ያገሩን ሰርዶ ባገሩ በሬ- የሕክምና ቁሳቁስን በሀገር ውስጥ ማምረት

ኢትዮጵያ ለጤናው ዘርፍ ትኩረት እንደመስጠቷ ለዘርፉ ለሚያስፈልጉ መድኃኒቶችና ሕክምና ነክ ቁሳቁስ አቅርቦትም እንዲሁ በትኩረት ትሰራለች። መድኃኒቶችንና የሕክምና ቁሳቁስን በሀገር ውስጥ ለማምረት እየተሠራ ቢሆንም፣ በሀገሪቱ ያለውን ፍላጎት በሀገር ውስጥ ምርት መሸፈን እንደማይቻል ታውቆ፣ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ በመመደብ መድኃኒቶችና የሕክምና ቁሳቁስ ከውጭ እንዲገቡ እየተደረገ ነው።

መንግሥት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ለተለያዩ አገልግሎቶች የሚውሉ የገቢ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ምርት ለመተካት በያዘው አቅጣጫ መሠረት ደግሞ ከውጭ የሚመጡ መድኃኒቶችንና የሕክምና ቁሳቁስን በሀገር ውስጥ ለማምረት ጥረት እየተደረገ ነው።

በዚህም መድኃኒትና መድኃኒት ነክ ቁሳቁስ ለሚያመርቱ ባለሀብቶች ምቹ ሁኔታ በመፍጠር እየሠራ ይገኛል። ባለሀብቶችም ይህን ምቹ ሁኔታ በመጠቀም መድኃኒት ፋብሪካዎችን እየገነቡ፣ ለመድኃኒት ፋብሪካ በሚል በተገነባው የቂሊንጦ ኢንዱስትሪ ፓርክ በመግባት ፋብሪካቸውን እየገነቡ መድኃኒት ወደ ማምረት የገቡበት ሁኔታ ይታያል።

የዛሬው የስኬት እንግዳችንም ከእነዚህ ባለሀብቶች መካከል ይጠቅሳሉ፤ በድሬዳዋ ከተማ በገነቡት ፋብሪካቸው በሀገር ውስጥ እየተመረቱ ካሉ የሕክምና መገልገያ ቁሳቁስ መካከል የሆኑትን ስሪንጅ፣ ለላቦራቶሪያ አገልግሎት የሚውሉ ብልቃጦችንና የግሉኮስ ገመድና የመሳሰሉትን ያመርታሉ።

ፋብሪካቸው ‹‹ሀሴት ሜዲቴክ›› ይባላል። በሀገሪቱ የሚታየውን የስሪንጅ እጥረት ለማቃለልና ከውጭ የሚገባውን ስሪንጅ ሙሉ በሙሉ ሀገር ውስጥ ለማምረት አለፍ ሲልም ምርቶቹን ወደ ጎረቤት ሀገራት በመላክ የውጭ ምንዛሪ ግኝትን ከፍ ለማድረግ አልሞ እየሠራ ይገኛል።

የሀሴት ሜዲቴክ መስራችና ባለቤት አቶ ሲሳይ በቀለ ድሬዳዋ ከተማ ነው ተወልደው ያደጉት። የአንደኛና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን የተከታተሉትም በዚህችው ከተማ ነው።

የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ባጠናቀቁ ማግስትም ከሀገራቸው ወጥተው አስር ዓመታትን በስደት አሳልፈዋል። የስደት ኑሯቸውን በዳላስ ቴክሳስ በማድረግ ያገኙትን ሥራ ሁሉ ሰርተዋል። ይሁንና ‹‹የሰው ወርቅ አያደምቅ›› በማለት ከአስር ዓመት የስደት ቆይታ በኋላ ጓዛቸውን ጠቅልለው ወደ እናት ሀገራቸው ተመልሰው በትውልድ መንደራቸው ለመሥራት ይወስናሉ።

