በአበበ ቢቂላ በተከታታይ ሁለት ኦሎምፒክ ድል የተገኘበትን የማራቶን ውድድር ማሞ ወልዴ በድጋሚ አሸንፎ ታሪክ በመሥራት ለሶስተኛ ጊዜ በማራቶን የኢትዮጵያን ክብር አስጠበቀ።
ይህ የማሞ ጀግንነት ለኢትዮጵያውን ኩራትንና ደስታን ሲያጎናፅፋቸው በጋዜጠኛ ሰለሞን የተደረሰውን ‹‹ማራቶን ልእልቷ›› ዜማንም አዘምሯቸዋል። ማሞ አትሌቲክሱን ከአበበ ቢቂላ ቀድሞ ቢጀምርም ስኬታማ ሆኖ በጀግንነት የወጣው እሱን ተምሳሌት አድርጎ ነው።
በሜክሲኮ በተካሄደው 19ኛ ኦሎምፒያድ ላይ ባገኛቸው የብርና የወርቅ ሜዳልያዎች ማሞ ወልዴ ከንጉሳዊው ሥርዓት የሻምበልነት ማዕረግ ተሰጥቶታል። በ1972 እኤአ በጀርመን ሙኒክ ከተማ በተካሄደው 20ኛው ኦሎምፒያድ ለመጨረሻ ጊዜ ኦሎምፒክን በ40 ዓመቱ ለአራተኛ ጊዜ ለመሳተፍ የበቃው ሻምበል ማሞ ወልዴ በማራቶን ሶስተኛ በመውጣት የነሃስ ሜዳሊያ ማግኘት ችሏል።
ሻምበል ማሞ ወልዴ በሩጫ ዘመኑ ቁመቱ 170 ሴንቲሜትሮች ክብደቱ 54 ኪሎ ግራም ነበር። ዋና አሰልጣኙ ከነበሩት ከስዊድናዊው ኢስካነን በኋላ ለረጅም ጊዜያት አብረውት የሰሩት አሰልጣኝ ንጉሴ ሮባ ናቸው። በ800 ሜትር፤ በ1500 ሜትር፤ በ5ሺ እና 10ሺ ሜትር የትራክ ውድድሮች ሯጭነት ከ15 ዓመታት በላይ ያሳለፈ ቢሆንም ከፍተኛውን ስኬት ሊያገኝ የበቃው በማራቶን ነበር።
በሩጫ ዘመኑ ከ15 በላይ ዓለም አቀፍ ውድድሮችን ያሸነፈ ሲሆን በኦሎምፒክ ከተሳተፈባቸው የማራቶን ውድድሮች ባሻገር በሰሜን አሜሪካ የተለያዩ ከተሞች በሚደረጉ የጎዳና ላይ ሩጫዎችና ግማሽ ማራቶኖች፤ በቦስተን፤ በአቴንስ ማራቶኖች መሮጡንም ከሕይወት ታሪኩ ለመረዳት ተችሏል። በመላው አፍሪካ ጨዋታዎች ፈር ቀዳጅ የሆነው ማሞ ወልዴ ኢትዮጵያ በውድድሩ የተሳትፎ ታሪኳ የመጀመሪያውን ሜዳሊያ እንድታገኝ ማስቻሉ የሚጠቀስ ጉልህ ታሪኩ ሲሆን በ5,000 ሜትር የነሐስ ሜዳሊያ ሲወስድ ኢትዮጵያን በአትሌቲክስ የደረጃ ሰንጠረዥ 12ኛ፣ ላይ ባጠቃላይ ስፖርት 18ኛ ላይ ማስቀመጡ ይታወሳል።
ከንጉሳዊው ሥርዓት በኋላ የደርግ መንግሥት ስልጣን ሲይዝ፤ የክቡር ዘበኛ አባል የነበረው ሻምበል ማሞ ወልዴ ከአብዮቱ ርምጃ ሕይወቱን ያተረፈው በኦሎምፒክ ባገኛቸው የሜዳልያ ክብሮች ነበር።
ከደርግ በኋላ ኢህአዲግ የመንግሥት ስልጣንን ሲረከብ የሻምበል ማሞ ወልዴ የሕይወት ውጣውረድ ወደ አሳዛኝ ምዕራፍ ተሸጋገረ። በቀይ ሽብር ወንጀል ተከስሶ ፍርድ ቤት ቀረበ። የክሱ ሂደት ከ9 ዓመታት በላይ የፈጀ ሲሆን በተከሰሰበት ወንጀል ጥፋተኛ ተብሎ ሲፈረድበት የ6 ዓመት እስር ተወስኖ በወህኒ ቤት እንዲቆይ ተደረገ። በእስር ቤት ቆይታው ባገኘው አጋጣሚ ከወንጀል ንፁህነቱን በይፋ ሲናገር ቢቆይም የሚጠበቀውን ምህረት ሊያገኝ አልቻለም።
በኢትዮጵያውያን፤ በስፖርት ቤተሰቡና አፍቃሪዎቹ ከኦሎምፒክ ጀግንነቱ በተያያዘም እንዲፈታ ከአየአቅጣጫው ከፍተኛ ጥረት ቢያደርጉም አልተሳካላቸውም ነበር። ነገር ግን ከፍርዱ በላይ ተጨማሪ 3 ዓመታት በእስር በመቆየቱ ወዲያኑ እንዲፈታ ተወስኖ ከ9 ዓመት እስር በኋላ ነፃ መሆን ችሏል።
በመጨረሻም በትራክ፣ በሀገር አቋራጭ እና በጎዳና ላይ ውድድሮች ከአፍሪካ እስከ ዓለም አቀፍ ውድድሮች ኢትዮጵያን የወከለው ሻምበል ማሞ ወልዴ በህመም ምክንያት ከዚህ ዓለም በሞት ተለየ። ሆኖም የማሞ ወልዴ የስፖርት ውለታ ከመቃብር በላይ ሆኖ ዘላለም የሚወሳ ነው። ሰላም!
ክብረአብ በላቸው
አዲስ ዘመን ረቡዕ ነሐሴ 1 ቀን 2016 ዓ.ም