ኢትዮጵያውያን ሳይማሩ ልጆቻቸውን በማስተማር ይታወቃሉ። ብዙ ውጣውረዶችን አልፈው፤ ብዙም ዋጋ ከፍለው ልጄ ከእኔ የተሻለ መሆን አለበት ብለው ልጃቸውን ያስተማራሉ፤ እያስተማሩም ይገኛሉ። ልጆቻቸውም በየመስኩ ተሰማርተው ከራሳቸውና ከቤተሰባቸውም አልፈው ለአገርና ለወገን አለኝታ ሆነዋል። የዕለቱ እንግዳችንም ከዚሁ ማኅበረሰብ እንደመገኘታቸው በተማሩበት ሙያ ሳይማር ያስተማራቸውን ቤተሰብ፣ ማኅበረሰብና አገርን በሕክምናው ዘርፍ እያገለገሉ ይገኛሉ።
እንግዳችን ተወልደው ያደጉት በአዲስ አበባ ከተማ መሀል መርካቶ ነው። የአንደኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ዑመር ሰመተር፣ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ደግሞ አዲስ ከተማ አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተከታትለዋል፤ የከፍተኛ ትምህርታቸውንም በሕክምና ዘርፍ በቀድሞ አጠራሩ በጅማ ጤና ሳይንስ ኢንስቲትዩት ተምረዋል። ሕክምናን ተምረው ሕክምና ውስጥ የኖሩት የዕለቱ እንግዳችን ዶክተር መሀመድ ኑሪ ዑስማን የኢትዮጵያ መድሃኒት ፋብሪካን ጨምሮ የሜዲቴክ ኢትዮጵያ የሥራ አስፈጻሚ ቦርድ ሰብሳቢ እና ዋና ሥራ አስፈጻሚ ናቸው።
ሙሉ ሕይወታቸውን በትምህርትና በሥራ ያሳለፉት ዶክተር መሀመድ፤ በተለየ ሁኔታ ለሕክምና ሥራቸው ልዩ ፍቅር አላቸው። ይህ ለምን ሆነ ካላችሁ፤ ሕክምና መማራቸው አንዱ ምክንያት ሲሆን፤ ሌላው ደግሞ ገና ከጅምሩ የአንደኛ ዓመት ተማሪ እያሉ ወላጅ እናታቸውን በመድሃኒት እጦት ማጣታቸው ነው። በወቅቱ ወላጅ እናታቸው የሚያስፈልጋቸው መድሃኒት በአገር ውስጥ አልነበረም። አቅም ኖሮ ከውጭ መግዛት አልተቻለምና እናት ወደማይቀረው ዓለም ተሰናብተዋል። ይህ ቁጭት የገባቸው ዶክተር መሀመድ፤ ንግድ ውስጥ በመግባት በተለይም ለማኅበረሰቡ አስፈላጊ የሆኑ የመድሃኒት አይነቶችን በማቅረብ ዜጎችን ለመታደግ ሲነሱ በልበ ሙሉነት ነበር።
ማኅበረሰቡን ይጠቅማል ለአገር ይበጃል ያሉትን በሙሉ ያለ ስስት የሚያካፍሉት ዶክተር መሀመድ፤ ተማሪ እያሉ ጀምሮ ጎበዝና ታታሪ መሆናቸውን ይገልጸሉ። ይህም በጥረታቸው ዛሬ ካሰቡት እንዲደርሱ አስችሏቸዋል። የሕክምና ትምህርት ለመማር ጅማ ጤና ሳይንስ ኢንስቲትዩትን የተቀላቀሉት ገና በ16 ዓመት ዕድሜያቸው ነበር። ይህ የሆነበት ዋናው ምክንያትም ከአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ጀምሮ ጎበዝ ተማሪ በመሆናቸው በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ሁለት ጊዜ ከክፍል ወደ ክፍል የመዘዋወር ዕድል አግኝተዋል።
