ለብዙዎች እፎይታ እየሰጠ ያለው ማዕከል

የኢትዮጵያ የልብ ህሙማን ህጻናት መርጃ ማዕከል በልብ ህመም ለሚሰቃዩና ህክምና ለሚያስፈልጋቸው ዜጎች ያለምንም ክፍያ በነጻ ህክምና የሚሰጥ ብቸኛው ተቋም ነው። ማዕከሉ ይህንን በጎ ተግባር ከሶስት አስርት ዓመታት በላይ ሲያከናውን ቆይቷል። የማዕከሉ መስራች ዶክተር በላይ አበጋዝ፤ በወቅቱ ‹‹አንድ ብር ለአንድ ልብ›› በሚል ሃሳብ ብዙ ኢትዮጵያውያንን ተሳታፊ ማድረግ እንደቻሉ አይዘነጋም።

ይህ በቅን ልቦች ጠንሳሽነት የተጀመረው በጎ ሥራ ከእያንዳንዱ ሰው ደርሶ ሃሳቡ ፍሬ እንዲያፈራ ብዙ ጥረት ተደርጓል። በተለይም ማህረሰቡን ተሳታፊ ለማድረግ መረጃውን በማሰራጨት በኩል 100 የሚጠጉ በጎ ፍቃደኞች፣ የማህበረሰብ አንቂዎች፣ የኪነጥበብ ባለሙያዎች በብዙ ተሳትፈዋል። የመገናኛ ብዙኃን በበኩላቸው ማዕከሉን በመደገፍ ረገድ የነበራቸው ሚና ቀላል ግምት የሚሰጠው አልነበረም። በዚህም በርካታ ታማሚ ልቦች እፎይታን ማግኘት ችለዋል።

አቶ ሙሳ ቃሲም የማዕከሉን አገልግሎት ፈልገው ከመጡ ታካሚዎች መካከል አንዱ ነው። አቶ ሙሳ፤ ልጁን ለማሳከም ከአርሲ ዞን መርተሪ ወረዳ አቦምሳ ከምትባል ወረዳ የመጣ ሲሆን፤ ልጁ የልብ ህመም እንዳለባት ያወቀው የአራት ዓመት ልጅ እያለች ነበር ከዚያም ባደረገችው ምርመራ ወደ ናዝሬት ለተሻለ ህክምና ተላከች። በተደረገላት ምርመራ የልብ ህመም እንዳለባት ማወቅ ችለዋል።

ወደ ማዕከሉ ከመጡ ሰባት ዓመታትን ማስቆጠራቸውን የሚናገሩት አባት አንድ ወቅት ወረፋቸው ደርሶ ነገር ግን ልጃቸው ጉንፋን በመታመሟ ምክንያት ሳትታከም ቀርታለች። ህክምና ለማግኘት ለዓመታት ወደ ማዕከሉ የተመላለሱት አቶ ሙሳ ያለውን ወረፋ ሲገልጹ ‹‹የምመጣው ከሩቅ ሀገር ነው 180 ኪሎ ሜትር ይሆናል። አሁን ከመጣሁ 15 ቀን ሆኖኛል ግን ምኖረው ለልጄ ስለሆነ እመላለሳለሁ›› በማለት ነው። በማዕከሉ አገልግሎቱን ማግኘት ከጀመሩ በኋላ ያለውን ጠቀሜታ ሲገልጹም ‹‹የልብ በሽታ እኔ በምኖርበት ቦታ ብዙም አይታወቅም እኔም የምትድን አልመሰለኝም እዚ ስመጣ ያገኘሁት መረጃ በጣም ጥሩ ነው›› ብለዋል። በማዕከሉ የልብ ህመም እንዳለባት ታውቆ ህክምናውን ስትጀምር የአራት ዓመት ልጅ የነበረችው ሀዊ ሙሳ አሁን የ 11 ዓመት ልጅ እና የአምስተኛ ክፍል ተማሪ ሆናለች።