በሀገር ቤት በተለያዩ ኢንቨስትመንቶች ለመሰማራት ሲወስኑም፣ በዋናነት ትኩረት ያደረጉት በውጭ ምንዛሪ ወደ ሀገር ውስጥ በሚገቡ ምርቶች ላይ ነው። ከእነዚህ ምርቶች መካከልም ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ የሚጠይቀውን እንዲሁም ብዙ ልፋት፣ ድካምና ከፍተኛ ጥንቃቄ የሚያሻውን የሕክምና ዘርፍ ምርጫቸው በማድረግ ወደ ሥራው ገቡ። በአሁኑ ወቅትም ድርጅቱ ‹‹የሀገሩን ሰርዶ በሀገሩ በሬ›› እንዲሉ የሕክምና መገልገያ ቁሳቁስን በተለይም ስሪንጅ፣ ቲዩብና ካፖችን ያመርታል።

በሀገሪቷ ያለውን የሕክምና መገልገያ ግብዓቶች እጥረት በማጥናት ወደ ሥራው የገቡት አቶ ሲሳይ፤ ፋብሪካውን ድሬዳዋ ከተማ ላይ የገነቡት በተለያዩ ምክንያቶች መሆኑን ይገልጻሉ። እሳቸው እንዳሉት፤ ፋብሪካውን በትውልድ ቦታቸው ድሬዳዋ ከተማ ላይ የመገንባታቸው ዋናው ምክንያት ድሬዳዋ እትብታቸው የተቀበረበት፣ የተማሩበትና ክፉ ደግ ያዩበት እንደመሆኑ ማህበረሰቡ ውስጥ ገብተው ሕዝቡን ማገልገል መቻላቸው ትልቅ ትርጉም ያለውና ውስጣዊ ፍላጎታቸው ስለሆነ ነው። ሁለተኛውና ዋነኛው ምክንያታቸው ደግሞ ምርቶቻቸውን ከሀገር ውስጥ ባለፈ ለጎረቤት ሀገራት ጭምር ማቅረብን ታሳቢ በማድረጋቸው ነው። ድሬዳዋን ለጎረቤት ሀገራት በተለይም ለሶማሊያና ለጅቡቲ ቅርብ በመሆኗ ምርቶችን ኤክስፖርት ለማድረግ ቀልጣፋና ምቹ በመሆኗ ጭምር ነው ምርጫቸው ያደረጓት።

ሀሴት ሜዲቴክ የተለያዩ የሕክምና አገልግሎት መስጫ ቁሳቁሶችን ለማምረት ታቅዶ የተገነባ ሲሆን፤ ፋብሪካው ደረጃውን በጠበቀ መንገድ በከፍተኛ ጥራትና በትልቅ አቅም የተገነባ ነው። በመሆኑም በአሁኑ ወቅት የኢንሱሊን ስሪንጆችን ጨምሮ የተለያየ ዓይነት ስሪንጆችን እያመረተ ይገኛል። በተጨማሪም ለላቦራቶሪ ምርመራ ሽንት፣ ሰገራና ደም ለመስጠት የሚያገለግል ቁስ (ዩሪን ካፕ) ያመርታል።

የሕክምና መገልገያ ቁሳቁሱ ማሟላት የሚገባቸውን የሕክምና ደረጃ ያሟሉ ስለመሆናቸው የገለጹት አቶ ሲሳይ፤ ፋብሪካው ከፍተኛ ወጪ የወጣበትና ደረጃውን የጠበቀ እንደሆነ አንስተዋል። የሕክምና መገልገያ ቁሳቁሱ ከዚህ ቀደም በከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ወደ ሀገር ውስጥ ይገቡ የነበሩ በመሆናቸው በአሁኑ ወቅት በሀገር ውስጥ መመረት መቻላቸው ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ እንዳለውም ነው የተናገሩት። በዋናነት የሕክምና ተቋማት መገልገያ ቁሳቁሱን በቀላሉ ማግኘት የሚያስችል ሲሆን፤ ከውጭ የሚገባውን ምርትም በሀገር ውስጥ በመተካት የውጭ ምንዛሪን በማዳን የሚኖረው አበርክቶ እጅግ የላቀ ነው ብለዋል።