በወቅቱ ከፍተኛ ውጤት በማምጣትም የሕክምና ትምህርት በመማር አራት ነጥብ አምጥተው አጠናቅቀዋል። ይህ ውጤትም ጎበዝና ታታሪ በመሆናቸው የተቀዳጁት ድል እንጂ በዘፈቀደ የተገኘ ዕድል አይደለም። የሕክምና ትምህርታቸውን ለሰባት ተከታታይ ዓመታት ተከታትለው በከፍተኛ ማዕረግ ሜዲካል ዶክተር የሆኑት ዶክተር መሀመድ፤ ባስመዘገቡት ከፍተኛ ውጤት መሰረት በኢንስቲትዩቱ የማስተማር ወርቃማ ዕድል አግኝተዋል።
ይሁን እንጂ የቅጥር ደብዳቤያቸውን በተቀበሉ ማግስት ወደ አዲስ አበባ ያቀኑት ዶክተር መሀመድ፣ ተወልደው ያደጉባት፣ የተማሩባትና ክፉ ደጉን የለዩባት አዲስ አበባ በዋዛ ልትለቃቸው አልፈቀደችም። እናም ወደ ኢንስቲትዩቱ ሳይመለሱ ንግድ ውስጥ ገቡ። ጅማ ጤና ሳይንስ ኢንስቲትዩት መምህርነትን ባይቀበሉም ዛሬ የጅማ ዩኒቨርሲቲ የቦርድ ዳይሬክተር ሆነው እያገለገሉ ይገኛሉ።
‹‹ንግድ ውስጥ እንድገባ ምክንያት የሆኑኝ አብሮ አደግ ጓደኞቼ ናቸው›› የሚሉት ዶክተር መሀመድ፤ ከትምህርት ሲመለሱ ዩኒቨርሲቲ መግባት ያልቻሉ ጓደኞቻቸው ሀብታም ነጋዴ ሆነው ነው አገኟቸው። ይህን ጊዜ ሕይወታቸውን መለወጥና ሳይማር ያስተማራቸውን ቤተሰብ ማገዝ የሚችሉት በመምህርነት ደመወዝ ሳይሆን ነጋዴ መሆን ሲችሉ እንደሆነ በማመን ጓደኞቻቸውን በዕውቀት ማገዝ ጀመሩ። በአንድ አጋጣሚ ዱባይ በማቅናት በሙያቸው መሥራት የሚያስችሏቸውን ሁኔታዎች በማመቻቸት ሮያል ፋርማሲን ከፈቱ።
‹‹ቀስ በቀስ እንቁላል በእግሩ ይሄዳል›› እንዲሉ የንግድ ሥራቸውን በዕውቀት በመምራት ንግዳቸውን ማቀላጠፍ ያዙ። ‹‹ሮያል ፋርማሲን ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል አካባቢ መክፈቴ ውጤታማ አድርጎኛል›› ያሉት ዶክተር መሀመድ፤ ሥራውን በዕውቀት መምራት በመቻላቸው ታዋቂነትን በማትረፍ ከአስር ዓመት በላይ ገበያ ውስጥ ቆይተዋል። በወቅቱ የመድሃኒት እጥረት በከተማ ውስጥ በመኖሩ አስፈላጊ የሆኑ መድሃኒቶችን ከአስመጪዎች በመረከብ ፋርማሲው 24 ሰዓት ይሰራ ስለነበረ ምሽት ላይ ራሳቸው ይሸጡ እንደነበር ያስታውሳሉ።
