ብዙዎች እንደሚሉት፤ በዚች ዓለም ውስጥ ስኬታማ ሆኖ ለመኖር እራስን ማጠናከርም ሆነ ማዳከም የሚፈጠረው በአእምሮ አጠቃቀማችን ልክ ነው፡፡ ያለውን አቅም በአግባቡ የማይጠቀም ሰው ደካማ ነው ሊባል ይችላል። የሚሆነውንና የሚችለውን ፈልጎ የማግኘት ጉዳይ ካልሆነ በቀር በተፈጥሮ ደካማ ሆኖ የተፈጠረ ሰው የለም፡፡ ወጣቶችም ይህን በውል መረዳት አለባቸው ፡፡ ተስፋ መሰነቅ ለወጣቶች ትልቅ ጉልበት ይሆናል፡፡ ጉልበት የሚሆነው ግን በዕውቀት ሲመራ ነው።
ወጣቶች ስኬታማ ለመሆን በመጀመርያ የራእይ ሰው መሆን እንዳለባቸው ብዙዎች ያነሳሉ፡፡ ራእይ የለሽ ሰው ካለበትና ከደረሰበት አልፎ ለመሄድ አይፈልግም ፡፡ ይህ የሚሆነው ዓይኑ የተተከለው በገሃድ በሚታየው ላይ ብቻ በመሆኑና በዓይነ ህሊናው የሚያየው እይታ ስለሌለው ነው ፡፡ ባለ ራእይ ሰው ባለበት ሳይወሰን ወደ አዲስ ነገር ለመግባት ይገሰግሳል ፡፡
ህልም ፤ተስፋ እና ትጋት በአንድ መንፈስ ከሄዱ መጨረሻቸው ድልና ስኬት ነው የሚባለው እንዲሁ ዝም ተብሎ አይደለም፡፡ ህልማቸውን ሰንቀው በትጋት የተራመዱ እና የስኬት ማማ ላይ የተቀመጡ ብዙዎቹ ስላሉ እንጂ። ዛሬ ስለ ስኬት ማንሳታችን ያለምክንያት አይደለም። የዚህ ሳምንት የወጣቶች አምድ እንግዳችን የማህበረሰብ ልማት (ኢንተርፕራይዝ) መሥራችና ሥራ ፈጣሪ የሆነው ወጣት ሀብተአብ አርጋው በመሆኑ አንጂ።
ወጣት ሀብተአብ ተወልዶ ያደገው በሲዳማ ክልል አለታ ጩኮ ወረዳ ነው። ትምህርቱን ለመከታተል በሶስት ዓመቱ የትውልድ ቀየውን ለቆ ልጅነቱን ሃዋሳ ከተማ ላይ ያሳለፈው ሀብተአብ የመጀመሪያና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን በሀዋሳ ከተማ ተከታትሎ ለከፍተኛ ትምህርቱ በትውልድ ከተማው ሃዋሳ ወደሚገኘው የሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ በማቅናት በኤሌክትሪካልና ኮሚፒዩተር ምህንድስና በመጀመሪያ ዲግሪ ተመርቋል።
በልጅነቱ በትምህርት አቀባበሉ ጎበዝ ከሚባሉ የደረጃ ተማሪዎች መካከል እንደነበር የሚናገረው ሀብተአብ፤ ከአንደኛ ክፍል እስከ አስረኛ ክፍል አንደኛ በመውጣት እንዳሳለፈ በዚህ ምክንያት በመምህራን ተወዳጅ ተማሪ እንደነበር የልጅነት የትምህርት ቆይታውን በማስታወስ ይናገራል።
