የኢትዮጵያውያንን የመረዳዳት እሴት እያጎለበተ የመጣው በጎ ፈቃደኝነት

የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በአዲስ አበባ ከተማ በተለያዩ አካባቢዎች ተግባራዊ መሆን ከጀመረ የቆየ ቢሆንም፤ በመደበኛነት ከ2002 ዓ.ም ጀምሮ በመዲናዋ በተለያዩ መርሐ ግብሮች በወጣቶች ሲተገበር መቆየቱን መረጃዎች ያመላክታሉ።

የበጎ ፈቃድ አገልግሎቱ በተለያዩ ምክንያቶች ተቀዛቅዞ የቆየውን የኢትዮጵያውያንን የጋራ እሴት በማነቃቃት ከፍተኛ አስተዋፅዖ እያበረከተ ነው፡፡ በዚህ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በርካታ ዜጎች ያዘመመ ቤታቸው ቀና እንዲል ሆኗል፤ ተማሪዎች ለቀጣዩ ትምህርት ተዘጋጅተውበታል፤ ለአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር መሳካት ትልቅ አበርክቶ በማድረግ የችግኝ ተከላና ሌሎች በርካታ ተግባሮች ተከናውነውበታል፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ እየጎለበተ የመጣው የበጎ ፈቃደኝነት አገልግሎት አሁን አሁን ደግሞ ወደ ሀገራዊ እንቅስቃሴ አድጓል። ዘንድሮም በመላ ሀገሪቱ የሚካሄደው የክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ሰሞኑን ይፋ ተደርጓል፡፡

እንደሚታወቀው ኢትዮጵያውያን አብረው በመብላት ብቻ ሳይሆን አብረው በመሥራት፣ በጎና መልካም በማድረግ፣ አዛውንቶችን በማክበር፣ ያለው የሌለውን በመደገፍ ይታወቃሉ፤ ይህን ማድረግ ለዘመናት የቆየ የጋራ እሴታቸው ነው። በተለይም 98 በመቶው ሕዝብ አማኝ መሆኑ የሚነገርላት ኢትዮጵያ በክርስትናውና በእስልምናው እንዲሁም በተለያዩ እምነቶችና መልካም እሴቶች የተቀረፁ ናቸው፡፡

ከዚህ የበጎነት እሴቶቻቸው ከመነጩትና በተለይ በመዲናዋ አዲስ አበባ በስፋት ተግባራዊ እየሆኑ ከሚገኙት የበጎነት ሥራዎች አንዱ የአቅመ ደካሞች ቤት እድሳት ነው። በዚህ የቤት እድሳት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ /ዶ/ር/ እንዲሁም ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናትን ጨምሮ የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች እየተሳተፉ ይገኛሉ፡፡ በዚህ የበጎ ተግባር ከተከናወኑ ተግባሮች መካከል የመኖሪያ ቤት እድሳት አንዱ ነው፡፡ ብዙ ሺ አቅመ ደካሞችና ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው ዜጎች የመኖሪያ ቤታቸው ታድሶላቸዋል፡፡ በርካቶችም አዳዲስ ዘመናዊ ባለብዙ ወለል መኖሪያ ቤቶች ተገንብተውላቸዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዋ የ85 ዓመቷ ወይዘሮ ዓለምነሽ ባሩዳ በበጎ ፈቃድ አገልግሎት የመኖሪያ ቤቶች እድሳት ተጠቃሚ ሆነዋል፡፡ የመኖሪያ ቤት እድሳቱ የተደረገላቸው በንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር አስተባባሪነት እና በበጎ ፍቃደኛ ባለሀብቶች ድጋፍ ነው፡፡

ከንጉሡ ዘመን ጀምሮ ቤተሰብ አፍርተው በራስ መኮንን ድልድይ አካባቢ በአሮጌ የቀበሌ ቤት ውስጥ የኖሩት ወይዘሮ አለምነሽ፣ የአንድ ሴት እና አንድ ወንድ ልጅ እናት ናቸው፡ ከወለዷቸው ልጆች በተጨማሪ አምስት ያሳደጓቸው ልጆች እንዲሁም እሳቸው በድምሩ ስምንት ቤተሰብ ሆነው ባዘመመ ጎጇቸው ይኖሩ ነበር፡፡

