ሲሞንፒየትሮ ሳሊኒ ፤-የኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ልጅ

የኢትዮጵያ ታሪክ በአብዛኛው የጀግንነት ታሪክ ነው፡፡ እጄን ለነጭ ወራሪ ለጠላት አሳልፌ አልሰጥም ብለው እራሳቸውን ከሰውት አጼ ቴዎድሮስ እስከ ዘመናዊ የዲፕሎማሲ መሳሪያ እስከታጠቁት ድረስ በርካታ ታሪኮች ተፈፅመዋል። እነዚህንም በርካታ ምሁራንና ጸሐፍት እንዲሁም ፖለቲከኞች ሲያወድሷቸውና ሲዘክሯቸው ዘመናትን አስቆጥረዋል።

ለዚህ ክብር እንድንበቃ ያደረጉን እትብታቸው በኢትዮጵያ ምድር የተቀበረ በሥጋ በደም ኢትዮጵያዊያን የሆኑት ብቻ አይደሉም። ከአፈሯ ሳይወለዱ ከሩቅ ሀገር ባህር ተሻግረው ለኢትዮጵያ ነፃነት የተዋደቁላት ልበ ኢትዮጵያውያኖችም ብዙ ናቸው።

በሌላ በኩል ሀገሪቱ ለዘመናት ሰቅዞ ከያዛት ድህነት ተላቃ የበለፀገች ሆኖ እንድትወጣ በሙያቸውና በእውቀታቸው ከጎኗ የቆሙ የችግር ጊዜ ደራሽ ባለውለታዎች ጥቂት አይደሉም። ከእነዚህ ግለሰቦች መካከል ከኢትዮጵያ ግዙፍ ፕሮጀክቶች ጀርባ ዐሻራውን ያሳረፈው የጣሊያኑ ሳሊኒ ኩባንያ መሥራች ሲሞንፒየትሮ ሳሊኒ በቀዳሚነት ይጠቀሳሉ።

አርክቴክት እና ግንበኛ ብሎም ታላቅ ሰብዓዊነት ያለውና በስትራቴጂያዊ ራዕይ እንደሚመሩ የሚነገርላቸው ሲሞንፒየትሮ ሳሊኒ በኢኮኖሚው በተለይ ጣሊያን ከሁለተኛው የዓለም ጦርነቱ በኋላ ዳግም ማንሰራራት እንድትችል ትልቅ አበርክቶ ነበራቸው። በዋና ዋና የመሠረተ ልማት ፕሮጀክቶች እና ህንጻዎች ላይ በሰሩት ሥራ በሀገሪቱ እ.ኤ.አ በ1960ዎቹ በመጣው የምጣኔ ሀብታዊ እድገት ላይ ያሳዩት ተፅዕኖ ከፍተኛ ነበር።

እ.አ.አ በ1956 ወደ ቤተሰብ ንግድ የገቡት ሲሞንፒየትሮ ሳሊኒ እ.አ.አ በ1962 የድርጅቱን አድማስ በዓለም አቀፍ ደረጃ ማስፋፋት ጀመሩና ከጥቂት ዓመታት በኋላ የወላጅ አባታቸውን ሞት ተከትሎ፣ የኩባንያውን መሪ በመሆን፣ ድርጅቱን ወደ ዓለም አቀፍ ታዋቂነት መምራት ቻሉ። ድርጅቱ በዋናነት ትኩረቱን አፍሪካ ላይ አድርጎ በአህጉሪቱ የተለያዩ ግዙፍ ፕሮጀክቶችን እውን እንዲያደርግ ፈር ቀደጅ የሆኑት ሲሞንፒየትሮ ሳሊኒ በዛን ጊዜ በትላልቅ ፕሮጀክቶች የመሥራት አቅም ለነበራቸው ኩባንያዎች ታላቅ እድሎችን ወደ ሰጠችው አህጉር ትኩረቱን በማድረግ ታላቅ ሥራ መሥራት ቻለ።

