ጀርመን በአፍሪካ ቀንድ ያላት ትኩረት ዕድሎች ፣ ስጋቶችና ቀጣይ አቅጣጫዎች

መግቢያ፤

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የአፍሪካ ቀንድ የተለያዩ ዓለም አቀፍ እና ቀጠናዊ ኃያል ሀገራት (global and regional powers) ትኩረትን ይበልጥ እየሳበ ይገኛል:: ለአፍሪካ ቀንድ ተጨማሪ ትኩረት መስጠት ከጀመሩ ሀገራት መካከል አንደኛዋ ጀርመን ናት::

ጀርመን በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ እ.ኤ.አ በጁን 2023 ላይ ሾማለች:: ልዩ መልዕክተኛው ኢትዮጵያን ጨምሮ የተለያዩ ሀገራትን እንዲሁም በአፍሪካ ቀንድ ዙሪያ የሚሰሩ እንደ የኤምሬት ፖሊሲ ማዕከል (Emirates Policy Centre) ያሉትን ጎብኝተዋል፤ የአውሮፓ ህብረት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛዋ ለጀርመን ፓርላማ አባላት እ.ኤ.አ ፌብሯሪ 21፣ 2024 ማብራሪያ እንዲሰጡ ተደርጓል::

የጀርመን ጦር በአውሮፓ ህብረት ስር በሶማሊያ ባህር ዳርቻ ፀረ-ባህር ላይ ውንብድና ተሳትፎ ያደርጋል:: ከዚህ ጋር በተያያዘ እንደ ትልቅ ርምጃ ሊታይ የሚችለው በጀርመን ፓርላማ ሁለተኛ ባለ ብዙ መቀመጫ የሆነው የክርስትያን ዲሞክራቲክና ክርስቲያን ሶሻል ጥምረት (CDU/CSU) “ጠንካራ የጀርመን ተሳትፎ በአፍሪካ ቀንድና በኤደን ባህረ ሰላጤ” (A stronger German involvement in the Horn of Africa and the Gulf of Aden) በሚል ርዕስ እ.ኤ.አ በጁን 6፣ 2024 ረቂቅ የውሳኔ ሃሳብ አዘጋጅቶ ማቅረቡና ፓርላማውም ረቂቁን ከተመለከተ በኋላ ለውጭ ግንኙነት ቋሚ ኮሚቴ መምራቱ ነው::

ሰነዱ የአፍሪካ ቀንድ ከፍተኛ ጂኦ- ፖለቲካዊ እና ጂኦ-ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ያለው ቀጠና ቢሆንም በጀርመን መንግሥት በኩል “ስትራቴጂካዊ ቸልተኛነት” እንዳለ በመተቸት ይህ ሁኔታ መቀየር እንዳለበት ያስቀምጣል:: በተለይም ተጨማሪ ዲፕሎማቲክ እና ወታደራዊ ባለሙያዎችን ወደ ቀጠናው መላክ እንደሚያስፈልግ ተመላክቷል::

በአጠቃላይ በንግድ፣ ርዳታና ድጋፎች ላይ የሚያተኩረው የጀርመን-አፍሪካ ቀንድ ግንኙነት ለፀጥታና ደህንነት ጉዳዮች ከፍተኛ ትኩረት ወደ መስጠት እየተሸጋገረ መሆኑን መገንዘብ ይቻላል:: ስለዚህ ረቂቅ ውሳኔ ሃሳቡ ሆነ አጠቃላይ የጀርመን ከፍ ያለ የአፍሪካ ቀንድ ትኩረት መነሻ ምክንያቶች ምንድናቸው ? ከኢትዮጵያ አንጻር ምን ስጋቶችንና ዕድሎችን ይዟል እንዲሁም ቀጣይ ትኩረት የሚሹ ጉዳዮች ምንድናቸው ? የሚለውን መዳሰስ አስፈላጊ ነው::

መነሻ ምክንያቶች፤

ጀርመን ለአፍሪካ ቀንድ የምትሰጠው ትኩረት እንዲጨምር የሚያደርጉ ብዙ መነሻ ምክንያቶች አሏት:: ከእነዚህም መካከል በአፍሪካ ቀንድ ያለው ያለመረጋጋት ሁኔታ ተጠቃሽ ነው። በተለይም በሶማሊያ የቀጠለው አለመረጋጋትና ፀረ-አልሸባብ ዘመቻው በተፈለገው ልክ ስኬታማ ያለመሆን ፤ የሱዳን እርስ በእርስ ጦርነት ለስደተኞች ቁጥር መጨመር እንዲሁም ለሽብርተኛነትና የባህር ላይ ውንብድና መጠናከር አስተዋጽኦ ማድረግ ለጀርመንም ሆነ ለአውሮፓ የደህንነት ስጋት ይደቅናል የሚለው የመጀመሪያው ምክንያት ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል::