ይሁንና ወይዘሮ አለምነሽ ቤታቸው ስለታደሰላቸው በእጅጉ ተደስተዋል፤ አሮጌውን ከጭቃ የተሠራ የቀበሌ ቤት አድሶ፣ አሳምሮ እንዲገቡበት ያደረጉላቸውን ወገኖች ሁሉ አመስግነው መጨረስ አልቻሉም፡፡ የቀድሞውን ቤታቸውን መፀዳጃ ቤት መንግሥት እንዳሠራላቸው አስታውሰው፣ ማዕድቤት እና አጥሩን ደግሞ በራሳቸው ሠርተው ይኖሩበት እንደነበር ይገልጻሉ፡፡ አሮጌውን ቤት በማፍረስ የተሻለ ቤት እንዲገነባላቸው ሲጠየቁ በእጅጉ ተደስተው የሀሳቡን አቅራቢዎች መርቀዋል፡፡

አሁን በታደሰው ቤታቸው እየኖሩ የሚገኙት ወይዘሮ አለምነሽ፣ የመንግሥት ባለሥልጣን እና አስተዳዳሪዎች፣ የሚኖሩበት ወረዳ መምህራን፣ ባለሀብት እና በጎ ፈቃደኞች ወጥተው፣ ወርደው፣ አቅመ ደካሞቹ ቤት ፈርሶባቸው፣ ጣሪያ አፍሶባቸው፣ በምን ላድስ፣ በምን ልሥራ ብለው ሲጨነቁ እንደ ፈጥኖ ደራሽ ደርሰው እከሌ ትልቅ ነው እከሌ ትንሽ ነው ሳይሉ ለሁሉም የዚህ አይነት ቤት ሠርተው በአጭር ጊዜ ውስጥ አስረክበዋል ሲሉም በቤት እድሳቱ የታየውን ርብርብና የተሰማቸውን ደስታ ገልጸዋል። የታደሰውን ቤት “እንደሰጡን ሁሉ ፈጣሪ አብልጦ ይስጣቸው፣ ወንበራቸው ከፍ ይበል” ብለው መርቀው እንደገቡበትም አስታውሰዋል።

በቀድሞው ቤታቸው እያሉ የዛሬ 20 ዓመት አካባቢ ወድቀው ታመው እንደነበር አስታውሰው፣ ከእድሜ መግፋት ጋር ተያይዞ የጤና ችግሮች እንዳሉ ነግረውናል። ታድሶ በተሰጣቸው የምድር ቤት ምንም ሳይቸገሩ በምርኩዝ እየተንቀሳቀሱ እንደሚገኙና ከጤናም አኳያ ጥሩ ሁኔታ ላይ እንዳሉ ይገልጻሉ።

በራስ መኮንን ድልድይ አካባቢ በአዲስ አበባ ቤቶች ኮርፖሬሽን የቤት እድሳት ተጠቃሚ ከሆኑት መካከል የ70 ዓመት አዛውንት ወይዘሮ ፅጌ ረጋሳ አንዷ ናቸው። ወይዘሮ ጽጌ ከደርግ ጊዜ ጀምሮ በአካባቢው ለበርካታ ዓመታት ኖረዋል፡፡ የቀድሞው የቀበሌ ቤታቸው የመፀዳጃ ቤቱ የሕዝብ ነበር፡፡ 14 ቤተሰብ ጋር የሚጠቀሙበትና ምቹ ያልነበረ ነው። ውሃም በጋራ ይጠቀሙ ነበር።

የአስም እና የደም ብዛት ታማሚ መሆናቸውን የገለጹት ወይዘሮ ፅጌ፣ ባለፈው ክረምት የቀድሞው የጭቃ ቤታቸው በአዲስ መልኩ መገንባት ሲጀመር፣ ቤተመንግሥት በሚባለው ትምህርት ቤት ውስጥ ለተወሰነ ጊዜ መቆየታቸውን ይገልጻሉ፡፡ ተማሪዎች ወደ ትምህርት ቤት ሲገቡም እሳቸውም ቅድስት ማሪያም ፊትለፊት አካባቢ በጊዜያዊነት ቆይተዋል።

