ድንቅ የፈጠራ ውጤቶች በቴክኒክና ሙያ ዓውደ ርዕይ

የቴክኒክ ሙያ ትምህርትና ሥልጠና ዘርፍ በኢትዮጵያ በተጨባጭ በግብርናው ዘርፍ ከአርሶና አርብቶ አደሩ ጎን ሆነው ድህነትን የተፋለሙ በሺህዎች የሚቆጠሩ የግብርና ኤክስቴንሽን ሠራተኞችንና በጤና ዘርፍ 80 በመቶ የመከላከል ሥራ ለማከናወን በአሥር ሺዎች የሚቆጠሩ የገጠርና የከተማ የጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎችን በማሠልጠን እና ብቃታቸውን በማረጋገጥ ለየዘርፉ ውጤታማነት ከፍተኛ ሚና ተጫውቷል፡፡

በሌላ በኩል ለአምራች እና አገልግሎት ሰጭ ኢንዱስትሪዎች መለስተኛና በመካከለኛ ደረጃ ብቁ ሙያተኞችን በማዘጋጀት ሀገሪቱ ወደ ኢንዱስትሪ መር ኢኮኖሚ ለመሸጋገር ለምታደርገው ጥረት ወሳኝ ዕገዛ አድርጓል፡፡ የቴክኒክና ሙያ ተቋማት እጅግ ፈታኝ የሆኑ የአመለካከትና የግብዓት ችግሮችን በመቋቋም ኢኮኖሚው በሚፈልገው ልክ ብቃት ያላቸው፣ በራሳቸው የሚተማመኑ፣ ቴክኖሎጂን በመጠቀም ተወዳዳሪ የሆኑ ምርትና አገልግሎቶችን ማቅረብና ሀብት ማግኘት የቻሉ ሥራ ፈጣሪ ዜጎችን ለማፍራት ጥረት እያደረጉ እንደሚገኝ ይነገራል።

በዚህ ዘርፍ የተሠሩ ሥራዎች የቀረቡበትና የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ጋር በመተባበር ያዘጋጀው 14ኛው ከተማ አቀፍ የቴክኒክና ሙያ ሳምንት “ቴክኒክና ሙያ ለዘላቂ ሠላም” በሚል መሪ ሃሳብ በአዲስ አበባ ኤግዚቢሽን ማዕከል ተካሂዷል። በኤግዚቢሽንና ባዛሩ ላይ ከተለያዩ የሙያና ቴክኒክ ተቋማት የተውጣጡ ወጣቶች የፈጠራ ውጤቶቻቸውን ይዘው ቀርበዋል።

ወጣት ኃይለየሱስ ወንደሰን በኤግዚቢሽን ሥራዎቻቸውን ይዘው ከቀረቡ ወጣቶች መካከል አንዱ ነው። ከቦሌ ማኑፋክቸሪንግ ኮሌጅ የመጣው ኃይለየሱስ ደረቅና የፕላስቲክ ቆሻሻ ወደ ነዳጅ የሚቀይርና በተረፈ ምርቱ ከሰል የሚያመርት ቴክኖሎጂ ነው ይዞ የቀረበው።

ይህንን የፈጠራ ሥራ ምክንያት ስለሆነው ነገር ወጣት ኃይለየሱስ ሲናገር፤ በሀገሪቱ ያለው የነዳጅ እጥረትና ከዚህ ጋር ተያይዞ የሚፈጠሩ የሰውን ሕይወት እያከበዱ ያሉ ነገሮችን በመመልከት ለዚህ ችግር ለምን ሀገር በቀል የሆነ መፍትሔ መስጠት አቃተን በሚል መነሻ ወደ ሥራ እንደገባ ይናገራል።