ከዚህ ጋር በተያያዘ መነሳት ያለበት ጉዳይ ከአውሮፓ ወጪና ገቢ ንግድ 20 ከመቶ በላይ የሚሆነው የሚዘዋወረው በአፍሪካ ቀንድ ዳርቻ የውሃ አካላት መሆኑ ነው:: ሌላኛው ምክንያት የተለያዩ ሀገራት በአፍሪካ ቀንድ ቀጥተኛና ቀጥተኛ ያልሆነ ወታደራዊ፣ ዲፕሎማሲያዊና ፖለቲካዊ ሚናቸው እየጎላ መምጣቱ ነው:: በመሆኑም ጀርመን ስትራቴጂያዊ ጥቅሟን ለማስከበርና እንደ ራሽያ፣ ቻይና፣ ቱርክ እና ኢራን ያሉ ሀገራትን ተጽዕኖ ለመቋቋም በራሷም ሆነ በአውሮፓ ህብረት ጥላ ስር እንቅስቃሴዎችን ማድረጓ ተጠባቂ ነው::

በሦስተኛነት ሊነሳ የሚችለው ምክንያት ጀርመን በአፍሪካ ቀንድ እየተስተዋሉ ካሉ ለውጦችና አዳዲስ ክስተቶች ተጠቃሚ የመሆን ፍላጎት ነው:: በዚህ ረገድ የቀጠናው ሀገራት ትላልቅና ድንበር ተሻጋሪ መሠረተ- ልማቶች እየጀመሩና እያቀዱ መሆኑ፤ በኢትዮጵያ ያለው ከፍተኛና ለብዙ ሀገራት ሊቀርብ የሚችል የታዳሽ ኃይል አቅምና ልማት፤ በሶማሌላንድ፣ በደቡብ ሱዳን እንዲሁም በኢትዮጵያ ለተለያዩ ኢንቨስትሜንቶች የተሻለ ምቹ ሁኔታ እየተፈጠረ መሆኑ ተጠቃሽ ናቸው::

በጀርመን በኩል እነዚህን ዕድሎች ከአውሮፓ ህብረት ግሎባል ጌትዋይ ኢንሼቲቭ (Global Gateway Initiative) ጋር በማስተሳሰር የማስኬድና የቻይናውን ቤልት ኤንድ ሮድ ኢንሼቲቭን (Belt and Road Ini­tiative) በአፍሪካ ቀንድ መቀናቀን የሚለው ትኩረት የተሰጠው ይመስላል::

አስቻይ ዕድሎች፤

ጀርመን ለአፍሪካ ቀንድ የምትሰጠው ትኩረት ከፍ ከማለቱ ጋር በተያያዘ ከተነሱት ስጋቶች ጎን ለጎን ዕድሎችም አሉ:: አንደኛ በልዩ መልዕክተኛው የኢትዮጵያ ጉብኝት ወቅት ሆነ በረቂቅ ሰነዱ ኢትዮጵያ ለቀጠናው ሰላም ስታበርክት የነበረውና ልታበረክት የምትችለውን አስተዋጽኦ በግልጽ ዕውቅና የተሰጠው መሆኑና በቀጣይም ሀገራችን ይህን ሚና በተሻለ እንድትወጣ ጀርመን ድጋፎችን እንደምታደርግ መመላከቱ በበጎ ጎኑ ሊነሳ የሚችል ነው::

ጀርመን ከሌሎች ምዕራባዊያን በተለየ ሁኔታ የኢትዮጵያ ወዳጅ ከሆነችው ቻይና ጋር በአፍሪካ ቀንድ ጉዳዮች አብራ መሥራት እንዳለባት መቀመጡ፤ ሀገሪቱ በአፍሪካ ቀንድ ያላትን ጂኦ-ፖለቲካዊ ፍላጎት ለማሳካት አብራ መሥራት እንዳለባት ከተለዩ አንዳንድ ሀገራት ጋር ኢትዮጵያ ጥሩ ግንኙነት ያላት መሆኑና በተለይም ከተባበሩት አረብ ኤምሬትስ (UAE) ጋር ካለን ስትራቴጂካዊ ወዳጅነት አንጻር ጀርመንን በሱዳን እና በሶማሌላንድ ላሉን ፍላጎቶች በጎናችን የምናሰልፍበት መልካም ዕድል ሊኖር ይችላል::

