ቡና አልሚው፣ አቅራቢውና ላኪው ባለሀብት

ተፈጥሮ አብዝታ ያደለቻት ኢትዮጵያ አብዛኞቹ አካባቢዎቿ በልምላሜ የተንቆጠቆጡና በአረንጓዴ ያሸበረቁ ናቸው:: ከእነዚህ አካባቢዎች መካከል ኢሉአባቦር ትጠቀሳለች::

ከጅማ ከተማ 265 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኘው ይህ የኢሉአባቦር አካባቢ በዩኔስኮ የተመዘገበ ሰፊ የደን ሽፋንም አለው:: የደን ሽፋኑ ያዮ ደን በመባል ይታወቃል:: ያዮ ደን ከአራት እስከ አምስት ወረዳዎችን የሚያካልል ሲሆን፣ ከፍተኛ መጠን ያለው ቡናም ይመረትበታል:: አብዛኛው የአካባቢው ቡና ከዚሁ ደን እና በደኑ ዙሪያ ከሚገኙ ስፍራዎች የሚገኝ የጫካ ቡና ነው:: ቡናውም የተለየ ጣዕም እንዳለው ይነገራል::

ኢሉአባቦር በዋናነት ከሚታወቅበት ከቡና ምርት በተጨማሪ የተለያዩ የቅመማ ቅመም አይነቶች፣ ማር፣ ቅቤና ከሰብል ምርቶችም እንዲሁ በቆሎ፣ ማሽላና የመሳሰሉት በስፋት ይመረቱበታል:: የአካባቢው ነዋሪዎችም በአብዛኛው በግብርና የሚተዳደሩ ሲሆኑ፣ ከግብርናው ጎን ለጎንም በርካቶች በንግድ ሥራ ተሰማርተውበታል:: የዕለቱ የስኬት እንግዳችንም በቡና አልሚነትና አቅራቢነት የሚታወቁ ሲሆኑ፤ ለገበያ ከሚያቀርቡት ቡናም አብዛኛው የአካባቢው መለያ ከሆነው ያዮ ደን የሚዛቅ ስለመሆኑ አጫውተውናል::

እንግዳችን አቶ ፈጠነ የኋላሸት ይባላሉ:: ተወልደው ያደጉት ኢሉአባቦር ዞን አልጌሳቺ ወረዳ ሱጴ ከተማ ነው:: ሱጴ ከተማ ዘመን ተሻጋሪ በሆኑ የሥነጽሁፍ ሥራዎቹ የምናውቀው ደራሲ በዓሉ ግርማ ተወልዶ ያደገበት ነው:: አቶ ፈጠነም ከዚሁ አካባቢ ነው ተወልደው ያደጉት:: አቶ ፈጠነ፤ የአንደኛና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በዚሁ አካባቢ ተከታትለዋል::

ቡና በማልማትና በማቅረብ የ27 ዓመት ልምድ ያላቸው አቶ ፈጠነ፤ ቡና አልሚና አቅራቢ ከመሆናቸው አስቀድሞ በተለያዩ የሥራ መስኮች ተሠማርተው አሳልፈዋል:: ከእነዚህም መካከል በኢትዮጵያ አየር ወለድ ጦር ውስጥ ያገለገሉት ይጠቀሳል:: በአየር ወለዱ የፓራሹት ዘላይ ሆነው ለሰባት ተከታታይ ዓመታት ሀገራቸውን አገልግለዋል:: ከኢትዮጵያ አየር ወለድ ሲለቁ የንግድ ሥራን አሰቡት:: ንግዱ ደግሞ ቡና እንዲሆን ፈለጉ:: ኢሉአባቦር ቡና በተለይም የጫካ ቡና በስፋት የሚለማበት የትውልድ ቦታቸው በመሆኑ ሥራውን ለመጀመር አላመነቱም::

እሳቸው እንዳሉት በኢሉአባቦር ሁሉም አካባቢዎች ቡና በስፋት ይለማል:: በተለይም በዩኔስኮ በተመዘገበው ያዮ ደን እና በዙሪያው ጥራት ያለውና በጣዕሙ የተለየ የጫካ ቡና በከፍተኛ መጠን ይለማል:: ይህንኑ የአካባቢያቸውን ገጸ በረከት ተጠቅመው በቡና ሥራ ላይ ሲሰማሩ አስቀድመው በአካባቢው ከሚገኙ አልሚዎች ቡና ገዝተው ለአቅራቢዎች በማስረከብ ነበር::