ሌላኛዋ ታካሚ ወይዘሮ ባንቻየሁ በለጠ ትባላለች። ባንቻየሁ የልብ ህመም እንዳለባት ያወቀችው በልጅነቷ ሲሆን፤ አሁን ላይ ትምህርቷን አጠናቃ በሥራ ላይ ትገኛለች። ወደ ማዕከሉ ከመምጣቷ በፊት እጅግ ታማ ከሀገር ውጪ ሄዳ እንድትታከም እና ከአንድ ሚሊዮን ብር በላይ ገንዘብ ለህክምናው ተጠይቃ እንደነበር ታስታውሳለች። ወደ ማዕከሉ መጥታ ክትትል ስጀምርም ከፍተኛ ወረፋ ጠብቋታል። ህመሙ ከቀን ወደቀን እየጨመረ ሲሄድ ከትዳር አጋሯ ጋር ሆነው ርዳታ ለመጠየቅ ወስነዋል። ‹‹ከውጭ ስታይ ደህና እመስላለሁ ነገር ግን በጣም ያመኛል። እናም በዚህ ሁኔታ እንዴት ርዳታ እጠይቃለሁ እያልኩ ወረፋዬ ደርሶ ተደወለልኝ›› የምትለው ባንቻየሁ ወረፋዋ ደርሶ ቀዶ ጥገናውን ካደረገች አሁን አንድ ዓመት እንደሆናትና በጥሩ ጤንነት ላይ እንደምትገኝ አጫውታናለች። በማዕከሉ ያሉ የጤና ባለሙያዎችን ለታካሚዎች በሚሰጡት ቦታና በሚያደርጉት እንክካቤም እጅግ ደስተኛ እንደሆነች ተናግራለች።

በውጭ ሀገር ለመታከም የወሰነችው ወይዘሮ ባንቻየሁ፤ ከአቅሟ በላይ የሆነ ወጪ በተጠየቀችበት ወቅት ህክምናውን በማዕከሉ ማግኘት በመቻሏ እጅግ ደስተኛ እንደነበረች ስትገልጽ፤ ‹‹ይህንን እድል ባላገኝ አሁን ላይ በሕይወት መቆየት አልችልም ነበር። ስለዚህ ህክምናው ለሁሉም መድረስ እንዲችል ሁሉም ሰው ይህንን ዓላማ መደገፍ አለበት›› በማለት ነው።

የኢትዮጵያ የልብ ህሙማን ማዕከል በሀገር ውስጥ የልብ ህክምና በነጻ የሚሰጥ ብቸኛው በመሆኑ እነዚህን መሰል ተቋማት እንዲበራከቱ እና የብዙዎችን ሕይወት ማትረፍ እንዲቻል ሁሉም ከማዕከሉ ጎን መቆም እንደሚገባ ያነሳችው ወይዘሮ ባንቻየሁ፤ ‹‹ማዕከሉን ለመደገፍ ትልቅ ገንዘብ ድጋፍ ማድረግ የማይችል ሰው የአጭር የጽሁፍ መልዕክት የአቅሙን መደገፍ ይችላል። ይህንን በማድረግም ብዙ ህጻናትን መደገፍ ይቻላል በማለት አስረድታለች።

