ከራስ ለራስ የተዘረጉ የበጎነት እጆች

የኢትዮጵያውያን የመደጋገፍና የመረዳዳት እሴት ከጥንት ጀምሮ ሲከውን የኖረ የአብሮነታቸው መገለጫ ነው። ለኢትዮጵያውያን አንዱ ሲጎድልበት፤ አንዱ እየሞላ፤ በመተሳሰብና በአብሮነት እየተደጋገፉና እየተረዳዱ መኖር የዕለት ተዕለት ሕይወታቸው ነው። ይህ በጎ ተግባር ከትውልድ ወደ ትውልድ እየተላለፈ መጥቶ ጊዜና ቦታ ሳይገድበው ሰው ሰው በመሆኑ ብቻ እየፈጸመው፣ ለተቸገሩ ሰዎች በፍጥነት በመድረስ የሚያደርገው የእርስበርስ መደጋገፍና መተሳሰብ ባህል እየዳበረ ይገኛል።

ሀገሪቱ ከችግሩ ስፋት አኳያ አያሌ ድጋፍ የሚያስፈልጋቸው ዜጎች ያሉባት ብትሆንም፣ ሰውን ለመርዳት እጃቸውን ከመዘርጋት፣ ልባቸው በጎ ተግባርን ከመፈጸም ወደኋላ የማይል ልበ ቀና ሰዎች ይነሱ እንጂ አላጣችም። የእነዚህ አልባሽና አጉራሽ ኢትዮጵያውያን የማይነጥፉ እጆች ዘወትር ለወገኖቻቸው ፈጥነው ይደርሳሉ፤ በሃሳብም ከወገኖቻቸው ጎን የሚቆሙ አብረው ውለው አብረው የሚያድሩ ናቸው። እነዚህ በጎ አድራጊዎች በየአካባቢያቸውና በየሠፈራቸው ያሉ አቅም ለሌላቸው፣ ደጋፊ ላጡ ሰዎች ጊዜያቸውንና ገንዘባቸውን በመሰዋት ባላቸው ሁሉ ይደግፋሉ።

የተቸገሩን ለመደገፍ የኢትዮጵያውያን እጆች ከመዘርጋት ባይቆጠቡም፣ ችግሩ ሰፊ እንደመሆኑ በተደራጀ አግባብ መፍታት የግድ እንደሚል ተረድተው የሚሠሩ የበጎ አድራጎት ድርጅቶችን የሚመሠርቱትም ጥቂት አይደሉም። በሀገሪቱ የተከሰቱ እንደ ድርቅ፣ ግጭት፣ ወረርሽኝ ያሉት አጋጣሚዎች ደግሞ ለብዙዎች በጎ አድራጊዎች መወለድ ምክንያት ሲሆኑ ይታያል። ለእዚህም የኮቪድ ወረርሽኝ በተከሰተበት ወቅት ብዙዎች አሰበውትም ይሁን ሳያስቡት በበጎነት ጎዳና ርዳታና ድጋፍ ከሚያስፈልጋቸው ጋር አብረው የተጓዙበት ሁኔታ ይጠቀሳል።

የኮቪድ ወረርሽኝ በተከሰተበት ወቅት በሀገሪቱ ዜጎች ላይ የተደቀነውን ስጋት በመገንዘብ ዜጎችን ለመርዳት ርብርብ ውስጥ የገቡት በሀገር ውስጥ ያሉ ዜጎች ብቻ አልነበሩም። በውጭ ሀገሮች የሚገኙ ኢትዮጵያውያን በሀገር ውስጥ ከሚገኙት ጋር በመሆን ለወገን ደራሽነታቸውን በተግባር አሳይተዋል። ይህ መነሻቸው ሆኖም በትንሽ ተነስተው ዛሬ ላይ ለብዙዎች መድረስ የቻሉ፤ በበጎ ተግባራቸው የሚጠቀሱ የበጎ አድራጎት ድርጅቶች ተፈጥረዋል።

ከእነዚህ ድርጅቶች መካከል የየካ ልጆች የበጎ አድራጎት ድርጅት አንዱ ነው። ድርጅቱ በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ የሚኖሩ የየካ አካባቢ ልጆች /አብሮ አደጎች/ በጋራ የመሠረቱት ነው።