ሀሴት ሜዲቴክ ትልቅ አቅም ያለው ፋብሪካ ቢሆንም፣ አሁን ላይ በመጀመሪያው ዙር የምርት ደረጃ ስሪንጆችን እና የላቦራቶሪ ውጤት መስጫ ቁሳቁስን በጥራት እያመረተ ይገኛል። በቀጣይም በሙሉ አቅሙ ማምረት ሲጀምር የተለያዩ የሕክምና ግብዓቶችን በማምረት በዘርፉ የሚስተዋለውን የግብዓት እጥረት ይቀርፋል ያሉት አቶ ሲሳይ፤ ፋብሪካው ስሪንጆችን በተለይም ሀገር ውስጥ በስፋት የሚፈለጉትን ባለአንድ ሚሊ ሊትር የኢንሱሊን ስሪንጆችን ጨምሮ ባለአንድ፣ ባለሶስት፣ ባለአምስትና ባለአስር ሚሊ ሌትር ስሪንጆችን እያመረተ መሆኑን አብራርተዋል።

ምርቶቹን ወደ ገበያ ለማውጣት የመንግሥትን ፈቃድ እየጠበቀ ያለው ባለሀብቱ፣ በአሁኑ ወቅት አስፈላጊ የሆኑ ሂደቶችን በሙሉ ማለፉንም አስታውቀዋል። በመሆኑም በቀጣይ መንግሥት በሚሰጠው አቅጣጫ መሠረት በቅድሚያ በሀገሪቱ ያለውን ፍላጎት ከግምት በማስገባት ምርቶቹን በሀገር ውስጥ ለሚገኙ የሕክምና ተቋማት ተደራሽ ያደርጋል ብለዋል። በሀገር ውስጥ ያለውን የስሪንጅ ፍላጎት በግማሽ ያህል የመሸፈን አቅም ያለው ሀሴት ሜዲቴክ፤ በቀጣይም አቅሙን በማሳደግ ሙሉ ለሙሉ ለመሸፈን እንዲሁም ከሀገር ውስጥ ባለፈ ለጎረቤት ሀገራት ተደራሽ የማድረግ ራዕይ ሰንቆ እየሰራ ነው።

እሳቸው እንዳሉት፤ ከሀገር ውስጥ ፍላጎት ባለፈ አቅሙን በማሳደግ ምርቶቹን ለጎረቤት ሀገራት በመላክ ሀገራዊ የውጭ ምንዛሪ ግኝትን ከፍ በማድረግ ጉልህ ሚና ይኖረዋል። ለዚህም ገና ከመነሻው ምርቱን የመግዛት ፍላጎት ያላቸው ጎረቤት ሀገራት ተገኝተዋል። ጥያቄ ካቀረቡ ጎረቤት ሀገራት መካከል ደቡብ ሱዳን፣ ጅቡቲ፣ ሱማሊያና ኬንያ ይጠቀሳሉ። ኮንጎን ጨምሮ የተለያዩ አፍሪካ ሀገራትም ፍላጎት ያሳዩ መሆናቸውን ጠቅሰው፣ ለእዚህም ምርትን በብዛትና በጥራት ማምረት እንደሚገባ አመላክተዋል።

ሀሴት ሜዲቴክ በዌብሳይት ያደረገው የማስተዋወቅ ሥራ ሀገራቱ ፍላጎቱ እንዲያድርባቸው ያደረገ አንዱ ምክንያት መሆኑን አመልክተው፣ የፋብሪካውን ማሽኖችን የሸጡላቸው ሀገራት ደንበኞቻቸው የነበሩ የአፍሪካ ሀገራትን ወደ ጎረቤታቸው ኢትዮጵያ ፊታቸውን ቢያዞሩ የተሻለ እንደሚሆን እየመከሩ እንደሆነና ይህም ጥሩ አጋጣሚ ስለመሆኑ አስረድተዋል።