በሀገራችን ያለው የነዳጅ መወደድ አሳሳቢ ደረጃ ላይ እየደረሰ በመሆኑና ከዚህ ጋር ተያይዞ በመዲናችን አዲስ አበባ ሆነ በክልል ከተሞች ከፍተኛ የትራንስፖርት ችግር በመኖሩ ለፈጠራ ሥራ እንዳነሳሳው የሚናገረው ወጣቱ ብዙ ጊዜ የፈጠራ ሥራ የሚመነጨውም ከችግር መሆኑን ያስረዳል፡፡

ተፈጥሯዊ ከሆነው ሂደት ውጭ ነዳጅ ለማግኘት የምንጠቀመው ፕላስቲክና ደረቅ ቆሻሻ እንደሆነ የሚናገረው ኃይለየሱስ፤ የተፈጥሮ ነዳጅ በራሱ ከሺህ ዓመታት በፊት መሬት ውስጥ ወድቆ የነበረ ቆሻሻ ወይም የተለያየ አይነት ሥርዓተ ምሕዳር ነው። ይህንን በመሳብና በማጣራት ነው ነዳጅ አምራች የሆኑ ሀገራት ኬሮሲን፣ ጋዞሊን፣ ዲዝል እያደረጉ የሚሸጡት፡፡ ከዚህ ባለፈ ተረፈ ምርቱን ፕላስቲክ እያደረጉ ይሸጣሉ፡፡ ይህንን ፕላስቲክ ነው መልሰን ነዳጅ እያደረግን ያለነው ይላል።

ለሥራው 800ሺህ ብር የወጣበት ይህ ማሽን ሥራውን ስለሚያከናውንበት ሂደት ወጣት ኃይለየሱስ ሲናገር፤ የኤሌክትሪክ ኃይል በመጠቀም 18 ኪሎዋት የሚሆን ሙቀት በመስጠት ደረቅና ፕላስቲክ ቆሻሻዎችን በማቃጠል ወደ ነዳጅ የሚቀይር ስለመሆኑ ይናገራል።

የጎማ ተረፈ ምርት በመጠቀም ለሦስት ሰዓት ፕሮሰስ በማድረግ 70 ሊትር ነዳጅ መስጠት ይችላል የሚለው ኃይለየሱስ፤ ይህንን ቁጥር ከፍ በማድረግ ከ150 እስከ 300 ሊትር ነዳጅ መስጠት እንዲችል አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲን ጨምሮ ከተለያዩ አካለት ጋር በመተባበር የዲዛይን ማሻሻያ ሥራዎች እየተሠሩ እንደሆነ ይናገራል።

ማሽኑ እንደ ሀገር የሚሰጠው ጥቅም ከፍተኛ እንደሆነ የሚናገረው ወጣት ኃይለየሱስ፤ ለአብነት ሆስፒታሎች በየቀኑ የሚያቃጥሉት የፕላስቲክ ቆሻሻ መጠን ከፍተኛ ነው። በዚህ ቴክኖሎጂ ቆሻሻ ወደ ኃይል ቀይሮ መጠቀም ይችላል፤ በሌላ በኩል በሀገሪቱ በሚገኙ ሐይቆች ከፍተኛ ችግር እየፈጠረ የሚገኘው የእንቦጭ አረም በዚህ ቴክኖሎጂ ወደ ነዳጅ መለወጥ እንደሚችል ያስረዳል።

በሌላ በኩል የከተማ ፅዳት ጠንቅ ሆኖ ያለውንና አዲስ አበባ ከተማን ጨምሮ በምሥራቅ ኢትዮጵያ በብዛት ጥቅም ላይ የሚውለው የጫት ተረፈ ምርት (ገረባ) በዚህ ማሽን ወደ ነዳጅነትና ከሰል መለወጥ ይቻላል። በተጨማሪም ቆሼ አካባቢ የሚገኙ ደረቅና የፕላስቲክ ቆሻሻዎች ጥቅም ላይ ማዋል እንደሚቻል ይገልጻል።

