ውስብስቡ የስፖርት አበረታች ቅመሞች ተጠቃሚነት

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በኢትዮጵያ ያለው የስፖርት አበረታች ቅመሞች ተጠቃሚነት በእጅጉ እየሰፋ መምጣቱ ይታወቃል። በአትሌቲክስ ስፖርት ስኬታማ ከሆኑት መካከል የምትመደበው ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተጋላጭ በሚል ክትትል የሚደረግባት ሃገር ናት። በእርግጥም ተጠቃሚነቱ በተለያየ ጊዜ ይፋ በሚሆኑ የአትሌቶች የምርመራ ውጤት የተረጋገጠ ሲሆን፤ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ስጋትን ባሳደረ መልኩ ቁጥሩ በመጨመር ላይ ይገኛል።

ይህንን ተከትሎም የኢፌዴሪ ባሕልና ስፖርት ሚኒስትር፣ የኢትዮጵያ ፀረ አበረታች ቅመሞች ባለሥልጣን እንዲሁም የጉዳዩን አሳሳቢነት በተደጋጋሚ በመግለጽ ላይ የሚገኘው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ተጨባጭ ውጤት ለማምጣት እየሠሩ ነው። በዚህም በኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ ባለሙያዎች የጉዳዩን መጠን የሚያመላክት ጥናት ተደርጓል። ጥናቱ የስፖርቱን ባለሙያዎችና ተጠቂ አትሌቶችንም ጭምር ያካተተ ሲሆን፤ በቁጥር የተደገፈ ማስረጃ ቀርቧል። ባለሥልጣኑ በአዋጅ ተቋቁሞ ወደሥራ ከገባበት ጊዜ አንስቶ የሕግ ጥሰት የፈጸሙ አካላትን በማጣራትና አስፈላጊው የእርምት እርምጃ በመውሰድ ላይ ይገኛል።

እስካሁን ድረስም የሕግ ጥሰት ከፈጸሙ 31 አትሌቶች ውስጥ 27ቱን እንደ ጥፋታቸው መጠን ከውድድር አግዷል። የወንጀል ጥፋተኝነትን አስመልክቶ በ5 አትሌቶች፣ 1 ሕገወጥ አዘዋዋሪ፣ 2 የሕክምና ተቋማት እንዲሁም 2 የሕክምና ባለሙያዎች ላይ የክስ አቤቱታ ለፌዴራል ፖሊስ ቀርቦ ክትትል ላይ ይገኛል። 7 በሚሆኑ የመድኃኒት መደብሮችና የሕክምና ተቋማት ላይም አስተዳደራዊ እርምጃ እንዲወስድባቸው ተደርጓል።

ይህ ሁኔታም የሃገርን በጎ ገጽታ ከማጉደፍና የስፖርቱን ተዓማኒነት ከማሳጣት አልፎ እንደሃገር ለከፍተኛ ወጪ እየዳረገም ነው። በኢትዮጵያ የአበረታች ቅመሞች ተጠቃሚነትን የሚለይ ተቋም ባለመኖሩ ናሙናው ወደ ውጪ ሃገራት ተልኮ ምርመራው እንደሚደረግ ይታወቃል። በዚህም የሽንት እና የደም ምርመራ ለማድረግ እያንዳንዳቸው በአማካይ ከ200 እስከ 270 የአሜሪካ ዶላር የሚጠይቁ ሲሆን፤ ለኤቢፒ ደግሞ ከ40እከ 50 ዶላር ክፍያ ያስፈልጋል።

