«ድንበር ተሻጋሪ በጎ ፈቃድ አገልግሎት ኢትዮጵያን እንድናውቃት አድርጎናል» በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች

የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የሰው ልጅ ምንም ዓይነት ክፍያ የማያገኝበት ይበጃል፣ ይሆናል፣ ያስደስታልና የህሊና እርካታ ያስገኛል ብሎ ያለ ምንም ቀስቃሽና ጎትጓች በእራሱ ተነሳሽነት የሚፈጸም ተግባር ነው። የበጎ ፈቃድ ሥራ ማንኛውንም ዜጋ የሚያሳትፍ ቢሆንም በዋናነት ግን ወጣቶችን በስፋት የሚመለከት ይሆናል።

ማህበራዊ ትስስርን፣ አንድነትንና ፍቅርን የበለጠ እንዲጠናከር ማድረግ ማስቻሉ ደግሞ ሌላኛው የበጎ ፈቃድ ፋይዳ ነው። መንግሥታትን ከከፍተኛ የገንዘብ ወጪ በማዳን የሀገራትን ኢኮኖሚ ማጎልበትም ከሚሰጠው ጥቅም ጋር ይደመራል። በዚህ የበጎ አድራጎት እንቅስቃሴ በበርካታ ሚሊዮን ብር ሊሰራ የማይችል ተግባር በየዓመቱ ሲከናወን ይስተዋላል፡፡

የበጎ አድራጎት ሥራ የእርስ በእርስ ትስስር አንድነት እንዲጎለብት ያደርጋል። ከዚህ በተጨማሪም የሚሰጠው ማህበራዊ መስተጋብር የጎላ ነው። በሀገር አቀፍ ደረጃ በዘንድሮው የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት የተደራሽነት አድማሱን በማስፋት 21 ሚሊየን ወጣቶች እንዲሳተፉ ዝግጅት ስለማድረጉ የገለጸው የሴቶች እና ማህበራዊ ጉዳይ ሚንስቴር በጎ ፈቃደኞቹ በ14 የሥምሪት መስኮች እንደሚሰማሩና በዚህም ከ52 ሚሊየን በላይ የኅብረተሰብ ክፍሎችን ተደራሽ ለማድረግ መታቀዱን ገልጾ ነበር።

የአረንጓዴ ዐሻራ፣ ደም ልገሳ፣ የአረጋውያንና አቅመ ደካሞች የቤት እድሳት፣ የትራፊክና የመንገድ ደኅንነት አገልግሎትና የማጠናከሪያ ትምህርት ከሚሰጡ አገልግሎቶች መካከል ተጠቃሽ ናቸው።

ጠቅላይ ሚኒስትር (ዶ/ር) ዐቢይ አሕመድ የበጎ ፈቃድ አገልግሎትን ከግንዛቤ በማስገባት በተለይ የዩኒቨርሲቲ ምሩቃን፣ ሁለተኛ ደረጃና መሰናዶ ተማሪዎች እንዲሁም የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች በዚህ መልካም ተግባር እንዲሳተፉ ጥሪ ማቅረባቸው የሚታወስ እውነታ ነው። ከዚህ ጥሪ ጋር አያይዘውም የበጎ ፈቃድ አገልግሎት እስካሁን ድረስ የሚከናወነው ወጣቶቹ በሚኖርበት አካባቢ የተወሰነ ነው፡፡

ይህ እንዳለ ሆኖ ወጣቶቹ ወደ ሌሎች አጎራባች ክልሎች በመዘዋወር እግረ መንገዳቸውን አንድነታቸውንና የባሕል ዕሴቶቻቸውን የሚያጋሩበትና የሚያጎለብቱበት ስለሆነ በዚህ ሁኔታ ቢሳተፉ መልካም ነው በማለት መልዕክት ማስተላለፋቸው ይታወሳል።

ይህንን የጠቅላይ ሚንስትሩን ሃሳብ መነሻ ያደረገው የ2016 ዓ.ም ወሰን ተሻጋሪ ወጣቶች የበጎ ፍቃድ አገልግሎት የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር አመራሮች በተገኙበት በጋሞ ዞን አርባ ምንጭ ከተማ ነበረ ጅማሮውን ያደረገው። የተለያዩ የሙያ ዘርፎችን ያካተተው የወሰን ተሻጋሪ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት “በጎነትና አብሮነት ለኢትዮጵያ ከፍታ” በሚል መሪ ሃሳብ የሁሉም ክልልና የሁለቱ ከተማ አስተዳደር ወጣቶችን ተሳታፊ ያደረገ ነው።