መነሻ ካፒታሉን 420 ሚሊዮን ብር ያደረገውና ከአራት ዓመት በፊት የተመሰረተው ሀሴት ሜዲቴክ በተለያዩ ውጫዊና ውስጣዊ ምክንያቶች በቶሎ ወደ ሥራ መግባት እንዳልቻለ ያነሱት አቶ ሲሳይ፤ ዓለም አቀፍ ወረርሽኝ የነበረው ኮቪድ 19 እና በሀገር ውስጥ የነበሩ ግጭቶች ጭምር እንቅፋት ሆነውበት እንደነበር አስታውሰዋል። በአሁኑ ወቅት ግን ማምረት መጀመሩን አስታውቀዋል።

ሕክምና ላይ መሥራት የተለየ ውስጣዊ ሰላምና እረፍት የሚሰጥ መሆኑን በመጥቀስ፤ ሥራውን በጉጉት እንደጀመሩ አስረድተዋል። እሳቸው እንዳሉት፤ ከሥራው ከሚገኘው ገቢ በበለጠ ለመንፈስ የሚሰጠው እርካታ በብዙ እጥፍ ይበልጣል። ሕክምና እንደማንኛውም ንግድ በመሸጥ፣ በመለወጥና በመግዛት በቀላሉ ገቢ የሚገኝበት አይደለም። ከዛ ይልቅ ብዙ ትርፍ የማይገኝበትና ቢገኝም ትርፉ ከብዙ ቆይታ በኋላ የሚገኝ ነው። ትልቁ ትርፉ ሥራው የሚሰጠው የመንፈስ እርካታ ነው። ለሰዎች መፍትሔ መሆን መቻል ከሁሉም በላይ የሚያስደስትና የመንፈስ እርካታን ያጎናጽፋል። ብዙዎች ወደ ዘርፉ ሲገቡ የማይታዩትም በዚሁ ምክንያት ነው። ወደ ሕክምናው ዘርፍ የሚገቡት መንፈሳዊ እርካታን የሚሹ ጥቂቶች ብቻ ናቸው።

ይሁንና እንደዚህ ዓይነት ረጅም ጊዜን የሚፈጁ፣ ብዙ ድካምና ወጪን የሚጠይቁና ግን ደግሞ ማህበረሰብን በብዙ የሚጠቅሙ ቢዝነሶች ፋይዳቸው ሀገራዊ በመሆኑ ለትውልድ የሚተርፍ ስም ይኖረዋል የሚሉት አቶ ሲሳይ፤ አሁን ላይ ኢትዮጵያ ውስጥ እየተለመደ የመጣው ቢዝነስ በአጭር ጊዜ ገቢ ማምጣት የሚችልና ዘላቂና ሀገራዊ ፋይዳቸው እምብዛም የሆኑ ቢዝነሶች እንደሆኑ መታዘብ ችያለሁ ይላሉ። እርሳቸው ግን ከልጅነት ጀምሮ የነበራቸው ራዕይ ለሀገርና ለትውልድ የሚተርፍ ሥራ መሥራት መሆኑን አመልክተው፣ ረጅም ጊዜ የሚፈልግ፣ ብዙ ድካም የሚጠይቀውን ግን ደግሞ ለትውልድና ለሀገር የሚተርፈው የሕክምና ሥራ መሆኑን ተረድተው ምርጫቸው አድርገውታል።

አቶ ሲሳይ እንዳሉት፤ ኢንቨስትመንትን ከማበረታታት አንፃር ድሬዳዋ ከተማ ላይ የተሻለ የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ አለ፤ ከተማ አስተዳደሩ ድሬዳዋን ለማሳደግ በተለያየ መንገድ እየሰራ ይገኛል። ከሚሰራቸው ሥራዎች መካከልም የድሬዳዋ ተወላጅ ዲያስፖራዎች ወደ ሀገር ቤት ገብተው ኢንቨስት ማድረግ እንዲችሉ ጥሪ ማቅረብና ምቹ ሁኔታ መፍጠር አንዱ ነው። በመሆኑም በርካቶች ወደ ሀገራቸው መግባት እንደቻሉና ከገቡት መካከልም እርሳቸው አንዱ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።