በሲሞንፒየትሮ ሳሊኒ መሪነት ግዙፍ ተቋም መሆን የቻለው ሳሊኒ ኩባንያ ባለፉት ዓመታት የአንዳንድ የአፍሪካ ሀገራትን ገፅታ በመለወጥ በአህጉሪቱ ዕድገት ላይ የራሱን አውንታዊ አስተዋጽኦ አበርክቷል። ከኢትዮጵያ እስከ ሴራሊዮን፣ ከጋና እስከ ናይጄሪያ፣ ከአልጄሪያ እስከ ሊቢያ በመሄድ ሀገራቱን በከፍተኛ ደረጃ ተጠቃሚ ያደረጉ ዋና ዋና የመሠረተ ልማት ፕሮጀክቶችን እውን ለማድረግ አስተዋጽኦ አበርክቷል።

ሲሞንፒየትሮ ሳሊኒ ለኩባንያው ዕድገት ባላቸው ቁርጠኝነትና በነበራቸው የሥራ ፈጠራ ችሎታ በጥቂት ሀብት የተጀመረው የቤተሰብን ንግድ ወደ ትልቅ የኢንዱስትሪ ኩባንያ እንዲቀይር ማድረግ ችለዋል።

ኩባንያው ዛሬ ላይ ከ50 በላይ በሆኑ 5 አህጉራት (አፍሪካ፣ አሜሪካ፣ እስያ፣ አውሮፓ፣ ኦሺኒያ) ከ8ሺ በላይ ሠራተኞች ይዞ እየሰራ ይገኛል። ድርጅቱ በግንባታ ሥራዎቹ ፣ የውሃ ኤሌክትሪክ ማመንጫዎች እና የሃይድሮሊክ ግንባታዎች፣ የውሃ መሠረተ ልማቶች እና ወደቦች፣ መንገድ፣ ባቡር ሀዲድ፣ ሜትሮ ሲስተም እና የመሬት በታች ሥራዎች፣ አውሮፕላን ማረፊያዎች፣ ሆስፒታሎች እና የኢንዱስትሪ መሠረተ ልማቶችና ግንባታዎች በሚሰራቸው ሥራዎች በዓለም አቀፍ ደረጃ እውቅና መግኘት ችሏል።

በሲሞንፕየትሮ ሳሊኒ አማካኝነት ታላቅና ዓለም አቀፍ ኩባንያ መሆን የቻለው ሳሊኒ ባፈራው የምህንድስና ልምድ በመላው ዓለም እስከ አሁን ከ257 በላይ ግድቦች እና የሃይድሮ ኤሌክትሪክ ማመንጫዎች መሥራት ችሏል። 6ሺ830 ኪሎ ሜትር የባቡር መስመሮች; 1ሺ450 ኪሎ ሜትር የመሬት ውስጥ ሥራዎች፤ 400 የሚሆኑት የምድር ውስጥ ባቡር መስመሮች፤ 51ሺ660 ኪሎ ሜትር መንገዶች እና አውራ ጎዳናዎች እና 350 ድልድዮች በተለያዩ ሀገራት መገንባት ችሏል።

የሲሞንፕየትሮ ሳሊኒ ኩባንያ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከተሳተፈባቸው ፕሮጀክቶች መካከል የሚከተሉት ለአብነት መጥቀስ ይቻላል፡፡ ካሪባ ግድብ፣ ዚምባብዌ/ዛምቢያ፣ ዴዝ ዳም ግድብ ኢራን፣ አኮሶምቦ ግድብ ጋና፣ የአቡ ሲምበል ቤተመቅደሶች፣ ግብፅ፣ ቤይ ኦፍ ፎንትቪዬል፣ ሞናኮ፣ ታርቤላ ግድብ፣ ፓኪስታን፣ ፍሬጁስ መንገድ ዋሻ ፈረንሳይ፣ ትራንስ-ጋቦን ባቡር ጋቦን፣ ሳን ሮክ ጎንዛሌዝ ደ ሳንታ ክሩዝ ድልድይ፣ አርጀንቲና/ፓራጓይ ይገኙበታል።