በወቅቱ ቡና ሰብሳቢ የሚባል የንግድ ሥራ ዘርፍ በመኖሩ የቡና ሰብሳቢ ፈቃድ በማውጣት የቡና ንግድ ሥራን የጀመሩት አቶ ፈጠነ፤ ከአካባቢው ቡና አምራች አርሶ አደሮች ቡና በመሰብሰብ ለአቅራቢ ነጋዴዎች ያስረክቡ ነበር:: ቡና ሰብሳቢ ሆነው የተወሰኑ ዓመታት ከሠሩ በኋላ ንግዳቸው እየደረጀ ሄዶ ቡና አቅራቢ ነጋዴ መሆን ችለዋል:: በዚህ ጊዜ ታዲያ የሰብሳቢ ፈቃድ በማውጣት ከቡና ሰብሳቢነት ቡና አቅራቢ ነጋዴ ተሸጋግረዋል::

በዚህ ወቅት ታዲያ ቡና አቅራቢ ነጋዴ ብቻ ሳይሆኑ ቡና አልሚም ነበሩ:: የልማት ሥራቸውን ከአቅራቢነት ጎን ለጎን ማስኬድ እንዲያስችላቸው በኢንቨስትመንት መሬት በመውሰድ ቡናን በስፋት ማልማት የሚያስችል ምቹ ሁኔታ ተፈጥሮላቸዋል:: በዚህም ቡና የማልማትና ገዝቶ የማቅረብ ሥራቸውን ጎን ለጎን በማስኬድ ውጤታማ መሆን ችለዋል:: አሁን ላይ 300 ሄክታር መሬት ላይ የሚያለሙትን እንዲሁም ከሌሎች አልሚዎች የሚገዙትን ቡና ጨምረው አልሚና አቅራቢ በመሆን ጥራት ያለውን ቡና ለላኪዎች ያቀርባሉ፣ እሳቸውም ይልካሉ::

ቡናን በጥራት ለማቅረብ ከፍተኛ ጥረት የሚያደርጉት አቶ ፈጠነ፤ ከልማቱ ጀምሮ አዘገጃጀቱ ላይ ከፍተኛ ጥንቃቄ በማድረግ ቡናቸው የተሻለ ዋጋ እንዲያወጣ በብዙ ይተጋሉ:: የኢትዮጵያ ቡና በውጭው ዓለም ያለውን ተቀባይነት ለማስቀጠልና ከዘርፉ የበለጠ ተጠቃሚ ለመሆን ከምርት ጀምሮ ብዙ ሥራ መሰራት አለበት ብለው የሚያምኑት አቶ ፈጠነ፤ እርሳቸው ቡናን ከምርት ጀምሮ በመከታተልና በማዘጋጀት ለላኪዎች ያቀርባሉ አለፍ ሲልም ኤክስፖርት ያደርጋሉ::

በአብዛኛው የሚያለሙትን ቡና በቀጥታ ኤክስፖርት የሚያደርጉ ሲሆን፤ ከአካባቢው አርሶ አደር የሚገዙትን ቡና ሰብስበውና በጥራት አዘጋጅተው ለላኪዎች ያቀርባሉ:: ያለሙትን ቡና ብቻ በቀጥታ ኤክስፖርት የሚያደርጉት አቶ ፈጠነ፤ ዘመናዊ የቡና ማጠቢያ ማሽኖችን እንዲሁም ሶስት ደረቅ ቡና ማበጠሪያ ማሽኖችን ተክለዋል:: እነዚህን ማሽኖች በመጠቀምም ቡናን በጥራት በማዘጋጀት የኢትዮጵያ ቡና ለዓለም ገበያ እንዲደርስ ከፍተኛ ጥረት ያደርጋሉ::