‹‹ድሬዳዋ ድንበር ላይ ያለች ከተማ በመሆኗ ለኢንቨስትመንት ምቹ ናት›› ያሉት አቶ ሲሳይ፤ በዋናነት የባቡርና የመኪና ትራንስፖርት ያለባትና ለጅቡቲና ለሶማሊያ ቅርብ መሆኗ በራሱ ለኢንቨስትመንት አመቺነቷን ያሳያል ይላሉ። ሌላው ድሬዳዋ የብዙ ብሔር ብሔረሰቦች መገኛ በመሆኗ ማህበረሰቡ በሰላምና በፍቅር ተሳስቦ የሚኖርባትና የክልሉ መንግሥት ከሕዝቡ ጋር ተባብሮ የሚሰራ መሆኑን በመግለጽ ከተማዋ ለኢንቨስትመት አመቺ መሆኗን አስረድተዋል።

አቶ ሲሳይ እንዳስታወቁት፤ ፋብሪካው በስድስት ሺ ካሬ ሜትር ስፋት ባለው ቦታ ላይ ነው የተገነባው። ከፍተኛ አቅም ያላቸውን ማሽኖችን የያዘ ፋብሪካ ነው። ለአብነትም አንዱ ማሽን ብቻ 200 ቶን ያህል ክብደት አለው። ይህ ትልቅ አቅም በቀን እስከ ሰባት መቶ ሺ ስሪንጆችን ማምረት ያስችላል። ይሁንና ማሽነሪዎቹ ከዚህ የበለጠ የማምረት አቅም ያላቸው በመሆናቸው በቀጣይም ሞልዶቹን ብቻ በመቀያየር አሁን ካለው የማምረት አቅም በብዙ እጥፍ ምርትን ማሳደግ ይቻላል።

በቀን ለስምንት ሰዓታት ብቻ እያመረተ ያለው ፋብሪካው፣ ሥራውን የጀመረው 64 ለሚደርሱ ዜጎች የሥራ ዕድል በመፍጠር ነው። ፋብሪካው በቀጣይ በሙሉ ሰዓት ማምረት ሲጀምር 200 ለሚደርሱ የአካባቢው ነዋሪዎች ቋሚ የሥራ ዕድል የሚፈጥር ይሆናል።

አሁን ላይ በሙሉ አቅም ማምረት ያልተቻለው ጥሬ ዕቃዎቹ በሚፈለገው መጠን ወደ ሀገር ውስጥ መግባት ባለመቻላቸው ሲሆን፤ በቅርቡም ጥሬ ዕቃውን በስፋት በማምጣት በሙሉ አቅሙ ማምረት የሚችል ይሆናል። እንዲያም ሆኖ ፋብሪካው ከሀገር ውስጥ ባለፈ ምርቶቹን ለጎረቤት ሀገራት የማቅረብ ዕቅድ ያለው በመሆኑ ማስፋፊያ ሥራ ይጠበቅበታል።

ለዚህም ከተማ አስተዳደሩ ማስፋፊያ ቦታ ለመስጠት ፈቃደኛ መሆኑን የገለጹት አቶ ሲሳይ፤ የማስፋፊያ ቦታው ሲፈቀድ ከዚህ በበለጠ አቅሙን አሳድጎ እንደሚያመርት ያስረዳሉ። ‹‹የሕክምና መገልገያ ቁሳቁስ ከፍተኛ ጥንቃቄ የሚያስፈልገውና ደረጃውን በጠበቀ መንገድ መቀመጥ አለበት። ለዚህም ጥሬ ዕቃውንም ሆነ ምርቶቹን በጥንቃቄ ማስቀመጥ የሚያስችል በቂ ቦታ ያስፈልጋል። ስለዚህ ማስፋፊያ ቦታ ያስፈልጋል›› በማለት ገልጸዋል። አሁን ፋብሪካው ካረፈበት ቦታ ውጭ ጥሬ እቃ ማከማቻና ያለቀላቸው ምርቶች የሚቀመጡበት ቦታ እጥረት መኖሩን ጠቅሰው፤ ከተማ አስተዳደሩ ችግሩን በሂደት መፍታት እንደሚችል ያላቸውን ዕምነት ገልጸዋል።