ይህንን ማሽን ለመሥራት የነበረው ፈተና ከባድ እንደነበርና ከሦስት ዓመት በላይ እንደወሰደ የሚናገረው የፈጠራ ባለሙያው፤ የኢትዮጵያ ማኅበረሰቡ አዲስ ነገር ለመሥራት አልያም የተሠራውን ለመቀበል ይፈራል፤ ተቋማት እንዲሁ መሰል የፈጠራ ሥራዎችን ለማበረታታት በተለያየ ምክንያት ፈቃደኝነት አይስተዋልባቸውም፡፡ ይህ ለዘርፉ ዕድገት የሚኖረው አሉታዊ አስተዋፅዖ ከፍተኛ ነው ይላል።

ማሽኑ ወደ ገበያ ሲወጣ የሚኖረው አዋጭነት እንደ ቆሻሻው አይነት እንደሚወሰን የሚናገረው ወጣት ኃይለየሱስ፤ ደረቅ ቆሻሻ ተጠቅሞ ሲሠራ ከፍተኛ ኃይል የሚፈልግ በመሆኑ አዋጭነቱ አነስተኛ ነው። ነገር ግን የመኪና ጎማን ጨምሮ የፕላስቲክ ቆሻሻዎችን በመጠቀም በሚሠራበት ወቅት ይበልጥ አዋጭ እንደሚሆን ያስረዳል።

መንግሥት ለዘርፉ በሰጠው ልዩ ትኩረት ቴክኒክና ሙያ ተቋማት ብቁ ባለሙያዎችን ከማፍራት ባለፈ በሀገር የልማት እንቅስቃሴ ላይ ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ የሚችሉ የፈጠራ ውጤቶችን በማበርከት የጎላ አስተዋፅዖ እያበረከቱ መሆኑን የሚናገረው ኃይለየሱስ፤ የፈጠራ ውጤቶችን መሥራት በብዛትና በጥራት ለማምረት የቦታና የግብዓት አቅርቦት ችግሮች መኖራቸውን ጠቁሞ፤ በዚህ ረገድ የሚደረጉ ድጋፎች ሊጠናከሩ ይገባል ይላል።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ መንግሥት በተለይ ለቴክኖሎጂና ፈጠራ ሥራዎች የሰጠው ትኩረት ይበል የሚያሰኝ ነው የሚለው ኃይለየሱስ፤ ይህ ዓውደ ርዕይም ሀሳብና በጅምር ያለ የፈጠራ ሥራ ያላቸው ወጣቶች የተገኙበት እንደመሆኑ በጅምር ያለ የቴክኖሎጂ ፈጠራ ሥራ ደግሞ ከፍተኛ ፋይናንስ የሚጠይቅ በመሆኑ የተለያዩ ኢንቨስተሮች አብረው እንዲሠሩ ለማድረግ ሥራዎችን ማሳየት የሚቻልበት አጋጣሚ መፈጠሩ በጎ ጅምር ስለመሆኑ ይናገራል።

ወደፊት ይህንን ሥራ የማሽኑን የማምረት አቅም በማሳደግ እንደ ማንኛውም ሀገር የራሳችንን ነዳጅ ማምረት የምንችልበት አቅም ለመፍጠር እቅድ እንዳለው የሚናገረው ወጣት ኃይለየሱስ፤ ይህ በሀሳብ ደረጃ ብቻ ሳይሆን መሬት ላይ ወርዶ የማየት ትልቅ ራዕይ እንዳለው ይናገራል።

በአሁኑ ወቅት አንዳንድ የምዕራቡ ዓለም ኩባንያዎች ቆሻሻን ወደ ሀገራቸው ከውጭ ገዝተው እንደሚያስገቡ የሚናገረው ኃይለየሱስ፤ የዚህ ምክንያት ደግሞ ሁለት ነው። አንደኛው ቆሻሻን ወደ ኤሌክትሪክ ይለውጡታል፣ በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ ወደ ነዳጅነት ይቀይሩታል፤ በዚህ ረገድ ይህንን ልምድ በመውሰድ ቆሻሻን በመጠቀም ሀገር የሚለውጥ ነገር ለመሥራት ጥረት ማድረጉን እንደሚቀጥል ተናግሯል።