የድርጅቱ ሊቀመንበር አቶ ቴዎድሮስ ውቤ እንደሚለው፤ ድርጅቱ የኮቪድ ወረርሽን መከሰቱን ተከትሎ በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገራት በሚኖሩ ኢትዮጵያውያን አብሮ አደጎች ትብብር የተመሠረተ ነው። ድርጅቱን የመመሥረት ሃሳብ የመነጨው በውጭ ሀገር በሚኖሩት የየካ ልጆች አማካኝነት ነው።

በተለያዩ የውጭ ሀገሮች የሚኖሩት የየካ አካባቢ ልጆች ባነሱት የበጎ አድራጎት ሃሳብ ላይ በሀገር ውስጥ ከሚገኙ ዘጎች ጋር ውይይት ከተደረገ በኋላ ፤ ሰውን መርዳት ከሚለው በጎ ዓላማ ጎን በመሰለፍ ፈጣን ምላሽ ለመስጠት በቁርጠኝነት በመነሳት ነው ድርጅቱ የተመሠረተው። የድርጅቱ ዓላማ በአካባቢያችን ያሉትን እጅ ያጠራቸውን አቅመ ደካሞች ለማገዝና መርዳት ነው።

አቶ ቴዎድሮስ እንደገለጸው፤ በ125 በጎ ፈቃደኛ በሀገር ውስጥና በውጭ በሚኖሩ የአካባቢው ልጆች በ2014 ዓ.ም የተጀመረው ይህ ድርጅት በየጊዜው የአባላቱ ቁጥር እየጨመረ መጥቶ አሁን ላይ 185 አባላት አሉት።

የበጎ አድራጎት ድርጅቱ በማህበራት ማደራጃ ኤጀንሲ ጥር 4 ቀን 2014 ሕጋዊነት አግኝቷል። ድርጅቱ በቦርድ የሚተዳደር ሲሆን ሁለት ውጭ የሚኖሩና ሦስት ሀገር ውስጥ በአጠቃላይ አምስት የቦርድ አባላት አሉት። የራሱ መተዳደሪያ ደንብ ስላለው ቦርዱ በሚያጸድቀው በጀት ይተዳደራል። ገቢ የሚሰበሰበው ከአባላቱ ሲሆን ድርጅቱን መርዳትና ገንዘብ መስጠት የሚፈልጉ አካላት ካሉ ግን ገንዘቡን በድርጅቱ ባንክ አካውንት እንዲያስገቡ ይደረጋል፡ ፡

ድርጅቱ ሥራውን ሲጀምር በአንድ ጊዜ ሁሉንም አካባቢ ማዳረስ ስለማይቻል አካባቢውን በመወሰን የዳሰሳ ጥናት ማድረጋቸውን አቶ ቴዎድሮስ ይናገራል። አንድ ሺህ 430 መኖሪያ ቤቶችን ላይ በተደረገ የዳሰሳ ጥናት የሰው ድጋፍ እና ርዳታ የሚፈልጉ በርካታ ወገኖች መኖራቸውን ማወቅ ተችሏል። ይሁንና ድርጅቱ ሁሉንም መደገፍና መርዳት የሚያስችል አቅም ስለሌለው ከእነዚህ ውስጥ ደጋፊ የሌላቸውን፣ የታመሙትን እና እድሜያቸው ለገፋ 450 ሰዎች ለመጀመሪያ ጊዜ በመመረጥ የቁሳቁስ ድጋፍ አድርጓል።

የቡድኑ አባላት የበጎ አድራጎት የሚያደርጉላቸውን ወገኖች በብዙ ማጣራት ከመረጡ በኋላ ድጋፍ የሚያስፈልጋቸውን አካላት እየደገፉ ይገኛሉ። ይህን ድጋፍ የመስጠት አገልግሎት ሳይቋረጥ እንዲሰጥ የሚያደርጉ ሥራዎችን በመሥራት እስካሁን ባለመቋረጥ ለአራት ተከታታይ ዓመታት ለችግረኛ ወገኖቻቸው እጆቻቸው በፍቅር እየተዘረጉ መሆናቸውን አቶ ቴዎድሮስ ጠቅሷል።