ያለሙትን ቡና ብቻ ወደ ውጭ ገበያ መላክ ከጀመሩ ሁለት ዓመታት እንደሆናቸው የሚናገሩት አቶ ፈጠነ፤ በማሳቸው ከሚያለሙት ቡና በተጨማሪ በአካባቢው የሚገኙ አርሶ አደሮች የሚያለሙትን ቡና ጨምረው ኤክስፖርት የማድረግ ዕቅድ እንዳላቸው ተናግረዋል:: እሳቸው እንዳሉት በቀጣይ 2017 ዓ.ም 700 ከሚደርሱ ቡና አልሚ አርሶ አደሮች ጋር በመሥራት ቡናቸውን ወደ ውጭ ገበያ ለመላክ ዝግጅታቸውን አጠናቅቀዋል::

ለዚህም ለአርሶ አደሮቹ የሚስፈልጋቸውን ሥልጠና ሰጥተዋል:: አርሶ አደሮቹም ባገኙት ሥልጠና መሠረት የሚያለሙትን ቡና በጥራት አምርተው እንዲያስረክቧቸው ስምምነት ላይ ደርሰዋል፤ አስፈላጊውን ድጋፍና ክትትልም እያደረጉ ይገኛሉ:: በተለይም አርሶ አደሩ ጥራት ላይ ትኩረት አድርጎ እንዲሠራና ምርትና ምርታማነቱ እንዲጨምር አስፈላጊ የሆኑ ሥልጠናዎችን የሰጡት አቶ ፈጠነ፤ በቀጣይ እነዚህ አርሶ አደሮች ያለሙትን ቡና እንዲሁም በማሳቸው ላይ የለማውን ጨምረው ወደ ውጭ ገበያ እንደሚልኩ ተናግረዋል::

እስከ አሁን ግን ከአምራች አርሶ አደሩ ገዝተው ለውጭ ገበያ ያዘጋጁትን ቡና ለላኪዎች እያቀረቡ ይገኛሉ:: በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ለውጭ ገበያ የተዘጋጀ 80 ኮንቴይነር ቡና ለላኪዎች አቅርበዋል:: ከዚሁ ጋር በተያያዘም በማሳቸው ያለሙትን ከአምስት እስከ ስድስት ኮንቴይነር የሚደርስ ቡና ወደ ውጭ ገበያ ለመላክ ዝግጅታቸውን አጠናቀዋል::

‹‹ቡና ለኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ዕድገት ትልቅ አቅም ነው›› የሚሉት አቶ ፈጠነ፤ መንግሥትን ጨምሮ ቡና ላኪውና አቅራቢው ተጠቃሚ የሚሆነው ዋናው የቡና ምንጭ የሆነው ቡና አምራች አርሶ አደር ሲኖር ነው ይላሉ:: እሳቸው እንዳሉት፤ ምንጫችን እንዳይደርቅና እንዲጎለብት በተለይም በቡና ልማት ላይ አርሶ አደሩን ማገዝ ያስፈልጋል:: አቅራቢውና ላኪው ምንጩን መንከባከብ ይጠበቅባቸዋል:: ለአብነትም አንድ ቡና አቅራቢ በትንሹ ለአምስትና ለስድስት አርሶአደሮች ድጋፍ ቢያደርግና መርዳት ቢችል በተመሳሳይ አንድ ላኪ ከ50 እስከ 100 አርሶ አደሮችን መርዳትና ማገዝ ይችላል:: በዚህ መንገድ እርስ በእርስ መደጋገፍ ከተቻለ አቅራቢውና ላኪው እንዲሁም ሀገር ተጠቃሚ መሆን ትችላለች::

አርሶ አደሩ ለቡና አቅራቢና ላኪዎች የመኖር ዋስትና እንደሆነ ያነሱት አቶ ፈጠነ፤ አርሶ አደሩን መንከባከብ፣ መጠበቅ፣ ማገዝና አስፈላጊ የሆኑ ግብዓቶችን ማቅረብ የግድ መሆኑን ሲገልጹ፤ ከአርሶ አደሩ ጎን በመሆን ቴክኖሎጂን በማስተዋወቅ፣ በማሳየትና በማለማመድ የቡና ምርትና ምርታማነትን ማሳደግና ጥራቱን ማስጠበቅ ይቻላል ብለዋል:: የቡና ምርትና ምርታማነትን ማሳደግና ጥራቱን ማስጠበቅ ከተቻለ በቀዳሚነት አርሶ አደሩ ተጠቃሚ ይሆናል በማለት አመላክተዋል::