ወጣት ሀብታሙ ብሩክ ከዘንድሮው የክረምት ወሰን ተሻጋሪ በጎ ፈቃደኞች መካከል አንዱ ነው። የመጣውም ከደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ወላይታ ዞን ነው። በአካባቢያችን በተለያዩ የበጎ አድራጎት ሥራዎች ላይ ተሳትፎ እያደረግን የነበርን ወጣቶች ነን ወደዚህ የወሰን ተሻጋሪ በጎ ፈቃድ ሥራ የተጠራ ነው የሚለው ወጣት ሀብታሙ፤ በብዙ መልኩ ማህበረሰቡን ለመጥቀም ጥረት ያደረግንበት ነበር ይላል።

በዚህ ሂደት ውስጥ ከአስራ ሁለቱም ክልልና ከሁለቱ ከተማ አስተዳደር የተወጣጡ ወጣቶች ጋር በጋራ በመሆን ወደ ኦሮሚያ ክልል፣ ጋምቤላ ክልል፣ ሲዳማ ክልል፣ ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል፣ ደቡብ ኢትዮጵያ ክልል፣ ማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል፣ ሀረሪ ክልል፣ ሶማሌ ክልል፣ አፋር ክልል፣ ትግራይ ክልል፣ አማራ ክልል እና ድሬዳዋ ተጉዘናል የሚለው ወጣት ሀብታሙ በመጨረሻም አዲስ አበባን መዳረሻ ስለማድረጋቸው ይገልጻል።

ከዚህ በፊት በአካባቢያችን ከጓደኞቻችን ጋር እንጂ በዚህ መልኩ ከተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች ከተወጣጡ ወጣቶች ጋር የበጎ ፈቃድ ሥራ የመሥራት ዕድሉ አልነበረኝም የሚለው ወጣት ሀብታሙ፤ ይህ አጋጣሚ ኢትዮጵያን ለማወቅ እንደረዳቸው ተናግሯል።

የተለያዩ ባሕሎች፣ ወግ፣ ሥርዓት፣ አለባበስ ነበር እኛ ደግሞ ከመጣንበት አካባቢ ውጭ ያለውን የሌሎች ኢትዮጵያውያንን አኗኗር በአጠቃላይ በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች በልዩነት ውስጥ ያለውን ውበት እና አንድነት እንድናውቅ እና እንድንረዳ መልካም አጋጣሚ ፈጥሮልናል ሲል ተነግሯል።

ወጣት ሀብታሙ እንደሚለው፤ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በባህሪው ሕዝብን ከሕዝብ ጋር በጥብቅ የሚያቆራኝ እና የሚያስተሳስር ተግባር ነው። በመሆኑም በመማር ማስተማር፣ በተፈጥሮ ሀብት ጥበቃና ከተማ ግብርና፣ በደም እጦት ለሚሞቱ ለሚሰቃዩና ሕፃናትና ወላድ እናቶችን ለመታደግ የደም ልገሳ የተከናወነበት ነበረ ይላል።

“ድር ቢያብር አንበሳ ያስር” እንደሚባለው የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በመስጠት ወሰን ተሻጋሪ በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች የአቅመ ደካሞችን ቤት በመሥራትና በመጠገን ለብርድ፣ ለዝናብ፣ ለአውሬ ለመሳሰሉት አደጋዎች እንዳይጋለጡ በማድረግ በስጋት ውስጥ ለሚኖሩት እፎይታን በመስጠት ድንቅ ተግባር አከናውነዋል የሚለው ወጣት ሀብታሙ፤ ይህ ሊሆን የቻለው ደግሞ ወጣቶቹ “ሀገሬ ለእኔ ምን ሰራችልኝ ሳይሆን እኔ ለሀገሬ ምን ሰራሁላት” የሚለውን መርህ መፈክር በማድረግ ለሀገራቸው ያላቸውን ሀገራዊ ፍቅር ስለገለፁ ነው ብሏል።

ከወላይታ አካባቢ ቢመጣም ደሜን የሰጠሁት ጋምቤላ ክልል ነው የሚለው ወጣት ሀብታሙ፤ ስለዚህ የእኔ ደም ጋምቤላ ያለችውን እናት በደም ዕጥረት ከመሞት ታድጓታል፤ ይህ ማለት እንደ ሀገር አንድነታችንን ከማጉላት ባሻገር በደም የተሳሰርን ሕዝቦች መሆናችንን የሚያንፀባርቅ ነው ይላል።