በዩኒቨርሲቲ በነበረው ቆይታ ከመደበኛ ትምህርቱ ባሻገር ተማሪዎች ከዩኒቨርሲቲ ሲወጡ ምን መሥራት እንዳለባቸው? እንዴት ሥራ መፍጠር እንደሚችሉ? የቢዝነስ ሃሳብ ያላቸው ወጣቶች እንዴት ቢዝነሰቸውን መምራት እንደሚገባቸው? ለማስገንዘብ የሚሰጡ የተለያዩ ሥልጠናዎችን በንቃት ይሳተፍ እንደነበር የሚናገረው ወጣት ሀብተአብ፤ የወሰዳቸው ስሥልጠናዎች ዛሬ ላለበት የሕይወት ጎዳና መሠረት የሆነው እንደሆነ ይናገራል።
“በዚህ የሥልጠና ወቅት ነው ሁለት የቢዝነስ ሃሳቦች የመጡልኝ” የሚለው ሀብተአብ የመጀመሪያ የማስታወቂያ ድርጅት መመሥረት ሲሆን ሁለተኛ በተለይ በገጠሩ ማህበረሰብ ዘንድ ያለውን የንፁህ ውሃ ተደራሽነት ችግር ለመቅረፍ የሚያስችል ሃሳብ ያለው ድርጅት የመመሥረት ውጥን ነበር ይላል።
“በ2013ዓ.ም የዩኒቨርሲቲ ትምህርቴን በማጠናቀቅ ወደ ሥራ ለመሠማራት ወደ ተለያዩ የግልና የመንግሥት ተቋማት በመሄድ የቅጠሩኝ ጥያቄ ባቀርብም አወንታዊ ምላሽ ማግኘት አልቻልኩም ነበር” የሚለው ወጣት ሀብተአብ፤ በዚህን ወቅት ነው ለምን ሥራ ከሚጠብቅ የሥራ ሃሳቦቼን ወደ ተግባር በመለወጥ የራሴን ሥራ አልጀምርም የሚል ሃሳብ የመጣልኝ” ይላል።
በዚህን ወቅት በውጭ ሀገር ከሚገኙ ከተለያዩ ድርጅቶች ጋር ግንኙነት ለመፍጠር ጥረት ማድረግ እንደጀመረ የሚናገረው ወጣቱ፤ ፕራይዝ በተሰኘውና መቀመጫው ሳንፍራንሲስኮ አሜሪካን ከሚገኝና የውሃ-ወለድ በሽታዎችን ለመቀነስ የሚያግዙ ቁሳቁሶችን (የውሃ ማጣሪዎች) እና የግንዛቤ ፕሮግራሞችን የንፁህ ውሃ አቅርቦት ውስንነት ባለባቸው ቦታዎች ለማዳረስ አልሞ የሚንቀሳቀስ ተቋም ጋር በመነጋገር ባገኘው የ20ሺህ የአሜሪካ ዶላር የፋይናንስ ድጋፍ (vital water purifier) የሚል ስያሜ የተሰጠው ድርጅት በመቋቋም ሥራውን ስለመጀመሩ ይናገራል።
ወጣት ሀብተአብ እንደሚናገረው፤ በኢትዮጵያ ከ62 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ንፁህ የመጠጥ ውሃ አያገኝም፣ በዓመት ከዘጠኝ ሺህ በላይ የሚሆኑ ህፃናት በውሃ ወለድ በሽታ ሕይወታቸውን ያጣሉ፣ ይህ ማለት በሀገሪቱ በአማካይ ከ 17 ህፃናት አንዱ በውሃ ወለድ በሽታ ይሞታል እንደማለት ነው። ከዚህ አኳያ እነዚህን ችግሮች ሁሉ በመንግሥት አቅም የማይፈቱ በመሆናቸው ችግሩን ለመቅረፍ የራሴን ድርሻ ለማኖር ነው ወደዚህ ሥራ የገባሁት ይላል።
መንግሥት 80 በመቶ ለሚሆነውና በገጠር ለሚኖረው ዜጋ ሁሉ መሠረተ ልማት ዘርግቶ ውሃም ሆነ ሌሎች አገልግሎቶችን ተደራሽ ለማድረግ ከፍተኛ ሀብትና ረዥም ጊዜ ይጠይቀዋል፡፡ ነገር ግን ማህበረሰቡ ንፁህ ውሃ የሚፈልገው ዛሬ ነው፤ ስለዚህ ወጪ ቆጣቢና አማራጭ የሚሆኑ መንገዶችን በመፈለግ ድርጅቱ ንፁህ ውሃ ለማህበረሰቡ ለማድረስ የተለያዩ ጥረቶችን እንደሚያደርግ ይናገራል።