እሳቸው እንደሚሉት ከሆነ ቡና ላኪዎችና አቅራቢ ነጋዴዎች የአርሶ አደሩን ቡና በሀገር ውስጥና በውጭ ገበያ የማስተዋወቅ ትልቅ ኃላፊነት አለባቸው:: ቡናውን ይዘው ወደ ገበያ ሲቀርቡ ከጀርባቸው ያለው አርሶ አደር ማን እንደሆነ ማስተዋወቅና ተጠቃሚ መሆን የሚችልበትን ዕድል መፍጠር ይገባቸዋል:: ይህም የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት ከማረጋገጥ ባለፈ ሀገራዊ ፋይዳው የጎላ ይሆናል:: ለዚህም መንግሥት ለዘርፉ የሰጠው ትኩረት የሚበረታታ እንደመሆኑ በቀጣይ የቡናው ዘርፍ ለአገር ኢኮኖሚ አለኝታነቱን ማረጋገጥ ያስችላል::

በግላቸው ከሚያለሙት ቡና በተጨማሪ 700 ከሚደርሱ አርሶ አደሮች ጋር በጋራ እያለሙ ለሀገር ውስጥና ለውጭ ገበያ የሚያቀርቡት ቡና አልሚ፣ አቅራቢና ላኪ የሆኑት አቶ ፈጠነ፤ ከሀገር ውስጥ ባለፈ ሰፊ የውጭ ገበያ እንዳላቸው ገልጸዋል:: ከእነዚህም መካከል መካከለኛው ምስራቅና ቻይና ተጠቃሽ የገበያ መዳረሻዎቻቸው መሆናቸውን ጠቅሰው፤ እንደ ቱርክ ያሉት የአውሮፓ ሀገሮች ላይም ጥሩ የገበያ ግንኙነት በመፍጠር ገበያውን ለመቀላቀል በቂ ዝግጅት ማድረጋቸውን አመላክተዋል::

ቡናን ማልማትን ጨምሮ ወደ ውጭ ገበያ በመላክ የሚታወቁት አቶ ፈጠነ፤ ለበርካታ ዜጎችም የሥራ ዕድል ፈጥረዋል፤ በቡና ልማት ሥራ ብቻ ማሳ ላይ ለሚሠሩ 340 ዜጎች እንዲሁም በቡና ማጠቢያ ማሽን እና ደረቅ ቡና ላይ ለሚሠሩ 120 ዜጎች በድምሩ ለ460 የአካባቢው ሰዎች የሥራ ዕድል መፍጠር ችለዋል::

ማህበራዊ ኃላፊነትን ከመወጣት አንጻር ከአካባቢያቸው እድር ጀምሮ በወረዳ፣ በቀበሌና ከዞንና ከክልል አመራሮች ጋር በመሆን በተፈለጉበት ጊዜ ሁሉ በመገኘት ሃሳባቸውን፣ ገንዘባቸውንና ጉልበታቸውን ጭምር ያለስስት በመስጠት ኃላፊነታቸውን እየተወጡ እንደሆነ የጠቀሱት አቶ ፈጠነ፤ በተለይም ግብር በወቅቱና በሀቀኝነት በመክፈል የዜግነት ግዴታቸውን እንደሚወጡም ነው ያስታወቁት::

በተለያዩ የቡናው ዘርፍ አደረጃጀቶች በመሳተፍ ለዘርፉ እድገትም የበኩላቸውን እያበረከቱ ይገኛሉ:: በአሁኑ ወቅትም በኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት የኦሮሚያ ቡና አቅራቢዎችና አዘጋጆች ማህበር ፕሬዚዳንት ሆነው እያገለገሉ ሲሆን፤ በኢትዮጵያ የቡና ማህበር ውስጥም እንዲሁ የቦርድ አባል ናቸው::

