ወጣት አዳነ ሹሜ ትውልዱም ሆነ እድገቱ በጉራጌ ዞን እንድብር ከተማ ልዩ ስሙ የሰሚ በተባለ ቦታ ነው:: ከልጅነቱ ጀምሮ የጤና ባለሙያ የመሆን ህልም ነበረው፤ ይህን የተረዱት ወላጆቹም የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን እንዳጠናቀቀ ወደ አዲስ አበባ ልከውት በግል የጤና ኮሌጅ በጤና መኮንንነት አስተማሩት::
ትምህርቱን እንዳጠናቀቀም አዲስ አበባ ከተማ በሚገኝ የግል ክሊኒክ ተቀጥሮ ለሁለት ዓመታት አገለገለ:: ይሁንና የሚከፈለው ደመወዝ እዚህ ግባ የማይባልና ለከተማ ኑሮ የማይበቃ በመሆኑ ሥራውን ለቆ ወደ ትውልድ ቀዬው መመለሱን ወጣት አዳነ ያስረዳል:: ‹‹በወቅቱ ይከፈለኝ የነበረው ደመወዝ አይደለም ለቤት ኪራይ ለቀለቤም አይበቃም ነበር›› ሲል ይገልፃል::
እንድብር ከተማ ላይ ከአክስቱ ጋር በመተባበር የራሳቸውን ጤና ጣቢያ በጋራ ይከፍታሉ፤ እሱም በሙያው መስራቱን ይቀጥላል:: ይሁንና ይህም ስራ እንዳሰበው አዋጭ ሆኖ አላገኘውም::
አሁንም ሥራውን ለቆ አዋጭ ይሆናል ባለው ንግድ ላይ ተሰማራ:: ንግዱም ቢሆን አልሳካልህ አለው:: ‹‹ ከመንግሥት 30 ሺህ ብር ተበድሬ ልብስ ንግድ ብጀምርም ከማገኘው በላይ ወጪዬ በዛ፤ ስለሆነም ከአራት ዓመታት በኋላ ከስሬ ሱቁን ዘጋሁት›› ሲል ይገልፃል::
ወጣቱ የጤና መኮንን ድህነትን ለማሸነፍና በሁለት እግሩ ለመቆም በጣረ ቁጥር ፈተናዎች ቢበዙበትም እጁን አጣጥፎ አልተቀመጠም፤ አዕምሮውም ሌላ አማራጭ ከማሰብ አልቦዘነም:: ይህንን የባለቤቱን ኪሳራ ያየችው የህይወት አጋሩ ግን የመንግሥት ስራ ተቀጥሮ እንዲሰራ ወተወተችው፤ እሱ ግን አሻፈረኝ አለ፤ ላጋጠሙት ችግሮችም እጅ ሳይሰጥ ሌሎች የስራ ዘርፎችን መቃኘት ያዘ::
ብዙ አውጥቶ ካወረደ በኋላ ያለጥቅም የኖረውን የወላጆቹን መሬት አሰበ፤ መሬቱን በማልማት ጥቅም ላይ ሊያውል የሚችልበትን ሁኔታ አውጠነጠነ፤ የተሻለ ገቢ እንደሚያስገኝለትም አለመ:: አልሞ ብቻም አልቀረም፤ ውጥኑን መሬት ላይ አወረደ::
ሰርቶ የመለወጥ ተስፋው ዳግሞ እንዲያንሰራራ ያደረገው ደግሞ በሌማት ቱሩፋት ህይወታቸው ተቀይሮ የተመለከታቸው ሰዎች እንደሆኑ ይናገራል:: ‹‹በተለይም ጠቅላይ ሚኒስትራችን በደቡብ ክልል የሌማት ቱሩፋት አማካኝነት የተሰራውን ስራ በቴሌቪዥን ሲገልፁ ካያሁኝ በኋላ በግብርና ስራ ላይ ለመሰማራት ልቤ ተነሳሳ›› ሲል ይገልፃል::