የድርጀቱ ዓላማ በተለይ በሀገሪቱ ገጠራማ አካባቢዎች የሚኖሩ የንፁህ የመጠጥ ውሃ የማያገኙ ኢትዮጵያውያንን ተደራሽ ማድረግ እንደሆነ የሚናገረው ሀብተአብ፤ ከዚህ አኳያ የተለያዩ የፋይናንስ ምንጮችን በማፈላለግ የውሃ ማጣሪያ ቁሳቁሶችን በማቅረብ ዜጎች የንፁህ ውሃ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ያደርጋል ይላል።
እንደ ወጣቱ ገለፃ፤ ህብረተሰቡን ስለ መሠረታዊ ንፅህናና የውሃ አጠቃቀም ማስተማር ከድርጅቱ ሥራዎች አንዱ ነው። በዓለም አቀፍ ደረጃ የተሠሩ ጥናቶች እንደሚያመለክቱት የውሃ ማጣሪያ መጠቀም 63 በመቶ የውሃ ወለድ በሽታን ይቀንሳ፤ በተጨማሪም ህብረተሰቡን ስለ መሠረታዊ የጤና አጠባበቅ ማስተማር 40 በመቶ ከውሃ ወለድ በሽታ ጋር ተያይዞ ከሚመጡ በሽታዎች ይከለከላል፤ ከዚህ አንፃር ድርጅቱ የተለያዩ የግንዛቤ መፍጠር ሥራዎችን እንደሚሠራ ይናገራል።
ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ውሃ በቀላሉ በውሃ ማጣሪያ ተጣርቶ ለመጠጥ መቅረብ የሚችል እንደሆነ የሚናገረው ወጣት ሀብተአብ፤ ከዚህ አኳያ ነው ድርጅቱ የተለያዩ ጥናቶች በመሥራት የውሃ ማጣሪያ በማቅረብ ህብረተሰቡ በቀላሉ የንፁህ መጠጥ ውሃ ተጠቃሚ ማድረግ ይቻላል በሚል የሚንቀሳቀሰው ይላል።
እንደ ወጣት ሀብተአብ ገለፃ፤ ለእያንዳንዱ ሰው የውሃ ማጣሪያ ገዝቶ ማቅረብ የማይቻል በመሆኑ ድርጅቱ በገጠር ያለው ማህበረሰብ የውሃ ማጣሪያ ተጠቃሚነቱ እንዲያድግ ፈጠራ በታከለበት መልኩ የተለያዩ ሥራዎችን እንደሚሠራ ይናገራል፡፡
ለአብነት ከጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎች ጋር በመነጋገር እነርሱ ለማህበረሰቡ ያላቸውን ቅርበት በመጠቀም ህብረተሰቡ ስለ ውሃ ማጣሪያ ጥቅም አውቆ ለመጠቀም ቁርጠኝነት እንዲኖረው ለማስቻል እንደሚሠሩ ይናገራል።
ድርጅቱ በሁለተኛ ደረጃ በገጠር ለሚገኙ አነስተኛ ሱቆች ማጣሪያውን በማቅረብ ህብረተሰቡ በአነስተኛ ዋጋ እንዲያገኝ የሚያስችል መንገድ እንደሚከተል የሚናገረው ሀብተአብ፤ ድርጅቱ በርካሽ ዋጋ የውሃ ማጣሪያዎች በማቅረብ ህልውናውን ከግብረሰናይ ድርጅቶች በሚያገኘው የፋይናንስ ድጋፍ እንደሚያስቀጥል ይናገራል።