«ሞት መልካም ሥራ እስከምንሰራ ድረስ አይጠብቃንም ስለዚህ መልካም ሥራ እየሰራን ሞትን እንጠብቅ» የሚለው ወጣት ሀብታሙ፤ እንዲህ እንዲል ያስገደደው ምን እንደሆነ ስናገር፤ በኢትዮጵያ ብዙ ጊዜ ሰዎች መልካምነት ለማድረግ የሆነ ደረጃ ላይ እስኪደርሱ ይጠብቃሉ መኪና፣ ቤት፣ ብር ሲኖረኝ ከነገ ዛሬ በጎ አደርጋለሁ ብለው ያስባሉ። ይህ ትክክል አይደለም፤ ስለዚህ ነገ እንደሚሞት ሰው ካለን ጥቂት ነገር በማካፈል ነው በጎ ማድረግን መጀመር ያለብን ይላል።

በተለይ የዚህ የመልካም ተግባር ባለቤት የሆኑ ወጣቶች ኖሮኝ ወይም የሆነ ደረጃ ላይ ደርሼ መልካም ሥራ እሰራለሁ ከሚል አመለካከት ወጥተው የሚያከናውነው ማህበረሰብ ተኮር የበጎ ፈቃድ አገልግሎት እንደመሆኑ ለጎዳና ተዳዳሪዎች፣ ለአረጋውያን፣ ለአቅመ ደካሞችና ለአካል ጉዳተኞች አቅማቸው በፈቀደ መጠን የተለያዩ የገቢ ማስገኛ ስልቶችን በመጠቀም እንደ ልብስ፣ ምግብና መሰል መሠረታዊ ፍላጎቶችን ከማሟላት ጀምሮ ሌሎች ድጋፎችን ማድረግ እንደሚገባው ይናገራል።

ወጣት ሀብታሙ እንደሚነገረው፤ ወጣቶች የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ከመስጠታቸው በተጨማሪ በማህበራዊ ሚዲያ ድህረ ገጾች አማካኝነት ሰላም ጠፍቶ ግጭት፣ ልማት ጠፍቶ ጥፋት፣ እድገት ሳይሆን ውድቀት እንዲነግስ ለማድረግ ብሔርን ከብሔር፣ ሃይማኖትን ከሃይማኖት በማጋጨት የራሳቸውን ትርፍ ለማጋበስ የሚውተረተሩ ኃይሎችን አደብ ሊያስገዙ ይገባል ይላል።

ከግጭት፣ ከትርምስ ኪሳራ እንጂ ትርፍ እንደሌለው በአንክሮ መምከር እና ማስተካከል እንዲሁም በመረጃዎቹ ዙሪያ እውነተኛውን ነገር በማውጣት ማጋለጥ ከወጣቱ የሚጠበቅ ተግባር ነው የሚለው ወጣት ሀብታሙ፤ የተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች ዞሬ እንደተመለከትኩት መሬት ላይ ያለው ፍቅር እና መተሳሰብ እንጂ በማህበራዊ ሚዲያ ላይ እንዳለው ጥላቻ እና ፅንፈኝነት አይደለም ብሏል።

«ከሶማሌ፣ ከአፋር በአጠቃላይ ከሀገሪቱ አራቱም ማዕዘን ከመጡ ወጣቶች ጋር የመተዋወቅ እንዲሁም ጓደኝነት የመመስረት ብሎም ባሕላቸውን የማወቅና የእኔንም የማሳወቅ ዕድል አግኝቻለሁ» የሚለው ወጣት ሀብታሙ ይህ የእርስበርስ ግንኙነትን በማጠናከር የጋራችን ለሆነችው ኢትዮጵያ አንድነት የሚኖረው ፋይዳ ትልቅ ነው ይላል።

ወጣት ሙሉቀን ታደገ ሌላኛው የወሰን ተሻጋሪ የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ተሳታፊና ከአማራ ክልል ዋግምራ ዞን ሰቆጣ ከተማ የመጣ ወጣት ነው እርሱ እንደሚናገረው፤ በሁሉም የኢትዮጵያ አካባቢዎች በመዞርበት ወቅት በጎ ተግባርን ከማድረግ ባለፈ ከሕዝቡ ጥሩ አቀባበልና ፍቅርን አግኝተናል ይላል።

በወሰን ተሻጋሪ የበጎ አድራጎት ሥራዎች ማህበረሰብን እያገለገልን ቆይተናል የሚለው ወጣት ሙሉቀን፤ በሀገሪቱ ውስጥ ከሚገኙ ከተለያዩ ብሔር ብሔረሰቦችና ክልሎች ጋር ከመጡ ወጣቶች ጋር ሥራውን እየሰራን መቆየታችን የተለያዩ ልምዶችን እንድናገኝ ብሎም የጋራ አንድነት እንድንፈጥር ረድቶናል ይላል።