በሶስተኛነት ሊጠቀስ የሚችለው ጀርመን በራሷና በአውሮፓ ህብረት ስር የምታከናውናቸው እንቅስቃሴዎች ለብሔራዊ ጥቅማችን አጋዥ ሊሆኑ የሚችሉ መሆኑ ነው:: በዚህ ረገድ የግሎባል ጌትዋይ ኢንሸቲቭ አካል የሆኑ ፕሮጀክቶች በሀገራችን ውስጥም ሆነ በቀጠናው ከታቀዱ የመሠረተ- ልማት ሥራዎች ጋር ሊናበቡ የሚችሉባቸውን ሁኔታዎች በማጤን የተጠናከረውን የጀርመን ፍላጎት እንደ አንድ ዕድል መጠቀም ይቻላል:: በተጨማሪ በአፍሪካ ቀንድ ባህር ዳርቻ የባህር ላይ ውንብድናን መከላከል አንዱ የጀርመን ትኩረት ጉዳይ ተደርጎ መቀመጡ በጉዳዩ አብሮ የመሥራት ዕድል ከመስጠት ባሻገር ችግሩ በኢትዮጵያ ላይ የሚያደርሰው ኢኮኖሚያዊና የደህንነት ተጽዕኖ እንዲቀንስ የጀርመን የተጠናከረ እንቅስቃሴ የራሱን አስተዋጽኦ ሊያበረክት ይችላል::

ተጠባቂ ስጋቶች፤

ከጀርመን የጨመረ የአፍሪካ ቀንድ ትኩረት ጋር በተያያዘ ሊነሱ የሚችሉ ስጋቶች አሉ:: አንደኛ ብዙም ጠንካራ ጂኦ-ፖለቲካዊ እንቅስቃሴዎችን አድርጋ የማታውቀው ጀርመን በዚህ ደረጃ ለአፍሪካ ቀንድ ትኩረት መስጠቷ የቀጠናውን ጂኦ-ፖለቲካዊ ጠቀሜታ ከማሳየት ባሻገር በኃያላንና ሌሎች ሀገራት መካከል ፉክክር እያየለ መምጣቱን የሚያሳይ ነው:: ይህም በቀጠናው ሀገራት መካከል ከኃያላን ያለን ወዳጅነት መነሻ በማድረግ ክፍፍልን ሊያሰፋ፣ ልዩነቶች እንዲባባሱ ብሎም የቀጠናው ሀገራት ቀጥታ በማይመለከታቸው የሌሎች አጀንዳዎች እንዲሳቡ የራሱን አስተዋጽኦ ሊያበረክት ይችላል::

ሁለተኛ በተለይም በረቂቅ ሰነዱ ሩስያን እና ኢራንን በስጋትነት በመፈረጅ ሀገራቱ በቀጠናው ያላቸውን እንቅስቃሴ መቃወም ከዋነኛ የጀርመን የአፍሪካ ቀንድ ትኩረቶቹ አንዱ መሆን እንዳለበት መቀመጡ እነዚህ ሁለቱ ሀገራት አፀፋዊ ርምጃ እንዲወስዱ በማድረግ የኢትዮጵያን ጥቅም ሊጎዳ ይችላል:: ለምሳሌ ሩስያ ለሱዳን ጦር ድጋፎችን ብታጠናክር እና በፖርት ሱዳን አካባቢ ጦር ሰፈር ብትገነባ፣ በተመሳሳይ ሁለቱ ሀገራት ለኤርትራ ወታደራዊና ሌሎች ድጋፎች ካጠናከሩ በቀጥታና በተዘዋዋሪ ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅም ሊደቅን ይችላል::

በሶስተኛነት ሊነሳ የሚችለው ከቀጣይ ትብብርና ዲፕሎማሲ አንጻር ከጀርመን ጋር ያለው ግንኙነት ክፍተቶች ሊፈጠሩ የሚችሉበት አዝማሚያ መኖሩ ነው:: ለምሳሌ በረቂቅ ሰነዱ የሶማሊያን መንግሥት ማጠናከርና አብሮ መሥራት እንደ አንድ ጉዳይ የተቀመጠ ሲሆን ይህም አሁን ካለው ቀጠናዊ ሁኔታ አንጻር ለፕሬዚዳንት ሀሰን ሼክ የፀረ ኢትዮጵያና ሶማሌላንድ እንቅስቃሴ ተጨማሪ ፖለቲካዊና ዲፕሎማሲያዊ አቅም ሊሆን ይችላል:: በተጨማሪ ረቂቅ ሰነዱ የልማት ትብብርና ድጋፎችን ከጂኦ-ፖለቲካዊ ፍላጎት ጋር ማስተሳሰር እንደሚያስፈልግ ማስመሩ ኢትዮጵያ ከጀርመን ጋር ያላትን ትብብር ሊያወሳስብ፣ አንዳንድ ድጋፎች እንዲቀንሱ ሊያደርግ የሚችል መሆኑ ተጠቃሽ ነው::