አቶ ቴዎድሮስ እንደሚለው፤ የድርጅቱ የመጀመሪያ ዓላማ የምግብ ዓብዓቶችን ተደራሽ ማድረግ ነው። ድርጅቱ የበጎ አድራጎት ሥራውን ሲጀምር በየወሩ 50 ድጋፍ ለሚሹ አካላት የምግብ ግብዓቶች በመስጠት ነበር። ነገር ግን በርከታ ሰዎች የድርጅቱን ርዳታ በመሻት ጥያቄ ማቅረባቸውን ተከትሎ በውጭ ሀገራት የሚኖሩት ኢትዮጵያውያን እንቅስቃሴውን በማየት የአባላትን ቁጥር ማሳደጋቸውን አስታውቀዋል።

ቀደም ሲል የየካ አካባቢ ልጆች ብቻ የነበሩበትን ሁኔታ ሰፋ በማድረግ የበጎ ሥራ ዓላማ የገባቸውና ዓላማውን እየደገፉ ሌሎች በውጭ የሚገኙት ኢትዮጵያውን በመኖራቸው የበጎ አድራጊዎች የድጋፍ እጅ እንዲጨምር ምክንያት ሆኗል። ይህም ድርጅቱ በየወሩ አስቤዛ ድጋፍ የሚረዳቸው ሰዎች ቁጥር ከ50 ወደ 100 እንዲያድግ አስችሎታል፡፡

በተጨማሪም ዘጠኝ ሴቶች በንግድ ዓለም ገብተው ራሳቸውን ችለው እንዲሠሩ ለማስቻል የኤሌክትሪክና ላቀች ምጣድ፣ አንድ ኩንታል ጤፍ እና የገንዘብ ድጋፍ ተደርጎላቸው ሥራ እንዲጀምሩ የተደረገበትን ሁኔታም ጠቅሰዋል። እነዚህ ወገኖች ወደ ሥራ እንዲሠማሩ የተደረገው ራሳቸውን ችለው ቤተሰባቸውን ደግፈው ትርፋማ እንዲሆኑ ለማድረግ ታስቦ መሆኑን አስታውቋል። ለእነዚህ ወገኖችም በየጊዜው ድጋፍና ክትትል ይደረግላቸዋል ሲል ያስረዳል። በተጨማሪ ከውጭ ሀገር የሚላኩት እና እዚህም የሚሰበሰቡትን አልባሳት ለእናቶች፣ ለአባቶች እና ለአቅመ ድካሞች ለሁሉም በሚሆን መልኩ እንደሚያከፋፍሉ ይናገራል።

ድርጅቱ አሁን ላይ በቋሚነት በየወሩ ለተለያዩ ሸቀጦች መግዣ የሚውል /አስቤዛ/ ድጋፍ ከመስጠት ባሻገር የአቅመ ደካሞችን ቤት በማደስ፣ በከፍተኛ ደረጃ በህመም ምክንያት ተጎድቶ የነበረን ልጅ ለህክምናና ለመድሃኒት የሚሆን አንድ መቶ ሺህ ብር የሚገመት የገንዘብ ወጪን በመሸፈን እና መሰል በርከት ያሉ የበጎ አድራጎት ተግባራት ሥራዎችን እየሠራ መሆኑን አብራርቷል፡፡

እነዚህ መልካም እጆች በጣም የተቸገሩ ጠዋሪ ቀባሪ የሌላቸውን ወገኖች እቅፍ ድግፍ አርገው መያዛቸውን ጠቅሶ፣ ድጋፍ የሚፈልጉ ወገኖች እያደር እየበዙ ቢመጡም፣ ያለማቋረጥ ለአራት ዓመታት በየወሩ ለእኒህ ችግረኛ ወገኖቻችን እጆች በፍቅር እንደተዘረጉ ናቸው ብሏል። ማህበሩ በቋሚነት ከሚያደርገው ድጋፍ በተጨማሪ በዘመን መለወጫ፣ በገና፣ በትንሳኤ እና በአረፋ በዓላት ለተወሰኑ ሰዎች የሠብዓዊ ድጋፍ እንደሚያደርግም ገልጿል።