ሮያል ፋርማሲ አሁን ለደረሱበት ደረጃ ትልቅ መሰረት የጣለ ስለመሆኑ አጫውተውናል። ‹‹በትምህርት ካገኘሁት ዕውቀት በተጨማሪ ሮያል ፋርማሲ ውስጥ በመሥራቴ እና ከማሕበረሰቡ ጋር በቀጥታ በመገናኘቴ ያካበትኩት ልምድ ዛሬ ለደረስኩበት ደረጃ ጠንካራ መሰረት ጥሎልኝ አልፏል›› በማለት ተናግረዋል። የሰሩትን ገንዘብ እንዲሁም ያገኙትን ዕውቅና ደምረው በሕክምናው ዘርፍ ሰፋፊ ሥራዎችን በመሥራት መድሃኒት አስመጪ የሆኑት ዶክተር መሀመድ፤ በወቅቱ ትልቅ የቢዝነስ ጉብኝት አግኝተዋል።
ጉብኝቱ አጠቃላይ የቢዝነስ ጉብኝት ሲሆን፤ በሕክምናው ዘርፍ ብቸኛ ተሳታፊ በመሆን ከአገር አገር በመጓዝ ለዘርፉ ጠቃሚ የሆኑ የተለያዩ መረጃዎችን ሰብስበዋል። ያኔ እንደዛሬው ዘመኑ በቴክኖሎጂ አልደረጀምና ሙሉ አቅማቸውን በመጠቀም ከየአገሩ የሰበሰቧቸውን ከ100 ኪሎ ግራም በላይ ካታሎጎችን በፖስታ ወደ አገር ቤት ልከዋል። በዚህም መድሃኒት አስመጪ የመሆን ዋንኛ ዓላማቸውን አሳክተዋል።
‹‹ዕውቀትን መሰረት በማድረግና ቁጭት በወለደው ከፍተኛ መነሳሳት የተጀመረው መድሃኒት የማስመጣት ሥራ ፍሬው ያማረ ነው›› ያሉት ዶክተር መሀመድ፤ ከፋርማሲው ጎን ለጎን ከዛሬ 25 ዓመት በፊት ሜዲቴክ ኢትዮጵያ መድሃኒት አስመጪና አከፋፋይ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበርን ማቋቋም ችለዋል። ሜዲቴክ ኢትዮጵያ የተለያዩ መድሃኒቶችን ጨምሮ አጠቃላይ ለሕክምና አገልግሎት የሚውሉ ግብዓቶችን በማቅረብ ይታወቃል። ሜዲቴክ ወደ ሥራ ሲገባ ነብስ አድን መድሃኒት ወይም በተለምዶ ግሉኮስ በአገሪቱ እጥረት የነበረ በመሆኑ በስፋት በማስገባት ለግልና ለመንግሥት ተቋማት በማቅረብ ፍላጎቱን መሙላት ችሏል።
በዕውቀትና ከልብ በመነጨ ፍላጎት የሚመራ ቢዝነስ አዋጭና ተመራጭ ነው የሚሉት ዶክተር መሀመድ፤ የሰው ኃይል ወሳኝ እንደሆነ በማመን አሉ የተባሉ ባለሙያዎችን በማፈላለግ እየቀጠሩ ሜዲቴክ ኢትዮጵያን በአጭር ጊዜ ከፍ ማድረግ ችለዋል። ሜዲቴክ ኢትዮጵያ ከጉልኮስ በተጨማሪ ኤች.አይ.ቪ ኤድስን በመከላከል ሥራ ውስጥ ትልቅ ድርሻ ነበረው። በሽታው በተስፋፋበት ወቅት ለመጀመሪያ ጊዜ የጸረ-ኤች. አይ. ቪ መድሃኒትን ሜዲቴክ ኢትዮጵያ ከመንግሥት ጋር በመሆን ለአራት ተከታታይ ዓመታት በብቸኝነት ሲያስመጣ ቆይቷል። በወቅቱ መድሃኒቱን ሳያገኙ ብዙዎች ቢያልፉም በርካቶችን በመታድግ ኢትዮጵያ ኤች.አይ.ቪ አስከፊ ከሆነባቸው አገራት ዝርዝር እንድትወጣ የበኩላቸውን ጉልህ አበርክቶ እንዳደረጉ ይጠቅሳሉ።