በተጨማሪም የአውሮፓ ፓርላማ አዲስ ሄሚሳይክል ፈረንሳይ፣ የሌሶቶ ሃይላንድ የውሃ ፕሮጀክት፣ የሮዶቪያ ዶስ ኢሚግራንትስ፣ ብራዚል፣ ቅጥያዎች ጋዚ ባሮታ ግድብ ፓኪስታን፣ ነትበይ ጀክር የሀይድሮ ኤሌክትሪክ ኃይል ፕሮጀክት፣ ህንድ፣ ሼክ ዛይድ ታላቁ መስጊድ፣ የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች፣ የካራህንጁካር የውሃ ኃይል ማመንጫ፣ አይስላንድ፣ ቱሪን–ሚላን እና ቦሎኛ–ፍሎረንስ ባለከፍተኛ ፍጥነት ባቡር ጣሊያን፣ በኦክስፎርድ የሚገኘው የቸርቺል ሆስፒታል ማስፋፊያ ይጠቀሳሉ።

ከዚህ ባሻገር ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ፣ ሲቲሪንገን፣ አዲስ የምድር ውስጥ ባቡር ክብ የከተማ መስመር በኮፐንሃገን፣ በኳታር የዶሃ ሜትሮ ፕሮጀክት፣ የቴክሳስ ማዕከላዊ ባቡር፣ ሮጉን ግድብ፣ ታጂኪስታን፣ የግራንድ ፓሪስ ኤክስፕረስ ፈረንሳይ በኔኦም ሳውዲ አረቢያ የግድብና ሰው ሰራሽ ሀይቅ ግንባታ በማከናወን ላይ ይገኛል።

ሳሊኒ በኢትዮጵያ፦

የቀድሞ ሳሊኒ ኢምፒሬጂሎ / Salini Impregilo የአሁኑ ዊ ቢውልድ/ We Build የግንባታ ድርጅት ባለቤት እና የኢትዮጵያ የልብ ወዳጅ ጣሊያኒያዊው ሲሞንፒየትሮ ሳሊኒ ለአፍሪካ በተለይም ለኢትዮጵያ የነበራቸው ፍቅርና ወዳጅነት ከፍተኛ እንደነበር ይነገርላቸዋል፡፡ ይህንንም በተለያዩ ጊዜያት በተግባር አረጋግጠዋል።

ፋሽስት ጣሊያን በአምስት ዓመቱ የመከራ ዘመን ላደረሰችው ግፍና በደል እንደ ካሳ የተቆጠረውን ለገዳዲ የመጠጥ ውሃ ግድብ፣ በሰው እጅ ለተገደሉት የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ጆን ኦፍ ኬኔዲ መታሰቢያ የተገነባው የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ኬኔዲ ቤተ መጽሐፍት፣ ደርግ የመቶ ሺህ ኢትዮጵያዊያን ሕይወት በዘመናዊ የመስኖ እርሻ ለመቀየር አቅዶ የሰራው የጣና በለስ የተቀናጀ ፕሮጀክት፣ የለገዳዲ ግድብ፣ የግልገል ጊቤ 1፣ 2 ፣ 3 ፣ ጊቤ 4 (ኮይሻ ) የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶች ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታን እውን በማድረግ ታላቅ ዐሻራውን አሳርፏል። በማሳረፍ ላይም ይገኛል።

በተለይ ኢትዮጵያ የሕዳሴ ግድብ ግንባታ ለማስጀመር እንቅስቃሴ ስትጀምር በወቅቱ ግብፅ በምዕራባዊያን ዘንድ የነበራትን ተሰሚነት በመጠቀም ማንም ለኢትዮጵያ የገንዘብ ብድር እና ድጋፍ፣ ቴክኒካል እገዛ እና ኢትዮጵያ በምታወጣው ዓለም አቀፍ ጨረታ ማንም እንዳይሳተፍ ዘመቻ በወጣችበት በዚያ ወቅት ተቋማቸው ላይ የሚደርሰውን ጫና ለመሸከም ኃላፊነት ወስደው የሕዳሴ ግድብ ግንባታውን በማስጀመር ዛሬ ላይ እውን እንዲሆን የላቀ ሚና ተጫውተዋል።