የቤቱ እድሳት ተጠናቆም ባለ ሁለት መኝታ ቤት ውስጥ ለመኖር በቅተዋል። ውሃ ለሁሉም ቤት መግባቱን፣ የመፀዳጃ ችግር መቀረፉን፣ የእቃ ማጠቢያ ለብቻ እንዳላቸውም አስታውቀዋል፡፡ በአዲሱ ቤት እስከ አሁን መብራት እንዳልገባም ጠቅሰው፣ ከጎረቤት መብራት ለመሳብ ሦስት ሺህ ያህል ብር አውጥተው ገመድ መግዛታቸውን ጠቁመዋል፡፡ መብራት እንዲገባላቸውም ጠይቀዋል።

በሀገራችን የእነወይዘሮ ዓለምነሽ ባሩዳን አይነት የበጎ ሥራ የተሠራላቸው አቅመ ደካሞች እጅግ በርካታ ናቸው፡፡ በተለይ በአዲስ አበባ በርካታ ነዋሪዎች የመኖሪያ ቤት እድሳት ተደርጎላቸዋል፤ ሌሎች በርካታ የሚሆኑም ቤታቸው በአዲስ መልክ ተገንብቶላቸዋል፡፡ ባለብዙ ወለል መኖሪያ ቤቶች ተገንብተው ለእነዚህ የኅብረተሰብ ክፍሎች ተላልፈዋል፡፡ በበጎ አድራጎት ተግባር ሌሎች በርካታ አገልግሎቶችም ተሰጥተዋል፤ እየተሰጡም ይገኛሉ፡፡ አገልግሎቱ በመላ አገሪቱ እንዲስፋፋ እየተሠራ ነው፡፡

በዘንድሮው የክረምት ወቅትም አገልግሎቱን ለመስጠት የሚያስችሉ መርሐ ግብሮች ሰሞኑን ተካሂደዋል፡፡ የዘንድሮው አገር አቀፍ የክረምት ወራት በጐ ፈቃድ የማኅበረሰብ አገልግሎት 40 ሚሊዮን የሚጠጉ ዜጐች እንደሚሳተፉ መርሐ ግብሩን አስመልክቶ ሰሞኑን መግለጫ የሰጡት የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ የሠላም ሚኒስቴርና ትምህርት ሚኒስቴር አስታውቀዋል፡፡

የየሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶቹ ሚኒስትር ዴኤታዎች ሀገር አቀፍ የክረምት ወራት በጐ ፈቃድ የንቅናቄ መርሐ ግብርን አስመልክተው በሰጡት የጋራ መግለጫ እንዳስታወቁት፤ የዘንድሮው የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት ማስጀመሪያ መርሐግብር “በጐነትና አብሮነት ለኢትዮጵያ ከፍታ” በሚል መሪ ቃል ይካሄዳል፡፡ በዚህም 50 ሚሊዮን ዜጎች ተጠቃሚ እንዲሆኑ ይደረጋል።

የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ሙና አሕመድ በዚህ ወቅት እንደገለጹት፣ ኢትዮጵያ በበጐ ፈቃድ አገልግሎት የረጅም ጊዜ ታሪክ ያላት ሀገር ስትሆን፣ በተለይ ከ2002 ዓ.ም ጀምሮ አገልግሎቱ በመደበኛ ሁኔታ ተጠናክሮ ቀጥሏል። ከሀገራዊ ለውጡ ወዲህ ለአገልግሎቱ በተሰጠው ትኩረትም የበጐ ፈቃድ አገልግሎት ሰጪ ዜጐች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ይገኛል።