ሕክምና ተምረው ሕይወታቸውን ሙሉ ለሕክምና የሰጡት ዶክተር መሀመድ፤ የተለያዩ መድሃቶችን ወደ አገር ቤት በማስገባት በዘርፉ ጉልህ አስተዋጽኦ አበርክተዋል። ኢትዮጵያ ውስጥ ካሉ መድሃኒት አስመጪዎች ብዙ መድሃኒቶችን በማስመዝገብና በማስመጣት ቀዳሚ በመሆን በአሁኑ ወቅት 550 አይነት መድሃኒቶችን ማስመጣት ችለዋል። ይህም በኢትዮጵያ ምግብና መድሃኒት ባለስልጣን የተረጋገጠ መሆኑን ይናገራሉ።
ሙያዊ ዕውቀትን መሰረት አድርገው መድሃኒት በማስመጣት ቀዳሚ የሆኑት ዶክተር መሀመድ፤ በግል ካቋቋሙት ሜዲቴክ ኢትዮጵያ በተጨማሪ ኢትዮጵያ ውስጥ በመድሃኒት አቅርቦት ትልቅ ስም ያለውና ስድስት አስርት ዓመታትን ያስቆጠረውን አንጋፋውን የኢትዮጵያ መድሃኒት ፋብሪካን ጭምር ከመንግሥት ገዝተው የኢንቨስትመንታቸው አካል አድርገውታል።
ስለመድሃኒት ጠንቅቀው የሚያውቁት ዶክተር መሀመድ፤ የኢትዮጵያ መድሃኒት ፋብሪካንም በልኩ ያውቁት ነበርና ከዛሬ አስር ዓመት በፊት ጨረታውን አሸንፈው ፋብሪካውን የግላቸው ማድረግ ችለዋል። በአሁኑ ወቅትም የተለያዩ መድሃኒቶችን ወደ አገር ውስጥ ከማስመጣት ባለፈ በአገር ውስጥ በማምረት ጭምር ማኅበረሰቡ ጋር በስፋት መድረስ ችለዋል።
የኢትዮጵያ መድሃኒት ፋብሪካን ሲረከቡ ፋብሪካው ያመርታቸው የነበሩ መድሃኒቶችን በማስቀጠል እንዲሁም ተጨማሪና አገሪቷ ውስጥ እጅግ ተፈላጊ የሆኑ መድሃኒቶችን በመለየት በአዲስ መልክ ወደ ሥራ ገብተዋል። የመድሃኒት አይነቶችን ከማስፋት ባለፈም ዘመናዊ ማሽኖችን በማስመጣት ስራውን ማስፋት የቻሉት ዶክተር መሀመድ፤ ‹‹ከፍትፍቱ ፊቱ›› እንዲሉ የመድሃኒት ማሸጊያዎቹን ጭምር ባማረና ሳቢ በሆነ አቀራረብ መቀየር ችለዋል። መድሃኒት እንደማንኛውም ሸቀጥ እንዳልሆነና ትልቅ ጥንቃቄ እንደሚፈልግም አስረድተዋል።
እሳቸው እንዳሉት፤ ለመድሃኒት ፋብሪካው ማስፋፊያ በማድረግ ሰፋፊ ሥራዎችን እየሰሩ ሲሆን፤ ከአገር ውስጥ ባለፈም 25 በመቶ በአገር ውስጥ የሚመረቱ መድሃኒቶችን ወደ ውጭ በመላክ የአገሪቷን የውጭ ምንዛሪ ግኝት ለማሳደግ ትልቅ ራዕይ ሰንቀዋል። ለዚህም በቂሊንጦ ኢንዱስትሪያል ፓርክ የማስፋፊያ ቦታ አግኝተዋል። በኢትዮጵያ መድሃኒት ፋብሪካ ብቻ 125 የሚደርሱ የመድሃኒት አይነቶች የሚመረቱ ሲሆን፤ በቀጣይም በማስፋፊያው 200 የሚደርሱ ይሆናል። ፋብሪካዎቹ የተለያዩ መድሃኒቶችን እያመረቱ ይገኛሉ። ለአብነትም ሽሮፕ፣ ክኒን፣ ካፕሱሎች፣ ቅባት ነክ የቆዳ መድሃኒቶች፣ መርፌዎች፣ ሕይወት አድን ንጥረ መድሃኒቶችና ሌሎችም ተጠቃሽ ናቸው።