በተወለዱ በ92 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩት የሳሊኒ ኮንስትራክሽን ባለቤት የነበሩት የአሁኑ WeBuild ግሩፕ ፕሬዚዳንት እና ከአፄ ኃይለሥላሴ ዘመነ መንግሥት ጀምሮ የረጅም ጊዜ የኢትዮጵያ ወዳጅ የነበሩ ሲሞን ፒዬትሮ ሳሊኒ ኢትዮጵያ ያላትን የተፈጥሮ ሀብት በመጠቀም ከድህነት ለመለቀቅ ባደረገችው ጥረት ከጎኗ በመቆም ዘመን የማይሽረው ሥራ ሠርተዋል።

ሳሊኒ በአሁኑ መጠሪያው ዊ ቢውልድ ግሩፕ በኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ መሠረተ ልማቶች ግንባታ ላይ ዐሻራውን ያኖረ ግንባር ቀደም ኩባንያ ነው።

በሀገራችን ኢትዮጵያ በርካታ ብሔራዊ እና ግዙፍ የግንባታ ፕሮጀክቶችን በማከናወን ዝናን ያተረፈው ሳሊኒ ኮንስትራክሽን ባለቤት ህልፈተ ሕይወት ተከትሎ ጠ/ሚ ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የተሰማቸውን ሀዘን በማህበራዊ ትስስር ገፃቸው ገልፀዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት ለሲሞንፒየትሮ ሳሊኒ ቤተሰብና ለመላው ዊ ቢውልድ ግሩፕ መጽናናትን ተመኝተዋል። ሳሊኒ ለኢትዮጵያ የነበራቸው ፍቅር በተግባር የተገለጠ እንደሆነ ጠቅሰው በሀገር ግንባታ ሂደት የተለያዩ የልማት ፕሮጀክቶች ማከናወናቸውንም አንስተዋል።

የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ማስተባበሪያ ፕሮጀክት ጽ/ቤት ዋና ሥራ አስኪያጅ ዶ/ር አረጋዊ በርሔም በሲሞን ፔትሮ ሳሊኒ ህልፈተ ሕይወት የተሰማቸውን ልባዊ ሀዘን ገልፀው ለቤተሰቦቻቸውና ለመላው የዊ ቢውልድ ግሩፕ መፅናናትን ተመኝተዋል።

የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ማስተባበሪያ ፕሮጀክት ጽ/ቤት የሕዝብ ግንኙነት እና የሚዲያ ኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ኃይሉ አብርሃም እንደሚናገሩት፤ ሲሞን ፔትሮ ሳሊኒ ከኢትዮጵያውያን በላይ ኢትዮጵያዊ ሆነው ለኢትዮጵያ ያላቸውን ፍቅር በተግባር ያረጋገጡ የሀገር ባለውለታ ናቸው ይላሉ።

እንደ አቶ ኃይሉ ገለፃ፤ ድርጅታቸው ባለፉት ዓመታት በኢትዮጵያ የተለያዩ ግድቦችን ሲሰራ ተከፋይ ኮንትራክተር ስለሆነ ብቻ ሳይሆን ሀገሪቱ አንድ ደረጃ ከፍ እንድትልና ለኢትዮጵያ ካለው ፍቅር የተነሳ እንደ ፕሮጀክት ባለቤት ጥራት ያለው ሥራ በመሥራት ከኃይለሥላሴ ዘመን ጀምሮ እስከ አሁን አገልግሎት የሚሰጡ የተለያዩ ፕሮጀክቶችን እውን ማድረግ የቻለ ስለመሆኑ ይናገራሉ።