‹‹ስሪንጆቹን ለማምረት አብዛኛው ጥሬ ዕቃ ከውጭ የሚገባ ቢሆንም፤ ያለቀለት ምርት ከማስገባት ጥሬ ዕቃውን አምጥቶ ስሪንጆቹን ማምረት የተሻለ ነው›› የሚሉት አቶ ሲሳይ፤ ስሪንጁ በሀገር ውስጥ መመረት መቻሉ 30 በመቶ ያህል ወጪን እንደሚቀንስም አስታውቀዋል። ያለቀለት ምርት ወደ ሀገር ውስጥ ሲገባ የመጓጓዣው ወጪና ሌሎች ተያያዥ ወጪዎች እንደሚኖሩ አመልክተው፣ መጠነኛ የሆነ ጥሬ እቃ በማምጣት ዋናውን ምርት በሀገር ውስጥ ማምረት የሥራ ዕድል ከመፍጠር ጀምሮ በርካታ ጠቀሜታዎች አሉት ብለዋል።

መንግሥት ለአምራች ኢንዱስትሪው በሰጠው ትኩረት አምራቾች እየተበረታቱ እንደሆነ ያነሱት አቶ ሲሳይ፤ አብዛኞቹ አምራች ኢንዱስትሪዎች ተመጋጋቢ ሥራ እንደሚሰሩም ተናግረዋል። የተለያዩ መድረኮችን በመፍጠር እርስ በእርስ እንዲተዋወቁና የልምድ ልውውጥ እንዲሁም የገበያ ትስስር እንዲፈጥሩ መሥራት ተገቢ መሆኑን ይገልፃሉ። በተለይም የዕውቀት ሽግግር በማድረግ እንደ ሀገር በየዘርፉ ለባለሙያዎች ስልጠና በመስጠት ባለሙያዎችን ማብቃት ተገቢ እንደሆነ በጽኑ ያምናሉ።

ሀሴት ሜዲቴክ ትልቅ አቅም ያለው ፋብሪካ መሆኑን አመልክተው፣ አሁን እያመረተ ካለው ምርት በተጨማሪ በቀጣይ በዋናነት ከሚያመርተው ስሪንጅ ጋር ተያያዥ የሆነውን የግሉኮስ ገመድ በቀላሉ በማምረት ለግሉኮስ አምራቾች በተመጣጣኝ ዋጋ በቀላሉ ለማቅረብ ዝግጁ ነው ብለዋል። ከዚህ በተጨማሪም ለዲያሌሲስ አገልግሎት የሚውል ቲዩብ ከውጭ እንደሚመጣ ጠቅሰው፣ ይህንንም በሀገር ውስጥ ለማምረት ዕቅድ እንዳለ ተናግረዋል።

ማህበራዊ ኃላፊነትን ከመወጣት አንጻር በትውልድ ከተማቸው ድሬዳዋ ላይ በርካታ ተሳትፎዎችን እያደረጉ እንደሆነ የገለጹት አቶ ሲሳይ፤ ሕክምና ላይ መሥራት በራሱ ትልቁ ማህበራዊ ተሳትፎ እንደሆነ ነው ያስረዱት። ያም ሆኖ በተለያዩ ሀገራዊ ጥሪዎች ምላሽ በመስጠት አጋርነታቸውን እንደሚያሳዩም አስታውቀዋል።

ፍሬሕይወት አወቀ

አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሐምሌ 20 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You