ኢትዮጵያ የተለያየ ቋንቋ የሚነገርባትና የተለያየ ባህል የሚንፀባረቅበት ሀገር ናት የሚለው ወጣት ሙሉቀን፤ ከዚህ አኳያ በወሰን ተሻጋሪ በጎ ፈቃድ ሥራ ከተወለድንበት አካባቢ ወጣ ብለን ያየነው በልዩነት ውስጥ አንድነት ያላት እንደ ሕዝብ በተለያዩ ጉዳዮች አመለካከታችን የተለያየ ቢሆንም ኢትዮጵያን በተመለከተ ግን የጋራ አቋም ያለን ሕዝቦች መሆናችንን ያረጋገጥኩበት ነው ይላል።

የአቅመ ደካማ ቤቶችን በመጠገን፣ ደም በመለገስ እንዲሁም ለተቸገሩ ወገኖች ከራሳችን ኪስ በመውጣት በዝቅተኛ ኑሮ ላይ የሚገኙ ዜጎችን የመደገፍ ሥራዎችን ሰርተናል የሚለው ወጣት ሙሉቀን፤ በተለይ በደም ልገሳ ፕሮግራሙ ሁሉም ወጣቶች ተሳታፊ ሆነዋል በዚህም ኢትዮጵያውያን በደም የተሳሰርን ዜጎች መሆናችንን ደግም ማረጋገጥ ችለናል ይላል።

ወጣት ሙሉቀን እንደሚናገረው፤ ወጣቱ በሚመለከተውና በማይመለከተው ጉዳይ ተጠምዶ በማህበራዊ ሚዲያ ላይ ነው ጊዜውን እያጠፋ ይገኛል። ይህ አካሄድ ደግሞ ለራሱ ለወጣቱ ብሎም ለሀገር ጉዳት እንጂ ጥቅም ይዞ አይመጣም። ስለዚህ በማህበራዊ ሚዲያዎች የሚለቀቁና መርዘኛ የሆኑ ሃሳቦችን እየተመለከተና ለሌሎች በማጋራት ጊዜውን በከንቱ ከሚያባክን አንዲት የተቸገረች እናትን ባለው አቅም በመደገፍ የህሊና እርካታ ማግኘት ቢችል የተሻለ እንደሆነ ይናገራል።

የበጎ ፍቃድ አገልግሎት የአንድ ጊዜ ተግባር ብቻ አይደለም የሚለው ወጣት ሙሉቀን፤ ወጣቶች ወደ መጡበት አካባቢ ሲመለሱ በጎ ተግባራቸውን በስፋት ሊተገብሩ ይገባል ይላል፤ በተለይም ወጣቶች በደረሱበት ቦታ ሁሉ ስለ ሰላምና ሕዝቦች አብሮነት በመሥራት ለሀገር ግንባታ በሚረዱ ጉዳዮች ላይ በአንድነት መቆም እንደሚያስፈልግ ይናገራል።

ኢትዮጵያውያን እንደዚህ ይወዳደሉ፣ ይከባበራሉ ወይ የሚለውን በአካል የማየት አጋጣሚ መገኘቱ እንዳስደሰተው የሚናገረው ወጣት ሙሉቀን፤ ‹‹ኢትዮጵያውያን ዛሬም እንደሚዋደዱ በተግባር አይቻለሁ ከተለያየ አካባቢ ለመጣን ወጣቶች በኢትዮጵያዊነታችን ብቻ ፍቅር እና እንክብካቤ በሄድንበት አካባቢ ሁሉ አግኝተናል›› ይላል።

ሙሉቀን እንደሚለው፤ ያለችን አንድ ሀገር ናት፤ በተለይ እንደ ወጣት ቁጭ ብለን በሕዝቦች መካከል ጥላቻ እና መቃቃርን ከመስበክ ይልቅ ያለንን አቅም ለበጎ ነገር በመጠቀም ሀገራችንን ከድህነት እና ኃላቀርነት ለመላቀቅ መትጋት መቻል አለብን ይላል። በተጨማሪም መንግሥት ከሀገሪቱ ሕዝብ ከፍተኛ ድርሻ የሚይዘውን ወጣት በማስተባበር መሥራት ከቻለ ሀገሪቱን መለወጥ እንደሚቻል ይናገራል።

ሀገር ማለት ሰው እንደመሆኑ ሀገር የሚለውጥ መልካም ሃሳብ ያላቸው ግለሰቦች ሀገራቸውን ለማቅናት መንገድ ስለሚሆን በበጎ አድራጎት ላይ ንቁ ተሳታፊ መሆን አለባቸው የሚለው ሙሉቀን፤ የወጣትነት ትኩስ ጉልበት ለበጎነት ሲውል ደግሞ እንደ ሀገር ትርጉሙ ብዙ በመሆኑ በተለይ ወጣቶች በዚህ የክረምት የበጎ አድራጎት ሥራ በንቃት መሳተፍ እንደሚገባቸው ያስገነዝባል።

ክብረአብ በላቸው

አዲስ ዘመን ዓርብ ሐምሌ 26 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You