የማዕከሉ ምክትል ዳይሬክተር ዶክተር ሜሮን ገብሩ በበኩላቸው በማዕከሉ በአሁኑ ሰዓት አራት ቀዶ ጥገና የሚያደርጉ ቀዶ ጠጋኝ ሀኪሞች እንዳሉ ገልጸው፤ አንድ የህክምና ባለሙያም በሳምንት ብቻውን አራት ቀዶ ጥገናዎችን መሥራት ቢችልም ለልብ ቆዶ ጥገና የሚያስፈልግና በቀጥታ ለልብ ታካሚ የሚያስፈልጉ ግብዓቶች እንዲሁም መድሃኒቶች በሀገር ውስጥ በበቂ ሁኔታ አይገኙም። መድሃኒቶቹም በሌሎች የህክምና ተቋማት በቀላሉ የሚገኙ አይደሉም ብለዋል። በማዕከሉ ከሚሰጡ አገልግሎቶች መካከል ለውስጥ ታካሚዎች የተዘጋጀ የራሱ የመድሃኒት ክፍል ስለመኖሩ አንስተው፤ የመድሃኒት እና የግብዓት እጥረት ስለሚያጋጥም ሀኪሞች መሥራት ከሚችሉት አቅም በታች እየሠሩ እንደሆነ ተናግረዋል። አያይዘውም እነዚህን ግብዓች ማሟላት ቢቻል የበለጠ መሥራት እና ታካሚዎችን ማስተናገድ እንደሚቻል አስረድተዋል።

የመድሃኒት አቅርቦት እጥረት በሀገር ደረጃ በተለያዩ የህክምና ተቋማት እጥረት ያግጥማል። ይህንን ችግር ለመፍታትም የተለያዩ ሥራዎች የሚሠሩ ሲሆን፤ እንደ ዳይሬክተሯ ገለጻ ማዕከሉ አገልግሎቱን በሙሉ አቅሙ ለመስጠት እንቅፋት ከሆኑበት ጉዳዮች መካከል የመድሃኒት እጥረት አንዱ ነው። የመድሃኒቶቹ ዋጋ ውድ መሆንና በሌሎች የህክምና ተቋማትም እንደ ልብ አለመገኘት፤ እንዲሁም የልብ ህክምና በነጻ ከሚሰጠው ተቋም ጨምሮ የልብ ህክምና የሚሰጥባቸው ተቋማት ውስጥ በመሆናቸው አቅርቦቱም እንደ ልብ ወደ ሀገር አይገባም። በዚህም ምክንያት አንድና ሁለት መድሃኒት በማጣት የሚዘገዩ ህክምናዎች ስለመኖራቸው የገለጹት ዶክተሯ፤ መድሃኒቱን ለማግኘት ከተለያዩ ተቋማት ጋር በትብብር እየሠሩ እንደሆነ ተናግረዋል።

በህክምናው ዘርፍ የሚገኙ ባለድርሻ አካላት፣ መንግሥትና ማህበረሰቡ በጋራ በመሆን መሥራት እንዳለባቸው ያነሱት ዋና ዳይሬክተሯ፤ በሌሎች የሀገሪቱ ክፍሎች የሚገኘውን የሰው ሃይል አቅም በመጠቀም ከከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ጋር መነጋገር አስፈለጊ እንደሆነም ተናግረዋል። እሳቸው እንዳሉት፤ አገልግሎት እንዴት መስጠት ይቻላል በሚለው ዙርያ መነጋርን ይጠይቃል። ይህ መሆኑም ህክምና ለማግኘት ከክልል የሚመጡ ዜጎች ወደ ክልል መምጣት ሳይጠበቅባቸው በሚኖሩበት ቦታ ህክምናውን በፍጥነት ማግኘት ያስችላቸዋል። ዋና ዋና የሚባሉ የልብ ችግሮች በዚያ እንዲታከሙ እና ተጨማሪ ህክምና የሚያስፈልጋቸው ሲኖሩ ደግሞ ወደ ማዕከሉ እንዲመጡ የሚደረግበትን አሠራር ወደፊት መፍጠር ያስፈልጋል።