የተለያዩ ጥሬ ዕቃዎችን ከውጭ በማስመጣት በአገር ውስጥ ቀምመው የሚያመርቷቸውን መድሃኒቶች በአገር ውስጥ ለሚገኙ መድሃኒት አስመጪና አከፋፋዮች እንዲሁም ለመንግሥት በማቅረብ ማኅበረሰቡ ጋር ይደርሳሉ። ሜዲቴክ ኢትዮጵያ ከውጭ ወደ አገር ውስጥ የሚያስገባቸውን የተለያዩ መድሃኒቶች ለባለሙያዎች በማስተዋወቅ ማኅበረሰቡ ጋር መድረስ እንዲችል ያደርጋሉ። ይሁንና የ60 ዓመት ታሪክ ያለው የኢትዮጵያ መድሃኒት ፋብሪካ የሚያመርታቸው መድሃኒቶች ባላቸው ጥራት በስፋት የሚታወቁና ከውጭው ይልቅ እጅግ ተፈላጊ እንደሆኑ የተናገሩት ዶክተር መሀመድ፤ በዚህም ከፍተኛ ኩራት ይሰማቸዋል።
መድሃኒት ሲመረት በከፍተኛ ጥንቃቄ እንደሆነና ከፍተኛ ወጪ እንደሚጠይቅ የሚናገሩት ዶክተር መሀመድ፤ መድሃኒት ከሌሎች ምርቶች ጋር ሲነጻጸር በብዙ እጥፍ የሚከብድ ነው ይላሉ። ምክንያቱም 99 በመቶ ያህሉ ጥሬ ዕቃ ከውጭ አገር የሚመጣ በመሆኑ ዘርፉን ከባድ ያደርገዋል። ከአገር ውስጥ የሚጠቀሙት ውሃ ብቻ ሲሆን፤ ውሃውም ቢሆን ታክሞና የተለያዩ ሂደቶችን አልፎ መድሃኒት መስሪያ የሚሆን ነው።
በአገሪቱ ከነዳጅ ቀጥሎ መድሃኒት ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ የሚጠይቅ እንደመሆኑ እሳቸውም ይህን ችግር ለማቃለል ከፍተኛ ጥረት እያደረጉ ነው። በአሁኑ ወቅትም መድሃኒት ለማምረት የሚያስችሉና መሰረታዊ የሆኑ ጥሬ ዕቃዎችን በአገር ውስጥ ለማምረት እየሠሩ ሲሆን፤ እስከዚያው ግን ጥሬ ዕቃውን ከውጭ ማስመጣት የግድ ነው ብለዋል።
መንግሥት አሁን ላይ ለአምራች ኢንዱስትሪው የሰጠው ትኩረት የሚበረታታ እንደሆነ የጠቀሱት ዶክተር መሀመድ፤ ይሁንና በፋርማሲቲዩካል ዘርፍ እየተሰጠ ያለው ማበረታቻ ግን መሻሻል እንዳለበት ገልጸዋል። በተለይም የውጭ ምንዛሪ እጥረት ከፍተኛ ችግር በመሆኑ መንግሥት ለዘርፉ እየሰጠ ያለውን ትኩረት ይበልጥ ማሻሻልና ቅድሚያ በመስጠት ተደራሽነትን ማስፋት ይጠበቅበታል ይላሉ። መንግሥት ቦታ ከመስጠት ጀምሮ አስፈላጊ የሆኑ ማሽነሪዎችን ከቀረጥ ነጻ ማስገባት እንዲቻል በርካታ ድጋፎችን እያደረገ ይገኛል ሲሉ ጠቅሰው፤ ይሁንና ሕጎችን ተፈጻሚ ከማድረግ አንጻር አፈጻጸም ላይ ክፍተት ይታያልና ይህ ሊታረም ይገባል ባይ ናቸው።
በሚሠሩት ሥራ ውጤት ማስመዝገብ ተቀዳሚ ዓላማቸው የሆነው ዶክተር መሀመድ፤ ‹‹ውጤት ማስመዝገብ የሚቻለው ተነሳሽነት ያለውና የተነቃቃ ሠራተኛ ሲኖር ነው›› ይላሉ። ለዚህም የሰው ኃይልን በማብቃት ረገድ ትልቅ ትኩረት ሰጥተው ይሰራሉ። የኢትዮጵያ መድሃኒት ፋብሪካን በግላቸው ለማስተዳደር በተረከቡበት ወቅትም ሰራተኛ ሳይቀንሱ የሁሉንም የሠራተኞች ደመወዝ ከመቶ እጅ በላይ አሻሽለዋል። ይህም ሠራተኞች የሥራ ተነሳሽነት ኖራቸው እንዲሰሩ ከማድረግ ባለፈ ውጤት ማስመዝገብ አስችሏቸዋል።