አቶ ኃይሉ እንደሚናገሩት፤ በተለይ የዓባይ ግደብ ሲሰራ ሙሉ የግንባታ ሥራውን ለመሥራት ሙሉ ኮንትራት ወስዶ ጨረታ አሸንፎ ሥራውን የጀመረው ሳሊኒ፤ መንግሥት ተጨማሪ የሀገር ውስጥ ኮንትራክተር ገብቶ የብረታ ብረት ሥራውን ይስራ የሚል ሃሳብ ስያመጣ ቅር ባለመሰኘት ሥራውን እንደቀጠለ ተናግረው፤ የዚህ መነሻም በሀገር ውስጥ አቅም ያለውና ግዙፍ ፕሮጀክቶችን መገንባት የሚችል ድርጅት እንዲፈጠር ከነበራቸው ፍላጐት መነሻ እንደነበር ያስረዳሉ።

ሳሊኒ የዓባይ ግድብን ግንባታ ስያከናውን፤ ብዙ ዓለም አቀፍ ተፅዕኖዎች እየደረሱበት እንደቆዩና ከፍተኛ ጫና ተቋቁሞ ዛሬ ላይ ፕሮጀክቱን በመጠናቀቅ ላይ እንደሚገኝ የሚናገሩት አቶ ኃይሉ፤ ኩባንያው ሥራውን እንዲያቆም የተለያዩ ሀገራት በተለይ ግብፅ የተለያዩ ማስፈራሪያዎች ስታደርግ ነበር ይላሉ።

የግብፅ መንግሥት ጣልያን ድረስ ሄዶ የሀገሪቱን ጠቅላይ ሚንስቴር በማነጋገር የግድቡ ግንባታ እንዲቆም ጥረት አድርጓል፡፡ የሳሊኒ ኩባንያ ግን ለዝናውና ክብሩ ብሎም ዓለም አቀፍ መመሪያዎችን በማክበር የሚሠራና ኢትዮጵያን የሚወድ በመሆኑ ሥራውን በመሥራት ቀጥሎ የዓባይ ግድብ አሁን ለደረሰበት ደረጃ እንዲበቃ ማድረግ ችሏል ይላሉ።

ከዚህ ባለፈ በግድቡ የግንባታ ወቅት የሀገር ውስጥ ኩባንያ የሥራ ድርሻው ወደኋላ በመዘግየቱ ምክንያት ሥራዎች ቢጓተቱበትም ችግሩን በትዕግሥት በማለፍ እስከ መጨረሻው ለገባው የሥራ ውል ታማኝ ሆኖ በአፍሪካ ግዙፉን ግድብ እውን ማድረግ የቻለ ነው ይላሉ።

ሲሞንፕየትሮ ሳሊኒን በትውልድ ጣልያናዊ ቢሆኑም ኢትዮጵያዊም ናቸው የሚሉት አቶ ኃይሉ፤ ከጣና በለስ እስከ ግልገል ግቤ በመቀጠልም ኮይሻ እንዲሁም ዓባይ ግድብ ድርጅታቸው ከነበረው የሥራ ድርሻ በተጨማሪ ከእውቀትና ቴክኖሎጂ ሽግግር አኳያ ዐሻራቸው ጉልህ እንደነበር ይናገራሉ።

እኛም በዚህ ለሀገር የላቀ አበርክቶ ያኖሩ የኢትዮጵያ ባለውለታ ግለሰቦችና ተቋማት በሰሩት ሥራ በሚመሰገኑበት አምድ ከኢትዮጵያ ግዙፍ ፕሮጀክቶች ጀርባ ታላቅ ዐሻራ ያኖሩትን እና በሥጋና በደም ኢትዮጵያዊ ባይሆኑም ለኢትዮጵያ ዘላቂ ተጠቃሚነት ያለስስት የሠሩትን የጣልያኑ የግንባታ ድርጅት ሳሊኒ መሥራች ሲሞንፕየትሮ ሳሊኒን አመሰገንን፤ ሰላም!

ለዚህ ፅሑፍ እንደ ምንጭነት የተለያዩ ማህበራዊ ድረ ገፆችን እና ቃለ መጠይቅ ተጠቅመናል።

ክብረአብ በላቸው

አዲስ ዘመን ረቡዕ ሐምሌ 17 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You