‹‹ከሁለት ሄክታር በላይ በሚሆነውና ከትውልድ ትውልድ ሲሸጋገር በቆየው በቤተሰቦቼ መሬት ላይ ባህር ዛፍ ብቻ ይለማ ነበር፤ ከዚህም በየስምንት ዓመቱ ተጠብቆ እስከ መቶ ሺ ብር ብቻ ይገኝ ነበር፤ ግን የበለጠ ተጠቃሚ የሚያደርገን ምርት ማምረት አለብኝ ብዬ ወሰንኩኝ›› ሲል ያስረዳል::
በዚህ መሰረት እድሜ ጠገቡንና ከትውልድ ትውልድ ሲሸጋገር የቆየውን የባህር ዛፍ ጫካ ሙሉ ለሙሉ መነጠረና በምትኩ ሙዝ፣ አቦካዶ፣ አፕልና ዝንጅብል ለመትከል ተዘጋጀ:: ይሁንና ዛፉ ረጅም ጊዜ ያስቆጠረ እንደመሆኑ ጉቶውን ነቅሎ ማውጣት ብዙ ገንዘብ፤ ጊዜና ጉልበት እንደጠየቀው ይናገራል::
ጉቶውን ማስወገድ ብዙ ቢያደክመውም ጥቅምም እንደሚያገኝበትም አሰበ:: ከጉቶው ከሰል አውጥቶ በመሸጥ ወጪውን ለመተካት ጥረት አደረገ:: በሌላ በኩል መሬቱ አሲዳማ እና ገደላማ በመሆኑ ምክንያት መሬቱን ለልማት ምቹ የማድረጉ ሂደትም ብዙ ዋጋ ያስከፈለው መሆኑን ይገልጻል:: ‹‹ በመሬቱ ላይ ኖራና አዛባ በማድረግ በማከም ለም ለማድረግ ብዙ ዋጋ አስከፍሎኛል፤ ከአንድ ዓመት በላይ ጊዜም ወስዶብኛል›› ይላል::
መሬቱን ካለማም በኋላ መጀመሪያ የተከለው አቦካዶ ነበር፤ ሆኖም አተካከሉን ባለማወቄ እና መሬቱም በባህር ዛፉ ተጎድቶ ስለነበር ከተከላቸው 100 የአቦካዶ ችግኞች ሶስቱ ብቻ ሲቀሩ 97ቱ በሙሉ ወደሙበት:: ወጣት አዳነ በዚህም ተስፋ አልቆረጠም፤ አንድ ከከንባታ አካባቢ የመጣ ጓደኛውን በጉዳዩ ላይ አማከረ ፤ እሱ ያለበት አካባቢ የአየር ንብረት ከከንባታ አካባቢ ጋር የሚመሳሰል በመሆኑ ዝንጅብል ቢተክል እንደሚያዋጣው ጓደኛው መከረው፤ ምክሩንም ተቀብሎ ተገበረ::
‹‹ግን ደግሞ ዝንጅብል በእኛ አካባቢ ያልተለመደ በመሆኑ ልከስር እንደምችል እያሰብኩኝ በ500 ካሬ ላይ 100 ኩንታል ተከልኩኝ፤ በዚህም 24 ኩንታል አገኘሁና ፤ ምርቱንም በ156 ሺ ብር ሸጥኩት›› ሲል ይገልጻል:: ‹‹ውጤቱን አበረታች መሆን ስመለከት የበለጠ ለመስራት አነሳሳኝ፤ ዛሬም ድረስ በግብርና ስራ ላይ እንድቀጥል አደረገኝ፤ ለካ መሬታችን ከሰራንበት ወርቅ ነው ብዬ እንዳስብ አደረገኝ›› በማለት ተስፋውን ያለመለመለትን አጋጣሚ ያስታውሳል::
ከዝንጅብሉ ያገኘውን ገንዘብ በሙሉ ኪሱ ሳይከት ጉቶ በመንቀልና የሚያለማበትን መሬት በማስፋፋት ከአርባ ምንጭ አንድ ሺ የሙዝ ችግኝ በማምጣት ተከለ:: በዚህም አልተወሰነም፤ አንድ አንድ ሺ 500 የቡና ችግኝ በሙዝ መሃል በመትከል የአካባቢውን ገፅታ ሙሉ ለሙሉ በሚባል ደረጃ መቀየር ቻለ::