ወይዘሮ ሙና እንደተናገሩት፤ በዘንድሮው የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት ተቋማዊ ቅንጅት በመፍጠር ውጤታማ ሥራ ለማከናወንና የሕዝብን የላቀ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ታቅዷል። በተለይም ብሔራዊ የወጣቶች የዜግነት አገልግሎት የሚባል አዲስ አዋጅ እየተዘጋጀ ነው። ይህም አገልግሎት እድሜያቸው ከ18 እስከ 35 ዓመት የሚሆኑ ኢትዮጵያውያን ወጣቶች ብቻ የሚሳተፉበት ነው። ወጣቶች የሀገር ፍቅር ስሜት እንዲኖራቸው፣ ማገልገል ክብር መሆኑን እንዲያስቡ እና ስብዕናቸው የተገነባ እንዲሆን የሚያግዝ አዋጅ ተዘጋጅቶ ለጠቅላይ ሚኒስትር ቢሮ የቀረበ መሆኑን አንስተዋል።

የሠላም ሚኒስትር ዴኤታ ከይረዲን ተዘራ (ዶ/ር) በበኩላቸው እንደተናገሩት፤ ሀገራችን ዘመናትን የተሻገረ ታሪክ ያላት ብትሆንም፣ ያንን የሚመጥን የፖለቲካ ባሕል አልነበረም፡፡ እነዚህን ችግሮች ለመፍታት አንዱ መሣሪያ የቆየውን የአብሮነት እሴት ማሳደግ ነው።

የበጐ ፈቃድ አገልግሎቱ ማኅበራዊ ትስስርን ለማጠናከርና ነባር የአብሮነት እሴትን ለማደስ ትልቅ ሚና አለው። ኢትዮጵያ ጥንታዊ ሀገር እንደመሆኗ ውስጥ የተለመደ የአብሮነት እሴት አላት። ይህንን ማምጣት እና በተለይ ዘመናዊ በሆነ መልኩ ለሀገረ-መንግሥት ግንባታ እና ለሀገራዊ አንድነት መጠቀም ይገባል።

ወጣቱ አሁን ባሕል አለው፣ በርካታ የአዛውንት ቤቶች እየታደሱ ነው። በቀደምት ጊዜያት በኢትዮጵያ ታሪክ የመንግሥት እና የማኅበረሰብ ተራክቦ ሻክሮ ቆይቷል። አሁን በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠሩ ወጣቶች በትምህርት ቤቶች እየተመገቡ ናቸው። በማኅበረሰቡ ውስጥ በሕዝብ ውስጥ ያደገና የተማረ ወጣት ለሀገሩ ታማኝ ይሆናል ሲሉ ከይረዲን (ዶ/ር) አብራርተው፣ ይህ የክረምት ሀገራዊ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ንቅናቄም ወጣት ብቻ ሳይሆን ሁሉም ኢትዮጵያዊ የሚሳተፍበት ሰፊ ሀገራዊ ፋይዳ እንዳለው አስገንዝበዋል።

በአገልግሎቱ ወደ ተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች በመሄድ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ለመስጠት የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ዝግጁ መሆናቸው የተገለጸ ሲሆን፣ በዚህም በመላ ሀገሪቱ 20 ሺ የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ለአገልግሎቱ እንደሚሠማሩ ተጠቁሟል፡፡ ለተማሪዎቹም የአንድ ሳምንት ሥልጠና እየተሰጣቸው ይገኛል፡፡

ሥልጠናውም የሀገር መሠረታውያን በሚባሉት በሀገራዊ ማንነት፣ በሀገራዊ ጥቅም እና በሀገራዊ የጋራ እሴቶች ላይ ያተኮረ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡ አንድን ሀገር የሚያቆም ካስማና ማገር የሆኑ በተለይ በሀገራችን አሉ የተባሉ ሀገራዊ እሴቶቻችን በጥናት የተሰነዱ መሆናቸውን ጠቅሰው፣ በእነዚህ ላይ ሥልጠናዎች ይሰጣሉ ብለዋል።

ወጣቶቹ ከበጎ ተግባር ሥራዎቻቸው ጎን ለጎንም ሀገራቸውንና እሴቶቻቸውን አውቀው ሀገራዊ መብቶቻቸውን አጠናክረው ሁሉም የሁሉም አካል መሆናቸውን አውቀው ከተወለዱበት አካባቢ ውጭ በሌላ ክልል እንደሚሰማሩም አመልክተዋል።