ለብዙዎች የሚደርስ ሥራ ለመሥራት ከልጅነት ጀምሮ ህልም ነበረኝ የሚለው ወጣት ሀብተአብ፤ ኢትዮጵያ ውስጥ ብዙ ችግሮች አሉ፡፡ እነዚህን ችግሮች ለመቅረፍ ደግሞ በቀላሉ ፋይናንስ ማግኘት አይቻልም፤ ስለዚህ እነዚህን ችግሮች ወደ ዕድል መቀየር እንዴት ይቻላል ብሎ በመነሳት ለብዙዎች እፎይታ የሚሆን ሥራ ለመሥራት ከተለያዩ የውጭ ድርጅቶች ጋር በመጻጻፍና ድጋፍ በማግኘት ነው እውን ማድረግ የቻልኩት ይላል።
ወጣት ሀብተአብ እንደሚናገረው፤ ኢትዮጵያ ውስጥ በአንድ ቤተሰብ ውስጥ በአማካይ አምስት ሰው ይኖራል ተብሎ ይታሰባል፤ ከዚህ አኳያ እስከአሁን በፕሮግራሙ ለ313 ቤተሰቦች መድረስ ተችሏል፤ ይህ ማለት 1878 ስዎች የንፁህ ውሃ ተጠቃሚ እንዲሆኑ በማድረግ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸውን ሰዎች ከተበከለ ውሃ ጋር ተያይዞ ከሚመጣ በሽታ ማዳን ስለመቻሉ ይናገራል።
እንዲህ አይነት የማህበረሰብ ኢንተርፕራይዝ የፋይናንስ ድጋፍ በምን መልኩ ማግኘት እንዳለበት የሚያመለክቱ ሥልጣናዎችን ከተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር በመተባበር እንወስዳለን የሚለው ሀብተአብ፤ ዘንድሮ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከሚገኙ የማህበረሰብ የልማት ኢንተርፕራይዞች ጋር በመወዳደር ምርጥ 84 ውስጥ በመግባት የፋይናንስ ድጋፍ ማግኘት እንደቻሉ ይናገራል።
በሚቀጥሉት ወራት እስከ አስር ሺህ ሰዎችን የንፁህ ውሃ ተጠቃሚ ለማድረግ ውጥን ይዞ እየተንቀሳቀሰ እንደሚገኝ የሚናገረው ሀብተአብ፤ ፕሮጀክቱ በአሁኑ ወቅት በሲዳማ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች ትኩረትን ያደረገ ቢሆንም በሚቀጥሉት ዓመታት ከፍተኛ የውሃ ችግር ወዳለባቸው የኢትዮጵያ አካባቢዎች በማተኮር የመሥራት እቅድ እንዳለው ይናገራል።
ኢንተርፕራይዙ በአሁኑ ወቅት 7 ለሚሆኑ ግለሰቦች የሥራ ዕድል እንደፈጠረ የሚናገረው ወጣት ሀብተአብ፤ ይህ ማለት ድርጅቱ ያለው ሀብት ውስን በመሆኑ የሠራተኛው ቁጥር አነስተኛ ሆነ እንጂ በሚቀጥሉት ዓመታት በእቅድ ደረጃ ያሉ ፕሮጀክቶች መሬት ላይ ወርደው በሚተገበሩበት ጊዜ ከፍተኛ ቁጥር ላላቸው ሰዎች የሥራ ዕድል መፍጠር እንደሚቻል ያስረዳል።
“በምንሰራቸው ሥራዎች የተለያዩ ዓለም አቀፍ ሽልማቶችን ማሸነፍ ችለናል” የሚለው ወጣት ሀብተአብ፤ ከዚህ ባሻገር በተለያዩ የዓለም ሀገራት ከሚገኙ ተመሳሳይ ሥራ ከሚሠሩ የማህበረሰብ የልማት ድርጅቶች ጋር በመገናኘት የልምድ ልውውጥ በማድረግና ሥልጠናዎችን በመውሰድ የተሻለ ተቋም ሆኖ ለመገኘት ያላሰለሰ ጥረት እያደረገ እንደሚገኝ ይናገራል።