ወጣቱ በአሁኑ ወቅትም ቡናው ማፍራት መጀመሩን ይናገራል:: ጥረቱን ያየው የከተማ አስተዳደሩ ደግሞ በወጣቶች ተዘዋዋሪ ፈንድ 300 ሺ ብር የብድር ድጋፍ አደረገለትና የእርሻ ስፍራውንም ሆነ የምርት መጠኑን በእጥፍ ከፍ ማድረጉን ይገልፃል::
ከተተከለ አንድ ዓመት የሆነው ሙዝም ቢሆን ማፍራት መጀመሩን ከስሩ የሚያበልቀውን ውላጅ ችግኝ (ሰከር) ለሌሎች የአካባቢው አርሶ አደሮች እየሸጠ ተጠቃሚ መሆን መቻሉን ወጣት እንዳለ ያስረዳል:: ‹‹ከአንድ ሙዝ ሰከር ብቻ 60 ብር አገኛለሁ፤ ሙዙ ሙሉ ለሙሉ ሲበስል ደግሞ እያንዳንዱ ግንድ 40 ኪሎ የሚይዝ በመሆኑ የማገኘው ገቢ በከፍተኛ መጠን እንደሚጨምር አልጠራጠርም›› ሲል በቁርጠኝነት ይናገራል:: ሙዙ ደርሶ ለገበያ ሲያቀርብም አንዱን ኪሎ እስከ 30 ብር ለመሸጥ ማቀዱን ተናግሮ፤ ይህም አሁን ያለውን የካፒታል አቅም በከፍተኛ ደረጃ ያሳድግልኛል ብሎ ተስፋ ጥሎበታል::
‹‹ከዚህ ቀደም የመንግሥት ጠባቂ ነበርኩ፤ አሁን ግን ከራሴ አልፌ ለሌሎች የአካባቢዬ ወጣቶች ተስፋ ሆኛለሁ›› ሲል ለበርካታ ወጣቶች ስራ መፍጠሩ ተጨማሪ ኩራት እንደሆነለት ይናገራል:: የእሱን ተሞክሮ ያዩ ጓደኞቹም የባህር ዛፍ መሬታቸውን እየመነጠሩ የምግብ ዋስትና ሊያረግጡ፣ ጥሩ የገቢ ምንጭ ሊሆኑ ወደሚችሉ የግብርና ስራዎች እንዲገቡ ምክር እንደሚሰጣቸው ይናገራል:: ይህን ምክር ለመስጠትና ተሞክሮውን ለማጋራት ደግሞ የአካባቢያቸው የወጣት ሊግ መሪ መሆኑ ጠቅሞታል:: ከዚህ ባሻገርም በመንደሩ ላሉ 40 አባወራዎች አንድ ኩንታል ዝንጅብል በመከፋፋል በነፃ ወስደው እንዲያለሙ ማድረጉን ነው ያመለከተው::
ወጣት እንዳለ በአሁኑ ወቅት ለ15 ወጣቶች ቋሚ፤ አምስት ለሚሆኑት ደግሞ በጊዜያዊነት የስራ እድል መፍጠር ችሏል:: ስራውን በማስፋት እስከ 100 ሺ ለሚደርሱ የአካባቢው ወጣቶች የስራ እድል ለመፍጠር አቅዷል::
ወጣት አዳነ፤ ከአንድ ዓመት በፊት ስራውን ሲጀምር ምንም ካፒታል እንዳልነበረው አስታውሶ፤ ላጋጠሙት ተግዳሮቶች እጅ ሳይሰጥ ቀን ከሌሊት በመልፋቱ አንድ ነጥብ አምስት ሚሊዮን ብር የሚደርስ ሃብት ማፍራት መቻሉን ይጠቁማል:: በእንድብር ከፍተኛ የችግኝ እጥረት መኖሩን የሚጠቅሰው ወጣት እንዳለ፤ ያዘጋጃቸውን የቡና፣ የሙዝ እና የተለያዩ ፍራፍሬዎች ችግኞች በዘንድሮው ክረምት ለህብረተሰቡ ለማቅረብ ዝግጅት እያደረገ መሆኑን ያመለክታል::