በኢትዮጵያ የልብ ህሙማን ማዕከል ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ሕሩይ ዓሊ ‹‹ኢትዮጵያ አሁን ላላት የሕዝብ ቁጥር ይህ አንድ ሆስፒታል ብቻውን በቂ አይደለም። የልብ ቀዶ ጥገና ቀላል የማይባል ህክምና ሲሆን፤ ተቋሙ ከሚያስተናግደው ወረፋ አንጻር ታካሚዎችን ለማስተናገድ የምንቸገርበት ጊዜ አለ›› ይላሉ። በማዕከሉ ቀዶ ጥገና ከሚደረግላቸው እና ህክምና ለማግኘት ወደ ማዕከሉ ከሚመጡት ባሻገር ቅድመ ክትትልና ድህረ ክትትል የሚደረግላቸው ታካሚዎችም አሉ። ያም ሆኖ በማዕከሉ በዓመት እስከ 14 ሺህ ለሚደርሱ ሰዎች ነጻ የልብ ህክምና ክትትል የሚደረግ መሆኑን ያስረዳሉ።

በአሁኑ ሰዓት በማዕከሉ ውስጥ ሰባት ሺህ ታካሚዎች ወረፋ በመጠበቅ ላይ ይገኛሉ። አንድ የልብ ታካሚም ከሶስት እስከ አራት ዓመት ወረፋ ይጠብቃል። ‹‹የሚኖረው ወረፋ ረጅም በመሆኑ ምክንያትም የወረፋ ጊዜያቸው ሳይደርስ ሕይወታቸው የሚያልፉ ታካሚዎች አሉን ይህ በማዕከሉ የሚገኙ ሀኪሞችን ልብ የሚሰብር ነው›› በማለት የጉዳዩን አሳሳቢነት እንዲሁም ማዕከሉ የሚሰጠው አገልግሎት ከታማሚዎች ቁጥር ጋር የሚጣጣም እንዳልሆነ አስረድተዋል።

አሁን ላይ ካለው ችግር አንጻር እየተሰጠ ያለው አገልግሎት ብዙ የሚቀረው ነው። የሚሉት ዋና ሥራ አስፈጻሚው ማዕከሉ እጅግ ለተቸገሩ እና ለተጨነቁ ልጆቻቸው ለታመሙባቸው ወላጆች እይፎታ እየሰጠ ነው ብለዋል። ህክምና ለማግኘት ወደ ማዕከሉ ከሚመጡ ታካሚዎች መካከል በሳምንት ከአራት እስከ ስምንት የሚደርሱ የልብ ቀዶ ጥገናዎችን ይከናወናል። ነገር ግን ለልብ ቀዶ ጥገና የሚያስፈልጉ የህክምና ቁሳቁሶች ግብዓቶች በሀገር ውስጥ በበቂ ሁኔታ የሚገኙ ባለመሆናቸው በግብዓት እጥረት ምክንያት በሳምንት አራት ቀዶ ጥገናዎች ብቻ ለማድረግ የሚገደዱ እንደሆነ አመላክተዋል።

ማዕከሉ ከተለያዩ ድርጅቶች እና በጎ አድራጊ ግለሰቦች ከሚያገኘው ድጋፍ ባሻገርም በኢትዮ ቴሌኮም በኩል በተዘጋጀው አጭር የጽሁፍ መልዕክት ማንኛውም ህብረተሰብ ድጋፍ እንዲያደርግ የሚያስችል ሥርዓት ተዘርግቷል። በአጭር የጽሁፍ መልዕክት በአንድ ወር ወደ አንድ ሚሊዮን የሚጠጋ ብር መሰብሰብ እንደተቻለ ያስታወሱት ዋና ሥራ አስፈጻሚው፤ ከዚህም ባሻገር ሌሎች የመገናኛ ብዙኃን ነጻ የአየር ሽፋን በመስጠት፣ የማስታወቂያ ሰዓት በመስጠት ማዕከሉን የማገዝ ሥራ የሠሩ መሆኑን አስታውሰው የምስጋና ፕሮግራም መዘጋጀቱን ተናግረዋል።