ወጣት አያና ቡልቻ ሌለው በዚህ ዓውደርዕይ የፈጠራ ሥራዎቻቸውን ይዘው ከቀረቡ ወጣቶች መካከል አንዱ ነው። በኤሌክትሪክ የሚሠራ ዘመናዊ የሸክላ እቃዎች ማድረቂያ ማሽን ከጓደኞቹ ጋር በማምረት ይዞ የቀረበው አያና ይህንን ሥራ ለመሥራት የተነሳሳበትን ምክንያት ሲናገር፤ የተለያዩ የዳሰሳ ጥናቶችን እንደሠራ በከተማዋ በተለያዩ አካባቢዎች በሸክላ ሥራ የተሠማሩ ሰዎችን በማነጋገር በዘርፉ ያለውን ችግር ለመቅረፍ ሁነኛ መፍትሔ የሚሆነው ይህ መሥሪያ እንደሆነ በመገንዘብ ማሽኑን እውን ለማድረግ እንደተነሳ ይናገራል።

“በሸክላ ሥራ የተሠማሩ ሰዎችን ባነጋገርንበት ወቅት በዓመት ወደ ሰባት ሰው ከሥራው ጋር በተያያዘ ሕይወቱ እንደሚያልፍ ተረዳን የሚለው አያና፤ የዚህ መነሻ ደግሞ ሸክላው የሚቃጠልበት መንገድ በኩበት ወይም በእንጨት በአጠቃላይ ባሕላዊ በሆነ መንገድ መሆኑ ነው። ይህንን ኋላቀር አካሄድ በማስቀረት ሥራውን ዘመናዊ ለማድረግ በማሰብ የተሠራ ማሽን ስለመሆኑ ይናገራል።

ማሽኑ ከ15 እስከ 20 ደቂቃ ባለው ጊዜ ውስጥ 24 ጀበናዎችን በማቃጠል ለአገልግሎት ማብቃት ይችላል የሚለው ወጣት አያና፤ የኤሌክትሪክ ኃይል አጠቃቀሙ ዘመናዊ በሆነ መልኩ የተሠራ እንደሆነ ሰዎችም በቀላሉ እንዲጠቀሙበት በማሰብ ውስብስብ ባልሆነ መንገድ የተመረተ ማሽን ነው ይላል።

ከዋጋ ሆነ ከአጠቃቀም አንፃር በተለይ እናቶችን ታሳቢ በማድረግ የተሠራ ማሽን ስለመሆኑ የሚናገረው ወጣት አያና፤ ለ15 ደቂቃ የኤሌክትሪክ ሙቀት ካገኘ እስከ ሶስት ሰዓት ድረስ የኤሌክትሪክ ኃይል ቢቆረጥ እንኳ ያለምንም ችግር ሥራውን እንደሚቀጥል ይናገራል።

ከግፊት መቆጣጠሪያው ውጭ ማሽኑን ለማምረት አብዛኛዎቹን እቃዎች በሀገር ውስጥ የሚገኙ ብረታብረቶችን እንደተጠቀሙ የሚናገረው አያና፤ በዚህ ምክንያት በብዛት ተመርቶ ገበያ ላይ በሚውልበት ወቅት ሰዎች ከፍተኛ ወጪ ሳያወጡ ቴክኖሎጂውን ማግኘት እንደሚችሉ ይገልጻል።

የዚህ ማሽን ጠቀሜታ እንደ ሀገር ከፍተኛ ነው የሚለው ወጣት አያና፤ የእናቶችን ሞት ከማስቀረት በተጨማሪ ከዚህ በፊት የሚጠቀሙት ባሕላዊ አሠራር በጤናቸው ላይ የሚያመጣውን ጉዳት ያስቀራል፤ ከዚህ ባሻገር በተለመደው አሠራር በክረምት ወይም የአየር ሁኔታው ቀዘቀዘ ሲሆን ምርት ማምረት አይቻልም ይህንን ሁሉ ችግር በመፍታት ረገድ የማሽኑ ጠቀሜታ ከፍተኛ ነው ይላል።