መፍትሔዎች፤

ከሚታዩ ስጋቶች እንዲሁም ከመፃኢ ዕድሎች አንጻር ኢትዮጵያ ምን ማድረግ አለባት የሚለው ቁልፍ ጥያቄ ነው:: በመሆኑም እየጨመረ ከመጣው የጀርመን የአፍሪካ ቀንድ ትኩረት አንጻር የስጋቶችን ተጽዕኖ ለመቀነስ እንዲሁም ዕድሎችን በተሻለ ለመጠቀም በኢትዮጵያ በኩል የተለያዩ ተግባራት መከናወን እንዳለባቸው ማስቀመጥ ይቻላል::

አንደኛ በቀጣናው የኢትዮጵያን ስትራቴጂካዊ ተፈላጊነት ይበልጥ የሚጨምረውንና ከሶማሌላንድ ጋር የተደረሰውን የመግባቢያ ስምምነት ወደ ተግባር ማሸጋገርና ለሶማሌላንድ የአጋርነት ዕውቅና በመስጠት ጭምር ተግባራዊ እንቅስቃሴዎችን መጀመር (ለምሳሌ ባህር ኃይላችንን ማስፈር) ቀዳሚ ርምጃ ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል:: በዚህም ሶማሌላንድ ከሌሎች የተሻለ ቁመናና እምቅ አቅም ያላት ብሎም ለጀርመን ሆነ ለአውሮፓ ህብረት አስተማማኝ ወዳጅና አጋር ልትሆን የምትችል እንደሆነች እንዲሁም ኢትዮጵያ ባህር ዳርቻውን ጨምሮ የቀጠናውን ሰላምና ደህንነት ይበልጥ ለማረጋገጥ አቅሙም ዝግጅነቱም ያላት መሆኑን ማጉላት ይቻላል::

ሁለተኛ ከጀርመን ጋር ያለንን ፖለቲካዊና ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ይበልጥ ማጠናከር ያስፈልጋል:: ለምሳሌ በመሪዎች ደረጃ ኢትዮጵያ የጀርመንን ጂኦ- ፖለቲካዊ ፍላጎት እንደምትረዳና በጋራ ጉዳዮች አብሮ ለመሥራት ሙሉ ዝግጁነት እንዳለ ማሳወቅ፣ ኢትዮጵያ ለቀጠናው የምታበረክተውን እንደ ስኬታማ ፀረ-ሽብር ሥራዎቻችን ያሉ ተግባራትን አጉልቶ ማስረዳት፣ ቁልፍ ሀገራዊ ተቋማት (በተለይም ፌዴራል ፖሊስ፣ ብሔራዊ መረጃ፣ መከላከያ) ከጀርመን አቻዎቻቸው በጋራ ጉዳዮች ዙሪያ የትብብር ዕድሎችን መቃኘት እንዲጀምሩና እንዲያጠናክሩ ማድረግ፤ ቀጠናዊ ስትራቴጂያችንን (ማለትም ኢጋድን በተመለከተ፣ ድንበር ተሻጋሪ መሠረተ-ልማቶችን በተመለከተ፣ ቀጠናዊ ሰላምና ደህንነትን በተመለከተ ያለንን ስትራቴጂ) ይበልጥ አጉልቶ ማሳወቅ በዲፕሎማሲ ረገድ ትኩረት ሊደረግባቸው የሚገቡ ጉዳዮች ናቸው::

በአጠቃላይ ጀርመን ለአፍሪካ ቀንድ የምትሰጠው ትኩረት ቀጣናውም ሆነ የዓለም ሁኔታ እየተለዋወጠ መምጣት ጋር የተገናኘ ሲሆን ሁኔታው ይዟቸው የሚመጣቸውን ስጋቶች ለመቀነስና ዕድሎችን ደግሞ ለመጠቀም የተጠናከረና የተቀናጀ ሥራ መሥራት ያስፈልጋል:: ለዚህም መነሻ ግብዓት የሚሆኑ ብዙ መደላድሎች ያሉ መሆኑ ሊጠቀስ ይገባል::

በፍቃዱ ቦጋለ (ከኢ.ፌ.ዴ.ሪ የውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት)

አዲስ ዘመን ሰኞ ሐምሌ 22 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You