በጎነት እና አብሮነት ዞሮ ዞሮ ከፍ አድርጎ ማሳየት ነው ያሉት ከይረዲን (ዶ/ር)፣ እነዚህ ሁሉ ተደማምረው ሲሄዱ እዚህም እዛም የሚታዩ የሠላም እጦቶች ተደራሽ የሚደረጉበት አንዱ አቅም መሆኑን አመላክተዋል።

በሀገራችን አብዛኛው አካባቢዎች በእምነታቻው የሚታወቁ ጠንካራ ባሕል ያላቸው፣ የሚረዳዱ ካለው የሌለውንም የሚያካፍሉ ናቸው። የትኛውም አካባቢ ያሉ ኢትዮጵያውያን በመሆናቸው ያሉብንን ችግሮች በአብሮነት የምንፈታቸው ናቸው። የሚያጋጩን ችግሮችም ከሚፈቱበት መንገዶች አንዱ አብሮነት፣ መደጋገፍ፣ ኢትዮጵያዊ የጋራ እሴት ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ /ዶ/ር/ ያስጀመሩት የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት ንቅናቄው በመላው የሀገሪቱ አካባቢዎች ይከናወናል። የኢትዮጵያ ሀገረ መንግሥት በሙሉ የዚህ የበጎነት ማስፈፀሚያ ወሰን መሆኑንም ጠቁመዋል።

የትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ኮራ ጡሽኔ በበኩላቸው እንደገለጹት፣ የበጐ ፈቃድ አገልግሎቱ እየተሸረሸረ የመጣውን የአገሪቱን የአብሮነት እሴት ለማደስ አይነተኛ ሚና ይኖረዋል። በንቅናቄው የትምህርት ሚኒስቴር 20 ሺህ የዩኒቨርስቲ ተማሪዎችን በወሰን ተሻጋሪ የበጐ ፈቃድ አገልግሎት ያሳትፋል።

ተማሪው ሀገር ውስጥ ያለውን እምቅ አቅም ሲረዳ የሌላውን ባሕል እና ቋንቋ፣ አኗኗር ሲያውቅ የሀገሪቱን ችግሮች እና ፈተናዎች፣ መልካም ዕድሎች መመልከት ሲችል ከዛ ተመልሶ ሲመጣ ጥሩና ሥራ ፈጣሪ ዜጋ ሊሆን ይችላል ሲሉም አመልክተዋል። ከሌሎች የማኅበረሰቡ አካላት ጋር ሲገናኝም፣ የሰከነ፣ ያደገ፣ የሠለጠነ ግንኙነት ይኖረዋል ተብሎ ይገመታል ያሉት አቶ ኮራ፣ ትምህርት በተግባር የሚያገኙበት አንዱ መንገድ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት መሆኑን አመላክተዋል።

የዘንድሮው/ የ2016 ዓ.ም/ የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት ንቅናቄ መርሐ ግብር ሰኔ 12 ቀን 2016 ዓ.ም በዓድዋ ሙዚየም በይፋ ተጀምሯል። በዚህ በዓድዋ በተጀመረው የንቅናቄ ማስጀመሪያ መድረክ ላይ የተገኙት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ የበጎ ፈቃድ አገልግሎትን በተደመረ ጉልበት እውቀትና ክህሎት ሀገር የመገንባት ሂደት ነው ሲሉም ገልጸውታል፡፡

ከዚህ ቀደም በበጎ ፈቃድ በተሰጡ አገልግሎቶች የማኅበረሰቡ አንገብጋቢ ችግሮች መፍታት ተችሏል ሲሉ ጠቅሰው፣ በዘንድሮው የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት ሚሊዮኖች ይደገፋሉ ብለዋል፡፡ አነስተኛ በጀት ባለበት ሀገር በበጎ ፈቃድ ሥራዎች ላይ መሳተፍ ያስፈልጋል በማለት፤ ኢትዮጵያ በሚገባት ልክ እንዳልተገኘች የሚያስብ ዜጋ ሁሉ በበጎ ፈቃድ ሠራዎች ላይ ሊሳተፍ እንደሚገባም አስገንዝበዋል፡፡

በኃይሉ አበራ

አዲስ ዘመን ዓርብ ሰኔ 14 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You