ከብዙ መመዘኛ አንፃር አዋጭነቱ ከፍተኛ ነው የሚለው ወጣት አያና፤ 220 ቮልት ኤሌክትሪክ የሚጠቀም በመሆኑ ማንኛውም ግለሰብ ሆነ ድርጅት ገዝቶ መጠቀም ይችላል። ከዚህ ባሻገር የእናቶችን ጉልበት በከፍተኛ ደረጃ የሚወስደውን ኋላቀር አሠራር በማስቀረት ትልቅ ትርጉም እንደሚኖረው ይናገራል።

ለሸክላ ማድረቅ ታስቦ የተሠራ ማሽን በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ ሀገር እስከአሁን እንዳልተሠራ የሚናገረው የፈጠራ ባለሙያው፤ ለኦቨን አይነት ምርቶች የሚመጡ ማሽኖች አሉ ነገር ግን የሚያስወጡት የውጭ ምንዛሪ እንዳለ ሆኖ የሚወስዱት የኤሌክትሪክ መጠን ከፍተኛ በመሆኑ ለሸክላ አምራቾች ከዋጋ አንፃር አዋጭ እንዳልሆኑ ያስረዳል።

ሌላው ነገር ማሽኑ ለኢትዮጵያ የአፈር አይነት ተስማሚ ሆኖ እንደተሠራ የሚገልጸው አያና፤ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተመሳሳይ ምርት ቢኖር እንኳ ለገበያ የሚቀርበው በዓለም አቀፍ ደረጃ መሠራት ነው። ይህ ደግሞ እንደየሀገራቱ የአፈር አይነት ውጤታማነቱ ውስን ነው። ከዚህ አኳያ የዚህ ማሽን ውጤታማነት ከፍተኛ ነው ይላል።

ወጣት አያና እንደሚናገረው፤ በሚቀጥሉት ዓመታት ይህንን ማሽን በስፋት በማምረት ለገበያ የማቅረብና በተለይ በተለያዩ ቦታዎች ተደራጅተው በሸክላ ሥራ ላይ ለተሠማሩ እናቶች በተመጣጣኝ ዋጋ በስፋት ለማዳረስ የተለያዩ ጥረቶችን እያደረገ እንደሚገኝ ያስረዳል።

ማሽኑን ለመሥራት 40ሺህ ብር ወጪ እንደሆነና ለገበያ ደግሞ በ60ሺህ ብር እንደቀረበ የሚናገረው አያና፤ የሥራው ዓላማ ትርፍ ከማግኘት ባሻገር ማኅበረሰቡን መጥቀም በመሆኑ በዚህ ዋጋ ለገበያ እንደቀረበ ይናገራል።

ቴክኖሎጂ በጥቂት የሰው ኃይልና ቦታ ትላልቅ ሥራዎች ለመሥራት ምቹ መሆኑ ዘርፉን በብዙ ተመራጭ እንደሚያደርገው የሚናገሩት ወጣቶቹ፤ በሚመጣው ዘመን ተወዳዳሪ ሆኖ ለመገኘት ለቴክኖሎጂ ሥራና ምርምር ትልቅ ትኩረት ያስፈልጋል። ከዚህ አንፃር የኢትዮጵያ መንግሥት ለቴክኒክና ሙያ ዘርፍ ልዩ ትኩረት በመስጠትና የነቃ ተሳትፎ በማድረግ ቴክኖሎጂን ከግምት በማስገባት የፖሊሲ ማሻሻያ በማድረግ ብሎም በቴክኖሎጂ ላይ ለተሰማሩ ተቋማትና ግለሰቦች አቅም በፈቀደ መጠን ሁሉ የፋይናንስ ድጋፍ በማድረግ መሥራት እንዳለበት መልዕክት አስተላልፈዋል።

ክብረአብ በላቸው

አዲስ ዘመን ሐምሌ 5/2016 ዓ.ም

 

Recommended For You