አቶ ሆርዶፋ ፍሰሃ አንዱ የበጎ አድራጎቱ ድርጅቱ ተጠቃሚ ናቸው። አቶ ሆርዶፋ ምንም ሥራ የሌላቸውና ጡረተኛ እንደሆኑ ይናገራሉ። የሚላስ የሚቀመስ አጥተው የሚገቡበት ባጡ ሰዓት ድርጅቱ በነፍሳቸው እንደደረሰላቸው አስታውሰው፣ ጤፍ፣ ቡና፣ ሽሮ፣ ዘይት እና መሰል ድጋፎች በየወሩ እንደሚደረግላቸው ይናገራሉ። ሌላ የሚደርስላቸው ሰው ስለሌላቸው ያገኙትን ቆጥበው እንደሚጠቀም የሚናገሩት አቶ ሆርዶፋ ፤ የማህበሩ አባላት ከልባቸው አመስግነው አይጠግቡም።

ሌላኛዋ የበጎ አድራጎት ተጠቃሚ ወይዘሮ አበቡ ነዶ ናቸው። በልምና እንደሚተዳደሩ የሚናገሩት ወይዘሮ አበቡ ‹‹ምንም ነገር አልነበረኝም ፣ ቤትም የለኝም ፤ ሰው ምግብ ሲያመጣልኝ ብቻ ነው እመገብ የነበረው›› ይላሉ። አሁን የበጎ አድራጎት አገልግሎቱ ተጠቃሚ መሆናቸውን ጠቅሰው፣ በየወሩ ጤፍ፣ ሽሮ እና ዘይት እንደሚያገኙ አስታውቀዋል። እግዚአብሔር ማህበሩን አብዝቶ ይባርከው ሲሉም መርቀዋል፡፡

ድርጅቱ የበጎ አድራጎት ሥራ ከተጀመረ በኋላ ይህንን የበጎ ተግባሩን ያዩ የአካባቢው ልጆች በአብሮነት እንዲበዙና እንዲሰባሰቡ እያደረገ ይገኛል የሚለው አቶ ቴዎድሮስ፤ ‹‹በአሁኑ ወቅትም ሥራዎቻችንን እያዩ አምነታቸው እየጨመረ የመጡ ብዙ ሰዎች አሉ ብሏል። የእነዚህ ዜጎች ቁጥር እየበዛ በመምጣቱ ተደራሽነትንም የበለጠ እየሰፋ እንዲሄድ ምክንያት ሆኗል›› ይላል ፡፡

‹‹የየካ ልጆች ይህን አገልግሎት የሚፈጽሙት አንዳችም ክፍያ ሳይኖር በነጻ ነው። ሁላችንም የግል ሥራ ያለን ነን፤ አቅመ ደካሞችን የምናገለግለውም ደስ እያለን በደስታ ስሜት ነው። ይህ ሥራ በዋናነት የምንሠራው የእግዚአብሔርን በረከት ለማግኘት፣ እንጂ ለትርፍ አይደለም ሲልም ተናግሯል። የአካባቢው ልጆች ለአንድ በጎ ዓላማ ተሰባሰበው ይህን የመሰለ ሥራ መሥራት መቻላቸው ለቀጣዩ ትውልድ እጅግ ጠቃሚ ጠቃሚ መሆኑንም ተናግሯል፡፡

‹‹የየካ በጎ አድራጎት ድርጅት ከዘር ፣ ከሃይማኖት እና ከፖለቲካ ነጻ የሆነና ሁሉንም በእኩልነት የሚያይ ለተረጂዎች መድረስ በሚገባ ሁኔታ ለመድረስ ነው የሚሠራው›› የሚለው ቴዎድሮስ፤ በባህርማዶዎቹ የየካ ልጆች ተጠንስሶ እዚያ ባሉት አባላት ተደግፎ ወገኖቹን እየደገፈ ያለ ድርጅት መሆኑን አጫውቶናል። ‹‹ሥራውን ለመጀመር ስናስብ አንድ ሺ430 ቤቶችን ጎብኘተናል፤ የሠራነውን የዳሰሳ በቪዲዮ በመቅረጽ ውጭ ላሉት የየካ አካባቢ ልጆች ላክነው፤ እነሱም ያን ተመለከቱት፤ ድሮ የሚያውቋቸው ነገር ግን የጠፉባቸው እናትና አባቶችን፣ በልጅነት የሚያውቋቸው ሰዎች ታመው ፣ ተርበው እና ታርዘው ተመልክተው በእጅጉ አንብተዋል›› ሲል አስታውሷል፡፡