የልብ ህመም የተያዙ ሰዎች በአሁኑ ሰዓት ቁጥራቸው እየጨመረ መሆኑን ያነሱት ዋና ሥራ አስፈጻሚው ከተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች የሚመጡ ታካሚዎች ሊያሟሉት የሚገባ ቅድመ ሁኔታ ይኖራል? ተብሎ ለቀረበው ጥያቄ ‹‹ሰው መሆኑ እና የልብ ህመም ታካሚ መሆኑ ብቻውን በቂ ነው። ምክንያቱም ድርጅቱን ያቋቋሙት ዶክተር በላይ አበጋዝ በጊዜው ህክምና የሚያስፈልጋቸውን ህጻናት ወደ ሌሎች ሀገራት ወስደው ያሳክሙ ነበር። እነዚያ ሀገራትም በጊዜው ታካሚዎቻችንን ተቀብለው ህክምናውን በነጻ የሚሰጡ ሰው በመሆናቸው ነበር። ማዕከሉ ወደፊትም ከሌሎች ሀገራት ህክምና የሚያስፈልጋቸውን ታካሚዎች ጭምር ተቀብሎ በነጻ የማከም ሃሳብ አለው›› ያሉት ዋና ሥራ አስፈጻሚው ከሌሎች ሀገራት ከኬንያ፣ ኡጋንዳ፣ ማላዊ፣ ሶማሊያ ታካሚዎችን ተቀብሎ በነጻ ከህክምና የመስጠት ጅምሮች እንዳሉም አንስተዋል።

ማዕከሉ የቅድመ ቀዶ-ጥገና እና ድህረ ቀዶ- ጥገና የህክምና ክትትሎችን የሚያደርግ በመሆኑ በየቀኑ ክትትል ሲደረግ ማዕከሉ በሆስፒታሉ ውስጥ ከሚሰጣቸው ህክምናዎች ባሻገር ወደ ማዕከሉ የሚመጡ ታካሚዎችን ከማዕከሉ አቅም በላይ ሲሆንና በፍጥነት ህክምና እንደሚያስፈልገው በህክምና ባለሙያዎች ሲታመንበት ወደ ሌሎች ሀገራት ሄደው እንዲታከሙ ያደርጋል። በሀኪሞች አፋጣኝ ህክምና የሚያስፈልጋቸው መሆኑ ካልተወሰነ በቀር ሁሉም ታካሚዎች ወደ ማዕከሉ በመጡበት የጊዜ ሰሌዳ መሠረት ይስተናገዳሉ። በተጨማሪም ማዕከሉ ህክምና በሚሰጥበት ወቅት የትኛው የልብ ችግር ይታከም የሚለው በማዕከሉ ያለው የህክምና ግብዓት ይወስነዋል ሲሉ ዋና ሥራ አስፈጻሚው ገልጸዋል። በዓመት ውስጥ ከ780 በላይ የሚሆኑ አዳዲስ ታካሚዎች ወደ ማዕከሉ ሪፈር ተጽፎላቸው ከተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ለህክምና ይመጣሉ።

ማዕከሉ ድጋፍ ከሚያገኝባቸው ተቋማትም ሆኑ ግለሰቦች ባሻገር ከኢትዮቴሌኮም ጋር በጋራ በመሆን በአጭር የጽሁፍ መልዕክት ህብረተሰቡ የሚሳተፍበትን የገቢ ማሰባሰቢያ አማራጭ ፈጥሯል። እንደ ዋና ሥራ አስፈጻሚው ገለጻም በአሁኑ ሰዓት በወር እስከ አንድ ሚሊዮን ብር በዚህ የአጭር የጽሁፍ መልዕክት ይሰበሰባል። ነገር ግን ማዕከሉ ከሚሰጠው አገልግሎት እና ካሉት ታካሚዎች አንጻር ይህም በቂ እንዳልሆነ አንስተዋል። የኢትዮ ቴሌኮም ተግባርም ለሌሎች ተቋማት እንደ ጥሩ ማሳያ መሆኑን አንስተዋል።

ሰሚራ በርሀ

አዲስ ዘመን ሰኔ 21/2016

Recommended For You