እነዚህንና መሰል ኃላፊነቶችን በአግባቡ በመወጣት አስፈላጊውን ድጋፍ እያደረጉ ያሉት አቶ ፈጠነ፤ በተለይም ከቡና ምርትና ምርታማነት እንዲሁም ከጥራት ጋር የሚነሱ ችግሮችን ዳር ቆሞ ከመመልከት ይልቅ በጋራ ተባብሮ ዘርፉን ወደላቀ ደረጃ ከፍ ለማድረግ እንዲሁም ችግሮቹን ለማቃለል እንደሚሠሩም ይናገራሉ::

ከዚህ በተጨማሪም የትውልድ ቦታቸው በሆነው ሱጴ አካባቢ ስድሰት በሚደርሱ ንጹህ የመጠጥ ውሃ መሠረተ ልማት ማሟላት ሥራዎች ላይ በነበራቸው ተሳትፎ 50 በመቶ ያህል ድጋፍ በማድረግ የአካባቢው ማህበረሰብ ንጹህ የመጠጥ ውሃ ማግኘት እንዲችል አድርገዋል::

በትምህርት ቤት ልማት ላይም እንዲሁ አቅማቸው የፈቀደውን በማድረግ በአካባቢው ትምህርት ቤቶች እንዲገነቡ በቅንጅት ሠርተዋል:: በአካባቢው መንገድ የማውጣትና ሌሎች የልማት ሥራዎች እንዲሠሩ ከማገዝና ከማስተባበር ባለፈ በልማት ሥራ የሚነሱ ቅሬታዎች የሚፈቱበትን መንገድ ለማፈላለግ በኮሚቴ ውስጥ በመንቀሳቀስ ከመንግሥት ጋር እየሠሩ ይገኛሉ:: በልማት ሥራ ከፍተኛ የሆነ ተሳትፎ ያላቸው አቶ ፈጠነ፤ እንደስማቸው ሁሉ የፈጠነና ውጤታማ ሥራ ለመሥራት ከፍተኛ ተነሳሽነት እንዳላቸውም ይገልጻሉ::

በቡናው ዘርፍ ከፍተኛ ተሳትፎ ያላቸው አቶ ፈጠነ፤ በቀጣይም በቡና ኢንዱስትሪ ሰፋፊ ሥራዎችን የመሥራት ራዕይ አላቸው:: በዘርፉ የተሰማሩ ሰዎች ከግል ተጠቃሚነት ወጥተው የጋራ ተጠቃሚ መሆን እንዲችሉ ለማድረግ ከፍተኛ ፍላጎትና ተነሳሽነት እንዳላቸውም ይገልጻሉ:: ለዚህም አቅራቢና አርሶ አደሩ ሥልጠና የሚያገኙበትን ዕድል ለመፍጠር ከሚመለከታቸው አካላት ጋር የመሥራት ፍላጎቱ አላቸው:: ይህም የኢትዮጵያ ቡና በዓለም ገበያ ተፈላጊነቱ ጨምሮ ጥሩ ዋጋ የሚገኝበትን በር እንደሚከፍት ጠቅሰው፣ እዚህ ላይ ትኩረት አድርገው መሥራት እንደሚፈልጉ ተናግረዋል::

ምዕራብ ኢትዮጵያ ጅማን ጨምሮ ኢሉአባቦር፣ ቦንጋ፣ ቴፒ፣ ሚዛን፣ ቤንች ማጂና በደሌ አካባቢ ቡና በስፋት እንደሚመረት ጠቅሰው፣ ጥራት ላይ ገና እንዳልተሠራ አቶ ፈጠነ አስገንዝበዋል:: በቀጣይ ጥራት ላይ ብቻ ትኩረት አድርጎ በመሥራት አሁን ያለውን የቡና ዋጋ ከፍ ማድረግ እንደሚቻል ገልጸው፤ ‹‹ጥራት ላይ መሥራት ከተቻለ አሁን ከምናገኘው ገቢ በእጥፍ ማግኘት እንችላለን›› ሲሉ በመግለጽ በቡና ጥራት ላይ ትኩረት ተደርጎ እንዲሠራ ጥሪ አስተላልፈዋል::

ፍሬሕይወት አወቀ

አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሐምሌ 13 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You