ሀብተአብ እንደሚናገረው፤ ድርጅቱ ከስያሜው ጀምሮ ለማህበረሰቡ የግድ አስፈለጊ የሆኑ ነገሮችን የሚያቀርብ ነው። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በየጊዜው በሚያወጣቸው ሪፖርቶች መነሻ በኢትዮጵያ በተለይ ከፍተኛ የንፁህ መጠጥ ውሃ ችግር እንዳለ ያሳያል፡፡ ይህ ማለት በሕይወት ለመኖር ከሚያስፈልጉ መሠረታዊ ከሆኑ ነገሮች አንዱ ተጓድሏል ማለት ነው። ከዚህ አኳያ ቫይታል የንፁህ ውሃ አቅርቦት ድርጅት በአቅሙ ችግሩን ለማቅለል እንደሚሠራ ይገልጻል።
ድርጅቱ በሚቀጥሉት ጊዜያት፤ አሁን ከሚሰጠው አገልገሎት በተጨማሪ በገጠር በፀሀይ ሃይል የሚሠሩ የሶላር መብራቶችን ተደራሽ ለማድረግ እቅድ እንዳለው የሚናገረው ወጣቱ፤ ገጠር ያለው ማህበረሰብ የኑሮ ዘይቤው ዘመናዊ እንዲሆን ጥረት እንደሚያደርግ ይናገራል።
ወደፊት ባሉት ጊዜያት በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ ሀገር ከሚገኙ መንግሥታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች ጋር ጥምረት በመፍጠር እንደ ውሃና መብራት ያሉ መሠረታዊ አገልግሎቶች ለህብረተሰቡ በስፋት ተደራሽ እንዲሆኑ ለማድረግ እቅድ አለን የሚለው ወጣት ሀብተአብ፤ በሌላ በኩል መንግሥትም እንዲሁ መሠረተ ልማት ተደራሽ ማድረግ እንዲችል ቀላል መንገድ በማመላከት የተለያዩ ተግባራትን ለማከናወን ውጥን እንዳለው ይናገራል።
በመጨረሻም ወጣት ሀብተአብ፤ ባስተላለፈው መልዕክት ነገሮችን የምናይበት መንገድ መቀየር አለበት ይላል። አንድ ነገር ለማድረግ ሲታሰብ ሁል ጊዜ ዋጋ መክፈል ይኖረዋል፡፡ ፀንቶና ተግቶ በመሥራት የማይሳካ ነገር ግን የለም፤ እችላለሁ የሚል እምነት ሊኖር ይገባል ይላል።
የኢትዮጵያን ነገ ብሩህ የማድረግ ሃላፊነትና ግዴታ ያለባቸው የዛሬው ትውልድ ወጣቶች በመሆናቸው ለዓላማቸው መሳካት መክፈል ያለባቸውን መስዋዕትነት ሁሉ መክፈል አለባቸው፡፡ የነገው ራዕያቸውን ከግብ ለማድረስ ቀን እና ሌሊት ሳይሉ እና ተስፋ ሳይቆርጡ መትጋት እንደሚገባቸው ተናግሮ፤ በተጨማሪነት የተለያዩ የክህሎት ሥልጠናዎችን በመውሰድ ያላቸውን ሃሳብ መሸጥ የሚችሉ መሆን እንደሚገባቸው፤ ያስገነዝባል።
ክብረአብ በላቸው
አዲስ ዘመን ሐምሌ 12/2016 ዓ.ም