ይህም ደግሞ ቀድሞ የታሰበው ሃሳብ እንዲቀየር ሰፋ አድርገን እንድናይ አስችሎናል ሲል ይገልጻል። በትንሹ የተጀመረው የበጎ ፈቃድ ሥራ አሁን ላይ ተጠናክሮ እንዲያድግና ለብዙዎች እንዲተርፍ ምክንያት ሆኗል ሲልም አብራርቷል፡፡

አቶ ቴዎድሮስ ‹‹ድርጅቱ እንኳን ተቋቋመ፤ ምንም አይነት ጥሪት፣ አንድም ደጋፊ ቤተሰብ የሌላቸውና የዕለት ጉርሳቸውን ከሰው እጅ እየጠበቁ የሚኖሩ ብዙ ሰዎች መኖራቸውን መገንዘብ ችለናል። ድርጅቱ በብዙ መልኩ ለተቸገሩ፣ የሚደርስላቸው ላጡ ሰዎች እየደረሰ ነው›› ይላል።

የዳሰሳ ጥናቱን ጠቅሶ ችግሩ በጣም ሰፊ መሆኑን ገልጿል፣፡ ከእለት ጉርስ በዘለለ የጤና ችግርም እንዳለ ያመለከተው አቶ ቴዎድሮስ፣ ችግሩ እንደሀገር ያለ ቢሆንም፣ በየአካባቢያችን ያለውን ችግር ዳስሰንና ደርሰን አልጨረስንም ብሏል። በተቻለ መጠን እገዛና ድጋፍ ማድረግ እንደሚያስፈልግም አስገንዝቧል።

አቶ ቴዎድሮስ እንዳስታወቀው፤ በቀጣይ ድርጅቱ በውጭ ሀገራት ያሉትን የአባላት ቁጥር በመጨመር ተጨማሪ ገቢ ለማግኘት የሚያስችሉ ሥራዎች ለመሥራት አቅዶ እየሠራ ነው። ድርጅቱ ባይደርስላቸው በሕይወት መኖራቸው የሚያጠራጥር አንዳንድ ተረጂዎች አሉ። እነዚህን ሰዎች ለመርዳት የድርጅቱ መኖር የግድ ይላል። ችግሩ ያላለቀ ስላልሆነና የሚያቆም እስካልሆነ ድረስ ድርጅቱ ከሚያደርገው ድጋፍ ወደ ኋላ አይልም።

ወደፊትም ይህን ሰፊ ችግር ለመፍታት ውጭ ሀገር ያሉትን የማህበሩ የአባላትን ቁጥር ለመጨመር እየተሠራ መሆኑን ገልጾ፣ በሀገር ውስጥ ባሉ አባላትም እንዲሁ የገቢ አቅምን ለመጨመር ባለሀብቶች እና የአካባቢውን ኤምባሲዎች በመጠየቅ ጭምር እንቅስቃሴዎች እየተደረጉ መሆናቸውን አመልክቷል። ችግሩ ሰፊ መሆኑን በመጥቀስም፣ ከመንግሥትም ሆነ ከሌሎች አካላት ለድርጅቱ ድጋፍ እንዲያደርግለትም ጠይቋል። የድርጅቱ ተደራሽነት የበለጠ እንዲሰፋ ሁሉም ሰው በሚችለው መጠን ከድርጅቱ ጎን እንዲቆምም ጥሪ አስተላልፈዋል፡፡

ወርቅነሽ ደምሰው

አዲስ ዘመን ሐምሌ 12/2016 ዓ.ም

 

 

Recommended For You