ለአብነት ያህል እአአ በ2021 ኢትዮጵያ 63 የደም ምርመራዎችን በራሷ አቅም ስታከናውን ከ12ሺ600 እስከ 17ሺ010 የአሜሪካ ዶላር አውጥታለች። ለ765 የሽንት ምርመራዎች ደግሞ ከ153ሺ እስከ 206ሺ550 የአሜሪካ ዶላር ከፍላለች። ይህም ምርመራውን ለማከናወን በግብዓትነት የሚገቡ ቁሳቁሶችን 54ነጥብ5 በመቶ ከፍተኛ ታክስን ጨምሮ እንደሆነም ጥናቱ ያመላክታል። በዚህም ከ2010 እስከ 2015 ዓ.ም ከተገኘው ዳሰሳዊ ጥናት ማረጋገጥ እንደተቻለው ወደ ውጪ ሀገር ላብራቶሪዎች የተላኩ ዓመታዊ ናሙናዎች ብዛት 4ሺ142 ሲሆኑ፤ 2ነጥብ7 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር በላይ ክፍያ ተደርጓል። ጥናቱ በዝርዝር ካሳያቸው ውጤቶች በመነሳትም በባለድርሻ አካላት ሊከናወኑ ስለሚችሉ ተግባራትም ምክረ ሃሳብ አቅርቧል።

ጥናቱን ተከትሎም የኢትዮጵያ ፀረ-አበረታች ቅመሞች ባለሥልጣን ዳይሬክተር መኮንን ይደርሳል፤ አበረታች ቅመሞች ተጠቃሚነት የዚህ ሃገር ችግር መሆን እንዳልነበረበት ይጠቁማሉ። ባለሥልጣኑ ጥናቱን አሳትሞ በቅርቡ ተደራሽ የሚያደርግ ሲሆን፤ ቀጣዩ ሥራ ደግሞ በጥናቱ የተመላከቱ የመፍትሔ ሃሳቦችን ተግባራዊ ማድረግ ነው። የአበረታች ቅመሞች ተጠቃሚነት ከጊዜው ጋር እየዘመነና እየጨመረ እንደሚሄድ ታሳቢ ያደረገ ስትራቴጂ ማዘጋጀት የግድ ነው።

ባለስልጣኑ ትኩረቱን ካደረገበት የግንዛቤ ማስጨበጥ ስራ ወደ ክትትልና ቁጥጥር ማለፍ ስላለበት ከመጪው በጀት ዓመት አንስቶ የስፖርት ማህበራት የስራቸው አካል እንዲያደርጉት ቅድመዝግጅት እየተደረገ ነው። የጸረ አበረታች ቅመሞችን ባለማወቅ የሚወስዱ አትሌቶች እንዳሉ ሁሉ ተዘጋጅተውበትና በተደራጀ ሁኔታ የሚወስዱ አትሌቶች ቁጥር እየጨመረ ከመሆኑ አንጻር ሥራው ውስብስብና ሰፊ በመሆኑ ባለድርሻ አካላት ሊረባረቡበት እንደሚገባም ነው ዳይሬክተሩ ያስገነዘቡት።

በኢፌዴሪ ባሕልና ስፖርት ሚኒስትር የስፖርት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር መስፍን ቸርነት፤ በበኩላቸው የአበረታች ቅመሞች ተጠቃሚነት በትውልድ ግንባታ ላይም አደጋን እየደቀነ ያለ ጉዳይ መሆኑን ይገልጻሉ። በተጠቃሚነት ከሚመዘገበው ቁጥር ይልቅ መለመዱ ይበልጥ አደገኛ የሚያደርገው ሲሆን፤ ለሃገርም ሆነ ለዓለም አቀፍ ስፖርት ስጋት ነው። ይህ ወቅት እንደ ኦሊምፒክና ሌሎች አሕጉርና ዓለም አቀፍ ውድድሮች የሚካሄዱበት እንደመሆኑ ግንዛቤውን ማሳደግ ይገባል። በመሆኑም ጥናቱን ሁሉም ባለድርሻ አካላትና የስፖርት ተቋማት በተገኙበት የውይይት መድረክ የሚዘጋጅ መሆኑንና ችግሩን ለመግታት በጋራ የሚሰራ መሆኑንም ነው ያመላከቱት።

ብርሃን ፈይሳ

አዲስ ዘመን ዓርብ ሰኔ 14 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You