የሰው ልጆች ከሕመማቸው የሚፈውሳቸውን መድሃኒት ሲያስመጡ፣ ሲያከፋፍሉና ሲያመርቱ የኖሩት ዶክተር መሀመድ፤ ሕክምና ተምረው ሕይወታቸውን ሙሉ ከሕክምናው ዘርፍ የተለዩ አይደሉም። ከሕክምናው በተጨማሪም የተለያዩ ኩባንያዎችን ያስተዳድራሉ። ከእነዚህም መካከል ከኢትዮጵያ መድሃኒት ፋብሪካ፣ ሜዲቴከ ኢትዮጵያ እና በጂቪ ጁልፋ ኢትዮጵያ (መድሃኒት አምራች) በተጨማሪ ቆንጆ ውሃ፣ እናት ኢንጂነሪንግ፣ ኤክሰለንስ ኮንስትራክሽን እና ሪልስቴት ይጠቀሳሉ።
እነዚህ እህት ኩባንያዎች አጠቃላይ ከሁለት ሺ ለሚልቁ ዜጎች የሥራ ዕድል በመፍጠር ለአገር አለኝታነታቸውን አስመስክረዋል። በቀጣይም በርካታ የሥራ ዕድል የመፍጠር ዕቅድ ያላቸው ዶክተር ሙሀመድ፤ የነብስ ጥሪያቸው ከሆነው የሕክምና ዘርፍ ውጭ የመስራት ብዙ ፍላጎት የላቸውም። ነገር ግን የሚሠሯቸው ተጓዳኝ ሥራዎች በሙሉ የሕክምናው ዘርፍ የሚያስፈልገውን ከፍተኛ ወጪ እንዲሚደግፉላቸው አጫውተውናል።
ለሰው መኖር የሕይወት ፍልስፍናቸው የሆነው ዶክተር ሙሀመድ፤ ‹‹የኢትዮጵያዊነት ዋና መገለጫ መረዳዳት ነው›› ይላሉ። ያለ ስስት የተሰጣቸው ጸጋ መልካምነት በመሆኑ ለተቸገሩ በመድረስ ለብዙዎች የጓዳቸው ሙላት ሆነዋል። በግልም ሆነ በድርጅት ስም በሚሰሩት በጎ ሥራ እንዲሁም ባስመዘገቡት ውጤት መንግሥታዊና መንግሥታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች ከ100 በላይ የዕውቅና ሰርተፍኬቶችን አግኝተዋል።
ዶክተር መሀመድ፤ ግብራቸውን በወቅቱና በታማኝነት ከመክፈል ባለፈ መንግሥታዊ ለሆኑ ማንኛውም ጥሪዎች በቀዳሚነት ምላሽ እንደሚሰጡ ይናገራሉ። ከመደበኛ ሥራቸው ባልተናነሰ ማኅበራዊ ኃላፊነትን በመወጣት ረገድ ጉልህ አበርክቶ እንዳላቸው ቢገልጹም፣ ‹‹ቀኝ እጅህ ሲሰጥ ግራህ አይመልከት›› በሚለው አስተምህሮ በዝርዝር መናገር አልፈቀዱም። ይሁንና ከብዙ በጥቂቱ በደቡብ ዞን ወራቤ አካባቢ በ13 ዞኖች ንጹህ የመጠጥ ውሃ አውጥተዋል፤ ትምህርት ቤቶች ገንብተዋል፤ ቂርቆስ ክፍለ ከተማ በሚገኝ አንድ ትምህርት ቤት 500 ተማሪዎችን በቋሚነት ይመግባሉ። በተጨማሪም ከኩባንያዎቻቸው ዓመታዊ ትርፍ ሶስት በመቶውን በየዓመቱ ለበጎ አድራጊ ድርጅቶች ተደራሽ በማድረግ ማህበራዊ ኃላፊነታቸውን በአግባቡ የሚወጡ ኢትዮጵያዊ ናቸው።
ፍሬሕይወት አወቀ
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሐምሌ 6 ቀን 2016 ዓ.ም