የመነጠረውን የባህር ዛፍ እንጨት በመጠቀም 90 ቆርቆሮ የወሰደ ትልቅ ቤት መስራቱን ጠቁሞ፤ ከእርሻው ጎን ለጎንም የእንስሳት እርባታ ለመጀመር የሚያስፈልጉትን ዝግጅቶች ማጠናቀቁንም ያመለክታል:: ‹‹አንድ ሃበሻ ከብት ገዝቼ ከፈረንጁ ጋር አዳቀልኩትና ከሰሞኑ ደግሞ ጊደር አግኝቻለሁ፤ ወደፊት ግን የእንስሳት እርባታውን ለማስፋፋት እቅድ አለኝ፤ ለዚህም ነው አስቀድሜ የማረባበትን ስፍራ ያዘጋጀሁት›› በማለት ወደ ከፍተኛ ባለሃብትነት ለመሸጋገር ያደረገውን ጥረት ያስረዳል::
በጥምር ግብርና ዘርፍ ወደ ኢንቨስተርነት የማደግ ተስፋ መሰነቁን የሚገልፀው አርሶአደሩ የጤና ባለሙያ፤ በአሁኑ ወቅት በንብ ማነብና ዓሳ ልማት ሥራም ለመሰማራት ዝግጅት እያደረገ መሆኑን አስታውቋል:: ‹‹በአሁኑ ወቅት ሁለት ዘመናዊ ቀፎ ገዝቻለሁ፤ የዓሳ ኩሬ ለመስራትም ዝግጅት እያደረኩ ነው›› በማለት ይጠቁማል::
ይሁን እንጂ አሁን ያለው ቦታ ላሰበው ሥራ በቂ እንደማይሆን ይነገራል:: ላሰበው ልማት የከተማው አስተዳደር ቦታ እንዲሰጠው ለመጠየቅ ማሰቡንም አጫውቶናል:: ይህ ከተሳካለት ደግሞ አቦካዶ፣ ዝንጅብል፣ ቡና እና ሌሎች የግብርና ውጤቶችን በስፋትና በጥራት በማምረት ወደ ተለያዩ የዓለም ሀገራት ለመላክና ለሀገሩ የውጭ ምንዛሪ ለማስገኘት ማቀዱን ተናግሯል::
ወጣት እንዳለ፤ ስራ አጥ የሆኑ ወጣቶች በተለይም ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ተመርቀው በሙያቸው ስራ ባለማግኘታቸው ምክንያት ተመልሰው ቤተሰብ ላይ የተቀመጡ ወጣቶች ከእሱ ህይወት እንዲማሩ ይመክራል:: ‹‹ስራ ካልናቁና ከሰሩ መለወጥ እንደሚቻል በራሴ ህይወት አይቻለሁ፤ ሌሎች ወጣችም የማንንም ድጋፍ ሳይጠብቁ እንደእኔ አዕምሯቸውንና ጉልበታቸውን በመጠቀም ስራ ፈጣሪ ሊሆኑ ይገባል›› ይላል::
‹‹እኔ በብር ብቻ አላምንም፤ ተነሳሽነቱ ከሌለ ገንዘቡ ቢኖርም ውጤታማ መሆን አይቻልም›› ያለው ወጣቱ፣ ስለዚህ ወጣቶች ብድር ማግኘት አልቻልኩም፤ የሚደግፈኝ አላገኘሁም ብለው እጃቸውን አጣጥፈው ሊቀመጡ እንደማይገባም አስገንዝቧል:: አጠገባቸው ያለውንና ተፈጥሮ የሰጣቸውን አቅም ተጠቅመው ራሳቸውን ሊለውጡ እንደሚገባም አስታውቋል:: ‹‹ትምህርት መማር ጥሩ ነው፤ ግን ደግሞ በተማርንበት ዘርፍ ስራ ካላገኘን ብሎ ማማረር ግን ተገቢ አይደለም፤ ይልቁንም ያላየነውና በእጃችንን ያለውን ሃብት ተረድተን ልንጠቀምበት ይገባል›› የሚለው ደግሞ የጤና መኮንኑ አርሶአደር ሌላው ምክሩ ነው::
ማህሌት አብዱል
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሰኔ 29 ቀን 2016 ዓ.ም